Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልኅብራዊው ክብረ በዓል

ኅብራዊው ክብረ በዓል

ቀን:

በሮም ፍራስካቲ ሠፈር የሚገኘው ትልቁ ባሰሊካ (ካቴድራል) የማያቋርጥ የደወል ድምፅ ይሰማል፡፡ እየቆየም ማስተጋባቱን ቀጥሏል፡፡ በአዘቦቱ ዘወትር ከሚሰማው የተለየውም በሀገረ ጣሊያን በምሥራቅ ኦርቶዶክስና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት ረቡዕ  ነሐሴ 9 ቀን 2010 .. በሮም ደግሞ ኦገስት 15 ቀን 2018 ዓመተ እግዚእ፣ (የአውሮፓና የተቀረው ዓለም ክርስቲያኖች በኢትዮጵያ ዓመተ ምሕረት እንደሚባለው እነሱም በላቲንአኖ ዶሚኒ› AD ሲተረጎም የጌታ ዓመት) የተከበረው የቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ሰማይ ያረገችበት የፍልሰታ ክብረ በዓል ስለሆነ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ክረምት (ዊንተር) ነሐሴና የአውሮፓ በጋ (ሰመር) ኦገስት በቤተ ክርስቲያን ባሕረ ሐሳብ የደስታ ብርሃን የሚንፀባረቅባቸው የበዓላት ቀኖች ቡሔና ፍልሰታ ናቸው፡፡ አንደኛው ቡሔ (እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ታቦር ተራራ ላይ ከሐዋርያት ጋር ከወጣ በኋላ መለኮታዊ ብርሃኑ የተገለጠበት) ነሐሴ 13 ኦገስት 6 ሲሆን፣ ሁለተኛው ነሐሴ 16 ኦገስት 15 የሚከበረው ፍልሰታ ማርያም ነው፡፡

በጣሊያን ሲሲሊያ ግዛት መሲና ከተማ ነዋሪዎች የድንግል ማርያም በዓለ ፍልሰታን ‹‹ፌስታ ዴላ አሱንታ›› ይሉታል፡፡ ዓመታዊና ታላቅ ክብረ በዓሉ ከጁላይ 31 እስከ ኦገስት 15 የሚቆይ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎችን እንደሚስብ ይነገርለታል፡፡ የከተማዋ ‹‹ጠባቂ ቅድስት›› የሚሏትን የቅድስት ማርያም ኪነ ቅርጽን ከ15 በላይ ሻማ ጋር ከ30 በላይ ወንዶች ተሸክመው በየመንገዱ እየዞሩና በየአደባባዩ እየቆሙ ያከብሩታል፡፡ በኦገስት የመጀመርያ ጥቂት ሳምንታትም የንዋየ ቅድሳት፣ የዕደ ጥበብ፣ የሥዕልና የፎቶግራፍ ዐውደ ርዕይም ይከፈታል፡፡

በዓሉ በኦገስት ወር ስለሚውልም ‹‹ፌራጎስቶ›› (Ferragosto) ሲሉት፣ መልካም ምኞትን ሠናይ በዓል ለሁሉም ብሎ ለመግለጽም ‹‹ቦን ፌራጎስቶ ቱቲ›› (Buon Ferragosto a Tutti) ይሉታል፡፡

 በዓሉ በአውሮፓና በአሜሪካ በአፍሪካም 13 አገሮች (ቡሩንዲ፣ ካሜሩን፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አይቮሪኮስት፣ ጋቦን፣ ጊኒ፣ ማዳጋስካር፣ ሞሪሸስ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ሲሸልስና ቶጎ) ብሔራዊ በዓል ሆኖ ነበር የተከበረው፡፡ በኢትዮጵያም ‹‹በዓለ ፍልሰታ ለእግዝእትነ ማርያም›› እየተባለ  እስከ 1966 .. ነሐሴ 16 ቀን ብሔራዊ በዓል ሆኖ ይከበር ነበር፡፡

