Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከቁጭት ይልቅ ትኩረት የሚሹ ታዳጊዎች

ከቁጭት ይልቅ ትኩረት የሚሹ ታዳጊዎች

ቀን:

ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከምድብ ጨዋታዎች እስከ ፍጻሜው ባደረገው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) ዋንጫ ድንቅ ክስተት በመሆን ውድድሮቹን አጠናቋል፡፡ ቁጭትና ተስፋ የቀላቀለበት ስሜት የፈጠረው የታዳጊዎቹ ቡድን፣ ሳይፈርስ እንዲቀጥል አልያም ክለቦች ለታዳጊዎቹ የመሰለፍ ዕድል እንዲሰጧቸው መጠየቅ ተጀምሯል፡፡

የታዳጊዎቹ ቡድን አጨራረስ እንደ አጀማመሩ የተጠበቀውን ውጤት ባያመጣም፣ በአጨዋወት ታክቲክ፣ በብቃትና ክህሎት እንዲሁም የተጋጣሚ ቡድኖችን እንቅስቃሴ በመገምገም በሜዳ ውስጥ ሲተገብራቸው የታዩ የታክቲክ ለውጦች ከፍጻሜው ጨዋታ በስተቀር የምድብ ተጋጣሚዎቹን በሙሉ አሸንፎ ለፍጻሜ እንዲደርስ አብቅተውታል፡፡ የታዳጊዎቹ ክህሎትና ብቃት ትኩረት እንዲቸራቸውም አስገድዷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሁሉም አቅጣጫ ከውድቀቱ በቀር ስለወደፊት አቋሙ ብዙም ለማይነገርለት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ያልተጠበቀ ተስፋን ያጫሩት ታዳጊዎቹ፣ ባሳዩት አጨዋወትና ድል አድራጊነት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን በለሥልጣናት ሳይቀሩ ትኩረት እንዲቸሯቸው አስገድደዋል፡፡ ምንም እንኳ ታዳጊዎቹ በሚቀጥለው ዓመት ምሥራቅ አፍሪካዊቷ ታንዛኒያ በምታዘጋጀውና ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች በሚጫወቱበት የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የነበራቸው ግስጋሴ በኡጋንዳ 3 ለ1 ሽንፈት ቢገታም፣ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ዓይነ ጥላ የገፈፈ ተሳትፎ ከአስገራሚ ብቃት ጋር ማሳየታቸው አድናቆት እንዲቸራቸው አድርጓል፡፡

ይህ የታዳጊዎቹ ስብስብ (አንዳንዶች ከወዲሁ የቀይ ቀበሮቹ ቡድን እያሉ ይጠሯቸዋል)፣ እንደ እስካሁኑ አካሄድ ሳይበተኑ በብሔራዊ ቡድኑ እንደተሰባሰቡ እንዲቆዩ የሚደረግበትን አሠራር መዘርጋት እንደሚገባ ሐሳብ የሚሰጡበት አሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር ክለቦች ዕድሜያቸው በገፋ  ተጨዋቾች ዝውውር ላይ ጊዜና ገንዘባቸውን ከሚያባክኑ ይልቅ ለዋናው ቡድናቸው ተገቢውን አገልግሎት ሊያበረክቱ የሚችሉትን ታዳጊዎች ሊመለከቷቸው እንደሚገባም የሚገልጹ አሉ፡፡ ምናልባትም እግር ኳስ የሚፈልገውን ብቃትና ችሎታ ሳያሟሉ በምኞትና ቁጭት ተሞልተው ባገኙት አጋጣሚ ስሞታ ለሚያቀርቡ የፌዴሬሽንና የክለብ አመራሮችና ሌሎችም አካላት የመፍትሔ አመላካች እንደሚሆንም እየተነገረ ነው፡፡

ከአምስቱ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ዞኖች፣ የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች (ሴካፋ) አንዱ ነው፡፡ በዚሁ ዞን ውስጥ በምድብ ሁለት ከጅቡቲ፣ ከኬንያና  ኡጋንዳ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ታዳጊ ቡድን፣ ለግማሽ ፍጻሜውና ፍጻሜው ጨዋታዎች የደረሰው ሁሉንም ጨዋታዎች በማሸነፍ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ በፍጻሜው ለሁለተኛ ጊዜ ያገኘውን የኡጋንዳ ቡድን በምድብ ጨዋታው 1 ለ0 ማሸነፉን ተከትሎ፣ ለታንዛኒያው የአፍሪካ ዋንጫ ማለፉ እንደማይቀር ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ተስፋ ብቻም ሳይሆን እርግጠኛ እስከመሆን የተደረሰበት ሥነ ልቦና ቢፈጠርም፣ ቡድኑ በመሸነፉ ሳይሳካ ቀረና በርካቶችን አስቆጨ፡፡

በምድብ ጨዋታው በአንድ ምድብ ከተደለደሉት ሁለቱ የኢትዮጵያና የኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድኖች የፍጻሜ ጨዋታ ላይ፣ ኡጋንዳውያን የዋንጫ ባለቤት ለመሆን በታክቲክ ረገድ የተሻሉ ሆነው መቅባቸውን ከቡድኑ አባላት መካከል ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሁለቱ ቡድኖች በዚህ ውድድር ሲገናኙ ለሁለተኛ ጊዜ እንደመሆኑ፣ በተለይ አሠልጣኞች የኡጋንዳዎችን የአጨዋወት ዘይቤና ቀደም ሲል ሜዳ ላይ ያሳዩትን ደካማና ጠንካራ ጎን በመገምገም ክፍተታቸው ምን ይመስል እንደነበር ብቻ ሳይሆን፣ ውድድሩ የፍጻሜ እንደ መሆኑም በታክቲክ በኩል ጥንቃቄ ማድረግ ይገባ ነበር፤›› በማለት ሐሳባቸውን ያካፈሉ የቡድኑ አባል፣ የእኛዎቹ ከዚህ አሰላለፍ በተቃራኒው ሆነውና ከሚገባው በላይ በራስ መተማመንና ተጋጣሚን አሳንሶ መመልከትን የሚያሳዩ ተደጋጋሚ ክፍተቶችን ሲፈጽሙ እንደታዩ አብራርተዋል፡፡

በፍጻሜ ጨዋታው በኡጋንዳውያኑ በኩል ሲደረግ የታየው፣ ኢትዮጵያውያኑ ከፍጥነትና ጉልበት ይልቅ ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት ምርጫቸው መሆኑን በመረዳት ፍጥነትና ጉልበት የተቀላቀለበትን አጨዋወት መምረጣቸውና የአሠልጣኞቻቸው ጨዋታን የማንበብ ብቃት የታየበት የጨዋታ ፍሰት እንደነበር ሙያዊ ልዩነቶችም ጭምር ውጤቱን እንደቀየሩት አስተያየት ሰጪው አመላክተዋል፡፡

በጥቂት ቀናት ውስጥ የታዳጊዎቹ ዋና አሠልጣኝ ተመስገን ዳባና ረዳቶቻቸው የቡድኑን አጠቃላይ ቴክኒካዊ ሪፖርት እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል፡፡ በቀድሞው የዋሊያዎቹ አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ሰብሳቢነት የሚመራው የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴም፣ በታንዛኒያው የታዳጊዎቹ ተሳትፎ ወቅት የታዩ ክፍተቶች ላይ ዕርምት እንደሚያደርግ ይታሰባል፡፡ ይህን ሐሳብ የሚነሰዝሩ አካላት በዋቢነት የሚጠቅሱትም፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የዕቅድ ማስፈጸሚያ ረቂቅ ሰነድ በማዘጋጀት ባለድርሻ አካላት እንዲተቹትና ግብዓት እንዲሰጡበት ማድረጉን በማስታወስ ነው፡፡ የማስፈጸሚያ ረቂቅ ሰነዱ ከሚመለከታቸው በርካታ ጉዳዮች ውስጥ የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ልማት አንዱና ዋነኛው ነው፡፡

ይሁንና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በየደረጃው የሚመራቸው ሊጎች የሚያሳዩት እንቅስቃሴና በተግባር የሚታየው እውነታ፣ የታዳጊ ወጣቶች ጉዳይ ሴካፋን የመሳሰሉ አኅጉራዊ መድረኮች ሲቃረቡ ካልሆነ ተቢው ትኩረት ሳይሰጠው መቆየቱ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ክለቦች ለታዳጊ ወጣቶች ትኩረት ይሰጡ ዘንድ፣ በተለይም ከኅብረተሰቡ መዋጮ በመሰብሰብ ክለብ የሚያስተዳድሩ የከተማና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ ለስፖርት ቢመድቡም ለተባለው ዓላማና ግብ ስለመዋሉ ግን ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል ማድረጉ ላይ ክፈተት ስለሚታይ በዚህ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ ማሳሰቢያ የሚሰጡ አልታጡም፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ክለቦች ለአገሪቱ እግር ኳስ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ያላመጡ የአገር ውስጥና የውጭ ተጨዋቾችን ለማስፈረም በሚሊዮን የሚቆጠር የሕዝብ ገንዘብ ሲያፈሱ ይስተዋላሉ፡፡ ይሁንና ለታዳጊ ወጣቶች ጥቂቱን ገንዘብ ቢያውሉና በየክለቡ እንዲጫወቱ ዕድል ቢሰጣቸው፣ ወጣት ተጨዋቾች ሰሞኑን ካሳዩትም የላቀ ውጤት አገሪቱም ክለቦችም ማስመዝገብ በተቻላቸው ነበር የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፣ ቁጭታቸውንም ተስፋቸውንም ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኑ ካሳየው ውጤት በመነሳት ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...