Thursday, July 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትራስን ሕግና ፈራጅ ማድረግ በሕግና በመብት የመኖር ሥርዓትን አያዋልድም

ራስን ሕግና ፈራጅ ማድረግ በሕግና በመብት የመኖር ሥርዓትን አያዋልድም

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

የሰው ልጅ ኑሮ ውጤቶች በአካባበቢውና በራሱም ተፈጥሮ ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ (ለውጥ) ያስከትላሉ፡፡ እያንዳንዳችን የወላጆቻችን ውጤት የሆንነውን ያህል በጥቅሉ የማኅበራዊ ዓውዳችን ውጤትም ነን፡፡ እያንዳንዳች የተገኘንባቸው የእናትና የአባት አባለዘሮች የተፈጥሮና የሰው ልጅ ኑሮ የዘመናት ተራክቦ ውጤት እንደሆኑ ሁሉ፣ እያንዳንዱ ፅንስና ሽል ዕድገት ላይ የኑሮ ድሎታችንና ጉዳቶቻችን የተፅዕኖ አሻራቸውን ያሳርፋሉ፡፡

ሽል ማህፀን ውስጥ ዕድገቱን ጨርሶ ከተወለደ ጊዜ አንስቶ ደግሞ በማኅበራዊ ኑሮ ማህፀን ውስጥ ተከታይ ዕድገቱን ይቀጥላል፡፡ ማኅበራዊ ማህፀን ስንል የቤተሰብና ከቤተሰብ ውጪ ያለውን ማኅበራዊ ዓውድ አንድ ላይ መግለጻችን ነው፡፡ ልጅ ገና ሲወለድ አንስቶ ከቤተሰብና ቤተሰብ አለፍ ከሆኑ መስታጋብሮች ጋር ይገናኛል፡፡ በዚህ በማኅበራዊ ማህፀን አሳዳጊነት ውስጥ በመጀመርያ ላይ የቤተሰብ ሚና ዋነኛውን ድርሻ ቢወስድም፣ በዕድገት ጉዞ ውስጥ የቤተሰብና የቤተሰብ ዘለል የድርሻ መጠኖች እየተቀየሩ ይሄዳሉ፡፡

በማኅበራዊ ኑሮ ማህፀን ውስጥ ያሉ የልዩነትና የተዛማጅነት ድርና ማጎች ልጆችን አዝጎርጉረውም አመሳስለውም ይቀርፃሉ፡፡ ቀላል የጨረፍታ ምሳሌዎች ለመስጠት ያህል፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ተወዳሽነት ዘመን ውስጥ ከጉልበት ሥራ እስከ ምርትና ጥሬ ገንዘብ ድረስ የሚገብር ገበሬና ጭሰኛ እንደነበረ ሁሉ፣ በጭሰኛ ላብ የሚኖር ደቃቃና የደረጃ ባለርስትም ነበር፡፡ ለምሳሌ እኔ በወጣትነቴ በማቃቸው ደጀዝማች ግቢ ውስጥ በአሸከርነት እያገለገሉ ይማሩ የነበሩ የተቋጥሮ ዘመድና የጭሰኛ ልጆች ነበሩ፡፡ እጅ ለመንሳትና ደጅ ለመጥናት ከገጠር እየመጡ እዚያው ለባላገር ማረፊያ በተሠራ ቅፅር የሚያርፉም አይታጡም ነበር፡፡ የደጃዝማችን ቤተሰብ የሚያገለግሉ ቄስም በዚያው ግቢ ውስጥ በቋሚነት ይኖሩ ነበር፡፡ ደጃዝማቹ ከውጭ ሲመጡ ከመኪና ወርደው ቤት እስኪገቡ ድረስ፣ በግቢው የነበረ ሰው ሁሉ ሚስት ሆኑ ልጆች ውይም እንግዳ ቆመውና አለባበሳቸውን አስተካክለው መቀበል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሊወጡ ነው ሲባልም እንደዚያው፡፡ ልጆቻቸው ሊያናግሯቸው ሲፈልጉ እንኳ በእልፍኝ አሽከር ወይ በእናት በእኩል አሳውቀው የኮት ቁልፋቸውን በወጉ ቆልፈው መግባት፣ እጅ መንሳትና በአንቱታ መጥራት ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ እሳቸው ቤት ውስጥ ልጅና አሽከር ሆኖ ማደግና የእሳቸው ይዞታ በሆነ የከተማ/የገጠር የተንጣለለ መሬት ላይ ጭሰኛ በሆኑ ሰዎች ኑሮ ውስጥ ማደግ ውጤቱ አንድ ዓይነት አይሆንም፡፡

