Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ስፖርት‹‹አረንጓዴ ጎርፎች›› እነማን ነበሩ?

  ‹‹አረንጓዴ ጎርፎች›› እነማን ነበሩ?

  ቀን:

  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሲዘከር አይረሴው የአረንጓዴው ጎርፍ ታሪክ አይዘነጋም፡፡ የአረንጓዴውን ጎርፍ ዝና ያናኙ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ በዓለም አደባባይ ያውለበለቡ በርካታ ባለውለታዎች ድንቅ ችሎታና ገድል ለኢትዮጵያ መድመቂያዋ ሆኖ ሲዘከር የሚኖር ቅርስ ነው፡፡

  ማርሽ ቀያሪው ‹‹ይፍጠር ዘ ሺፍተር›› ምሩፅ ይፍጠር (ነፍስ ኄር) ከሞስኮ ኦሊምፒክ የአምስትና የአሥር ሺሕ የወርቅ ሜዳሊያ ጣምራ ድሎች እስከ የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ከዚያም ባሻገር የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤፍ) በሚያዘጋጃቸው ውድድሮች ለአራት ጊዜያት የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀ የአገር ባለውለታ ነው፡፡

  ምርጡ ምሩፅን ጨምሮ በአረንጓዴው ጎርፍ ወይም ‹‹ዘ ግሪን ፍለድ›› ከዚህም ባሻገር ‹‹የደጋው በራሪዎች›› እና ‹‹የሰማይ ዳርቻ የማይበግራቸው›› እየተባሉ የሚጠሩ አናብስት አትሌቶች የፈለቁባት ምድር፣ በዓለም ስሟ የገነነበት ወቅት የምንጊዜም ትዝታ ለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በወቅቱ አትሌትና አሠልጣኝ ብርሃኑ ግርማ፣ በቅርቡ በካናዳ ሕይወቱ ያለፈው ከበደ ባልቻ (ነፍስ ኄር)፣ ደረጀ ነዲ፣ መሐመድ ከድር፣ ዮሐንስ መሐመድና ሻምበል ቶሎሳ ቆቱ ለአረንጓዴው ጎርፍ ስያሜ ትልቁን ውለታ ከዋሉት ውስጥ ይካተታሉ፡፡

  እንደዚህ ያለው የአንጋፋዎቹ አትሌቶች ገድልና ታሪክ በአግባቡ ሊታወስና ሊዘከር ሲገባው፣ ይህ እየሆነ አይደለም የሚሉ ቅሬታዎች እየተደመጡ ነው፡፡ ከእነዚህ ቅሬታ አቅራቢዎች ውስጥ የሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ልጅ አቶ ቢያም ምሩፅ ይጠቀሳል፡፡ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› የሚለው ስያሜ የተሰጠው ከ1970 እስከ 1980ዎቹ መጀመርያ በነበሩት የውድድር ዓመታት ውስጥ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያኑ ኦሊምፒክንና የዓለም ዋንጫን ጨምሮ በበርካታ የሩጫ መድረኮች የማንኛውንም አገር አትሌት ጣልቃ ሳያስገቡ በሚያሳዩት የአጨራረስ ብቃትና ውጤት ያገኙት መጠሪያ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ታላላቅ የዓለም መገናኛ ብዙኃንም በአረንጓዴው መለያቸው መላውን ዓለም ያስደመሙት ኢትዮጵያውያኑ እውነትም አረንጓዴው ጎርፍ እንጂ ሌላ ተቀጽላ እንደማይገልጻቸው ስለመዘገባቸውም መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

  ይህ ስያሜ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ልዩ መጠሪያቸው ሆኖ እስካሁን መዝለቁን የሚናገረው አቶ ቢኒያም፣ በዋናነት ለዚህ ስያሜ የሚጠቀሱትም የሞስኮ ኦሊምፒክ በአምስትና አሥር ሺሕ ሜትር ወርቅ ሜዳሊያ የድርብ ድል ባለቤቱ ሻምበል ምሩፅ ፍጠር፣ በዚሁ የሞስኮ ኦሊምፒክ በ10,000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገበው መሐመድ ከድር፣ ሻምበል እሸቱ ቱራ በ3,000 ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት፣ ከበደ ባልቻ፣ ደረጀ ነዲ፣ ዮሐንስ መሐመድ፣ ብርሃኑ ግርማ፣ ግርማ ወለድሃናን ጨምሮ ሌሎችም ድንቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እንደሆኑ ይናገራል፡፡

  የስያሜው ዋነኛ ተጠቃሾች አትሌቲክሱ እንዲህ እንደ አሁኑ የመግቢያ ክፍያን ጨምሮ ክፍተኛ ሽልማት በማያስገኝበት፣ ለሚወዷት አገራቸውና ሕዝባቸው ልዕልናና ክብር የተጉ ስለመሆናቸው የጠቀሰው አቶ ቢኒያም፣ አረንጓዴው ጎርፍ የሚለውን መጠሪያ የተጎናፀፉት አትሌቶች ተገቢው ክብርና ምሥጋና ሊቸራቸው ሲገባ፣ ይህ በአግባቡ ሲተገበር እንደማይታይ ይናገራል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት አወቀውም ይሁን በስህተት፣ ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ የሚለውን ስያሜ ያስገኙት አትሌቶች ሌሎች፣ በዚህ ስያሜ የሚተዋወቁት ግን ሌሎች አትሌቶች እየሆኑ ግራ የሚያጋባ ነገር በመገናኛ ብዙኃን እየተመለከትኩ ነው፤›› ብሏል፡፡

  ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› በማለት የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እያቀረበ የሚገኘው የስፖርት ፕሮግራም፣ ስያሜውን በምስል የሚያቀርብበት መንገድ ትክክል አለመሆኑን የሚናገረው አቶ ቢኒያም፣ ፕሮግራሙ ሌላው ቢቀር በመግቢያና መዝጊያው ላይ በስያሜው ሙሉ በሙሉ የማይወከሉ፣ ነገር ግን ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› በሚለው የስፖርት ፕሮግራም ሲተዋወቁ መመልከት ቅር እንደሚያሰኝ ገልጿል፡፡ ‹‹አረንጓዴው ጎርፍ›› ከአሸናፊነትም በላይ ለአሁኑ የአትሌቲክስ ተዋንያን በአስተማሪነቱ ትልቅ ታሪክ ያለው መሆኑ ሊታወቅ እንደሚገባ ያሳስባል፡፡ ‹‹አንድ ኢትዮጵያዊ አትሌት ብቻውን በማሸነፉ የተሰጠው ስያሜ ሳይሆን፣ አራትና አምስት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በመሀላቸው ማንንም ጣልቃ ሳያስገቡ ውድድሩን በመቆጣጠር፣ የቡድን ሥራ በትልቁ የሚንፀባረቅበት፣ አንዱ በሌላው ተንኮልና ሸፍት የማይሠራበት፣ እውነተኛ ወንድማማችነትና አጋርነት የሚሰተዋልበት የአሸናፊነት ልዩ ታሪክ ስላለው ነው፤›› በማለት ስያሜው የሚመለከታቸው አትሌቶች ሊተዋወቁበት እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

  የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የስፖርት ክፍል ኃላፊ አቶ ዮናስ ተሾመ በበኩላቸው፣ ፕሮግራሙ በፍፁም እነዚያን እንቁ የአረንጓዴ ጎርፍ ባለታሪኮች ታላቅ ገድል የሚያሳንስ ሳይሆን፣ ይልቁንም ለአሁኑ አትሌቲክስ በአርዓያነቱ ጎልቶ እንዲጠቀስ የሚያደርግ ስለመሆኑ ይናገራሉ፡፡

  በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ የአረንጓዴው ጎርፍ ስፖርት ፕሮግራም አዘጋጆች እውነታውን በትክክለኛው አግባብ ተጠቅመው ታሪኩን ለኅብረተሰቡ ሊያቀርቡ አስበው ከሆነ ‹‹የስያሜው ባለቤቶች ሙሉ ምስላቸው ጭምር በማስረጃ ተደግፎ ቁጭ ብሎ እያለ፣ ቢያንስ በፕሮግራሙ መክፈቻና መዝጊያ ማሳየት በተገባ ነበር፤›› በማለት አቶ ቢኒያም ይሞግታል፡፡

  የኢትዮጵያ አትሌቲክስ እዚህ ደረጃ እንዲደርስ፣ ከአረንጓዴው ጎርፍ ባለታሪኮች አስቀድሞ ከአገሩም አልፎ ለመላው አፍሪካ ሕዝቦች የአሸናፊነት ተምሳሌት ሆኖ በታሪክ የሚዘከረው ሻምበል አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴን የመሳሰሉ ጉምቱ አትሌቶች እንደምን ሊዘነጉ ይቻላል? ሲል የሚጠይቀው አቶ ቢኒያም፣ ፕሮግራሙን ደጋግሞ እንደተመለከተው ግን ስያሜውን የሚወክል ምስል ሲተላለፍ እንደላስተዋለ ማረጋገጡን  ይገልጻል፡፡

  የፕሮግራሙ ጽኑ ፍላጎትና ምኞት የእነዚያን የታሪክ ባለውለታዎች ለማስታወስ፣ ብሎም በወቅቱ የነበረውን ወርቃማ የአትሌቲክስ ዘመን ተመልሶ እንዲመጣ የማድረግ ፍላጎት ካልሆነ በቀር የተለየ ነገር እንደሌለው የሚናገሩት የስፖርት ክፍል ኃላፊው አቶ ዮናስ፣ በፕሮግራሙ ቅሬታ ያደረበት ማንኛውም ተመልካች በአካል ቀርቦ የሚሰማውን ሁሉ የማንፀባረቅ፣ የመተቸትና የመውቀስ ሙሉ መብት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

  የአገሪቱን ስምና መልካም ገጽታ ለዓለም ማኅብረተሰብ በማስተዋወቅ ረገድ ከአትሌቲክሱ የበለጠ ዕድል እንደሌለ የሚናገረው አቶ ቢኒያም፣ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን ጨምሮ ሌሎችም የስፖርት ዝግጅት ክፍሎች የፕሮግራሞቻቸው ይዘቶች በቀደምቶቹ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችና ባለታሪኮችን ሊያካትቱ እንደሚገባም ይናገራል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  የትርፍ መጠኑን በ127 በመቶ ያሳደገው አቢሲኒያ ባንክ ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ

  የአቢሲኒያ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ  ካፒታል በ2.5 ቢሊዮን ብር...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...