Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ልጓም ያልተበጀለት ሥልጣን የሴረኞች መጫወቻ ይሆናል!

  የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአኗኗር ዘይቤዎቹ የሚጠቀምባቸው በርካታ ምሳሌዎችና አባባሎች አሉት፡፡ ቋንቋና ባህል ሳይገድባቸው የሚመሳሰሉ አባባሎች በርካታ ናቸው፡፡ ሕዝብ ብርቱውን የበለጠ ለማበረታታት፣ ደከም ያለውን ለማነቃቃት፣ ጥሩ የሠራውን ለማሞገስና ያጠፋውን ለመገሰፅ የሚጠቀምባቸው ምሳሌዎች አስተማሪነት አላቸው፡፡ ብልሆች ነገን እያሰቡ የዛሬ ሥራቸውን በአግባቡ ሲወጡ፣ ለዚህ ያልታደሉት ግን ካለፈ በኋላ ሲቆጩና ጥርሳቸውን ሲያፋጩ ይገኛሉ፡፡ ለእንዲህ ዓይነቶቹ፣ ‹‹ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ››፣ ‹‹በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርም››፣ ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ››፣ ‹‹የፈሰሰ ውኃ አይታፈስም››፣ ወዘተ በሕዝባችን ውስጥ በስፋት የሚታወቁ አባባሎች ናቸው፡፡ ትናንት አገር በሥርዓት የምትገነባበትን መንገድ ለማመላከት የተቻላቸውን ያህል ጥረት ያደረጉ አዳማጭ በማጣታቸው የደረሰው ይታወቃል፡፡ ገፋ ብለው የተጋፈጡ ደግሞ ያጋጠማቸው ፈተና በሚገባ ታይቷል፡፡ እየተከናወነ ያለው ድርጊት ለአገር አይጠቅምም ሲባሉ አንሰማም ያሉትም የት እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ ‹ከታሪክ የማይማር ታሪክን ለመድገም ይገደዳል› እንዲሉ፣ ሴረኞች ወጥመድን ለሥልጣናቸው ሲሉ ከማጥመድ ባለፈ፣ ነገን ማሰብ ባለመቻላቸው ታሪካዊ ስህተት ይፈጽማሉ፡፡

  አገርን በሴራና በአሻጥር ለመምራት መሞከር ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ ለሌሎች የሸረቡት ሴራ ጠልፎ ይጥላልና፡፡ የሥልጣን ቁንጮ ላይ ተቀምጠው ለዘመናት በዳበረ የሴራ ፖለቲካ ሕጋዊነትን ለሕገወጥነት አሳልፈው የሰጡ፣ ሕግን የሕዝብ አለኝታና መከታ ማድረግ ሲገባቸው የገዛ ወገንን ለማጥቃት እንደፈለጉ የተጫወቱበት፣ የፖለቲካ ተፎካካሪን ከምኅዳሩ በማባረር የፈነጩበት፣ በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ ታሳሪዎች ላይ ሰቆቃ የፈጸሙና ያስፈጸሙ፣ ለአገር በገንዘብ የማይለካ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ወገኖችን ከማግለል አልፈው ያሳደዱ፣ አገሪቱን በዴሞክራሲ ስም ገሃነም ያደረጉና የሕዝብ ቅሬታ ተከማችቶ አመፅ እንዲፈነዳ ምክንያት የሆኑ በአገር ላይ ወደር የሌለው ጉዳት አድርሰዋል፡፡ በተጣመሙ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ምክንያት ከደረሱ ሰብዓዊ ቀውሶች በተጨማሪ፣ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ለዝርፊያና ለውድመት ተጋልጧል፡፡ በቅርቡ እንደሰማነው ደግሞ የሰው ልጅ ከዱር አራዊት ጋር እየታሰረ መፈጠሩን እስኪረግም ድረስ ምርመራ ይካሄድበት ነበር ተብሏል፡፡ ሥልጣን ልክ እንደ አልኮል መጠጥ ማሰቢያቸውን ያዛባባቸው ሹማምንት አገርን አተራምሰዋል፡፡ ይህም ሆኖ ይቅርታ ለማለት የከበዳቸው ሞልተዋል፡፡ ሴረኝነት ተጠናውቷቸዋልና፡፡

