የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2010 ዓ.ም. ላስተናገዳቸው ውሎች የተሰጠው የመድን ሽፋን መጠን 2.2 ትሪሊዮን ብር መድረሱንና በበጀት ዓመቱም 946.3 ሚሊዮን ብር (ከታክስ በፊት) ማትረፉን ገለጸ፡፡
መድን ድርጅት የ2010 ዓ.ም. ጠቅላላ ጉባዔውን ዓርብ ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደበት ወቅት እንዳስታወቀው፣ በተሸኘው በጀት ዓመት የደረሰበት የዋስትና ሽፋን መጠን ከቀዳሚው ዓመት በ32.8 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡
በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ የ127,802 ውሎች ሽያጭና ዕድሳት ያከናወነ ይህም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር የ4.8 በመቶ ዕድገት ያሳየ እንደሆነ ያመለክታል፡፡ ሆኖም በዕቅድ ተይዞ ከነበረው ቁጥር ማሳካት የተቻለው 87.4 በመቶውን ነው፡፡
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ በ2010 ዓ.ም. 2.97 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ አስመዝግቧል፡፡ ይህም የዕቅዱን 91.1 በመቶ እንዲያሳካ አስችሎታል፡፡ የተመዘገበው የዓርቦን መጠን ካለፈው ዓመት የ9.4 በመቶ ወይም የ255.9 ሚሊዮን ብር ጭማሪ የታየበት ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡
ከተመዘገበው ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ 2.85 ቢሊዮን ብር ወይም 96.1 በመቶው ከጠቅላላ መድን ዘርፍ የተመዘገበ የሚያመለክተው የዋና ሥራ አስፈጻሚው ዓመታዊ ሪፖርት፣ ድርጅቱ ከኢንዱስትሪው አንፃር ያለውን የዓረቦን ገቢ ድርሻ 35.5 በመቶ እንዲሆን ማስቻሉን ይጠቅሳል፡፡
ቀደም ካሉት ዓመታት ሲንከባለል ከመጣው ተሰብሰቢ ሒሳብና በበጀት ዓመቱ ከተመዘገበው ዓረቦን ውስጥ 85 በመቶውን ለመሰብሰብ ታቅዶ፣ መሰብሰብ የተቻለው 82.1 በመቶ ሲሆን፣ ይህም የዕቅዱን 96.6 በመቶ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ያቀረቡት ሪፖርት ያሳያል፡፡
በደንበኞች ንብረትና ሕይወት ላይ ለደረሰ አደጋ እንዲሁም ሕጋዊ ኃላፊነት ላይ ለቀረቡ የካሳ ክፍያ ጥያቄዎች በአጠቃላይ 1.16 ቢሊዮን ብር ክፍያ ተፈጽመዋል፡፡ ከተከፈለው ካሳ ውስጥ የጠቅላላ መድን ድርሻ 1.1 ቢሊዮን ብር ወይም 94.6 በመቶ ሲሆን፣ የረጅም ጊዜ መድን ዘርፍ 63 ሚሊዮን ብር ወይም 5.4 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡
የድርጅቱ የጉዳት ካሳ ምጣኔ 49.8 በመቶ ሲሆን፣ ይህ ከዕቅድም ሆነ ከኢንዱስትሪው የጉዳት ካሳ ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው ያለው የድርጅቱ ሪፖርት፣ ዓመታዊ ትርፉ እንደጨመረም ይጠቁማል፡፡
እንደ ድርጅቱ ሪፖርት በ2010 ዓ.ም. ካከናወናቸው የኦፕሬሽን ሥራዎች፣ ከኢንቨስትመንትና ከሌሎች ገቢዎች የ1.4 ቢሊዮን ብር ጠቅላላ ገቢ ተመዝግቦ 946.3 ሚሊዮን ብር ትርፍ ከታክስ በፊት ተገኝቷል፡፡ የተገኘው ውጤት ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነፃፀር በ12.9 በመቶ እንዲሁም ካለፈው በጀት ዓመት ውጤት ጋር ሲነፃፀር በ35.69 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ነው፡፡
የኢንቨስትመንትና ሌሎች ገቢዎች አፈጻጸም ስንመለከት በአጠቃላይ ከወለድ፣ ከሕንፃ ኪራይና ከሌሎች ገቢዎች 299 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር የ36.5 ሚሊዮን ብር ወይም 13.9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ እንዲሁም ባለፈው በጀት ዓመት ከተገኘው የ84.9 ሚሊዮን ብር ወይም የ39.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