Thursday, July 25, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያና የኤርትራ ተመሳሳይ ቅርሶች

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ባህል ሰዎች በአንዱ ወይም በሌላ ራሳቸውን የሚገልጹበት ወይም የሚያሳውቁበት ባህሪያቸውን፣ ልምዳቸውን፣ ተሞክሯቸውንና ግንዛቤያቸውን የሚያጠቃልል ነው፡፡ ባህል ከዚህም በተጨማሪ የሰው ልጅ ለመኖር ከተፈጥሮ ጋር ያደረገውንና የሚያደርገውን ትግል፣ እምነቱን፣ በተሞክሮ ያገኛቸውን፣ አመለካከቱን፣ ፀባዩን፣ ምርቱንና የአመራረት ሥልቱን፣ እንደ ማኅበራዊ ህልው ፍጡር ፍላጎቱን ዕውን ለማድረግ የሚጠቀምባቸውን ወዘተ. . . በሌላ አገላለጽ አንድ ሰው ወይም ሕዝብ ያሳለፈው የታሪክ ሒደት፣ እሴቶቹ፣ ልጆቹ፣ እምነቶቹ፣ ሞራሉ፣ ዓለማዊ ዕይታው፣ በአጭሩ እንደ ኅብረተሰብ አባል ሆኖ ያካበታቸው ወይም ያገኛቸው ሁሉ በባህል ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ ይልቁንም ከጥንት ጀምሮ የወረሳቸውና እንደ ሁኔታውም በታሪክ ሒደት እየቀየረ ያዳበራቸው የባህል ቅርሶች፣ ለአያሌ ዘመናት ተቀራርቦና ተሳስቦ እንዲኖር አድርገውታል፡፡ ይሁንና ባህልና የባህል እሴቶችን በሚገባ ለልማት ማዋል አስፈላጊነት የታወቀ ቢሆንም፣ በዚህ ረገድ የሚደረገው ጥረት በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በዚህ ጥናታዊ ጽሑፍ ውስጥ የጋራ ባህሎችና የጋራ የቅርሶች ባህላዊ የጋራ ቅርሶቻችን የትኞቹ ናቸው ይተነተናል።

የኢትዮጵያና የኤርትራ ተመሳሳይ የጋራ ባህሎችና የጋራ ቅርሶቻችን

በኢትዮጵያና በኤርትራ በተለይም ሕዝብ የእምነት ልዩነት ሳያደርግ (የኦሪት፣ የክርስትናና የእስልምና እምነት ተከታይ) በአንድ ላይ የሚያከብራቸው በዓላት እንደ ነበሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ ፈጣሪ ዝናብን፣ ጎርፍን፣ በረዶን አስወግዶ ፀሐይ የፈነጠቀበት የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል ወይም እንቁጣጣሽ፣ የዘራው ሰብልና በተፈጥሮ በክረምት ወራት የበቀሉ ተክሎችና ፍራፍሬዎች ለመበላት በመድረሳቸው ፈጣሪውን ችቦ ለኩሶ የሚያመሰግንበት የደመና ሳምንት፣ የእሸት ወር አልፎ የመኽር እህሉን ሰብስቦ በማስገባቱ በገና ጨዋታ፣ በልጎሽ፣ በሙሻሙሾ፣ በጅዋጅዌ ጨዋታ የሚያከብረው የመኽር ወር፣ የፀሐይን ወር የሚያቀዘቅዝ ደመናና ዝናብ እንደመጣ ወደ ፈጣሪው ልመና የሚያቀርብበት የግንቦት ወር፣ ፈጣሪ ልመናውን ሰምቶለት በሰኔ፣ በሐምሌና በነሐሴ ወራት ዝናብ አዝንቦ አዝርዕት በመብቀላቸው ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት የሻደይ ወር በዓል፣ ከጥንታዊ መልካው በተለየ ሁኔታ የአንድ እምነት ተከታይ በዓላት መሆናቸውን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ አስፈላጊ ነው፡፡

