Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርተሃድሶ ለሚዲያ ቃላቶቻችን

ተሃድሶ ለሚዲያ ቃላቶቻችን

ቀን:

በሰለሞን መለሰ

እጅግ የሚከበረውና ሁልጊዜም መደመጥ ባለበት መጠን እየተደመጠ የማይሰማኝ ምርጡ ጋዜጠኛ ደረጀ ኃይሌ (ኃይሌ ዘበቅሎ ቤት) በአንድ ወቅት የዛሬውንና የትናንቱን ሬድዮና፣ የሬድዮ ጋዜጠኝነት ሲያነፃፅራቸው፣ “እንዲህ እንደ ዛሬው ማንም መንገደኛ እንደ መቅደስ በሚቆጥረው የሬድዮ ስቱዲዮ ሰተት ብሎ በማይገባበት፣ እንዲህ እንደ ዛሬ፣ ሥራ ባጣ ባጣ ኤፍ ኤም ሬድዮ አላጣም እየተባለ በማይዘፈንበትና በማይዘየርበት፣ እንዲህ እንደ ዛሬ፣ ሰማይን ደግፈው ያቆሙ ይመስል ከራስ ስም አልፈው የአክስትና የአጎት፣ የአማችና የዓይን አባትን ስም ማስተዋወቅ ፈሊጥ ባልነበረበት ጊዜ፣ እንዲህ እንደ ዛሬ፣ ለመሆኑ ምን የሚደመጥ ነገር አለና ሬድዮ ይከፈታል በማይባልበት ዘመን፣ እንዲህ እንደ ዛሬ፣ የራስ ጉዳይ፣ የቤተዘመድ ግብዣ፣ የሰንበቴ ማኅበርና ድግስ በሬድዮ በማይሠራጭበት ጊዜ፣ እንዲህ እንደ ዛሬ፣ የጋዜጠኝነት ሙያ ክብሩና ሥነ ምግባሩ ባልተናቀበትና ባልተዋረደበት ዘመን የተፈጠሩ የሬድዮ ሞገስና ሽቶ የነበሩ፣ የሚወደዱና የሚከበሩ በርካታ ጋዜጠኞች ነበሩን፤” ማለቱን አስታውሰዋለሁ፣ አንደበቱ ይባረክ፡፡ የደረጀን ያህል የሬድዮውን ጓዳና ጎድጓዳ ባላውቀውም በጥቂቱም ቢሆን እሱ ይገልጸው የነበረውን ጊዜ ሬድዮ ጣቢያ አውቀው ስለነበርና ከጊዜ በኋላም በወሰድኩት የጋዜጠኝነት ትምህርት መገናኛ ብዙኃን እንዴት ሊሆኑ እንደሚገባ በመማሬ፣ የደረጀን ጭንቀትና ሕመም በመጠኑ እረዳለታለሁ፡፡

የኤፍ ኤም ሥርጭት በአገራችን በመደበኛነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሬድዮ ጋዜጠኝነት የጀመረውን የቁልቁለት ጉዞ እንዲህ በቀላሉ ታኮ አድርገን ልናስቆመው የማንችልበት ደረጃ ላይ የደረስን ይመስለኛል፡፡ ከላይ ደረጃ የዘረዘራቸውና እሱም ያላስታወሳቸው ጉድለቶች የመጡት በአንድ ጀምበር ሳይሆን አንዱ የአንዱን ስህተት እያየ የተሻለ የሚለውን ስህተት እየጨመረበት፣ ስህተትንም የሚያርም ሲጠፋና ቁጥራቸውም ከዓመት ዓመት እየጨመረ ሲመጣ፣ ሁሉም ሥራቸው ያውጣቸው እያለ ሲተዋቸው ቀስ በቀስ መሆኑን ማንም ይረዳዋል፡፡ አንድ ኢንተርኔት ቤት ለመክፈት ቢያንስ የIT ዲፕሎማ በሚጠየቅበት አገር፣ በሬድዮ ስቱዲዮ የቀጥታ ሥርጭት ላይ ቀርቦ ያሻውን ለመናገር ግን ስፖንሰር (ገንዘብ) ብቻ አምጣ እንጂ እንዳሻህ ሁንበት ብሎ አንድን ሰው መልቀቅ የጋዜጠኝነት ሙያን መናቅ ብቻ ሳይሆን፣ በዜጎችና በአገር ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ በወጉ አለመረዳትም ጭምር ነው፡፡ ዛሬ የመገናኛ ብዙኃኖቻችንን የሚያስተዳድሯቸው አካላቶችም ሆኑ፣ እቆጣጠራቸዋለሁ የሚለው መንግሥት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ነገ ለምትገኝበት ከፍታ ይሁን ዝቅታ የዛሬዎቹ የኤፍኤም ሬድዮ ጣቢያዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ የመገናኛ ብዙኃን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡

ጋዜጠኝነት በርካታ ሙያው የሚጠይቃቸው ደረጃዎችች (Steps) ያሉትና ጥብቅ ዲስፒሊንን የሚጠይቅ ሲሆን፣ ከሁሉም በፊት ግን ለሙያው የሚገባ አካላዊና አዕምሮአዊ ብቃት፣ እንዲሁም ሐሳብን በጽሑፍ የማስፈር ችሎታ ያስፈልገዋል፡፡ አንድ ሾፌር ተሽከርካሪ ከመዘወሩ በፊትና ሙያውንም ለመማር ከመጀመሩ በፊት አካላዊና አዕምሮአዊ ብቃቱ የሚታየውን ያህል፣ በሬድዮ የአየር ሞገድ በሚናኘው ንግግራቸው ወይንም ጋዜጣና መጽሔት ላይ የሚያትሙት ጽሑፎች ብዙ ጉዳቶችን ከማድረሳቸው በፊት፣ በጋዜጠኝነት ሙያ ለመቀጠል የሚሹ ሰዎችም ቢያንስ መሠረታዊ የሆነውን ብቃትና ዝግጅት እንዲያሟሉ ሊደረጉ ይገባል፡፡