የአፄውና የባለርስት አስገባሪነት ሥርዓት ፈርሶ አብዮተኛ ነን የሚሉ ቡድኖች ይገዳደሉ በነበረበትና “ፍለጠው! ቁረጠው!” በሚሉ “አብዮታዊ” ዘፈኖች በተሞላ አንቀጥቃጭ ማኅበራዊ አየር ውስጥ ማደግ፣ በቀይ ሸብር ነጭ ሽብር ልጆቹን በተነጠቀ መናጢ ቤተሰብ ውስጥ ማደግ፣ “ርስቱ”ንና የሚከራይ ቤቱን፣ ሁሉ ተወርሶ አንድ በተረፈችለት ቤት ጠጅ ነገር ከፍቶ ያለፈ ድሎቱን እያመሰኳ በሚቆዝም ወላጅ ማደግ ይለያያሉ፡፡ ብሔርና ቋንቋ ላይ ያተኮሩ ክልሎች በተፈጠሩበት በሕወሓት (ኢሕአዴግ) ዘመን ውስጥ፣ ከመባረር የተረፈ ኤርትራዊ ቤተሰብ ውስጥ፣ በመጤነት የተንጓለለ ቤተሰብ ውስጥ፣ ፀረ ሰላም/አሸባሪ የተባለ ድርጅት አባል ናችሁ የሚል አጎሳቋይነት በተመላበት ቤተሰብ ውስጥ ማደግ ብዙ ልዩነት ያመጣል፡፡ በጠቃቀስናቸው ሦስቱም ሥርዓቶች ውስጥ ጭው ባለ የገጠር ጨለማ ውስጥ መኖርና በከተማ ውስጥ ብዙ ዓይነት ማኅበረሰባዊ አመጣጥ ባለቸው ሰዎች መሀል በብዙ ዓይነት የሥልጣኔ ግሳንግስ ተከቦ ማደግ፣ የሰማይና የመሬት ያህል ውጤቱ የተራራቀ ነው፡፡ በምዕራብ የቁሳቁስ፣ የፊልምና የቲቪ ውጤቶች እየተኮተከቱ ማደግ ወጣቶችን በ‹ፋራነትና› በ‹አራዳነት› ዘመናይነት እየለየ ይዘረዝራል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ‹ፋራ› ተብለው ሳይሳቅባቸው ዘመናይነትን ለመቀላቀል የሚሹ ወጣቶች ጫት አቃቃምንና ሲጋራ አጫጫስን ተደብቀው እስከ መለማመድ ድረስ ይሄዳሉ፡፡ ጭው ባለ የሐረርጌ ገጠር ውስጥ ከተወለደበት መንደር ባልራቀ ክትር ኑሮ ውስጥ ኦሮሚኛን እስላምኛ ብሎ የሚጠራ፣ ስሙ መሐመድ ሆኖ አማራ ነኝ የሚልና ኦሮሚኛ የማይችል ሰው ቢያጋጥመው ጉድ የሰማ ያህል የሚገርመው ገበሬ ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ በጎንደር አርማጭሆ ውስጥ ደግሞ ከሕግ መንገድ ይልቅ ጥቃትን በጥይት የሚመልስ፣ በጥንቱ የባሪያ ‹ዘር›ና የጠራ ‹ዘር› አመለካከት ውስጥ ገና እየኖረ ያለ ሰው ዛሬም ልናገኝ እንችላለን፡፡ የዛሬ ወጣቶች በጥቅሉ ያሉን ዝንጉርጉር የአስተሳሰብ ዝግንትልና ሥነ ልቦናዎች ከቤተሰብ እስከ ደጅ (እስከ ባልንጀራ፣ አስከ ትምህርት ቤትና እስከ ኤሌክትሮኒክ ሚዲያ ድረስ፣ ወዘተ) የረዘሙ ቀጥተኛና ዘዋራ መስተጋብሮች ውጤቶች ናቸው፡፡

ማኅበራዊ አካባቢያችን ያሳደገን መልካም ምግባሮቹንና ሐሳቦቹን እየሰጠ ብቻ ሳይሆን ጥላቻዎቹን፣ ሸሮቹን፣ ጭፍን አመለካከቶቹንና አቋሞቹን ሁሉ እየሰጠን ነው፡፡ በየዕድገት ደረጃችን እያንዳዳችን የሚኖረን የልቦናና የህሊና ሙሽት፣ በውጫዊ ሰበዞችና በእያንዳንዳችን ውስጣዊ አቅም መስተጋብር የሚወሰን ነው፡፡ ለምሳሌ “ጡጥ” የሚል ድምፅ ሲሰማ የያዘውን ዕቃ የሚወረውር ወይም ፊቱ ያገኘውን ሰው የመምታት አመል ያለበት ሰው የማንም መጫወቻ ለመሆን የተጋለጠ ነው፡፡ በዚሁ አመሉ ምክንያት ከሰው ጋር በቀላሉ ሊጋጭ ይችላል፡፡  ብዙ ወጣቶችም ዛሬ የ“ጡጥ” አመለኝነት ዓይነት ችግር ውስጥ ነን፡፡ “ትግሬ የሚባል ሰው!…”፣ “አማራ! አማራ! …”፣ “ኦሮሞ ድሮስ…” ወዘተ የሚሉ ዓይነት ጅምላና ግልብ ሽክሹክታዎችንና የተዛቡ ግንኙነቶችን እየተነፈስን ያደግን ወጣቶች ደግሞ፣ የሚቆራኘን ጭፍን ድምዳሜና ጥላቻ ቀመስ ዝንባሌ ከ”ጡጥ” አመል በላይ የጠለቀ ነው፡፡

አንድ ቀን በአዳራሽ ተገናኝቶ እየተላቀሱ ይቅር በመባባል ያደጉበትን፣ የኖሩበትንና አሉታዊ ስሜትና አመለካከት ማጠብ አይቻልም፡፡ ላዩን ስሜታችን ሲቀልና እፎይታ ሲሰማን የለቀቀን ይመስላል እንጂ፣ ከሥር አሸልቦ ይቆይና ለግርሻ የሚስማማ አጋጣሚ ሲያገኝ ብቅ ይላል፡፡ የሆነ አናዳጅ ድርጊት ተፈጥሮ ገና ማን እንዳደረገው እንኳ ሳይታወቅ “ያለነሱ ይኼንን የሚያደርገ የለም!! እነሱ! እነሱ! …” የሚል ጭፍን ግምት ውስጥ ከገባንና ግምታችንን የእውነት ያህል አምነን ከበገንን፣ ከዚያም ይባስ ብለን አንድን ጥፋት የጠቅላላው ብሔረሰብ ባህርይ አድርገን አቅራቢያችን ያገኘናቸውን ንፁኃን ለመበቀል ከተነሳሳን እዚያው ጥላቻ ውስጥ ነን ማለት ነው፡፡ ጥላቻንና ጭፍን ፍረጃን ተገላገልነው ማለት የምንችለው ጥፋቶችንና ጠቦችን የመላ ብሔረሰብ ከማድረግ ፈንታ፣ የግለሰቦች አድርጎ መውሰድ ውስጥ ስንገባ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ እስካልገባን ድረስ ምን ብንሳሳቅ ጭፍን አመለካከቶቻችንና ስሜቶቻችንን በሳቅ ውስጥ ከመደበቅና ዓይን አፋር ከማድረግ አላለፍንም፡፡

