Thursday, July 25, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አረንጓዴው ዓብይ አብዮት እንዴት?

የሥራ መስኮች የሚፈጠሩበት የፕሮጀክት ሐሳብ በአጭሩ ሲብራራ

በበኃይሉ ዘውገ ቦጂያ

ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ዕትም 601,000  የሥራ መስኮች የሚፈጥርበት የፕሮጀክት ሐሳቤ ‹‹ማሳሰቢያ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር›› በሚል ርዕስ ታትሞ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ የጋዜጣ ክፍሉ ጽሑፌን ተቀብሎ ማቅረቡን ከምሥጋና ጋር የምጠቅሰው ቢሆንም ‹‹ማሳሰቢያ›› በሚል አርዕስት ሥር መቅረቡ ቅር አሰኝቶኛል፡፡ ለጉዳዩ ትኩረት ለመስጠት በቅንነት የተደረገ መስሎ የታየኝ ስለሆነ፣ የእኔን ጽሑፍና ስሜን ጠቅሶ በሚታይ ርዕስ ላይ የሚገኝ ግድፈት በመሆኑ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እጠይቃላሁ፡፡ ለነገሩ ጉዳዩን ወደ ጋዜጣ ክፍሉ ለመላክ የተገደድኩበት ምክንያት ሐሳቤን ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ለማድረስ የነበሩ ዘመናዊ መንገዶች አልሠራም ስላሉኝ ነው፡፡ ምናልባት ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ድጋፋቸውንና ምክራቸውን ለመለገስ የፈለጉ ዜጎች ሁሉ ይህ ችግር በወቅቱ ሳያጋጥማቸው አይቀርም ብዬ እገምታለሁ፡፡

 ወደ ጉዳዩ ስመለስ ግንቦት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በወጣው የሪፖርተር ዕትም 601,000 የሥራ መስኮች መስኮች የሚፈጠሩበትን አጭር አስተያየቴን፣ በተለይም በገጠሩ የአገራችን አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ፈጠራ ዕድል የሚጠቅስ በመሆኑ ጽሑፉ በመስኩ ውስጥ በመሥራት የሚገኙትን ባለሙያዎችን፣ በልዩ ልዩ መስክ በመሥራት ላይ የሚገኙ ምሁራንን፣ የአገር ወዳድ ዜጎችን ትኩራት አግኝቶ በአያሌ የኢሜይል መልዕክት፣ የስልክ ጥሪዎች እንዲሁም በአካል በቢሮዬ በመገኘት ስለጉዳዩ ለመረዳት መፈለጋቸውን ተገንዝያአለሁ፡፡ የሁሉም ዋነኛው ትኩረት በጥቅሉ ይኼን ያህል ሥራ ሊፈጥር የሚያስችለውን ሁኔታ በቅርበት ለመረዳት የመፈለግ ዝንባሌ ነው፡፡ ለእዚህ የነበረኝ አጭሩ መልሴ 601,000 የሥራ ቦታ በጋዜጣው ላይ በሚቀርብ አስተያየት የተገለጸ  እንጂ፣ በዚህ ፕሮጀክት መነሻነት እጥፍ የሆነ የሰው ኃይል ሥራ መፍጠር እንደሚቻል ማስረዳት ነበር፡፡ ነገሩን ለመረዳት ከመጡት አንድ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ምሁር በቢሮዬ ከተገኙ በኋላ፣ ጉዳዩን በዝርዝር ተረድተው በመጨረሻ የተናገሩት ቃል  ‹‹አረንጓዴው ዓብይ አብዮት ሊመጣ ነው ይበሉኛ!›› ነበር ያሉት፡፡

