Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊትን የማስቀጠል ኃላፊነት የሁሉም ኃይሎች ነው

ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊትን የማስቀጠል ኃላፊነት የሁሉም ኃይሎች ነው

ቀን:

በስመኘው አራጌ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ካለፉት 40 ዓመታት ወዲህ በሁለት ኃይሎች ተወጥሮ እየተላተመ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ በበርካታ የፖለቲካና የታሪክ ጸሐፊዎች ተደጋግሞ እንደሚገለጸው፣ እነዚህ ኃይሎች ኅብረ ብሔራዊ አስተሳሰቦችን የሚያራምዱና ብሔር ተኮር አስተሳሰቦችን የሚያቀነቅኑ ናቸው፡፡

የኅብረ ብሔራዊነት አስተሳሰብ የሚያራምዱ ኃይሎች ከዘመነ መሳፍንት ማለቂያ ወዲህ በተፈጠረችው ኢትዮጵያ የነበረው ጭቆና የመደብ እንጂ ብሔራዊ ጭቆና አልነበረም ብለው የሚያምኑ ሲሆን፣ ይህ የመደብ ጭቆና የተፈጠረው ራሱን ከሰሎሞናዊ ሥርወ መንግሥት ዘር ባስተሳሰረው የዘውድ አገዛዝ በኢትዮጵያ በተዘረጋው ፊውዳላዊ ሥርዓት በሁሉም ሕዝቦች ላይ ጭቆና፣ በደልና ግፍ በእኩል በመድረሱ ለውጥ ያስፈልጋል ብለው ትግል ሲያደርጉ የቆዩ ኃይሎች ናቸው፡፡

በዚህ ረገድ በቀድሞው የተማሪዎች እንቅስቃሴ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1960ዎቹ መጀመርያ ጀምሮ በተማሪው ይካሄድ በነበረው እንቅስቃሴ እንደነ ዮሐንስ አድማሱ ያሉት ገጣሚዎችና ጸሐፊዎች፣ ‹‹ኢትዮጵያን የሚያስፈልጋት አንድነቷን በልዩነቷ ቃኝቶ ልዩነትን በአንድነቷ አድምቆ የሚገነባ ማኅበረሰብ ነው፤›› የሚል አስተሳሰብ ያራምዱ እንደነበር የተማሪዎች ንቅናቄ ታሪክ ይነግረናል፡፡  

በሌላ ወገን ኢትዮጵያ የሚባለው ስም በኃይል የተጫነብን የአንድን ብሔር፣ ቋንቋ፣ ባህልና አስተሳሰብ ብቻ በኃይል አንድንቀበል ያደረገ ስለሆነ በኢትዮጵያ የብሔር ጭቆና ነበር ብለው የሚታገሉ ኃይሎች ናቸው፡፡ ይህንን አስተሳሰብ በዋናነት ያራምዱ የነበሩት ተማሪዎች እንደነ ዋለልኝ በኋላም መለስ ያቀነቀነው አስተሳሰብ እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል፡፡ ጨቋኝ ብሔር ካለተጨቋኝ ብሔር ሊኖር ስለማይችል በኢትዮጵያ ውስጥ የብሔር ጭቆና ያደርግ የነበረው ብሔር አማራ ነው ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ ይህ አስተሳሰብ አማርኛ ቋንቋ የመንግሥት ቋንቋ ከመሆኑ አንፃር እያደገ የመጣ አስተሳሰብ ከመሆኑ ውጪ፣ የአማራ ነገድ ከማናቸውም የኢትዮጵያ ሕዝብ በላይ መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር ዒላማ የሆነ አሳዛኝ ሕዝብ መሆኑ እውነታው ያስረዳል፡፡ በቀድሞው የተማሪዎች ንቅናቄ ተሳታፊ ከነበሩት ወጣቶች ውስጥ በሽግግሩ መንግሥት ጊዜ የትምህርት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኢብሳ ጉተማ ‹ማን ነው ኢትዮጵያዊ?› በሚል ርዕስ የጻፉትን ግጥም ያስታውሷል፡፡