በጋዜጠኝነት ሙያ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ቋንቋ ነው፡፡ ሲጀመርስ ቋንቋ ባይኖር ጋዜጠኝነት እንዴት ይታሰብ ነበር? በዚህም መሠረት የመገናኛ ብዙኃን የራሳቸው የሆነ የቋንቋ አጠቃቀም አላቸው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ (ሬድዮና ቴሌቭዥን) ሚዲያዎች የቋንቋ አጠቃቀም ከሕትመቱ ሚዲያ ከሚለይበት ነገሮች አንደኛው ሬድዮና ቴሌቭዥን መደበኛ ያልሆነ (Informal) ቃላቶችን በመጠቀም የአድማጭ ተመልካቾችን ቀልብ መያዝ ሲኖርበት፣ የሕትመት ውጤቶች ግን ታዳሚዎቻቸው (አንባቢዎች) በተሻለ የቋንቋ እውቀት ደረጃ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ስለሚታሰብ መደበኛ (Formal) የሆኑ ቃላቶችን መጠቀም የግድ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ማለት የሬድዮ አድማጮች ዝቅ ባለ የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አብዛኞቹ ባይሆኑም ከጋዜጣ አንባቢዎቹ ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ወይንም በተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙ አድማጮች መኖራቸውንም መዘንጋት አያስፈልግም፡፡ ምንም እንኳን ለሬድዮና ቴሌቭዥን ፕሮግራሞች መደበኛ ያልሆነ ቋንቋ መጠቀም የሚበረታታ ቢሆንም ቅሉ፣ እጅግ የወረዱና በተለምዶ “የመንደር” ሊባሉ በሚችሉ ተራ (Derogatory) ቃላት መነጋገር ግን ፈጽሞ የተከለከለ ነው፡፡ ሬድዮ መንደር ሳይሆን አገር መሆኑን መረዳት ግድ ይላል፡፡

ወቀሳ ስህተቶችን ለይተን እንድናይ ቢያስችለንም በቀጣይ ግን ምን ማድረግ እንዳለብን አይነግረንም፡፡ ስለ ኤፍ ኤም ሬድዮ ችግሮች በተደጋጋሚ ከተለያዩ አካላት እሮሮ ቢሰማም ጉዳዩ በመሻሻል ፈንታ እየባሰ ሲሄድ የሚታየውም ለዚህ ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃኑን በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ሰዎች ያለውን ችግር ቢረዱትም ምን ማድረግ እንዳለባቸው አለማወቃቸውም ሊሆን ይችላል ለውጡን የገደበው፡፡ የጋዜጠኝነት ትምህርትን ለማስተማር አንጋፋው ጋዜጠኛ ጋሽ ማዕረጉ በዛብህን የመሳሰሉ ሰዎች ሞክረውታልና ፈለጋቸውን ተከትለው ሌሎችም ሊያጠናክሩት እንደሚገባ አምናለሁ፡፡ ለአሁኑ ግን ሙያውን የተመለከተ እውቀት ሳይሆን በዕለት ተዕለት ውሏችን በምናስተውላቸው ጥቃቅን በሚመስሉ፣ ግን አላዋቂነትን አጉልተው በሚያሳዩ የቋንቋ አጠቃቀሞች ላይ በመመሥረትና፣ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሠሩ ሰዎች እየፈጸሙ የሚገኙት ስህተቶች ላይ አተኩሬያለሁ፡፡ አንባቢዎቼም በተለይ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚሠሩ ሰዎች ማስተዋል እንዲጀምሩ በማስቻል፣ የመገናኛ ብዙኃን ተከታታይ ለሆኑትም በሚከታተሏቸው ፕሮግራሞች ላይ የሚያገኙት መረጃና የቃላት አጠቃቀም ሁልጊዜም ትክክል እንደሆነ ስለሚረዱ፣ አንዱ የሬድዮ አቅራቢ እንደዋዛ የሚናገረውን አባባል ሰዎች በዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ላይ ሲጠቀሙበትና እንደ ትክክለኛ አነጋገር ሲወሰድ አስተውያለሁና በዚህ አጋጣሚ እነዚህን ስህተቶች ሊያስተካክሏቸው እንዲችሉ ዕድሉን ይከፍታል እላለሁ፡፡

የብዙዎቹ የኤፍ ኤም ሬድዮ አቅራቢዎች የወረደ የቋንቋ አጠቃቀም የሚጀምረው ከሰላምታቸው ነው፡፡ እስኪ ጥቂቶቹን በየተራ ለመመልከት እንሞክር፡፡

  1. ሄሎ፣ ሃይ፣ ቻው . . . ወዘተ፡- አንድ በአማርኛ ቋንቋ ዝግጅቱን የሚያቀርብ ሰው በምን መስፈርት ነው በእንግሊዝኛ ይሁን በጣሊያንኛ ወይንም በቻይንኛ ሰላም ብሎን ዝግጅቱን የሚጀምረው? የቋንቋ ችሎታውን ሊያስረዳን ነው ወይንስ ዘመናዊነቱን ሊያሳየን? በመገናኛ ብዙኃን የሚነገሩ ጉዳዮች በሙሉ ምክንያት ሊኖራቸው ያስፈልጋል፡፡ ምክንያትም ሲባል ተጨባጭ የሆነ ምክንያት እንጂ፣ እንዲያው በደፈናው ለማሳቅ (ለማዝናናት)፣ ለማሳወቅ ወዘተ . . . ብለን አለባብሰን የምናልፋቸው አይደሉም፡፡ ካዛንቺስ በአንድ መጠጥ ቤት ውስጥ ሁለት ሰዎች ተደባድበው በአቅራቢያቸው ወደሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ሄዱ ቢባል መረጃ ነው፡፡ ግን በምን ይዞታው ነው በአገሪቱ የተለያዩ ማዕዘናት ለሚገኙ አድማጮች ሊቀርብ የሚችለው? ለዚህ ነው የትኛውም ጉዳይ ያለ በቂ ምክንያት በመገናኛ ብዙኃን ሊነገር አይገባውም የሚባለው፡፡ እዛው መንደሩ ውስጥ ወይንም ከጓደኞቹ ጋር ነው እንዲህ ያለ ሰላምታውን ወይንም ውይይቱን ሊያደርግ የሚገባው፡፡ ዘወትር የሚንቁንን፣ የሚያንቋሽሹንንና እስከነመፈጠራችንም የማያውቁንን የባዕዳን ቃላትን ለመጠቀም አይደለም፡፡ የአገራችንን ውብ ብሔረሰቦችን ቃላት እንኳን እንጠቀም ብንል ምክንያታችንን በአግባቡ ማወቅም ማሳወቅም አለብን፡፡
  2. ጤና ይስጥልኝ . . . አብሮ ይስጥልኝ፡- ሰላምታ የምናቀርብባቸው ቃላት ዋጋ ያላቸውን ያህል፣ ሰላምታውን የምንመልስበትም ሁኔታ እንዲሁ በዘፈቀደ ሊሆን አይገባም፡፡ ጤና ይስጥልኝ ብሎ ሰላምታ መስጠት አግባብነት ያለውና ለየትኛውም ወቅት የሚሆን ተስማሚ ሰላምታ ቢሆንም መልሱ መሆን ያለበት ግን ‹አብሮ ይስጥልኝ› ሳይሆን ራሱኑ በመድገም ጤና ይስጥልኝ፣ ሊሆን ይገባዋል፡፡ አብሮ ይስጥልኝ ብለን የምንመልሰው፣ እግዚአብሔር ይስጥልኝ ወይንም አላህ ይስጥልኝ ብሎ ለመረቀን ሰው ነው፡፡ “ጤና ይስጥልኝ” ምርቃት ሳይሆን ሰላምታ ነው፡፡
  3. እንደምን ዋላችሁ፣ አደራችሁ፣ አመሻችሁ . . . ወዘተ፡- ሰላምታ በትክክለኛው ቋንቋና አግባብ የመገለጹን ያህል ትክክለኛውን ጊዜም ሲጠብቅ ያምራል፡፡ የኤፍ ኤም ጣቢያዎቻችን አብዛኛዎቹ ከማለዳ እስከ ምሽት ድረስ የሚዘልቁ በመሆናቸው ለየደረሱበት ሰዓት የሚሆነውን የሰላምታ አሰጣጥ አቅራቢዎቹ ሊያውቁት ይገባል፡፡ ይኼንን ጉዳይ በተመለከተ በተለይ የሰዓቶች ድንበርን አስመልክቶ አከራካሪ ጉዳይ ሊፈጠር ቢችልም በበኩሌ ከዚህ በታች በተገለጸው መልኩ ቢቀርብ አመክራለሁ፡፡

