Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናብአዴን በጥረት ኮርፖሬት ላይ ጥፋት ፈጽመዋል ያላቸውን አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ...

ብአዴን በጥረት ኮርፖሬት ላይ ጥፋት ፈጽመዋል ያላቸውን አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳን አገደ

ቀን:

ነባር አመራሮች በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እንዲሳተፉ የሚፈቅደው መመርያ ተሻረ

የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ነሐሴ 17 እና 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው የሁለት ቀናት ስብሰባ፣ በጥረት ኮርፖሬት ላይ ጥፋት መፈጸማቸው ተረጋግጧል ያላቸውን መሥራች አባላቱን አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው ማገዱን አስታወቀ፡፡

የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተርና የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አቶ ንጉሡ ጥላሁን ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ ሁለቱ የብአዴን መሥራች አባላት ባሉበት ወቅታዊ አቋም የአማራን ሕዝብ ጥቅም እንደማያስጠብቁ በድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተረጋግጧል፡፡ በጥረት ኮርፖሬት ላይም ጥፋት በመፈጸማቸው እስከሚቀጥለው መደበኛ ጉባዔ ድረስ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው መታገዳቸውን አስረድተዋል፡፡

ማዕከላዊ ኮሚቴው ሌላው በስብሰባው ያሳለፈው ውሳኔ፣ ነባር አመራሮች በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ እንዲሳተፉ የወጣው መመርያ መሻሩን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በሚደረጉ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች አባል ያልሆነ ነባር አመራር እንደማይሳተፍ መወሰኑን አቶ ንጉሡ አክለዋል፡፡

ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. የዳሸን ቢራ አክሲዮን ማኅበር ከፍተኛ ባለድርሻ የሆነው የእንግሊዝ ኩባንያ ዱኤት ተወካይና የቦርድ ሰብሳቢው ሚስተር ዴቪድ ሐምፕሻየር አቶ በረከት ስምዖንን፣ አቶ ታደሰ ካሳንና አቶ ወንድወሰን ከበደን ከቦርድ አባልነታቸው ማሰናበታቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ጥረት ኮርፖሬት በትግሉ ወቅት የደረሱ ጉዳቶችን በማኅበራዊ ልማት ሥራዎች በመደገፍ ለአማራ ክልል ሕዝብ ምቹ የሆነ የማኅበራዊና ኢኮኖሚ ልማት ለማረጋገጥ፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር ከ483 እስከ 506 በተመለከቱት ድንጋጌዎች መሠረት ከ22 ዓመታት በፊት በጥቅምት ወር 1988 ዓ.ም. መመሥረቱን የመመሥረቻ ጽሑፉ ይገልጻል፡፡ ጥረት ኮርፖሬት አቶ በረከት ስምዖን፣ አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ አቶ ታደሰ ካሳ፣ አቶ ዮሴፍ ህላዌ፣ አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን፣ አቶ ከበደ ጫኔ፣ አቶ ዮሴፍ ረታ፣ ከበደ ታደሰ (ዶ/ር)፣ ገነት ዘውዴ (ዶ/ር)፣ አቶ አያሌው ጎበዜ፣ አቶ ደመቀ መኮንን፣ ሜጄር ጄኔራል ኃይሌ ጥላሁንና ቄስ ተገኝ ተፈራን ጨምሮ በ25 የብአዴን አባላት መሥራችነትና በሥጦታ በሰጡት ገንዘብ የተቋቋመ ነው፡፡

ጥረት ኮርፖሬት መሥራች አባላቱ በነፍስ ወከፍ 2,400 ብር በሥጦታ ሲያበረክቱ፣ ከብአዴን በጥሬ ገንዘብና በዓይነት በተገኘ በ26,053,813 ብር መነሻ ካፒታል የተመሠረተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ ሀብቱ 9.78 ቢሊዮን ብር መድረሱ ታውቋል፡፡ ጥረት ኮርፖሬት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ 32 ኩባንያዎች በሥሩ እንዳሉት ተጠቁሟል፡፡

ጥረት ኮርፖሬት በአማራ ክልል ውስጥ በማኑፋክቸሪንግ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግና በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ይሳተፋል፡፡ በክልሉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍና ኢኮኖሚውን ለማጠናከር የሚል ዓላማ አንግቦ እንደሚንቀሳቀስና በማኅበራዊ ዘርፍም በትምህርት፣ በጤናና በሌሎች ሥራዎች በመሳተፍ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡ በክልሉ የሚኖሩና ተቋሙን በቅርበት የሚያውቁ አስተያየት ሰጪዎች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኮርፖሬቱ የተቋቋመበትን ዓላማ በአዲስ አመራር እያሳካ ቢገኝም፣ ቀደም ሲል ግን ለክልሉ ሕዝብ ያን ያህል የረባ ፋይዳ እንዳልነበረው ይናገራሉ፡፡

ጥረት ኮርፖሬት በተለያዩ ኃላፊነት ከምሥረታው ጀምረው እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ በረከትና አቶ ታደሰ፣ ‹‹በፈጸሙት ጥፋት ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው ታግደዋል፤›› ቢባልም፣ ሪፖርተር ማተሚያ ቤት እስከገባበት ቅዳሜ ነሐሴ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ምሽት ድረስ ጥፋታቸው በዝርዝር ምን እንደሆነ የገለጸ አካል የለም፡፡

በአሁኑ ወቅት የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተርና የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ አህመድ አብተው የጥረት ኮርፖሬት ቦርድ ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ የአማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅትን (አመልድ) በዋና ሥራ አስኪያጅነት በስኬት እንደመሩ የሚነገርላቸው አምሳሉ አስረስ (ዶ/ር) ደግሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ አቶ በረከት የቦርድ ሰብሳቢነቱን ለአቶ አህመድ ያስረከቡት ከአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በፊት መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ በረከት ሰሞኑን ‹‹ትንሳዔ ዘ ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ አዲስ መጽሐፍ ገበያ ላይ ያዋሉ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡ አቶ በረከት  በቅርቡ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦርድ ሰብሳቢነት መነሳታቸውም ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...