Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልኦኒ ኒስካነን ከሮሱንዳ እስከ ጃንሆይ ሜዳ

ኦኒ ኒስካነን ከሮሱንዳ እስከ ጃንሆይ ሜዳ

ቀን:

‹‹አበበ ቢቂላ በዚያ ምሽት ሐውልቱን ቀና ብሎ ሲመለከት ደሙ ፈላ:: ሐውልቱ በጨለማው መሀል እንደ ጆቢራ ተገትሯል:: ቆፍጣናው ወታደር በግፍ የተጨፈጨፉት ወገኖቹ ታሰቡት:: በባዶ እግራቸው እስከ መጨረሻው እስትንፋስ ድረስ ለተዋጉት የኢትዮጵያ አርበኞች ደም መላሽ ሆኖ ፋሺስቱን የጣሊያን መንግሥት ሊበቀለው ቆረጠ:: ትንፋሹን አሰባስቦ ፍጥነቱን ጨመረ:: እስካሁን ድረስ ከጎኑ አላፈናፍን ያለውን ሞገደኛውን የሞሮኮውን ራህዲ ትቶት ወደፊት ሸመጠጠ:: መዳረሻው ላይ ጣሊያን ሠራሹ ድንጋያማው ኦሊምፒያድ ስታዲዮም  ባልደፈርም ባይነት እየራደ ነው፤›› እያለ የሚተርከው በቅርብ ወራት ውስጥ በስዊድን የታተመው አንድ የታሪክ ድርሳን ነው፡፡

ይህ በሰሎሞን ሐለፎም የተዘጋጀው ድርሳን ‹‹ኦኒ ኒስካነን ከሮሱንዳ እስከ ጃንሆይ ሜዳ ከ1910 – 1984›› ይሰኛል፡፡ የ1960 የሮም ኦሊምፒክ ጨዋታዎችን (በ1952 ዓ.ም.) ሮም ስታስተናግድ በማራቶን የተሳተፈችው ኢትዮጵያ በአበበ ቢቂላ አማካይነት አንፀባራቂ ድልን ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም. ማግኘቷ ይታወሳል፡፡ ዋና አሠልጣኙም ኦኒ ኒስካነን ነበር፡፡ ድርሳኑ ያንን የአበበ ቢቂላ ገድል መዘከሩን ቀጥሏል፡፡

‹‹አበበና የኮንስታንቲን ቅያስ ፊት ለፊት ተፋጠጡ:: የኢትዮጵያን ሕዝብ
አደራ ያነገበው ጥቁሩ አፍሪካዊ ከፊት ለፊቱ ተገትሮ የሚርደውን ግምብ ድጋሚ በዓለም ፊት ለማዋረድ ፍጥነቱን ጨምሮ በቁርጠኝነት ወደ ፊት ተፈተለከ። የመጨረሻውን ክር ሲበጥስ የድካም ስሜት ፈጽሞ አልታየበትም። ሁለት ሰዓት ከአሥራ አምስት ደቂቃ ከአሥራ ስድስት ሰከንድ:: አኩሪ ሰዓት:: እየተቅበጠበጠ በጉጉት ሲጠብቅ የነበረው አሠልጣኙ ኦኒ ኒስካነን በሰዎች መሀል እየተሽሎከሎከ መጥቶ አበበ አንገት ላይ ተጠመጠመ፡፡››

ኦኒ ኒስካነን ከሮሱንዳ እስከ ጃንሆይ ሜዳ

 

ኢትዮጵያ ወርቃዊ ድል ማጣጣም የጀመረችበት በደማቋዋ የአውሮፓ በጋ  ምሽት፣ ጳጉሜን 5 ቀን 1952 .. ወርቃማዋ ጀንበር ሚካኤል አንጀሎ በነደፈው ካምፒዶልዮ ተብሎ በሚጠራው አደባባይ ጀርባ ባዘቀዘቀችበት አጋጣሚ አንድ ያልታወቀ ጥቁር ገጽታ ያለው አትሌት፣ የማራቶኑን ሩጫ በአውራ ጎዳናው በቀዳሚነት ፈጸመ፡፡ በባዶ እግሩ የሮጠው አበበ ቢቂላ 2 ሰዓት 16 ደቂቃ 15 ሰከንድ የመጨረሻውን መስመር በጥሶ በማለፍ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከሁሉም በላይ እንድትውለበለብ አደረጋት፡፡ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አበበ ዋቅጅራም እንደ አበበ ቢቂላ ሁሉ በባዶ እግሩ ሮጦ በሰባተኛነት አጠናቅቋል፡፡

