Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየዓባይ ጎርጅ በመሀል ቦሌ

  የዓባይ ጎርጅ በመሀል ቦሌ

  ቀን:

  ዙሪያውን አለት የከበበው ዋሻ መሀሉ እንደ ግላዲያተር ግንብ ክፍት ነው፡፡ ፍፁም አረንጓዴ የሆነው ሥፍራው ውኃ ያቆሩ ጉድጓዶች ይበዙበታል፡፡ እግር ያልበዛበት በመሆኑ ለመንቀሳቀስ ጢሻ መበጠስ፣ ረዘምዘም ያሉትን ሳሮች ማጋደም ግድ ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ በአረንጓዴ የተሸፈነው ይህ ሥፍራ ቅዝቃዜው አይጣል ነው፡፡

  እንደ ቤተ መንግሥት አጥር ወደ ላይ የተቆለለው አለትን አልፍ ብሎ በትንንሽ የብረት በሮች የተዘጉ መግቢያና መውጫዎች አሉ፡፡ ውስጥ ለውስጥ የሚወስደው መንገድ ጎርፍ የተመላለሰበት ይመስል ቦረቦር ይበዛዋል፡፡ አልፎ አልፎ የቆሙት የድንጋይ ምሶሶዎች ተፈጥሮ ዘመናት ፈጅታ ያነፀቻቸው ይመስላሉ፡፡ በግራና በቀኝ በኩል የተገጠሙት ከብረት የጠነከሩ፣ ድምፅ የማያስወጡ የማያስገቡ መስታወቶች በኩል የሚገባው ብርሃን ዋሻው ወለል ብሎ እንዲታይ አድርጎታል፡፡ መስታወቶቹ አንበሳን መቋቋም እንዲችሉ ተደርገው የተሠሩ ናቸው፡፡

  በብረትና በሽቦ ፍርግርግ ግጥግጥ ተደርገው የተሠሩ የአንበሶች ማደሪያ፣ ወደ ውስጥ ደግሞ ሕክምናና ሌሎችም ለእንስሳቱ የሚያስፈልጉ አገልግሎቶችና የመሳሰሉት የሚሰጡባቸው ልዩ ልዩ ክፍሎች አሉ፡፡ እነዚህ ክፍሎች በተቻለ መጠን ተፈጥሯዊ ይዘት እንዲኖራቸው ተደርገው የታነፁ የዋሻው አካል ናቸው፡፡ ይህንን የዱር እንስሳት መናኸሪያ ከሌሎቹ ፓርኮች ለየት የሚያደርገው ፓርኩ ያለው ከከተማ ርቆ በሚገኝ ጫካ ወይም ተራራ ላይ ሳይሆን የአፍሪካ መዲና በሆነችው አዲስ አበባ ለዚያውም መሀል ቦሌ ላይ መሆኑ ነው፡፡ ለአንበሶች መዋያነት የታሰበው ዋሻ በትልልቅ ቋጥኞች የተዋቀረ ነው፡፡ ከፍተኛ የቦታ ችግር ባለበት የአዲስ አበባ ምድር ለዚያውም ቦሌ መሰል የተፈጥሮ አሻራ ያረፈባቸው መስህቦች ሊኖሩ እንደማይችሉ ጥርጥር የለውም፡፡ ታዲያ ዋሻው ከየት መጣ? ያሉ እንደሆነ እንደዚያ ተነባብረውና ውስጣቸውን ክፍት አድርገው ዋሻ የሠሩትን ትልልቅ ቋጥኞች ካሉበት ፈልፍሎ ወደዚህ ያመጣም ከባድ ተሽከርካሪ የለም፡፡ እነዚህ ባቢሌ አካባቢ ያሉ ቋጥኞችን የሚመስሉት፣ ለዓባይ ጎርጅ ግርማ ሞገስ በሆኑት አለቶች አምሳያ የተዋቀሩት ቋጥኞች እንደ ሊጥ ተቦክተው እዚሁ የተጋገሩ ሰው ሠራሽ አለቶች ናቸው፡፡