ከጠዋት 12፡00 ሰዓት እስከ ጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ድረስ እንደምን አደራችሁ፡፡

ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት እስከ ቀኑ 6፡00 ሰዓት ድረስ እንደምን አረፈዳችሁ፡፡

ከቀኑ 6፡00 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12፡00 ሰዓት ድረስ እንደምን ዋላችሁ፡፡

ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት በኋላ እንደምን አመሻችሁ፡፡ ቢባል በበኩሌ ትክክል ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሻለ እውቀት ያላቸው ሰዎች ቢከራከሩበትና አንድ የሚያስማማ ውሳኔ ላይ ቢደረስ ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ከጠዋቱ 2፡00 ሰዓት ዜና ሲያነቡም ሆነ ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ላይ እንደምን ዋላቸሁ ብሎ መጀመር፣ ጠዋት 4፡00 ሰዓትና 5፡00 ሰዓት ላይ እንደምን አደራችሁ ብሎ ሰላምታ፣ በበኩሌ ያለ አዋቂ ሰላምታ ስለሆነ መቅረት አለበት እላለሁ፡፡ የትኛውን ሰላምታ ለማቅረብ አቅራቢው ግራ የሚጋባም ከሆነ ፕሮግራሙን እንዲያው በደፈናው ጤና ይስጥልን፣ ብሎ መጀመርም ይችላል፡፡

  1. ፕሮግራሙ በሰላምታ የመጀመሩን ይህል ለስንብቱም ሰላምታ የግድ ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው የጋዜጠኞቻችን አስቂኝ ሰላምታዎች ብቅ የሚሉት፡፡ (“መልካም ተዝናኖት” ብሎ ፕሮግራሙን የዘጋውን ሰውዬ ትቼው) ሰናይ ጊዜ፣… ብሩህ ቀን፣… ቀና ቀን፣… ባይ ባይ፣… ቻው፣ . . . ወዘተ እያሉ ቀላሉን ሰላምታ ለምን ማወሳሰብ እንደሚያስፈልግ አስቤ፣ አስቤ ልደርስበት ያልቻልኩት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ውብ የሆኑና ሁላችንንም ሊያግባቡን የሚችሉ የሰላምታ (የስንብት) ቃላቶች እያሉልን ደህና ሲያዳምጠን የነበረውን አድማጭና ተመልካች በመጨረሻ ኮሚክ በሆነ ሰላምታ ማደናገር ለምን እንደሚያስፈልግ ግራ ያጋባኛል፡፡ ደህና ዋሉ፣ ደህና አምሹ፣ ደህና እደሩ፣ የሚባሉት ግሶች ከላይ እንደተገለጸው የሚያምታቱን ከሆኑ በአጭሩ “መልካም ጊዜ” ወይንም “ጤና ይስጥልን” ብለን መሰናበትም እንችላለን፡፡

ከመገናኛ ብዙኃኖቻችን ሰላምታ ወጣ ብለን ደግሞ ሌሎች ሊታረሙ ይገባቸዋል ብዬ የማምንባቸውን አንዳንድ አላስፈላጊና የተሳሳቱ የቋንቋ አጠቃቀሞችን ከዚህ በኋላ በየተራ እንመልከታቸው፡፡

ነባራዊ ሃቅ…..ነባራዊ ሁኔታ፡- ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል እንደሚባለው አንዳንድ ስህተቶች እጅግ እየተለመዱ ሲመጡ ትክክል እንደሆኑ የሚቆጠሩበት ጊዜ ቀላል አይደለም፡፡ በእኛም አገር የመገናኛ ብዙኃን እንዲህ ዓይነት ስህተቶችን ሲደጋግሙ ይስተዋላሉ፡፡ በእርግጥ ሁሉም ናቸው ሊባል በሚችል መልኩ ካለማወቅ እያደረጉት እንደሚገኙ በበኩሌ ከማምንባቸው አነጋገሮች አንዱ ከላይ የጠቀስኩት “ነባራዊ” የሚባለው ቃል ነው፡፡

በመሠረቱ ይህንን አባባል የምንጠቀምበት ጊዜን ለማመልከት ነው፡፡ ለምሳሌ ነባራዊው ሁኔታ የሚያሳየን ኢትዮጵያውያን ከመስረቅ መሥራትን ይመርጡ እንደነበር ነው ስንል፣ በአንድ ወቅት የነበረውን የሰዎችን አስተሳሰብ ለመግለጽ ያስችለናል፡፡ ነባራዊ በሚለው ቃል ላይ ተመሥርተንም ወቅቱ/ጊዜው መቼ እንደሆን እናውቅበታለን፣ ነበረ ካለ ትናንትን እንጂ ዛሬን አያመለክትምና አባባሉ ቀድሞ የነበረን ልማድ እንደሚያስረዳን ለማወቅ ያስችለናል፡፡ በአንፃሩም በአሁኑ ወቅት የሚገኝን ሁኔታ ለመግለጽ የምንጠቀምበት ግስ ወቅታዊ ሁኔታ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ከላይ በሰጠነው ምሳሌ ላይ ተመሥርተን ዛሬን መግለጽ ስንሻ ልንጠቀምበት የሚገባው አባባል ወቅታዊው ሁኔታ የሚያሳየን ግን፣ ሰዎች በአቋራጭ ለመክበር ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ነው የሚለው ይሆናል፡፡