በዚህም ሆነ በዚያ ሁለቱም አስተሳሰቦች በሕዝብ ውይይትና በመነጋገር ሳይሆን፣ አንዱ ሌላውን ተዋግቶና አጥፍቶ በመሣሪያ ኃይል የራሱን አስተሳሰብ ለማራመድ በተደረገው የትግል ሒደት፣ በዚህች አገር በአንድ አገር ሕዝቦች  መካከል መገዳደል ብዙ ሕይወትና ንብረት ጠፍቷል፡፡ አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ በማይነቃነቅ መሠረት ላይ መቆም አልቻለችም፡፡ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የብሔር ጭቆና በኢትዮጵያ አለ ብለው የታገሉ ኃይሎች በመሣሪያ አሸንፈው ላለፉት 27 ዓመታት ሕገ መንግሥት ቀርፀው፣ አዲስ ትውልድ ለመቅረፅና አዲሲቱን ኢትዮጵያ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ ለመመሥረት በሚል በብሔር ፖለቲካ በታቀፈ የብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ሲመሩ ቆይተዋል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ከሰኔ 24 እስከ ሰኔ 28 ቀን 1983 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተካሄደው የሽግግር ጉባዔ በፀደቀው ቻርተር ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ይህንኑ ሐሳብ በማጠናከር በአዋጅ ቁ1/1987 በወጣው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት ተጠናክሮ ላለፉት 27 ዓመታት ቀጥሏል፡፡

በቻርተሩም ሆነ በሕገ መንግሥቱ የሰፈሩት ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች መልካም ሊባሉ የሚችሉ ቢሆንም፣ በአገሪቱ የፌዴራል አወቃቀርና በአተገባበራቸው ላይ የኅብረ ብሔራዊ አስተሳሰብ በሚያራምዱ ኃይሎች ብዙም ተቀባይነት ያገኙ አልሆኑም፡፡ በሽግግሩ ወቅት ኅብረ ብሔራዊው የቀድመው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) በውስጡ ያሰባሰባቸውን ኅብረ ብሔራዊ አስተሳሰብ የነበራቸውን አባላቱን በትኖ፣ በሽግግሩ መንግሥት ምንም ውክልና ያልነበረውን አማራ ተወካይ ሆኖ ክልላዊ መንግሥት ሲያቋቋምም፣ በተለይ በአማራ ክልል ብዙም አመኔታ ያተረፈ ፓርቲ ለመሆን አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ከመሠረቱ አማራን ወክሎ ያልተነሳና እንደ ትግራዩ ሕወሓት በብሔር ፖለቲካ አባላቱ ያልተካኑ በመሆናቸው የአማራ ብሔርተኝነትን ካባ ሊደርብ አልቻለም፡፡

