Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ለውጭ ባንኮች ክፍት የማድረግ አስፈላጊነት

የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ለውጭ ባንኮች ክፍት የማድረግ አስፈላጊነት

ቀን:

በኤርሚያስ አመልጋ

ኢትዮጵያ በባንክ ኢንዱስትሪ በራቸውን ለውጭ ኢንቨስትመንት ዝግ ካደረጉ የመጨረሻዎቹ የዓለም አገሮች አንዷ ናት፡፡ በዚህ ረገድ ኤርትራና ሰሜን ኮሪያን ከመሳሰሉ  አገሮች ተርታ እንመደባለን፡፡ ኢኮኖሚው በዚህ ከልካይና ዘመን ያለፈበት ፖሊሲ ሳቢያ ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያን የባንክ ዘርፍ ለውጭ አገሮች ባንኮች ክፍት ማድረግ

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ የውጭ ባንኮች በኢኮኖሚያቸው ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ ከሚያግዱ ጥቂት አገሮች ውስጥ አንዷ ናት፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዚህ ከልካይና ጊዜ ያለፈበት ፖሊሲ ከፍተኛ ዋጋ መክፈሉን ቀጥሏል፡፡

በኢትዮጵያ ተገቢ የካፒታል አቅርቦት ያለመኖር፣ የትርፋማ ኩባንያዎችና የንግድ ተቋማት ዕድገትን እየገደበ ነው፡፡ የንግድ ሥራ ፈጣሪዎች በአገር ውስጥና በውጭ ገበያዎች፣ ትርፋማና ውጤታማ የመሆን አቅም ባላቸው የቢዝነስ ዕድሎች ላይ ደፍረው ኢንቨስት እንዳያደርጉ እያገዳቸው ነው፡፡ በአጠቃላይ ባንኮች ፕሮጀክት ተኮር ለሆነ ኢንቨስትመንት የፋይናንስ አገልግሎት ለማቅረብ ክህሎት የላቸውም፡፡ ስለዚህም ብድር ድርጅቶች በሚያቀርቡት የማስያዣ (ኮላተራል) ወይም የዋስትና መጠን የተገደበ ነው፡፡ አሊያም እምብዛም ፍሬያማ ላልሆኑ ኢንቨስትመንቶች ይፈሳል፡፡ ለምሳሌ ባንኮች እንደ ማስያዣ  (ኮላተራል) የሚቆጥሯቸው የሪል ስቴት ልማቶች ናቸው፡፡

የዕድገት መልካም አጋጣሚዎችን የሚፈጥሩ የአምራች ወይም ኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂን የመሳሰሉ ዘርፎች፣ የፋይናንስ አቅርቦት የመሳብ ዕድላቸው እምብዛም ነው፡፡ ሪስክ ካፒታል ለማግኘት የሚያጋጥሙ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለኢትዮጵያ ፋይዳ ያለው ምርታማነትን ለማሳደግ ቁልፍ ለሆነው ምርምር፣ ልማትና ፈጠራ የሚኖረውን  የፋይናንስ አቅርቦት ይበልጥ ይገድቡታል፡፡   

የሚገርመው ደግሞ የኢትዮጵያ ባንኮች 90 በመቶ የሚሆነውን ዝቅተኛ የኅብረተሰብ ክፍል የባንክ ፍላጎት ለማሟላት ምንም ጥረት ሳያደርጉ መቅረታቸው ነው፡፡ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የልማታዊ መንግሥት ሞዴል ዓላማና ግብ ቢሆንም፣ ብዙኃኑን ወይም ደሃውን ታሳቢ ያደረጉ የፋይናንስ ውጤቶች ወይም አገልግሎቶች የሉም፡፡ በኢትዮጵያ ሀብታሙ የኅብረተሰብ ክፍል በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ መበደር ይችላል፡፡ ለሸማቹ የአንድ ሺሕ ብር ብድር ግን የለም፡፡

ለባንክ ዘርፉ ልማት፣ እንዲሁም ለግል ዘርፉና በጥቅሉም ለኅብረተሰቡ ዕድገት የሚመጥኑ የፋይናንስ አገልግሎቶች ለማቅረብ  ትልቁ ማነቆ አዲስ የአመራር ክህሎት አለመኖር ነው፡፡ አዳዲስ የአመራር ክህሎቶችና ሐሳቦች ዕጦትም ዘርፉ እንዳይሻሻል ገድቦታል፡፡ አብዛኛው አንጋፋ አመራር በመንግሥት ባንኮች ውስጥ ከሠለጠነና ልምድ ካዳበረ በኋላ በግሉ የባንክ ዘርፍ የተቀጠረ ነው፡፡ ይኼ መዋቅራዊ ጉዳይ በአንጋፋ የባንክ አመራሮች ብቃት፣ አቅምና አጀንዳ ላይ አሻራውን አሳርፏል፡፡

