Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉለውጡ በተሟላ ውህድ ፕሮግራምና ዕቅድ ይመራ

ለውጡ በተሟላ ውህድ ፕሮግራምና ዕቅድ ይመራ

ቀን:

በአበበ ተክለ ሃይማኖት (ሜጀር ጄኔራል)

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የሽግግር ሒደት ተያይዛዋለች፡፡ ይህ የለውጥ ሽግግር እንዳይቀለበስ የሽግግር ምንነትና ባህሪያት ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በሦስተኛው የዴሞክራሲ ማዕበል የተሸጋገሩ አገሮች ተሞክሮ መቅስምም ግድ ይላል፡፡ ጽሑፉ የኢትዮጵያ ልዩና ውስብስብ ሽግግር ለማስገንዘብ ይሞክራል፡፡ የመጀመርያ ሽግግር ጥፋት እንዳይደግም የነበረውን መሠረታዊ ጥንካሬና ድክመት መገምገም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የመጀመርያው ሽግግር በበጎም ይሁን በመጥፎ ግብዓት ስለሆነ፡፡ ኢትዮጵያ ቤተ ሙከራ ለመሆን ጊዜውም ሁኔታውም አልፈቀደላትም፡፡ ነገር ግን ካለፈው መማር ደግሞ የግድ ይላል፡፡ በመጨረሻም የሚታየኝን የለውጥ ፕሮግራም እንደ መነሻ ይቀርባል፡፡ ታሳቢ የሚደረገው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ይፈልጋሉ ነው፡፡ ይህ እውን ሊሆን የሚችለው በዳበረ ፖለቲካዊና ዴሞክራሲ ከሚልም ነው፡፡

የሽግግር ምንነትና ባህሪያት

የምዕራብ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ አሁን ወዳሉበት ሁኔታ ለመድረስ ከሁለት ምዕተ ዓመታት በላይ ፈጅቶባቸዋል፡፡ ሆኖም ሃንቲንግተን በዓለም ደረጃ መጽሐፉ እስኪታተም (1991) ድረስ ሦስት የዴሞክራሲ ማዕበሎች እንዳሉና የመጀመርያና ሁለተኛ ማዕበሎች የኋልዮሽ ጉዞም እንደገጠማቸው ያትታል፡፡

በሰሜን አሜሪካና በአውሮፓ እየታየ ያለው መረር የለቀቀ ብሔርተኝነት (Ultra Nationalism, ወይም ፉኩያማ የሚለው ፖለቲካዊ መበስበስ (Political Decay) የሦስተኛው የኋልዮሽ ጉዞ ምልክት ይሆን እንዴ? ሸግግር ሲባል በአንድ ፖለቲካዊ ሥርዓት (Regime) እና በሌላ ፖለቲካዊ ሥርዓት የሚገኝ ክስተት ነው፡፡ ከአምባገነናዊ ወይም ከፊል አምባገነናዊ ሥርዓት ወደ ሌላና የማይታወቅ (Something Else) የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡ ውጤቱ ሕዝቦችና መሪዎቻቸው የሽግግር ባህሪ ተገነዝበው ግባቸው አነጥረው ሳይሸበሩ በሰከነ መንገድ ከተንቀሳቀሱ ዴሞክራሲ ማደላደል ሊሆን ይችላል፡፡ ካልሆነ ግን ወደ ሌላ የተሸፈነ ከፊል አምባገነንነት ወይም ወደ ፍፁም አምባገነንነትም ሊያደርስን ይችላል፡፡ ሽግግር ከምናውቀው ወደ ምናልመው የሚደረግ በመሆኑና አሮጌ አስተሳሰቦች አደረጃጀቶችና አሠራሮች እያስወገደ፣ አዳዲስ እየተካ የሚሄድ ከፍተኛ ላይ ታች ያለበት እርግጠኛ የማትሆንበት (Uncertainity) ግራ መጋባት የሚበዛባት ከፍተኛ ስህተቶች የሚፈጸምበትና ፅንፈኛ አመለካከት የሚከሰትበም ጭምር ነው፡፡ ድንገተኝነት (Surprises) የበዛበት፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች አጣብቂኝ (Dilemma) የሚገቡበት በመሆኑ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሽግግሩ ስለሚከሰትበት ሁኔታና ሒደት (Huntington 1991: 114-115) “Transformation Transplacement and Replacement” ብሎ ይገልጸዋል፡፡ ለውጥ (Transformation) ማለት በሥልጣን ላይ ያሉ ልሂቃን ዴሞክራሲን ለማምጣት መሪነቱን ሲጨብጡ ሲሆን፣ መተላለፊያ (Tranceplacement) የሚባለው ደግሞ በሥልጣን ላይ ያሉትና ተቃዋሚ ልሂቃን በጋራ ሆነው ለውጡን ሲያመጡት ነው፡፡ መተካት (Replacement) ደግሞ አምባገነናዊ መንግሥት ሲሸነፍ ወይም ሲወድቅና በተቃዋሚ ልሂቃን መሪነት ወደ ዴሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር ሲጀምር ነው፡፡ እንደ ሃንቲንግተን ገለጻ ከሦስቱም መንገዶች ሽግግሩ የሚከሰትበት ሁኔታ በመተካት (Replacement) የሚደረገው ሽግግር ያልተለመደ (በጥናቱ ከተካተቱ 35 አገሮች በስድስቱ ብቻ የተከሰተ) ሲሆን፣ ዴሞክራሲን ለማጠናከር የሚደረገው ሽግግር ከባድ መሆኑን ያሰምርበታል፡፡

የኮሪያ፣ የስፔንና የአርጀንቲና ሽግግር

የኢትዮዽያ ሽግግር ከወቅቱ አኳያ ከሦስተኛው ዴሞክራታይዜሽን ማዕበል የሚመደብ ሊሆን ይችላል፡፡ የተወሰነ የሽግግር ሥዕል ለመያዝ ይረዳ ዘንድ በሦስተኛው  ዴሞክራታይዜሽን ማዕበል ከተሸጋገሩት ሦሰት አገሮች ማለት ደቡብ ኮሪያ ከእስያ፣ ስፔን ከደቡብ አውሮፓና አርጀንቲና ከደቡብ አሜሪካ መዳሰስ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡

ዴሞክራቲክ ኮሪያ (ደቡብ) ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጣች በኋላ እ.ኤ.አ በ1948 የመጀመርያ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አካሄደች፡፡ ሕገ መንግሥትም አፀደቀች፡፡ ነፃና ዴሞክራሲ ተባለች፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1950 እስከ 53 ኃያላን መንግሥታት ለሁለት ተከፍለው በየፊናቸው እየደገፉ የሁለቱ ኮሪያዎች አስከፊ ጦርነት ተካሄደ፡፡ በደረሰው ውድመት ምክንያት ደቡብ ኮሪያ በዓለም የመጨረሻ ደሃ አገር ተባለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ1960 የተጭበረበር ምርጫ ተካሄደ፡፡ ከእንድ ዓመት በኋላ መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶ በወታደራዊ ዕዝ ሥር መተዳደር ጀመረች፡፡ በድህነታቸው ምክንያትም በከፍተኛ ቁጭትና አርበኝነት በመነሳሳት ወደፊት ለመጓዝ ፍላጎታቸው ተንተርሶ ወታደራዊ መንግሥቱ በመራው የኢኮኖሚ ተሃድሶ ታዛቢዎች The Miracle on the Hangang River” የተባለለት ዕድገት አስመዘገቡ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ግን የኮሪያ ሕዝብ ለዴሞክራሲዊ መብቱ ከመታገል አላገደውም፡፡ በሕዝቡ ከፍተኛ ጫና እ.ኤ.አ. በ1987 የገዥው ፓርቲ በማጎብደዱ ዴሞክራሲያዊና ቀጥተኛ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተደርጎ ደበብ ኮሪያ እንደገና ወደ ዴሞክራሲያዊ ካምፕ ተቀላቀለች፡፡ እ.ኤ.አ. (1948 እስከ 2018) ባሉት 70 ዓመታት ደቡብ ኮሪያ በጣም የደኸዩ አገሮች ተርታ ወጥታ፣ በዓለም ካሉት ኢኮኖሚያዊ ትላልቅ ቡድን (Economic Powerhouse) ተቀላቀለች፡፡ ዴሞክራሲው ግን በአንዴ ተሠርቶ የማያልቅ በመሆኑ አሁንም የተለያዩ ችግሮች መከሰታቸው አልቀረም፡፡

ስፔን በ19ኛውና በመጀመርያ 20ኛው ክፍለ ዘመናት የግርግር አገር ነበረች፡፡ ጫፍ የያዘ ማኅበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውስ የነበሩበት ወታደራዊ አመጽ የሚደጋገምባት፡ የንግሥና ግጭቶች የበዛባት አገር ነበረች፡፡ ከ1874 እስክ 1923 ዓ.ም. በፓርላሜንታዊ ንጉሣዊ አገዛዝ ሰላምና ብልፅግና እንዲሁም ዴሞክራሲ ለመተግበር ቢሞከርም በመፈንቀለ መንግሥት ከሸፈ፡፡ አምባገነን አገዛዙ ጥልቅ የሆኑ መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ባለመቻሉ ለከፍተኛ ተጋድሎ ወደቀ፡፡ አምባገነኑ አገዛዝ ሁለተኛ ሬፓብሊክ (1931 እስከ 1936 ዓ.ም.) በሚባል የዴሞክራሲ ሙከራ ቢተካም የተረጋጋ ካቢኔ አለመኖር የፓርቲዎች እጅጉን መከፋፍል (Fragmentation) በአይዶሎጂ ዝንፈትና (Polarization) ተግባራዊ የማይሆኑ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተስፋዎች ታክሎበት ሥርዓቱ ተንገዳገደ፡፡ በጄኔራሊ ፍራንኮ በከፊል የተሳካ መፈንቅለ መንግሥት ምክንያት ስፔን ወደ እርስ በርስ ጦርነት (1936 እስከ 1939 ዓ.ም.)  ተዘፈቀች፡፡ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ሕዝቧ ካለቀ በኋላ ፍራንኮ ፍፁም አምባገነናዊ የሆነ መንግሥት መሠረተ፡፡ ከ1960 እስከ 1974 በነበረው ጊዜ ስፔን አይታው የማታውቀው ዕድገት አሰመዘገበች፡፡ በየዓመቱ 6.9 በመቶ ዕድገት ተመዝግቦ የነብስ ወከፍ አማካይ ገቢ (GDP Per Capital) ከ $300 ወደ $3,260 ተመነደገ፡፡ የፈጣን ዕድገቱ ማሳያ ይሆኑ ዘንድ መካከለኛ መደቡ ከጠቅላለ ሕዝቡ 14 በመቶ  የነበረው ወደ 43 በመቶ ሲያድግ በ1960 ዓ.ም. አንድ በመቶ ቤተሰቦች ብቻ ቴሌቪዢን ሲኖራቸው በ1975 ግን 90 በመቶ ነበራቸው፡፡ አስተዳደሩ በቀጣይነት ፕሮፌሽናልና በችሎታ የተመሠረተ እንዲሆን በመደረጉ ለለውጡ እንቅፋት አልሆነም፡፡ ከፍተኛ ትምህርት በእጅጉ ሲስፋፋ የተቃውሞ ማዕከል መሆኑ ግን አልቀረም፡፡