አንድ የጋራ ባህል በጋራ መበልፀግ፣ የጋራ አብሮነት መገለጫ መሆን፣ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ የአንድ ሃይማኖት ባህላዊ እሴት የመሆኑ ጉዳይ ምን ያህል እንደጠቀመና እንደጎዳ ለማወቅ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጥንታዊው ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ ወደ ጋራዎች እየወጣ መስዋዕት እያቀረበ፣ በፍል ውኃዎች እየታጠበ ወይም ተጠመቀ፣ በትልልቅ ዛፎች እየተቀመጠ ፈጣሪውን ከሕመም እንዲፈውሰው እየለመነ፣ መስዋዕት እያቀረበ ሲጠቀም እንደነበር ይታወቃል፡፡

ከትውልድ ትውልድ በአፍ ሲተላለፍ የመጣው የኢትዮጵያና የኤርትራ ታሪካዊና ባህላዊ የአለባበስ፣ የአመጋገብ፣ የአኗኗር ልማድ፣ ሥነ ጥበብና ሕግ የተጨባጭና ረቂቅ ቅርስ አካል መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ ይኼም ተመሳሳይነት እንደሚከተለው ይዳሰሳል።

አለባበስ

የኤርትራውያንና የኢትዮጵያውያን ሴቶችና ወንዶች የአለባበስ ተመሳሳይነት ሲኖራቸው፣ የልብሶቹ ደረጃም የሰዎቹን ማኅበራዊ ሥፍራ የሚያመለክቱ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የሕፃናት፣ የወጣቶችና የአዛውንቶች ተብለው በዕድሜ የተከፋፈሉ ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ከጥበብና ውበት ጋር በእጅጉ የተያያዘው የሴቶች ስለሆነ፣ በአብዛኛው በዚያ ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡

ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ተመሳሳይ የሆነ አለባበስ ሲኖራቸው፣ በተለይም ሴቶቹ ከፈትል የተሠራ ቀሚስ መልበስና ወገባቸው ላይ መቀነት ማድረግ ያዘወትራሉ፡፡ የቀሚሱ ፈትል እንደ ሁኔታው ቀጭን፣ መካከለኛና ወፈር ያለ ሲሆን፣ ቀሚሱ ከኋላ በኩል ወይም ዙርያ ምላሹን በተለያየ መልክ የተሠራ ጥለት ይደረግበታል፡፡ ጥለቱም ከምትለብሰው ሴት ፍላጎት ጋር የተያያዘ ሲሆን አረንጓዴ፣ ሰማያዊ፣ ሐምራዊና ቀይ ሊሆን ይችላል፡፡ መጠኑም ቢሆን ከለባሾቹ አቅም ጋር የሚሄድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ሀብት ያላቸው፣ የጋት ያህል ወይም ከዚያ በለጥ የሚል ጥለት ሲያደርጉ ሌሎቹ ደግሞ አንድ፣ ሁለት ወይም ሦስት ጣት ስፋት ያለው ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

 በሁለቱም ሕዝቦች ጥቁር ጥለት የሚደረገው ለሐዘን ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ከአንድ ጥለት በተጨማሪ የተለያየ መልክና አሠራር ያለው ጥበብም በቀሚሱ በስተኋላ ወይም ዙሪያ ምላሹ ሊደረግ ይችላል፡፡ በቀሚሱ ግርጌ ዙሪያ የሚደረገው ጥልፍም ቢሆን፣ እንደ አንድ ጥለቱ ሁሉ የለባሹን ደረጃ የሚያመለክት ነው፡፡ ቀሚሱ በተጨማሪ ከፊት ለፊት በአንገት ዙሪያ አድርጎ እስከ ግርጌ የሚወርድ ጥልፍ ሊደረግበት ይችላል፡፡ የጥልፉ ስፋት ወይም ከጥልፉ ግንድ በሁለት በኩል ወደ ቀኝና ግራ ጡት የሚሄደው ጌጥም እንደ ጥለቱ ሁሉ፣ እንደ ሴትየዋ አቅም ሲሰፋ የበለጠ ወይም ያነሰ ውበት ሊኖረው ይችላል፡፡ የቀሚስ ልብስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ጫፎቹ የመስቀል ቅርፅ እንደነበራቸው ይታወቃል፡፡ የቀሚሱ ጥልፍ ከብር የተሠራ ‹‹መልጎም›› የተባለ ጌጥ የሚደረግበት ሲሆን፣ መልጎምም በአንገት ዙሪያ ጫፍ ላይ ይወርድና ከፊት ለፊት በኩል የጥልፉን መሀል ይዞ በመውረድ እስከ ጫፍ ይደርሳል፡፡