ይህ አሉታዊ ሁኔታ ደካማ የኩባንያ አመራር ባለበት፣ ሙስናና ብልሹ አሠራር በሰፈነበት የባንክና የቢዝነስ ድባብ ይባባሳል፡፡ በዘርፉ የውጭ ፉክክር አለመኖር አሁን ያሉት ባንኮች እርስ በእርስ ብቻ እንዲገዳደሩ ያስገዳዳቸው ሲሆን፣ ይህም የአዲስ አሠራርና እሴት ፈጠራ ዕጦትን አስከትሏል፡፡  

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ በሚከተሉት ባህርያት ይገለጻል፣

  • የባንክ አገልግሎት የማያገኝ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ
  • ደካማ የደንበኛ አገልግሎት አሰጣጥ
  • ከፍተኛ ዋጋ ዝቅተኛ ጥራት ያላቸው ምርቶችና አገልግሎቶች
  • አዳዲስ አሠራር የሌለው 
  • ፉክክርና ውድድር የሌለበት
  • ሙስና በብድርና በውጭ ምንዛሪ አገልግሎት
  • የተሳሳተ የአገራዊ ሀብት ምደባ
  • ደካማና ራዕይ የሌለው አመራር
  • እጅ በእጅ (በካሽ) ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ኤሌክትሮኒክ የአከፋፈል ሥርዓት የሌለበት፡፡

የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ስትራቴጂ ምን ይመስላል?

የፋይናንስ መሠረተ ልማት የኢኮኖሚ አንጎል፣ ልብና የደም ሥር የመሆኑን ያህል፣ የፋይናንስ መሠረተ ልማት ዕጦት (አልያም ቁጠባን በመሳብ የሚያስተናብርና ኢንቨስትመንትን የሚመግብ ሌላ አማራጭ መንገድ ማጣት) ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያጨልም ክፉ አደጋ ነው።

በገበያ ሥርዓት ላይ የተገነባ የፋይናንስ መሠረተ ልማት በአገሪቱ የልማት ስትራቴጂ ውስጥ መሟላት ከሚገባቸው ዋና ምሰሶዎች መካከል አንዱ ቢሆንም፣ ሳይካተት የታለፈው በአጋጣሚ ሳይታወቅ ቀርቶ ወይም ተዘንግቶ አይደለም። ቦታ ለመንፈግ የተፈለገውና ሆነ ተብሎ የተወሰነው፣ የገበያ ጉድለቶች (እንከኖች) የተሰኘውን ንድፈ ሐሳብ በመንተራስ ነው። የገበያ ጉድለቶች በታዳጊ አገሮች ውስጥ ሁሉንም የኢኮኖሚ ዘርፎች ያዳረሱ፣ በተለይ ደግሞ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የተንሰራፉ ችግሮች እንደሆኑ በዚህ ንድፈ ሐሳብ ይታመናል። የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያሰፈሩት ሐሳብ ቃል በቃል እንዲህ ይላል፡፡

‹‹አኅጉሪቱ በዝቅተኛ ብድርና በዝቅተኛ ቁጠባ ወጥመድ አጣብቂኝ ውስጥ ተይዛለች። በቁጠባና በብድር ወለዶች መካከል ያለው ልዩነት ተለጥጦ የተጣራ የወለድ ምጣኔው ከመናሩ የተነሳ፣ የማይቀመስ የሆነባቸው የአምራች ዘርፍ ኢንቨስትመንቶችን ከጨዋታ ውጪ አድርጓቸዋል። በካፒታል ዕጦት በእጅጉ በተጠሙ አገሮች ውስጥ፣ ለግብይት የሚውል ተንቀሳቃሽ ገንዘብ ግን ሞልቶ ይትረፈረፋል፡፡ ለወትሮም የረባ ቁጠባ በሌላቸው አገሮች ውስጥ፣ ቁጠባን በመሳብና በማስተናበር የሚመጣና ባንኮችን ለትጋት የሚያነሳሳ የገበያ ጥቅም ሲጠፋ፣ አንዳንዴም ለቁጠባ የሚመጡ ደንበኞችን ላለማስተናገድ ጀርባቸውን ሰጥተው ሲመልሱ ይታያል። የፋይናንስ ዘርፉ አገናኝ የፋይናንስ ድልድይ የመሆን ተግባርና አገልግሎቱን መወጣት ጨርሶ አቅቶታል።

