Thursday, May 30, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

በሕግ አምላክከተዛነፉት የመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙነቶች

ከተዛነፉት የመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙነቶች

ቀን:

በውብሸት ሙላት

ባለፈው ሳምንት በዚሁ ዓምድ ሥር ስለመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙት ቀረበው ጽሑፍ ላይ መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማትና ከአማኞቹ ጋር ያለውን ግንኙነት አፈጻጸሙን መሠረት ባደረገ መልኩ ቀጣይ ክፍል እንዳለው ተገልጿል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረትም ይኼው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ጽሑፍ አማኞች እምነታቸውን ለመግለጽና ለማስፋፋት ካለቸው መብት ብሎም የመንግሥት ግዴታ ላይ የተቀነበበ ነው፡፡ ለዚያውም ሃይማኖትን በሚዲያ ማስፋፋት ላይ፡፡

የሃይማኖት (የእምነት) ነፃነት መቻቻልን ይጠይቃል፡፡ መቻቻሉ ደረብረብ ያሉ ፈርጆች አሉት፡፡ መንግሥትና ሃይማኖት መቻቻል አለባቸው፡፡ አንዱ የሃይማኖት ተቋም ከሌላው የሃይማኖት ተቋም ሊሆን ይችላል፡፡ አማኞች ደግሞ እርስ በራሳቸው መቻቻል ያለባቸው መሆኑን ይይዛል፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትም በዚሁ ቅኝት መቻቻል እንዲኖር ዋስትና ሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ላይ ከተደነገገው በተቃራኒው በመጓዝ መንግሥትና ሃይማኖት ሳይቻቻሉ፣ መንግሥት በሃይማኖት ነፃነትን አልችል ሲል ተስተውሏል፡፡ አንዳንዴም የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጽም ተስተውሏል፡፡ ይህን ፈጻሚዎቹ በመንግሥት መዋቅር በተለያየ እርከን ላይ ያሉ መንግሥታዊ አካል ናቸው፡፡ የክልል መንግሥታት፣ የወረዳ፣ የፌዴራል ወይም የቀበሌም ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አስረጂዎችን ዝቅ ስንል እንመለስባቸዋለን፡፡

- Advertisement -

የእምነት ነፃነት ህሊናዊ (ውስጣዊ) ስለሆነ ለክልከላም ለመጣስም ብዙም አይመችም፡፡ እንግዲህ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27 ላይ የእምነት ነፃነትን ነገር መልክና ቅርፅ ሰጥቶታል፡፡ በመሆኑም ማንም ሰው የመሰለውን እምነት የመያዝ መብት አለው፡፡  በህሊናው የያዘውን እምነትም የመግለጽም መብት ከሌለው የመጀመርያው ከንቱ ይሆናል፡፡ በመቀጠልም ሐሳብን በነፃነት ከመግለጽ ጋር በተያያዘም ሃይማኖቱን በማስፋፋት ሌሎች እንዲከተሉት የማድረግ መብትንም ይይዛል፡፡ በኃይል እንዲያምን ወይም እንዳያምን ወይም እንዳያመልክ ማሰናከልንም ይኼው አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ ዋስትና ሰጥቶታል፡፡ የእምነት ነፃነት በሆነ (በማናቸውም) እምነትም አለማመንም ይጨምራል፡፡ በእምነቱ መሠረት ሃይማኖቱ (እምነቱ) የሚጠይቀውን መተግበርና መግለጽም እንዲሁ መብት ናቸው፡፡ እነዚህን መብቶች እንዲከበሩ፣ አስፈላጊ የሆኑትን ሥርዓት ማበጀት ደግሞ የሕግ ሚና ነው፡፡ በሕግ የወጡትን ማስከበር ደግሞ በዋናነት የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ የአንዱን መብት ሌላው እንዳይጥስ ጥበቃ ማድረግ መንግሥት ራሱም ከመጣስ በመቆጠብ ማክበር ይጠበቅበታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ያለውን ተነፃፃሪ ግዴታና ሥልጣን እንዲሁም ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ሃይማኖትን እንደ አንድ የፖለቲካ መሣሪያ በመጠቀም ከሌላ ሃይማኖት አማኞች ጋር ግጭትና ጦርነት ሊገባ ይችላል፡፡ የተለያዩ ሰበቦችን በማዘጋት አማኞችን ሊጎዳ፣ እንዲጎዱ ሊያደርግ፣ ሲጎዱ ጥበቃ ባለማድረግ ኃላፊነቱን ሳይወጣ ሊቀር ይችላል፡፡ ራሱም ጉዳት ሊፈጽም ይችላል፡፡ በቅርቡ በሶማሌ ክልል የተፈጸመው እነዚህን ሁሉ ያካተተ ነው ማለት ይችላል፡፡ በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበረው የክልሉ መንግሥት የክርስትና እምነት ተከታዮችና ቤተ ክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ከመንግሥት ግዴታን ካለመወጣት አልፎ ሄዶ በተለያዩ መዋቅሮቹ አማካይነት ራሱ ፈጻሚ ሆኗል፡፡ ይህ ደግሞ በቅርቡ የክልሉ ገዥ ፓርቲ ያወጣው መግለጫ ዋቢ ነው፡፡ በአጭሩ የመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙነት በዚህ መልክ ከሕግ ውጭ መንግሥት መጣሱ ተስተውሏል፡፡