ከፍተኛ ምሥጋና ይሁንላቸውና እኔም ለጽሑፌ በእዚህ አጋጣሚ ትክክለኛውን ርዕስ አገኘሁለት ብዬ ከላይ ተጠቅሜበታለሁ፡፡ ሌላው ከእኚህ ሰው የተረዳሁት ሁሉም ሊረዳው በሚችልበት ሁኔታ ይኼንን ሐሳብ ማራመድና ማሳወቅ እንዳለብኝ ነው፡፡ በዚሁ መሠራት ‹‹601,000›› የሥራ ቦታ የሚፈጠርበት የፕሮጀክት ሐሳብ ቀመር ባለፈው ጽሑፌ ሲጠቀስ፣ በአገሪቱ ‹‹የእንስሳትና ዓሣ ዘርፍ የማዘመን የለውጥ እንቅስቃሴ›› ትኩረት እንዲያገኝ በቂ ግንዛቤ በሁሉም አካባቢ እንዲኖር መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ መጀመር፣ ይኼንን ዘርፍ የሚመለከት በአዲስ ቅኝት ስትራቴጂካዊ ፕላን እንዲዘጋጅ በአስቸኳይ ማስደረግ፣ የሚዘጋጀው ስትራቴጂካዊ ፕላን የባለድርሻ ፍላጎት ያካተተ ሆኖ፣ በአገሪቱ የአሁኑ የዕድገት ፍላጎት አንፃር ማየት፣ የሚዘጋጀውን ስትራቴጂካዊ ፕላን መሠረት በማድረግ በአገሪቱ ውስጥ ለሁሉም የእንስሳት ዓይነት መኖ የሚያቀነባብሩ በመንግሥትና በባለሀብቶች የጋራ ትብብር የሚመሠረቱ ትልልቅ ፋብሪካዎችን ማቋቋም፣ ይኼንን መኖ ተጠቅሞ ወደ ሥራ ሊገቡ የሚችሉ ክፍሎችን ሁሉ ትልልቅ ፋብሪካዎች፣ መካከለኛ ፋብሪካዎች፣ አነስተኛ ፋብሪካዎች፣ ጥቃቅን አምራቾችና እንዲሁም በትርፍ ጊዜያቸው ከብቶችንና ዶሮዎችን የሚንከባከቡ ዜጎችን አቅም፣ ዕውቀት፣ ክህሎትና የገቢያ ትስስር ሊያሳድጉ የሚችሉ የቀጥታ ትምህርቶችን፣ ኮርሶችን፣ ሥልጠናዎችን እንዲሁም ሠርቶ ማሳያ ጣቢያዎችን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ማቋቋም፣ በአነስተኛ ሥፍራ ዘመናዊ የግጦሽ ልማት የማከናወን ዘዴ ሥልጠናዎችን ማከናወን፣ በዚህ መስክ የተሠማሩትን መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተገቢውን ድጋፍ እንዲሰጡ የሚያስችላቸውን አቅም እንዲያጎለብቱ መርዳት፣ ይህ ዘርፍ የተፋጠነ ለውጥ እንዲያስመዘግብ አስቻይና አጠናካሪ የሆኑ የሕግ ድጋፎችን የሚያስገኙ ሕጎችና ደንቦች እንዲቀረፁ ማስደረግና ለምሳሌ የቀረጥ፣ የውጭ ንግድ ድጋፍ ወዘተ. . . ባለፈው ጽሑፌ ላይ የተጠቀሱ ጉዳዮች ነበሩ፡፡

በዚህ መሠረት ከላይ የቀረበው ሐሳብ በተሟላበት አኳኋን ይኼ መስክ ያለውን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ተግባራዊ ለማድረግ፣ በአዲሱ የለውጥ ዕይታ ረገድ ካሉት የአተገባበር ሥልቶች ውስጥ አንዱ አማራጭ ሆኖ ሊሠራበት የሚገባውን ‹‹የከብቶች እርባታን›› ብቻ በምሳሌነት ወስደን፣ የአገራችን የከብቶች አረባብ ሥርጭት ባማከለ ሁኔታ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ብንወስን የሚከተለውን ዘዴ መከተል እንችላለን፡፡