      ከላይ የተገለጹት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች (Transformotion) ለገዥዎች ያልተፈለገ ውስብስብ ፖለቲካዊ ውጤት አስመዘገበ፡፡ በ1973 ዓ.ም. የነበረው የነዳጅ ቀውስ የተሟሟቀውን ዕድገት አቀዘቀዘው፡፡ የተማሪዎችና የላብ አደሮች የተቃውሞ እንቅስቃሴ በረታ፡፡ ብዙ ሌሎች መሠረታዊ ምክንያቶች ቢኖርም፣ የፍራንኮ በ1975 ዓ.ም. መሞት በገዥው መደብ የነበረው መከፋፈል አጦዘው፡፡ በወግ አጥባቂዎችና በለውጥ ፈላጊዎች መካከል ልዩነት ሰፍቶ ለ1975 እስከ 1978 ዓ.ም.  ከላይ ለመጣው ሽግግር ለዴሞክራሲ በር ከፈተ፡፡ ከታች ከሕዝቡ የነበረው ከፍተኛ ጫና ቀጣይነቱ መረጋገጥ ጀመረ፡፡ በ1979 ዓ.ም. በነበረው ሁለተኛ የነዳጅ መሻቀብ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አዲስ ማኅበራዊ ሁከት አስከተለ፡፡ በ1978 እና 1981 ዓ.ም. የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች ቢደረጉም ሥርዓቱ በ1978 ዓ.ም. ሕገ መንግሰት ታጅቦ በተደረገው ምርጫ ተጠናከሮ መቀጠል ችሏል፡፡ በፖሊቲካዊ ልሂቃን ማለት በፖለቲካዊ ፓርቲዎች፣ የላብ አደር ማኅበሮች፣ ሙሁራንና የካቶሊክ ቸርች ጭምር ያደረጉት ውይይትና ድርድር ዴሞክራሲን ከማጠንከር አኳያ ከፍተኛ ሚና ነበረው፡፡

      እንደማናቸውም ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ክስተት የስፔን ዴሞክራሲም ከፍተኛ ተግዳሮት እያጋጠመው ነበር፡፡ በ2008 እስከ 2014 ዓ.ም. ያጋጠመው የተራዘመ ኢኮኖሚያዊ ውድቀት 26 በመቶ ሥራ አጥነትን፣ የኑሮ ውድነትና ማኅበራዊ ልዩነት መስፋት ሲያስከትል በሌላ በኩል ደግሞ የካታላን መንግሥት ባልተጠበቀ ሁኔታ ነፃ አገር ለመመሥረት ያደረገውና እስካሁንም እልባት ያልተገኘለት ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ ፈጥሮ ፖለቲካዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ አውድቆታል፡፡

      የአርጀንቲና ኃይል እንደ ለውጥ መሣሪያ (Replacement) ከመጠቀም አኳያ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያመሳስላት ነገር ያለ ይመስላል፡፡ የሽግግር ውጣ ውረድ በተሟላ የሚታይበትም ነው፡፡ በ1955 ዓ.ም. በሲቪልና ወታደር አመጽ የፔሮን መንግሥት ከተወገደ በኋላ ያሉት 28 ዓመታት የቀውስ ዓመታት ነበሩ ይላሉ የዘርፉ ምሁራን፡፡ በሕገ መንግሥታዊ መንገድ የተመረጡት ሦስት መንግሥታት የሥልጣን ጊዜያቸውን ለመጨረስ ያልቻሉበትና አራቱ ወታደራዊ መንግሥታትም ዓላማቸውን ሳያሳኩ ወይም የሚፈልጉዋቸውን ተከታዩች ሳያስመርጡ የተወገደበት ሁኔታ እናያለን፡፡ በ1976 ዓ.ም. በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ መንግሥት ‹‹የቆሻሻ ጦርነት›› (Dirty War) በማወጅ ኅብረተሰቡን በአመጽ ለመግዛት ቢሞክርም፣ የላብ አደር ማኅበራት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው በተለይ ልጆቻቸው የጠፋባቸው እናቶችና ሌሎች ሲቪል ማኅበራት ያደረጉት ትግል ሥርዓቱን አነቃነቁት፡፡ በ1982 በፎክላንድ ጦርነት መሸነፍ አቀጣጣይ ሆነ የሙያና የሰብዓዊ መብትና ሲቪል ማኅበራት ከፍተኛ ተቃውሞ ወታደራዊ መንግሥት አምበርክኮ በ1983 ዓ.ም. ምርጫ እንዲደረግ ሆነ፡፡ 

በዚህ ሒደት ዋነኛው የፔሮን ፖለቲካዊ ፓርቲ ራሱን ለተቃዋሚ ፖለቲካዊ ወድድር ያልተዘጋጀ በመሆኑ (ልክ እንደ ኢሕአዴግ) ኅብረተሰቡን በተሟላ መንገድ ማንቀሳቀስ የሚችል ራዲካል ፓርቲ ሲፈጠር፣ የወታደራዊ ተቋሙን ሚና በማሳነስ ሁሉም ፖርቲዎች የየራሳቸውን ቦታ የሚያገኙበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ፓርላማው በሁለት ምርጫ መካከል የተለያዩ የጥቅም ግንኙነቶች ስምምነቶችን በሁለት ዋናና አናሳ ፖርቲዎች የሚፈጸምበት ሁኔታ በመሆኑ ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ዴሞክራሲው እየተንገዳገደ ይገኛል፡፡

ለማጠቃልል ሽግግር ከፍተኛ ውጣ ውረድ የበዛበት ወደ ኋላ የሚንሸራተት ግን ወደፊት በቀጣይነት የሚራመድ መሆኑን አይተናል፡፡ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉ፣ ካፒታሊዝም በሚገነባው የሚመለከተው ባለሀብት ሽግግሩን መምራቱ፣ የተቋማት የተሻለ ህልውና መኖሩ፣ ኅብረተሰቡም ከቀን ተቀን ኑሮ (Subsistence Economies) መላቀቅ መጀመሩ፣ ሽግግሩ በተነፃፃሪ በተሻለ ምቹ (Smooth) እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ልማት የዴሞክራሲን ዕድገትን የማቀለጠፍ ሚና ስላለው፡፡

