Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርሁለቱ የኢኮኖሚ ምሁራን የተራራቁ የኢኮኖሚ አመለካከቶች

ሁለቱ የኢኮኖሚ ምሁራን የተራራቁ የኢኮኖሚ አመለካከቶች

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ለሥራ ጉዳይ ከምዘዋወርበት ከደቡብ ክልል የኢንተርኔት ግንኙነት ባገኘሁበት አጋጣሚ ስለኢኮኖሚ ጉዳይ ሁለቱ ታዋቂ ምሁራን በነሐሴ ወር በሪፖርተር ጋዜጣ ያወጡትን ጽሑፎች አይቼ ቀልቤ ተስቧል፡፡ የምሁራንን በሚታወቅ ቋንቋ ሐሳባቸውን ለሰፊው ሕዝብ ማካፈል የዘወትር ምኞቴ ስለተሳካም ደስ ብሎኛል፡፡ ከእነዚህ ከፍተኛ ሙያዊ ዕውቀት ካላቸው ኢኮኖሚስቶች ብዙ መማር የምንችል ይመስለኛል፡፡

የፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ ጽሑፍ ርዕስ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አየር መንገዱ በከፊል ይሸጣል ማለታቸው ከኢኮኖሚ ትንተና አንፃር አሳሳቢ ስህተት ነው የሚል ሲሆን፣ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ጽሑፍ ርዕስ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመስቀለኛ መንገድ ላይ (የነፍስ አድን ዕርምጃ) የሚል ነበር፡፡

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ምንም እንኳ አመለካከታቸውን ለመግለጽ በቅድሚያ የመረጡት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በከፊል መሸጥ ቢሆንም፣ ልማታዊ መንግሥትን ለማራመድ የመንግሥት ይዞታን ጠቃሚነት ሲደግፉ አቶ ኤርሚያስ ግን ትልልቅ ድርጅቶችን ወደ ግል ማዞር ከልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና ማፈንገጥ አይደለም የሚል አመለካከት እንዳላቸው ወስጄአለሁ፡፡ ለአቶ ኤርሚያስ ‹ቢግ ፑሽ› ለሚሉት የዕድገት መንደርደሪያ ወሳኝ የሆኑ ኢንዱስትሪዎችን መርጦ በፖሊሲ ትኩረት መስጠት በዕቅድ ውስጥ ማስገባት እንጂ፣ የመንግሥትና የግል የይዞታ ምርጫ አይደለም፡፡

ሁለቱንም አመለካከቶች አጥብቦና አስፍቶ ማየት ስለሚቻል የእኔ ሙከራ የተለየ አመለካከትን ለማራመድ ሳይሆን፣ ምሁራኑ ግንዛቤያችንን ለማስፋት ትንታኔያቸውን ሰፋ አድርገው እንዲያቀርቡልን ጥያቄ መሰል አስተያየት ለማቅረብ ይሆናል፡፡ አቶ ኤርሚያስ በሁለት ዙር ያቀረቡት ጽሑፍ ሰፋ ያለ ቢሆንም፣ ፕሮፌሰር ዓለማየሁም በሌሎች ምሳሌዎች እመለስበታለሁ ስላሉ ሰፋ ያለ ትንታኔ እንደሚሰጡ እጠብቃለሁ፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የታዳጊ አገሮች መንግሥታትና ተፎካካሪዎቻቸው የፖለቲካ ሰዎች ልቅ ስለሆነ ነፃ ገበያም ሆነ በፖሊሲ ስለሚገራ ነፃ ገበያ የጠለቀ ዕውቀት ስለሌላቸው፣ የሊበራል ኢኮኖሚ ወይም የልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚ የሚሉትን ቃላት ከመደጋገም በስተቀር ምን እንደሆኑ አብራርተው ተናግረው በማያውቁበት አገር፣ የሁለቱ ታዋቂ ኢኮኖሚስቶች አመለካከት የወደፊቷን ኢትዮጵያ አቅጣጫ ለመተለም ፋይዳው ብዙ ነው፡፡