መቼ እንደተጀመረ ባላውቀውም የቀድሞውንም ይሁን የአሁኑን ጊዜያት ለሚያመለክት (በአብዛኛው የአሁን ላይ የሚገኝ ኹነትን ለመግለጽ) አገላለጽ በአጠቃላይ ነባራዊው ሁኔታ፣ ነባራዊው ሃቅ እየተባለ ሲገለጽ በብዛት ይታያል፡፡ ከመገናኛ ብዙኃን አልፎም ለቃለ ምልልስ የሚጋበዙ ሰዎች ላይም ተፅዕኖው በመኖሩ ዛሬ ዛሬ በምንሰማቸውም ሆነ በምናያቸው ፕሮግራሞች ላይ ‹ወቅታዊው› የሚለው ቃል እየጠፋ፣ ስለ ዛሬ እየነገሩን እንኳን ነባራዊው ሃቅ ሲሉን ይታያሉ፡፡ በጣም የሚያስደንቀው ጉዳይ እርስ በርስ የሚቃረኑ ቃላት በአንድ ዓረፍተ ነገር ላይ ሆነውም ስህተቶችን ማስተዋል ሲቸገሩ ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን ላይ ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየን . . .  ሲባል መስማት የተለመደ አባባል ሆኗል፡፡ ልብ ላለው ሰው አሁንና ነባራዊ የሚሉት ሁለቱ ቃላት ተቃራኒዎች ናቸው፡፡ በአንድ ዓረፍተ ነገር ውስጥ ተስማምተው መቆም በፍጹም አይችሉም፡፡ ‹አሁን› የሚገልጸው ዛሬ ላይ ያለን ሁኔታ ሲሆን ‹ነባራዊው› ግን ቀድሞ የነበረውን፣ ዛሬ ላይ የሌለውን፣ ምናልባትም ተመልሶ የማይመጣውን ሁኔታ ነው የሚያሳየው፣ በመሆኑም ዛሬ ላይ ስላለው ጉዳይ ለመነጋገር ተስማሚው ግስ ወቅታዊው ሁኔታ/ሃቅ የሚለው ሲሆን፣ ከዚህ በፊት፣ ቀደም ሲል፣ ድሮ፣ ወዘተ . . .የተከናወኑትን ሁኔታዎች ለመግለጽ ደግሞ የምንጠቀመው ነባራዊው ሁኔታ/ሃቅ በማለት ይሆናል፡፡ በዚህ መልኩ የመገናኛ ብዙኃን ትክክለኛ ያልሆኑ የቃላት አጠቃቀምን በማስተካከል ለሌሎቻችን ሞዴል ሊሆኑ ይገባል እንጂ እነርሱ ራሳቸው ደህናውን ቃል በማጣመም ውዥንብር ውስጥ ሊከቱን አይገባም፡፡

. . . ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡- ብዙዎቻችን በታሪክ እንደዚህ ያለ ግራ የሚያጋባና ምን ለማለት እንደተፈለገ እንኳን ለማወቅ የሚያስቸግር አነጋገር በተደጋጋሚ ሰምተን የምናውቅ አይመስለኝም፡፡ እስቲ አንድ ምሳሌ እንውሰድና ሊኖሩ የሚችሉትን ትርጉሞች እንመልከታቸው፡፡

ለምሳሌ አንድ ሰው የመንገድ ግንባታው እየተጠናቀቀ ያለበት ሁኔታ ላይ ነው ያለው ብሎ ሲገልጽ፣

1ኛ የመንገድ ግንባታው ተጠናቋል፡፡

2ኛ የመንገድ ግንባታው ተጀምሯል፡፡

3ኛ የመንገድ ግንባታው ከመጠናቀቁ በፊት ቆሟል፡፡

4ኛ የመንገድ ግንባታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ይቀረዋል፡፡

    5ኛ የመንገድ ግንባታው ለመጠናቀቅ ገና ብዙ ይቀረዋል፡፡ ወዘተ . . . ለሚሉት ትርጉሞች ሁሉ ክፍት የሆነ አባባል ሆኖ ይቀርባል፡፡   

በትክክል እገሌ ጀመረው ወይንም በዚህ ጊዜ ተጀመረ ለማለት ባልደፍርም፣ የዚህ ዓይነቱን አባባል ያመጡት በፖለቲካው ምኅዳር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ሰዎች ናቸው፡፡ አሁንም ቢሆን በይበልጥ እየተጠቀሙበት የሚገኙት እነዚሁ ፖለቲከኞቻችን ናቸው፡፡ እርግጥ አባባሉ ለፖለቲካ የተመቸም ነው፡፡ ነገሮችን አለባብሶና ለትርጉም ክፍት አድርጎ መተው የፖለቲካ ሰዎች የሚጠቀሙበት የተለመደ አካሄድ ነው (ዛሬ ቀርቷል ካልተባለ በስተቀር) ለዓመታት የተጓተተን የመንገድ ሥራ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አንድ ባለሥልጣን ቢጠየቅ ከላይ ከተገለጸው አባባል የተሻለ ሐሳቡን ሊገልጽበት የሚችልበት ቋንቋ አያገኝም፡፡

ጋዜጠኛ ግን ዋነኛ ሥራው ጉዳዮችን አጥርቶና ምንም ዓይነት የትርጉም ክፍተት እንዳይኖር በማድረግ ለአድማጭ/ተመልካቹና ለአንባቢዎቹ ማቅረብ በመሆኑ፣ ከላይ በተገለጸው ሁኔታ አለባብሶ ሊመልስ የሚሞክር ሰው ሲያጋጥመው፣ “ምን ለማለት ፈልገው ነው? ”በማለት አፋጦ ትክክለኛውን ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ በተገላቢጦሹ የኛ አገር ጋዜጠኛ ተብዬዎች ይህንኑ አደናጋሪ አባባል ከፖለቲከኞቹ አፍ ተቀብለው የስቴዲዮሙ በሮች ጠዋት አምስት ሰዓት ላይ የሚከፈቱበት ሁኔታ ነው ያለው በማለት ግራ ያጋቡናል፡፡ አድማጭ ምን ብሎ ይህንን አባባል ይረዳዋል?  ስምስት ሰዓት ላይ በሮቹ ይከፈታሉ፣ ይከፈቱ ይሆናል፣ ሊከፈቱም ላይከፈቱም ይችላሉ . . . ወዘተ፡፡ እናስ በዚህ ሁኔታ የቀረበ መረጃ መረጃ ተብሎ ይቆጠራል?

