የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ፣ በሚቀጥለው በ2011 ዓ.ም. ለሚያካሂዳቸው 40/60 ቤቶች ግንባታ 11 ቢሊዮን ብር በጀት ጠየቀ፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይህንን ገንዘብ ያቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ የአዲስ አበባ ከተማ መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ለቤቶች ግንባታ የሚሆን 38 ሔክታር መሬት ማስረከቡም ታውቋል፡፡
ግንባታዎቹ የሚካሄዱት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ቦሌ አራብሳ አካባቢ እንደሆነ፣ ኢንተርፕራይዙ ከሚመለከታቸው የአስተዳደሩ መዋቅሮች ጋር በመሆን የወሰን ማስከበር ሥራ እያከናወነ መሆኑ ታውቋል፡፡
በ2011 ዓ.ም. በ38 ሔክታር መሬት ላይ ግንባታቸው የሚከናወነው 8‚428 ቤቶች ሲሆኑ፣ በብሎክ ደረጃ ደግሞ 54 ሕንፃዎች ናቸው ተብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት በ40/60 ፕሮግራም የ38‚200 ቤቶች ግንባታ በመከናወን ላይ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 17‚700 ቤቶች የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተከናወኑባቸው መሆኑን ከኢንተርፕራይዙ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይፈቀዳል ተብሎ የሚጠበቀው 11 ቢሊዮን ብር፣ የተጀመሩትን ሥራዎች ለማጠናቀቅና አዲስ የሚካሄዱትን 40/60 ቤቶች ግንባታ ለማስጀመር ነው ተብሏል፡፡
አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) በቀጥታ ሊከታተሏቸው ካቀዷቸው ፕሮጀክቶች መካከል መሬትና መሬት ነክ ሥራዎች፣ የቤቶች ግንባታና የውኃ ፕሮጀክቶች ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡
በመሬት ዘርፍ ለውጥ የሚያመጡ ሥራዎችን ለማካሄድ በቅድሚያ ሪፎርም ለማካሄድ እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን፣ የሪፎርሙ አባል የሆነ የመሬት ኦዲትም በቅርቡ እንደሚጀምር መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በውኃ ዘርፍም የአሠራር ለውጦች እየተደረጉ ሲሆን፣ በቤቶች ግንባታ ዘርፍም በርካታ ለውጦች ይደረጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተለይ በ20/80 እና በ40/60 ቤቶች ፕሮግራም በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተመዝግበው እየተጠባበቁ ቢሆንም፣ ግንባታው በዕቅዱ መሠረት መሄድ ባለመቻሉ ቅሬታዎች በብዛት እየቀረቡ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ኢንተርፕራይዙ ግዙፍ ግንባታዎችን ለማካሄድ በሚያስችል ደረጃ ራሱን እያደራጀና የሰው ኃይሉንም እያሟላ መሆኑን ይናገራል፡፡