በከፍተኛ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ በከረሙት የቀድሞ የኢትዮጵያ መረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ተወልደና በሦስት ግለሰቦች ላይ ማክሰኞ ነሐሴ 22 ቀን 2010 ዓ.ም. የሙስና ክስ ተመሠረተ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ተረኛ ችሎት በከፈተው ክስ ተከሳሽ አድርጎ የጠቀሳቸው አቶ ቢኒያም ተወልደ፣ አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ፣ ወ/ሮ ጽጌ ተክሉና አቶ ይርጋለም አብርሃ ናቸው፡፡
ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎች ላይ የመሠረተው ስድስት ክሶችን ነው፡፡ በክሱ ላይ ከ72 ሚሊዮን ብር በላይ በመንግሥትና በሕዝብ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት አከማችተው መገኘታቸውንና ሌሎችንም ነጥቦች ጠቁሟል፡፡
ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ 881/07 አንቀጽ (1ሐ እና 2) የሙስና ወንጀሎችን ለመከላከል የተደነገገውን በመተላለፍ፣ የሙስና ወንጀል መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ጠቁሟል፡፡ አቶ ቢኒያም የኢንሳ ምትክል ዳይሬክተርና የሥልጠናና የትምህርት ተቋም ዳይሬክተር ሆነው ሲሠሩ፣ የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተውና ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም መንግሥትንና ሕዝብን የሚጎዳ ተግባር መፈጸማቸውን ዓቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡ ለራሳቸው ጥቅም ለማግኘትና ለሌላው ለማስገኘት በማሰብም የሚስጥራዊ አገልግሎት ግዥ ወይም ‹ሳይበር ታለንት ማኔጅመንት ፕሮግራም› ግዥ ለመፈጸም፣ ከእስራኤል አፎሜጋ ድርጅት ጋር የተፈጸመን ውል ምክንያት በማድረግ፣ ሥልጠና ላልሰጠ ድርጅት ሥልጣና እንደሰጠ በማስመሰል 32,472,000 ብር ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ዘርዝሯል፡፡
ክፍያው የተፈጸመው ሥልጠና ሊሰጥ የነበረው ድርጅት ሥልጠናውን ሰጥቶ እንዳጠናቀቀ የሚገልጽ ሠርተፊኬት ከኢንሳ እንደተሰጠው በማስመሰል፣ ክፍያው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል መፈጸሙን ክሱ ያብራራል፡፡ የሥልጠና አገልግሎት ግዥ የተፈጸመው በ3,200,000 ዶላር ወይም 72,160,000 ብር ሲሆን፣ ክፍያ ሊፈጸም ስምምነት የተደረገው በሦስት ጊዜ ቢሆንም፣ ተከሳሾች ግን ውሉን ያልጠበቀና ጉዳት የሚያደርስ ክፍያ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል፡፡
ሌሎችም ተከሳሾች በመመሳጠርና ምንጩ ያልታወቀ ሀብት በማፍራት ክሳቸውን ለመስማት ለጥቅምት 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