አበበ ቢቂላ በሮም በሽልማት ሰገነቱ ላይ እንደወጣ የመጀመሪያው «ጥቁር አፍሪካዊ» የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ አጥላቂ ሆነ፡፡ በውድድሩ ማግሥትም፣ የጣሊያን ጋዜጦች ‹‹ኢትዮጵያን ለመውረር የጣሊያን  ወታደር ሁሉ አስፈልጎ ነበር፤ ኢትዮጵያ ግን አንድ ወታደር ብቻ ልካ ድፍን ሮምን ወረረችው፤›› የሚል ጽሑፍ ይዘው ወጡ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ውድድር አሸንፎ የወርቅ ሜዳሊያ የወሰደ ጥቁር አፍሪካዊ አበበ ቢቂላ ነው። ይህም አጋጣሚ ብዙ ጥቁር አፍሪካውያን በዓለም አቀፍ ውድድሮች እንዲሳተፉ በር ከፍቷል። የአበበ ቢቂላ ዝናም ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተዳረሰ። አበበ ቢቂላን ለዚህ ስኬት ያበቁት ደግሞ ኦኒ ኒስካነን ናቸው፡፡

ኦኒ ኒስካነን ከሮሱንዳ እስከ ጃንሆይ ሜዳ

 

አበበ ቢቂላና አበበ ዋቅጅራ በባዶ እግር ለምን ሮጡ?

በሮም ኦሊምፒክ አበበ በባዶ እግሩ የሮጠበት ምክንያት በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች ሲንፀባረቁ ኖረዋል፡፡ የኦሊምፒክ ድረ ገጽን ጨምሮ የተለያዩ ምንጮች ‹‹ለአበበ የሚስማማ ጫማ በመጥፋቱና የሞከረውም ጫማ ስለጠበበው ያለጫማ መሮጥን መርጧል፤›› ሲሉ ጽፈዋል፡፡ ጸሐፊዎቹ አበበ ዋቅጅራም በባዶ እግሩ ስለመሮጡ እንኳ ያነሱት ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ እውነታውን በተመለከተ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑካን መሪው የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማ እሸቴ የገለጹት እውነታ ከኦኒ ማስታወሻ አግኝቶ ሰሎሞን በመጽሐፉ ከጻፈው ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

‹‹ከውድድሩ በፊት ሮም በነበርንባቸው ቀናት አበበ ቢቂላና አበበ ዋቅጅራ የማራቶን መሮጫውን ጎዳና እንዲለማመዱት አድርጌ ነበር፡፡ አራት አምስት ጊዜ ተለማምደውበታል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመካከለኛውንና የመጨረሻውን ክፍል እየለዋወጥን መሮጫውን አስቀድመው እንዲያጠኑት አድርገናል፡፡ በጫማም ያለጫማም ሞክረውታል፡፡ ከአበበ ቢቂላ ኋላ ኋላ በመኪና እየተከታተልኩ የአሯሯጡን ሥልት የርምጃውን ፍጥነት ወዘተ. ስቆጣጠርና ስለካም ነበር፡፡ በጫማ ሲሮጥ በባዶ እግሩ ከሚሮጠው በደቂቃ አምስት ስድስት ዕርምጃ ያህል ይቀንሳል፤ አሯሯጡም በባዶ እግሩ እንደሚሮጠው የቀለጠፈ እንዳልሆነ ልብ አልኩ፡፡ እኔን ጥየቃና እግረ መንገዱንም ውድድሩን ለመመልከት ከስዊድን የመጣው ታናሽ ወንድሜ አርነ ደግሞ በሌላ መኪና አበበ ዋቅጅራን እየተከተለ እንዲሁ ሲያጠና ነበር፡፡ ከዚሁ ግምገማ በኋላ ከነሱ ጋር ተመካክረን ሁለቱም ሯጮች በባዶ እግራቸው እንዲሮጡ ወሰንን፡፡

ከአራት ዓመት በኋላ ለኢትዮጵያ ሦስተኛዋ በሆነው የቶኪዮው የኦሊምፒክ ተሳትፎ፣ አበበ ቢቂላ ጥቅምት 11 ቀን 1957 .. ተጫምቶ በመሮጥ በኦኒ ኒስካነን አሠልጣኝነት ለሁለተኛ ጊዜ የማራቶን ድሉን አዲስ የዓለምና የኦሊምፒክ ክብረ ሰዓትን 2 ሰዓት 12 ደቂቃ 11.2 ሰከንድ በመፈጸም መስበሩ ብቻ ሳይሆን፣ የትርፍ አንጀት ቀዶ ሕክምና ባደረገ ስድስት ሳምንት ውስጥ ማሸነፉ ገድሉን ልዩ ያደርገዋል፡፡ ከእሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከእሱም በኋላ 16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድል ፈጸመ፡፡ ይኼም ብቻ አይደለም በአሸናፊነት የገባበት ሰዓትም እጅግ በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባሲል ሔትሌይ 2 ሰዓት 13 ደቂቃ 55 ሰከንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረ ወሰን 1 ደቂቃ 438 ሰከንድ የሰበረበት ነው፡፡ ‹‹እንደበረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ፣ ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደቆሎ›› ብለው በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914-1979) እንዲቀኙለት አድርጓቸዋል፡፡