  ለዘመናት የወረደ ዝናብ የቀረፃቸው የሚመስሉ ጠርዞች እንዲኖራቸው፣ ግለት ያቀለጣቸው እንዲመስሉ፣ ጎርፍ ያደቀቃቸው እንደሆኑ አድርገው ያነፁዋቸው ባለጥበቦች ደግሞ ሰዓሊና ቀራፂያኑ ፍፁም ውብሸት፣ ቶማስ ተሾመ፣ ሄኖክ አዘነ፣ ታደሰ ማሩና ሳሙኤል ገብረ ሕይወት ናቸው፡፡ የእነሱ ዋና ተግባር የአንበሶች መዋያ ተብሎ የተለየውን ሥፍራ ሙሉ ለሙሉ ተፈጥሯዊ ይዘት እንዲኖረው አድርጎ ማዘጋጀት ነው፡፡ ሰው ሠራሽ የሆኑትን ቋጥኞች ተፈጥሯዊ ይዘት እንዲኖራቸው ሲሚንቶን ከተለያዩ ኬሚካሎች ጋር ቀላቅሎ አንድ ላይ ማቡካትና ልዩ ልዩ ማቅለሚያዎችን መጠቀም ነበረባቸው፡፡

  ይህንን ሰው ሠራሽ ዋሻና ገደላገደል ለመሥራት ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሰው ጥናት ማድረግ፣ የተለያዩ መልከዓ ምድሮችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች መውሰድ ነበረባቸው፡፡ ወደ ምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ተጉዘው ባቢሌን ጎብኝተዋል፣ ዓባይ በረሃ ወርደው ሰማይ ጠቀስ አለቶችን በካሜራቸው አስቀርተዋል፡፡ የጁራሲክ ፓርክ የሚመስለውን ዋሻም 3ዲ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ፍጻሜው ላይ ሲደርስ ምን ዓይነት ገጽታ እንደሚኖረው የሚያሳይ ቪዲዮም አዘጋጅተዋል፡፡

  ፍፁምና አራቱ ጓደኞቹ በአንድ በኩል ያላቸውን የቅርፃ ቅርፅ ጥበብ ተጠቅመው ድንጋዩን ድንጋይ ለማስመሰል ሲጥሩ እነዚህ አለቶች የሚነባበሩበትን የኢንጂነሪንግ ጥበብ ደግሞ የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ጨረታ የወሰደው መከላከያ ኮንስትራክሽን አዘጋጅቷል፡፡ እያንዳንዱ አለት የሚያርፍበት ቦታ ሲታይ በዘፈቀደ ይምሰል እንጂ ራሱን የቻለ ሥሌት አለው፡፡ የአለቶቹ ክብደት፣ የሚይዙት ቦታና ሌሎችም የተፈጥሮ ለዛ እንዲኖራቸው ያደረጉ ይዘቶች በሙሉ በሒሳብ የተቀመሩ ናቸው፡፡

   ‹‹አርቲስቲክ ነገር ብቻ ያለው አይደለም፡፡ የኢንጂነሪንግ ይዘት አለው፡፡ የሚሠራው በብረት ስለሆነም የኮንስትራክሽን ሙያም ይጠይቃል፡፡ ብረቶች እየተበየዱ ነው ድንጋዮቹ የሚያርፉበት ቦታ የሚዘጋጀው፡፡ የኮንክሪትና የሲሚንቶም ሥራዎችም አሉት፤›› ይላል ፍፁም፡፡ ሁለት ሔክታር የሚሆን ቦታ ላይ ያረፈው የዚህ ዋሻ ግንባታ ከተጀመረ ዓመት ከመንፈቅ ሆኖታል፡፡ የግንባታው 96 በመቶ ያህል የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በመካከል ተቋርጦ እንጂ ከዚህ ቀደም ብሎ ማለቅ ይችል እንደነበር ፍፁም ይናገራል፡፡

  ‹‹ሥራው አዲስ እንደመሆኑ በመሀል አለመግባባቶች ተፈጥረው ነበር፡፡ የልኬት ሁኔታዎች ላይ እንደ መደበኛ ኮንስትራክሽን የማሰብ ነገር ስለነበር ሥራው ተስተጓጉሎ ነበር፤›› የሚለው ፍፁም ልኬቱ ከመደበኛ ኮንስትራክሽን የተለየ፣ ቀራፂያኑ አለቶቹ ተፈጥሯዊ ይዘት እንዲኖራቸው ለማስመሰል የፈጠራ አቅማቸው በልኬት ሳይወሰን መሥራት እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ ይህና አንዳንድ ጉዳዮች እንዳይስማሙ ቢያደርጋቸውም ለጥቂት ጊዜያት ሥራውን ካቆሙ በኋላ ለመቀጠል ወስነው ወደ ሥራ ከገቡ ቆይተዋል፡፡ ‹‹እንዲህ ዓይነት ሥራ በኢትዮጵያ የመጀመርያው ነው፡፡ ለእኛ ትልቅ ልምድ የምናገኝበትና የምንታወቅበት አጋጣሚ ስለሆነ በጎን እየተደራደርን ለሥራው ቅድሚያ ሰጥተን እየተንቀሳቀስን ነው፤›› ይላል፡፡

