Saturday, December 3, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የሶማሌ ክልልን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሊመሩ ነው

  የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ የሶማሌ ክልልን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሊመሩ ነው

  ቀን:

  ሹመታቸው በክልሉ ምክር ቤት ይፀድቃል ተብሏል

  በሶማሌ ክልል ያጋጠመውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመቅረፍ የክልሉ ፓርቲ ጀምሮታል በተባለው እንቅስቃሴ፣ ከኃላፊነት የተነሱትን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመተካት እንዲሠሩ የኢትዮጵያ ሶማሌ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶሕዴፓ) የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹን አቶ ሙስጠፋ ዑመር ለምክትል ፕሬዚዳንትነት አጨ፡፡

  ኢሶሕዴፓ አቶ ሙስጠፋ ዑመርን ረቡዕ ነሐሴ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በምክትል ፕሬዚዳንትነት በማጨት፣ የርዕሰ መስተዳድር ኃላፊነቶችን እንዲወጡ ወስኗል፡፡ የክልሉ ምክር ቤትም ሹመቱን ያፀድቀዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

  በክልሉ የተቀሰቀሰውን ፖለቲካዊና ሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት በመምከር ላይ የሚገኘው ኢሶሕዴፓ አቶ ሙስጠፋ ክልሉን በምክትል ፕሬዚዳንትነት እንዲያገለግሉ ከመወሰኑም በተጨማሪ፣ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መሾሙን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

  አቶ ሙስጠፋ በሶማሌ ክልል በደገሃቡር ከተማ ተወልደው ነው ያደጉት፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በዚያው አካባቢ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሐረር ከተማ መድኃኔዓለም ትምህርት ቤት ማጠናቀቃቸውን የቅርብ ወዳጆቻው ይናገራሉ፡፡

  በአሁኑ ወቅት የ45 ዓመት ጎልማሳ የሆኑት አቶ ሙስጠፋ የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ያገኙ ሲሆን፣ በግብርና ኢኮኖሚክስ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ይዘዋል፡፡

  በሥራ ዓለም በኢትዮጵያ የመንግሥት ተቋማት ለተወሰኑ ጊዜያት ያገለገሉ ቢሆንም፣ በአመዛኙ ግን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ ተቋም በሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪነት መሥራታቸውን፣ በሌሎች ኃላፊነቶች ከኢትዮጵያ ውጭ በሚገኙ የተቋሙ ተልዕኮዎች ለአብነትም በዚምባብዌ፣ በኬንያና በሶማሊያ ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ወዳጆቻቸው ያስረዳሉ፡፡

  አቶ ሙስጠፋ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በሶማሌ ክልል መንግሥት ይፈጸሙ የነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በማኅበራዊ ድረ ገጾች በማጋለጥ፣ በመሟገትና ጫና በመፍጠር ይታወቃሉ፡፡

  አቶ ሙስጠፋ የኢሶሕዴፓ አባል ቢሆኑም የፖለቲካና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች በመሆን የክልሉ መስተዳድርን በማጋለጣቸው ወደ ክልሉ መግባት እንዳይችሉ ከመከላከላቸው በተጨማሪ፣ በቤተሰቦቻቸው ላይ ጉዳት በማድረስ ከተግባራቸው እንዲቆጠቡ ቢነገራቸውም የሚበገሩ እንዳልነበሩ የቅርብ ወዳጆቻቸው ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ምክንያትም ወንድማቸው በአሰቃቂ ሁኔታ በክልሉ የመንግሥት መዋቅር እንደተገደሉባቸው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት የቅርብ ወዳጃቸው ዓብዲ ዋሳ (ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙኃን በቅርቡ ተናግረዋል፡፡

  አቶ ሙስጠፋ ክልሉን በበላይነት እንዲመሩ በምክትል ፕሬዚዳንትነት በመሾማቸው፣ በርካታ የክልሉ ተወላጆች ደስታቸውን በማኅበራዊ ገጾች በመግለጽ ላይ ናቸው፡፡

  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ከቅርብ ወዳጆቻቸው መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ የአቶ ሙስጠፋን ብቃትና ሰብዕና በተመለከተ የግል ግንዛቤያቸውንና ዕውቂያቸውን ለሪፖርተር አካፍለዋል፡፡

  ‹‹ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጀምሮ አቶ ሙስጠፋን አውቀዋለሁ፡፡ የረዥም ጊዜ ወዳጄ ነው፡፡ ሙስጠፋ በሐሳብ ሙግት የሚያምን፣ ልዩ ባህሪው ደግሞ ከእሱ የተለየ ሐሳብ መስማትና በልዩነት ውስጥ መኖር የሚችል ነው፤›› ብለዋል፡፡

  በጣም ጨዋታ አዋቂና በፍጥነት የመረዳት ችሎታን የተላበሱ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡

  ከ23 ዓመታት በላይ የሥራ ልምድ በተለይም በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በማገልገል ያካበቱ መሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡

  ከሁሉም በላይ ግን በሥራ ቆይታቸው የሶማሌ ክልልና የአካባቢውን ተለዋዋጭ ሁኔታዎች በቅርብ የመከታተልና የመረዳት ዕድል የነበራቸው ስለሆነ፣ የተሻለ ለውጥ በክልሉ ያመጣሉ ብለው እንደሚያምኑ አቶ መለስ የግል አስተያየታቸውን ተናግረዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...