‹‹ኒዮ ሊበራል የአስተሳሰብ ቅኝት ግን በፋይናንስ ዘርፍ ውስጥ የሚታዩትንና በመንግሥት ውጤታማ ጣልቃ ገብ ዕርምጃ ብቻ ሊስተካከሉ የሚችሉ መሠረታዊ የገበያ ጉድለቶችን መገንዘብ አልሆነለትም። ገበያው በትክክል ሲሠራ ብቻ ሳይሆን እክል ሲኖርበትም፣ ከጣልቃ ገብ ዕርምጃ መቆጠብ ያስፈልጋል ከሚለው እምነቱ ለመላቀቅ አልቻለም። በመዋቅር ማሻሻያ ዘመን በጅምር መክኖ የቀረውን የአፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ ከቆሞ ቀርነት የሚታደግ፣ ከመድረሻ ቢስነት የሚያወጣ መንገድ መክፈት አልቻለም።

‹‹ተጨባጭ ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ የገበያ ጉድለቶች፣ የመንግሥት ጉድለቶች ያህል መጥፎ ናቸው፡፡ በመጨረሻ ሁለቱም የፋይናንስ ዘርፉን መድረሻ ቢስና ቆሞ ቀር ያደርጉታል፡፡ ለጥፋት ያሰፈሰፈ ወሮበላ መንግሥትና ‹‹መንግሥት ገነን›› ፖሊሲዎች እንዲሁም የዋሽንግተን ኮንሰንሰስ በየራሳቸው የተለያየ አቅጣጫ፣ በማያምር መካነ ጉዞ የአፍሪካን የፋይናንስ ዘርፍ መድረሻ ቢስና ቆሞ ቀር አደረጉት፡፡ የዚህኛው ቆሞ ቀርነት ከዚያኛው ቆሞ ቀርነት አይሻልም፡፡ የአፍሪካ የፋይናንስ ዘርፍ መድረሻ ቢስ ሆኖ እንዳይቀርና ከመካነ ጉዞ እንዲወጣ፣ ሁለቱም አቅጣጫዎች ተነቅለው መወገድ ይኖርባቸዋል፤›› ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፋይናንስ ዘርፍ ስትራቴጂ ላይ ያንፀባረቁት ሐሳብ  በጣም ግልጽ ነው፡፡ የፋይናንስ ዘርፍ ዕድገትን ገበያው እንዲመራው ከመተው ይልቅ፣ በመንግሥት መመራቱን መርጠዋል፡፡ በኢትዮጵያ ይህ አሠራር የተተገበረው ሁለት በመንግሥት የሚተዳደሩ ባንኮችን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ዋነኛ የፋይናንስ ተቋማት በማድረግ ነው፡፡ የኢኮኖሚውን የፋይናንስ ፍሰት በበላይነት የሚመሩና የሚቆጣጠሩ፡፡ መንግሥት አገሪቱ አንፃራዊ የተወዳዳሪነት ብልጫ አላት ተብለው  የሚታሰቡ (ቀዳሚ) የኢንቨስትመንት ዘርፎችን በመለየት፣ ዘርፎቹን ለማልማት የሚያስፈልገውን  የፋይናንስ አቅም ይመድባል፡፡

በምሳሌነት ከሚጠቀሱ ዘርፎች ውስጥ ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ሆርቲካልቸር፣ ኤክስፖርት፣ ወዘተ ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም እነዚህ ሁለት የመንግሥት ባንኮች ለበርካታ የመንግሥት  ድርጅቶች፣ በመንግሥት ለሚከናወኑ ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም ለፓርቲ (ኢንዶውመንት) ኩባንያዎችና ፕሮጀክቶች ከፍተኛ መጠን  ያለው፣ አድሏዊ የፋይናንስ አቅርቦት አድርገዋል፡፡ እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት እንደ መንግሥት ግምጃ ቤት ሆነው ነው ያገለገሉት፡፡ የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ የተደረገውም በዚህ ምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሁለቱ የመንግሥት ባንኮች በኢኮኖሚው የፋይናንስ ፍሰት ላይ ያላቸውን በበላይነት የመቆጣጠር አቅም ለአደጋ ሊያጋልጥ ከሚችል ፉክክር ለመታደግ ነው የውጭ ባንኮች ተሳትፎ የተከለከለው፡፡ 

የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ታሪክ

በ1950ዎቹና 60ዎቹ የውጭ ኢንቨስትመንት የተለመደና በሁሉም ዘርፎች ያለ ምንም ገደብ በስፋት የተሠራጨ  ነበር፡፡ የጣሊያን፣ የግሪክ፣ የህንድ፣ የየመን፣ የአርመን፣ ወዘተ… የውጭ አገር ዜጎች፣ የአገር ውስጥ ኢኮኖሚና ማኅበረሰቡ አካል ነበሩ፡፡ የእነዚህን በአንድ ወቅት ክፍትና ንቁ የነበሩ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ቅሪቶች፣ ዛሬም ድረስ በራሳቸው በመሠረቷቸው አያሌ የማኅበረሰብ ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶችና ምግብ ቤቶች አማካይነት ማየት እንችላለን፡፡ የግሪክ ትምህርት ቤት፣ የህንድ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት፣ ጁቬንቱስ ክለብ፣ ግሪክ ክለብ፣ የጣሊያን የባህል ማዕከል፣ ከአያሌዎቹ ውስጥ ጥቂት አብነቶች ናቸው፡፡

በ1930ዎቹ ኢትዮጵያ በአኅጉሪቱ መቶ በመቶ በአፍሪካውያን ባለቤትነት የተያዘ የመጀመርያው ባንክ ባለቤት ነበረች፡፡ ኢትዮጵያ በ1950ዎቹ በአኅጉሪቱ የአክሲዮን ገበያ ያላት ሁለተኛዋ አገር ነበረች፣ ከግብፅ በመቀጠል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሦስት የውጭ ባንኮችና 16 የውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ነበሩ፡፡ ኢኮኖሚው ክፍት በመሆኑ ከውጭ ካፒታል፣ አመራርና ቴክኖሎጂ በእጅጉ ተጠቃሚ ሆኗል፡፡ የኢኮኖሚውንና የኅብረተሰቡን የዝመናና የለውጥ ሒደት፣ በፊታውራሪነት የሚመራው የግል ዘርፉ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ ከምታስገባቸው ምርቶች ይልቅ ወደ ውጭ ገበያ የምትልከው ይበልጥ ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሪ በቋሚ ተመን በቀላሉ ማግኘት ይቻል ነበር፡፡ ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ከአንድ ሺሕ ዶላር በላይ ስለነበር፣ ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ያላት አገር አድርጓታል፡፡ ኢኮኖሚው ንቁና አዳዲስ አሠራሮችን የሚከተል ሆኖ ሚዛናዊ የመዋቅር ትራንስፎርሜሽን ሒደት ላይ ነበር፡፡

አዲሱ የአፍሪካ የባንክ ኢንዱስትሪ 

አፍሪካ በፈጣን ታሪካዊ ግስጋሴ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን፣ ይህም ግስጋሴ ሚሊዮኖችን ከድህነት አረንቋ እያወጣ ነው፡፡ አዲስ ሸማች የኅብረተሰብ ክፍል እየፈጠረ ነው፡፡ በብዙ አገሮች የኢኮኖሚው ዕድገት ወደፊት እያራመደ ነው፡፡ ይህን መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድገት በሚያንፀባርቅ ሁኔታ፣ አፍሪካ ዛሬ በዓለም ሁለተኛው ፈጣን ዕድገት ያስመዘገበ  የባንክ ገበያ ያላት አኅጉር ሆናለች፡፡ 

ዓይነተ ብዙ ገጽታዎች  

የአፍሪካ የባንክ ኢንዱስትሪ በዓይነተ ብዙ ገጽታዎቹ የሚታወቅ ነው፡፡ በስፋት በመሠረተ ልማት፣ በባንክ አገልግሎት ሥርጭትና በዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም የጎላ ልዩነት ያላቸው ብሔራዊ ገበያዎች ያሉት ነው፡፡ በአፍሪካ የባንክ ገበያዎች ውስጥ አራት ዓይነተኛ ዘርፎች አሉ፡፡ እያንዳንዳቸው በነፍስ ወከፍ ገቢ፣ በባንክ አገልግሎት ሥርጭት፣ በገቢ ዕድገት፣ በትርፋማነትና በፋይናንስ መሠረተ ልማት ጉልህ ልዩነት የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡  

የመጀመርያው በአንፃራዊነት የዳበረ ገበያ ሲሆን፣ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢና የሀብት ሥርጭት ያላቸውን ግብፅና ደቡብ አፍሪካ የመሳሰሉ አገሮችን የሚያካትት ነው፡፡ እነዚህ ገበያዎች ከፍተኛ የቅርንጫፍ ሥርጭት አላቸው፡፡ ለ100 ሺሕ ሰዎች 17 ቅርንጫፎች ሲሆን፣ በአንፃሩ የአፍሪካውያን አማካይ አምስት ቅርንጫፎች ናቸው፡፡ ለ100 ሺሕ ሰዎች፡፡ በተጨማሪም 22 በመቶ ያህሉን አዋቂዎች የሚሸፍን ከፍተኛ የብድር አገልግሎት ሥርጭት አላቸው፡፡ ይህም ከአፍሪካውያን አማካይ እጥፍ ነው፡፡ በእነዚህ ገበያዎች ‹ሪቴይል› ባንኪንግ ከፍተኛውን የገቢ ድርሻ የሚወስድ ሲሆን፣ ይበልጥ የዘመኑ የፋይናንስ አገልግሎቶችም ተስፋፍተዋል፡፡ ለምሳሌ የሀብት አስተዳደርና የሞርጌጅ ብድሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 

ሁለተኛው በፈጣን ዕድገት ላይ የሚገኘው የሽግግር ገበያ ሆኖ ጋና፣ ኮትዲቯርና ኬንያን የመሳሰሉ አገሮችን ያካትታል፡፡ በእነዚህ አገሮች የባንክ አገልግሎት ሥርጭቱ ከተለመደው ልቆ የተሻገረ ነው፡፡ እነዚህ ያደጉና የተወዳዳሪነት አቅም ያላቸው የሪቴይል ባንኪንግ ገበያዎች ሲሆኑ፣ በከፍተኛ ደረጃ የሞባይል ባንኪንግና ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን የሚያቀርቡ ናቸው፡፡

ሦስተኛው ዓይነተኛ ገበያ አንጎላንና ናይጄሪያን የመሳሰሉ የሚያንቀላፉ ግዙፍ አገሮችን የሚያካትት ነው፡፡ እነዚህ አገሮች ሰፊ ገበያዎች ያላቸው ሲሆን፣ የባንክ አገልግሎት ሥርጭት ከገቢ ደረጃቸው አንፃር ዝቅተኛ ነው፡፡ እነዚህ የሚያንቀላፉ ግዙፍ አገሮች ደግሞ ነዳጅ በመላክ የሚታወቁ  ናቸው፡፡ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ የነዳጅ ዘይት ጉልህ ቦታ ሲኖረው፣ ብዙውን ጊዜ ባንኮች ለሌሎች ዘርፎች ወይም ለሸማች ገበያው ብድር ከመስጠት ያፈገፍጋሉ፡፡ በእነዚህ ገበያዎች የብድር አገልግሎት ሽፋን ሦስት በመቶ ብቻ መሆኑንም እናያለን፡፡ ይህም ከአራቱ ዓይነተኛ ገበያዎች ዝቅተኛው ሽፋን ነው፡፡ የሞባይል የገንዘብ ዝውውር በመሳሰሉ ዘርፎችም አዲስ አሠራር እምብዛም ነው፡፡

የመጨረሻው ዓይነተኛ ገበያ ገና ለጋ ገበያ ሲሆን፣ ዝቅተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢና የሀብት ሥርጭት ያላቸው ኢትዮጵያና ታንዛንያ የመሳሰሉ አገሮችን ያካትታል፡፡ 100 ሚሊዮን የሆነው ከፍተኛ የሕዝብ ብዛቷ ከፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገቷ ጋር ተዳምሮ፣ ኢትዮጵያን ለውጭ ባንኮች እጅግ ማራኪ ገበያ ያደርጋታል፡፡ 

የወደፊቱ የአፍሪካ የባንክ አገልግሎት – የሞባይል ባንኪንግ አብዮት 

የባንክ ተጠቃሚ ያልሆኑ በርካታ ሕዝቦችና አንዳንዴም በከተሞች መካከል ሰፊ ርቀት ባሉባት አፍሪካ ሞባይል በወደፊቱ የባንክ አገልግሎት ያለ ጥርጥር ወሳኝ ሚና ይኖረዋል፡፡ በአፍሪካ የባንክ አገልግሎት ቀጣዩ ምዕራፍ በክልላዊ ባንኮች መምጣትና በትልልቅ ተቋማት ብቅ ብቅ ማለት እየተገለጸ ይገኛል፡፡ ኢንዱስትሪው ወደ ሞኖፖሊ እየተጓዘ ባለበት ሁኔታ፣ አሁን እየመጣ ባለው ሁነት ቴክኖሎጂ እንደ ጀርባ አጥንት ያገለግላል፡፡