የብሔር አስተሳሰብ ላለፉት 27 ዓመታት በሕዝብ እንዲሰርፅ ቢደረግም፣ ቁርሾዎችን ለመቀነስ ካለመቻሉም በላይ በሕዝቦች መካከል አለመተማመን ፈጥሯል የሚሉ ወገኞች ያሉትን ያህል፣ ሥልጣን በጨበጡት የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች ደግሞ ለማናቸውም አለመረጋጋትና ለኢትዮጵያ የወደፊት ሥጋት የሆኑት የጠባብና የትምክህተኛ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ኃሎች ናቸው በማለት ሲከራከሩ ከርመዋል፡፡ በእነሱ አስተሳሰብ ጠባብ ተብሎ የተፈረጀው የኅብረተሰብ ክፍል ባለፉት ሥርዓቶች ተጨቁኖ ግፍና በደል ደርሶብናል ብሎ ስለሚያምን፣ ሌሎች አማራጮች ሁሉ ዘግቶ መገንጠል ብቻ የሚያራምድ ኃይል ነው ሲሉ ይኮንኑታል፡፡ ትምክህተኛው ብለው የሚፈርጁት የኅብረተሰብ ክፍል ደግሞ ሲወርድ ሲዋረድ በኢትዮጵያ በተፈራረቁት ገዥ መደቦች መጠቆሚያ ሆኖ የቆየ ከመሆኑም በላይ፣ የነበረውን ክብር ስምና ዝናን ለማስጠበቅ በኢትዮጵያ ስም ራሱን ሸብቦ ሌሎች አስተሳሰቦችን ለማስተናገድ የማይችልና አገሪቱን ለመበታተን አደጋ የሚያጋልጥ ኃይል ነው እያሉ ሲሰብኩ ኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታ ስናየው ኅብረ ብሔራዊም ሆነ ብሔር ተኮር አስተሳሰብ የሚያራምዱ ኃይሎች በአፈሙዝ የበላይነት ለመጨበጥ የቻሉና የሚያምኑ፣ ባለፉት 40 ዓመታት ሲያራምዱ የቆዩትን አስተሳሰብ በሕዝቡ ላይ የጫኑና ለመጫን የሚታትሩ እንጂ፣ አሁን ከተፈጠሩት አስተሳሰቦች አንፃር ለወደፊቷ ኢትዮጵያ አንዳችም መፍትሔ ሲያቀርቡ አይታይም፡፡ ሁለቱንም አስተሳሰቦች የሚያስተናገድ አዲስ አስተሳሰብ ማፍለቅና በዚህም ላይ መሟገት ለመጪዋ ኢትዮጵያ እጅግ አስፈላጊና ጠቃሚ ነው፡፡ አንዱን አስተሳሰብ ጥሎ ሌላውን ለማንሳት መሞከር ያለፉት 27 ዓመታት የተጓዝንበት መንገድ አያስችለንም ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ፡፡ ሁለቱንም አስተሳሰቦች አለማስተናገድ ኢትዮጵያን መፈረካከስ፣ እንዲሁም ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከማስደሰት ውጪ ለማናችንም እንደማይጠቅመን መገንዘብ  በእጅጉ ጠቃሚ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ የፖለቲካ ሥርዓት ማስፈለጉ አጠራጣሪ ሊሆን አይገባም፡፡ ነገር ግን ኅብረ ብሔራዊ አስተሳሰብ ለብዝኃነት ጠቃሚ አይሆንም በማለት ማጣጣልም ጠቃሚ አይደለም፡፡ ወደድንም ጠላንም የኢትዮጵያ ሕዝብ በደምና በሥጋ ብቻ ሳይሆን በጥቅም ተሳስሯል፡፡ ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ ለተፈጠረችው ኢትዮጵያ ሁሉም ሕዝብ የየራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ለክፉም ለደጉም የጋራ ኃላፊነት አለበት፡፡ ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ ለተፈጠረችው ኢትዮጵያ በግዛት መስፋፋት፣ በሥልጣን መሻኮትና በእኔ እበልጥ እኔ በሕዝቦች መካከል ከነበረው የመጠፋፋትና የመስፋፋት ታሪካችን ችግሮች አልተፈጠሩም ሊባል አይችልም፡፡ በሕዝቦች መካከል የነበረው ፍጅት ረገድ የወጡ መረጃዎች ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል ወጥተው ሊሆን ስለሚችል ሙሉ በሙሉ ለመቀበልም ያስቸግራል፡፡ ታሪክ ግን የሚያስተምረን የኢትዮጵያ ሕዝብ በክፉም በደጉም ያለፈበትን ታሪክ አልፎ የየራሱን አሻራ እየተወ አሁን ያለንበት ደረጃ ደርሰናል፡፡

የፖለቲካ ሥርዓታችንና የመንግሥት አወቃቀራችን ምን ቢሆን ነው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ማስቀጠል የሚቻለው? ለሚለው መፍትሔ ማፈላለግ የሁሉም ኃይሎች  ግዴታ ነው፡፡ ሁሉም ኃይሎች የፖለቲካውን ጨዋታ ወደ ጎን ትተው ወደ ልባቸው መመለስ አለባቸው፡፡ እርግጥ ሥልጣንና ገንዘብ ልብ እንደሚሰውር ባለፉት ዓመታት ከታየው ቅጥ ያጣ ስግብግብነት የተማርነው አለ፡፡  የየማኅበረሱ ልሂቃን ግን ከዚህ ወጥተው በአሁኑ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ልብ ለልብ ተቀራርበው ለፖለቲካ መሪዎቻችን ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ይገባቸዋል፡፡