ወደ ሌላ አስረጂ እንሸጋገር፡፡ አሁንም መንግሥት የእምነት ነፃነትን ከማስጠበቅ በመዛነፍ የፈጸመውን ለማስረዳት ነው፡፡ ማንም አማኝ ሃይማኖቱን የማስፋፋት መብት እንዳለው ሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጂ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማት የብሮድካስት ባለቤት እንዳይሆኑ በአዋጅ ከልክሏል፡፡ በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማት ደግሞ የብሮድካስት አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ ሊያገኙ አይችሉም በሕግ ስለተከለከለ፡፡ እርግጥ ነው በተግባር ግን በርካታ የሃይማኖት ተቋማት የቴሌቪዥንና የሬዲዮ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ለሥርጭቱ የሚሆኑት ቀረፃዎችም በአገር ውስጥ ይዘጋጃሉ፡፡ በአገር ውስጥ ተዘጋጅተው ከሌላ አገር ተሠራጭተው ተመልሰው ለኢትዮጵያውያን ይቀርባሉ፡፡ ሕጉ በአገር ውስጥ ፈቃድ በማውጣት የብሮድካስት አገልግሎት መስጠትን ቢከለክልም ዞሮ ዞሮ ሥርጭቱ ግን አለ፡፡ ከዚህ አንፃር ሕጉ ማሳካት የፈለገውን ግብ አላሳካም፡፡ በቁጥር ሲሰላም ሃይማኖታዊ ካልሆኑት ይበልጣሉ፡፡ ሕጉና እየሆነ ያለው እዚህና እዚያ ማለት ነው፡፡

ማንም ሰው የራሱን ሃይማኖትን የማስፋፋት መብቱ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡ በምን ዓይነት ሥልትና በምን ዓይነት የመገናኛ ዘዴ ማስፋት እንደሚቻልና እንደማይቻል ግን አልተገለጸም፡፡ ስለሆነም በማናቸውም ዓይነት የመገናኛ ዘዴም ጭምር ማስፋፋት እንደተፈቀደ ይቆጠራል፡፡ ካልተከለከለ ተፈቅዷል አይደል የሚባለው? ይሁን እንጂ የብሮድካስት አዋጁ የሃይማኖት ተቋማት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ማቋቋም እንዳልተፈቀደላቸው ደንግጓል፡፡ ይህንን በብሮድካስት ማስፋፋትን ክልከላ  ከየት የመጣ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ማለትም ሕገ መንግሥታዊ መሠረቱ ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ማንም እምነት ያለው ሰው እምነቱን የመግለጽ መብት ቢኖረው  ገደቦችም እንዳሉበት ይታወቃል፡፡ ፍፁም ገደብ አልባ መብት ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ ሆኖም እነዚህ እምነትን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ የሚኖሩ ገደቦችም አስቀድመው በሕግ የወጡና የታወቁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሕግ ለመገደብ ግን አሁንም ሌሎች ምክንያቶች አሉ፡፡ ምክንያቹም የሕዝብን ደኅንነት፣ ሰላም፣ ጤና፣ ትምህርት፣ የሕዝብን ሞራል፣ የግለሰቦችን መሠረታዊ መብትና ነፃነት እንዲሁም የመንግሥትን ከሃይማኖት ገለልተኛ መሆንን የሚጥሱ ከሆኑ ብቻ ነው በሕግ ሊታገዱ የሚችሉት፡፡ መስገድና መፀለይ ወዘተ. ሊከለከሉ የሚችሉት አማኙ በመስገዱ ወይም በመፀለዩ ምክንያት የሕዝብ ደኅነነት ከታወከ ወይም የሚያውክ ከሆነ፣ ሰላምን የሚነሳ ለጤናና ለትምህርት አደናቃፊ አዋኪ ከሆነ መስገድ ወይም መፀለይ ሊከለከል ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የአንዱ መስገድ ወይም ፀሎት ማድረግ የሌሎች ሰዎችን መሠረታዊ መብትና ነፃነት ከተጋፋ እንዲሁም ለመገደብ የሚያስችል ሕግ ሊወጣ ይችላል፡፡ ከዚህ አልፎም መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር በሚኖረው ግንኙነት ላይ ገለልተኛ እንዳይሆን የሚከለክል አለበለዚያ አድልኦን የሚስከትል ከሆነ መስገዱ ወይም መፀለዩ ሊገደብ ይችላል ማለት ነው፡፡