  በሰነድነት ካለው መረጃ አንፃር የቆየ ቢሆንም፣ እ.ኤ.አ በ20112/2013 ወይም በ2005 ዓ.ም. በአገራችን በጥናት ተተንትኖ በቀረበ መረጃ መሠረት፣ 745,478,53 ከብቶች መኖራቸውንና ይኼም በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ተሠራጭተው እንደሚገኙ ያሳያል፡፡ ይህ የከብቶች ቁጥር በግልጽ የሚያመለክተው አገራችን ኢትዮጵያ ለከብቶች እርባታ የተመቸች አገር መሆንዋ ብቻ ሳይሆን፣ ለከብቶች እርባታ አስፈላጊ ሁኔታዎች ውኃ፣ የግጦሽ ሳር ወዘተ. . . በበቂ ሁኔታ መኖሩ፣ ከከብቶች በእጅጉ ተጠቃሚ የሆነ ቁጥሩ የበዛ ሕዝብ መኖሩ፣ ከብቶችን ለመንከባከብ ልምዱ በበቂ ሁኔታ መኖሩ፣ በዚህ መስክሰ አያሌ ችግሮች ያሉ ቢሆንም፣ ልምዶችም በዚያው ልክ ዳብረው ያሉ መሆኑንና ይህ መስክ ትልቁ አገራችን በከፍተኛ ደራጃ ብልጫዋን ያስመዘገበችበትና ጥሩ ስምም ያገኘንበት መሆኑ ናቸው፡፡

ከእዚህ እውነታዎችና እንዲሁም በእዚህ መስክ ከሚገኙ ማገናዘቢያ ጉዳዮች በመነሳት ወደ ፊት ይኼ የባህላዊ ዘዴ አረባብ አያሌ ችግሮች ውስጥ ሆኖ ይኼን ያህል ከፍተኛ ውጤት ካስገኘ፣ በዘመናዊ መንገድ ቢሠራና ለአገሪቱ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ሆኖ እንዲያገለግል፣ ለዜጎችም የሥራ መስክ ፈጣሪ ሆኖ ወደ ዘመናዊ አመራረት እንዲቀየር ቢታቀድና ተግባራዊ ቢደረግ፣ በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የአረንጓዴ ለውጥ ያስገኛል የሚል ጥብቅ እምነት አለ፡፡

በዚህ እምነት ላይ በመመርኮዝ ሥራዎች ቢታቀዱ፣ ለምሳሌ ያህል በሚከተለው ሁኔታ ፕሮጀክቱን በመላው የአገራችን ክፍሎች በሰፊው ማስጀመር ይቻላል፡፡

ለመነሻ ከላይ የጠቀስነው በአገራችን በሚገኙ የከብቶች ቁጥር አንፃር 74,547,853 ወስደን በእያዳንዱ 1,200 ከብቶች ባሉበት ሥፍራ ሁሉ አንድ ዘመናዊ የከብት እርባታ ፕሮጀክት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንዲኖር ፕሮጀክት ብንቀርፅ፣ የምናገኘው የክብት እርባታ ፕሮጀክቶች ቁጥር 62,123 ይሆናሉ፡፡ የእነዚህ ፕሮጀክቶች ይዘት ምን ይሆናል ብለን መልሱን በአንድ ፕሮጀክት ውስጥ አግኝተን፣ ከዚያ 62,123 ፕሮጀክቶች እንደ አካባቢው ሁኔታ ልዩነቶችን በማገናዘብ እንዲቀረፁና እንዲከናወኑ ለማድረግ እንድንችል በመጀመርያ አንዱ ፕሮጀክት ምን ሊመስል እንደሚችል በቅርበት እናያለን፡፡