አንዳንድ ጋዜጠኞች በፖለቲካው መስመር ውስጥ የሚገኙ (የፓርቲ አባላት) በመሆናቸው የሥራ መደበላለቅ ሲፈጠር የሚከሰት ቋንቋ ችግር ሊሆን እንደሚችል ቢገባኝም፣ ከመገናኛ ብዙኃን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሊጠፉ ከሚገቡ አባባሎች መካከል አንዱ ይህ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው የሚባለው አባባል ነው፡፡ አሁን ባለንበት ጊዜ ወደ እንደ አጠቃላዩ ሕዝብ ገብቶ በጥቅም ላይ አልዋለም እንጂ (እጅግ ግራ አጋቢ አባባል በመሆኑ ይሆናል) አባባሉ በቅርቡ ተለምዶ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ላይ ጥቅም ላይ ሲውል እንዴት እንደምንደነቋቆር ማንም መገመት ይችላል፡፡

የሕክምና ባለሞያዎች እንደሚነግሩን በሽታዎች ተላላፊና የማይተላለፉ ተብለው እንደሚለዩት ሁሉ፣ እነዚህም የመገናኛ ብዙኃን ችግሮች (ሕመሞች) በከፍተኛ ደረጃ ተላላፊ በመሆናቸው ዛሬ ይሻላል እንኳን ብለን ልንጠራው የምንችለው የኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያ እያጣን መምጣታችን ብቻ ሳይሆን፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ብዛታቸው እየጨመረ በመጣው የቴሌቭዥን ጣቢያዎችችን ጭምር እግሩን አሾልኮ እየገባ ይገኛል፡፡ ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ጉዳይ የሕትመት ሚዲያዎቻችን እንዳያድጉ ከፍቃድ አሰጣጥና የሕትመት ዋጋ መናር ጋር በተያያዘም ጭምር ከፍተኛ ተፅዕኖ እየተደረገባቸው፣ ቁጥራቸው በጣት የሚቆጠሩ ብቻ እየሆኑ በመጡበት አገር (የሕትመት ሚዲያዎቻችን ችግር የለባቸውም ወይንም አልነበረባቸውም ለማለት ባልደፍርም፣ ከነችግሮቻቸው ቢያንስ አንባቢ ትውልድ እያፈሩ የነበሩ በመሆናቸው ዛሬ በከፍተኛ ፀፀት ልናስታውሳቸው ግድ ይለናል፡፡ በየቤቱና በየካፌው ተቀምጦ ቴሌቭዥን ከማየትና በሞባይልም ይሁን በሌላ ሬድዮን ከመስማት፣ ምንም ዓይነት የሕትመት ውጤት ማንበብ የተሻለና አንባቢ ሊባል የሚችል ትውልድ ሊያፈራ እንደሚችል ማንም ተራ ሰው ሊረዳው እንደሚችል ግልጽ ይመስለኛል)፣ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያው እንደዚህ እንደልቡ እንዲሆን የተፈቀደበት ምክንያት ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽ እንደሆነብን ይገኛል፡፡

የሚቀርቡና የማይቀርቡ ዝግጅቶች፡- ከሰላምታቸው ቀጥለው ብዙዎቹ የፕሮግራም አቅራቢዎች በዕለቱ ፕሮግራሞቻቸው የሚያቀርቧቸውን ዝግጅቶች መዘርዘር የተለመደ ነው፡፡ እነዚህና እነዚያን ጉዳዮች በዛሬው ፕሮግራማችን እንዳስሳለን ከተባለ በኋላ አንድ ሁለቱን ጉዳዮች ጠቃቅሰው በመሃል ያልተያዘ አጀንዳ (አንዳንዴም ከርዕሱ ጋር ምንም ግንኙነት በሌለው ጉዳይ) ላይ ሲሟገቱ ይውሉና፣ ይቅርታ አድማጮቻችን ሰዓታችን ሳናስበው ስላለቀብን የቀሩትን ጉዳዮች በሚቀጥለው ፕሮግራማችን ይዘንላችሁ እንቀርባለን መባሉ እየተለመደ ብቻ ሳይሆን ደንብ እየሆነ የመጣ እስኪመስል ድረስ ይደጋገማል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በተለይ የተካኑ አዘጋጆችን መጥቀስ ይቻላል፡፡

ለዚህ መሰሉ ችግር ዋነኛው ምክንያት የፕሮግራም ቅድመ ዝግጅት ማነስ ነው፡፡ አንድ ፕሮግራም ከመቅረቡ በፊት በተወሰነው ሰዓት ሊቀርቡ የተዘጋጁት ነገሮች ቀድመው መታወቅና የሚወስዱትም ሰዓት ተመጥኖ ነው ወደ ስቱዲዮ የሚገባው፡፡ ከስንት አንድ ጊዜ አስቸኳይ ወይንም ‹ሰበር› የሆኑ ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ቢታመንም፣ ከዚህ ውጪ ግን የሚቀርቡት ሙዚቃዎች፣ ማስታወቂያዎችና ሌሎችም ግብአቶች ቀድመው የታቀዱ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ምናልባት የሰዓት መጣበብ ከተፈጠረም (ሊሆን የማይገባው ቢሆንም) የትኛውን ሙዚቃ ወይንም ዝግጅት ማጠፍ እንደሚያስፈልግ አዘጋጁ ቀድሞ ማሰብ አለበት፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ ግን ይቀርባል የተባለን ጉዳይ ሳያቀርቡ ሰዓት አለቀብን በሚል ሰበብ መውጣት እንደ እኔ አድማጩን መናቅ ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው፡፡ ጉዳዩን ሁሉ ትቶ ‘ይኼንንስ ጉዳይ ዛሬ መስማት አለብኝ፣ በዚህ ነገር ላይ በቂ መረጃ እንዲኖረኝ ስመኝ ነበር’ ብሎ ሲጠብቅ የቆየን አድማጭ፣ ይኼንን ነገር ሌላ ቀን ነው የምንነግርህ፣ ያቃጠልከው ጊዜም የራስህ ጉዳይ ነው ብሎ መሄድ ለጤነኛ ሰው የሚቻል አይመስለኝም፡፡

