Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኢትዮ ቴሌኮም ከዚህ በኋላ ለሚመጣው ለውጥ ራሱን ማዘጋጀት አለበት››

ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ኢትዮ ቴሌኮም ረቡዕ ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው በተለያዩ አገልግሎቶቹ ላይ የዋጋ ቅናሽ አድርጓል፡፡ የኢትዮ ቴሌኮም አዲሷ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለጸው፣ ኢትዮ ቴሌኮም የታሪፍ ማሻሻያ ብቻ ሳይሆን የደንበኞች ጥያቄዎች ሆነው ሳይፈቱ የቆዩ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ አንዳንድ አሠራሮች ተስተካክለዋል፡፡ በተለይ ለአንድ ዓመት ያህል ሥራ ላይ የቆየው ያልተመዘገበ የሞባይል ስልክ ሥራ ላይ እንዳውይል ለማድረግ ሲሠራ የነበረውን ምዝገባ አቋርጧል፡፡ አዲስ አደረጃጀት ስለመቅረፁም አስታውቋል፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው በተለይ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክልል ከተሞች የተፈጠረው የኔትወርክ መጨናነቅና የአገልግሎት ጥራት መጓደል እንደተፈጠረ የገለጹበትም መድረክ ነበር፡፡ በታሪፍ ማሻሻያውና አዲሱ የኢትዮ ቴሌኮም አመራር ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኋላ የሠራቸውንና ለመሥራት ያቀዳቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ማብራሪያውን ተከትሎ ከመገናኛ ብዙኃን ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ዳዊት ታዬ ከሪፖርተርና ከሌሎች የመገናኛ ብዙኃን ለወ/ሪት ፍሬሕይወት ከቀረቡላቸውን ጥያቄዎችና ከሰጡዋቸው ምላሾች የተወሰኑትን እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡

ጥያቄ፡- ኢትዮ ቴሌኮም አድርጌዋለሁ ያለው የታሪፍ ቅናሽ አሁንም ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ ከፍተኛ ነው፡፡ እስከ ዛሬ የኢትዮ ቴሌኮም የአገልግሎት ዋጋ ከፍተኛ ነው ሲባል ከተቋሙ ይሰጥ የነበረው ምላሽ፣ እንዲውም የኢትዮጵያ የቴሌኮም ዋጋ በዓለም ላይ ዝቅተኛ ነው የሚል ነበር፡፡ አሁንም የአገልግሎት ዋጋው ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡ ወደዚህ የተገባው እንዴት ነው? አሁን የተደረገው ቅናሽ ከአገሪቱ ለውጥ ጋር ይያያዛል? ምክንያቱ ምንድነው?

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- በዓለም አቀፍ የቴሌኮም ዩኒየን መሥፈርት መሠረት አንድ ግለሰብ ከገቢው ለቴሌ ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ለአንድ ጂቢ ከወርኃዊ ገቢ በአማካይ ማውጣት ያለበት፣ ከአምስት በመቶ በላይ መሆን የለበትም የሚል ነው፡፡ ከኢትዮጵያ አንፃር ቀደም ሲል በነበረው ታሪፍ ሲታይ፣ አንድ ግለሰብ የሚያወጣው አማካይ ወጪ ከአምስት በመቶ በላይ ነበር፡፡ አሁን ባደረግነው ማሻሻያ ግን ይህን የቴሌኮሙዩኒኬሽን አማካይ ወጪ 2.49 በመቶ ሆኗል፡፡ የማውጣት አቅም 2.49 በመቶ ደረሰ ማለት የተሻለ ያደርገዋል፡፡ ሌላው ድምፅ ላይ ከዚህ ቀደም ድምፅ ርካሽ ነበር የተባለው ለምንድነው ለተባለው ደግሞ፣ አንድ ጊዜ የወጣ ታሪፍ ሳይነካ ይቆያል ማለት አይደለም፡፡ በመሠረቱ መሆን የነበረበት የደንበኞችን አጠቃቀምና የቴሌኮም መሠረተ ልማትን ተከትሎ የሚተገበር ተለዋዋጭ ታሪፍ ነው፡፡ አሁን ዓለም እየተጠቀመበት ያለው ይህንን ነው፡፡ ለምሳሌ ቀን ላይ መርካቶ ብትሄዱ ጭንቅንቅ ነው፡፡ ማታ ስትሄዱ ደግሞ ዜሮ ነው፣ መጨናነቅ የለም፡፡ ይህ ማለት ተለዋዋጭ ታሪፍ ቢኖረን ኖሮ ማታ ላይ የሚኖረን ዋጋ በጣም ዝቅተኛ ይሆን ነበር፡፡ ይህ ሊሆን ይችል የነበረው ማታ ላይ ስለሆነ ሳይሆን፣ ኔትወርኩ ሥራ ስለሌለበት ሀብቱን እየተጠቀምንበት ስላልሆነ ማለት ሎጂኩ እሱ ነው፡፡ ቀን ላይ ስለተጨናነቀ መሆን ያለበት እሱን ተከትሎ ታሪፉ ይጨምራል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን አሠራር ተለዋዋጭ ታሪፍ ይሉታል፡፡ ስለዚህ ደንበኞች ከአንድ ቦታ ወደ አንድ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ያልተጨናነቀ ኔትወርክ ስላለ እዚህ አካባቢ በቅናሽ ተጠቀሙ ይባላል፡፡ ለዚህም መልዕክት ይደርሳቸዋል፣ ይጠቀማሉ፡፡ በሌላ አካባቢ ደግሞ እንደ ኔትወርኩ ሁኔታ እየታየ የሚሠራበት ታሪፍ አለ፡፡ በእኛ አገር ሁኔታ ግን ወጥ የሆነ አንድ ታሪፍ ነው የተቀመጠው፡፡ እኛ ትራፊካችንን ስንለካው ቀን ያን ያህል አይሸከምም፡፡