በወደፊት የአፍሪካ ባንኮችና በአጠቃላይ በባንክ አገልግሎት ላይ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናሉ፡፡ የአፍሪካ ተለዋዋጭ የቢዝነስ ከባቢ በአኅጉሪቱ ላይ የሞባይል ባንኪንግን በጥልቀት ለማስፋፋት፣ ባንኮች የኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል ይሰጣል፡፡ ይህም በቂ የባንክ አገልግሎት ያላገኙና ጨርሶ የባንክ ተጠቃሚ ያልሆኑት፣ በሞባይል ስልካቸው አማካይነት የፋይናንስ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ የፋይናንስ አካታችነትን የማሳደግ አቅም አለው፡፡ በአኅጉሪቱ ያሉ ደንበኞች ከቅርንጫፎች ባሻገር አማራጭ የአገልግሎት አቅርቦቶችን ለመጠቀም ይበልጥ እየሻቱ ነው፡፡ ሞባይል ባንኪንግ የአፍሪካ ዜጎች የሚሠሩበትን፣ የሚኖሩበትንና የንግድ ሥራ የሚያከናውኑበትን መንገድ እየቀየረው ነው፡፡

የክልላዊና የፓን አፍሪካን ባንኮች መምጣት

ስኬታማ የአፍሪካ ባንኮች እያደጉም እየተስፋፉም ነው፡፡ ክልላዊ መስፋፋት ዋነኛ የአፍሪካ ባንኮች ስትራቴጂዎች አካል ሆኗል፡፡ እነዚህ በአገር ውስጥ በመንቀሳቀስ የሚታወቁ ባንኮች ለማደግ የማያቋርጥ ፍለጋቸውን በመቀጠላቸው፣ እንዲሁም በአገራቸው የገበያ ፉክክሩ ሲያይል የገቢ ምንጫቸውን የሚያሰፉበትን መንገድ በመሻታቸው፣ አሁን 15 ገደማ የባንክ ቡድኖች ከአገራቸው ክልል ውጪ በሆኑ አገሮች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከፉክክር እየጨመረ መምጣት ጋር ተያይዞ ቀልጣፋ አገልግሎትና አዳዲስ አሠራሮች  አብበዋል፡፡  

በአፍሪካ የባንክ ኢንዱስትሪ ክልላዊ በመሆን የስኬት አብነት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል የኬንያ ባንኮች ይገኙበታል፡፡ ለምሳሌ የኬንያ ንግድ ባንክ፣ የአፍሪካ ንግድ ባንክ፣ ኢኩቲ ባንክና ኮ ኦፕ ባንክ ወደ ኬንያ የምሥራቅ አፍሪካ ጎረቤት አገሮች (ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛንያ፣ ኡጋንዳ፣ ቡሩንዲና ሩዋንዳ) ስኬታማ መስፋፋት አድርገዋል፡፡

ከክልላዊ ባንኮች ባሻገር ሌላው እየመጣ ያለው አዝማሚያ፣ የባንኮች ክልላዊ ድንበሮችን መሻገርና ከከፍተኛ የገበያ ዕድገት ተጠቃሚ ለመሆን ከአገራቸው በእጅጉ ርቀው መንቀሳቀሳቸው  ነው፡፡ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው  ጥቂት  የናይጄሪያ ባንኮች በመላው አፍሪካ ያደረጉት ፈጣን መስፋፋት ነው፡፡ እነሱም የአፍሪካ ዩናይትድ ባንክ፣ ፈርስት ባንክ ኦፍ ናይጄርያ፣ አክሰስ ባንክና ዜኒት ባንክ የሚገኙበት ሲሆን፣ እነዚህ ባንኮች አሁን በአኅጉሪቱ ውስጥ በስፋት ይገኛሉ፡፡

በልማድ በሰሜን አፍሪካ ውስጥ በንቃት በመንቀሳቀስ የሚታወቁት የሞሮኮ ባንኮች፣ ከበርካታ አገራዊ ባንኮች አክሲዮኖችን በመግዛት ቀዳሚነቱን ይዘዋል፡፡ መቀመጫውን በሌጎስ ያደረገው የአፍሪካ ዩናይትድ ባንክ፣ ናይጄሪያን ጨምሮ በ19 የአፍሪካ አገሮች እንዲሁም በፈረንሣይ፣ እንግሊዝና አሜሪካ ውስጥ ይንቀሳቀሳል፡፡

የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የመፍቀድ ፋይዳዎች  

የፓን አፍሪካን ባንኮች መምጣት ለአስተናጋጁ የባንክ ዘርፍ ፉክክርና ቀልጣፋ አሠራርን አሳድጓል፡፡ አዳዲስ የአሠራር ዘዴዎችንና ይበልጥ ዘመናዊ የአመራርና ኢንፎርሜሽን ሲስተሞችን አስተዋውቋል፡፡ የላቁ ክህሎቶችና ሙያዊ  ብቃቶችን  አምጥቷል፡፡ በርካታ የፓን አፍሪካን ባንኮች፣ አዳዲስ የቢዝነስ ሞዴሎችንና የአገልግሎት አሰጣጥ መንገዶችን (ለምሳሌ የሞባይል ባንኪንግ በኬንያ ተቋማት) ለአስተናጋጅ አገሮች ልከዋል፡፡ እነዚህ ግስጋሴዎች የባንክ አገልግሎቶችና አሠራሮች ተደራሽነት  (የፋይናንስ በጥልቀት መስፋፋት) እንዲስፋፋ አግዘዋል፡፡

የፓን አፍሪካን ባንኮች በቂ የባንክ አገልግሎት አቅርቦት ለሌላቸው ሰዎች የባንክ አገልግሎቶችን ሰጥተዋል፡፡ ለምሳሌ የኬንያ ባንኮች በሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አባል አገሮች ውስጥ ሥራቸውን ሲጀምሩ፣ በወኪልነትና በሞባይል ባንኪንግ ዘርፍ ያካበቱትን ሙያዊ ክህሎት በቂ የባንክ አገልግሎት ተደራሽነት ለሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ አገልግሎት ለመስጠት አውለውታል፡፡ 

በተመሳሳይ የሞሮኮ ባንኮች ፈረንሣይኛ ተናጋሪ በሆኑ የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ውስጥ የጥቃቅን የገንዘብ ተቋማት አሠራሮችን ያስፋፉ ሲሆን፣ ቅርንጫፎቻቸው ደግሞ ለአነስተኛና ለመካከለኛ የንግድ ተቋማት ብድር መስጠት ላይ አተኩረው ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የናይጄርያ ባንኮች በምዕራብ አፍሪካ የቅርንጫፎችን ቁጥር በማሳደግ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በተለይ በገጠር አካባቢዎች፡፡

የፓን አፍሪካን ባንኮች መከሰት አስተናጋጅ አገሮች የፋይናንስ አመራር ደረጃቸውን ለማሳደግ ሊያግዛቸውም ይችላል፡፡ ያደጉ የአፍሪካ አገሮች ባንኮች፣ በቅርንጫፎቻቸው ውስጥ የአገራቸውን  የላቀ የፋይናንስ አመራር ደረጃ የሚተገብሩ  ሲሆን፣ የአስተናጋጅ አገሮች ኃላፊዎች ከዘመናዊ የሪፖርት አቀራረብና የቁጥጥር አሠራሮች  ጋር ይተዋወቃሉ፡፡ ለምሳሌ በባስል ኮሚቴ (የባንክ አሠራርን የሚቆጣጠር ዓለም አቀፍ ቡድን) ዕውቅና ያገኘው የካፒታል ስታንዳርድና በዓለም አቀፍ የአካውንቲንግ ስታንዳርድስ ኮሚቴ የተደነገገው  ዓለም አቀፍ የፋይናንስ  ሪፖርቲንግ ስታንዳርድስ፡፡

የድንበር ተሻጋሪ የባንክ ቡድኖች በመላው አፍሪካ መስፋፋት ለአስተናጋጅ አገሮቹ ኢኮኖሚዎች መልካም አጋጣሚዎችንና ጠቀሜታዎችን ይፈጥራል፡፡ የፓን አፍሪካን የባንክ ቡድኖች መስፋፋት ጠቀሜታዎች (አፍሪካዊ ካልሆኑ የውጭ ባንኮች አንፃር) ፉክክር፣ ቀልጣፋ አሠራር፣ የፋይናንስ በጥልቀት መስፋፋትና አቃፊነትን ያካትታል፡፡

ድንበር ተሻጋሪ ባንኮች ፉክክርን በማሳደግ የላቀ ክህሎትና የሙያ ተደራሽነትን በማጎልበት፣ የተሻለ የካፒታል ተደራሽነትን በመፍጠርና ኢኮኖሚውን በማስፋት የአስተናጋጅ አገሮችን የባንክ ዘርፍ ይጠቅማሉ፡፡ ይበልጥ በስፋት ሲታይ፣ የአስተዳደር መዋቅሮችን በማሻሻል በጎ ተፅዕኖ ሊፈጥሩም ይችላሉ፡፡

ያላደገ የባንክ ዘርፍ በሚገኝበት የኢትዮጵያ ዓውድ ውስጥ የበለጠ ክህሎት ያላቸው፣ በተሻለ መንገድ የተመሩና የተሻለ የገንዘብ አቅም ያላቸው ተፎካካሪዎች መምጣት ትርጉም ያለው በጎ አስተዋፅኦ ሊያበረክት ይችላል፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ባንኮች ከአገራቸው የተለየ ሙያዊ ክህሎትን በማምጣት የፋይናንስ አካታችነትን ያስፋፋሉ፡፡ ቀድሞ የባንክ  አገልግሎት ያላገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎችን መድረስ  ከቻሉ፡፡

በባንኮች መካከል ጠንካራ ፉክክር ሲኖር ለብድር አገልግሎቶች የሚከፈለውን የወለድ መጠን በእጅጉ ዝቅ ያደርገዋል፡፡ ብድር የሚሰጡ ባንኮች ሲበራከቱ የአገር ውስጥና የውጭ ተበዳሪዎች የአነስተኛ ወይም ትልቅ ቢዝነስ የብድር አገልግሎት በማራኪ የወለድ መጠንና ውል ለማግኘት ይችላሉ፡፡

መንግሥት ለአገራዊ  ባንኮች ከለላ የሚያደርገው ለምንድነው?

ለአገራዊ  ባንኮች ከለላ ማድረግ ስንል በትክክል እየተናገርን  ያለነው  ስለማነው? ስለአክሲዮን ባለቤቶች? ስለደንበኞች? ወይስ ስለኢኮኖሚው? ጉዳዩ በእርግጠኝነት ደንበኞችን የሚመለከት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ በአፍሪካ እጅግ ወደ ኋላ ከቀሩት  አንዱ ነው፡፡ ፉክክር ወይም አዲስ አሠራር የሌለውና የተዘጋ ገበያ ከመሆኑ ጋር ተደምሮ፣ ለኢኮኖሚው ትልቅ ማነቆ ነው፡፡ የብዙኃኑ ሸማች ገበያ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አይደለም፡፡ አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ተቋማትና ግለሰቦች ውስን የብድር  አቅርቦት ነው ያላቸው፡፡  

የግል ባንኮች ባለ አክሲዮኖች (በግምት 120 ሺሕ ገደማ የሚደርሱ) እና ሁለቱ በመንግሥት ባለቤትነት የተያዙ የፖሊሲ ባንኮች ብቻ ናቸው ከውጭ ባንኮች መገለል የሚጠቀሙት፡፡

ማጠቃለያ

የውጭ ኢንቨስትመንትን ከባንክ ዘርፉ በሚያገለው ፖሊሲ ሳቢያ ኢኮኖሚው ከፍተኛ ዋጋ እየከፈለ ነው፡፡ ፉክክር፣ ቀልጣፋ አሠራር፣ ፈጠራና አካታችነት በከፍተኛ የኢኮኖሚ ዋጋ መስዋዕት እየተደረጉ ነው፡፡ የአሁኑ ዝግ የባንክ ዘርፍ ፖሊሲ ለምን ኖረን? ቀደም ሲል በዝርዝር ከቀረበውና የዚህ ፖሊሲ ፈጣሪ ከነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ አስተያየት በግልጽ መረዳት ይቻላል፡፡ አሁን ከ20 ዓመታት በላይ ያለፈ ሲሆን፣ ፖሊሲው እጅግ ትልቅ ለሆነውና ይበልጥ ለዳበረው ለዛሬው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚመጥን አይደለም፡፡

ፖሊሲን መለወጥና የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድን በተመለከተ እምብዛም ማቅማማት ሊኖር አይገባም፡፡ ዝግ የባንክ ዘርፍ ካላቸው የመጨረሻዎቹ የዓለም አገሮች ውስጥ  አንዱ እኛ ነን፡፡  በዚህ ረገድ ኤርትራና ሰሜን ኮሪያን የመሳሰሉ አገሮች አጋሮች ነን፡፡ ትንሿ ጂቡቲ፣ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳን እንኳን በኢኮኖሚያቸው ውስጥ በውጤታማነት የሚንቀሳቀሱ የውጭ ባንኮች አሏቸው፡፡ እኛ፣ ኤርትራና ሰሜን ኮሪያ ትክክል ሆነን የቀረው ዓለም ተሳስቶ ይሆን? የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከመሠረታዊ የኢኮኖሚክስና የፋይናንስ ሳይንስና መርሆዎች ውጪ የሚሆንበት የተለየ ሁኔታ አለው እንዴ? በዚህ ወቅትና ዘመን ምን ዓይነት ልማታዊ መንግሥት ነው ዝግ የባንክ ዘርፍ ያለው? ለምንድነው እኛ ዝግ የባንክ ዘርፍ ሊኖረን የቻለው?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል [email protected] አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...