አለመታደል ሆኖ የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ የመጠቃቀሚያ እንጂ፣ የአገርና የሕዝብ  የጋራ ተጠቃሚነትን ቀጣይነት የማረጋገጫ ማዕከል ሆኖ ማገልገሉ ሲዘነጋ ኖሯል፡፡ ለዚህ መጣጥፍ ጸሐፊ ሁልጊዜ የሚያሳስበው በቻርተሩ አንቀጽ ሁለት (ሐ) ላይ የሰፈረው ‹‹ብሔር ብሔረሰብና ሕዝቡ ከተጠቀሱት መብቶች ታገዱ፣ ተረገጡ፣ ወይም ተሸራረፉ ብሎ በሚልበት ጊዜ የራሱን ዕድል በራሱ እሰከ ነፃነት ድረስ የመወሰን መብት አለው፤›› የሚለውና  በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39/7/ ‹‹ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ ራሱን ዕድል በራሱ መወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማንኛውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው፤›› የሚሉት ናቸው፡፡ 

የዚህ መጣጥፍ ጸሐፊ በሕገ መንግሥቱ ላይ በአንድ ወቅት ሥልጠና ሲወስድ ይህ አባባል ለጽንፈኞች በር የሚከፈት፣ ማናቸውም ወገኖች ባኮረፉ ቁጥር እንገንጠል እያሉ ጥያቄ በማቅረብ መረጋጋት የሚነሳ ለአገር ሥጋት የሆነ አንቀጽ ነው የሚል ሥጋቱን ሲገልጽ፣ የተከበሩ ዶ/ር ፋሲል ናሆም በሰጡት መልስ በኢትዮጵያ መገንጠልን ተግባራዊ ማድረግ አንድ ሰው በአውሮፕላን ላይ 2,000 ከፍታ ጫማ እየበረረ ባለበት ጊዜ በመስኮት ዘሎ በሕይወት የመትረፍ ያህል ነው ብለው ነበር፡፡ ይህም በሬዲዮና በቴሌቪዥን መተላለፉን ያስታውሳል፡፡ ጊዜው በ1995  ዓ.ም. ይመስለኛል፡፡

የዚህ መጣጥፍ ጸሐፊ ገና ሥራ በጀመረበትና ወጣት በነበረበት ጊዜ በ1985 ዓ.ም. የአንዳርጋቸው ጽጌ ‹የአማራ ብሔርተኝነት ከየት ወዴት?› የሚለውን መጽሐፍ ባነበበት ጊዜ ጠባበ ብሎ የፈረጀበትን ሁኔታ ከአሁኑ ጋር ሲያስታውስ፣ ያ ሰው ከሁሉ ቀድሞ ያሰበ ነበር ለማለት ይቻላል፡፡ ከ27 ዓመታት በኋላ የተፈጠረው ትውልድ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን አመፅና በማኅበራዊ ድረ ገጾች የሚጻፉትን ጽሑፎች ስንመለከት፣ ይህች አገር ወዴት እያመራች እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ  ሕዝብ ብልህ ነው አይበታተንም፣ ኢትዮጵያ አትፈራርስም፡፡ በሚል በየዋህነት የምናልፈው ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሥልጣን ላይ የተቀመጠው የብሔር ፖለቲካ አራማጁ ኃይልም ወደ ልቡ ተመልሶ፣ በለውጥ ኃይሎች የቀረበለትን አማራጭ መቀበል ግድ ይለዋል፡፡ መሣሪያ እጃቸው የሚገባ ጽንፈኞችና ተጨቁነናል ብለው በሚያምኑ ታጋዮች በሚደረግ ትግል ሥልጣን እጁ ላይ በወደቀ ጊዜ በሚፈጠር ክፍተት፣ እንደማንኛውም ወገንተኛ ቡድን ለራሱ ወገኖች በሚያደርገው አድልኦና ወገናዊነት ኢትዮጵያ አደጋ ላይ መውደቋ አይቀሬ ነው፡፡