  አንበሶቹ ሊዘሏቸው ከማይችሏቸው ገደሎች ባሻገር የሚገኙ ክፍት ቦታዎች ጎብኚዎች በነፃነት አንበሶቹን ቆመው የሚመለከቱበት ነው፡፡ አንበሶቹ ወደ ጎብኚዎች እንዳይዘሉ የሚያግዷቸው ዙሪያውን የሸፈኑት አለቶች ሲሆኑ፣ ጫካ ያሉ ይመስል በነፃነት ሲንቀሳቀሱ፣ ሲበሉና ሲጠጡ ማየት በሚያስችል መልኩ ነው ዋሻው የታነፀው፡፡ የሽቦ አጥር የሚባል ነገር የለም፡፡ ሁለት ሔክታር ላይ ያረፈውን ይህንን የአንበሶች መኖሪያ ተፈጥሯዊ ይዘት እንዲኖረው የሚያደርጉት እነፍፁም ጨረታውን ያሸነፉት ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡

  ይህ ዋሻ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ላይ የሚገኘው የፒኮክ ፓርክ ውስጥ የሚገኝ ውስን ቦታ ላይ የተዋቀረ ነው፡፡ ስያሜው አዲስ ዙ ፓርክ ማዕከል በሚል  የተተካው ፒኮክ ፓርክ፣ በአንበሳ ግቢ የሚገኙ እንስሳት እንዲዘዋወሩበት ታቅዶ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ቆይቷል፡፡

  ‹‹አፄ ኃይለ ሥላሴ በ1940ዎቹ የመጀመርያውን አንበሳ ፓርክ በመሀል አራት ኪሎ ሲከፍቱ አንበሳ አይተው የማያውቁ የከተማ ነዋሪዎች አንበሳ ምን እንደሚመስል እንዲያዩ በሚል ነበር፡፡ አንበሳ ግቢ በአሁኑ ወቅት 25 ዓይነት የዱር እንስሳትና አንበሶች መኖሪያ ለመሆን ችሏል፤›› የሚሉት የማዕከሉ ዳይሬክተር ሙሴ ክፍሎም (ዶ/ር) በአንበሳ ግቢ ከቦታ ጥበት አኳያ ያለውን የአገልግሎት ችግር ለመቅረፍ በማሰብ የፒኮክን ፓርክ የማዘመንና እንስሳቱን ወደ ፒኮክ ለማዘዋወር ታስቦ ወደ ግንባታ መገባቱን ይናገራሉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ የአንበሳ ግቢ መስከረም 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ለዕድሳት የተዘጋ ሲሆን፣ የግንባታው የመጀመርያ ምዕራፍ ተጠናቋል፡፡ የሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታም በ28.3 ሚሊዮን ብር ተጀምሯል፡፡ የአንበሳ ግቢ የልጆች መዝናኛ፣ የንፅህና መጠበቂያ ክፍሎች፣ ክበቦችና ሌሎችም አገልግሎቱን ማዘመን የሚችሉ አገልግሎቶች የሚሰጡበት ይሆናል፡፡

  ‹‹በአንበሳ ግቢ ውስጥ በ1032 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ግለሰብ ይኖር ነበር፡፡ አንበሳ ግቢ ካርታም አልነበረውም፡፡ ካርታ የወሰደው በ2010 ዓ.ም. ነው፡፡ አላግባብ የተወሰዱ የፓርኩ ክልሎችና ቤቶችን አስመልሰን በመንግሥት ሥር አድርገን የማስፋፊያ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን፤›› ይላሉ ሙሴ (ዶ/ር) የግንባታውን ሒደት ሲያብራሩ፡፡ የምዕራፍ ሁለት የግንባታ ሒደት 12 በመቶ ያህል መጠናቀቁን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ በላይ እንደቆየና ኮንትራክተሩ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲያጠናቅቅ ጥብቅ ትዕዛዝ እንደተሰጠው ተናግረዋል፡፡