ሽግግር በኢትዮጵያ ልዩና ውስብስብ

ከፊል አምባገነን የሆነውን የኢሕአዴግ አገዛዝ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በፀረ ዴሞክራሲያዊ መንገድ አንገዛም በማለት አነቃንቀውታል፡፡ ታላቅ ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን በለውጥ ስካር ጮቤ እየረገጥን መኖር አንችልም፡፡ ዋናውና ቀዳሚው ሥራው የሚተካው ሥርዓት በመገንባት ጉዳይ ስለሆነ፡፡ ማናቸውም ሽግግር አስቸጋሪ ቢሆንም የኢትዮጵያ ሽግግር ልዩና ውስብስብ የሚየደረጉት ባህሪያት አሉት፡፡ ከሌሎች ብዙ አገሮች በተለየ ወደ ዴሞክራሲና ወደ ካፒታሊዝም የሚደረገው ጉዞ በአንድ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ የአገራችን ሁኔታ ሁለቱም እንድናደርግ ያስገድደናል፡፡ መጀመርያ ኢኮኖሚያዊ ልማት በኋላ ዴሞክራሲ አያስኬድም፡፡ አንዳንድ የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉትም በማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ዴሞክራታይዜሽን የዕድል (Probability) እንጂ የአንዱ ለሌላው ምክንያትነት (Not Causality) አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥታችንም አይፈቅድም፡፡ ዴሞክራሲ መብቶች ብቻ ሳይሆን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሳይከፋፈሉ እንዲተገበሩ ዕውቅና የሰጠ በመሆኑ፡፡

በመጀመርያው ሽግግር ሲገባ ኢትዮጵያ ውስጥ ያልዳበረ ኢኮኖሚ በዕዝ አስተዳደር የነበረበት፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ለስም እንኳን ባልነበረበት፣ ዋናው ተጠቃሚ የሆኑት ባለሀብቶት (ትርጉም አልባ የሆኑበት)፣ ዴሞክራሲውን የሚሸከመው ኃይል (Middle Class) በእንጭጩ ባለበት ሁኔታ ‹‹እንደ ሻማ እየቀለጥን›› በሚሉ ታጋዮች ካፒታሊዝም የሚመራበት ነበር፡፡ በኃይል በማሸነፋቸው በትዕቢት ለውይይትና ለድርድር በማይመች ሁኔታ ስለሚፈጥር ሽግግሩ በጣም አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡

  ሁለተኛው ሽግግርም ቢሆን ገና ወደ መካከለኛ ገቢ ተርታ ባልተሠለፍንበት ባለሀብቱ መሪነቱ ባልያዘበት ነው፡፡ በኃይል የተገኘ በመሆኑ ልዩና ውስብስብ መሆኑ አይቀርም፡፡ ሆኖም በመጀመርያ ሽግግር ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግብዓቶች  በሚገባ አመራር ከተሰጠበት የተሻለ የሚሆንበት ዕድል አለው፡፡ በፀረ ዴሞክራሲ መንገድ አንገዛም የሚል ኅብረተሰብ በአጠቃላይ በተለይ አዳዲስ ማኅበረሰባዊ ኃይሎች መፈጠራቸው ራሱ ለዴሞክራሲ የምናደርገው ጉዞ የተሻለ ያደርገዋል፡፡ በሽግግር ወቅት እዚህም እዚያም የተለያዩ የፀጥታ ችግሮችና አደጋዎች መከሰታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ከተሸብርን ሽብር ልናባዛ ነው፡፡ ችግሮች በበዙ ቁጥር ዋና ሥራችን ማልቀስ ብቻ ከሆነ መጥፋታችን ነው፡፡ ያሉንን ዕድሎች (Opportunities) ማስፋት በማጥለቅና አደጋዎችን (Challenges)  በመቀነስ የሽግግር ባህሪ መሆኑን ተገንዝበን በሰከነ መንገድ ከተመራ ግን ሁኔታዎች ተረጋግተው ወደ ግንባታ በከፍተኛ ደረጃ የመዝለል ዕድል ይሰጠናል፡፡

ሁለተኛው ሽግግር የኢትዮጰያ ፖለቲካዊ ማዕከል በመዘወሩ (Shift) በማድረጉ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በአማራ/ትግራይ ወይም በተለምዶ  አቢሲኒያ  ተብሎ ሲጠራ ከነበረው ፖለቲካዊ ማዕከል ወደ ደቡብ መሻገሩ ነው፡፡  ትግራይ፣ ጎንደርና ሰሜን ሸዋ ማዕከሉ  የነበረው የአፄ ቴዎድሮስ፣ የአፄ ዮሐንስ፣ የአፄ ምኒሊክ፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴ፣ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ  ማዕከል፣ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ብሎም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ሥልጣን መሸጋገሩ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፡፡  የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ማዕከልና ድንበር (Center-Periphery) የሥልጣን ተዋረድ እንዳይኖር በሕግ ከልክሎታል፡፡  ከእንግዲህ ወዲህ ማዕከል የሚሆነው መሠረታዊ መዋቅር ጉዳያትና በልሂቃን  ተነፃፃሪ ብቃት ነው የሚወሰነው፡፡ የኢትዮጵያ ማክሮ ኢካኖሚ ማዕከል፣ የሕዝብ ብዛት፣ የጂኦግራፊ ማዕከልነትና በሕገ መንግሥቱ  በላቀ ተጠቃሚነት ያለው አስተሳሰብ ነው፡፡  ይህ ፖለቲካዊ ማዕከል መዛወር (Shift) የራሱ አዎንታዊ ተፅዕኖ አለው፡፡  በጣም ኋላ ቀር ከፊል አምባገነናዊ ፖለቲካዊ ባህል ወደ ሌላ የሚሸጋገርበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ፕሮፌሰር ህዝቄል ጋቢሳ ይህን ለማመልከት ይመስላል ከጥቂት ዓመታት በፊት እንዲህ ያሉት፡-

