Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየአትሌቲክሱ ሰንደቅ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ (1939 – 2008)

የአትሌቲክሱ ሰንደቅ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ (1939 – 2008)

ቀን:

ዘመኑ 1916 ዓ.ም. ነበር፡፡ የፓሪስ ኦሊምፒክ የተካሄደበት፤ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሥተ ነገሥት መንግሥት ዘመን አልጋ ወራሽና ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴ የነበሩት ልዑል አልጋወራሽ ተፈሪ መኰንን (ኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) በአውሮፓ ጉብኝት አጋጣሚ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች ከክብር ተከታዮቻቸው ጋራ በመገኘት ተመልክተዋል፡፡ ወንዶችና ሴቶች ሲወዳደሩም አይተዋል፡፡

እኛስ ለምን አንወዳደርም ብለው በቀጣዩ ኦሊምፒያድ ለመካፈል ያስባሉ፡፡ ጉዞው ቀላል ባለመሆኑ ኢትዮጵያን ተካፋይ ለማድረግ ስምንት ኦሊምፒያድ ጠብቀዋል፡፡

በሮም ኦሊምፒክ የአበበ ቢቂላ ድል (ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም.) በኋላ በወንዶች ብቻ የተገደበው የኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ድል፣ በሴቶች በኩል ፍሬ ማፍራት የጀመረው ግን በ1984 ዓ.ም. ነበር፡፡ በባርሴሎና ኦሊምፒክ በዕንቁዋ ፌቆ፣ ደራርቱ ቱሉ የ10,000 ሜትር ወርቃዊ ድል፡፡ አበበ ቢቂላን ለድል እንዳበቁት አሠልጣኙ ሜጀሪ ኦኒ ኒስካነን ሁሉ የሴቶች ፋና ወጊ ድል የተገኘው በዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ አሠልጣኝነት ነበር፡፡ ከሞስኮ ኦሊምፒክ (ሐምሌ 1972 ዓ.ም.) በማጣሪያ ተፎካካሪነት ብቻ ተገድቦ የነበረው የኢትዮጵያውያት አትሌቶች የሩጫ ጉዞ በወርቅ መታጀብ የጀመረው ባርሴሎና ላይ ነበር፡፡ በአራት ዓመቱ አትላንታ ላይ ቀጠለ፡፡ በታዋቂው አሠልጣኝ ንጉሤ ሮባ ዘመን በሞስኮ ኦሊምፒክ (1972 ዓ.ም.) በ5,000 እና በ10,000 ሜትር ወርቆችን ያገኘው ምሩፅ ይፍጠር የድል ሰንደቅ ዳግም ሕይወት የዘራው ከአራት ኦሊምፒያድ 16 ዓመት ቆይታ በኋላ ነበር፡፡

ይህም በአትላንታ ኦሊምፒክ በአሠልጣኝ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ዘመን በ10,000 ሜትር በኃይሌ ገብረሥላሴ በተገኘው ወርቅ አማካይነት ነው፡፡ በተከታታይ በመጡት የሲድኒ፣ አቴንስና ቤጂንግ ኦሊምፒኮች ዋና አሠልጣኝ የነበሩት ዶ/ር ወልደመስቀል፣ ከኃይሌ ገብረሥላሴ ዳግመኛ ድል ከደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ መሠረት ደፋር፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ጌጤ ዋሜ የ10,000 እና የ5,000 ሜትር ድሎች ስኬት ጋርም ስማቸው ይያያዛል፡፡

በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ በተለይ ከባርሴሎና ኦሊምፒክ ወዲህ በውጤታማነት ከተገኙባቸው የመጨረሻዎቹ አምስት ኦሊምፒያዶች የተመዘገቡት 28 ሜዳሊያዎች (13 ወርቅ፣ 5 ብርና 10 ነሐስ) የዶ/ር ወልደመስቀል የዋና አሠልጣኝነት ትሩፋቶች ናቸው፡፡