  በአንበሳ ግቢ የሚገኙ አንበሶችን ወደ አዲሱ ዙ እንዲዘዋወሩ ለማድረግ ታስቦ የተጀመረው የፒኮኩ ፕሮጀክትም እስካሁን መጠናቀቅ አልቻለም፡፡ በ36.4 ሔክታር መሬት ላይ ያረፈውን የአዲስ ዙ ፓርክን በዓለም ላይ ከሚገኙ አምስት ታዋቂ ፓርኮች መካከል መሆን የሚያስችለው ፕላን ወጥቶለት ነው ወደ ሥራ የተገባው፡፡ ይህንንም ለማድረግ 26.4 ሚሊዮን ዩሮ በጀት በከተማው አስተዳድር በኩል ተመድቧል፡፡

  የዓለም አቀፍ የፓርኮች ማኅበር ዕውቅና እንዲኖረው ተደርጎ እየተሠራ ያለው አዲሱ ዙ ፓርክ በስድስት የሥነ ምኅዳር ክልሎች ተከፋፍሎ የሚገነባ ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ የሥነ ምኅዳር ክፍል የአገሪቱን ልዩ ገጽታዎች የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ ግንባታው በ96 በመቶ የተጠናቀቀው ብሉ ናይል የሚባለውን የፓርኩ ክፍል ነው፡፡

  ብሉናይል በዋናነት ለአንበሳ፣ ለአዞ፣ ለጉማሬና ለኢትዮጵያ የዱር ውሾች መኖሪያ ይሆናል፡፡ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅም በአንበሳ ግቢ ከሚገኙ አናብስት መካከል ስድስቱ ወደዚህ እንዲዘዋወሩ ይደረጋል፡፡ አንበሶቹን ወደ አዲሱ ዙ ፓርክ የማዘዋወር ሥራ ይከናወናል ከተባለበት ጊዜ በእጥፍ መዘግየቱን የሚናገሩት ሙሴ (ዶ/ር)፣ አለት መሰል የግንባታ ሥራ በኢትዮጵያ ያልተለመደና አስቸጋሪ በመሆኑ ፈጥኖ መጨረስ አለመቻሉን ይናገራሉ፡፡

  የጨረታ ሒደቱ ብቻ ከዘጠኝ ወራት በላይ የፈጀ፣ ግንባታውን ለማስጀመር ከዋጋ ተከላ ጀምሮ የተለያዩ ጉዳዮች ረዘም ያሉ ጊዜያትን ፈጅተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ለጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ያለመስጠት ችግር የግንባታ መጠናቀቂያ ጊዜውን ካራዘሙ ጉዳዮች መካከል ናቸው ብለዋል፡፡ እስካሁን ግንባታው የተጀመረው የፓርኩ ክፍል ብሉናይል ብቻ ሲሆን፣ ሙሉ ጨረታውን ያሸነፈው መከላከያ ኮንስትራክሽን በ91.2 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

  በካርታ ላይ የሰፈረው የፓርኩ ግዛት 36.4 ሔክታር መሬት ሲሆን፣ ትልቋን ኢትዮጵያ ማሳየት የሚችሉ ስድስት ሥነ ምኅዳሮች በፕላኑ ተካተዋል፡፡ በዓባይ ምሳሌ የሚገነባው ብሉናይል የአማራ ክልልን የሚወክል ይሆናል፡፡ የራስ ዳሸንና የሶሎዳ ተራሮችም የዚሁ ፓርክ አካል ይሆናሉ፡፡ በአፋር ክልል የሚገኘው ደናክል ዲፕሪሽን የሚወክል የኤርታሌን ገጽታ የሚወክል ሰው ሠራሽ አለትም የፕሮጀክቱ ክፍል ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልልን የሚወክለውን የሀረና ደን በዚሁ በአዲስ ዙ ፓርክ ውስጥ እንዲለማ ይደረጋል፡፡

  በደናክል ዲፕሪሽንና አዋሽ ቫሊ ውስጥ ለውስጥ ወደ ታች አሥር፣ ወደ ጎን አሥር ሜትር ጥልቀትና ርዝማኔ ያለው የሶፍ ኡመር ዋሻን የሚመስል ጎብኚዎች ውስጥ ለውስጥ በታንኳ እየቀዘፉ የሚጎበኙት ዋሻ ይኖራል፡፡ ይህ ዋሻ ከስምንት እስከ አሥር ሔክታር መሬት ላይ ከሚያርፈው ኦሞ ቫሊ ሐይቅ ጋር የሚገናኝ እንደሚሆን ሙሴ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ስድስቱ የሥነ ምኅዳር ክፍሎች የሚሠሩት በ26.4 ሚሊዮን ዩሮ ከስምንት የተለያዩ የአገልግሎት ቦታዎች ጋር ነው፡፡