በሌላ ምሳሌ ለማስረዳት አንድ የሃይማኖት መምህር ዋና ሥራው ማስተማርና ፀሎት ማድረግ  ቢሆን ይኼንን የፀሎትና የማስተማሩ ተግባር ከሚያከናውንብት መንገዶች አንዱ በሚዲያ ቢሆን በሚዲያ ማድረግን (መግለጽ) የሚከለከለው ከላይ የጠቀስናቸው ምክንያቶች መሆን አለባቸው፡፡ ከእነዚህ ውጭ ከሆነ ሕገ መንግሥቱን መቃረን ይመጣል፡፡ ለነገሩ ሌላም ሕገ መንግሥታዊ መከራከሪያ አለ፡፡ እምነትን መግለጽ ሐሳብን መግለጽ በመሆኑ፣ ያው ሃይማኖታዊ ሐሳብንም ይጨምራል፡፡ ከዚህ አንፃር በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(6) ላይ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ እንደተገለጸው ሐሳብን በፕሬስና በማናቸውም መገናኛ ብዙኃን ማንኛውም ሰው ሲገልጽ የሐሳቡ ይዘት ምንም ይሁን ምን፣ ሐሳቡ በመገለጹ የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ መከልከል እንደማይቻል ተገልጿል፡፡ የብሮድካስት አገልግሎት ሰጪዎችን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በሕግ የሚገደብባቸው ‹የወጣቶችን ደኅንነት የሚያናጉ፣ የግለሰብን መብት የሚጥሱና ሰብዓዊ ክብርን  የሚነኩ የአደባባይ መግለጫ ማድረግ፣ የጦርነት ቅስቀሳ ማድረግ› ብቻ ናቸው፡፡

ከላይ ከተገለጹት አራት መሠረታዊ ገደቦች በስተቀር በአገሪቱ በየትኛውም ደረጃ ላይ የሚገኝ ሕግ የማውጣት ሥልጣን የተሰጠው አካል ይዘቱን መሠረት ያደረገ ሐሳብን በነፃነት መግለጽን የሚገድብ ሕግ ማውጣት አይችልም፡፡ አራቱ በተራቸው ወደ በርካታ ዝርዝር ክልከላ ሊመነዘሩ ይችላሉ፡፡ ሲመነዘሩ ቢኖሩም ግን የግለሰብን መብትና ሰብዓዊ ክብር፣ እንደ ቡድን የወጣቶች አስተዳደግን የሚመለከት፣ እንደ ተቋም ደግሞ ከጦርነት ቅስቀሳን የሚመለከቱ ብቻ መሆን አለባቸው፡፡ ሕገ መንግሥቱ የሚተላለፈው ሐሳብ የሚያስከትለውን ውጤት በማሰብ የሐሳብን ነፃነት በሕግ መገደብ እንደማይቻል ይገልጻል፡፡ በመሆኑም በኅትመትም ይሁን በሌላ መንገድ የሚገለጽ ሐሳብ መንግሥት ላይ አመኔታ እንዳይኖር ወዘተ. በማለት ወንጀል ማድረግን ሕገ መንግሥቱ ፈጽሞ አይፈቅድም፡፡ ገደቦቹ እነዚህ ከሆኑ የሃይማኖት ተቋማት በሬዲዮና በቴሌቪዥን ማስተማርን እምነቱን ማስፋፋትን መከልከሉ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚስማማ ነው ብሎ ማስረዳት ወይም መከራከር አዳጋች ነው፡፡