‹‹At no other time in Ethiopia’s political history has a nonviolent transition to democracy been more desirable and achievable.  Additionally, at no other time in the past have Ethiopians viewed the Oromo as a force for democratizing the Ethiopian empire-state.››

ሁለተኛው ሸግግር ለውጡ በኃይል መምጣቱ ብቻ ሳይሆን እንደ ወታደራዊ ተቋም ያልተደራጀ በወጣት ስብስብ የተገኘ በመሆኑ የራሱ ተግዳሮት አለው፡፡ የመንግሥት ተገቢ የማስገደድ መሣሪያዎች (Instrument of Coercion) ከወጣቱ ጋር በተለይ ከቄሮ ጋር የተጋራ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ልዩ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ የፖለቲካና የፀጥታ ስትራቴጂ የግድ ይላል፡፡ በኃይል ብቻ ለመፍታት መሞከር ጥፋተን ሊጋብዝ ይችላልና፡፡ ሁለተኛው ሸግግር ከሌላው ልዩ የሚያደርገው የትውልድ ሸግግር (Generational Change of Leadership) መኖሩ ነው፡፡ አዲሱ ትውልድ እኛ መምራት አለብን እያለ ነው፡፡ አገራችን የዴሞክራሲ ሰብዕና በተላበሱ በጥናትና ምርምር የሚመሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቁ ዕውቀትና ጉልበቱም ባላቸው ጎልማሳ አመራር ልትመራ ጊዜው እየጠየቀ ነው፡፡ የ60ዎቹ ትውልድ ደግሞ በትዕቢት ከእኛ በላይ ላሳር እያለ ነው፡፡  የዕድሜ ጉዳይ አይደለም፡፡ የዚህ ትውልድ ልዩ ባህሪና ሁኔታ ነው፡፡ ምንም ጭላንጭል በሌለው መስፍናዊ ኅብረተሰብ ያደገ፣ ማርክሳዊነት በተሞላ መንገድ ሳይገባው ፀረ  ዴሞክራሲ መስፍናዊ አስተሳሰቡ እንዲጠናከር ያደረገ ነው፡፡ እኔ ብቻ ያልኩት ካልሆነ በሚል በተለይ በትጥቅ ትግል አመራር የነበረው በወታደራዊ አስተሳሰብ መስፍናዊ ፀረ ዴሞክራሲ የዳበረ በመሆኑ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ግትርነት የሚያጠቃው፣ የተወሳሰቡ ነገሮችን የማቅለል አባዜ ያለው፣ ሁሉን ነገር ከአንድ ማዕከል ለመጠቅለል የሚፈልግና አንድነቱን እያጣ ስለሆነ ለዘመኑ አመራርነት የማይመጥን ነው፡፡ ይህ ዓይኑን አፍጥጦ የሚታየው ጡረታ በተገለሉና ባሉት የሕወሓትና የብአዴን አመራር ነው፡፡ ልክ እንደ ጓድ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምና አፄ ኃይለ ሥላሴ ኋላ ቀር አስተሳሰብ እነሱ ካልመለሱት አገር እንደምትጠፋ አድርገው ነው የሚያሰቡት፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አዲሱ ትውልድ ሥልጣን በሚገባ ለመጠቀም በተሟላ መንገድ ያለ መዘጋጀቱ የሚፈጥረው ክፍተትም አለ፡፡

የፓርቲዎች መሸጋሸግና ወጤቱ

የኢትዮጵያ የተደራጀ ጠንካራ ፖለቲካዊ ተቃውሞ ውጭ ነበር፡፡ ምኅዳሩ በመስፋቱና ሁሉም ሊባል በሚችል ወደ አገር ውስጥ መግባቱ በፖለቲካዊ ፓርቲዎች ሽግሽግ (Re-alignment) እና የእውነት ኅብረ ፓርቲ ሥርዓት (Multi-party System) እንዲኖር የሚያመቻች ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በኦሮሞ ብሔራዊ ድርጅቶች መዋሀድን ብሎም ጠንካራ ሁለት/ሦስት ተፎካካሪ ድረጅቶች ይኖር ይሆን እንዴ? በአማራ በብአዴን አብንና ሌሎች ብሔራዊ ድርጅቶች ምን ዓይነት የአሠላለፍ ለውጥ ሊኖር ይችላል?  ሕወሓት ካልታደሰ፣ ተቀዋሚዎች ከልተዋሀዱ የትግራይ ፖለቲካ ምን ሊሆን ነው? የክልል ጥያቄ የበረታበት ደኢሕዴን እንዳለ ይዘልቃል? ይህ ለኢሕአዴግ ምን ማለት ነው? ለአጋር ድርጅቶችስ? ኅብረ ብሔራዊ ድርጅቶች ተዋህደው  ጠንካራ ሁለት/ሦስት ተፎካካሪ ድረጅቶች ይፈጥሩ ይሆን እንዴ? ብለን እንድንጠየቅ የሚያደርግ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ በርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን መቶ በመቶ፣ 90 በመቶና 80 በመቶ ምርጫ እስከ ወዲያኛው ያለመኖሩ ነው፡፡

በቆሻሻ የቆሻሻ ቤት እንጂ ሕንፃ አይሠራም

የምንተካው ሥርዓት በባዶ ሜዳ ሊጀምር አይችልም፡፡ ለውጥ ያለ ቀጣይነት፣  ቀጣይነት ደግሞ ያለ ለውጥ እውን ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ከዜሮ የሚነሳ ለውጥ ሊኖር አይችልም፡፡ ምክንያቱም ለውጥ x 0=0 ስለሚሆን ነው፡፡ ያለፉት 27 ዓመታት በፖለቲካና ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድሎች የተገኙበት ቢሆንም፣ እጅግ ከፍተኛ ቆሻሻም የታየበት ነው፡፡ በጥላቻ ሳይሆን በፍቅርና በአንድነት ያለፈውን የመጀመርያ ሽግግር እስኪ እንገምግመው፡፡ ቆሻሻው እንዳይደገም የተሠራው በጎ ሥራ መረማመጃ እንዲሆነን መልካም መልካሙን እንደምረው፡፡ መደመር ከሆነ ያለፈውም ጭምር ስለሆነ ማለት ነው፡፡