ሁለተኛው የሰዓት መጣበብ መንስኤ፣ ዝግጅቶቹ የሚቀርቡት በተጻፈና በተጠና መልኩ ሳይሆን  በብጫቂ ወረቀት ላይ ነጥቦቹን ብቻ በማስፈርና፣ አልፎ አልፎም ባዶ እጅና እግርን (ከረጅም ምላስ ጋር) ብቻ ይዞ ስቱዲዮ በገባ አቅራቢ ስለሚሆን በዚህ አያያዙ ሰዓቱን ሊገምት የሚችልበት ምንም ዓይነት ሁኔታ ባለመኖሩ ነው፡፡ ለዚህም መፍትሔው በተቻለ መጠን ዝግጅቶቻቸው በጽሑፍ የሠፈሩ (Scripted) መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ እንደዚሁም ለአንድ የሬድዮ ፕሮግራም በስቱዲዮ የሚገኙትን ሰዎች ቁጥር መመጠንም እንዲህ ዓይቱን ችግር (የጊዜ መጣበብን) ለማስቀረት ይረዳል፡፡ አቅራቢዎቹና አስተያየት ሰጪዎቹ በበዙ ቁጥር ሐሳቡም እየሰፋ ስለሚሄድ በኋላ ላይ መሰብሰብ ያስቸግራል፡፡

እገሌ የተባለው ሰው እየመጣ ነው፡- ሌላው በተደጋጋሚ የሚደመጠውና የኤፍ ኤም ጣቢያዎቻችን ዘይቤ እየሆነ የመጣ አባባል ነው፡፡ በጋዜጠኝነት መርህ ሰዓት ማክበር ትልቁ ለሙያው ያለንን አክብሮት ማሳያ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይኼንን ከሚያስታውሱን የእንግሊዘኛ አባባሎች መካከል የሚከተለው ይገኝበታል ‹‹If you are early you are on time, if you are on time you are late, if you are late never assume your job›› ወደ አማርኛ ስመልሰው ‹‹ከሰዓትህ ቀድመህ ከተገኘህ ትክክለኛው ሰዓት ነው፣ በሰዓቱ ከደረስክ አርፍደሃል፣ ካረፈድክ ደግሞ ሥራህን ቀይር›› ተብሎ ሊተረጎም የሚችል ይመስለኛል፡፡

ጋዜጠኛ ሰዓት ሁለመናው ነው፡፡ አንድ ጋዜጠኛ በሰዓቱ ባለመድረሱ ጋዜጣዊ መግለጫ ሊያመልጠው ይችላል፣ ለቃለ ምልልስ የቀጠረውን ባለሙያ ሊያጣው ይችላል፣ የአየርም ይሁን የምድር ትራንስፖርት ሊያመልጠው ይችላል፣ ወዘተ . . . በዚህም የሚጎዳው ራሱን ብቻ ሳይሆን እወክለዋለሁ ያለውን መገናኛ ብዙኃንና በመጨረሻም ከእርሱ ብዙ ነገር የሚጠብቀውን አድማጩን ነው፡፡ በሰዓቱ ቦታቸው ላይ ባልተገኙ ጋዜጠኞችና ሌሎች ባለሙያዎች ምክንያት የጣቢያዎች የመክፈቻ ጊዜ ሲስተጓጎል አይተናል፣ የዜና ሰዓቶች ሲተላለፉ (ሲራዘሙ) አስተውለናል፣ ፕሮግራሞች በሙዚቃ ሲሸፈኑ አጋጥሞናል፡፡ አሁን አሁን ደግሞ እገሌን እየጠበቃችሁ እስከዛው ከእኛ (ከእኔ) ጋር ትቆያላችሁ የሚል አሳፋሪ አነጋገር መደመጥ ጀምሯል፡፡ ደግነቱ ይመጣል የተባለው ሰው ሳይመጣ ቢቀርም የሚያጎድለው ብዙም ቁምነገር ስለሌለ፣ የቀረበልንን እንደነገሩ የሆነ ዝግጅት አጣጥመን ጊዜአችንን እናበቃለን፡፡ ከዚህ ይልቅ ሊሆን የሚገባው ነገር ማንም ይሁን ማን በምንም ምክንያት የሚያረፍድ ከሆነ የእርሱን ቦታ ሊሸፍን በሚችል ሰው መተካት የመጀመሪያው አማራጭ ሲሆን፣ ዝግጅቱ ግን ካለእርሱ ፈጽሞ የማይታሰብ ከሆነ ቀረፃውን በቅድሚያ አጠናቆ በሰዓቱ ለአድማጭ ማቅረብ ሁለተኛው አማራጭ ነው፡፡

መልዕክቶችን፣ መረጃዎችን . . . እንስማ፡- በመገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡ ማናቸውም ጉዳዮች መረጃዎች ናቸው፣ ስለዚህም የሆነ መልዕክት ሊኖራቸው ግድ ይላል፡፡ ፕሮግራሙ የመዝናኛ እንኳን ቢሆን የሆነ መልዕክት ወይንም መረጃ ይኖረዋል ተብሎ ይታሰባል፣ አለበለዚያ ግን እየቀረበ ያለው ጉዳይ እንዲያው እንቶ ፈንቶ ነው ማለት ነው፡፡ አስቂኙ ነገር በሬድዮና ቴሌቭዥን አቅራቢዎች መረጃ ወይንም መልዕክት በሚል ኩል ተቀባብተው የሚቀርቡት ጉዳዮች ምንም ነገር ሳይሆኑ ማስታወቂያዎች ናቸው፡፡ ማስታወቂያ ደግሞ አንድ ድርጅት ይሁን ግለሰብ ገንዘብ ከፍሎ ምርቱን ወይንም አገልግሎቱን ለሰዎች የሚያስተላልፍበት መንገድ ነው፡፡ ምንም ያህል ለአድማጩ ወይንም ለተመልካቹ መልካም ነገር ይኑረው፣ ማስታወቂያ የአስነጋሪውን ጥቅም በማስቀደም የሚተላለፍ ሲሆን ለመገናኛ ብዙኃኑ ደግሞ የገንዘብ ምንጭ ሆኖ የሚያገለግል ቁስ ነው፡፡ ምናልባት ታዳሚዎች ማስታወቂያ ስሙ (ተመልከቱ) ቢባሉ ደስ ላይሰኙ ይችላሉ ተብሎ በጋዜጠኞቻችን ዘንድ ስለታሰበ ይሁን ወይንም በሌላ ምክንያት፣ ማስታወቂያ ሰምተን እንመለስ የሚለው አባባል በተለይ ከኤፍ ኤም ጣቢያዎቻችን ላይ እየጠፋ የመጣ ሲሆን፣ እንደ ጥሩ ልማድ ደግሞ በቴሌቭዥን መስኮት ላይ የሚቀርቡ ሰዎችም ሲሉት ይታያል፡፡

