Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርየአዳማ ሕዝብ ለውጡን በሥጋት እያየው ይሆን? 

የአዳማ ሕዝብ ለውጡን በሥጋት እያየው ይሆን? 

ቀን:

ከአገሬ ከኢትዮጵያ በስተቀር ሌላ አገር እንደሌለኝ፣ ሊኖረኝም እንደማይችል ስለማምንና ስለምገነዘብ የአገሬ ጉዳይ ዘወትር ዕረፍት ይነሳኛል፡፡ ውስጤን ይበላኛል፡፡ ፍትሕ ሲደማ፣ በብሔር የፖለቲካ ድርጅቶች ምሽግነት ምንም ዕውቀት ሳይኖራቸው ከዲፕሎማ እስከ ማስትሬት ዲግሪ ድረስ ከመሬት ወረራና ከሥልጣን መከታ ባሰባሰቡትና ባካበቱት ሀብት የዘመናዊ ሕንፃ፣ ፋብሪካና መኪና ባለቤት በመሆን የሥልጣን ምንጭና ባለአገር የሆነውን ሕዝብ በመናቅ የሚያላግጡ ኃይሎች የዘርፋ መዋቅራቸው አሁንም በረቀቀ ዘዴና ታክቲክ እየተካሔደ ስለሆነ የጽሑፍና የቋንቋ ክህሎት ባይኖረኝም የውስጤን እሳት በትንሹ ለማብረድ ይህችን ጽሑፍ ለመላክ ወሰንኩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)ና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ፣ የኢትዮጵያ መሪዎች ናቸው ለማለት የደፈርኩት፣ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ላለው የተሃድሶ ለውጥ ዋና ሐዋርያት እንደሆኑ ስለማምን ነው፡፡

የዚህች ጽሑፍ አቅራቢ የየትኛውም ፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለሁም፡፡ የሥልጣን ጥማትም ሆነ ሀብታም የመሆን ጉጉት የሌለኝ፣ ለሕግና ለህሊናዬ ተገዢ ሆኜ፣ ባለኝ ሙያ ከወገኖቼ ጋር በእኩልነት፣ በፍቅር፣ በአንድነትና በነፃነት ሠርቼ የምኖር፣ የለውጡ ደጋፊ ሆኜ በመደመር ‹‹ነፃነት ያለ መስዋዕትነት የለምና፤›› መስዋዕትነት ለመክፈል ከተዘጋጁ እውነተኛ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነን፡፡ ይህንኑ በማረጋገጥ ከዚህ በታች ያለውንና ገንቢ ስለመሆኑ የማምንበትን ሐሳቤንና ቅሬታዬን አቀርባለሁ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የተወሰዱት ዕርምጃዎች በውጭ ዲፕሎማሲም ሆነ በውስጥ ጉዳዮች ለውጦች ታይተዋል፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው የጥል ግድግዳም ያለ ሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት በአጭር ጊዜ ፈራርሶ መገኘቱ የሰው ልጅን ብቃት ብቻም ሳይሆን፣ የፈጣሪ አምላክ ጣልቃ ገብነት የታየበት መሆኑን በማመን ጭምር አደንቃለሁ፡፡ ፈጣሪ ለመሪዎቻችን ኃይልና ብርታቱን፣ ጥበብና ፍቅሩን ያብዛላቸው እላለሁ፡፡

በታየው ለውጥ የረኩና የተደነቁ ቢኖሩም፣ በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መሐንዲስነትና ፊታውራሪነት የተፈጠሩ የክልል መንግሥታት ፓርቲዎች ለምሳሌ፣ ኦሕዴድ በኦሮሚያ ክልል በወረዳ ተፈጠርኩ እያለ ለ25 ዓመታት የቆየውና የ28ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር፣ አባዱላ ወደ ትግራይ በመጓዝ በሕወሓት አደራጅተው በሽሬ ውስጥ መፈጠራቸውን ያረጋገጡበት ማስረጃ በየሚዲያዎች የዜና ክምችት ውስጥ ይገኛል፡፡ ለ25 ዓመታት የተከማቸን ችግርና ጋንግሪን፣ እንኳንና በሦስት ወይም በአራት ወራት ቀርቶ በሦስት ዓመታት ውስጥም ለመፍታት ከባድ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይሁንና የለውጥ መሪዎች ብቻችሁን የማይቻላችሁ እንደሆነ ያለኝን እምነት እየገለጽኩ፣ እንደ መፍትሔ ሐሳብ ቀጥሎ ያሉትን ነጥቦች ላስቀምጥ፡-