ጥያቄ፡- የኔትወርክ መጨናነቅ እያለ የታሪፍ ቅናሽ ቢደረግም መጨናነቁ አለ፡፡ ዋጋ ሲቀነስ ደግሞ ወደ ኔትወርኩ የሚገቡ ካሉ ኔትወርኩን የበለጠ አያጨናንቅም?

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- ምንም እንኳን አዲስ አበባ ውስጥ የምናየው ከደንበኞች ፍላጎት አንፃር የተጨናነቀ ቢሆንም፣ ይኼ የታሪፍ ማሻሻያ የሚረዳን ነገር አለ፡፡ ቀን ላይ ብዙ ተደራሽ ስላልሆንን የብዙዎችን ደንበኞች የስልክ ጥሪ ፍላጎት ወደ ማታ ገፍተነዋል፡፡ ማታ ያለው ትራፊካችን ሲታይ በከፍተኛ ሁኔታ የተጨናነቀ ነው፡፡ ስለዚህ ማታ ላይ የአገልግሎት ጥራቱ ይወርዳል፡፡ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚረጋገጠው የማስፋፊያ ሥራ በማከናወን ብቻ አይደለም፡፡ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚረጋገጠው አጠቃቀምንም በማስተካከል ነው፡፡ ስለዚህ ቀን ላይም ቢሆን ያልተጨናነቀ መሠረተ ልማትን መጠቀም ማስቻል አለብን ማለት ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ታሪፍ ከእነ ተጨማሪ እሴት ታክሱ 0.83 ሳንቲም ነበር፡፡ ማታ ደግሞ 0.35 ሳንቲም ነው፡፡ ስለዚህ የስልክ ጥሪው በአብዛኛው ወደ ማታ ይሄዳል፡፡  ስለዚህ እኛም ቀን ላይ የዘረጋነውን መሠረተ ልማት በአግባቡ እየተጠቀምን አይደለም ማለት ነው፡፡ አሁን ይህንን የታሪፍ ቅናሽ ስናደርግ ሳይፈልግ ወደ ማታ ሄዶ የነበረው ደንበኛ ወደ ቀን የመመለስ ዕድል ይኖረዋል፡፡ ይህ ማለት ያለንን ሀብትና የደንበኞችን ፍላጎት ያዛመደ ታሪፍ እንዲኖረን ያስችላል፡፡ ይህ ማለት ግን ፍፁም ነን ማለት አይደለም፡፡ ሲሆን ሲሆን ሊኖረን የሚገባው ተለዋዋጭ ታሪፍ ነው፡፡ የኔትወርኩን አቅም ያገናዘበና የደንበኞችን ፍላጎት ያማከለ አጠቃቀም ነው መሆን ያለበት፡፡ አሁን ግን እሱን መተግበር አልቻልንም፡፡ ምክንያቱም እጃችን ላይ ለዚህ የሚሆን መሣሪያ ወይም መፍትሔ ስለሌለና ሌሎች የሚያስፈልጉን ነገሮች ስላሉ ነው፡፡