በሐበሻ ቀሚስ ላይ ብዙ ጊዜ ከሁለት ጫፎቹ በኩል ጥለት የሚደረግበት መቀነት መታጠቅ የተለመደ ሲሆን፣ የመቀነቱ ጥለት ስፋትም ቀጭን ወይም ጠባብ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ ሴቶች ከመቀነቱ ጫፍ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ እስከ ወገብ የሚደርስ ጥለት አልፎ አልፎ ሊያስደርጉት ይችላሉ፡፡ የትልልቅ ሴቶች መቀነት አብዛኛውን ጊዜ ሁለት ዙር ሲሆን፣ ሕፃናትና ወጣቶች ግን አንድ ዙር መቀነት ብቻ ሊበቃቸው ይችላል፡፡ ቀሚሱ ከልብሱም በላይ የተለያየ ዘውግ ያለው የነጠላ፣ የኩታና የጋቢ ዓይነት ይደርቡበታል፡፡ ከነጠላው ዓይነት ድፍን ፈትል በድር፣ ዝርዝር፣ ጀበርባሬ፣ ቀጭንና ወፍራም እየተባለ እንደሚለይ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ሁለት ነጠላዎች የሚሰፉትም ወፍ እግር ጥልፍልፍ ውበት ነው፡፡ በሥሬቱ ቀጭን ወይም ወፍራም የሆነ የተደረበ ነጠላ ባለ አራት አርበ ኩታ ከቀሚስ ላይ ሊደረብ ይችላል፡፡ የሦስት ነጠላ መጠን ወይም ስድስት አርብ ያለው ጋቢም አልፎ አልፎ የሚለበስ ሲሆን፣ ለሴቶች የሚከብድ ስለሆነ በጣም ቀጭን ካልሆነ አይዘወተርም፡፡ ሆኖም የሀብታም ሚስቶች ወይም ሀብታም ሴቶች፣ በተለይም ትልልቅ ሴቶች በበዓል ለብሰውት ሊቀመጡና እንግዳ ሊያስተናግዱ ይችላሉ፡፡

የሕፃናትና የወጣቶች ቀሚስ አለባበስም የራሱ የሆነ የአሠራር ልማድን የተከተለ ሲሆን፣ በጣም ሕፃናቱ ጥለት ያልተደረገበት ቀሚስ፣ ወጣቶቹ ደግሞ ጥለቱ ያልሰፋ ቀሚስ እንዲለብሱ ይደረጋል፡፡ ሆኖም ሲታጩና አሸንዳ ወይም እንቁጣጣሽ ወይም ሌላ ባህላዊ በዓል ሲኖር ከዳሌያቸው እስከ ታች የሚወርድ ጥለት አልፎ አልፎ ሊደረደርላቸው ይችላል፡፡ ይህ ትፍትፍ ይባላል፡፡ ይህ አለባበስ በአብዛኛው በአሸንዳ ጊዜ የሚዘወተር ነው፡፡ አንዲት ወጣት ትፍትፍ ቀሚስ፣ መቀነት፣ ማርዳ ወይም ድሪ ካደረገች መታጨቷን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ወጣቶች ካገቡ በኋላ ከአዋቂዎች ጋር ተመሳሳይ የሆነ አለባበስ ሊለብሱ ይችላሉ፡፡