 የኢሕአዴግ መንግሥት (ሕወሓት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድና፣ ደኢሕዴን) የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብት ለማፈን፣ በምርጫ ወቅት ድምፅ እንዲሰርቁና ኮሮጆ እንዲሞሉ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከክልል መንግሥታት ፕሬዚዳንቶች ጽሕፈት ቤቶች ጀምሮ እስከ ቀበሌዎች የተዘረጉ ጽሕፈት ቤቶች፣ በጎጥና በአንድ ለአምስት የተደራጁ የስለላ፣ የዝርፊና የአጭበርባሪዎች መዋቅሮች ሳይለወጡ፣ መልካም አስተዳደር፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ሊኖር ስለማይችል፣ በአስቸኳይ በእነዚህም ላይ እንደ ኢኮኖሚው አብዮት ያለ የሌቦች መንጥር አብዮት ይከፈት፡፡

በዚህ ነጥብ ላይ በተለይ ለፕሬዚዳንት ለማ የማነሳው ነጥብ አለኝ፡፡ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የአዳማ ከተማ ነዋሪ ነው፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኦሮሚያ ክልል የከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮ ኃላፊ በነበሩ ጊዜ፣ ፕሬዚዳንት ለማ ከለውጥ ፈላጊ ካቢኔዎች ጋር መክረውና ወስነው የኦሮሚያን ከተሞች ለማልማትና ከተሞችን ለመለወጥ መጀመሪያ ለውጡን ከአዳማ ከተማ እንጀምር ብለን ወስነናል ብለው ነበር፡፡ ይህን ካሉ በኋላ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዳማ ከተማ ከንቲባ ሆነው መሾማቸውንና አዳዲስ የካቢኔ አባላቶቻቸውንም በቀን ኅዳር 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በገልማ አባገዳ አዳራሽ ለተሰበሰበው ሕዝብ ሲያስተዋውቁ ‹‹አዳማ ከተማን ለመለወጥ፣ የቱሪዝምና የኢንዱስትሪ ከተማ እንድትሆን ለማድረግ መንግሥትና ሕዝብ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?›› በሚል ርዕስ ሕዝቡን አወያይተዋል፡፡

