Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበቴፒ ከተማ ግጭት ሳቢያ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በቴፒ ከተማ ግጭት ሳቢያ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ቀን:

 የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሊቀመንበርና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ሙፈርያት ካሚል ሐምሌ 27 ቀን 2010 ዓ.ም. የከተማውን ነዋሪዎች ካወያዩ በኋላ፣ በውይይት መድረኩ ላይ ተሰድበናል ባሉ ግለሰቦች በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የኪ ወረዳ በቴፒ ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት የተጠረጠሩ ሰባት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታወቀ፡፡

በግጭቱ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ የተለያዩ የመንግሥትና የንግድ ተቋማት ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል፡፡ የንግድ ተቋማትና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አገልግሎትም እስከ ሰኞ ነሐሴ 14 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዳልጀመረ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በቴፒ ከተማ የተከሰተውን ግጭት ለማርገብ የመከላከያ ሠራዊት ከነሐሴ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሥፍራው ተሰማርቶ በወቅቱ የነበረውን ከፍተኛ የሆነ ብጥብጥ ለማስቆም መቻሉን፣ በቴፒ የተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት ሬጅመንት የ53ኛው ሞተራይዝድ አዛዥ ኮሎኔል ፀጋዬ አብርሃም ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የመከላከያ ሠራዊቱ በአካባቢው የነበረውን ፀጥታ መልሶ ቴፒን ከሚዛንና ከሌሎች ከተሞች ጋር የሚገናኙ መንገዶችን ቢያስከፍትም፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት ሥራ አለመጀመራቸው ታውቋል፡፡

‹‹ሕዝቡ አሁን ከቤት ወጥቶ መንቀሳቀስ ችሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት ከቤት መውጣት እንኳን አልቻልንም፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት አገልግሎት በከተማው ውስጥ የለም፤›› ሲሉ ሪፖርተር ያጋገራቸው አንድ የከተማው ነዋሪ ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡

አፈ ጉባዔ ሙፈርያት ከቴፒ ከተማ ነዋሪዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት ተሰድበናል ያሉ አካላት ሰዳቢዎቹ ይጠየቁልን በማለት ወደ ብጥብጥ ያመሩ መሆኑን፣ ይህ ምን ያክል አሳማኝ ምክንያት እንደሆነ ባለፈው ሳምንት ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበላቸው አፈ ጉባዔዋ፣ በውይይቱ የወጣቶች ውክልና አናሳ ነበር የሚል ጥያቄ እንደነበርና ወጥተውም በውጭ የተሰበሰቡ ወጣቶችን ማግኘታቸውን ገልጸው፣ ‹‹ውይይቱ ጥሩ መግባባት የተደረገበት ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ግለሰብ አመራሮች ስማቸው ይጠራል፡፡ ይህ ነውር ሳይሆን መከበር ያለበት ባህል ነው፡፡ ስሜ ለምን ተጠራ ብሎ መበጥበጥ አግባብ አይደለም፡፡ የግለሰብ ስምን ከብሔር ጋር የሚያገናኙ አሉ፡፡ ይህን በመድረኩም ለማረም ሞክረናል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ‹‹ከአንድ ብሔር የመጡ ግለሰቦች ተሰደቡ ማለት ብሔሩ ተሰደበ ማለት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

በአካባቢው በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች እንደሚኖሩ በማውሳትም፣ በቀጣይ የአመራር ተዋፅኦው ኅብረተሰቡን እንዲመስል እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

በሥፍራው ለማረጋጋት የገባው የመከላከያ ሠራዊት ከተለያዩ የኅብረተሰብ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ላይ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ የሬጅመንቱ አዛዥ ኮሎኔል ፀጋዬ እንዳሉት፣ የንግድና የመንግሥት አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ውይይቶች እየተደረጉ ነው፡፡ የኅብረተሰቡ በርካታ ጥያቄዎች በብዛት ፖለቲካዊ መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች እንደሚነሱም ኮሎኔሉ አክለዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ጥያቄዎች ወደ መንግሥት እንዳይደርሱ የሚያደናቅፉ አካላት አሉ ብለዋል፡፡

በግጭቱ ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ የመከላከያ ሠራዊት አንድ አባል እንደተጎዳና በሕክምና ላይ እንደሚገኝም ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...