በኢትዮጵያና በኤርትራ በተለይም በትግራይ የታጨች ልጃገረድ ማርዳና ጥልፍ (ዛሬ በቀለበት ተተክቷል) በማድረግ ተለይታ ትታወቃለች፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ወንዶች አለባበስ እንደ ብሔረሰቦቹ የሚለያይ ሲሆን፣ ጥንታዊው የትግሬዎች አለባበስ እጀ ጠባብና ተነፋነፍ ወይም እጀ ጉርድ እስከ ጉልበት የሚደርስ ከግራና ከቀኝ በኩል ቀዳዳ ያለው፣ ከፊት ደረት ላይ አንድም በግራ በኩል ወይም ከግራና ከቀኝ ኪስ ያለው ቀሚስ መሰል ሸሚዝ የሚለብሱ ሲሆን፣ በእሱም ላይ ነጠላ ኩታ፣ ወይም እንደ ሁኔታው ጋቢ ሊደርቡ ይችላሉ፡፡

ቀደም ሲል የተጠቀሰው አለባበስ በአብዛኛው ጥንታዊ አለባበስን የሚያመለክት ነው፡፡ ከዘመኑ ጋር እየተለወጠ በእጅ የሚሰፋው በመኪና፣ በመቀነቱ ምትክ ሽንሽን፣ በጥልፉ ምትክ ተለጣፊ ጥበብ ሲሆን ሊስተዋል ይችላል፡፡ የፈትሉ፣ የድሩ፣ የጥለትና የአሸማመኑ ዓይነትም ከዘመኑ ጋር እያደገ መምጣቱ አሌ አይባልም፡፡

የፀጉር አሠራር

የኢትዮጵያና የኤርትራ የሴቶች ፀጉር አሠራር እንደ ብሔረሰቡ፣ እንደ ዕድሜው፣ እንደ ጋብቻው ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን እንደ ገቢው የሚለያይ ቢሆንም አንድ ቦታ ላይ ይገናኛል፡፡ በዚህም መሠረት የትግሬዎች፣ የአፋሮች፣ የኩናማዎች፣ የሳሆዎች የፀጉር አሠራር ከዕድሜና ከገቢ አንፃር ለማየት እንሞክር፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ የሴቶች ፀጉር አሠራር በአጠቃላይ የሚያመሳስለው በተለያየ ሁኔታ በመጎንጎኑ ሲሆን፣ የመጎንጎኑ መሠረታዊ ምክንያትም ከሥራ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሥሬቱ በቅባት ሊወዛ ይችላል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕፃናት ሴቶች ፀጉር አሠራር እስከ ልጃገረድነት ጋሜና ቁንጮ ሲሆን፣ ሁለቱም ዕድሜያቸው ከፍ እያለ በሄደ መጠን የጋሜውም ሆነ የቁንጮው ወይም የቁንዳላው ስፋት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ተማሪዎች ዛሬም ቢሆን ፀጉራቸውን ቢደፍኑም የጋሜና የቁንጮ አሠራር አልቀረም፡፡

የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ትልልቅ ሴቶች ፀጉራቸውን በተለያየ ዘይቤ (በወፍራም ወይም በመካከለኛ ወይም በቀጭን ወይም በአልባሶና ጉንጉን የሚሠሩት ሲሆን፣ ጉንጉኑም በሦስት በወስፌ ወይም በማበጠሪያ ወይም ለእዚህ ተብሎ በተሠራ ቀጭን እንጨት በዓይነት ግምት ከዋናው ፀጉር እየተለየ የሚሠራ ነው፡፡ የሴቶች ፀጉር በአብዛኛው ከአናት ለሁለት በመክፈል ከቀኝ በኩል ያለውን ግማሽ ከጨረሱ በኋላ፣ ቀጥሎም በግራ በኩል ግማሽ ያለው ይሠራል፡፡ ፀጉር ሠሪዋ እያንዳንዱን ጉንጉን ስትሠራ ተሠሪዋ የማይሠራውን በእጇ ትይዛለች፡፡