– የውይይት ርዕሱን ሲተነትኑም፡-

  • ‹‹ለዚህ ለውጥ የሕዝብ ድርሻ ምን ይሁን? የመንግሥትስ ድርሻ ምንድነው? እንደሌሎች ከተሞች አዳማም ዕድገት ማሳየቷ ባይካድም፣ ‹‹የስምጥ ሸለቆ ዕንቁ፤›› ከመባል ያለፈ ማደግ የሚገባትን ያህል እንዳላደገች ገልጸዋል፡፡ አዳማ ከተማ ሹመኞች እንደ ሸሚዝ ከሚለዋወጡባት በስተቀር ብዙ ለውጥ እንዳላሳየች ግልጽ ነው፡፡ ‹‹የኦሮሚያን ከተሞች ለመለወጥ መጀመሪያ አዳማን መለወጥ ያስፈልጋል፤›› ካሉ በኋላ፣ ለውጥ ለማምጣት ፍላጎት መኖር ወይም ውይይት ማድረግና መወሰን ብቻ ሳይሆን፣ ተግባር አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑንም ተናግረው ነበር፡፡ አዳማ በአጭር ጊዜ የመለወጥ ዕድል ያላት ከተማ ስለመሆንዋ ሲያብራሩም ከአዲስ አበባ ቀጥላ የማደግ ዕድሏ ከፍተኛ ስለመሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ጠቅሰዋል፡፡
  • የንግድ ማዕከል ወይም ምንጭ በመሆን ማገልገል እንደምትችል፣
  • የወደብ ከተማ በመሆኗ ቶሎ የማደግ ሰፊ ዕድል እንዳላት፣
  • ከተማዋን መለወጥ የሚቻለው ሕዝብና መንግሥት ተቆራኝተው ሲሠራ ብቻ እንደሆነና ለሕዝቡም አዳማ ቤታችን ነች ማለት የሚያስችሉትን አገልግሎቶች በማስፋፋት ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ሥርዓት ስትዘረጋ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
  • መልካም አስተዳደር፣ ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት ተፈጥሮ፣ ሁሉም በአቅሙ ሠርቶ ራሱንም ሆነ ከተማዋን መለወጥና ማሳደግ የሚችልባት ከተማ ሆና መገኘት እንዳለባት፣ ለዚህም ለውጥ የባህል አብዮት ተካሄዶ ዕድገትና መለወጥ በሌብነትና በማጭበርበር ሳይሆን፣ በሥራና በችሎታ ብቻ እንደሆነ የሚያምን ትውልድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንቱ አብራርተው ነበር፡፡ ይህንን ማድረግ ከባድ በመሆኑ እያነዳንዱ ሰው በራሱ ላይ አብዮት ማካሄድ እንደሚያስፈልገውም ጠንካራ መመሪያ ሰጥተዋል፡፡

ክቡርነትዎ የወ/ሮ አዳነችን ከንቲባነትና ካቢኔያቸውን ለሕዝብ ሲያስተዋውቁ ‹‹ከአሁን በኋላ በፊት እንደሚደረገው አመራሮችን በደብዳቤ መሾም ሳይሆን፣ ከሕዝብ ጋር በመማከርና በማስተዋወቅ እንሠራለን፤›› በማለት ስለከንቲባዋና ካቢኔያቸው ብቃትና የትምህርት ዝግጅት ጠቅሰዋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከንቲባና የትምህርት ዝግጅት በሕግ ሙያ የማስትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ አቶ ካሳሁን ጎንፌ ምክትል ከንቲባ የትምህርት ዝግጅት የማስትሬት ዲግሪ (አሁን የፌደራል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሚኒስትር ዴኤታ)፡፡ አቶ ጁንዲ አሊይ የከተማዋ ሥራ አስኪያጅ፡፡ የትምህርት ዝግጅት የማስትሬት ዲግሪ፡፡ አቶ ቦንሳ ባይሳ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፡፡ የትምህርት ዝግጅት የማስትሬት ዲግሪ፡፡ አቶ አብዱልጀሊል ሙስጠፋ የመሬት አስተዳደር ኃላፊ መሆናቸውን ለሕዝቡ አስተዋውቀዋል፡፡

‹‹በአዳማ ላይ ከንቲባ እንዳይበረክትና እንደሸሚዝ እንዲለዋወጥ ያደረገው የተሾሙት ሰዎች ስላልተማሩ ሳይሆን፣ ሀሺሽ በመስጠት የሚያደነዝዙ ኃይሎች በከተማው ውስጥ ስላሉ ነው፡፡ የአሁኑ መሪዎችን በእናንተ ፊት እመክራለሁ፡፡ ራሳቸውን ይጠብቁ፡፡ አመራሮችንም የሚያሳስቱ ያቁሙ፤›› በማለት ካስጠነቀቁ በኋላ መድረኩን ከእርሶ ጋር ይመሩ የነበሩት  የክልሉ መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንትም፣ ‹‹ከተማዋን በፕላን እንድትመራ እናደርጋለን፣ በከተማዋ ውስጥ በመሬት ላይ እሮሮ፣ በመሠረተ ልማት ላይ እሮሮ አለ፡፡ ይህንን ለመለወጥ በቁርጠኝነት በመሥራት እሮሮን ወደ ቀረርቶ እንለውጣለን፤›› ብለው ነበር፡፡ ባለሀብቶችም ራሳቸውን ማበልፀግ ብቻ ሳይሆን፣ ለሥራ አጥ ወጣቶችም ሥራ መፍጠር እንደሚገባቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ ሐሳብ ተስፋን የሚያለመልምና ለሥራ የሚያነሳሳ በመሆኑ፣ ተስፋን ሰንቀን ወደ የቤታችን ብንመለስም ወ/ሮ አዳነችና ካቢኔያቸው ለሕዝቡ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ሳያሳዩ እንደተባለውም ካቢኔያቸውን እንደሸሚዝ ሲቀያይሩ ቆይተዋል፡፡ ሌላው ቢቀር ድልድይ ሳይሠራ ሠርተናል በማለት ከከተማው አስተዳደር አምስት ሚሊዮን ብር ስለዘረፉት አካላት ለኦቢኤን ቴሌቪዥን መግለጫ ከመስጠት ባለፈ ለሕግ እንዲቀርቡ ሳያደርጉ ለማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት መሾማቸው ሕዝቡ በለውጡ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት እያደረገ ስለሆነ መፈተሽ አለበት፡፡