በሌላ ወገን በሕገ መንግሥቱ መሠረት ጭቆና ሊመጣብን ነው ብለው የመገንጠል ጥያቄ በሚያቀርቡና በሚገነጠለው ክልል ጥቅምና ፍላጎት አለን ሀብት ንብረት አፍርተናል፣ የሚያስተሳስረን ገመድ ሊበጠስ አይገባም፣ ቀድሞ በኢትዮጵያዊነት ባገኘነው መብትና ጥቅም ላይ ማናቸውም ሊያዝብን አይገባም በማለት በሚታገሉ ኃይሎች መካከል በሚነሳ ግጭት፣ ወደ ማያበራ የእርስ በርስ ጦርነት የማንገባበት ምክንያት  ሊኖር አይችልም፡፡  ኢትየጵያ የሚለውን አገር ስሙን መስማት የማይፈልጉ ወገኖች ባሉበት አገር፣ ኢትዮጵያ የሚለውን እንኳን ትተን የየራሳችን አገር እንመሥርት ብለን ብንነሳ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ትግሬ፣ አፋር፣ ሶማሌና ከደቡብም ክፍለ ግዛት ለመሆን የሚችሉ አገሮች ተፈጠሩ ብንል እንኳን ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከማስደሰት ውጪ እርስ በራሳችን ሰላም አግኝተን የየራሳችን አገር ፈጥረን ለመኖር በፍፁም አይቻለንም፡፡ በአማራና በኦሮሞ መካከል በወሰን የማይገናኙበት ድንበር የለም፡፡ በእነዚህ የኢትዮጵያ ምሰሶ በሆኑ ታላላቅ ሕዝቦች መካከል ለዘመናት በተዛባ መንገድ ሲነገር የኖረው ቁርሾ የማያገረሽበት ምክንያት የለም፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል ታሪክንና ወቅታዊ ሁኔታን አዛብተው በሚነግሩና በሚተርኩ አንገት አልባ ሰዎች ምክንያት፣ ውዝግብ የነበረ መሆኑና የመጣው ሥርዓት ሁሉ የእነሱን አለመግባባት ሲጠቀም መኖሩ የማይካድ ነው፡፡

በእነዚህ ሕዝቦች መካከል የነበራውን መልካም መስተጋብር ከእውነትና ከታሪክ ቆፍረን በመካከላቸው የእውነት መተማመን እስኪፈጠር ድረስ ጊዜ ያለን አይመስልም፡፡ ትግራይ ከአማራ ጋር  በብዙ  አቅጣጫ የሚዋሰን ከመሆኑም አንፃር፣  ባለፉት 27 ዓመታት በተፈጠረው ሥርዓት ይበልጥ ተጠቃሚ ነበር የሚሉና ቂም ያረገዙ ኃሎች እየተፈጠሩ ነው፡፡ አጎራባች አገሮች ሆነው ሲፈጠሩም ብዙ ፈተና ሊገጥመን ይችላል፡፡ ለጥቅምና ለድንበር ሲባል ወደማያባራ ጦርነት ልንገባ የማንችልበት ምክንያት የለም፡፡ ሕወሓትና ሻዕቢያ ይጣላሉ ብሎ ያሰበ ማን ነበረ? የሶማሌ ወንድሞቻችን አንድ ቋንቋና አንድ ሃይማኖት እየተናገሩና እያመኑ ለምን ወደ ማይወጡበት አዘቅት ውስጥ ገቡ? እኛ ሰዎች አይደለንም እንዴ? ስለዚህ ኅብረ ብሔራዊም ሆነ ብሔር ተኮር የፖለቲካ አራማጆች ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለማስቀጠል የሚፈልጉ ከሆነ፣ የመፍትሔ ሐሳቦችን በነፃ ፍላጎት ማንፀባረቅና ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሥልጣንና ገንዘብ ልቦናቸውን የሰወራቸው ኃይሎች ካልሆኑ በስተቀር፣ በመጪዋ ኢትዮጵያ ወገናችን ምን ሊገጥማቸው ይችላል ብለው ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው፡፡