ስለዚህ የማስፋፊያ ሥራው ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ካላደረግን ጥሪ ማድረግ የማንችልበት ደረጃ ላይ ነው የምንደርሰው፡፡ የአዲስ አበባ ኔትወርክ እያስተናገደ ያለው ለዘርፉ ከተቀመጠው በላይ ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ማለት ጥራቱ የተጓደለ አገልግሎት እየሰጠን እንቀጥላለን ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በደንበኞች አገልግሎት ላይም ሆነ በገቢ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ‹ኮል ድሮፕ› አለ፡፡ የጥሪ ስኬት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ይህ የሆነው ከመጨናነቅ የተነሳ ነው፡፡ ምናልባት አሁን ያደረግነው የታሪፍ ቅናሽ ሊጠቅመን ይችላል ብለን ከምናስበው ውስጥ፣ ደንበኞቻችን የሚያነሱትን ቅሬታ ከመፍታትና ከመክፈል አቅማቸው ጋር የተገናዘበ ታሪፍ ማስቀመጥ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ ያለንን ሀብት በአግባቡ መጠቀምን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የተደረገው የታሪፍ ቅናሽ እንደሌላው ጊዜ ዛሬ ላይ ተደርጎ ስድስትና ሰባት ዓመታት አንጠብቅም፡፡ የደንበኞችን አጠቃቀም እያየን በቀጣይነት ማሻሻያዎችን እናደርጋለን፡፡ ለምሳሌ እሑድ ላይ ያለን ትራፊክ የተጨናነቀ ነው፡፡ በወር ውስጥ ያሉት አራት እሑዶች ተደምረው ከቀሪዎቹ 26 የወሩ ቀናት ጋር ሲነፃፀሩ፣ የአራቱ እሑዶች ጥሪዎች ይበልጣሉ፡፡ መሆን የነበረበት ግን ‹ኦፍ ፒክ› የሚባለው ኔትወርክ ሥራ ሳይኖረው ዋጋ መቀነስ ነበረበት፡፡ እኛ ግን ደንበኛውን ወደ እሑድ ስለገፋነው ትራፊኩ ከፍ ይላል፡፡ ይህ ደግሞ የአገልግሎት ጥራቱን ያወርዳል፡፡ ያጨናንቃል፡፡ ሥርጭቱን በተወሰነ ደረጃ ብናስተካክለው ደንበኞች የተሻለ አገልግሎት ያገኛሉ፡፡

ጥያቄ፡- የታሪፍ ቅናሹ በኢትዮ ቴሌኮም ገቢ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አለ?

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- በ2011 በጀት ዓመት ተቋሙ አገኛለሁ ብሎ ያቀደው 47 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህንን የታሪፍ ቅናሽ አድርገንም የምናገኘው ከ47 ቢሊዮን ብር በላይ መሆን እንደሚችል አረጋግጠን ነው ቅናሹን ያደረግነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ምን ያህል ኔትወርኩንና ሲስተማችንን በሚገባ እየተጠቀምንበት እንዳልነበረ ነው፡፡ ታሪፍ ብቻውን የደንበኛ እርካታ አይጨምርም፡፡ ታሪፍ ብቻውን መጨመር የገቢ ጭማሪን አያረጋግጥም፡፡ ስለዚህ ታሪፍ ማሻሻል አንድ ነገር ቢሆንም አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ፣ የአገልግሎት ቅልጥፍናን ማሻሻልና ሌሎች ጉዳዮችም ታሳቢ መሆን አለባቸው፡፡ በዋናነት መታሰብ ያለበት ግን ኅብረተሰቡ አቅም ኖሮት ይህንን አገልግሎት መጠቀም ይችላል ወይ የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም በኢንፎርሜሽን የበለፀገ ማኅበረሰብን እንገነባለን፡፡ የሚስብና የሚያበረታታ የአገልግሎት ታሪፍ ይዘን ከተቀመጥን አደገኛ ነው የሚሆነው፡፡ ይህም የሚሆነው አንደኛ ዘርፉን እንደምታውቁት ቴክኖሎጂው በየጊዜው የሚለዋወጥ በመሆኑ፣ ትናንት የተዘረጋ መሠረተ ልማት ሳይገለገሉበት ከአገልግሎት ሊወጣ ይችላል፡፡ የዘረጋነውን መሠረተ ልማት ዛሬ በአግባቡ መጠቀም አለብን፡፡ ስለዚህ በአገልግሎት አሰጣጥ ችግርና በታሪፋችን ውድነት ምክንያት ደንበኞች አልተጠቀሙበትም ማለት፣ በድምሩ ባለቤቱ መንግሥትም ኅብረተሰቡም እንደ ደንበኛ እየተገለገሉበት አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ስናይ ከዳር እስከ ዳር ማየት አለብን ብዬ ነው የማስበው፡፡ በአጠቃላይ የቴሌኮም ድርሻ ሌሎች የቢዝነስ ተቋማት ውጤታማ እንዲሆኑ የራሱን ሚና መጫወት ነው፡፡ እንቅፋት መሆን የለበትም፡፡ የአገልግሎት ታሪፋችን ውድ ነው እያሉ በቴክኖሎጂ ያልታገዙ ተቋማትን በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ በማድረግ፣ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ማስቻል አለብን ማለት ነው፡፡

ጥያቄ፡- የሞባይል ቀፎዎች ሥራ ላይ ከመዋላቸው በፊት በኢትዮ ቴሌኮም መመዝገብና መከፈት እንደሚኖርባቸው ወጥቶ የነበረው አስገዳጅ አሠራር ከፍተኛ ችግርና እንግልት አድርሷል፡፡ በየቅርንጫፎች የሞባይል ቀፎ ለማስመዝገብና ለማስከፈት ያለውን ችግር  ከዚህ ቀደም መስተካከል እንዳለበት ሲገለጽም ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ይህንን አሠራር አቁመናል ብላችኋል፡፡ ነገር ግን ይህ አገልግሎት ሲጀመር እንደ ምክንያት የተጠቀሰው፣ የአገር ውስጥ የሞባይል ቀፎ አምራቾችን ለማበረታታትና ሕገወጥነትን ለመከላከል ነበር፡፡ ይህ ተሳክቷል? የተባለው አመለካከት ቀርቷል ማለት ነው?