የወልደመስቀል መሠረት

የዶ/ር ወልደመስቀል የአሠልጣኝነት ሕይወት መሠረቱ አትሌትነታቸው ነው፡፡ በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ዘመን፣ በአስፋ ወሰንና ደጃች ወንድይራድ ትምህርት ቤቶች ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ሯጭነትን ችላ አላሉትም፡፡ የአጭርና የመካከለኛ ርቀት በ400፣ 800 እና 1500 ሜትር ተወዳዳሪነታቸው ይጠቀሳል፡፡ እግር ኳስ ተጨዋችነቱንም ተያይዘውታል፡፡

በ800 ሜትርና 1,500 ሜትር ውጤታማነታቸው በ1957 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1964) የቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመወዳደር የሚያስችላቸውን ዕድል ቢያገኙም የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ሀንጋሪ በማግኘታቸው ቅድሚያውንም ለርሱ በመስጠታቸው በኦሊምፒክ መድረክ በተወዳዳሪነት ለመቅረብ አልቻሉም፡፡

ይሁን እንጂ ከተወዳዳሪነት ይልቅ በአሠልጣኝነት ስማቸው ከኦሊምፒክ ጋር በስኬት ተቆራኝቷል፡፡

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአካል ማጎልመሻ ትምህርት ባገኙባት ሀንጋሪ በዩኒቨርሲቲ ጨዋታዎች ኮሌጃቸውን ወክለው በ5,000 ሜትርና 10,000 ሜትር ተወዳድረዋል፡፡ ወደ አገር ቤት ከተመለሱ በኋላ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በ1962 ዓ.ም. በስፖርት መምህርነት ሥራቸውን እየመሩ በተጓዳኝ ለብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን በአካል ብቃት አሠልጣኝነት ከቆይታም በኋላ የቅዱስ ጊዮርጊስንም በተመሳሳይ አሠልጥነዋል፡፡

በ1964 ዓ.ም. በሙኒክ በተካሄደውና ማሞ ወልዴና ምሩፅ ይፍጠር በማራቶንና በ5,000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያዎች ባገኙበት 20ኛው ኦሊምፒያድ የዋና አሠልጣኙ ንጉሤ ሮባ ረዳትም ነበሩ፡፡

ድኅረ አብዮት፣ ለድኅረ ምረቃ ትምህርት ወደ ሐንጋሪ በመመለስ በስፖርት ፔዳጎጂ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ ዳግም እንደተመለሱም፣ በአካል ማሠልጠኛና ስፖርት ኮሚሽን ተመድበው ከሠሩ በኋላ፣ ከ1977 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአሠልጣኝነት ተመድበው ከመካከለኛ እስከ ረዥም ርቀት እስከ ዋና አሠልጣኝነት መድረሳቸው ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡

ከታዋቂው አሠልጣኝ ንጉሤ ሮባ ኅልፈት በኋላ የዋና አሠልጣኝነት በትሩን በመቀበል ከባርሴሎና እስከ ቤጂንግ በተካሄዱት ኦሊምፒኮች፣ እንዲሁም በስምንት የዓለም ሻምፒዮናዎች በውጤታማነት ገዝፈው ታይተዋል፤ ቆፍጣናው ዶ/ር ወልደመስቀል፡፡

በአሠልጣኝነት ሕይወታቸው፣ ከሳተና ሯጮች ጀርባ ያላቸው ልዕልና እንዳይዘልቅ ተደቅኖባቸው የነበረውና የከፋ ጉዳት አድርሶባቸው የነበረው የመኪና አደጋ ከሙያው እንዲለዩ አላደረጋቸውም፡፡ ታግለውት አሸንፈውታል፡፡ በተጓዳኝ ሕመም ቢገታቸውም፡፡