ከዚሁ የማስታወቂያ ርዕስ ሳንወጣ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን አሳሳቢ የሆነው ጉዳይ ደግሞ፣ ከዜና አንባቢዎች ውጪ ሁሉም የፕሮግራም አዘጋጆች ለስፖንሰሮቻቸው የሚሰጡትን የአየር ሽፋንና ድጋፍ (Endorsement) ነው፡፡ በዚህም ያልበሉትንና ያልጠጡትን ምርት ሳይቀር፡ ጣፋጭና ከገነት የወረደ ጣዕም ያለው እያስመሰሉ ማውራት፣ ያላገኙትን አገልግሎት እንከን የሌለውና እፁብ ድንቅ አድርጎ መናገር፣ በተለይ ገንዘብ ለከፈለ ድርጅት ሲሆን ፈጽሞ ከሚዲያ ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ይሆናል፡፡ የሰለጠኑት አገሮችን የመገናኛ ብዙኃን ተሞከሮ ሙሉ በሙሉ እንተግብረው ለማለት ባይዳዳኝም ከላይ እንደተጠቀሰው የንግድ ማስታወቂያ ሙሉ በሙሉ የአስነጋሪውን ጥቅም በማስጠበቅ ላይ የሚያተኩር በመሆኑ የፕሮግራም አቅራቢው ስፖንሰሩን በስም ከማስተዋወቅና ማስታወቂያውንም ከማስተላለፍ ውጪ የስፖንሰሩን ምርትና አገልግሎት ከማሻሻጥ (ለማሻሻጥ ከመሞከር) ራሱን ማቀብ አለበት፡፡ ለነገሩማ ትክክለኛውን የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር እንተግብረው ካልን ጋዜጠኞቹ (ሚዲያው) ምንም ዓይነት ምርትና አገልግሎት በስጦታ አይቀበሉም፡፡ በቀላል ምሳሌ የዜና ዘገባ ለመሥራት በሚጓዙበት ወቅት የትራንስፖርትም ሆነ የሆቴል አገልግሎት የሚሸፍነው ጋዜጠኛውን የላከው የመገናኛ ብዙኃን እንጂ ዜናው እንዲሠራለት የጋበዛቸው አካል ሊሆን አይችልም፡፡ ያ ከተደረገ እንደመማለጃ (ጉቦ) ይቆጠራል፡፡ ሌላው ቀርቶ ጋዜጠኞቹ የድርጅቱን የፕሮሞሽን ቁሳቁሶች እንኳን አይቀበሉም፡፡ በእኛ አገር ትራንስፖርት ካልቀረበልንና አበል ከሌለው፣ አልፎ አልፎም የክፍያውን መጠን ወስነው ከዚህ ውጪ ዜናውን አንዘግብም (የምሳ ቡፌው ላይ እና እንደ እስክርብቶና ኮፊያ ፍለጋ የሚጋፉትን ሳይጨምር) ለሚሉት “ጋዜጠኞች” እና “የመገናኛ ብዙኃን” መጥኔ የሚያስብል ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃኑ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙት በብዙ መከራና ልመና በመሆኑ፣ እንዲህ በሉልን የተባሉትን ሁሉ እየጨማመሩም ቢሆን ማለታቸው ጥሩ ጥሩ ደንበኞችን እንደሚያስገኝላቸው ቢታወቅም፣ በከተማችን ውስጥ እንደምናያቸው ደላሎች ዓይናቸውን ጨፍነው ምርቶችንና አገልግሎቶችን የሚያሻሽጡበትን ጉዳይ ቀነስ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መቼም ሕግ ይከበርበታል በሚባልበት አገር ውስጥ አይደለንም እንጂ፣ የማስታወቂያ ሕጉ (759/12) በግልጽ ከሚደነግጋቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የሚሠራጩ ማስታወቂያዎችና የፕሮግራሙ ይዘት በግልጽ መለያየት እንደሚኖርባቸው፣ በፕሮግራሞቹ ይዘት ላይም ተፅዕኖ ማሳደር እንደሌለባቸው ነው፡፡ እንደውም ደረጃቸውን በጠበቁ የውጪ መገናኛ ብዙኃን ታዳሚዎች ማስታወቂያውንና የመገናኛ ብዙኃኑን አንድ እንደሆኑ ቆጥረው እንዳይታለሉ የሚቀርብ ማሳሰቢያ (Disclaimer) ማስታወቂያው በቀረበበት ወቅት አብሮ ይገለጻል፡፡ ከዚህም አልፎ በምርቱ፣ በአገልግሎቱ ወይንም በሌላ ተያያዥ ጉዳይ የዜና ዘገባ የሚሠራለትን የንግድ ድርጅት፣ ማስታወቂውን በተመሳሳይ ወቅት ማቅረብንም የሚከለክሉ የመገናኛ ብዙኃን አሉ፡፡ ‘ዝግጅትህን ስፖንሰር አደርግልሃለሁ ይኼንን የዜና ዘገባ ሥራልኝ ወይንም ይኼንን ጋዜጣዊ መግለጫ አንብብልኝ’ ማለት ጉቦ ከመስጠት በምንም አይተናነስምና፡፡

በቅርቡ የመጣው ሌላ ፈሊጥ ደግሞ ፕሮግራማችንን ያበቃልን የሚል አነጋገር ነው (በእውነት ምን ለማለት እንደተፈለገ በሚናገረው ጋዜጠኛም ዘንድ ግልጽ ያልሆነ ቋንቋ ነው)፡፡ በምን ዓይነት ሁኔታ ያንን ዝግጅት አንድ ማስታወቂያ የሚያስነግር ድርጅት እንዳበቃው አስቤ አስቤ ሊገባኝ ያልቻለ ነገር ሆኖብኛል፡፡ ማንም ሕጋዊ ማንነት ያለው አካል በሕጉ በተቀመጡት መሥፈርቶች መሠረት ያሻውን ጉዳይ ባሻው የመገናኛ ብዙኃን ላይ ለማስተላለፍ ከእርሱ የሚጠበቀው ገንዘብ መክፈል ብቻ ነው፣ እናም የተሻለ ቁጥር ያለው አድማጭ አገኝበታለሁ በሚለው ፕሮግራም መሃል ያንን ማስታወቂያ እንዲያስተላልፉለት ገንዘብ ይከፍላል እንጂ ይህንን ፕሮግራም አብቁልኝ ብሎ ችሮታ የሚያደርግ ድርጅት ወይንም ግለሰብ ተፈጥሯል ካሉኝ፣ በሬድዮ ታሪክ ትልቅ . . . ትልቅ እመርታ መታየት ጀምሯል ማለት ነበር፡፡ ይልቁንስ ተቃራኒው አባባል ትክክል ሊሆን ይችላል፡፡ ማስታወቂያውን በተባለው ሰዓት ላይ ለመደመጥ ያበቃው ዝግጅቱ ወይንም የሚቀርበው ፕሮግራም ነውና፡፡