አምባገነናዊው  ደርግ በተገረሰሰ ማግሥት ኢትዮጵያ እንደ ዩጎዝላቪያና እንደ ሶማሊያ በእርስ በርስ ጦርነት ትበታተናለች ስትባል በሽግግር ቻርተር ሰላምና መረጋጋት መጎናፀፍ ጀመረች፡፡ በድል ተወጥታ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለአንዴ ላትመለስ የዴሞክራሲ ጉዞ ግንባታ ጀመረች፡፡ የሦስት ትውልዶች ሰብዓዊ መብቶች (Three Generations of Human Rights) ታጥቃ መሠረታዊ የሆነ የአገዛዝ ለውጥ (Paradigm Shift) መረማመድ ጀመረች::  የግለሰብ መብቶችን ያካተተ ሕዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩባቸው መብቶች ዕውቅና ተሰጥቶ የተጎናፀፉበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ ይህን ለማሳካት ሲባል ብሔር ተኮር ፌዴራላዊ ሥርዓት በመዘርጋቱና ሕዝቦች ተጠቃሚዎች በመሆናቸው፣ ያቺ ትፈርሳለች የተባለችው አገር ለ25 ዓመታት ሰላም የሰፈነባት አገር ሆነች፡፡

እስከነ ሁሉም ዓይነት ችግሮች (በሽግግር ግዜ ዴሞክራሲ በከፍተኛ ደረጃ ይሸራረፋል)  እስከ 1997 ዓ.ም. ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ወርቃማ ዕድል የዚህ እንቅስቃሴ ውጤት ነው፡፡ ከምርጫው በኋላ ሥርዓታቸው ሊናጋ እንደሚችል ያውቁት ከፍተኛ አመራሮች የራሳቸውን ሥልጣን ለማደላደል ሕገ መንግሥቱን በግላጭ መጣስ ጀመሩ፡፡ የብዙ ሰዎች ሕይወት ተቀጠፈ፡፡ ሥርዓቱ የበለጠ እየበሰበሰ፣ የባሰ አፋኝና የከፋ ዕርምጃ መውሰድ ጀመረ፡፡ ፍርኃትም ነገሠ፡፡ የነበረውን የዴሞክራሲ ጭላንጭል ለማጥፋት ከአሥር ዓመታት በኋላ በ2007 ዓ.ም. ምርጫ በኢሕአዴግ መቶ በመቶ አሸናፊነት ተጠናቀቀ ተባልን፡፡ በማስፈራራትም በማጭበርበርም የተገኘው ውጤት አደገኛነቱ ቢገለጽላቸውም፣ በትዕቢትና ድንቁርና ተወጥሮው ከበሮ መደለቅ ጀመሩ፡፡ ሰርከሱ ስድስት ወር ሳይሞላው መንግሥት በሕዝባዊ እሳት መለብለብ ጀመረ፡፡ መንግሥት በሕዝቦችና በሕገ በመንግሥት ሲያምፁ፣ ተፈጥሯዊ መብቶቻቸውን ተጠቅመው ሥርዓቱን አንቀጠቅጡት፡፡ ከፍተኛ አመራሮቹ ራሳቸውን ለማዳን ከተሃድሶ፣ ወደ ጥልቅ ተሃድሶ እንደገና ወደ ሌላ ተሃድሶ ሲንከባለሉ ጊዜ መሽቶባቸው እዚህም እዚያም ሰያላዝኑ ከየት መጣ ሳይባል አዲስ ተስፋ የሚሰጥ አመራር ብቅ አለ፡፡ ሕዝቦች በ1983 ብሎም በ1987 ዓ.ም. ያገኙት ድል የታገሉለትና የሚኮሩበት  ቢሆንም፣  የኢሕዴግ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አመራር ከሚሸከሙት በላይ በመሆኑ በከፍተኛ አመፅ ሥርዓቱን በመቀየራቸው በሁለተኛው ሽግግር ላይ እንገኛለን፡፡

ከማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አንፃር ሲታይ በአገሪችን ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ዕድገት የተመዘገበባቸው 27 ዓመታት ነበሩ፡፡ በዓለም ውስጥ ካሉት በከፍተኛ ደረጃ ዕድገት ካስመዘገቡ አገሮች ተርታ ኢትዮጵያ ተሠልፋለች፡፡ በአፍሪካም ሆነ  በዓለም አቀፍ ደረጃ ተገቢውን ሥፍራ መያዝና ከፍ ከፍ ማለት የጀመረች አገር ሆና ነበር፡፡ የተለያዩ ማኅበራዊ ኃይሎች እየተፈጠሩ ፍላጎታቸው እያደገ ሕገ መንግሥቱ ያወቀላቸውን መብቶች ለማረጋገጥ የሚታገሉ ማኅበራዊ ኃይሎች በመፈጠራቸው፣ ለሁለተኛ ሽግግር በሩን ከፈቱልን፡፡ ሆኖም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለ ዴሞክራሲ ፍትሕ የሚጣስበት፣ አድልኦ የበዛበትና በሙስና የተተበተበ በመሆኑና የሕዝቦችን ጥቅም የሚፃረር በመሆኑ፣ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመፅ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸውን የሚያረጋግጥ መንግሥት ፍለጋ ተንቀሳቀሱ፡፡ በፀረ ዴሞክራሲያዊ መንገድ አንገዛም ብለው የፖለቲካ ፍንዳታ (Political Explosion) ወይም የፖለቲካ ሱናሚ (Political Tsunami) ውስጥ እንገኛለን፡፡ ግለቱን ጠብቀን ትክክለኛ አቅጣጫ በማስያዝ ኢትዮጵያ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማሸጋገር ዕድሉን ለማስፋት ከመጀመርያው ሽግግር መማር ይኖርብናል፡፡