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፓርላማ ከተገኙባቸው ስብሰባዎች በአንዱ፣ አገር ሲያሸብር የነበረው ራሱ መንግሥት ነው በማለት በይፋ የኢትዮጵያ ሕዝብን ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ ቀደም ሲል ባገኙት ተቀባይነት ላይ የበለጠ የሕዝብን ልብ የነኩበት ይህ ማብራሪያቸው፣ መንግሥት ምን ያህል በሕዝብ ተተፍቶ እንደነበር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በተለይ በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ የታየው ከፍተኛ ትግል፣ በለውጥ ፈላጊዎችና በነበረበት መቀጠል አለበት በሚሉት መካከል ከፍተኛ ልዩነት ፈጥሯል፡፡ ይህ ልዩነት ደግሞ ሕዝቡ ከለውጥ ፈላጊዎች ጋር አብሮ እንዲቆም፣ ኢሕአዴግ ደግሞ ከእነ ችግሮቹም ቢሆን እስካሁን በሥልጣን ላይ ለመቆየት አግዞታል፡፡ ይህም ሆኖ ግን አሁንም ሕዝብ ድጋፉን ለሰጠው ለውጥ ጀርባ የሚሰጡ አሉ፡፡ ችግሩ ጀርባ መስጠታቸው ሳይሆን አሁንም የኢትዮጵያን ሕዝብ ፍላጎት ለመረዳት ወይም ዕውቅና ለመስጠት አለመፈለጋቸው ነው፡፡ የአፈና አገዛዝን ቅድስና ለማስረዳት ይዳክራሉ፡፡ በአንድ በኩል የለውጡ ጀማሪዎችንና ግንባር ቀደም መሪዎችን ሕዝብ በግልጽ እያወቃቸው፣ በሌላ በኩል የለውጡ ጀማሪዎችማ እኛ ነበርን የሚሉ መመፃደቆችን ያሰማሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ በፓርላማ ሥልጣን ተረክበው ታሪካዊ ንግግር ካደረጉ አምስት ወራት ተቆጥረው፣ የት እንደነበሩ የማይታወቁ እኛም ነበርን ሲሉ ጤንነታቸው ያጠራጥራል፡፡ ሕዝብ እኮ ሁሉንም ነገር ያውቃል፡፡ የሴራ ፖለቲካ ውጤቱ ግራ ተጋብቶ ግራ ማጋባት ነው፡፡

  ባለፉት 27 ዓመታት ካጋጠሙ ችግሮች መካከል በዋነኛነት የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ችግሮች ይነሳሉ፡፡ በኢኮኖሚው መስክ ተመዘገቡ የሚባሉ መልካም ነገሮች ቢኖሩም፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ ለሕዝብ የሰጠው ጠቀሜታ ላይ ብዙ ነገሮች ይነሳሉ፡፡ ጥቂቶችን ሚሊየነር እያደረገ ብዙኃኑን ለጉስቁልና ከመዳረግ በላይ፣ አገሪቱን ለዕዳ ጫና ያጋለጠ ነው ተብሎም ይተቻል፡፡ በመልሶ ማልማት ስም ድሆች ከመኖሪያ ቀዬአቸው እየተባረሩ፣ የእነሱ ይዞታ ለጥቂቶች ሕንፃ መሥሪያና መዝረፊያ መመቻቸቱ ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብቶች ላይ የተፈጸመው ድርጊት ግን አገሪቱን ጥላሸት ቀብቷታል፡፡ ገጽታዋንም አበላሽቶታል፡፡ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ በወጡት የሚዲያ፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት፣ እንዲሁም የፀረ ሽብርተኝነት ሕጎች ምክንያት የደረሰው በደል እስካሁን ጠባሳው አለ፡፡ ምርጫን ሙሉ በሙሉ አሸንፌያለሁ ማለት የተደረሰው እኮ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ በመንገሡ ነው፡፡ ከእነዚህ ድርጊቶች በስተጀርባ ስማቸው ጎልቶ የሚነሳ ቱባ ሹማምንትም ይታወቃሉ፡፡ ለጊዜው ሥልጣንን ለማጠባበቅና ረግጦ ለመግዛት ከወጡት ሕጎች በተጨማሪ፣ በሙስና የተከሰሱ ሰዎችን ዋስትና ለመከልከል በጥድፊያ ተሻሽሎ የወጣው ሕግ ታክሎበት በበርካቶች ላይ የደረሰው ሰቆቃ ተነግሮ አያልቅም፡፡ ነገን ባለማሰብ የተፈጸሙ የትናንት ድርጊቶች ዛሬ ባለተራዎቹን ቢጠብቁ ምን ይገርማል? የሴራ ፖለቲካ ውጤት ነውና፡፡