ክቡር ፕሬዚዳንት በገልማ አባገዳ የስብሰባ ማዕከል ስለአዳማ ከተማ መለወጥ ከሕዝቡ ጋር ባደረጉት ውይይትና ባነሱት ሐሳብ መሠረት፣ ከንቲባዋ ምን ጥሩ ነገር ሠሩ፣ ማስረጃ አልባ ለሆኑ የመሬት ይዞታዎች፣ የመሠረተ ልማት ችግሮችን በተመለከተ ስላለው እሮሮ ምን ሠርተው ነው በአጭር ጊዜ ወደ ከፍተኛ የሥልጣን ዕርከን የተሸጋገሩት? የሚለውን ሕዝቡ እያነሳ ቅሬታውን እየገለጸ ስለሆነ፣ ለሕዝቡ ቅሬታ ትኩረት ይሰጠው፡፡ በተጨማሪም የተከበሩ ፕሬዚዳንት በአባ ገዳ የስብሰባ ማዕከል ለአዳማ ከተማ ሕዝብ በሰጡት ተስፋ መሠረት እሮሮ ወደ ቀረርቶ መለወጡ ቀርቶ ከላይ የፈነጠቀው የለውጥ እንቅስቃሴው ወደታች መውረድ እንዲችል ይሠራ፡፡

ከወ/ሮ አዳነች ካቢኔ ጀምሮ የሕግ የበላይነት እየተጣሰ የከንቲባው ኮሚቴ የመንግሥቱን ሕግ ወደጎን በመተው በሕዝብ ላይ ሕገወጥ ውሳኔ እያስተላለፈ ነው፡፡ እንደ ምሳሌ ለማንሳት አንድ ጉዳይ ብጠቅስ ‹‹አምባገነን›› የተባለው የደርግ መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የመንግሥት ሠራተኞች በተለይም የአዳማ ትራክተር መገጣጠሚያ ፋብሪካ ሠራተኞች በአነስተኛ ወጪ ሠርቶ ያከራያቸውን የቁጠባ ቤቶች፣ ከ30 ዓመታት በላይ እየኖሩበት፣ በጡረታም ሲገለሉም አሁንም እዚያው ለሚገኙ ከ400 በላይ በሚሆኑ አባወራዎች ላይ በአንድ ጊዜ ከ700 በመቶ እስከ 1,554 በመቶ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ባወጣው መመሪያ ቁጥር 10/2006 መሠረት የተጣለው ሕግን በመጣስ ነው፡፡ ይህ ደግሞ አዳማ ከተማ አሁንም እንደ በፊቱ በመልካም አስተዳደር ዕጦት እየተንገላታ የሚገኝ ሕዝብ የሚኖርባት ለመሆኗ ጉልህ ማስረጃ ነው፡፡