የመጀመርያ ሽግግር በአንድ ወር ውስጥ የሽግግር ቻርተር አፅድቆ የፖለቲካ አስተዳደሩ አቅጣጫ በግልጽ አስቀምጧል፡፡ ከተወሰነ የሽግግር ዓመታት ሕገ መንግሥት ፀድቆ የአገር ግንባታ ቀጠለ፡፡ ከሕገ መንግሥቱ የሚመነጩ ፖሊሲዎችና ሕጎች ተደንግገው የዴሞክራሲ ጎዳና ከእነ ብዙ ችግሮች ቀጠሉ፡፡ ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ ግን በተግባር ሲታዮ የነበሩት ፀረ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች በሕግ ተደግፈው አምባገነንነትን በተለይ የሥራ አስፈጻሚው አምባገነንነትን ወደ አንድ ሰው  አምባገነንነት ያወረደበት፣ ከ2005 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽባ የሆነበት፣ ከ2008 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ መንግሥት አለ ወይ? የሚያሰኝበት ሁኔታ መታየት ጀመረ፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቱን በሚመለከት የነበረው የመንግሥት ቁርጠኝነትና አርቆ አሳቢነት ከመጀመርያው ሽግግር የምንማረው ነው፡፡ 27 ዓመታት ሙሉ ቆሻሻ ብቻ ነበር ማለት የኢትዮጵያን ሕዝቦች መስደብም ማንኳሰስም ነው፡፡ ለወጡ በኢሕአዴግ መሪነት ቢሆንም የለውጡ ዋና ተዋናይ ግን ሕዝቦች ስለሆኑ፡፡

የለውጥ አቅጣጫና ዕቅድ

ሁለተኛው ሽግግር የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግር፣ የአገሪቱን የህዳሴ ጉዞና አቅጣጫ ፍንትው አድርጎ የሚያመለክት ነበር፡፡ ይህን ተንተርሶ በተለያዩ ከፍተኛና እርባና ያላቸው ዕርምጃዎች በመወሰዳቸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተስፋ እየለመለመ ይገኛል፡፡ የተጀመረው አካታች ፖለቲካ ቀጣይነትና የሚያሰተማምን እንዲሆን ይፈለጋል፡፡ እነዚህ አቀጣጣይ ዕርምጃዎች ከፍተኛ ተስፋ የጫሩ ቢሆንም ከአቀጣጣይነታቸው አያልፉም፡፡ አቀጣጣይ በሌላ መሠረታዊ መፍትሔ ካልተተካ ተቃጥሎ የሚቀር ነው የሚሆነው፡፡ የለውጥ ፕሮግራም በዝርዝር ተዘጋጅቶ ዕቅድ ወጥቶለት  በሥራ ላይ መሆኑን ለመገንዘብ አልቻልንም፡፡

አግላይ ፖለቲካ የነገሠው የሕዝቦች አደረጃጀቶች በተለይ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማት ሽባ በመሆናቸው ነው፡፡ የለውጥ ፕሮግራሙ ማዕከል የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዴት ይረጋገጡ ሲሆን፣ ዋስትና የሚኖረው እነዚያ ተቋማት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ግዴታቸውን ሲወጡ ነው፡፡ የ27 ዓመታት ጉዟችንን ስንገመግመው አሁን ለደረስንበት ቀውስ ዋና ምክንያቱ የሕግ የበላይነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለመኖሩ የተከሰተ ከፍተኛ ችግር ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱና ፖለቲካው ተፃራሪ በመሆናቸው ነው ሕዝቦች የታገሉት፡፡ ፖለቲካው እንደ አዲስ መሠራት (Overhall) ይገባዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ካፒታላዊ ሥርዓት የሚገነባው በውደድርና በትብብር ነው፡፡ በፖለቲካና ኢኮኖሚ በሁለም መስክ የሚደረግ ውድድር፣ በፓርቲ ውስጥ የተሟላ ወድድር፣ በፓርቲዎች መካከል የተሟላ ወድድርና የገበያው ውደድር ማዕከል ያደረገ ሲቪል ሰርቪሱ የባለሙያዎች ውድድር፣ ወዘተ፡፡

የፖለቲካ ልሂቃን ወደ ድርድር፣ ግልግልና ስምምነት እንዳይደርሱ የተለያዩ  የአመለካከትና የአሠራር እንቅፋቶችን መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡ አንደኛው ሁሉ ነገር ነጭ ወይም ጥቁር፣ አንደኛው ከሌላው ጋር ሊታረቅ የማይችልና (Mutually Exclusive)  ቂመኝነትና (Vindictive)  አጥፊ ተጋላጭነት (Destructive Confrontation) ለግልግል እንቅፋት ነው፡፡ ሁለተኛ አሁን በአገራችን ሁኔታ ያለው ግንዛቤ ነው፡፡ ሁለት ጫፎች የያዘ አመለካከት ነው፡፡ ቀደም ብሎ የነበረው የሥልጣን ግንኙነት (Power Relations) በመሠረቱ የተቀየረ መሆኑን ካለማወቅ (ካለመፈለግ)፣ ድሮ እንደነበረው እንዳለ አድርጎ በመወስድ በትዕቢት ለድርድር መቅረብ ነው፡፡ ሌላው አሁን ሕዝቦች የሰጡትን መብት (Mandate) በማጋነንና በትዕቢት አዋርዶ ለመጣል የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡ የፖለቲካ ተቋማት ዕድገት ከማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጡ ጋር መሄድ አለመቻል ትልቁ የፖለቲካ ችግር ነው፡፡