አንዱ ፕሮጀክት አምስት ሔክታር ስፋት ያለው መሬት የሚያስፈልገው ሆኖ በውስጡ ፋርም ሐውስ፣ ከብቶች፣ በረት፣ አጥርና መኖ ማዘጋጃ ቤት፣ ውኃ ማጠራቀሚያ፣ የእርሻ ማሠርያዎች፣ አነስተኛ ጎተራ፣ ከብቶች ማዋያ ወዘተ. . .  የሚኖሩት ይሆናል፡፡ ይኼ ፕሮጀክት ላሞች፣ ጊደሮች፣ ኮርማዎች፣ ወተት፣ ቅቤና አይብ፣ ወዘተ. . . የሚያመርት ሲሆን፣ በገቢ በኩል ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ ሲገመገም በትንሹ 30 በመቶ አዋጭነት ያለው ነው፡፡ ለዚህ አንድ ፕሮጀክት የሚያስፈልገው የሰው ኃይል 12 ሠራተኞች ሲሆኑ፣ በዝርዝር ሲጠቀሱ የፕሮጀክቱ ኃላፊ፣ ሒሳብ ሠራተኛ፣ ግምጃ ቤት ሠራተኛ፣ ሁለት የሽያጭ ሠራተኞችና በፕሮጀክቱ ላይ የሚሠሩ ሰባት ፋርም ሠራተኞች ኛቸው፡፡   

 እነዚህና ሌሎችም አነስተኛ ተጨማሪ ነገሮች በዝርዝር ሲታሰቡ የፕሮጀክቱ የመጀመርያ ወጪ በቀረበ ግምት 18,000,00 ብር ይሆናል፡፡ ለአንድ ፕሮጀክት ይኼንን ያህል ካስፈለገ ለ62,123 ፕሮጀክቶች ምን ያህል ያስፈልጋል? ሲባል 111,821,400,000 ብር ይሆናል፡፡ ይኼንን ብር ወደ ዶላር ብንለውጠው ወደ 3‚993‚621‚428 ዶላር  ይሆናል፡፡ ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ገደማ ማለት ነው፡፡

አንድ ፕሮጀክት 12 ሰዎች የሚያስፈልገው ከሆነ 62,123 ፕሮጀክቶች 74,5476 ሠራተኞች ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ እንግዲህ በፕሮጀክቱ ሳይት የሚገኝ የሰው ኃይል ነው፡፡ በሰው ኃይል ውስጣዊና ውጪያዊ የሥራ መፍጠር አቅም አንፃር በዚህ መስክ ያሉ ፕሮጀክቶች ሲገመገሙ፣ የአንድ ፕሮጀክት የሥራ ፈጠራ አቅም 64 በመቶ ሲሆን፣ 35 በመቶ ፕሮጀክቱ በተዘዋዋሪ ሥራ የመፍጠር አቅም እንደሚኖረው ይታመናል፡፡ በእዚህ መሠራት ይኼንን ማዕ     ቀፍ ይዘን እየተነጋገርንላቸው ያሉ ፕሮጀክቶችን ስንገመግም 745,476 የሥራ መስኮች ከመፍጠር ባሻገር 43,4861 በተዘዋዋሪ ሁኔታ የሚፈጠሩ ሥራዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ፣ በጠቅላላው 1,180,337 የሥራ ቦታዎች በዚህ ፕሮጀክት መነሻነት ሊፈጠሩ እንደሚችሉ እንገነዘባለን፡፡  