  ትናንት የሥልጣንና የጥቅም ተቀናቃኞችን ለማጥፋት እንደ ወጥመድ ያገለገሉ ደርጊቶች ዛሬ ተረኞችን ሲጠብቁ፣ አሁን ሥልጣን ላይ የተቀመጡ ወር ተረኞች እንደ ትምህርት ሊቀስሙ ይገባል፡፡ ሰውየው የጓሮ እርሻው ውስጥ የተከላቸውን ፍራፍሬዎች ጃርት እንዳይበላበት በመተላለፊያዎች ላይ ወጥመድ ይሠራል፡፡ ፍራፍሬዎቹን ከሰበሰበ በኋላ ደግሞ ወጥመዶቹን ያነሳል፡፡ በአንድ ወቅት አንድ ወጥመድ በመርሳቱ የጓሮ እርሻው ውስጥ ሲዘዋወር እግሩን ለቀም ያደርገዋል፡፡ ሰውየው በራሱ ድርጊት እየሳቀ፣ ‹ለጃርት ያጠመድኩት የራሴን እግር ይያዘኝ?› ብሎ መገረሙ፣ እንደ መልካም ትምህርት ሊቀሰም ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ልቡ ለይቅርታ ክፍት የሆነውን ያህል አስነዋሪ ድርጊቶችን ደግሞ ይፀየፋል፡፡ ከአስነዋሪ ድርጊቶች መካከል ሥልጣንን ያላግባብ በመጠቀም ፍትሕ ማዛባት፣ የገዛ ወገንን ማሳደድ፣ ሥልጣን ዘለዓለማዊ ይመስል በበደል ላይ በደል መፈጸምና ትውልድ ታሪክ ይቅር የማይላቸው የሴራ ድርጊቶችን ማስፈን ናቸው፡፡ በተጨማሪ በሕዝብ ስም እየነገዱ ሕዝብንና አገርን ማተራመስ፣ በክፋት መንፈስ ግጭት በመቀስቀስ ንፁኃንን መግደልና ማፈናቀል የይቅርታ መንገድን ይዘጋሉ፡፡ እነዚህ የሴራ መጥመዶች ናቸው ነገን የሚያበላሹት፡፡

  የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ለይቅር ባይነትና ለፍቅር የሰጠው ግምት እንዳለ ሆኖ፣ ለአገርና ለሕዝብ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ሲባል ግን ሙሉ ትኩረቱን የሕግ የበላይነት ላይ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ በፊት ሕዝብ ሲጠይቃቸው የኖሩ ሕጎች እንዲሻሻሉ፣ የማያስፈልጉ ካሉም እንዲወገዱ፣ በግለሰቦች ፈቃድ የሚፈጸሙ መመርያዎችና ደንቦች በሕግ ማዕቀፍ እንዲካተቱና ጠንካራ ተቋማት እንዲፈጠሩ ያለመታከት መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ እንደ ጓሮ ጎመን ይታይ የነበረው የመንግሥት ሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት ሕዝብ እንደሆነ ሊታመን ይገባል፡፡ ከፓርቲ ርዕዮተ ዓለም በላይ የአገር ህልውና እንደሚቀድም መታወቅ አለበት፡፡ ግለሰቦች ሰጪና ነሺ የሆኑባቸው ብልሹ አሠራሮች የሕግ ልጓም ሊበጅላቸው የግድ ይላል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በሕግ ፊት እኩል መሆናቸው የሚረጋገጥበት ሥርዓት እንዲገነባ ደግሞ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ዜጎች በሙሉ የድርሻቸውን ማዋጣት አለባቸው፡፡ ለዚህም ሜዳውም ፈረሱም ይኸው መባል አለበት፡፡ ልጓም የሌለው ሥልጣን የሴረኞች መጫወቻ ይሆናል! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም ኅብረተሰብ የብድር አገልግሎት የሚያስገኙ ሁለት ክሬዲት ካርዶች ይፋ አደረገ

  አዋሽ ባንክ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በዘመናዊ መንገድ ብድር ማስገኘት...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

  ‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...

  የጉድለታችን ብዛቱ!

  ከፒያሳ ወደ ሜክሲኮ ልንጓዝ ነው። ጎዳናውን ትውስታ እየናጠው ሁለትና...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...