ከኮከብም ኮከብ

ከሦስት አሠርታት በላይ በአትለቲክሱ ዓለም ላቅ ያለ ተግባር ማከናወናቸው የተገነዘበው ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ‹‹ከኮከብም የሚበልጥ ኮከብ›› አለ በማለት፣ በ1999 ዓ.ም. የዓለም አቀፉን ፌዴሬሽን ታላቁን የአሠልጣኞች ሽልማት ሸልሟቸዋል፡፡ በተለይ ከ1970ዎቹ አጋማሽ ወዲህ በተከታታይ ያስመዘገቡትን በዲሲፕሊን የታጀበ ውጤት ይሁንታ ሰጥቶበታል፡፡ የዓመቱ የዓለም ኮከብ አሠልጣኝነትን የእ.ኤ.አ. 2006  (1998- 1999 ዓ.ም.) አክሊል የተቀዳጁት በሞናኮ ሞንቴ ካርሎ አደባባይ ነበረ፡፡

‹‹አልጋ በአልጋ?››    

ዶ/ር ወልደመስቀል የሙያ ጉዟቸው በስኬት የታጀበው ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አውሮፓዎችና ከሰሜን ኮሪያ ጋር አብራ ከሁለት ኦሊምፒያዶች (ሎስ አንጀለስና ሴዑል) ከተፋታች በኋላ፣ ዳግም ባርሴሎና ላይ የኦሊምፒክ ብርሃኗን እንድታይና ለውጤትም እንድትበቃ ካደረጓት መካከል አንዱ ዶ/ር ወልደመስቀል ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ የ1984ቱ ኦሊምፒክ (እ.ኤ.አ 1992) ባለፈ በዓመቱ በያኔው የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት ባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር የተከሰተው ‹‹አፈርሳታ›› ርሳቸውን ከመድረክ አስገልሏቸው ነበር፡፡ በዓለም አቀፍ የውድድር መድረክ ላይም የአገሪቱ ውጤቱ ማሽቆልቆል ጀምሮ ነበር፡፡ በወቅቱም ‹‹… አፈርሳታው ሚኒማውን ድባቅ መታ›› አሰኝቶም ነበር፡፡

በ1986 ዓ.ም. የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5,000 ሜትር የመሸነፉ ሁኔታ ያስቆጨው ኃይሌ ገብረሥላሴ ከውድድሩ ሥፍራ ወደ አዲስ አበባ በመደወል ከአሠልጣኝነታቸው የተነሡትን ዶ/ር ወልደመስቀል ምክርን የፈለገበትና በምክራቸው ምርኩዝነት የ10,000 ሜትር ወርቃዊ ድሉን ያጣጣመበት እዚህ ላይ ይታወሳል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት ከአሠልጣኝነታቸው በተነሱበት አጋጣሚ፣ በዴጉ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የታየው የአገሪቱ ደረጃና ውጤት ካሳሰባቸው መካከል አንዱ ዶ/ር ወልደመስቀል ነበሩ፡፡ ከአሠልጣኝነት ተነስቼያለሁ፣ አይመለከተኝም በማለት ሳይገደቡ ሙያዊ ምክርና ሒስ ከመስጠት አልተቆጠቡም፡፡ ለሪፖርተር በወቅቱ ከሰጡት ሰፊ ቃለ ምልልስ ሦስቱን ለአንክሮ፣ ለተዘክሮ እዚህ ላይ ማስቀመጥ ወደድን፡፡

ሪፖርተር፡- ውድድሩን ስንመለከት በወንዶቹም በሴቶቹም ያ የምንታወቅበት የቡድን ስሜት አልተንፀባረቀም፡፡ አንዳንዶቹ እንደሚሉት፣ አሠልጣኞቹ በቅጡ የሚያውቋቸው አይመስሉም?

ዶ/ር ወልደመስቀል፡- ተወዳዳሪዎቹን ያመጧቸው ከየክለቡ ነው፡፡ ሁለተኛ ነገር ዕውቀቱ ሊኖራቸው ይችላል፤ ብዙዎቹ አላቸው፡፡ ከእኛም ጋር ብዙ ጊዜ ቆይተዋል፡፡ የአስተዳደሩ ሁኔታ ግን አስቸጋሪ ነው፡፡ ልጆቹን አይመሯቸውም፡፡ መሪዎቹ ልጆቹ ናቸው፡፡ በጣም ያከብሯቸዋል፡፡ አሠልጣኝና አትሌት መከባበራቸው ጥሩ ነው፡፡ ግን የተገላቢጦሽ ነው፡፡ መጀመሪያ ነገር መምራት ያለበት አሠልጣኙ እንጂ ተወዳዳሪው መሆን የለበትም፡፡ የአንድ አሠልጣኝ ቃል መከበር አለበት፡፡ ሥርዓታዊ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ትልቁ ውድቀታችን እርሱ ነው፡፡ እንደ ባለሙያ አስተያየት እንዳይደገም እላለሁ፡፡ ኮንትሮል መደረግ አለባቸው፡፡ ሲወዳደሩኮ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማና መዝሙር ይዘው ነው፡፡  ያ ደግሞ የአገርም የመንግሥትም ጉዳይ ነው፡፡ ካሁኑ እንንቃ፡፡ መሻኮቱን ተወውና ሙያዊ አስተያየት ለመስጠት እፈልጋለሁ፡፡ አሁን ወድቀናል፡፡ አሁን ስናየው ተተኪ የለንም፤ በፊትም ሥጋቱ ቢኖረንም አንድ ውድድር ሲመጣ ማን ማን እንደሚወክል እንዘጋጃለን፡፡ እነ ኃይሌን የተኩት እነ ቀነኒሳ ናቸው፡፡ እነ ኃይሌ እነ ፊጣን ነው የተከተሉት፡፡ ይኸ የክትትል አሠራር ሥርዓት (ሲስተማችን) ሁሉ ቀርቷል፡፡ የሲስተም ድሀ አይደለንም፡፡ ወጣቶች ሞልተዋል፤ ትንሽ መያዝና ተቆጣጥሮ ማሠልጠን ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እስካሁን በአትሌቲክሱ ለተገኘው ውጤት ክለቦች አስተዋጽዖ ነበራቸው፡፡ እንደማረሚያ፣ ኦሜድላ፣ መከላከያ አሁን ያለው አካሔድ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ወልደመስቀል፡- ለክለቦች አክብሮትም፣ ዕውቅናም ብዙም የለም፡፡ አሠልጣኙ ሲናገር እርሱን መቅጣት፣ ማስጠንቀቅ፣ ማግለል እነዚህ ነገሮች አሉ፡፡ አትሌቱ መጀመርያ ከእናትና አባቱ፣ ከትምህርት ቤት በኋላ የምታገኘው ክለብ ውስጥ ነው፡፡ ክለብን አልፈው ወደ ብሔራዊ ሲመጡ ደግሞ አሠልጣኞቹን ያገሏቸዋል፡፡ ክለብ ቤታችን ነው፡፡ የአትሌቲክስ ልጁ ክለብ ነው፡፡ የክለብ አመራርና አደረጃጀት ወሳኝ ነው፡፡ ድጎማ ካስፈለገው ድጎማ ማድረግ ነው፡፡ ለክልሎች ብቻ ሳይሆን ለማረሚያ፣ ለሙገር፣ ለመከላከያ፣ ለፌዴራል ፖሊስ፣ ለባንክ፣ ወዘተ ክለቦች በዋነኛነት ድጎማም ዕውቅናም ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ እነርሱን አግልሎ ልጆቹን የኔ ናቸው ሊባል አይገባም፡፡ የት ያውቃቸዋል? አልወለዳቸው፣ አላሳደጋቸው፣ ደሞዝ በኋላም ጡረታ የሚሰጣቸው ክለባቸው ነው፡፡ መጀመርያ ለክለቦች ዕውቅና ያስፈልጋል፡፡ ልጆቹን ብቻ ማለትም መሠረትን፣ ደራርቱን ብቻ ሳይሆን ክለባቸውን ባንክን፣ ማረሚያን፣ ፌዴራል ፖሊስን ማክበር አለብን፡፡ የክለቦቹ አደረጃጀት የፌዴሬሽኑ አደረጃጀት ሊሆን ይችላል፡፡ እርሱ ፊት ፊት እየሔደ ምሳሌ መሆን አለበት፡፡ አሠልጣኞችን መጥላት የለብህም፡፡ በእነርሱ የሠለጠኑና ከእነርሱ የወጡ ናቸው፡፡ በየክልሉ እየዞሩ እየመለመሉ አምጥተዋል፡፡ የልጆቻቸው ባለቤት ናቸውና አክብሮት ይገባቸዋል፡፡ ይኼ የለም፡፡ እንዲያውም አባርርሃለሁ የሚል ነገር ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ጥሪ መጥቶሎታል ይባላል?