የጭፍን ስሜቶችና ድምዳሜዎች ተገዢ ሆኖ አንድ ነገር በተፈጸመ ቁጥር፣ የጭፍን ቁጣና ግምታዊ ፍርድ ፈረሰኛ ሆኖ የግርታ ቅጣት በንፁኃን ላይ ማውረድ ዘግናኝ እውርነት ነው፡፡ የስሜት ባርነትም ነው፡፡ ለዚህ ዓይነት እውር ቀጪነት እጅ ሰጥቶ ከዛሬ ነገ የቁጣ እሳት ወረደብኝ እያሉና ጅምላ ማኅበረሰብን እየፈሩ መኖርም (ሲመቸው የዚያው ዓይነት ጅምላ ተበቃይነት የማያጣው) ሌላ የባርነት ገጽ ነው፡፡

ከሌላ ክልል በመጣ የኳስ ቡድን የራስ ቡድን “በገዛ ምድሩ” ላይ መሸነፉ ክልላዊ መዋረድና መሸነፍ ተደርጎ ከታየ፣ ድብደባም የሽንፈት ማካካሻ ሆኖ ከተቆጠረ፣ ድብደባን ለማስቆም መሞከርና አጥፊዎችን ለሕግ አሳልፎ መስጠት በፖሊስም በተመልካችም የገዛ ክልልን እንደመካድ ተደርጎ ከታየ፣ ይኸው አመለካከት “መጤ” የተባለ ወገን ላይ ንብረት በመዝረፍ፣ በማቃጠልና ነፍስ በማጥፋት ቢገለጽ ምን ይደንቃል? በአንዲት ሐሰት ወሬ ወደ ጅምላ ቁጣና ጭፍን ዕርምጃ ለመነዳት ከመቅለል በላይ መጫወቻ የመሆን ምን ውድቀት አለ? ቦምብ ይዟል የሚል ሽውታን እውነት ይሁን ውሸት ለማጣራት ጊዜ ሳይሰጡ፣ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን ያረፈደችው ኢትዮጵያ በዴሞክራሲና በፍትሕ ውስጥ ለመኖር በምትጥርበት ሰዓት፣ ራስ ሕግ ሆኖ በዘመነ አረመኔነት በነበረ ጭካኔ ሰውን ቀጥቅጦ ከመግደል በላይ የኋሊት ጉዞ ምን አለ? የማገናዘብና የርህራሔ አቅምን ለአንድ ግፈኛ ፈላጭ ቆራጭ አስረክቦ ብጤ ፍጡርን የሚከትፍና በእሳት የሚያንጨረጭር የግፍ በትር መሆን ደግሞ ከሁሉም የከፋ ነው፡፡

ድቀታችን ይኼንን ያህል መክፋቱን ወጣቶቻችን እንዳይመለከቱ ደግሞ የቅርብ ፖለቲካ ልምዳችን ልብ የሚደፍን ግብዝነትን አሳቅፎናል፡፡ ከግንፍልነትና ከውድመት ጋር የተዋደደ የቅርብ ጊዜ ትግል የአሁኑን የለውጥ ዕድል ለማዋለድ በመታደሉ ብቻ፣ አደገኛ አንሸራታች መንገድነቱ ተጋርዶ እየተወደሰ ይገኛል፡፡ ይህ መሆኑም ወጣቶች ግርታን እንደ በጎ ሥልት አቅፈው እንዲይዙት፣ ሁሉን ማድረግ እንደሚችል ወንበር ያልያዘ ገዥ ወይም አንቀጥቅጥ ፓርቲ አድርገው ራሳቸውን እንዲያስቡ እያገዘም ነው፡፡ ዱቄት ተገኝቶ እህል ለመቅመስ መቻል ዱቄቱ የተገኘበትን የትኛውንም መንገድ ትክክል አያደርገውም፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ሳይወድ ነው ወደ ለውጥ የገባው ብሎ ማለት እውነትነቱ ከፊል ነው፡፡ የወጣቱ ከጥፋት ጋር የተዛመደ ትግል ወደ ፍጅት ሊንሸራተት ይችል እንደ ነበር ሁሉ፣ የኢሕአዴግም ገዥነት የነበረው ምርጫ የጠቅላይ ሚኒስትር ለውጥ ብቻ አልነበረም፡፡ ኢሕአዴግ የከፋ ፈላጭ ቆራጭነትን መርጦ ቢሆን ኖሮ፣ የወጣቱ ትግል የዚህ ዓይነት ጨካኝ አገዛዝ አማጭ ተደርጎ መታየቱ አይቀርም ነበር፡፡ ትግራዊ ሰዎች ላይ የደረሱ ጥቃቶች ሠራዊቱንና የደኅንነት አውታራቱን እስከ መከፋፈልና ብሔረሰብ የለየ መከታከት ውስጥ እስከ መግባት አንከባለውት ቢሆን ኖሮ ደግሞ፣ የመቀመቅ ጉዟችን መቆሚያው በራቀ ነበር፡፡ ከጥፋት ጋር የተያያዘ የግርታና የቱግታ ትግል አደገኛና ውጤቱ የማይታወቅ እንደነበር፣ ይህ የትግል ሥልት የሙገሳ ዘውድ ሊደፋ የቻለው የኢሕአዴግ ገዥዎች የወሰዱት ምርጫ ቀና ምርጫ ስለሆነ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡

ወጣቱ ባንድ ጊዜ አገር ተረካቢም ገንቢም የመሆኑ ሚስጥር በታላላቆቹ ሥር የሚበስልና የሚተባ ለጋ ግን ባለብዙ ዕምቅ አቅም መሆኑን ከዘነጋ፣ ታላላቆቹም (ምሁራንና መዓት ፖለቲከኞች) መግራት የማይችሉ ተመልካቾች ከሆኑ ከዚህ የበለጠ ተያይዞ ጉዞ ወደ መቀመቅ ምን አለ!? ሜዳ ያጣበበው ፓርቲ ንቅናቄ ነኝ ባይ ሁሉ፣ እዚያም እዚያም ቱስ ቱስ እያለ የሚያንገላታንን ግጭትና ግርግር ሕግንና ሥርዓትን ወደ ተከተለ ትግል መምራት ካልቻለ የፖለቲካ ሰውነት አለኝ ሊል ነው? ይህን ሁሉ ከጀርባ ሆነን የምንለኩሰው እኛው ነን (ዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ እንዲፈጥን) የሚል ካለም መቸም ዝቅጠቱ ከሚታሰበው በላይ ከፍቷል ማለት ነው፡፡ ሶማሌ ክልል ውስጥ በቤተ እምነት ላይ የተደረገ ጥቃት ደም ፍላታም አፀፋን በሌላ ሥፍራ የመጥራት ነገረኛነት ነበረው እኮ! የዚህ ዓይነት የበቀል ምልልስ መከፈት ወዴት ይዞን እንደሚሄድ ለፖለቲከኞቹ ማስታወስ ያስፈልጋል! አስፈሪው ልምድ እኮ ለፖለቲከኛውም ለሕዝብም፣ ለወጣቱም የመዘናጊያ ጊዜ የለምና አንድ ላይ ተረባርበን፣ ከአፍንጫ ከማይርቁ ብጥስጣሽ ፍላጎቶችና ከታወረ ግንፍልነትና ግርታ መጫወቻነት የሚያላቅቅ የአተያይና የፖለቲካ አደረጃጀት (የፓራዳይም) ለውጥ እንዲመጣ መፍጠንን የሚጎተጉት ነው! በዚህ ዓይነቱ ሥርዓት አልባነት ውስጥ እየዳከሩና የፍትሕና የእኩልነት ጠንቅ እየሆኑ ወይም የዚህ አሽቆልቋይ ጉዞ ተመልካች ሆኖ ዴሞክራሲና ፍትሕ ጠማን እንደምን ሊባል ይቻላል!!! 

የጅምላ ቀጪነትና ተቀጪነት መጫወቻ ከመሆን ነፃ ለመውጣት ለጅምላ አመለካከት መነሻ የሆኑ የተበላሹ እውነታዎችንና ግንኙነቶችን ለይቶ እስከ መቀየርና በሁለት በኩል ያሉ ብሶቶችንና ጉዳቶችን እስከ መረዳትና እስከ መጋራት የዘለቀ ዕርቅ ማድረግ፣ ዕርቁም እየጠነከረ እንዲሄድ መከባበርና መተሳሰብ ያልተለየው መቀራረብን እያሳደጉ መሄድ ግድ ነው፡፡ በገዥዎች ጣጣ ምክንያት የሆነ ሕዝብ ላይ የተላከኩ አሉታዊ ስሜቶች በአጭር ጊዜ የትግል ትግግዝም ሆነ፣ ያ ወይም ይህ ሕዝብ እንደ ሌላው ሕዝብ ሁሉ ተበዳይ ስለመሆኑ በመግለጽ ብቻ ተነቅሎ አይወገድም፡፡ ገና የተባበረ ትግልን የሚሻ ረዥም የዴሞክራሲ ሥርዓትና ባህል ግንባታ ከፊታችን እንደመደቀኑ፣ በዚህ የጋራ ትግል ጉዳይና በሚያስማሙ ሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ፖለቲከኞቹና ምሁራኑ ተያይዘው ለወጣቶች ምሳሌ መሆናቸው፣ ወጣቶችም በየአካባቢያቸውም ውስጥ ሆነ አካባቢያቸውን በዘለለ ደረጃ እስከ ማዕከላዊ ከተማ ድረስ በኅብረ ብሔራዊ መድረኮች እየተገናኙ መወያየቻቸው፣ ኅብረ ብሔራዊ የአጋርነትና የአንድነት ማኅበር ብጤም መፍጠራቸው እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

በሚያስማማሙ ጉዳዮች ረገድ ማዶ ለማዶም ሆነ በጋራ መድረኮች መስተጋብር ቢደረግም፣ ከበፊት ጀምሮ የተጻፉ ዛሬም እየተጻፉ ያሉ የተዛቡ ነገሮች ከመዛባት አልፎ እርግማንና ውዳሴ የሚያጎርፉ የፖለቲካና የታሪክ ስንክሳሮች ህሊናና መንፈስን መጎንተላቸው አይቀርም፡፡ በተለይ የቅርቡን የሕወሓት ገነን የጥርነፋ አገዛዝን የተመለከቱ ብዙ የግፍ ታሪኮች ገና ወደፊት የሚገለጡ እንደመሆኑ፣ የብሔረተኛ ገዥነት በደሎች የሚያሳድሩት መራራ ስሜት ወደ ብሔረሰቦችም ለመተላለፍ መተናነቁ አይቀርም፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን ፈተና ለማሸነፍ በአካባቢ ደረጃም ሆነ በፌዴራል ደረጃ የተካሄዱ ከቡድኖች ጋር የተያያዙ በደሎችንና ዘረፋዎችን፣ ሁሉም ሕዝቦችና ወጣቶች “የእኛ”፣ “የእነሱ” ሳይሉ አንድ ላይ ለመኮነን መቻላቸው ወሳኝ ዕርምጃ ነው፡፡ ከእነዚህ (ከጥፋተኛ) ቡድኖች ተፈልቅቀው የወጡ የለውጥ ወገኖችም በዚህ ሒደት ውስጥ ቀዳሚ ተዋናይ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

ወጣቶች ያልተጨፈነ አዕምሮ ለመቀዳጀት፣ ለጋራ መግባባትና ለዴሞክራሲ ሲሉ እስከ ዛሬ በመጻሐፍትም ሆነ በትምህርት ቤትና በሚዲያ የኢትዮጵያ ተብለው ሲባዘቱ የኖሩ የታሪክ ሐተታዎችን፣ በእርግማንም ሆነ በውዳሴ ወደ አፈ ታሪክነት የተቀየሩ የታሪክ ሰዎችን በአውነታዊ ዓይን ለመገንዘብ አዕምሯቸውን ክፍት ማድረግና ለዚህም የሚሆን የተዘማመደ የታሪክ አገዳ የሙያው ምሁራን እንዲሰጧቸው መጠየቅ አለባቸው፡፡ ይህ አገዳ በሚኖረው ተቀባይነት ላይ ልዩነት ሊኖር እንደሚችልም ከወዲሁ ማወቅ ላለመወራጨት ይበጃል፡፡ በተቀባዮች ደረጃ ይቅርና በታሪክ ሊቃውንቱ ደረጃም ይህ እንዲሆን አይጠበቅም፣ እንዲሆንም አይፈለግም፡፡ ምክንያቱም የትንታኔ ልዩነት የታሪክ ግንዛቤ ይበልጥ እየጠለቀና እየጠራ የሚሄድበት መንገድ ነውና፡፡

ዋናው ነገር ከሰሜን በኩል የአፄዎቹ መስፋፋት ከታች ከነበሩት መንግሥታት እንቅስቃሴና ከእነ አህመድ ኢብራሂም (“ግራኝ”) እንቅስቃሴ ጋር ተገናዝበውና ተዛምደው በአንድ አገር ግንባታ ውስጥ የተጫወቱት ሚና በክፍልፋይ ቲፎዞነት ሳይወላገድ መፈልቀቁ፣ የገዥዎቹ ዘመቻና መስፋፋት ደግሞ ከማኅበረሰቦች ወደ ላይና ወደታች እንቅስቃሴ ጋር፣ በተለይም ከኦሮሞ ግዙፍ እንቅስቃሴዎች ጋር ተሸራርቦ መመርመሩ ነው፡፡ ምክንያቱም ዋናው የታሪክ ሥዕል የሚገኘው ውስጣዊና ውጫዊ የገዥዎች የተስፋፊነት ጉዞዎችና ፍጭቶች ከማኅበረሰባዊ ፍልስቶች ጋር ተመጋግበው በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ግንባታና የአገዛዝ ታሪክ ላይ ያስከተሉት ፈትል ሲታይ ነው፡፡ 

ዛሬ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉ መረጃዎች ከጥንት አንስቶ እስከ ዛሬ ከሰሜን እስከ ደቡብ በተካሄደ የታሪክ ጉዞ ውስጥ ሁሉ የቅድመ ኦሮሞ (ፕሮቶ ኦሮሞ) እና የኦሮሞ አሻራና ተሳታፊነት ያለበት መሆኑን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡ በዚህ በኩል የዛሬዎቹ ወጣት የታሪክ ምሁራንም በነተቡና በደረቁ የታሪክ ሐተታዎች ሳይንጋደዱ፣ ለዛሬ የፖለቲካ ዝንባሌዎች ሳያጎበድዱ የታሪክ መረጃዎችን ለመበርበር ስልና ደፋር መሆናቸው በጣም ተፈላጊ ነው፡፡

በቁጥር የገዘፉት ኦሮሞና አማራ ዛሬ ወንድም ዘመዳም ሕዝቦች መባባላቸው፣ አምባገነናዊ አገዛዝን ከሞላ ጎደል ሰላማዊ ሊባል በሚችል የትግል ሥልት አንሸራቶ ወደ ዴሞክራሲ ፈር በማስገባት ክንዋኔ ረገድ የታየ ታክቲካዊ መደጋገፍን በማሞካሸት ደረጃ ጠቦ መታየት የለበትም፡፡ በታሪክ ዓይን የዛሬ ኦሮሞነትን ጀርባ ስናስተውል ዛሬ ልዩ ልዩ ብሔረሰብ ብለን የምንቆጥራቸውን ማኅበረሰቦችን እየዘገነ ኦሮሞነትን ማበራከቱን እንደምንረዳ ሁሉ፣ በኢትዮጵያ አያሌ ብሔረሰቦች ማንነት ውስጥ ራሱን ረጭቶና ተላልሶ ለሌሎች መበራከቻ እንደሆነም እናየናለን፡፡ በአማራነት አመጣጥ ታሪክም ውስጥ ልዩ ልዩ ማኅበረሰቦችና የማኅበረሰቦች ፍንጥቅጣቂዎች መዘማመዳቸውን እንደምናስተውል ሁሉ፣ አማርኛ ተናጋሪነት የትኛውም ብሔረሰባዊ ማኅበረሰብ ውስጥ ራሳቸውን መመደብ የሚቸገሩ በቅልቅል ማኅበራዊ ድባብ ውስጥ ያደጉ የአገር ልጀችንም ያመለክታል፡፡ ከእነዚህ ማኅበራዊ ባህርያት አኳያ ተነስነተን ኦሮሞነትንም ሆነ አማራነትን የኢትዮጵያ ሕዝቦች የተገለጡባቸው ሌላ ሁለት መልኮች አድርጎ ማየት ስህተት አይሆንም፡፡

ብሔረተኛ ፖለቲካ በኢትዮጵያ መንበረ ሥልጣንና የፖለቲካ ሜዳ ላይ ነግሶ ህሊናን በጠባቡ እይታዎች ለማሟሸት መቻሉና ዜጎችን ቤተኛና ባይተዋር አድርጎ ባንጓለለ አገዛዝ ያደረሰው ጉዳት ቀላል አይደለም፡፡ የፖለቲካ ጠንቄ ባሉት ሰው ላይ ወንጀል ፈልስፎ ወይም በተውሸለሸለ (ከባዶ በማይሻል) የሰውና የሰነድ ማስረጃ ‹‹ረትቶ›› ማስፈረድ የሚቻልበት የጭቦ አገዛዝ ከፌዴራል አስተዳደር እስከ ክልሎችና የወረዳዎች ጉራንጉር ድረስ መባዛቱ አንዱ ነው፡፡ የጭቦኝነት ግፉ ከትልልቅ ክስ (የታምራት ላይኔ፣ የስዬ አብረሃ፣ የቅንጅቶች ክስ) አንስቶ እስከ ትንንሽ የመሥሪያ ቤት አስተዳደራዊ ክስ ድረስ የተንሰራፋ ነው፡፡ የጭቦ እድፋምነቱም ቤተ መንግሥት ከገባው የአገዛዙ አውራ እስከ ትንንሹ የቀበሌና የወህኒ አለቃ ድረስ የተዛመተና የንፅህና ደረጃ የማይወጣለት ነበር ቢባል ማጋነን አይሆነም፡፡ የፍትሕ አልባነትን የከፋ ግፍ የምናገኘውን ግን በሌላኛው ገጽታ ላይ ነው፡፡ ለማነፃፀር እንዲመቸኝ ወደ ኋላ መለስ ልበል፡፡

የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘውድ አገዛዝን መንግሥት ሲመራ የነበረው የጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ ካቢኔ ከለቀቀ ጊዜ አንስቶ ደርግ በ1967 ዓ.ም. መስረከም ሙሉ ለሙሉ ሥልጣን መያዙን እስኪያውጅ ድረስ፣ የሥልጣን ወንበሩ ክፍት ሆኖ ቆይቶ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ የደርግ ፈላጭ ቆራጭነት ነኩቶ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ወደ ሐራሬ ከፈረጠጠበት ጊዜ አንስቶ፣ ኢሕአዴግ መላ አገሪቱን ለመቆጣጠር እስከ በቃበት ጊዜ ድረስ የሥልጣን ክፍተት ተፈጥሮ ነበር፡፡ በእነዚህ ክፍት ጊዜያት ውስጥ አንዱ ወገን ከሌላው የሕዝብ ወገን ጋር የተላተመበትና ጭፍጨፋና ማፈናቀል የተከሰተበት ድርጊት አልነበረም፡፡ በ1966 ዓ.ም. አብዮት ጊዜ የሕዝብ ሁሉ ትኩረት ብሶት በማስተጋባትና ጭቆና በቃኝ በማለት ላይ ያነጣጠረ ነበር፡፡ ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም በኋላ ተሰይሞ በነበረውና  ቤተ መንግሥት ጠባቂ ከመሆን ባልተሻለው መንግሥት ጊዜም፣ ሕዝብ ሥርዓት አልባነት ውስጥ ሊገባ ይቅርና ፀጥታው እንዳይናጋ እየተንከባከበ የደርግ ሌባ ሻንጣ ይዞ እዳይጠፋ እስከ መጠበቅ ድረስ ጨዋነት አሳይቶ ነበር፡፡ የተበታተነው የአገሪቱ ወታደርም ቢበዛ መሣሪያ ሸጦ እህል ከመቅመስ በቀር ዝርፊያ ውስጥ አለመግባቱ የሚደንቅ ነበር፡፡ ዝርፊያ የመጣው በመጨረሻ ሰዓት ወያኔ ከሚዘርፈው እየተባለ ነበር፡፡

ዛሬ ግን የመንግሥት ክፍተት በሌለበት፣ እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የመንግሥት ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማያውቅ የሕዝብ ድጋፍ ተጥለቅልቆ ያላንዳች የእበላባይነት ፍላጎት የሙገሳ ዘፈን እየተንቆረቆረለት፣ ቅኔ እየተዘረፈለትና በክርስቲያኑም በሙስሊሙም ሕዝብ አካባቢ “ከእግዜር የተሰጠ መሪ” ለመባል በቅቶ ሳለ፣ ከቦታ ቦታ ዘግናኝ የጥቃትና የጥፋት ግርግሮች ከመፈጸም አልተገቱም፡፡ እነዚህ ጥፋቶች የቱንም ያህል “ጥያቄ አለን” ከሚል ጉዳይ ጋር ቢያያዙም፣ በብጥስጣሽ ብሔረተኝነት የህሊና መኮመታተር ምን ያህል ሰላም ነሺ ድቀት እንደሆነ የሚያሳዩ መስታወቶች ናቸው፡፡

በብጥስጣሽ ብሔረተኛ ሚዛን ሕዝብን ከሕዝብ እያንጓለሉ የሚገዙና የሚዘርፉ አልጠግብ ባዮች (በ27 ዓመታት የኢትዮጵያ ልምድ እንደታየው)፣ “የእኛ” የሚሉትና የሚላቸው ሕዝብ ዘረፋና ግፋቸውን እንዳያይባቸው ለመከለል ወይም በደላቸው የአደባባይ ሚስጥር ሆኖ ሕዝብ ሊተፋን ነው የሚል ሥጋት ሲገባቸው፣ በክልላቸው ውስጥ ባሉትና ባይተዋር ተደርጎ ለመታየት በተፈረደባቸው “መጤ” ማኅበረሰቦች ላይ፣ ሀብትና ጥቅም ተቀራመቱ ወይም ምሥጋና ቢስ እብሪትና መዳፈር አሳዩ የሚል ዓይነት ነገር እየሠሩ፣ ወይም ተጎራባች ሕዝብ ወሰን እየገፋ ስለመሆኑ ወሬ አቡክተውና ፀብ አስነስተው በዜጎች እንባና ደም ለብሔራቸው ‹‹ተቆርቋሪነታቸውን›› ይጋግራሉ፣ አንዱን ግፍ በሌላ ግፍ ያረሳሳሉ፣ ይሰውራሉ፡፡ በዚህ አልጭበረበር ወይም አልደለል ያለ ከራሳቸው ብሔር የበቀለ ተንከሲስ ሲገጥማቸው ደግሞ፣ በአሸበሪነትም ሆነ በሌላ ወንጀል ጠልፈው ወህኒ ይከቱታል፣ ደብዛውን ያጠፉታል፡፡