ኅብረተሰቡ የለውጥ አካል ሆኖ በአሁኑና በወደፊቱ ብርሃን የሚያይበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል፡፡  አሁን የተገኘው ትልቅ ተቀባይነት ሊቀጥል የሚችለው በለውጥ ሒደቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት የተላበሰ ኅብረተሰብ ወቅታዊና በቂ መረጃ ሲያገኝ ነው፡፡  መንግሥት ለውጡን በመምራት ብቃትም በቀጣይነት ሲያሳይ ነው በኅብረተሰቡ  ውስጥ ያለው ኋላ ቀርነት እየተቀረፈ የሚያስተማምን ጉዞ ሲኖር ነው፡፡ ለዚህም ባህላዊ፣ ሲቪልና የሙያ ማኅበራት ነፃነት ተጠብቆ በተጠናከረ መንገድ ለመብቶቻቸው እየታገሉ፣ መንግሥትንም ጭምር እያስተካከሉ እንዲሄዱ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ መታገል ያለብን የመንጋ ፖለቲካን ነው፣ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚሉት ካልሆነ ወይም እኛ የምንለው ካልሆነ ሁሉም ፀረ ለውጥ ነው፡፡ ሁሉም የጥፋት መንገድ ነው የሚለው አካሄድ ኅብረተሰቡን እንዲሸማቀቅ በማድረግ የተጀመረውን የፖለቲካ መነሳሳት የሚገድል በመሆኑ፣ ይህንን በማገናዘብ ለውጡን ተቋማዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ብሔርን ማዕከል ያደረገው ፌዴራላዊ ሕገ መንግሥት በርካታ ጥያቄዎች እየተነሳበት ነው፡፡ ብዙዎች የሚደግፉት ቢመስልም ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሲቃወሙት ይታያሉ፡፡ አገራዊ መግባባት በሕገ መንግሥቱ እንዲኖር በዋና ዋና ምሰሶዎችና ምልክቶች (ሰንደቅ ዓላማና ብሔራዊ መዝሙር) እንዲኖሩ የለውጥ አካል ሆኖ ዕቅድ ቢያዝበት፡፡ የሚቀጥለው ምርጫ እንዲራዘም በማድረግ ሕገ መንግሥቱ ለሕዝበ ውሳኔ እንዲቀርብ ማድረግ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ለማራዘም የማይቻል ከሆነ ከምርጫው በኋላ የግድ መደረግ ያለበት ይመስለኛል፡፡

በመንግሥትና በገዥው ግንባር ያለው ግንኙነት ሕገ መንግሥታዊ ማድረግ፡፡ ለፀረ ዴሞክራሰያዊነት መንግሥት ከኅብረተሰቡ ጋር ያለው ፖለቲካዊ ባህል መቀጠል ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ገዥው ግንባር በሥልጣን ላይ ለመቆየት ዓላማው በሕዝቦች ይሁንታ ሳይሆን የመንግሥት መዋቅር፣ የመንግሥት ሚዲያ፣ የመንግሥት ቢሮ፣ ገንዘብና ጊዜ፣ ጠመንጃና አሉ የሚባሉ እርከኖችን ለፓርቲ ሥራ ስለሚያውል የፉክክር ሜዳው ዴሞክራሲን የሚያስችል (Democracy Enabling) እንዳይሆን አድርጎታል። ሁሉም ከአንድ ማዕከል እንዲፈስ በማድረግ ለፌዴራል ማዕከሉና ለክልሎች የተሰጠውን ፖለቲካዊ የሥልጣን መዘባረቅ ‹‹Organized System of Irresponsibility›› የሚሉት ዓይነት ሁኔታ ፈጥሯል፡፡  ግንባሩ አይዶለጂውንና ፖለቲካዊ ሥራውን የሚሠራባቸው የፖለቲካ ሹመቶች በሙሉ በሕጉና በብቃታቸው ብቻ የሚመለመሉበት ሰዎች ያሉበት እንዲሆን የሚያደርግ ዝርዝር ሕግ መውጣት ይኖርበታል፡፡ የመንግሥት ሥልጣንን እንደማትጊያ ተጠቅሞ በስፋት የሚመለምል ድርጅት እንዳይኖር በሕግ ጭምር መደንገግ ይኖርበታል፡፡

የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የአገር መሪነቱን በሚገባ የሚወጣበት ሕግ፣ አደረጃጀትና አሠራር ያዘለ ማሻሻያ፣ ምክር ቤቶች የሕዝቡ ሉዓላዊነት መገለጫ የዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እምብርትና የዴሞክራሲያዊ አገዛዝ አውራ ተቋማት እንዲሆኑ ነፃነታቸውን በጠበቀ መንገድ ብቃታቸው የሚያረጋግጥ ማሻሻያ፡፡ የዴሞክራሲ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ተጠሪነቱ ለተወካዮቹ ምክር ቤት የሆነ፣ ገለልተኛና ተዓማኒነት ባላቸው ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች እንዲመራ ማድረግ፡፡ ሕግ ተርጓሚው ጠንካራ ተቋማዊ ሰብዕና እንዲኖረው የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪልና የሙያ ማኅበራት በዴሞክራሲዊ ግንባታ ላይ ያላቸውን ሚና የሚመጥን ሕግና ተግባር የምርጫ የሚዲያ ሕጎች ለዘመኑ የሚመጥኑ ሆኖ እንዲሻሻሉ፣ የኢትዮጵያ የውጭና የብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ በማሻሻል ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ እንዲሆንና የመከላከያ ሠራዊት፣ የደኅንነትና የፖሊስ መዋቅሮች ፕሮፌሽናሊዝም የሚያሳድግና አፋኝ ሕጎች በተሟላ መንገድ ቢሻሻሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የለውጥ እንቅስቃሴዎች በክልሎች ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ክልላዊ መንግሥታት እስከ ወረዳና ቀበሌ ያሉት ተቋማት ቢካሄድ አጠቃላይ ሕዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠር ለውጡ ወደፊት እንጂ ወደ ኋላ የማይሄድበት ሁኔታ እንፍጠር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ነባር የኢሕአዴግ ታጋይና የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ የነበሩ ሲሆን፣ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...