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- የሞባይል ቀፎን ለማስከፈት ችግር ነበር፡፡ ብዙ ነገሮች ታሳቢ ተደርገው ነው የሞባይል ምዝገባ ሲስተም የተዘረጋውና ሥራ ላይ ውሎ የነበረው፡፡ ነገር ግን ዛሬ ላይ ቆመን ምን ያህሉን አሳክተናል የሚለውን ለመመዘን ሞክረናል፡፡ በምሳሌነት የማነሳው የኮንትሮባንድ የሞባይል ቀፎዎችን ለመከላከልና በአግባቡ መቅረጥ የሚለው አንዱ ነው፡፡ አሁን ኢትዮ ቴሌኮምና የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሳያውቁትና ሳይቀረጡ፣ እየተመሳሰሉ ሲስተም ላይ እየተመዘገቡ እንዲገቡ እየተደረጉ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ሁለቱም ዓላማቸውን አላሳኩም ማለት ነው፡፡ ዓላማቸውን ካለማሳካት ባሻገር ግን ትክክለኛ ደንበኛ ደግሞ እየተጉላላ ነው፡፡ ደንበኞቹን በአግባቡ ማገልገል ያለበት ኢትዮ ቴሌኮም ደግሞ ክፍተቱን ዓይቶ ማሻሻያ ማድረግ አለበት፡፡ አለበለዚያ ሲስተሙ በትክክል እንዲሠራ ማድረግና ወጥ የሆነ ትክክለኛ አሠራር መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ይህን አገልግሎት ለማግኘት በየቢሮው ያለው ሠልፍ በየትኛውም ዓለም የሌለ ነው፡፡ በተለያዩ አገሮች ሄደን ያየነው በዚህ ሁኔታ ሲያስተናግዱ አይደለም፡፡ ስለዚህ ምርጥ ተሞክሮው ይህ አይደለም፡፡ ስለዚህ መሻሻል ስላለበት የወሰድነው ዕርምጃ ነው፡፡ የሞባይል ቀፎን የማስመዝገብ አሠራር በተተገበረባቸው ጊዜያት ደንበኞች እንዲንገላቱ ከመደረጉም በላይ፣ በዚህ ምክንያት ምንም እንኳን በገንዘብ መተመን ባንችልም ደንበኞች የሞባይል ቀፎ ይዘው መጥተው በቀጥታ ወደ ኔትወርኩ ባለመቀላቀላቸው የኢትዮ ቴሌኮምን ገቢ አሳጥቷል፡፡

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም ለፖለቲካ ዓላማ ሲውል ይታያል፡፡  በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ግጭቶች ሲነሱ ኢትዮ ቴሌኮም መሀል ገብቶ ኔትወርኩን ያቋርጣል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለመሆን ለሚፈልግ አንድ ትልቅ ተቋም እንዲህ ያለ ተግባር ይጠቅማል?  መሆን ነበረበት? ስለዚህ ኢትዮ ቴሌኮም ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀሚያ ሆኗል ለሚሉ ሰዎች ያለዎት ምላሽ ምንድነው? ችግር በተፈጠረ ቁጥር ኔትወርክ መቆራረጡ ዕርዳታ ለመጠየቅ እንኳን እያስቸገረ ነው፡፡ በእርስዎ ዘመን ችግር በተፈጠረ ቁጥር ኔትወርክ ማቋረጡ ይቀጥላል? ወይስ አይቀጥልም? ሰሞኑን በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል የአገልግሎት መጓደል የተከሰተው ለምንድነው?