በቀጣዩ አራት ዓመት አበበ ቢቂላ ለሦስተኛው ድል ሜክሲኮ ላይ ቢሮጥም፣ 17ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ባጋጠመው የጡንቻ መሸማቀቅ አቋርጦ ወጥቷል፡፡ ቢሆንም ድሉ ከኢትዮጵያ አላፈተለከም፡፡ በመስከረም 1961 .. (... 1968) የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ማሞ ወልዴ በኦኒ አሠልጣኝነት ኢትዮጵያን ለሦስተኛ ጊዜ አሸናፊ ያደረጋትን ድል አስመዘገበ፡፡ መርአዊ ገብሩም ስድስተኛ ሆነ፡፡ ማሞ 10,000 ሜትር ሩጫም ከኬንያዊው ናፍታሊ ቲሙ ጋር እልህ አስጨራሽ ፉክክር አድርጎ የብር ሜዳሊያ ለማጥለቅ ችሏል፡፡ የማሞ የማራቶን ድልም በሰሎሞን ተሰማ ገጣሚነት እንዲህ ቀረበ፤

‹‹ማራቶን ማራቶን ማራቶን ልዕልቷ

 አበበና ማሞ ሆኑ ባለቤቷ

ማራቶን ደንግጠሽ አቤን ብትቆጪ

ዞሮም አልቀረልሽ የትም አታመልጪ፤

ሮም በባዶ እግሩ ቶኪዮ በጫማ

ድል ነሺው አበበ በሁለቱ ከተማ፤

አበበ ቢወጣ በእግር ወለምታ

ማሞ ድልን ነሳ በሞቀ ሰላምታ…›› ተብሎም ተዘፈነ፡፡

20ኛው ኦሎምፒያድ የጀርመኗ ሙኒክ ከተማ 1964 .ም. (1972) ስታዘጋጅ የተካፈለችው ኢትዮጵያ ለወርቅ ባትታደልም በነሐስ ሜዳሊያ ለመታጀብ ችላለች፡፡ ማሞ ወልዴ 40 ዓመት ዕድሜው ማራቶንን ሮጦ ሦስተኛ በመሆኑ፣ አንጋፋው የኦሊምፒክ ማራቶን ባለሜዳሊያ ተሰኝቷል፡፡

በመጽሐፉ የተጠቀሱትና ስለኦኒ ኒስካነን ትውስታቸውን ያጋሩት ማሪያነ ሳውተር፣ ኦኒ በፊንላንድኛ መልካም ዕድል ማለት ነው ይላሉ፡፡ እንዳሉትም ከዕድለኛነታቸው መገለጫዎች መካከል የበኩር አትሌት አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴ ስኬቶች ይጠቀሳሉ፡፡  ‹‹…ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንዲሉ እሱም ዕድለኛም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዓለም ላይ ብዙ ቦታዎችን ጎብኝቷል፡፡ የልጅነትና የወጣትነት አፍላ ጊዜውን ያሳለፈበት ሶልናና ለሁለት ዓመት ኮንትራት ሄዶ የዕድሜውን እኩሌታ ያህል የኖረባት አዲስ አበባ ግን በኦኒ ልብ ውስጥ እጅግ ላቅ ያለ ሥፍራ ነበራቸው፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡

መታሰቢያነቱን ለነባር የማራቶን ጀግኖች አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴ፣ አበበ ዋቅጅራና ዋሚ ቢራቱ የተደረገው የሰሎሞን ሐለፎም መጽሐፍ የሚያጠነጥነው በኦኒ ኒስካነን ሕይወት ታሪክ ሆኖ ስምንት ዓበይት ምዕራፎች አሉት፡፡

ነዋሪነቱ በስዊድን የሆነው ደራሲው ሰሎሞን እንደገለጸው፣ የኦኒ ኒስካነን ታሪክ ለመጻፍ ያነሳሳው ከሦስት ዓመት በፊት በስዊድን ቴሌቪዥን የተመለከተው ‹‹ስዊድናዊውና በባዶ እግር ሯጩ›› የተሰኘው የአንድ ሰዓት ዘጋቢ ፊልም ነው፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ የተካተቱት ፎቶዎችም የተገኙት ከኦኒ ቤተሰቦችና የቅርብ ወዳጆች ነው፡፡

መጽሐፉ የኦኒ ኒስካነን ዘርፈ ብዙ ታሪክ፣ ስዊድን ቅድመ ፋሺስት ወረራና ከድል በኋላ ለኢትዮጵያ በጤና፣ በትምህርት፣ በጦር ኃይል፣ ወዘተ. ያከናወነችውን ተግባራት በተጨማሪነት ይዟል፡፡ ደራሲው ለሪፖርተር እንደገለጸው መጽሐፉ በኢትዮጵያም ይታተማል፡፡

በሔኖክ ያሬድ፣ ስቶክሆልም፣ ስዊድን

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...