በሌላ በኩል ይህ የፕሮጀክት ሐሳብ በተጓዳኝ የሚፈጥረው የሥራ መስክ አለ፡፡ ይኼውም ፕሮጀክቱ ፋርም ሐውስ፣ በረት፣ አጥር፣ መኖ ማዘጋጃ ቤት፣ ውኃ ማጠራቀሚያ፣ የእርሻ መሳሪያዎች፣ አነስተኛ ጎተራ፣ የከብቶች ማዋያ ያስፈልጉታል ብለናል፡፡ በእነዚህ ሥራዎች የሠለጠኑ ወጣቶች በአነስተኛ የማምረቻ ማኅበራት  ተደራጅተው ይኼንን ሥራ በኮንትራት እንዲሠሩ ስለሚጠበቅ፣ ከእዚህ አንፃር ከፍተኛ ሥራ ይፈጠራል፡፡ በሌላ በኩል የዚህ ፕሮጀክት ስኬታማ የኢንዱስትሪ ዕድገትን ያስከትላል፡፡ እነዚህን ፕሮጀክቶች ለማከም የተፈጠረውን የመገንባት፣ የፕሮጀክት ማከሚያ ግብዓቶች በመጠቀም አያሌ መሰል የግል ፕሮጀክቶች በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንዲስፋፉ መንገድ ይከፍታል፡፡ በተለይም ይኼንን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ለመጠቀም በትንሹ በብዙ እጥፍ ኢንቨስተሮች ከብት ነክ መሰል የግል ፕሮጀክቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ በእርግጠኝነት ለመናገር የሚያስችል ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ምክንያቶች በበቂ ሁኔታ አሉ፡፡ አንዱ ሠርቶ ውጤታማ የሆነበትን ተከትሎ የመሥራት ልምድ በአገራችን በሰፊው ያለ መሆኑን በማጤን የተጠቀሰ ነው፡፡

በእዚህ ዓይነት በተፈጠሩ ፕሮጀክቶች ምርትና ውጤት ላይ በመመሥረት የሚስፋፉ ኢንዱስትሪዎችን በስፋት የማስገኘት ዕድሉ አለ፡፡ የሥጋ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ የቆዳ ማዘጋጃ፣ የወተት ምርት ማቀነባበሪያ፣ የዘመናዊ ቅቤ ማቀነባበሪያ፣ የአይብ ማቀነባበሪያ ድርጅቶች፣ የፎርማጆ መሥሪያ፣ በአገር ውስጥ አከፋፋይ ድርጅቶች፣ ወደ ውጭ ላኪ ድርጅቶች፣ ወዘተ. ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

ለፕሮጀክቱ መሳካት ከሚያስፈልጉ ነገሮች ጥቂቶቹ፣ ለእዚሁ ሥራ የተመደበ ፕሮጀክት አስፈጻሚና ክትትል አካል፣ ለዚሁ ሥራ በባንኮች የጋራ ትብብር የተቋቋመ ብድር ሰጪ ባንኮች፣ ለእዚሁ ሥራ በባንኮች የጋራ ትብብር የተቋቋመ ብድር አስመላሽ አካላት፣ ለዚሁ ሥራ የጋራ ትብብር የተቋቋሙ የቴክኒክ ቡድኖች፣ ለዚሁ ሥራ የጋራ ትብብር የተቋቋመ የትምህርት ምክርና ሥልጠና አካላት፣ ለዚሁ ሥራ የጋራ ትብብር የተቋቋመ ጤና ነክ ተመልካች አካላት፣ በመንግሥትና በዕርዳታ ድርጅቶች በነፃ ለፕሮጀክቶቹ የሚቀርቡ የተዳቀሉ የከብት ዝርያዎች (ቁልፍ ወሳኝነት አለው)፣ በፕሮጀክቱ በቅርበት የሚሰጥ ቴክኒካዊና ወደ ዘመናዊ አመራረት አሸጋጋሪ ድጋፎች (ቁልፍ ወሳኝነት አላቸው)፡፡