በመጀመርያ ደረጃ ሥጋቱን ሁላችንም የምንጋራው መሆኑን በሠለጠነ መንገድ በውይይት ማዳበር አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህ መጣጥፍ  አቅራቢ እምነት መጪዋ ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊና ብሔራዊ አስተሳሰቦች በጋራ የሚስተናገዱባት አገር እንድትሆን ይመኛል፡፡ መፍትሔው  በሰላማዊም ይሁን በጦርነት ኢሕአዴግን ከሥልጣን ማስወገድ አይደለም፡፡ የኢሕአዴግ ድርጅቶች ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎ ሊወክሉ እንዳልቻሉ ባለፉት 27 ዓመታት ያሳለፍናቸው ሁነቶች ያስተምሩናል፡፡ ወደድንም ጠላንም በአብዛኛው ሕዝብ እምነትም ይሁን ውሸትም ይሁን ዕውነት፣ በመረጃ የተደገፈም ይሁን አይሁን የሕወሓት የበላይነት ባለፉት ዓመታት ተንሰራፍቶ ነበር የሚለው አስተሳሰብ በብዙ መንገድ ሲራመድ ቆይቷል፡፡ በርካታ መጫሚያ ያልነበራቸው  የሕወሓት ታጋዮች ማንባብና መጻፍ እንኳን ሳይችሉ፣ አሥር ከዚያ በላይ በትምህርትና በንግድ ዓለም ከቆየን ሰዎች ጋር ሲነፃፀሩ ልዩነት ማሳየታቸውን መካድ ለፖለቲካ ጨዋታ ካልሆነ በስተቀር ልቦናችን ያውቃል፡፡ በደም ያገኙት ነው ከተባለ በካሳ መልክ በግልጽና ተጠያቂነት ባለበት መንገድ መስጠት ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ይዘን በመቻቻል መቀጠልና ከዚህ በኋላ የአድልኦ ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሰላማዊ መንገድ ማቆም ግድ ይለናል፡፡

መፈራረጁና ፍጅቱ ከዘመነ መሳፍንት እስከ ምንሊክ የግዛት መስፋፋት የተደረገው ይበቃል፡፡ ዓድዋ በደምና በአጥንት አስተሳስሮናል፡፡ ጠባብነትና ትምክህት የሚሉት መርዛማ ቃላት በአሁኑ ጊዜ ስለማንሰማቸው ምን ይህል ዕፎይታ እንደሰጡን እንገነዘባለን፡፡ በኢሕአዴግ የውስጥ ትግል የፈለቀው የለውጥ ኃይል ከተጠመቀበት ብሔር ተኮር ፖለቲካ ወጣም አልወጣ፣ አሁን እያቀነቀነው ያለውን ኢትዮጵያዊነት ከልብ ወይስ ጊዜ መግዣ? ታላቁ የዘመናችን ሰው ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከቲም ለማ ወገን አስተሳሰቡን የሚያራምድለት፣ በእሱና ከእሱ ዕድሜ በኋላ ባሉ ትውልዶች ተበራክተዋል የሚሉት ጽንሰ ሐሳቦች ወደፊት የሚታዩ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የማስቀጠል ኃላፊነት የሁሉም ኃይሎች ኃላፊነት ነው፡፡ በመሆኑም  አማራጭ ሐሳቦችን በማቅረብ አሁን የተጋረጠብንን አደጋ ልንታደገው ይገባል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ዓላማ ዕውን የሚሆነው ‹‹በጋለ ጭብጨባ› ብቻ ሳይሆን በሕግና በፖሊሲ መሆኑን ማመን ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...