ትግርኛ ተናጋሪ የኢትዮጵያና የኤርትራ የሴቶች ሥሬታቸውን ከፊት ለፊት ጀምሮ ዙሪያውን በሳር ገታ ማጠር፣ በስተግንባር በኩል ሳር ገታው መሀል አናትን አቋርጦ ከሚያልፍ ጉንጉን ሊያያዝ ይችላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ነጠላ አልባሶ የሚባለውም ይኼው ጉንጉን አንድም ያለተጨማሪ የውጭ ፀጉር ያለበለዚያም ‹‹ሴንቴቲክ›› ወይም ‹‹ሂዩማን ሄይር›› በውስጡ እየተደረገበት ሊሠራ ይችላል፡፡

አፋሮች፣ ሳሆዎች፣ ኩናማዎች፣ ናራዎችና ረሻይዳዎ ደግሞ ፀጉራቸውን ከመሀል መሀል ይከፍሉና በግራና በቀኝ ጎን፣ እንዲሁም ወደኋላ እየጎነጎኑ ወደ ጀርባ ያወርዱታል፡፡

አመጋገብ

በኢትዮጵያና በኤርትራ የአመጋገብ ሥርዓቱ እንደብሔረሰቡ የተለያየ ቢሆንም፣ እንኳን ከተለያዩ የጥራጥሬ ዘሮች እንጀራ፣ ቂጣ፣ አምባሻ፣ ህብስት፣ አነባበሮ፣ ብርኩታ እየተሠራ በወጥ ይበላል፡፡ ወጡም ሥጋ ወጥ (በግ፣ የፍየል፣ በሬ፣ ዶሮ)፣ ሽሮ፣ ምሥር ወጥ፣ አተር ወጥ፣ ሊሆን ይችላል፡፡ ከወጡ በተጨማሪ ወተት፣ እርጎ፣ እልበት፣ ተልባ ብጥብጥ፣ ጎመን ወጥ፣ ወዘተ. . .  ሊሆን ይችላል፡፡

በሁለቱም አገሮች በአብዛኛው የሚበላው በቀን ሦስት ጊዜ ሲሆን ቁርስ፣ ምሳና እራት ናቸው፡፡ ከእነዚህም ሌላ በምሳና በእራት መካከል የቂጣ፣ የዳቦ፣ የቆሎ፣ የንፍሮ ወዘተ. . . መቅሰስ ሊኖር ይችላል፡፡ ቡና በሚፈላበትና ሻይ በሚቀርብበት ጊዜም ቡና (የእንጀራ፣ የቂጣ፣ የቆሎ፣ ወዘተ . . . ) ቁርስ ማቅረብ የተለመደ ነው፡፡

በሁለቱም አገሮች የሚኖረው የምግብ አዘገጃጀት ተመሳሳይ ሲሆን፣ ምግብ ማብሰያውም ሆነ ማቅረቢያው ተመሳሳይ ነው፡፡ ከምግቦች ውስጥ እንጀራንና ወጥን ምሳሌ አድርገን ብንወስድ እንጀራው ከጤፍ፣ ከማሽላ፣ ከበቆሎ፣ ከዘንጋዳ፣ ከስንዴ ወይም ከገብስ ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ የሚጋገረውም በምጣድ ወይም ጎድጎድ ባለ ሞቅሎ በተባለ ምጣድ መሰል ሸክላ ነው፡፡ ምጣድም ሆነ ሞቅሎ እንጀራ ሲጋገር በአክንባሎ ይከደናሉ፡፡

በሁለቱም አገሮች የሚሠራው የወጥ ዓይነት እንደ ቤተሰቡ አቅም የሚበዛ ወይም የሚያንስ ቢሆንም ቀይ ወጥ፣ አልጫ፣ ጥብስ፣ ዱለት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ሁሉም ወጦች ዘይት፣ ወይም ቅቤ፣ ወይም ተልባ ተጨምሮላቸው ሊጣፍጡ ይችላሉ፡፡