በሶማሌ ክልል ውስጥ አብዲ ኢሌ ከነገሠና የክልሉ ፓርቲም መንግሥታዊ አውታርም የንግድ መረብም እሱና ቡድኑ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ የተበዳዮች የሰሚ ያለህ ጩኸትም የንጉሡ አንቀጥቃጭነትም ባህር ማዶ ድረስ ከተሻገረ ሰንብቷል፡፡ ነገር ግን ኢሕሶዴፓ ነን ከሚሉት ሰዎች ዘንድ እንኳ ይህ ነው የሚባል መፈራገጥ አላየንም፡፡ የግርግር ንፋስን ተንተርሶ የታጠቁ ጥቃቶችን እያራቡ በሚሊዮን የሚቆጠር ኦሮሞን ከሶማሌ ክልል ከማፈናቀል አንስቶ፣ እስከ ዛሬ በተደጋጋሚ የተፈጸሙ የወሰን አካባቢ ግጭቶች፣ በቅርቡም ብሔርና እምነት ለይቶ የመኖሪያ ቤትና የንግድ ንብረቶችንና ባንክን እስከ መዘረፍ፣ ሰውን በገጀራና በድንጋይ ከመቀጥቀጥ አንስቶ እሳት ውስጥ እስከ መማገድ ድረስ የተፈጸሙ ሰቅጣጭ ድርጊቶች ሁሉ፣ የገዥነት ግፍን ለብሔሬ የቆምኩ በሚል ቀጣፊ ካባ ለመሸፈን የተሞከረባቸው መሰሪና ጨካኝ “ጥበቦች” መሆናቸው ነው፡፡

ያ ሁሉ ሕዝብ በገፍ እንዲፈናቀል የተደረገው፣ ከዚያም በኋላ ቁጣ ውስጥ የሚያስገቡ ወሰን ዘለል የግድያ ጥቃቶች በተደጋጋሚ የተፈጸሙት ጨፍጭፎ ተጨፈጨፍን  እስከ ማለት ዓይነት ደረቅ ውሸት ሲለቀቅ የነበረው ሁሉ ከቁጥጥር የወጣ ዘመቻ ኦሮሞ ከፍቶ ወይም መከላከያ የግድያና የገፍ እስራት ከፍቶ ይኸው የሶማሌ ሕዝብ ተዘመተብህ? ምን ትጠብቃለህ? የሚል ኡኡታ አቅላጭ ለመሆንና ከዚህ ሸረኛ ኡኡታ ጀርባ የሶማሌን ሕዝብ ሁሉ ለማሠለፍና ከተመቸ በኢትዮጵያ መንግሥት አይነኬ ገዥነትን ለማደስ፣ ካልተመቸ ደግሞ ወደ ሶማሊያና ወደ ሶማሌላንድ ዘንበል ብሎና በሰላማዊ ጉርብትና ላይ ሽብልቅ ሆኖ “የአርነት መሪነት” ዘውድ ለመድፋት ነበር፡፡ ምን ያደርጋል ግን ለዚህ ማመከኛ የሚሆን ማዕበል ከኦሮሚያ ገንፍሎ ወደ ሶማሌ ክልል አልፈስ አለ፡፡ ፌዴራል መንግሥትም የፌዴራል የፀጥታ ኃይሉን አንቀሳቅሶ ጣልቃ ሊገባ የሚችልባቸውን ሕገ መንግሥታዊ ቀዳዳዎች ሁሉ ለመጠቀም አልፈጥን አለ፡፡ ንጉሥ አብዲ ኢሌና ማፊያ ቡድኑ ላይ ሲነሳ የቆየው የሶማሌ ሕዝብ
እሮሮ ደግሞ መቆሚያ አጣ፡፡ ፌዴራል መንግሥት አንድ ነገር እንዲያደርግ የአቤቱታ ደጅ ጥናቱ አዲስ አበባ ከገባ ውሎ አደረ፡፡ በዚያው ልክ የተቅበጠበጠውና ሥጋት የገባው የክልሉ ንጉሥ ከበፊቱ የበለጠ የኢትዮጵን ፌዴራል መንግሥትንና መከላከያን ጥይት በአስቸኳይ የሚያመጣ ሌላ ብርቱ ትንኮሳ ውስጥ ገባ፡፡ ቀሳውስት እስከ መግደልና ቤተ ክርስቲያኖች እስከ ማቃጠል … ከዚያም አልፎ የሶማሊያን ባንዲራ እስከ መስቀልና የመነጠል ምክር ቤታዊ ሴራ እስከ ማዘጋጀት ይለይ አለ፡፡ ያ ሁሉ በተገንጣይ አሸባሪነት እየጠለፉ የመቅጠፍ፣ ወህኒ የማበስበስ፣ የማሰቃየት፣ የማውደም፣ የመዝረፍ፣ የማፈናቀልና የገጀራ ግፍ ሁሉ አንድ ዱርዬ ፈላጭ ቆራጭ ከኢትዮጵያ አካባቢያዊ ገዢነት እስከ “ነፃ አውጭነት” እየተፈናጠረ በሕዝብ ጫንቃ ላይ እንዲቆምር የተከፈለ ግብር!! የዚህ ግብር ከፋዮች እነማን  ናቸው? ሶማሊዎችና ጥርቅምቅም ዜጎቻችን!!

ይህ በሶማሌ አካባቢ የታየ እጅግ መራራ ልምድ በብጥስጣሽ ብሔርተኝነት ህሊናና አገዛዝ ውስጥ መውደቅ ወገን ሳይለይ፣ ሁላችንንም የመልቲዎች መጫወቻ ለመሆን ምን ያህል እንደሚያጋልጥ የማይረሳ ትምህርት የሚሆን ነው፡፡ ትምህርቱ ደግሞ ቋንቋን የተከተለ አጥር ከማጠር መውጣትን፣ አንዱን ሕዝብ ከሌላው ከሚያገልል ብሔርተኛ የፓርቲ አደረጃጀትና ገዥነት ወጥቶ ሁሉን አሳታፊ ወደ ሆነ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲና የአካባቢን ጥንቅር ያንፀባረቀ የመንግሥታዊ አውታራት ግንባታ ውስጥ መግባትን፣ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ዴሞክራሲን፣ ፍትሕና እኩልነትን መተማኛ አድርጎ በተግባር መያዝን ይጠይቃል፡፡