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከሚገደብባቸው ሁኔታዎች ውስጥ የትኛውም ዓለም አቀፍ ሰነድም ይሁን ብሔራዊ ሕግጋት ከሚጋሯቸው አንዱ የጦርነት ፕሮፓጋንዳ መንዛት ነው፡፡ የጦርነቱ ፕሮፓጋንዳው የእርስ በርስም ሊሆን ይችላል፡፡ በአንድ አገር ውስጥ በሚኖሩ  ነገር ግን በተለያዩ ብሔሮች፣ ጎሳዎችና ሃይማኖተኞች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ያለማቋረጥ ማነሳሳትም እንዲሁ ፕሮፓጋንዳ ነው፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት የጦርነት ፕሮፓጋንዳን አያካትትም ማለት ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ትምህርቱ ወይም በማንኛውም ሚዲያ ቢሰጥ የጦርነት ፕሮፓጋንዳ ከሆነ ሕገ መንግሥቱ ሊታገድ እንደሚችል አስቀድሞ መሥፈርት በማድረግ አስቀምጦታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የብሮድካት አገልግሎት አዋጁ ቁጥር 533/1999 ገደብ እንዲሆን ያስቀመጠው ሕዝብን ከሕዝብ ወይም አንድ ብሔርን ከሌላ የሚያጋጭ እንዲሁም ጦርነትን የሚቀሰቅስ ይዘት ያለውን ፕሮግራም ማስተላለፍን ነው፡፡ እዚህም ልብ ልነለው የሚገባው ጉዳይ የሚተላለፈው ወይም የሚሠራጨው ፕሮግራም ይዘቱም ይሁን ምንጩ ትክክልና እውነት መሆን ወይም አለመሆን መለኪያ አይደለም፡፡ የተከለከለው፣ የሚተላለፈው ፕሮግራም አንድን ብሔር ከሌላ ሊያጋጭ የመቻሉ ጉዳይ ነው፡፡ እውነት ሆኖም የሚያጋጭ ከሆነ፣ ትክክለኛ መረጃም ሆኖ የእርስ በርስም ይሁን ከሌላ አገር ጋር ጦርነትን የሚቀሰቅስ ከሆነ ብሮድካስተሮች ማሠራጨት አይችሉም፡፡ እነዚህ ክልከላዎች የተቀመጡት አዋጁ አንቀጽ 30(4) ላይ ነው፡፡

አንዳንድ ሰዎች ለሃይማኖት ተቋማት የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ባለቤት እንዲሆኑ መፍቀድ ለብሔራዊ ደኅንነት ግጭት መነሻ እንዳይሆኑ ከመሥጋት ነው የሚሉም አሉ፡፡ ነገር ግን ከላይ እንደተገለጸው ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ በመሠራጭት ላይ ናቸው፡፡ እስካሁን የተፈራውን ሥጋትም አላስከተሉም፡፡ በዚያ ላይ ብሔር መሠረት ያደረጉ የማኅበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ የክልል ቴሌቪዥንና ሬዲዮም ካለ ከብሔር ይልቅ እንደውም ሃይማኖት የተሻለ ሥነ ምግባር ሊኖራቸው እንደሚችል ቀላል ነው፡፡ ባለቤት ባይሆኑም አንዳንድ ጊዜ መንግሥት ራሱ ለአንዳንድ ሃይማኖቶች ቀጥታ ሥርጭት ሁሉ እንደሚፈቀድና የተለያዩ ሃይማኖታዊ ተግባራት እንደሚተላለፉ ይታወቃል፡፡ ይህ ከሆነ፣ ሃይማኖታዊ ሁነቶች አልፎ አልፎም ቢሆን በመንግሥት ጣቢያ ከተላለፉ የራሳቸው ኑሯቸው ቢያሠራጩ ምንም የሚገድብ ተጠያቂነት አናገኝም፡፡ የምናገኘው የሚከለክል ሕግ ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ አንዱ መንግሥት ሃይማኖትን በሚመለከት ሥልጣኑን በብቸኝነት ወደ ራሱ እንዲያመዝን አድርጎ ሃይማኖት ላይ ከሕገ መንግሥቱ የራቀ ሕግ አውጥቷል፡፡ ይህ ሕግ በአንድ በኩል ሃይማኖትን እንደ ተቋም የጎዳ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተለያዩ እምነት ተከታዮችን በሕገ መንግሥቱ ዕውቅናና ጥበቃ የተሰጠውን መብታቸውን አቀጭጯል፡፡ ጥሷልም፡፡ ማክበርና መጠበቅ ሲገባው ተቃራኒውን ተጓዘ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ማሻሻያ ለማድረግ ቃል ከገባባቸው ሕግጋት አንዱ ሚዲያን የሚመለከቱ ሕግጋትን ስለሆነ የብሮድካስት አዋጁን ቢፈትሹት ከላይ የተገለጹትን ተቃርኖዎች መፍታት ይችላሉ፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...