  ‹‹ራስ ዳሸን ተራራን ለመፍጠር በቦሌ ድንጋይ አንቆልልም፡፡ ውስጡ ባለ20 ፎቅ የሆነ ለቢሮዎችና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎች ያለው፣ ውጫዊ ገጽታው በሰው ሠራሽ አለት ተራራ የሚመስል ሕንፃ ነው የምናቆመው፤›› ብለዋል፡፡ የምሥራቅ አፍሪካ ዙ ኪፐርስ ማሠልጠኛ እዚህ የማቋቋም ሐሳብ አለን የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህንን ዕውን ለማድረግ አቅሙም ብቃቱም ያላቸው ባለሙያዎች ስላሉ ቀላል እንደሚሆንም አስረግጠረዋል፡፡

  የቀድሞው ፒኮክ ፓርክ ለዚህ ጉዳይ የተመረጠው ያረፈበት ቦታ ከሌሎቹ በተለየ ሰፊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፡፡ ፓርኩን አቋርጦ የሚያልፈው የቡልቡላ ወንዝ አግበስብሶ የሚያልፈውን ቆሻሻና ከየተቋሟቱ የሚለቀቁ መጥፎ ጠረን ያለውን ፍሳሽ  ወደ ፓርኩ ከመግባቱ በፊት በባዮ ፊልትሬሽን ሲስተም ውኃውን እንዲታከም ይደረጋል፡፡ በብሉ ናይል ሥነ ምኅዳር ላይ ለመፍጠር ለታሰበው የጢስ ዓባይ ፏፏቴ ናሙና የተጣራው የቡልቡላ ወንዝ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡

  ‹‹ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከ55 እስከ 60 የሚሆኑ እንደ ቀጭኔ፣ የሜዳ አህያ፣ አንበሳና የመሳሰሉት ትልልቅ እንስሳቶች ወደ ፓርኩ ይገባሉ፡፡ የተወሰነ ጥያቄ የሚኖረው ዝሆን ላይ ነው፡፡ ይህን በተመለከተ ከዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር መነጋገር ይኖርብናል፡፡ ቅድሚያ የምንሰጠውም ሁሉም ሊያውቃቸው ስለምንፈልግ ለአገራችን የዱር እንስሳት ነው፤›› ብለዋል፡፡

  በአነስተኛ ሥፍራ ላይ ያረፈውን የአንበሳ ግቢ በዓመት በ1.4 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ጎብኝዎችን ያስተናግድ ነበር፡፡ አዲሱ ዙ ፓርክ ግን በዓመት እስከ አራት ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች እንደሚጎበኙት በእርግጠኝነት ይገልጻሉ፡፡ አንድ ጎብኚ ስድስቱን የሥነ ምኅዳር ክፍሎችና ስምንቱን የአገልግሎት መስጫ ቦታዎችን በሙሉ ማየት ከፈለገ በቀን ከስምንት እስከ 12 ሰዓታት ድረስ በፓርኩ ጊዜ ያጠፋል፡፡ በዚህ ፓርክ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ የሚዘጋጁት ባህላዊ ምግቦች ይሆናሉ፡፡ የፓርኩ ግንባታ ከተጀመረ እስካሁን በክልሉ ሰፍረው የነበሩ 183 አባወራዎች የተነሱ ሲሆን፣ የተወሰኑ ደግሞ እስካሁን አልተነሱም፡፡ 7.5 ሔክታር የሚሆነው የፓርኩ ክልልም በግብርና የተያዘ በመሆኑ እነዚህን ሰዎች እንዲነሱ ምክክር እየተደረገ ይገኛል፡፡

  ‹‹ያዘገየን የልማት ተነሺዎች ጉዳይ ነው፤›› የሚሉት ሙሴ (ዶ/ር)፣ ሁሉም በአጭር ጊዜ ውስጥ መነሳት ቢችሉ አጠቃላይ የፓርኩ ግንባታ በአራት ዓመታት ውስጥ እንደሚያልቅ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፡፡ ሁሉንም የግንባታ ሒደት በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች መጨረስ የማይደራደሩበት ጉዳይ ሲሆን፣ የብሉናይል ግንባታ በእምነታቸው እንዲፀኑ እንዳደረጋቸውም ማየት ይቻላል፡፡ ግንባታው በተጠናቀቀ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ የወጣበትን ገንዘብ መልሶ ሌሎችን መደጎም የሚያስችለውን አቅም እንደሚገነባ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...