Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ንግድ ሚኒስቴር በፓልም ዘይት ንግድ ለሚሰማሩ ረቂቅ መመርያ አዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢንዶውመንት ድርጅቶች ከፓልም ዘይት ንግድ እንዲወጡ ተጠየቀ

ንግድ ሚኒስቴር ከውጭ ፓልም ዘይት አስመጥተው ማከፋፈል የሚፈልጉ ኩባንያዎችን ማስተናገድ የሚያስችል ረቂቅ መመርያ አዘጋጀ፡፡ በተዘጋጀው ረቂቅ መመርያ ላይ ንግድ ሚኒስቴር ከክልልና ከተማ አስተዳደር፣ ከመንግሥት፣ ከኢንዶውመንትና ከግል ድርጅቶች ጋር መክሯል፡፡

በአዳማ ከተማ በተካሄደው በዚህ ውይይት የኢንዶውመንት ኩባንያዎች የተሻለ አቅም ያላቸው ስለሆኑ፣ ከፓልም ዘይት ንግድ እንዲወጡና በሌሎች ትልልቅ ሥራዎች ላይ ቢሰማሩ ይሻላል የሚል ሐሳብ ቀርቧል፡፡

ዝቅተኛውን የኅብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ በመንግሥት የዋጋ ተመን ወጥቶላቸው ከቀረጥ ነፃ ከውጭ ከሚገቡ ሸቀጦች አንዱ የፓልም ዘይት ነው፡፡

ይህንን የፓልም ዘይት አስገብተው እንዲያካፍሉ የሞኖፖል ኃላፊነት የተሰጣቸው ከመንግሥት አለ በጅምላ፣ ከኢንዶውመንት አምባሰል፣ ጉና፣ ቱምሳና ወንዶ ናቸው፡፡ ከግል ኩባንያዎች ደግሞ በላይነህ ክንዴ ግሩፕ፣ አልሳም ትሬዲንግ፣ ሆራይዘን ፕላንቴሽን (አህፋ)፣ ደብሊውኤንና አማሬሳ ምግብ ዘይት ፋብሪካ ናቸው፡፡

በተለይ የግል ድርጅቶች የዘይት ንግድ ሥራ የተሰጣቸው የየራሳቸውን ግዙፍ የዘይት ፋብሪካ እየገነቡ ስለሆነ፣ ልምድ እንዲያገኙና የሚገኙትንም ትርፍ ይህንኑ ሥራቸውን እንዲደጉሙበት መሆኑ ሲነገር ቆይቷል፡፡

ነገር ግን ይህ የፓልም ዘይት ንግድ ለተወሰኑ ነጋዴዎች ብቻ ሊሰጥ አይገባም በማለት በርካታ ቅሬታዎች ሲቀርቡ የቆዩ በመሆናቸው፣ ንግድ ሚኒስቴር ሥራው የተሰጠው የዘይት ፋብሪካ ለሚገነቡ ብቻ ነው የሚል አቋም በመያዙ የቅሬታ አቅራቢዎቹ ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡

 የዘይት ፋብሪካ እየገነቡ በመሆናቸው የዘይት ንግድ ሥራ ሊሰጣቸው እንደሚገባ የሚገልጹ ኩባንያዎች እየተበራከቱ በመምጣታቸው፣ ንግድ ሚኒስቴር መመርያ እንዲያወጣ አድርጎታል፡፡

ምንጮች እንደገለጹት በተዘጋጀው ረቂቅ መመርያ ወደ ዘይት ንግድ የሚገቡ ኩባንያዎች ፋብሪካ እየገነቡ መሆን እንዳለባቸው፣ 100 ሚሊዮን ብር ካፒታልና በቂ መጋዘን ያላቸው መሆን እንዳለባቸው መሥፈርት ተቀምጧል፡፡

በወቅቱ ጎልተው ከወጡ ሐሳቦች መካከል በተለይ በአራቱ ትልልቅ ክልሎች አማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ የኢንዶውመንት ኩባንያዎች ገዘፍ ያለ አቅም ያላቸው ስለሆኑ፣ ወደ ሌላ ሥራ እንዲገቡና ይህንን ሥራ ለንግዱ ማኅበረሰብ እንዲለቁ የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፋብሪካ እንደሚገነቡ በመግለጽ ሥራው የተሰጣቸው የግል ኩባንያዎች የተወሰኑት እየገነቡ ባለመሆናቸው፣ ሥራውን መነጠቅ እንዳለባቸው የሚጠይቅ ሐሳብም ተነስቷል፡፡

በተለይ አልሳምና ሆራይዘን የፋብሪካ ግንባታን በሚመለከት ተግባራዊ እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎቹ በአጠቃላይ በግምት 480 ሚሊዮን ሊትር ፓልም ዘይት በማስገባት በመላ አገሪቱ ያከፋፍላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች