በሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ የሚከሰተውን የማህፀን በር ካንሰር ለመከላከል በመደበኛነት ክትባት መሰጠት ሊጀመር መሆኑ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሞላቸው ልጃገረዶች የሚሰጠው ይህ መከላከያ ክትባት፣ ከመጪው ዓመት ጥቅምት ወር ጀምሮ ተግባዊ እንደሚደረግና በጤና ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶችና በጊዜያዊ የክትባት ማዕከሎች እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡ የማህፀን በር ካንሰር ክትባት በሙከራ ደረጃ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲያካሂድ መቆየቱን ሚኒስቴሩ በፌስቡክ ገጹ አስታውቋል፡፡
በዓለም ላይ ከ200 በላይ የካንሰር ዓይነቶች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፤ ከነዚህ ውስጥ የማህፀን በር ካንሰር አንዱ ነው፡፡ የማህፀን በር ካንሰር በሽታ በኢትዮጵያ ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በስፋት በወሊድ ዕድሜ ክልል ለሚገኙ ሴቶች ሞት ምክንያት ነው፡፡ በኢትዮጵያም በየዓመቱ 7,000 የሚሆኑ ሴቶች በበሽታው የሚጠቁ ሲሆን፣ በበሽታው ከተጠቁት ውስጥም ከ3,200 በላይ ይሞታሉ፡፡
በዓለም ላይ በየዓመቱ በካንሰር ከሚያዙ 14 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ስምንት ሚሊዮኑ ይሞታሉ፡፡ በኢትዮጵያ በዓመት ወደ 60 ሺሕ የሚገመቱ ሰዎች በካንሰር በሽታ የሚያዙ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ከ44 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ይሞታሉ፡፡
የማህፀን በር ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ከሚከሰቱ የካንሰር ዓይነቶች በሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በዓለም በየዓመቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች በማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታ የሚያዙ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ 90 በመቶ የሚሆነው ሞት የሚከሰተውም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ላይ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በስፋት በአዋቂ ሰዎች ከሚታወቁ የካንሰር በሽታ ዓይነቶች መካከል የጡት ካንሰርና (30.2 በመቶ) የማህፀን በር ካንሰር (13.4 በመቶ) ናቸው፡፡
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት የማህፀን በር ጫፍ ካንሰር በሽታን ለመከላከል ክትባት ዓይነተኛና መፍትሔ ነው፡፡ በተጨማሪም ከአቅመ ሄዋን በፊት ከሚፈጸም የግብረ ሥጋ ግንኙነት በመታቀብ፣ ኮንደምን ሁል ጊዜ በመጠቀም፣ በአንድ በመወሰንና የማህፀን በር ካንሰር ጫፍ ቅድመ ምርመራ በማድረግ መከላከል እንደሚቻል ይመከራል፡፡
ከ30 እስከ 45 ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች የማህፀን በር ቅድመ ካንሰር ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡ ለማህፀን ካንሰር መንስዔ የሆነው ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ምልክት ሳያሳይ ለረዥም ጊዜ በሰውነት ውስጥ የመቆየት አቅም አለው፡፡ ቫይረሱ የቅድመ ካንሰር ምልክት ለመድረስ ቢያንስ ከ10 እስከ 15 ዓመታት ይፈጃል፡፡ ቫይረሱ ተለውጦ በማህፀን ውስጥ የማህፀን ክፍሎች ላይ ለውጥ አምጥቶ፣ የማህፀን ግድግዳ ክፍሎችን በመጉዳት ቁስለት፣ ቁስል ደግሞ ደም ውስጥ በመግባት ወደ ሰውነት ይተላለፋል፡፡
ለዚህም እንደ ምክንያት ከሚቆጠሩት መካከል የመረጃ እጥረት፣ የመሠረተ ልማት አለመስፋፋትና የመድኃኒት አቅርቦት ችግር ሲሆን፣ የግንዛቤ እጥረት መኖሩም በከፍተኛ ሁኔታ ጉዳት በማስከተል ላይ ነው። በኅብረተሰቡ ዘንድ ቅድመ ምርመራና የመከላከል ሥራዎች የሚሠራበት ልምዱና አመቺ ሁኔታዎች በስፋት አለመኖር ችግሩ ሥር እንዲሰድ መንገድ ከፋች ነው፡፡