በድጎማ የተቋቋሙ ካልሆኑ በስተቀር ለንግድ ተብለው ለሚደራጁ የመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያ የጀርባ አጥንታቸው ነው፡፡ እንደ ጋዜጣና መጽሔትን የመሳሰሉት የሕትመት ውጤቶች በሚሸጡት ኮፒ መጠን መጠነኛም ቢሆን ገንዘብ የሚያገኙ ቢሆንም፣ በተለይ ለሬድዮ ግን እንዲህ ዓይነቱ ገቢ የሚታሰብ ባለመሆኑ ጠቅላላ ህልውናቸው የተመሠረተው ጥሩ አድርጎ በሚከፍል ማስታወቂያ አስነጋሪ ድርጅት ላይ ነው፡፡ የአገራችን የሕትመት ውጤቶች መረጃ ባይኖረኝም፣ ባደጉት አገሮች የአንድ ጋዜጣ ህልውናም በከፍተኛ ሁኔታ የተንጠለጠለው በማስታወቂያ ሽያጭ ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህም የማስታወቂያ ገቢ የጋዜጣውን አጠቃላይ ወጪ እስከ 75 ከመቶ ድረስ ይሸፍናል፡፡ እንዲያም በመሆኑ ነው መገናኛ ብዙኃኑ ለሚያገኙት የማስታወቂያ ገንዘብ ከፍተኛ ሥፍራ ሲሰጡት የሚታየው፡፡ በእርግጥም ሊሰጡት ያስፈልጋል፣ ግን ታዳሚዎቹ በሚከፍሉት ዋጋ መሆን የለበትም፡፡ መገናኛ ብዙኃን ትኩረት ሊሰጡት የሚገባው፣ ለታዳሚዎቻቸው በሚያቀርቡት ቁምነገር ላይና የታዳሚዎቻቸውን አመኔታን እንዲሁም ቁጥራቸውን ከፍ በማድረግ ላይ ነው እንጂ፣ እንዴት አድርገን የማስታወቂያ ባለቤቶችን ቀልብ እንስባለን ለሚለው ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ ሚዲያው ተወዳጅ ሆኖ ብዙ አድማጭ/አንባቢ ካተረፈ ማስታወቂያው ያን ጊዜ ሳይወድ በግዱ ይመጣል፡፡

ለማጠቃለለም ያክል ሌላው በኤፍ ኤም ሬድዮ ጣቢያዎቻችን ላይ ያለው ከፍተኛ ችግር የሬድዮ ጋዜጠኝነትን ከመናገር ብቃት ጋር ብቻ አያይዞ የማሰብ ችግር ነው፡፡ ለነገሩማ በየትኛውም የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ላይ ለመሰማራት የሚፈልግ ጋዜጠኛ ከምንም ነገር በፊት እንከን የማይወጣለት ጸሐፊ መሆን መቻል ነበረበት፡፡ የጋዜጠኝነትን ሙያ ከበርካታ ሙያዎች የተለየ የሚያደርገው ጉዳይ ቢኖር በርካታ ተሰጥኦዎችን (Skills) በአንድ ላይ መጠቀም የግድ የሚል መሆኑ ነው፡፡ አንዱ ከአንደኛው ተነጥሎ ከወጣ በግልጽ የሚታይ ጎዶሎ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ጋዜጠኛ ጥቃቅን የሚባሉ (ሌሎች ልብ የማይሏቸውን) ጉዳዮችንም ጭምር የሚያይና በአንክሮ ለማዳመጥ የሚችል መሆን ይገባዋል፡፡ በተጨማሪም ይህንኑ ጉዳይ ሳይጨምርና ሳይቀንስ ለሌሎች ማካፈል ለመቻል አሁንም ልዩ ተሰጥኦ ያስፈልገዋል፡፡ ይህንኑ ተመሳሳይ ጉዳይ በጽሑፍ ማስፈር መቻሉ ደግሞ ከሁሉም የከበደውና የጋዜጠኝነት ብቃቱንም የሚያስመሰክርበት ሌላው ችሎታ ነው፡፡ ሊህም ነው በዓለማችን ላይ የሚገኙት ብዙዎቹ የተዋጣላቸው ደራስያን (ከአገራችንም ብርሃኑ ዘሪሁንና ጳውሎስ ኞኞን መጥቀስ ይቻላል) በቀደመ ሥራቸው ጋዜጠኞች የነበሩት፡፡ አንድ ዓረፍት ነገር እንኳን በወጉ አገጣጥሞ መጻፍ የማይችል ሰው፣ ምንም ያህል የመናገር ብቃት ቢኖረውም ጋዜጠኛ ከመሆን ይልቅ ሌሎች በንግግር ብቻ ሊከወኑ የሚችሉ የሥራ ዘርፎችን (እዚህ ላይ መጥቀስ አስፈላጊ ባይሆንም) ቢቀላቀል የተሻለ ሥራ ሊሰራ ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሌሎች የጻፉትን ማንበብ በራሱ ችሎታን የሚጠይቅ ጉዳይ ቢሆንም፣ ጋዜጠኝነት ግን ከዚህም በላይ ነው፡፡ አሁን አሁን በአገራችን ውስጥ ጋዜጠኛ ተብለው የምናየቸው ሰዎች መጻፍ አይደለም የተጻፈ ለማንበብ እንኳን የሚቸገሩ ሆነው እያረጋገጥን ነውና ሳይቃጠል በቅጠል እንደሚሉት አባቶቻችን ያለፈውን ጥፋት ትተን ከዚህ በኋላ ለሚመጣው ጉዳይ ሁነኛ መፍትሔ ይፈለግለት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...