ሰዎች ብሔራዊ ኢኮኖሚው በየዓመቱ በአሥራ አንድ በመቶ እያደገ ለምን ገበያ ውስጥ ምርት ይጠፋል? የሸቀጦች ዋጋ ለምን ይወደዳል? ወጣቶች ለምን ሥራ አያገኙም? ለምን ከውጭ አገር ሰዎች ተበድረንና ተረድተን እንኖራለን? ብለው ያስባሉ፡፡ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት የሚባለውን የብሔራዊ ኢኮኖሚ መጠን ለኪዎቹንም ሥራ ትክክለኛነትና ተዓማኒነት ይጠራጠራሉ፡፡ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ሒሳብ ባለሙያዎች ግን የተባበሩት መንግሥታትን ዘዴ ተጠቅመን የምንለካ ስለሆነ ያላመነ የራሱን አለካክ ይጠቀም እንጂ፣ እኛ ትክክለኛ ነው የምንለውን ነው የምንናገረው ይላሉ፡፡

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ባዘጋጀው ውይይት በእሳቸው የአለካክ ሞዴል ኢኮኖሚው ከአምስትና ከስድስት በመቶ በላይ እንዳላደገም ገልጸዋል፡፡ በቆጠራ የተለካው ነው? ወይስ በናሙና ሞዴል የተለካው ነው? ወደ እውነቱ የሚቃረበው የሚለው እንዳለ ሆኖ የፕሮፌሰር ዓለማየሁ የሞዴል ልኬት የካፒታል ምርታማነትን፣ የሰው ኃይል ምርታማነትንና የቴክኖሎጂ ምርታማነትን በመለካት የግብዓተ ምርትንና የምርትን ተዛምዶ ስለሚያሳይ ለፖሊሲ ውሳኔ የተለየ ጠቀሜታ አለው፡፡

በራስ አቅም ሳይሆን በብድርና በዕርዳታ በተገኘ ገንዘብ ብዙ ሺሕ ኪሎ ሜትሮች መንገዶችና የባቡር ሐዲዶች የተዘረጉበት፣ በሺሕ የሚቆጠሩ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጩ ግድቦች የተገነቡበት፣ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችና ሆስፒታሎች የተሠሩበት፣ ከተሞች ያደጉበትና የተዋቡበት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቆጠራ ዘዴ ተለክቶ አሥራ አንድ በመቶ ቢያድግም፣ በግሉ ኢኮኖሚ ምርታማነት ያልተደገፈው ብሔራዊ ኢኮኖሚ የሸቀጦች ዋጋ ሳይረጋጋበት፣ ለወጣቱ በቂ ሥራ ሳይፈጠርበትና የውጭ ምንዛሪ ክምችት ሳያድግበት ባዶ ቅል ሆኖ አለፈ፡፡

ቅል ባህላዊ የውኃ መጠጫ ኮዳ ሲሆን፣ ውኃ ባልያዘበት ጊዜ ሲያንኳኩት በጣም ይጮሃል፡፡ ቅሉ ሲያንኳኩት እንዳይጮህ ውኃ መሙላት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢኮኖሚም እንዲሁ ነው በየዓመቱ በአሥራ አንድ በመቶ አደግሁ እያለ ይጮሃል ውስጡ ግን ባዶ ነው፡፡ እንዳይጮህ በግል ኢኮኖሚው ተሳትፎ መሞላት አለበት፡፡

የዋጋ ንረት ሁለት አኃዝ ውስጥ ተንጠልጥሎ መውረድ አቅቶታል፡፡ ሥራ አጥነት ከሃያ በመቶ በላይ ሆኖ በየዓመቱ እየጨመረ ነው፡፡ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ልማቱ ተገቷል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዲሱ መንግሥት የዋጋ ንረቱንና የሥራ አጥነቱን ችግሮች በይደር አስተላልፎ ጊዜ በማይሰጠው የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ላይ እየተረባረበ ነው፡፡