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- ኢትዮ ቴሌኮም በተለያዩ ጊዜ ለፖለቲካ ፍጆታ ይውላል ለሚለው ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባት እናንተ በተገነዘባችሁበት ሁኔታ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሰሞኑን የነበረውን ነባራዊ ሁኔታ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም ስንሄድባቸው የነበሩትን ጠንካራ ጎኖች እንይዛለን፡፡ ደካማ ጎኖችን በተመለከተ ግን እዚያ ላይ ጊዜዬን ማጥፋት አልፈልግም፡፡ ተቋሙ የቢዝነስ ተቋም ነው፡፡ የታሪፍ ማሻሻያ ስናደርግ የቢዝነስ ተቋም እንደ መሆኑ ደንበኞችን ያማከለና ለሚሰጠው አገልግሎት ተመጣጣኝ ታሪፍ ማውጣት ስላለብን ነው ያደረግነው፡፡ ስለዚህ ታሪፉ የፖለቲካ ግፊት አይደለም፡፡ የቢዝነስ መሠረታዊ ዓላማ አድርገን ነው ያመጣነው፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ትናንትና ከትናንትና በስቲያ በጎዴ፣ ቀብሪደሃርና ደገሀቡር የቴሌኮም አገልግሎት አልነበረም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ፋይበር ስለተቆረጠ ነው፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች አለመረጋጋት ነበር፡፡ አሁን በተለይ በጅግጅጋ በከፍተኛ ሁኔታ መረጋጋት አለ፡፡ ወደ ቀድሞ የተረጋጋ ሁኔታ እየተቀየሩ ቢሆንም፣ በርካታ ሠራተኞቻችን ከጅግጅጋ ወይም አገልግሎት ከምንሰጥባቸው ጣቢያዎቻችን ወጥተው እንደ ድሬዳዋና የመሳሰሉት ከተሞች በመሄዳቸው ጥገናውን በፍጥነት ማድረግ አልቻልንም፡፡ በዚህ ምክንያት አገልግሎቱ ተቋርጧል ማለት ነው፡፡ ይህንን ያነሳሁት እንዲህ ዓይነት አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል ብዬ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ተቋሙ ካጋጠሙት ተግዳሮቶች አንዱ በተለያዩ ክልሎች ያጋጠሙ አለመረጋጋቶችና የመሠረተ ልማት መቋረጥ የአገልግሎት ጥራቱን ካለማስጠበቅ ባሻገር ችግር ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ልታዩት ይገባል፡፡

ጥያቄ፡- በአሁኑ ወቅት በቴሌኮም ማጭበርበር የሚከናወኑ ሕገወጥ ተግባራት መልካቸውን እየቀያየሩ ነው፡፡ ቴሌ መሥራት የነበረበትን ሥራ በድብቅ እየሠሩ እንዳሉ ይነገራል፡፡ በዚህም ምክንያት የኢትዮ ቴሌኮም የዓለም አቀፍ ጥሪዎችን ያዳከሙት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የቴሌን የዓለም አቀፍ ጥሪ እያስቀሩ ከዚህ የሚገኘው ገቢ እያነሰ ነው፡፡ በቴሌኮም አገልግሎት ማጭበርበር ዓለም አቀፍ ጥሪዎችን በድብቅ ያከናውናሉ የተባሉት ላይ ምን ዓይነት ዕርምጃ እየወሰዳችሁ ነው?

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- ዓለም አቀፍ ጥሪዎች ላይ የተነሳው ጥያቄ ልክ ነው፡፡ ከዓለም አቀፍ ጥሪ ተቋሙ ያገኝ የነበረው ገቢ ከዓመት ወደ ዓመት እየቀነሰ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ የቴሌኮም ማጭበርበር ስላለ ነው፡፡ ምናልባት ከጥቂት ቀናት በፊት በመገናኛ ብዙኃን እንደሰማችሁት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የፀጥታና የደኅንነት፣ እንዲሁም የፍትሕ አካላት ጋር በመሆን ዕርምጃ መውሰድ ጀምረናል፡፡ በዚህም ምክንያት ባለፉት ሁለት ቀናት ብቻ በአራት መቶ ሺሕ ዓለም አቀፍ ጥሪው ጨምሯል፡፡ ይህ ማለት ሕገወጦችን ከመስመር ስናስወጣቸው አጥተናቸው የነበሩ ጥሪዎች እየጨመሩ ይመጣሉ ማለት ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን አጠቃለናል፣ ሁሉንም ሕገወጦች ይዘናል ለማለት አይደለም፡፡ ጅምር ላይ ነው ያለነው፡፡ ብዙ በርካታ ሕገወጥ ሥራዎች በቴሌኮም መሠረተ ልማት ላይ እየተካሄዱ መሆናቸውን፣ ሌሎችም ወንጀሎች እየተከናወኑ እንዳሉ ደርሰንበታል፡፡ ሰሞኑን በሁለትና ሦስት ቀናት የምናሳውቃቸው ነገር ይኖሩናል፡፡ ይህንን በሚያከናወኑ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡ ስለዚህ ይህንን በአንድ ጊዜ ከሲስተም እናስወጣለን ብለን ቃል ባንገባም፣ ከዚህ ቀደም ከቅንጅት ጉድለትም ይሁን በተለያዩ ምክንያቶች ኢትዮ ቴሌኮም ብቻውን የሚዋጋው አይደለም፡፡ ሌሎችም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ስላሉ ከእነሱ ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በማጭበርበር ተግባር ላይ የተሰማሩ ተቋማትንም ሆነ ግለሰቦችን፣ በሲስተም በመታገዝ ይዘን ለሕግ እናቀርባለን፡፡ አሁንም ዕርምጃ እየወሰድን ነው፡፡

ጥያቄ፡- የሞባይል ኔትወርክ የማስፋፊያ ፕሮጀክት አይሠራም ሲባል ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ይሠራል ተብሏል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ለውጥ አለ ማለት ነው? ማስፋፊያው ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል?

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- ሁለተኛው ማስፋፊያ ይጀመራል ተብሎ የታቀደው እ.ኤ.አ. በ2016 ነው፡፡ አሁን 2018 ውስጥ ነን፡፡ ማስፋፊያው እንዲያሳካ የታሰበው ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን ድረስ ወደ ትግበራ ወይም ወደ ኮንትራት አልተቀየረም፡፡ አሁን በቅርቡ ደግሞ ፕሮፖዛል ያቀረቡ ቬንደሮች ነበሩ፡፡ እነሱም ማራዘሚያ በመጠየቃቸውና እኔም አዲስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆኔና ተቋሙን ተረክቦ ከመምራት አንፃር ማስፋፊያው ያስፈለገበት ምክንያት፣ እንዴት ተግባራዊ እንደምናደርገው፣ መንግሥት ካወጣም ሆነ ከያዘውም የቴሌኮም ሪፎርም አንፃር ይኼ ትራንስፎርሜሽን እንዴት ሊመራ ይገባዋል? የሚሉትን ሁሉ መመልከት ስለነበረብን ነው፡፡ በእውነት ደግሞ የዕድገትና ትራንስፎሜሽን ዕቅዱን ከማሳካት አንፃር እንችላለን ወይ? የሚለውንም ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን የቀረው ሁለት ዓመት ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ይኼ ማስፋፊያ ሥራ በጥቅል ሲታይ አሁን ያለንን የኔትወርክ አቅም በእጥፍ የማሳደግ ያህል የሚታይ ነው፡፡ ይህ ማለት አሁን ያለውን በእጥፍ ማድረግ ማለት ነው፡፡ አሁን ያለውን መሠረተ ልማት ለመዘርጋት የወሰደበትን ያህል ጊዜ እንደሚወስድ የምትረዱት ይመስለኛል፡፡ በቀሪው ሁለት ዓመት ይህንን እናሟላለን ወይ? ግልጽ ነው፡፡ ጊዜው አስፈላጊው ፋይናንስ እጃችን ላይ የለም ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አገልግሎት ከመስጠትና ቢዝነሱን ከማስቀጠል አኳያ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለይተን እንዴት ይህንን ፕሮጀክት ማራመድ ይገባናል? የሚለውን ከቃኘን በኋላ እንዳስፈላጊነቱ የምንፈልግ ይሆናል፡፡ ማስፋፊያው የሚካሄድ ከሆነም የምናካሂድበትን መንገድ እናሳውቃለን፡፡ ስለዚህ ይኼንን ማስፋፊያ የሚካሄደው ከቴሌኮም ሪፎርሙ ጋር በተጣጣመ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን የመሰረዝ ነገር የለም፡፡ ሌላ የተፈረመ ኮንትራትም የለም፡፡ ማራዘሚያ ነው የሰጠነው፡፡ ከዚህ ቀደም ተሳትፈው የነበሩት ማራዘሚያ ስለጠየቁ፣ እንዲሁም አስረግጬ መናገር የምፈልገው ይህንን ዕቅድ ተቋሙን ተረክቦ ከማስተዳደር አንፃር ይህንን ፕሮጀክት በቀሩት ሁለት ዓመታት እናሳካለን ወይ? እንዴት እናሳካዋለን? ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ምንድነው የምናገኘው? የሚሉት መፈተሽ ስላለባቸው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአንድ ወር ጊዜ ወስደናል፡፡

ጥያቄ፡- ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ማስፋፊሪያ ሥራዎች ጋር ተያይዞ ምን ያህል ብድር አለበት? ካለባችሁ ዕዳ ምን ያህሉን ከፍላችኋል?

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- ‹ኔክስት ጄኔሬሽን› በምንለው የመጀመርያው የማስፋፊያ ሥራ የ1.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ተካሂዷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 1.4 ቢሊዮን ዶላር ያህሉን ተጠቅመናል፡፡ በሁለተኛው የማስፋፊያ ፕሮጀክት ደግሞ ‹‹TP1 ትራንስፎርሜሸን ኤክስፓንሽን›› በምንለው በድምሩ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የማስፋፊያ ሥራ ተካሂዷል፡፡ በጠቅላላው በሁለቱም ፕሮጀክቶች ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ውስጥ ከ2.3 ቢሊዮን ዶላር የተጠቀምን ሲሆን፣ ያልተጠበቀ ትርፍ ገንዘብ አለ ማለት ነው፡፡ ወደ 634 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ያልተጠቀምንበት ገንዘብ ስላለ ይህንን እንዴት እንደምንጠቀምበት እያየን ነው፡፡ ከፍለን የቀረብን ዕዳ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከማስፋፊያ ሥራዎቹ ጋር ተያይዞ ያለውን ብድር ለመክፈል መርሐ ግብር አውጥተን ከሚመለከታቸው፣ በተለይም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር እየሠራን ነው ያለነው፡፡  እዚህ ላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢያችን እየቀነሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በ2010 በጀት ዓመት ብድር ለመክፈል በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ብድሩን ለመክፈል አልቻለም፡፡ ብድሩን ለመክፈል ያልተቻለውም የብድር ችግር ኖሮበት ሳይሆን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ስለነበር ነው፡፡ እንዲሁም በውጭ ምንዛሪ ይገኝ የነበረው ገቢ በመቀነሱ ጭምር ነው፡፡

ጥያቄ፡- ኢትዮ ቴሌኮም በከፊል ወደ ግል ይዞራሉ ከተባሉ ተቋማት መሀል አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድ እናንተ ምን እየሠራችሁ ነው?

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- የፕራይቬታይዜሽን ሒደቱን በተመለከተ ተቋሙ ሕዝብንም አገርንም በሚጠቅም ሁኔታ በተሰጠው አቅጣጫ በቀጥታ ይሳተፋል፡፡ ለፕራይቬታይዜሽኑ በተዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ ተቋማችን ግብዓት ለመስጠት፣ ጥናቱ ሲደረግም በቀጥታ በመሳተፍ ፕራይቬታይዜሽኑ ወይም ሪብራላይዜሽኑ እንዴት ይከናወናል? እንዴት ብናደርገው የተሻለ ጥቅም እናገኛለን? የሚለውን በጋራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እንሠራለን፡፡ ስለዚህ አሁን ያደረግናቸው ማሻሻያዎች የታሪፍ ቅናሾች በምንም ሁኔታ ከዚህ ከፕራይቬታይዜሽን ጋር የተያያዙ አይደሉም፡፡ ምናልባት ከዚህ ጋር ልናያይዝ የምንችለው በቀጣይ ፕራይቬታይዜሽኑም መጣ ሊብራላይዜሽን፣ የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች የውድድር አስተሳሰብን ማካበት ይኖርባቸዋል፡፡ ተቋሙ ፕራይቬታይዝ ቢደረግም ተቋቁሞ ለመሄድ የሚያስችለውን ቁመና አሁን መገንባት አለበት፡፡ አስተሳሰቡ መምጣት አለበት፡፡ እስካሁን በሞኖፖሊ አስተሳሰብ ስንመራው ቆይተናል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ከዚህ በኋላ ለሚመጣው ለውጥ ራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡ ለአመራሩም ለሠራተኞችም በዚህ ዙሪያ የአቅም ግንባታ እናከናውናለን፡፡ በተወዳዳሪነት አመለካከት ተቋሙን ለመምራት የሚያስችለን ቁመና እንዲኖረን የሚያስችል ግንባታ እናካሂዳለን፡፡

ጥያቄ፡- በቅርቡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የስልክ ግንኙነት ተጀምሯል፡፡ ነገር ግን የአገልግሎቱ የጥራት ደረጃ ዝቅተኛ ነው እየተባለ ነው፡፡

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- አሁን ባለው ሁኔታ ጥሪ እየተደረገ ያለው በሳተላይት ነው፡፡ አሁን ወደ ማይክሮዌቭ እንቀይራለን ብለናል፡፡ ስለዚህ በሁለቱም በኩል መሥራት ያለብን ነገር አለ፡፡ እኛ ኃላፊነቱን ወስደናል፡፡ ለእኛ ጥሩ አጋጣሚ አድርገን የምንወስደው ነው፡፡ ስለዚህ የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ ማለት ነው፡፡ በቀጥታ በሳተላይት ሲሆን የአገልግሎቱ ዋጋ ውድ ነው፡፡ ሁለተኛ ጥራቱን ማስጠበቅ አይቻልም፡፡ ጥራቱ ይወርዳል፡፡ ስለዚህ ወደ ማይክሮዌቭ እንቀይረዋለን፡፡ በዚህ ላይ መደረግ ያለባቸውን ሥራዎች ጀምረናል፡፡ በኤርትራ በኩል ካለው ተቋም ጋር በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እየተነጋገርን ነው፡፡ ኃላፊነቱን ወስደን ግንኙነት አድርገናል፡፡ ምላሻቸውን እንዳገኘን ቀጣይ ሥራዎችን እናከናውናለን፡፡ ስለዚህ የአገልግሎቱ የጥራት ሁኔታ በምናከናውነው ሥራ ይሻሻላል፡፡  

ጥያቄ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባደረጉት ጥሪ መሠረት በርካታ ዳያስፖራዎች ይመጣሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ዳያስፖራዎች ሲመጡ የኢትዮ ቴሌኮምን አገልግሎት ይሻሉ፡፡ ለአጭር ጊዜ ወይም ለእነሱ የሚሆን የተለየ አሠራር ይኖራል?

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- በዚህ ጉዳይ ቡድኔ መልካም ዜና እንዳለው አውቃለሁ፡፡ አዲስ ሲም ካርድ  አዘጋጅተናል፡፡ ከውጭ ለሚገቡ ብቻ ሳይሆን አገር ውስጥ ላሉም ደንበኞቻችን በ15 ብር የሚገዙት ሲም ካርድ ለሦስት ወራት የሚገለገሉባቸው የተለያዩ የድምፅ፣ የኢንተርኔትና የአጭር መልዕክት ፓኬጅ ያለው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ከዚህ በተጨማሪ አዳዲስ አገልግሎቶችም አሉን፡፡ በተለይ ‹ፕሪሚየም› የሚባል አዲስ አገልግሎት ጀምረናል፡፡ እዚህ ላይ የደንበኞችን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ አዳዲስ አገልግሎቶች ማምጣት እንዳለብን ተረድተናል፡፡ ባህላዊ የሆኑ አገልግሎቶችን ይዘን መዝለቅ የለብንም፡፡ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑና የደንበኞቻችንንም ጥያቄዎች መመለስ እንዲችሉ፣ ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን በቀጣይ ይዘን እንቀርባለን ማለት ነው፡፡ 

ጥያቄ፡- በቅድመ ክፍያ የሞባይል አገልግሎት የሚውለው ካርድ ተፍቆ ነው፡፡ ይህ አሠራር ያረጀ ነው፡፡ ይህንን ለማስተካከል ምን ዕርምጃ ትወስዳላችሁ? ካርዱን ፍቆ አራት ጊዜ ሙከራ አድርጎ ካልተሳካ ስልኩ ለሦስት ሰዓት ይዘጋል፡፡ ይህንን አሠራር ለማስተካከልስ ምን ታስቧል? ካርዱን በአገር ውስጥ ለማሳተም ዕቅድ ነበር፡፡ ዕቅዱ ምን ላይ ደርሷል?

ወ/ሪት ፍሬሕይወት፡- ይህ ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ በመሠረቱ እዚህ ማምረት ነበረብን፡፡ ቫውቸር ካርድ ወይም ስክራች ካርድ በውጭ ምንዛሪ ነው የምንገዛው፡፡ በዚህ ዓመት (2011 ዓ.ም.) ካቀድናቸው ሥራዎች አንዱ ለቮውቸር ካርድ የምናወጣውን ወጪ መቀነስ ነው፡፡ ይህም በኤሌክትሮኒክ ዘዴ ቅድመ ክፍያ መፈጸም የሚቻልበትን አገልግሎት ማስፋፋት ነው፡፡ ይህ አገልግሎት አሁንም አለ፡፡ ግን ክፍተቶች አሉ፡፡ ኤሌክትሮኒክስ በሙሉ አቅማችን መጠቀም የምንችልበት ሲስተም ላይ ማሻሻያዎች እየሠራን ነው፡፡ አሁን ይህ አገልግሎት ላይ ውሏል፡፡ ነገር ግን በምንፈልገው አቅም እየተገለገልንበት አይደለም፡፡ በሙሉ አቅም እየሠራ አይደለም፡፡ የተወሰኑ ክፍተቶች አሉ፡፡ አሁን ኤሌክትሮኒክሱ ያለው ድርሻ ሦስት በመቶ ብቻ ነው፡፡ በገጠራማ አካባቢዎች ላሉ ደንበኞቻችን የቫውቸር ካርድ እንደሚያስፈልግ እናውቃለን፡፡ ይህንን በአጭር ጊዜ እንለውጣለን ማለት አይደለም፡፡ እንደተባለው ሌላ ዓለም እየተገለገለ ያለው በቫውቸር ካርድ አይደለም፡፡ እኛ ዘንድ የምንተገብራቸው መፍትሔዎችና አገልግሎቶች የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታና የደንበኞችን ፍላጎታች ያማከሉ መሆን አለባቸው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ሙሉ ለሙሉ ቫውቸር ካርድ ማስቀረት አለብን፣ በኤሌክትሮኒክስ እንተካለን ብንል ብንነሳ ገጠር አካባቢ ያሉ ደንበኞቻችንን ለማገልገል እንቸገራለን፡፡ ነገር ግን የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎቱን ማግኘት ለሚችሉ ሁሉ ወደ እዚህ እንዲገቡ በማድረግ ለቫውቸር ካርድ ያለ አግባብ እያወጣን ያለነውን የውጭ ምንዛሪ እንቀንሳለን ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ በስትራቴጂ እየሠራን ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ‹ኢንተርናሽናል ቶፕአፕ› ጀምረናል፡፡ በሙከራ ላይ ነው ያለው፡፡ የመጀመርያው ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ተጠናቋል፡፡ ይህ አገልግሎት ውጭ ላሉ ኢትዮጵያውያን፣ ወይም ሌሎች ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ የቴሌኮም ደንበኞች ክሬዲት መሙላት ቢፈልጉ ካሉበት ሆነው ‹ቶፕአፕ› ለማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ይህ ሁለት ጥቅም አለው፡፡ አንደኛው የደንበኞችን ፍላጎት ማሳካት፣ ሁለተኛው ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ምንጫችንን ያሰፋል ማለት ነው፡፡ ሌላ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ አማራጭ ሆኗል ማለት ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...