ዶ/ር ወልደመስቀል፡- ውጭ አገር እንድሔድ ተጋብዣለሁ፡፡ ግን የአገሬ ስፖርት ሲሞት/ሲወድቅ ምን ማለት ነው? መሸሽ ነው? የት ለማን ነው ትቼ የምሔደው? በግሌም ቢሆን ይኸው አንድ ዓመቴ  በጃንሜዳ እየሠራሁ ነው፡፡ ለምን እሸሻለሁ? አሜሪካ ሔጄ ብዙ ጥሪዎች ነበሩኝ ምን ያደርግልኛል? አልፈልግም፡፡ ለሆዴ ከሆነ ከጡረታዬ ጋር መንግሥትም ሕዝብም ያበላኛል፡፡

ጀንበሯ ስትጠልቅ

ዶ/ር ወልደመስቀል በአንድ ወቅት ያጋጠማቸው የከፋው የመኪና አደጋ በተደጋጋሚ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች ከፍተኛ ሕክምና ሲከታተሉበት ቆይተዋል፡፡ ከአምና ወዲህ ተጓዳኝ ሕመም በመፈጠሩ አደባባይ ከመዋል ገድቧቸው ኖሯል፡፡

በ1939 ዓ.ም. ረቡዕ ጥር 21 ቀን፣ ከአባታቸው ከአቶ ኮስትሬ ሰበሬና ከእናታቸው ወ/ሮ እናት ገብርኤል ደስታ፣ በቀድሞው አጠራር በሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ ተጉለትና ቡልጋ አውራጃ ሳሲት እንግድ ዋሻ የተወለዱት ዶ/ር ወልደመስቀል ያረፉት እሑድ ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ ማክሰኞ ግንቦት 9 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በመቶዎች የሚቆጠሩ በተገኙበት፣ ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡ በ69 ዓመታቸው ያረፉት ዶ/ር ወልደመስቀል የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡

በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ዐውደ ምሕረት ገጸ ታሪካቸው ሲገለጥ እንዲህ የሚል ተገኘበት፡-

‹‹ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ አትሌቶችና አሠልጣኞች ሙያውን እንዲወዱ በጠንካራ ዲሲፕሊን የሚመሩ እንዲሆኑ የተጉ ናቸው፡፡ ከሁሉም በላይ አትሌቶቻችን አገራቸውን፣ ሕዝባቸውን፣ ሰንደቅ ዓላማቸውን እንዲያስቀድሙ ለማድረግ በሥልጠና ዘመናቸው ሁሉ የደከሙ፣ ይህን ዓላማቸውንም ያሳኩ፣ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ባለውለታ አገር ወዳድ አሠልጣኝ ነበሩ፡፡››

የዶ/ር ወልደመስቀልን ዜና ዕረፍት ሰምቶ፣ የሐዘን መግለጫ ለማውጣት ቀዳሚ የሆነው ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር፣ ‹‹ኮስትሬ በብዙዎች ዘንድ የኢትዮጵያ የረዥም ርቀት ስኬት መሐንዲስ (አርክቴክት) ተደርገው የሚቆጠሩ ናቸው›› በማለት ሐዘኑን ገልጿል፡፡

የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ለሪፖርተር በላከው የሐዘን መግለጫው፣ ‹‹አገራችን በእስካሁኑ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋ ካገኘቻቸው 45 ሜዳሊያዎች ውስጥ 28ቱ የተመዘገቡት በዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ የአሠልጣኝነት ዘመናቸው መሆኑ፣ ለአገራችን የአትሌቲክስ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ የነበራቸው አሠልጣኝ መሆናቸው ትልቅ ማሳያ ነው፤›› ብሏል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...