ኅብራዊው በዓል

በሰሜንና ሰሜናዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ከተሞች በነሐሴ መንፈቅ፣ ልዩ ድባብ የሚያለብሳቸው ከተሜዎቹንም ሆነ ከዚያም ውጪ ያለውን ኅብረተሰብ ቀልብ የሚገዙበት አጋጣሚን ያገኛሉ፡፡ ዓመት ሄዶ ዓመት ሲመጣ 12ኛው ወር ላይ ከምትመጣውና ከፍልሰታ ለማርያም በዓል ጋር ከተያያዘው እንደየአካባቢው አጠራር አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሻደይ፣ ሶለል፣ ዓይኒ ዋሪ፣ ማርያ፣ ዋዒምቦ ጋር ይገናኛሉ፡፡

 ሴቶች ልጃገረዶች በልዕልና የሚታዩበት፣ በነፃነት ነግሠው የሚጫወቱበትም ነው፡፡  ከሕፃን እስከ አዋቂ የበዓሉ መገለጫ በሆኑ አልባሳትና ማጋጊያጫዎች የሚታዩት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡ ክብረ በዓሉ ጎልቶ የሚታይባቸው ትግራይና አማራ እንደወትሮው ሁሉ ዘንድሮም በልዩ ልዩ ባህላዊ መሰናዶዎች እያከበሩት ነው፡፡

የትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዳስታወቀው፣ የአሸንዳ በዓል ሰላምና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች ከማክበር ባለፈ ዋናው የክብረ በዓሉ ሥፍራ የመቐለ ባሎኒ ስታዲየም ነው። ባህላዊና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ በበዓሉ ላይ ዐውደ ርዕይም ይዘጋጃል፡፡ በክልሉ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች በአሸንዳ በዓል ላይ በመገኘት ባህላቸውን እንዲያንፀባርቁም ታድመዋል፡፡

የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እንዳስታወቀው፣ የሻደይና አሸንድዬ የልጃ ገረዶች በዓል ባህላዊ ትውፊቱን ለትውልድ ለማስተላለፍ በክልል ደረጃ ነሐሴ 19 እና 20  በተለያዩ መሰናዶዎች በባህር ዳር ስታዲየም ይከበራል። አስቀድሞ ግን በዋግ ህምራ ሰቆጣ ከተማ የሻደይ፣ በሰሜን ወሎ ላሊበላና ዓይና ቡግና የአሸንድዬና በቆቦ ከተማ ደግሞ የሶለል አሸንድዬ በዓል ነሐሴ 16 ቀን እንደሚከበር፣ በበዓሉ ከየአካባቢው የተውጣጡ እናቶችና ልጃገረዶች የሻደይና አሸንድዬ ባህላዊ ጭፈራዎችንና የሚጠቀሙባቸው ባህላዊ ቁሳቁሶችን ለዕይታ በማቅረብ ልምድ የሚለዋወጡበት ይሆናል ብሏል።

ክብረ በዓሉ ሲገለጥ

በክረምት ወቅት ከሚበቅለው ተክል ስሙን የወረሰው በትግራይ አሸንዳ፣ በሰቆጣ ሻደይ (በኸምጣኛ ቋንቋ ‹ለምለም› ማለት ነው)፣ በላሊበላ አሸንድዬ፣ በቆቦ ሶለል ሲባል ዓይንዋ ከሚያምረው ወፍ ‹‹ዓይኒ ዋሪ›› ጋር ልጃገረዶቹን በማነፃፀር በዓሉ በአክሱም ይጠራል፡፡

ከነሐሴ አጋማሽ የሚጀምረውና የተለያዩ ስያሜዎች ያሉት ክብረ በዓሉ መነሻው ከቤተ ክርስቲያን ጋር ተያይዞ የመጣና መጽሐፋዊ መሠረት እንዳለው ይወሳል፡፡ በተለያዩ ጽሑፎች እንደተጠቀሰው ከዘመን መለወጫ፣ አዳምና ሔዋን ከገነት ሲባረሩ ካገለደሙት ቅጠል ‹‹አዳምና ሔዋን ክብራቸውን ተገፈው ከገነት የተባረሩባትን ዕለት በማሰብ በወቅቱ ያገለደሙትን ቅጠል በምልክትነት በመውሰድ የሻደይ ቅጠልን በገመድ ላይ ጎንጉነው በወገባቸው አገልድመው ያስራሉ፤›› ይላል አንድ መጣጥፍ፡፡

በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ መጉደሉ በወይራ ቅጠል ካበሰረችው ርግብ፣ ከመጥመቁ ቅዱስ ዮሐንስ አንገት መቆረጥ፣ ከቅድስት ድንግል ማርያም ትንሳዔ (ፍልስታ) እና ከመስፍኑ ዮፍታሔ ልጅ ታሪክ ጋር ያስተሳስሩታል፡፡ ጎልቶ የሚነገረውና የሚተረከው ግን ከቅድስት ማርያም ፍልሰታ በዓል ጋር የተያያዘው ነው።

ከማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች መካከል የሚገኝና ልዩ ልዩ ቁሳዊ መገለጫዎች አሉት፡፡ የፀጉር አሠራሩ ከአልባሶ እስከ ግልብጭ፣ ከጋመ እስከ ድርብ፣ ከደቃቅ እስከ ጉልህና ከሕፃን እስከ አዋቂ ተቆናጅተው የታዩበትም ጭምር ነው፡፡ ከቱባው ባህል ልብስ አንሥቶ ከዘመናዊው ስፌት ከተገኙት ጃርሲ፣ ሽፎን ቀሚስ ጋር ተውበው የሚታዩበትም ነው፡፡

በመቐለ፣ ዓቢይ ዓዲ፣ ሰቆጣ፣ ላሊበላ፣ ቆቦና ሌሎችም የአካባቢው ከተሞች ነሐሴ አጋማሽ ላይ የከተሜውንም ሆነ እንግዳውን ቀልብ የሚስቡበት ባህል ነው፡፡ ልጃገረዶች ሴቶች በነፃነት ነግሠው አደባባይ ወጥተው ይጫወቱበታል፡፡

ነሐሴ 16 ቀን ከሚከበረው የቅድስት ማርያም በዓል ጋር የተያያዘው ክብረ በዓል ከዋዜማው እስከ ማግስት ልጃገረዶች የአሸንዳ ቅጠልን አሸርጠው አደባባይ በመውጣትና በየቤቱ በመዞር እየጨፈሩና እያዜሙ ያከብሩታል፡፡ ከሕፃን እስከ አዋቂ የበዓሉ መገለጫ በሆኑ አልባሳትና መጋጊያጫዎች ተውበውታዩበታዋል፡፡ የፀጉር አሠራራቸው ከአልባሶ እስከ ግልብጭ፣ ከጋመ እስከ ድርብ፣ ጋሜ፣ ቁንጮ፣ ሳዱላና ቅርድድ ተሠርተው አደባባይ የሚውሉበት ነው፡፡ ጌጣ ጌጣቸውም ልዩ ልዩ ዓይነት ሕንቆ፣ አልቦ፣ ድሪ፣ ድኮት፣ ጉትቻ፣ ማርዳ፣ መስቀል ሲሆን፣ አለባበሳቸውም በመልጉም /ጥልፍ ቀሚስ/ ሹፎን፣ ጃርሲ ይታጀባል፡፡

የአሸንዳ መንፈስ፣ በፀጉር አሠራርና በአልባሳት፣ በመዋቢያ ቁሶችና በመጋጋጪያዎች ብቻ አይደለም የሚገለጠው፣ርሱን የሚያገዝፉ የሚያጎሉ የተለያዩ ዘፈኖች ይገኙበታል፡፡ 

ለሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት

ከሦስት ዓመት በፊት በመቐለው አሸንዳ በክብር እንግድነት ተገኝተው የነበሩት በምህፃሩ ዩኔስኮ ተብሎ የሚጠራው የመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ተቋም ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው እንግዳ፣ ዩኔስኮ የሴቶች በዓል የሆነው አሸንዳ አከባበር ልዩ ትርጉም እንደሚኖረው በምክንያትነት ያብራሩት፣ ‹‹የጾታ እኩልነትን ማረጋገጥና የአፍሪካ አኅጉርን መደገፍ ድርጅቱ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የትኩረት አቅጣጫ በመሆናቸው ነው፤›› በማለት ነበር፡፡

የነሐሴውን ክብረ በዓል የሰው ልጆች ድንቅ የባህል ቅርሶች ወካይ የዓለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እንዲቻል ሁለቱም ክልሎች ባለፉት ዓመታት ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጥያቄ አቅርበው በጋራ ሲያስጠኑ ነበር፡፡ የባለሥልጣኑ ባለሙያዎች የሠሩት ጥናትም ዓምና ታትሞ መቅረቡ ይታወሳል፡፡

በሔኖክ ያሬድ፣ ሮም፣ ጣሊያን

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...