 የምንመኛትን፣ የምንታገልላትንና ዜጎቿ በእኩልነትና በነፃነት ሠርተው የሚኖሩባትን አዲሲቷን ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ከላይ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ወደታች በማውረድ በአሁኑ ጊዜ የለውጥ ደጋፊና ፈላጊ በመምሰል ሕዝብና መንግሥትን እያቃቃሩ ያሉ የየከተማው አስተዳድርና የየቀበሌው መሬት ኤጀንሲ፣ የየቀበሌው አስተዳደር ካቢኔ፣ ቀጣናና ጎጥ የተባሉ አካላት ለውጡን እያበላሹ ስለሆነ ይታዩ፡፡ እነዚህን ጥቃቅን ቀበሮዎች ሕዝቡ ማጋለጥ እንዲችል በቀበሌ ደረጃ የውክልና ዴሞክራሲ አሠራር ቀርቶ፣ ከአሥር ዓመት በፊት እንደነበረው የቀበሌው አመራርና ሕዝብ በየሦስት ወሩ ቀጥተኛ የጋራ ውይይት የሚያደርግበት የጋራ ስብሰባና ግምገማ አሠራር ቢኖር፡፡

ሕዝቡ መሪዎቹን የሚቆጣጠርበትና ካጠፉም የሚሽርበት፣ ካለሙም የሚሸልምበትና አብሮ የሚጓዝበት፣ በሥራ ዕቅዱ መሠረት ምን እንደተሠራ፣ ምን ችግር እንደተፈጠረ፣ ምን ልማት እንደታቀደ ሕዝብ አውቆ አጥፊዎቹን ማጅራታቸውን እየያዘ ለሕግ በማቅረብ ለለውጡ የድርሻውን ሚና እንዲጫወት ካልተደረገ በስተቀር፣ አሁንም በፓርቲ አባልነት ደብተር ከአንድ ቀበሌ ወደሌላ ቀበሌ፣ ከአንድ ወረዳ ወደ ሌላ ወረዳ፣ ከአንድ ዞን ወደሌላ ዞን፣ ጥቃቅን ቀበሮዎችንና የኦሮሚያ የቀን ጅቦች ቡችሎችን በዚያው በፓርቲው ቀለበት ውስጥ ሸሽጎ ማሽከርከሩ ለለውጡ አደጋ ነው፡፡ በለውጡ ኃይሎች ላይም ጥርጣሬንና ትዝብትን እየፈጠረ ሕዝቡን ለቅሬታ የሚያነሳሳ ስለሆነ በአዳማ ላይ አስቸኳይ ፍተሻ ይደረግ፡፡ የአዳማ ከተማ መለወጥ ለሌሎች ከተሞች መለወጥ እንደሞዴል እንጠቀማለን ያሉትን ያስታውሱ፡፡

የአዳማ ከተማ መሬት በወረራ እንዲያዝ፣ ሕገወጥ ግንባታዎች እንዲያስፋፉ፣ ሕዝብን በመዝረፍና በማዘረፍ ከአቅማቸው በላይ ሀብት ያካበቱ የኦሮሚያ የቀን ጅቦች መቼ ለፍርድ ይቀርባሉ እያለ ሕዝብ ሲጠብቃቸው የነበሩ ቁንጮ ዘራፊዎችን  ለምሥራቅ ሀረርጌዋ አወዳይ ከተማና ወደ ለፌዴራሉ መንግሥት መሥሪያ ቤት መሾማቸው በምን መለኪያ ነው? እያለ የአዳማ ሕዝብ እየጠየቀ ስለሆነ ይፈትሹት፡፡

ስለዚህ ቶሎ ማስተካከያ ተደርጎ ካልታረመ፣ አሁንም እንደበፊቱ አዳማ የምትተዳደረው በሦስት መንግሥታት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይኸውም የኢሕአዴድ መንግሥት፣ የደላላ መንግሥትና በኢንቨስትመንት ስም በሚሠሩ ዘራፊ ባለሀብቶች እየተዳደረች ነው በሚል ሕዝብ እምነት እንዳያጣ የተፋጠነ ዕርምጃ ይወሰድ፡፡

(ከራጂ አዳማ ቦሰት፣ ከአዳማ ከተማ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...