Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አዲስ ፖሊሲ ለኢኮኖሚ ለውጥ

ለዓመታት የተጠራቀሙ ችግሮችን ለመፍታት ይቻል ዘንድ ከተለያዩ አካላት የመፍትሔ ሐሳቦች እየቀረቡ ናቸው፡፡ በፖለቲካዊና በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ እየተከናወኑ ያሉ የለውጥ ሒደቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ዙሪያ በንግዱ ማኅብረሰብና በምሁራን በኩል በርካታ ሐሳቦች እየተደመጡ ነው፡፡ እነዚህ የመፍትሔ ሐሳቦች እስካሁን ሲሠራበት የቆየውን ፖሊሲ እስከማሻሻል የሚደርስ ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

ከመንግሥት አንፃር ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የተመለከቱ አንዳንድ የፖሊሲ ለውጦች እንደሚኖሩ አመላካች ተግባራት እየታዩ ነው፡፡ ምሳሌ የሚሆኑትም ግዙፍ  የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በከፊልና ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ለማዛወር መታሰቡ  ማሳያ ነው፡፡ ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ሒደቱ ግልጽና ሕጋዊ እንዲሆንም ምክር ቤት ተዋቅሯል፡፡

በዚህ ዙሪያ ግንዛቤው ያላቸው፣ በግልና በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦችና ፖለቲከኞችም ጭምር የምክር ቤቱ አባል ሆነዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አወቃቀር አዲስ ክስተት ነው፡፡ የለውጡ መጀመሪያ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እንደሚወስዳቸው የሚጠበቁ የማሻሻያ ዕርምጃዎች መካከል በኢኮኖሚው ዙሪያ ሚና እንደሚኖራቸው የሚገመቱ ክንውኖች ሰፊ ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን የአገሪቱ ዋነኛ ወይም አንድ ወጥ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምን እንደሆነ ጥርት ብሎ አልቀረበም፡፡

ልማታዊ መንግሥት የሚለው አካሔድ እየተቀነቀነ ነው፡፡ ለዓመታት ሲተገበር የቆየው ይህ አስተሳሰብ አሁን በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከሚፈለገው ለውጥ አንፃር ምን ያህል ጠቃሚ ነው የሚለውም እያነጋገረ ነው፡፡ መንግሥት አሁንም ልማታዊ ነኝ ማለቱ እንዳለ ሆኖ የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ግን ከዚህ ለየቅል ሆነው መገኘታቸው እየታየ ነው፡፡ ይህ ከመሆኑ አንፃር ኢኮኖሚያዊ ለውጡ እንዴት መጓዝ አለበት የሚለው ላይ ብዥታ ይፈጥራል እየተባለ ነው፡፡ ለማንኛውም በእስከ ዛሬው አካሔድ ኢኮኖሚውን አንቀው የያዙ ችግሮችን መንግሥት በልማታዊ አስተሳሰብ በመቃኘቱ የተፈጠሩ ናቸው የሚለውንም አስተያየት የሚያጎሉ ትችቶችም ይቀርባሉ፡፡

እርግጥ ነው ልማታዊው መንግሥት በአብዛኛው የግሉ ዘርፍ አይደፍራቸውም በሚባሉ ዘርፎች ውስጥ የአንበሳውን ሚና እየተወጣ በመጓዝ፣ ይህንን ዘርፍ እያሳደገ ለኢኮኖሚው የመሪነት ቦታ ያበቃዋል ሲባል ቆይቷል፡፡ በተግባር ግን የግሉ ዘርፍ ሲገፋ እንጂ ሲሰፋ አልታየም፡፡ እስከዛሬ አላላውስ ሲሉ የቆዩና ቢሮክራሲ ያሽመደመዳቸው ፖሊሲዎች ካልተለወጡ በቀር፣ ወደፊት መራመድ እንደማይቻል እርግጥ ስለመሆኑ ብዙዎች የሚስማሙበት ሐሳብ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ከዚህ አንፃር ለአገር ኢኮኖሚ ወሳኝ የሆነውን የወጪ ንግድ በቀዳሚነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ስለወጪ ንግዱ ችግሮችና መልካም ዕድሎች ለ20 ዓመታት ያህል ስንሰ የቆየነው ጉዳይ ነው፡፡ የወጪ ንግዱን ለማሳደግ ይህ ነው የተባለ ውጤታማ ዕርምጃ አልተወሰደም፡፡ ይህም የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለአሥር ዓመታት ወደ ኋላ ያስቀረ ሆኗል፡፡ ዛሬም የወጪ ንግዱ ለውጥ ያስፈልገዋል የሚለው ሐሳብ መልኩን ቀይሮ እየቀረበ ነው፡፡ የፖሊሲ ለውጥ እንኳ ቢደረግበት ኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የወጪ ንግድ ምርት ማቅረብ እየተሳናት መምጣቷ ያሳስባል፡፡ የወጪ ንግድ ምርት ለዓለም ገበያ ለማቅረብ መንገዱ አቀበት እየሆነባት ተፈትናለች፡፡ እንደውም በወጪ ንግዱ ላይ የሚታየው መንገራገጭ ምርትን እንደሚገባ በውጭ ገበያዎች ለማቅርብና ለመሸጥ ካለመቻሉ ጋር ይያያዛል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችና ላኪዎች እንደሚሉትም፣ አገሪቱ ከወጪ ንግድ አንፃር ያለችበት ደረጃ እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡ ዘርፉን ለማሳደግ ተደረጉ የተባሉት ማበረታቻዎችም ቢሆኑ ዘርፉን  ከተዘረረበት ቀና ሊያደርጉት አልቻሉም፡፡

የወጪ ንግዱን ለማበረታታት የብር ምንዛሪ ተመን እንዲዳከም የማድረግ ዕርምጃ በተለያየ ጊዜም ቢሆን፣ ተደጋግሞ ተወስዷል፡፡ ዕርምጃው በአገሪቱ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ግሽበት አስከትለ እንጂ እንደተፈለገው ከወጪ ንግዱ የሚገኘውን ገቢ ሊያሻሽላ አልቻለም፡፡ ጭራሹኑ ለወጪ ንግድ የሚሰጡ ማበረታቻዎችን ጠልፈው ለመጠቀም የሚስገበገቡ አንዳንዶች የላኪነት ፈቃድ በማውጣት በአቋራጭ መጠቀሚያ እያደረጉት ስለመሆኑ መስማት ያሳዝናል፡፡ አነሰም በዛ የተወሰነ የውጭ ምንዛሪ የሚገኝባቸው ምርቶች በጥራት ጉድለት የአገሪቱን የወጪ ንግድ ጥያቄ ውስጥ እያስገቡ ሲሆን፣ ከዚህ አንፃር በገዢዎች ዘንድ እምነት እንዲታጣ የሚያደርግ አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡ ለአገሪቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም መዳከምና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ የሚገኘው ሰንኮፍ የኮንትሮባንድ ንግድ ነው፡፡

በኮንትሮባንድ ንግድ አገር እየተጎዳች ብቻ ሳይሆን፣ እየተሸጠች ነው ማለት ይቻላል፡፡ በኮንትባንድ የሚወጡ የወጪ ንግድ ምርቶቻችንን እየተቀበሉ የሚሸጡ አገሮች ከኢትዮጵያ የበለጠ ዶላር ካሳቸው እያገባ ነው፡፡ ከብት ተነድቶ ሲወጣ ሃይ የሚል  የለም፡፡ ወርቅ ታፍሶ ሲወጣ የሚጠይቅ የለም፡፡ ይህ ሥር ሰዶ ኮንትሮባንድ ሕጋዊ የወጪ ንግድ እየመነመነ ነው፡፡ ከውጭም የሚገባም እንደዛው እየሆነ ነው፡፡

ስለዘህ የአገሪቱን የወጪ ንግድ ለመታደግ እንዲያገግም ካስፈለገ፣ ጥራት ያለው ምርት ማምረቱ ላይ በማተኮርና ዘመናዊ አመራረትን በማጠናከሩ ላይ ከፍተኛ ርብርብ ማድረግ ይገባል፡፡ የጥራት ሰንሰለትን ማጠናከርና የምርት ሒደትን ከመነሻው እስከመድረሻው ለመከታተል የሚያስችል ሥርዓት በማዘጋጀት ዘርፉን መታደግ ያስፈልጋል፡፡ የኮንትሮባንድ ንግዱም ሊገታ የሚችልትን ጠንካራ አሠራር መፍጠር ግድ ይላል፡፡ ሰሞኑን እንደሰማነው፣ በኮንትሮባንድ የተያዙ የብረታ ብረት ምርቶች በአምስት ዓመት ውስጥ ከአምስት እጅ በላይ ጨምረዋል፡፡ በኮንትሮባንድ ይገባል ተብሎ የሚገመተውና በአንፃሩም ወደ ውጭ የሚወጣው የአገር ሀብት አሁን በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቁጥጥር ስለመያዛአው ከሚነገረው መጠን ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት አለው፡፡ ስለዚህ የወጪ ንግዱ የሚገጥሙትን አዳዲስ ተግዳሮቶች በመፈተሽ እንዲሁም የኮንትሮባንድ ንግድን የመቆጣጠር ሥራ በማጠናከር ወጪ ንግዱን መታደግ ደም ሥርን የማዳን ጉዳይ ይሆናል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት