Thursday, September 21, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የነፃነት አየር መተንፈስ የሚቻለው የሕግ የበላይነት ሲከበር ነው!

ለኢትዮጵያ የሚያዋጣው ዋስትና ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ ብቻ ነው፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲን ከመመኘት በላይ ደግሞ ተግባራዊ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ቁርጠኝነት የሚመጣው ግን ከፍተኛ የሆነ የአገር ፍቅርና ሕዝብን የማገልገል ጥልቅ ስሜት ሲኖር ነው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የሚሳተፉ ኃይሎች መጀመርያ የአገር ፍቅር ስሜትና የሕዝብ አገልጋይነትን ብቃት ሊላበሱ ይገባል፡፡ የአገር ፍቅር ሳይኖር አገርን ማልማትና ማበልፀግ አይቻልም፡፡ የሕዝብ ፍቅር ሳይኖር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት ዘበት ነው፡፡ ሕዝብ ደግሞ ከማንም የበለጠ ሁሉንም ነገር ያውቃል፡፡ አገር ከአምባገነናዊ አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትሸጋገር ከተፈለገ፣ ለሐሳብ ነፃነት ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል፡፡ ከማንነት ብዝኃነት በተጨማሪ ለሐሳብ ብዝኃነት ትኩረት መሰጠት አለበት፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት አይደለም ሊባል የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት ሲባል፣ የእያንዳንዱ ሰው ነፃነትም ክብር ሊነፈገው እንደማይገባ መተማመን ያስፈልጋል፡፡ ዴሞክራሲ የተለያዩ ሐሳቦች የሚስተናገዱበት መሆኑን ለደቂቃም ቢሆን መዘንጋት አይገባም፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ግን የሕግ የበላይነት ይከበር፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ከስደት ወደ አገር ቤት እየተመለሱ ነው፡፡ የቀሩትም በቅርቡ ይመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአፈና ምክንያት የተሰደዱ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት ሲመለሱ፣ የመጀመርያ ተግባራቸው ለሐሳብ ነፃነት ዕውቅና መስጠት መሆን አለበት፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚታየው የሌሎችን ሐሳብ ማንቋሸሽ፣ በጠላትነት መፈረጅና ከዚያም አልፎ ተርፎ በዛቻ የተሞሉ ማስፈራራቶችን በአደባባይ ማውገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ደጋፊዎቻቸውን ካለማወቃቸውም በላይ የትግሉን ስፋትና ጥልቀት የተረዱ እንዳልሆኑ፣ ከሚያወጡዋቸው መግለጫዎች መረዳት ይቻላል፡፡ አሁን ግን ሕዝብ ዘንድ እየደረሱ ስለሆነ ተጨባጭ ሁኔታዎችን መገንዘብ አለባቸው፡፡ ከዓመታት በፊት የተለዩት ደጋፊና አሁን የሚያገኙት አዲሱ ትውልድ በብዙ ነገሮች ይለያያሉ፡፡ የአሁኑ ትውልድ ትምህርት ላይ የሚገኝ፣ ሞጋች የሆኑ ጥያቄዎችን የሚያቀርብ፣ ዝም ብሎ በስሜት የማይነዳና መረጃ የታጠቀ በመሆኑ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ ድጋፍና ተቃውሞ ከስሜት ይልቅ ምክንያታዊነት ላይ ስለሚመረኮዙ፣ የሐሳብ ገበያው ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚደራ መገንዘብ ይገባል፡፡ የሐሳብ ነፃነት እንዲከበር ደግሞ የሕግ የበላይነት መኖር አለበት፡፡

