የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያቋረጠውን የመሬት ጉዳዮች መስተንግዶ፣ ከመስከረም 2011 ዓ.ም. ጀምሮ መቀበል እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ሥልጣን በተረከቡ ማግሥት፣ በተለይ አራት ዓይነት መሬት አገልግሎቶች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጡ አዘው ነበር፡፡
ከኦሮሚያ ክልል ወደ አዲስ አበባ በመዛወር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የተረከቡት አቶ ሽመልስ እሸቱ (ኢንጂነር) እንደገለጹት፣ ለጊዜው አገልግሎት እንዳይሰጡ የታገዱ አገልግሎቶች በመስከረም ወር ሥራ ይጀምራሉ፡፡
በቅርቡ ቢሮውን የተረከቡት አቶ ሽመልስ መመርያና ደንቦችን ከማየት ባሻገር፣ ከዚህ ቀደም የተሰጡ አገልግሎቶችን ሁኔታ ሲመረምሩ ቆይተዋል፡፡
አቶ ሽመልስ እንደገለጹት፣ የመመርያ ጥሰት የተፈጸመባቸውን አሠራሮች ተለይተዋል፡፡ ‹‹የነበረው አሠራር መሬት መስጠት ላይ ያተኮረ እንጂ፣ የተሰጠው መሬት ለተገቢው ልማት መዋሉ ላይ ትኩረት አይሰጥም ነበር፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ሽመልስ፣ ‹‹ውስን የሆነው የመሬት ሀብት በሕጋዊ መንገድ ለተገቢው ዓላማ መዋል አለመዋሉ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል፤›› በማለት ቀጣዩን የአስተዳደሩ ትኩረት ኢንጂነሩ አመላክተዋል፡፡
በዕግድ የቆዩት መስተንግዶዎች አዲስ የግል የኢንቨስትመንት መሬት ጥያቄ፣ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራት የቤት መሥሪያ ቦታ ጥያቄ፣ ሰነድ አልባና አግባብ ባለው አካል ሳይፈቀድ የተያዙ ቦታዎች መስተንግዶ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ዘግይቶ ወጥቶ የነበረው 30ኛው የሊዝ ጨረታ ከታገዱ አገልግሎቶች መካከል ይገኝበታል፡፡
አስተዳደሩ እነዚህን መስተንግዶዎች ከማገዱ በተጨማሪ በመሬት ዘርፍ አጠቃላይ ኦዲት እንደሚያካሂድ ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህንን ግዙፍ ሥራ በጥልቀት ለማካሄድ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊዎች ላይ ሹም ሽር ተካሂዷል፡፡
በ12 ኃላፊነቶች ላይ ሹም ሽር የተካሄደ ሲሆን፣ አቶ ሽመልስ ከተሿሚዎቹ ጋር ተዋውቀዋል፡፡ የተሾሙት የሚከተሉት ደግሞ፣ ወ/ሪት ሰላማዊት ሐዱሽ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ባህሩ ግርማ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የካዳስተር መረጃና ቅየሳ ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር፣ አቶ ተስፋዬ አሰፋ የመሬት ይዞታ ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ልማት አስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር፣ አቶ ተሾመ ለታ የመሬት ልማትና መልሶ ማደስ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ሚሊዮን ግርማ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ አቶ ኤልያስ ዘርጋ (ኢንጂነር) የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ፣ ወ/ሮ እየሩሳሌም ሽመልስ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፣ አቶ ሳህለ ፈርሻ የተቀናጀ መሬት መረጃ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር፣ አቶ ለሙ ገመቹ የይዞታ አስተዳዳሪ ጊዜያዊ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ተስፋዬ ጥላሁን የመሬት ልማት ባንክና ማስተላለፍ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ነጋሽ ባጫ የመሬት ልማትና ከተማ ማደስ ኤጀንሲ ምክትል ሥራ አስኪያጅና አቶ ዘሪሁን ቢቂላ የመሬት ይዞታዎች ማረጋገጥ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነዋል፡፡