በግላዊ ኢኮኖሚው ጥንካሬ ላይ ተመሥርቶ ያልተገነባ ብሔራዊ ኢኮኖሚ፣ የየአንዳንዱን ዜጋ ምርታማነት ያላሳደገ ብሔራዊ ኢኮኖሚ፣ ሸማቹና አምራቹ አዋቂ ተገበያዮች ያልሆኑበት ብሔራዊ ኢኮኖሚ፣ የግሉ ስለብሔራዊው፣ ብሔራዊውም ስለየግሉ በቂ መረጃ የሌለበት ብሔራዊ ኢኮኖሚ፣ ጠንካራ መሠረት ሳይወጣለት እንደተሠራ ፎቅ ቤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመፈራረስ የተመቻቸ ነው፡፡ በገበያ የሚመራው የግል ኢኮኖሚ በፖሊሲ ለሚመራው ብሔራዊ ኢኮኖሚ መሠረት ካልሆነ ዝርዝሩና ጥቅሉ አይታረቁም፡፡

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማቃናት ሁለቱን የግሉንና ብሔራዊውን አጣምሮ ከማየት እንዲደጋገፉ ከማድረግ ውጪ ምንም መፍትሔ የለም፡፡ የግሉ ኢኮኖሚ ለብሔራዊ ኢኮኖሚው መሠረት ካልሆነ ብሔራዊ ኢኮኖሚው ውስጡ ባዶ እንደሆነ ቅል ሲሆን፣ ውጪውም በቀላሉ የሚፈራርስ የእንቧይ ካብ ነው፡፡

ብዙ የታዳጊ አገሮች ለዕድገታቸው ስለሚመርጡት ልታማዊ ኢኮኖሚ አስተሳሰብና የሁለቱን ከፍተኛ ምሁራን አመለካከት ካራራቀው የግልና የመንግሥት ይዞታ ጥያቄ አዘል አስተያየቴን ከማቅረቤ በፊት፣ የዚህ ዘመን የካፒታሊዝም ሥርዓት የኢኮኖሚ ሊቃውንትን ለሁለት ጎራ ስለከፈሉት የኢኮኖሚ አስተሳሰቦች ሁለት ፍልስፍናዎች በጥቂቱ ማየት ይጠቅማል፡፡

በ21ኛው ክፍለ ዘመን የካፒታሊስት አገር ኢኮኖሚስቶች ለሁለት ጎራ በመከፈል፣ አንደኛው የጥንታውያን ኢኮኖሚስቶችን ገበያ ተኮር ኢኮኖሚ የሚደግፉ አዲሶቹ ለጥንታውያን (New Classical) እና የኢኮኖሚስት ኬንስን ፖሊሲ ተኮር ኢኮኖሚ የሚደግፉ አዲሶቹ ለኬንሳውያን (New Keynessians) ተብለው ለሁለት ይከፈሉ እንጂ፣ ሁለቱም በጎራ ከመከፋፈል የአንድ አገር ኢኮኖሚ አስተዳደር ገበያውንና ፖሊሲን በጥምረት ቢይዝ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣ ያስተምራሉ፡፡

ገበያ ተኮር ኢኮኖሚን የሚያራምዱ ኢኮኖሚስቶች፣ ሸማቾችና አምራቾች ወይም ፈላጊዎችና አቅራቢዎች በግብይት ሒደት ውስጥ አዋቂዎች ስለሆኑ የገበያ ጉድለትን በፍጥነት ያስተካክላሉ የሚል እምነት ሲይዙ፣ ፖሊሲ ተኮር ኢኮኖሚስቶች ግን ሸማቾችና አምራቾች ወይም ፈላጊዎችና አቅራቢዎች የገበያውን ጉድለት በፍጥነት ስለማያስተካክሉ መንግሥት ረዥም እጁን አስገብቶ ገበያውን መግራት አለበት ይላሉ፡፡