 በሁሉም ከብቶች በባህላዊ ዘዴ በመራባት በሚገኙ ዋና ዋና ሥፍራዎች የፕሮጀክቱ ሥራ የሚከናወኑባቸው ይሆናል፡፡ ከእነዚህ ሥፍራዎች አንፃር በከፍተኛ ደረጃ የአዋጭነት ጥናቶች በጥንቃቄ ይዘጋጃሉ፡፡ በእዚህ ፕሮጀክት ውስጥ የሚከተለው ታሳቢ ሊደረግ ይችላል፡፡ በመጀመርያው ዙር በአገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ ጠቅላላ ፕሮጀክቶች 62,123 ናቸው ብለናል፡፡ በዚሁ መሠረት በመጀመርያው ዙር እነዚህ ፕሮጀክቶች በ62,123 ገበሬዎች በባለቤትነት እንዲጀምሩ ይደረጋል፡፡ በሦስት ዓመት ውስጥ መጀመሪያ ከተበደሩ ገበሬዎች በተከፈለ ብድር ላይ ተመርኩዞ፣ ሌሎች 62,123 ገበሬዎች ይኼንን ዕድል በሁለተኛ ዙር ያገኛሉ ተብሎ ተገምቷል፡፡ ለመጀመር ያህል በሥራቸው የተመሠገኑ ገበሬዎች በዕጣ ዕድሉ እንዲደርሳቸው ማድረግ አንዱ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡ የመሬት ጥበት ባለበት ሥፍራ ለምሳሌ ጥጃዎችን ሊያስገኝ በሚችሉ ሥራዎች ስፔሻላይዝ አድርገው ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት መንገድ መከተልም በዚህ ሥራ ውስጥ ጠቀሜታ የሚያስገኝ ሐሳብ ይሆናል፡፡ ገበሬው አልያም ገበሬዋ ብድሩ 180,000 በስሙ ከተያዘ በኋላ ፋርም ሐውስ፣ በረት፣ አጥር፣ መኖ ማዘጋጃ ቤት፣ ውኃ ማጠራቀሚያ፣ የእርሻ መሣሪያዎች፣ አነስተኛ ጎተራ፣ ከብቶች ማዋያ ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ለእዚሁ ሥራ በሠለጠኑ ወጣቶች ተሠርቶ ሒሳቡ ከሒሳባቸው ላይ ተቀናሽ ይደረጋል፡፡ ሙያውን እንዲያውቀው እንድታውቅ የሚያደርገው ዕውቀት በሠርቶ ማሳየት ግብረ ኃይል በሥራ በተደገፈ ሁኔታ በቅርበት በፕሮጀክቱ ሥፍራ ይሰጣል፡፡ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ መሆኑን የዕለት ተዕለት የሙያ ድጋፍ ይደረጋል፡፡ የዘመናዊ ከብት አያያዝ ሥርዓቶች ማከናወኛ ዘዴዎች ሁሉ ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡ ገበሬው አልያም ገበሬዋ ከሒሳብ የሚቀነስ መሣሪያዎችን ከአገር ውስጥም ከውጭም ከቀረጥ ነፃ ያገኛሉ፡፡ የተሰጠው ብድር ላይ መዋሉና ለሚቀጥለው ተረኛ ገበሬዎች ዕድሉን በተከታታይነት እንዲያገኙ ቅርበትና ድጋፍ የታከለበት የብድር መመለስ ቁጥጥር ይደረጋል፡፡