የኢትዮጵያ ወጣቶች የዚህ ዓይነቱ ለውጥ ዋና ሠልፈኞች መሆን አለመሆናቸው ከ27 ዓመታት ብጥስጣሽነትና መናጨት የመገላገል ጉዳይ ነው፡፡ የእነሱ ከተኮማተረ ዕይታ መገላገልና አለመገላገል የአገሪቱምን መጪ ዕጣ ይወስናል፡፡ ሁሉን አሳታፊ ለሆነ ዴሞክራሲ የመታገል ነገር ደግሞ ዞሮ ዞሮ በግብታዊ ስሜት እየተነዱ ራስን ሕግና ፈራጅ ከማድረግ መውጣትን ይጠይቃል፡፡ ዛሬ “ዕርቅና ይቅርታ! መደመር!” የምንል ወጣቶች የምንለውን የምናምንበትና የገዛ ነፃነታችን ቀበኛ መሆን ካልፈለግን፣ ብሔር አለፍ ግንኙነቶችን መድፈርና ማንኛውንም ጥያቄ ከጥቃትና ከውድመት በፀዳ ጨዋነት ማቅረብ ውስጥ መግባት ግዳችን ነው፡፡ መልካም መፈክር እየፈከርን ፊት በለመድነው የብሔርተኛ ድንኳንና ሹክሹክታ ውስጥ መኖር ከቀጠልን ግን ለውጣችን ሁሉ ከአንገት በላይ እንደሆነ ይቆያል፡፡ የጅምላ ጥርጣሬ፣ የጀምላ ፍርድና የጅምላ ዕርምጃ ካቴናችንም አብሮን መቅጨልጨሉ ይቀጥላል፡፡

ሁለት ነጥቦችን አስረግ ላስቀምጥና ላጠቃልል

      1ኛ/ አሁን በምንገኝበት የፖለቲካ ድባብ ውስጥ የማይረጭ ነገር የለም፡፡ አንዳንዶች ብሔርተኝነት (ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኛነት) አርነት መውጣት ሆኖ ይታያቸዋል፡፡ አርነት መውጣት ከጭቆና (ከብሔር ጭቆናም ሆነ ከሌላ) መውጣት ነው፡፡ ዓለም ሁሉ ዘገየም ፈጠነ የሚያመራው የሰው ልጆች ሁሉንም ዓይነት ጭቆና እያራገፉ የተያያዘ ዕጣቸውን አንድ ላይ ወደሚንከባከቡበት አቅጣጫ እንጂ ወደ ክፍልፋይነት አይደለም፡፡

ብሔረሰብነትና ብሔርተኝነት ሳይነጣጠሉ ሁሌም አብረው እንደሚኖሩ አድርጎ ማሰብም እውነተኛ ግንዛቤ አይደለም፡፡ ያለ ኦሮሞ ብሔርተኝት ኦሮሞነት ኖሯል፡፡ ሌሎችም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ያለ ብሔርተኛነት ለዘመናት ኖረዋል፡፡ የኢሕአዴግ ዘመን ያራባው በብሔርተኛነት የተከታተፈ ዕይታ የኅብረተሰብ ተከፋፍሎ መደቆሻ መሆኑ ከታየ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ቀልብ ከሞላ ጎደል ብሔረሰባዊ የእኩልነት መብቶች የተከበሩባት አንዲት ጠንካራ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አገር ላይ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ከመነጠል ፍላጎት ጋር ስሙ ተያይዞ የነበረው ኦሮሞም የዚህ እንቅስቃሴ ፊት መሪ ሆኖ እያየነው ነው፡፡ ነገ ደግሞ የብሔረሰቦች እኩልነት ተራ ነገር ሲሆን፣ ብሔሬ ብሔሬ ባይነት በአያሌው የተዘነጋ ነገር መሆኑ አይቀርም፡፡

2ኛ/ ፖለቲካ ትልመኛነት ነው፣ ትልሙ ያዋጣም አያዋጣ፡፡ የመንጋ የግርታ ሥራ ደግሞ ከጀርባ ምሪት ሰጪ ቢኖርበት እንኳ ከቁጥጥር ማፈትለኩና ውጤቱ ሊገመት በማይችል ግብታዊነት ውስጥ መስገሩ ባህርይው ነው፡፡ ለዚህ ነው መንጋንና ፖለቲካን ማዛመድ አሳሳች የሚሆነው፡፡ ወንጀልና ግፍ የግድ የፖለቲካ ባህርዮች አደሉም፡፡ ቁጣ የቀዘፈው ግርታ ግን ምንም ዓይነት መልካም ጥያቄ አንጠልጥሎ ቢነሳ፣ በወንጀልና በግፍ ሥራዎች ከመጉደፍ አለማምለጡ ድሮም ዘንድሮም የታወቀ ነው፡፡

አምባገነንነት በሰፈነበት ኑሮ ውስጥ ሰላማዊ መተንፈሻ ያጣ የቁጣ ማዕበል በንብረትና ጠላቴ ባለው ላይ እልሁን እየተወጣ አገዛዙን በድንጋጤ ለመምታት ይችል ይሆናል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ዴሞክራሲ የመገንባት ዕድል ውስጥ በገባችበት ሁኔታ ውስጥ የሚመጣ የግልፍታ ማዕበል ግን በምንም ዓይነት ዴሞክራሲን ሊጠቅም አይችልም፡፡ ጅምላ ስሜትና ጉልበተኛነት እንዳዘዘን መሆንና ማድረግ እንዴት በሕግና በመብት ውስጥ የመኖር ሥርዓትን ሊያዋልድ ይችላል?

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

“ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ኤርትራ የማደርገውን በረራ እንዳሳድግ ተጠይቄ ነበር” የኢትዮጵያ አየር መንገድ

ኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኤርትራ የሚያደርገውን በረራ እንዲያሳድግ የሚጠይቅ...
00:06:46

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...