ጌጣጌጥ

በኢትዮጵያና በኤርትራ ጌጣጌጥ የሚያደርጉት በአብዛኛው ሴቶች ሲሆኑ ወንዶችም ከመዳብ፣ ከነሐስ ወይም ከብረት የተሠራ አምባር፣ የጣት ቀለበት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ድሮ ወንዶች የጆሮ ሎቲ ከላይ ጫፍ ወይም ከሥር ጫፍ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

የሴቶች ጌጣጌጥ ከራስ ፀጉር ጀምሮ እስከ እግር ጣት ያለውን አካል ሊያጠቃልል ይችላል፡፡ የራስ ጌጥ የምንላቸው ፀጉር ላይ የሚሰካ ወለባ፣ ግንባር ላይ የሚደረግ ጹሩራ፣ ጆሮ ላይ የሚደረግ ጉትቻ፣ ሎቲ፣ አንገት ላይ በሀብል በማህተብ፣ ወይም በሌላ የሚታሰሩ መስቀል፣ ሀብል፣ እንጥልጥል፣ ማርዳ፣ ጠልሰም፣ ወዘተ. . . ሊሆን ይችላል፡፡ ጣት ላይ በልዩ ልዩ መልክ የተሠሩ ቀለበቶች፣ እጅ ላይ የሚደረጉ አምባሮች ወይም ጠፍጣፋና ድብልብል ድኮቶች፣ እግር ላይ የሚደረጉ አልቦዎች፣ ጣት ላይ የሚደረጉ ቀለበቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ጌጣጌጦቹ ከብረት፣ ከነሐስ፣ ከመዳብ፣ ከብርና ከወርቅ የሚሠሩ ሲሆን በእነሱም ላይ የሚያርፈው ጥበብ እንደ ሁኔታው ሊለያይ ይችላል፡፡ ጌጡ የሚገዛበት ዋጋ ከፍ ባለ ቁጥር የጌጡ ዓይነት ጥራት ከፍ እያለ ይሄዳል፡፡

የሸክላ ሥራ

በኢትዮጵያና በኤርትራ ተመሳሳይ የሆነ የተለያየ መጠንና ዲዛይን ያለው የምጣድ፣ የእንስራ፣ የገንቦ፣ የድስትና የጣባ ሥራ ሲኖር አገልግሎቱም ተመሳሳይ ነው። ከሸክላ ሥራዎች ውስጥም በተለይም ጀበና፣ እንስራ፣ ምንቸትና ድስት በውጭ አካላቸው ላይ ዓይን የሚስቡ የመስመር ጌጦች ይደረግባቸዋል። ከኤርትራ ሸክላ ሥራዎች የከረን ጀበና በውበቱ የበለጠ ተወዳጅ ነው።

ሙዚቃ

በኢትዮጵያና በኤርትራ ሙዚቃ በአገልግሎት ላይ የሚውለው በአብዛኛው በደስታ ጊዜ ሲሆን በለቅሶ፣ በሃይማኖት በዓላት፣ በጦርነት ወቅት በአገልግሎት ላይ ሊውል ይችላል፡፡ በሁለቱም አገሮች ተመሳሳይ የሆኑ ዜማዎች፣ ውዝዋዜዎችና የሙዚቃ መሣሪያዎች ሲኖሩ የትግርኛ፣ የአፋር፣ የሳሆና የኩናማ ዘፈኖች በአብዛኛው ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ውዝዋዜዎቹንም ይኼ የዚህ አገር ነው፣ ይኼኛው ደግሞ የዚህኛው ነው ብሎ መለየት ያስቸግራል፡፡ ምናልባት መለየት የሚቻል ቢሆን በሚያነሱት የአካባቢ ስም ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ኤርትራዊው ‹‹ኤርትራ አደዬ›› ቢል ኢትዮጵያዊው ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያ አደዬ›› ሊል ይችላል፡፡ በጥሞና ላደመጠው ደግሞ በአነጋገር ዘይቤ ልዩነቱ የየትኛው አካባቢ መሆኑን ለይቶ ሊያውቀው ይችላል፡፡

     ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles