Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየኢንሳ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ

  የኢንሳ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ

  ቀን:

  በቅርቡ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር በመሆን ተሾመው የነበሩት አብርሃም በላይ (ዶ/ር)፣ ከነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሾሙ፡፡

  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ በአቶ ግርማ ብሩ (አምባሳደር) ነሐሴ 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ አብርሃም (ዶ/ር) የተሾሙት፣ ለአምስት ዓመታት የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ሲሠሩ የነበሩትን አዜብ አስናቀ (ኢንጂነር)ን በመተካት ነው፡፡

  ረቡዕ ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የተሰበሰበው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አመራር ቦርድ ከፍተኛ ግምገማ ማድረጉ ታውቋል:: ተቋሙ ከሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል ቀዳሚ የሚባለውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትንና ሌሎችም ፕሮጀክቶችን እየከናወነ መሆኑን በመጠቆም፣ ይኼንን ፕሮጀክት ተከታትሎና ሥራውን በብቃት በመወጣት አገራዊ ፋይዳ ያለው ውጤት ለማስገኘት የአመራር ለውጥ ማስፈለጉን፣ ቦርዱ በሙሉ ድምፅ ስምምነት ላይ መድረሱን ምንጮች ተናግረዋል፡፡

  ቦርዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አዜብ (ኢንጂነር) በሠሩባቸው ዓመታት ያስመዘገቧቸው ውጤቶችን በሚመለከት አመሥግኖ፣ የአሠራር ድክመቶቻቸውንም በመንገር ከኃላፊነት እንዲነሱ ውሳኔ ላይ በመድረስ ሌላ አስፈጻሚ መሾሙንም ምንጮች አክለዋል፡፡

  በመሆኑም በኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን፣ በኤሌክትሪካል ኮንትሮል ኢንጂነሪንግ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንና በኤሌክትሪካል ኢነርጂ ማኔጅመንት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ማግኘታቸው የተነገረላቸውን አብርሃም (ዶ/ር) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ ቦርዱ ሾሟል፡፡ አዲሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንሳ ውስጥ በሪሞት ሴንሲንግና ካርቶግራፊ የሙያ መስክ የጂአይኤስ (GIS) አገራዊ ገቨርናንስና አርክቴክቸር የምርምር ዘርፍ ተሰማርተው በማጠናቀቅ ላይ እንደነበሩ ተገልጿል፡፡

  ከ1991 ዓ.ም. እስከ 1995 ዓ.ም. ድረስ የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት አባል በመሆን እስከ ሌተና ኮሎኔል ማዕረግ መድረሳቸውም ታውቋል፡፡ ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ሲሠሩ መቆየታቸውን፣ በ2008 ዓ.ም. በአገር ደረጃ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተዘጋጀ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤት ውድድር በማሸነፍ፣ የ3.9 ሚሊዮን ብር ተሸላሚ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ በአጭር ጊዜ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይልን የሥራ መዋቅር ሠርተው፣ የሥራ አመራር ለውጥ እንደሚያደርጉም ተጠቁሟል፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በመሐንዲስነት ሥራ መጀመራቸው የሚታወቁት አዜብ (ኢንጂነር)፣ የቀድሞው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከዘጠኝ ዓመታት በፊት በገጠመው የሰው ኃይል እጥረት ምክንያት፣ የግልገል ጊቤ ሦስት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ በማድረግ እንደሾማቸው ይታወሳል፡፡ ብዙ ውጣ ውረድ የነበረበትንና ከተቀመጠለት የማጠናቀቂያ ጊዜ ገደብ የዘገየው ግልገል ጊቤ ሦስት ፕሮጀክት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ላለፉት አምስት ዓመታት የቀድሞውን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ምሕረት ደበበ ተክተው፣ በደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ይመራ በነበረው የኮርፖሬሽኑ ቦርድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡      

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img