በፍጥነት የሚለው ቃል ቁልፍ ቃል ነው የማታ ማታ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ ጎደሎ ገበያዎች እንደሚስተካከሉ የሁለቱም ጎራዎች ኢኮኖሚስቶች ያምናሉ፡፡ ሆኖም ገበያዎች እንዲስተካከሉ ኢኮኖሚው መዳበር አለበት፡፡ የታዳጊ አገር ገበያዎች የማይስተካከሉትም ኢኮኖሚው ስላልዳበረና በውጭ አገሮች ሸቀጥ ላይ ጥገኛ ስለሆነ ነው፡፡

ታዳጊ አገሮች ገበያዎቻቸው ያልዳበሩ በመሆናቸው ወደ ካፒታሊዝም ለማደግ በመንግሥት ከግል ባለሀብቱ ጎን ለጎን በምርት ተግባር መሳተፍ ይገባዋል ከሚሉ አክራሪ የልማታዊ መንግሥት ደጋፊዎች አንስቶ፣ ከዚህ ለዘብ ባለ ሁኔታም መንግሥት በቅድሚያ ማደግ የሚገባውን ኢንዱስትሪ መርጦ አምራቹ እንዲከተለው ዕቅድ በማውጣትና አቅጣጫ በማስያዝ የኢኮኖሚ ልማት መንገድ መከተል አለበት የሚሉ አሉ፡፡ ሆኖም ታዳጊ አገሮች ይህን የዳበሩ ካፒታሊስት አገሮች ከያዙት መርህ ውጪ ሦስተኛ አማራጭ የሚመስል አቋም ቢይዙም፣ ገበያ ይብለጥ ወይስ ፖሊሲ ይብለጥ የሚሉት የካፒታሊስት አገሮች እንቆቅልሾች አልለቀቋቸውም፡፡

እኔ ለፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳና ለአቶ ኤርሚያስ አመልጋ የማነሳው ጥያቄ አዘል ሐሳብም ሦስቱን የኢኮኖሚ አመለካከቶች የሊበራል ነፃ ገበያን፣ የፖሊሲ ነፃ ገበያንና የልማታዊ መንግሥት ነፃ ገበያን መርሆች አንድ በአንድ ተንትነው ኢትዮጵያ ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ወደ የትኛው ብትጠጋ በፍጥነት ለማደግም ሆነ ዕድገቷ በሕዝቦቿ መካከልና በአካባቢያዊ ሥርጭት ረገድ የተስተካከለ እንደሚሆን እንዲያብራሩልን ነው፡፡

ለፕሮፌሰር ዓለማየሁ የማነሳው ሐሳብና የምጠይቃቸው ጥያቄ መንግሥት የኢትዮጵያ አየር መንገድን የመሰለ ውጤታማና ለሀብታሙ የኅብረተሰብ ክፍል አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅትን ቢያስተዳድር ይሻላል? ወይስ ለግል ባለሀብቶች በከፊል አስተላልፎ በሚያገኘው ሀብት የአዲስ አበባ ሕዝብ የሚጨናነቅበትን የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ቢያቀርብ ይሻላል?

መንግሥት ከአየር መንገዱ በሚያገኘው ዓመታዊ ፈሰስ እንደ የከተማ የሕዝብ ትራንስፖርትን የመሳሰሉ ለዝቅተኛው ኅብረተሰብ የሚቀርቡ አገልግሎቶችን የሚደጉም ቢሆን፣ በመሸጡ ከሚገኘው ጥቅምና በዓመታዊ ፈሰሱ መካከል ያለውን ጥቅምና ጉዳት ለክቶ መምረጥ ይቻላል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ትንግርታዊ ዕድገት ያመጣው እንደ ሌሎቹ የኢኮኖሚ ዘርፎች ሀብት ከደሃው ወደ ሀብታሙ ስለፈሰሰና የአየር መንገዱ አገልግሎት ተጠቃሚዎችም ብር የሞላቸው ምሳ አዲስ አበባ እራት ዱባይ፣ በማግሥቱ ሻንግሀይ ያደረጉ ሀብታሞች ስለሆኑ እንጂ፣ መንግሥት ታሪካዊ የሀብት መመጣጠን ኃላፊነቱን ቢወጣ ኖሮ ሌላው በመንግሥት የሚተዳደረው የከተማ አውቶቡስ መንገደኞች ረዥም ሠልፍ ይዘው እየተሰቃዩ አየር መንገዱ ትርፍ በትርፍ አይሆንም ነበር፡፡

የከተማ ትራንስፖርትን ለአብነት አነሳሁ እንጂ፣ ሰማንያ በመቶ ለሚሆነው የገጠር ሕዝብ በመንግሥት የሚሰጥ አገልግሎትን ወደ ጎን ትቶ በአየር መንገዱ ይዞታ ላይ ቢያተኩር ይሻላል ወይ? በገበያ ኢኮኖሚ ካፒታሊዝም ሳይቀር ታሪካዊ የመንግሥት ሥራዎች ናቸው የሚባሉትን መሠረተ ልማቶች የመገንባትና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ተቋማትን የመገንባት አቅሙን አሟጦ ተጠቅሞ በተረፈው ነው ወይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከግሉ እኩል ወደ አምራችነት ልማታዊ መንግሥት የተሸጋገረው?

አቶ ኤርሚያስ አመለካከት ልቅ ነፃ ገበያም ያልሆነ ወደ ልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚም በጣም ያላዘነበለ በፖሊሲና በዕቅድ የሚመራ የካፒታሊስት ኢኮኖሚ ግንባታን የሚደግፉ ይመስላል፡፡ ይህ ፖሊሲ በርካታ የዳበረ ኢኮኖሚ ያላቸው የካፒታሊስት አገሮች ፖሊሲ ሲሆን፣ በታዳጊ አገሮች ውስጥም ይሠራል ወይ የሚለው በጥያቄ መልክ ሊነሳ የሚችል ነው፡፡

ለአቶ ኤርሚያስ የማነሳው ጥያቄ ቢጂአይ የራያ ቢራን አክሲዮን ከፊት ገጽታ ዋጋው ሰባት እጥፍ የሚበልጥ የገበያ ዋጋ ሰጥቶ እንደገዛው ሳይሰሙ አልቀሩም፡፡ በሽንኩርትና በድንች የዕለት ተዕለት ግብይት የገበያ ማጣሪያ ዋጋ ፈጥሮ በተረጋጋ ሁኔታ መገበያየት ያቃተው ሃያ በመቶ ከሚሆነው የከተማ ኗሪ ውስጥ፣ እጅግ በጣም ጥቂቱን የገንዘብ ገበያ ተዋናይ በማድረግ አገሪቱን እናሳድጋለን? ወይስ እንደ ራያ ቢራ ሀብታችንን በሙሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጭ ኢንቨስተሮች አስረክበን ባዶ እጃችንን እንቀመጣለን? ኢትዮጵያውያን የሚያስቡት ስለዛሬ የውጭ ኢንቨስተሮች የሚያስቡት ከሃምሳና ከመቶ ዓመታት በኋላ ስለሚሆነው እንደሆነ የራያ ቢራ ፋብሪካ ጥሩ ምሳሌ ሊሆን አይችልም ወይ?

ከቃሊቲ እስከ ቢሾፍቱ ተኮልኩለው ለውጭ አገር ሸማች የኤክስፖርት ምርት የሚያመርቱ ባዕዳን ወይም የእነሱን ማረፊያ ውብ ሆቴሎች በአዲስ አበባ የሚገነቡ ኢንቨስተሮች፣ የላሊበላና የጂንካ የደንቢዶሎና የቀብሪደሃር ደሃ ኢትዮጵያዊን የኑሮ ደረጃን እንዴት ይለውጣሉ?

ከዓመት ዓመት በእንሰት በተከበቡ ጎጆ ቤቶች ውስጥ እንሰት እየተቀለቡ ከዓለም የዕድገት ደረጃና መገናኛ ተሰውረው ያሉ ሰማንያ በመቶ የሚሆኑ የደቡብ ሕዝቦችና ኮረብታ ላይ ከሰፈረው ቆጡ ወደ ሸለቆ ወርዶ የሚያርሰው የሰሜን ገበሬ ሕይወት፣ ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን ሕዝብ ቁጥር ይዘው ወደ ካፒታሊዝም መጓዝ ይቻላል ወይ?

የልማታዊ መንግሥት ቁጥር አንድ ተሟጋች ነኝ ይሉ የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ እንኳ የማታ ማታ ወደ ካፒታሊዝም መጓዝ የማይቀር ሲሆን፣ ጥያቄ የሚሆነው ወደ ካፒታሊዝም የምንገባው አጎንብሰን ነው ወይስ ቀና ብለን ነው ይሉ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚታየው ባህላዊና ዘመናዊ የምርት አደረጃጀት፣ እንዲሁም የሸማችነትና የአምራችነት አዋቂነት ተነስተው እርስዎ እንደሚያስቡት አሁን ወደ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ የምንገባው አጎንብሰን ነው ወይስ ቀና ብለን ነው?

የፕሮፌሰር ዓለማየሁም ሆነ የአቶ ኤርሚያስ አመለካከት ጽንፍ የያዘ አይመስለኝም፡፡ ሆኖም የመንግሥትና የግል የገበያ ኢኮኖሚና የልማታዊ መንግሥት ኢኮኖሚ በሚሉት ጎራዎች ቅንብር ላይ የተራራቀ አመለካከት ያላቸው ይመስላል፡፡

ኢኮኖሚስቶች በኢኮኖሚ ፍልስፍናዎች ላይ የተለያየ አመለካከት መያዛቸው አዲስ ነገር አይደለም፡፡ እንዲያውም ጤናማ አስተሳሰብ ነው፡፡ ከሁለቱ አመለካከቶች ቅንብር ውጪ ያለ አማራጭ ያለም አይመስለኝም፡፡ ዋናው ጥያቄ ሁለቱን በምን ዓይነት ቅንብር እናጣምር የሚል ስለሆነ፣ ሌሎች ኢኮኖሚስቶችም ስለሁለቱ ቅንብር ሰፋ አድርገው ቢጽፉ ለመንግሥት ትክክለኛውን አቅጣጫ ለመያዝና ለሕዝብም የመንግሥትን ስትራቴጂና ፖሊሲ ተረድቶ እንቅስቃሴውን በሚጠቅመው መንገድ እንዲገራ ይጠቅመዋል፡፡ ሸማቹና አምራቹ የመንግሥት ፖሊሲ ገበያውን እንዴት እንደሚገራው አውቀው መልካም አጋጣሚ ከሆነ ለመጠቀም፣ የሚጎዳቸው ከሆነም ጉዳቱን ለመቀነስ የራሳቸውን እንቅስቃሴ አስተካክለው ለመምረጥ ፖሊሲውን በራሳቸው ዕውቀትና በባለሙያ ትንታኔ መረዳት አለባቸው፡፡

ብዙ ጊዜ ፖሊሲዎች ለባለሙያዎች የወጡ እስከሚመስል ድረስ የግሉ ሴክተር አያነባቸውም፣ አያውቃቸውምም፡፡ አንዳንዴም ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች እርስ በርሳቸው ይቃረናሉ፡፡ ለምሳሌ የመንግሥት ግብርና መር ኢንዱስትሪያላይዜሽን መመርያ ላለፉት በርካታ ዓመታት ብሔራዊ ባንክ እንደ ዋነኛው ፖሊሲ ይዞ፣ የገበሬውን ቁጠባ ለሕንፃ መሥሪያ ወደ ከተማ ሲያፈስ ኖሯል፡፡ ደሃው ገበሬ አበዳሪ፣ ሀብታሙ ሕንፃ ሠሪ ተበዳሪ ሆነው ያለፉትን ሃያ ሰባት ዓመታት አሳልፈዋል፡፡

ስለዚህም ኢኮኖሚስቶች ነን የምንል ሰዎች የሁለቱን ምሁራን አመለካከት በመምሰልም ሆነ በመለየት ጽፈን ብንቀላቀላቸው፣ ፖሊሲ አውጪዎችንም ሆነ ሰፊውን ሕዝብ በሙያችን እናግዛለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...