በመርካቶ በአንድ ሰዓት ውስጥ 6,000 ለሚጠጉ የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች አገልግሎት መስጠት የሚችል የአውቶቢስ ተርሚናል ግንባታ ተጀመረ፡፡ ይህ ተርሚናል በከተማው አስተዳደር በ200 ሚሊዮን ብር በጀት ግንባታው የተጀመረ ሲሆን፣ ግንባታው በ2011 በጀት ዓመት ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የሚገባ ይሆናል፡፡
የአውቶቡስ ተርሚናሉ በ4,125 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈና በአንዴ ለ20 አውቶቡሶች በባለሁለት ሕንፃው አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ ሁለቱ ወለሎች የራሳቸው መግቢያና መውጫ ያላቸው ሆነው አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ ታስቦ እየተገነባ ይገኛል፡፡ የአውቶቡስ ተርሚናሉ በዋናነት የአውቶቡስ መጠበቂያ ቦታ፣ የትኬት ሽያጭ፣ የተሳፋሪ መጫኛና የማራገፊያ ቦታ፣ ዘመናዊ ስምሪት አገልግሎት፣ የአውቶቡስ መርሃ ግብርና የአስተዳደር ቢሮዎችን ያካተተ ይሆናል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ትልቁ ክፍት የገበያ ማዕከል በሆነው መርካቶና በቀን ከ50,000 እስከ 80,000 ገበያተኛ ሕዝብ በሚንቀሳቀስበት አካባቢ ነው የአውቶቡስ ተርሚናሉ የሚገነባው፡፡
በተመሳሳይም በመሬት ላይ ብቻ የሚጠናቀቅ ሆኖ በአንድ ጊዜ ከ250 እስከ 300 አውቶቡሶችን በተመቻቸ ሁኔታ የማቆም አቅም ያለው የሸጎሌ ዴፖም ግንባታ እንዲሁ ተጀምሯል፡፡ መንግሥት በመደበው 500 ሚሊዮን ብር ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኘው 52 ሺሕ ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ዴፖ በ21 ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ይህ ፕሮጀክት በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ከመሬት በላይ ያለው ሥራ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡ የጥገና ክፍሉን የከንች ሰቀላ ሥራን የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ጣሪያ የማልበስና ተያያዥ ሥራ በመጀመር ሒደት ላይ ነው፡፡ የአስተዳደር ሕንፃውን በተመለከተ የሁለተኛ ፎቅ ሥራም ተጠናቆ የጣሪያ ሥራና የማጠናቀቂያ ሥራ ከሥር ከሥር በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