ሕዝብ በነፃነትና በሰላም መኖር የሚችለው አማራጭ ሐሳቦች ሲቀርቡለት ነው፡፡ አማራጭ ሐሳቦች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያዊያን በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ውስጥ ነፃነት እንዳላቸው እንዲሰማቸው ይረዳሉ፡፡ ዴሞክራሲ የሐሳብ ገበያ ነው የሚባለው፣ ለአገር እስከጠቀመ ድረስ ማንኛውም ሰው የመሰለውን ማንፀባረቅ ስለሚችልበት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የመሰላቸውን በነፃነት ከመናገራቸው በላይ፣ ነፃና ግልጽ ማኅበረሰብ ለመገንባትም ያግዛል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን ይህ ፍላጎት ብርቅ ነው፡፡ ተቃራኒ ሐሳብን ላለማድመጥ ሲባል ብቻ ከማናናቅ ታልፎ አስከፊ የስም ማጥፋቶች ይካሄዳሉ፡፡ ከዚያም ባለፈ ለግጭትና ለውድመት የሚዳርጉ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ፀጋ ተገፎ፣ በርካቶች ለሥቃይና ለስደት ከመዳረግ አልፈው ሕይወታቸውን ገብረዋል፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ በርካታ ጠቃሚ ሐሳቦች እየተቀጩ የአንድ ወገን የበላይነትን የሚሰብኩ ብቻ ሲንሰራፉ፣ አገር ምን ያህል ወደኋላ እንደተጎተተች ታሪካችን ይናገራል፡፡ ሌላው ሌላው ትርክት ቀርቶ ከምርጫ 97 በኋላ ያጋጠሙ ችግሮች ብዙ ይናገራሉ፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በአገሪቱ የታዩ ሕዝባዊ አመፆችም፣ ለዓመታት የተጠራቀሙ የብሶት ወጤቶች መሆናቸውን ማንም አይዘነጋም፡፡ የሐሳብ ነፃነት አፈና በርካታ ችግሮችን አድርሷል፡፡ የሕግ የበላይነት ባለመኖሩ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አሳዛኙን የታሪክ ምዕራፍ በመዝጋት ለሐሳብ ነፃነት ዕውቅና በመስጠት በሁሉም መስኮች ለውጥ ቢጀመርም፣ የለውጡን መሠረታዊ ዓላማ የሚፃረሩ እኩይ ድርጊቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ በለውጥ ወቅት ችግሮች የሚያጋጥሙ መሆናቸው የሚታወቅ ቢሆንም፣ በአንዳንድ ሥፍራዎች የሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች ግን ያሳፍራሉ፡፡ ለነፃነት የተከፈለን ዋጋ የሚያሳንሱና የትናንት አሳዛኝ የታሪክ ጠባሳዎችን ለመድገም የሚሯሯጡ ወገኖች አገርና ሕዝብን ከማተራመሳቸው በተጨማሪ፣ በሰላማዊ መንገድ ወደ ዴሞክራሲ ሊደረግ የሚገባውን ሽግግር እየተፈታተኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ወገኑን እንደ ባዕድ ‹መጤ› እያለ ከሚያሳድድ ሥርዓተ አልበኛ፣ የማይጥመኝን ነገር ለምን ትናገራለህ እስከሚል ጀብደኛ ድረስ ነፃነትን እየተጋፉ ነው፡፡ ሕግ ባለበት አገር እጃቸውን በንፁኃን ደም የሚታጠቡ አረመኔዎችም ታይተዋል፡፡ ከእነዚህ ሥርዓተ አልበኞች ጀርባ የፖለቲካ ነጋዴዎች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩን ነፃ ለማውጣት ጥረት ሲደረግ ከበስተጀርባ የጥፋት እጃቸውን የሚያስገቡ ካሉ፣ በእርግጥም ከፊታችን ብርቱ ትግል እንዳለ ግልጽ ነው፡፡ በሕግ መባል አለበት፡፡  

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አሁንም ትልቁ ችግር የመደማመጥ ባህል አለመኖር ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ሳያዳምጥ ወደ ዘለፋና ስም ማጥፋት የሚሮጠው ለሐሳብ ነፃነት ልዕልና ደንታ በመጥፋቱ ነው፡፡ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የኖረው የመመካከር፣ የመደማመጥና የመግባባት የጋራ እሴት እየተናደ ነው፡፡ ሕዝባችን ልዩነቶች ሳይገድቡት በጋራ እናት አገሩን የጠበቀበት ማኅበራዊ መስተጋብር ያልነበረ ያህል እየተቆጠረ ነው፡፡ ነገር ግን በአራቱም ማዕዘናት ተከባብሮና ተዋልዶ በፍቅር የኖረው ሕዝባችን ለሐሳብ ብዝኃነትና ነፃነት የሰጠው ዋጋ ትልቅ ነበር፡፡ ይህ ትልቅ እሴት ፖለቲከኞቻችን ዘንድ እየጠፋ ሸፍጥ፣ አሻጥር፣ ሴራ፣ ቂምና በቀል ነው የሞላው፡፡ በክፉና በደግ ጊዜ በሰላም የሚኖር ሕዝብን እርስ በርሱ በማጋጨት አገር ማተራመስ የዘመኑ ፋሽን ሆኗል፡፡ መነጋገርና መደማመጥ እየጠፋ የንፁኃን ሕይወት በከንቱ ማጥፋትና አገርን ማመሰቃቀል ነው የተለመደው፡፡ ከዚህ አሳዛኝ ሰቆቃ ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ለሕግ የበላይነት መስፈን ትግል መደረግ አለበት፡፡

ዋስትና ያለው ሰላምና ዴሞክራሲ የሚገኘው ሐሳቦች በነፃነት ሲንሸራሸሩ ነው፡፡ የሐሳቦቹ ፈራጅ ደግሞ ሕዝብ ነው፡፡ ሕዝብን ማክበር ደግሞ የዴሞክራሲ አንዱ ፈርጅ ነው፡፡ ነፃ፣ ዴሞክራሲና ፍትሐዊ ምርጫ የሚኖረው የሐሳብ ነፃነት ሲኖር ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ውሸት ነው፡፡ ውሸት ደግሞ ለሰላምም ሆነ ለዴሞክራሲ ፋይዳ የለውም፡፡ የሕግ የበላይነት የሚጣሰው በውሸታሞችና በስግብግቦች ነው፡፡ ስግብግቦች ደግሞ አምባገነኖች ናቸው፡፡ በሕዝብ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚገነባው፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ነፃነት እንዲሰማው ሲደረግ ነው፡፡ በጅምላ መደገፍና መቃወም መብት ቢሆንም፣ የግለሰብን መብት መጋፋት ግን የዴሞክራሲያዊና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መኖሩ የሚረጋገጠው የእያንዳንዱ ሰው ሐሳብ በነፃነት ሲንሸራሸር ብቻ ነው፡፡ የሐሳብ ነፃነት መከበር አለበት፡፡ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ማኅበራት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች ሳይቀሩ ለሐሳብ ነፃነት ልዕልና ክብደት ሊሰጡ የግድ ነው፡፡ የሐሳብ ነፃነት ሳይከበር የሕግ የበላይነት አይኖርም፡፡ የነፃነት አየር መተንፈስ የሚቻለው የሕግ የበላይነት ሲከበር ነው!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...

በሰጥቶ መቀበል መርህ መደራደርና ሰላም ማስፈን ለምን ያቅታል?

በያሲን ባህሩ አገር ግንባታ የትውልድን ትልቅና ታሪካዊ ኃላፊነት የሚጠይቅ ተግባር...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...

ለሕዝብና ለአገር ክብር የማይመጥኑ ድርጊቶች ገለል ይደረጉ!

የአዲሱ ዓመት ጉዞ በቀናት ዕርምጃ ሲጀመር የሕዝብና የአገር ጉዳይን በየቀኑ ማስታወስ ግድ ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲ፣ ልማትና ዕድገት ያስፈልጋሉ ከሚባሉ ግብዓቶች...