የፕሮጀክቱ የገንዘብ ምንጭ ስናስብ ይኼንን ፕሮጀክት አያሌ ክፍሎች ሊረዱትና ገንዘብ ያቀርቡለታል በሚል በሚከተሉት ምክንያቶች ከፍተኛ እምነት አለ፡፡ የአገራችንን የከብት ልማት ያዘምናል፣ የምግብ ዋስትና ይፈጥራል፣ የአገሪቱን ገበያ ያረጋጋል፣ የውጭ ንግድ ያሳድጋል፡፡ በተለይም በቅርበት ለሚገኙ አፍሪካ አገሮች ምግብ የማቅረብ ሰፊ ዕድል አለው፡፡ ድህነትን ለመቀነስ የጎላ ሚና አለው፡፡ የዜጎች መሰደድ ለመቀነስ ይረዳል ወዘተ. . . ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች በተገቢው መሠረት ደረጃውን ጠብቆ የፕሮጀክት ሰነድ ቢዘጋጅለት፣ የሚከተሉት ውስጣዊና ውጫዊ አካላት ለዚህ ተግባር ፋይናንስ ሊያቀርቡ ዕድሉ አለ ተብሎ ይታመናል፡፡ እነዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በድህነት ቅነሳ ላይ የሚሠሩ ተቋማት፣ የዓለም ባንክ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ፣ ዕድገት መርህ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ተቋማት፣ ቻይናና አሜሪካ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ወዘተ. . . ከእነዚህ ድርጅቶች አንዳንዶቹ እንኳን ለዚህ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ላለው ፕሮጀክት ቀርቶ ‹‹ለመመገብ›› ፕሮጀክቶች የትየለሌ ሚሊዮን ዶላር ብድር ያቀረቡልን፣ አንድም ገበሬ በመለወጥ ላይ ያነጣጠረና በከብቶች ስም ብቻ ለሚጠራ ፕሮጀክት እንደዚሁ አያሌ ሚሊዮን ዶላር የሰጡን ስለሆነ፣ ሠርተን ለመመለስ መልሰን በቋሚነት ለምናድግበት ጉዳይ ሙሉ ድጋፋቸውን እንደማይከለክሉን አያጠራጥርም፡፡

በመጨረሻ ይህችን አንዲት ቀልድ ጨምሬ ወደ ድምዳሜው ልምጣ፡፡ ሰውዬው ጫማ ለመግዛት ፈልጎ ጫማው ይገኝበታል ብሎ ወዳሰበው መደብር ይሄዳል፡፡ ነገር ግን እንዳሰበው ሳይሆን ጫማ የለንም ይሉታል፡፡ በጣም ይገርመውና ‹‹እሺ ቆዳ አላችሁ?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ‹‹አለን›› ይሉታል፡፡ ‹‹የጫማ ሶል አላችሁ?›› ብሎ ይጠይቃል ‹‹አለን›› ይሉታል፡፡ ‹‹ማጣበቂያ አላችሁ?›› ብሎ ይጠይቃል ‹‹አለን›› ይሉታል፡፡ ‹‹ክር አላችሁ?›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ ‹‹አለን›› ይሉታል፡፡ ‹‹እናንተ ሰዎች በፈጠራችሁ ጫማ የማይኖራችሁ ለምንድነው?›› አላቸው ይባላል፡፡ ነገሩን ወደ እኛው እንመልስና በቂ መሬት አለን፣ በቂ ውኃ አለን፣ በቂ ለከብቶች አመቺ የአየር ንብረት አለን፣ በቂ ሊባል የሚችል አጋዥ ባለሙያዎች አለን፣ ታዲያ አንድ የሚጎድለንን የገንዘብ አቅም መንገዱን ፈልገን የጎደለንን አሟልተን የአፍሪካ ሆላንድ የማንሆንበት ምክንያት ምን አለ? ወጣቶቻችንስ በአፍሪካ ብሎም በዓለም ድንቅ ዘመናዊ አምራቾች የማናደርግበት ምክንያት ምን አለን? በከተማ የሚገኙ ወገኖቻችንስ ከምግብ ዋጋ ግሽበት አዙሪት ማዳን እየቻልን የማናደርግበት ምክንያት ምን አለን? ተስፋችን ተፈጥሯል! ትኩረቱን እንሻለን! እንችላለን! በእዚህ አቅጣጫ የተጠናቀረና የተዘጋጀ ፕሮጀክት ለአገራችን ከፍተኛ ተስፋ የሚሰጥና የተጀመረውን ለውጥ በተግባር አጋዥ ይሆናል የሚል ጥብቅ እምነት አለኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው ሲኒየር ኮንሰልታንት፣ የፎከስ ቢዝነስና ኮንሰልቲንግ ግሩፕ የግል ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የቀድሞ የጀርመን ተመላሾች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አሶሼት ኮንሰልታንት ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles