Monday, May 20, 2024

የብአዴን መግለጫ የሚያመላክታቸው አገራዊ ፋይዳዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ከአራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ከነሐሴ 17 እስከ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ስብሰባ ካካሄደ በኋላ ያወጣው ድርጅታዊ መግለጫ፣ ኢሕአዴግም ሆነ አባላቱ ይታወቁባቸው የነበሩ በርካታ ጉዳዮች እንደሚለወጡ አቅጣጫዎችን ያመላከተ ነበር፡፡

ድርጅቱ ያወጣው መግለጫ በዋናነት በመስከረም 2011 ዓ.ም. ለሚካሄደው ድርጅታዊ ጉባዔ ላይ የሚቀርብ ረቂቅ ሪፖርት ለማዘጋጀት ውይይት እንደተደረገ የገለጸ ሲሆን፣ ድርጅቱ ራሱን ለመለወጥና ሕዝቡ በተደጋጋሚ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉት ውሳኔዎች የተላለፉበት ነው፡፡

የሁለት ቀናት የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የድርጅቱን ስያሜና ፕሮግራም ከመቀየር ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ እስከ መዘጋጀት የደረሱ ውሳኔዎች የላለፉበት ሲሆን፣ በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሲሳተፉ የቆዩ ነባር አመራሮችን ያገደበት ነበር፡፡

የድርጅቱን ፕሮግራምና ስያሜ መቀየር

ብአዴን የኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን) ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ሌሎቹም አባል ድርጅቶች የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም አብዮታዊ ዴሞክራሲ እንደሆነ፣ ይህም ትክክለኛውና አማራጭ የሌለው አቅጣጫ መሆኑን፣ ከዚህም አልፎ ተፈጻሚነቱን ለማረጋገጥ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን የተከተለ ክትትል የሚደረግበት ድርጅት ሆኖ የተገነባ ነው፡፡

ይህ የኢሕአዴግ ፕሮግራም ከርዕዮተ ዓለሙ የተቀዳ ሲሆን፣ ሁሉም የድርጅቱ አባላት የሚከተሉት በተደጋጋሚም በሚደረጉ ግምገማዎች ለፕሮግራሙ አፈጻጸም ክፍተቶች ያሏቸውን ድርጊቶችና አስተሳሰቦች በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡

የኢሕአዴግ መተዳደሪያ ደንብ፣ ‹‹ኢሕአዴግ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም የሚመራና በፕሮግራሙ ላይ ለሰፈሩት ዓላማዎች የሚታገል ድርጅት ነው፤›› ሲል ያብራራና፣ ‹‹ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራሙን በሥራ ላይ ለማዋል በሚያስችል ደረጃ ምልዓተ ሕዝቡን የማንቀሳቀስ ግንባር ቀደም ሚና ሊጫወት የሚችለው፣ በኢሕአዴግና በአባል ድርጅቶቹ ውስጥ ከላይ እስከ ታች አስተማማኝ የሐሳብና የተግባር አንድነት ሲኖር ነው፤›› ሲል የግንባሩ አባል ድርጅቶች ይኼንኑ ፕሮግራም ለመከተል የሚጠበቅባቸውን ያትታል፡፡

መተዳደሪያ ደንቡ አክሎም፣ ‹‹ብሔራዊ ድርጀቶች የሚመሩበትን አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ፕሮግራም በየክልላቸው ተግባራዊ በማድረግ የብሔር ብሔረሰባቸውን ሰፊ ሕዝብ መብትና ጥቅም ለማስከበር ያለሙ አደረጃጀቶች ናቸው፤›› ሲል የብሔራዊ ድርጅቶችን ማንነት ትርጉም ይሰጣል፡፡ ስለዚህም፣ ‹‹ኢሕአዴግ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ዓላማ ተግባራዊነት የሚንቀሳቀስ ድርጅት ስለሆነ፣ በአባልነት ሊቀበልና ሊያሰባስብ የሚችለው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ዓላማን በግልጽ በፕሮግራማቸው ላይ የቀረፁ ድርጅቶችን ብቻ ነው፤›› ሲል ይደመድማል፡፡

በዚህ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የኢሕአዴግ አባል የሆነ ድርጅት የሚከተለው ፕሮግራም ከኢሕአዴግ ጋር የሚጣጣም መሆን እንዳለበት የሚገልጽ ሲሆን፣ የብአዴን ፕሮግራም የመቀየር ትልም ኢሕአዴግ ውስጥ የቆየውን ባህል ወደ ጎን የማለት አዝማሚያ እንደሆነ፣ ምናልባትም የግንባሩ አባላት ሊከፋፈሉ ይችላሉ የሚሉ አሉ፡፡

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ፓርቲው ሙሉ ለሙሉ ድርጅታዊ የፕሮግራም/ የርዕዮተ ዓለም ለውጥ ያመጣል የሚሉም አልጠፉም፡፡

ብአዴን ምንም እንኳን ስያሜውን እንደሚቀይር ከዚሁ የፕሮግራም ለውጥ ጋር የጠቆመ ቢሆንም፣ እንዴትና ወደ ምን የሚለው በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ ይሁንና፣ የኦሕዴድን ፈለግ ተከትሎ በተመሳሳይ ለውጥ ሊያደርግ እንደሚችል የሚጠቁሙ  አሉ፡፡

ይኼንን የሚመለከተው የድርጅቱ መግለጫ ክፍል እንደሚስረዳው፣ ‹‹የአማራን ሕዝብ ታሪክ፣ ትግል፣ ባህልና ሥነ ልቦና በአግባቡ የተገነዘበና የተረዳ፣ እንዲሁም አሁን ከተፈጠረው አዳጊ አገራዊና ክልላዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚራመድ የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ድርጅቱ ቀደም ሲል ሲመራበት የነበረው ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ የሕዝቡንና የአባላቱን ፍላጎት መሠረት በማድረግ ግልጽ በሆነ ተሳትፎ እንዲሻሻል ይደረጋል፡፡ በዚህ ረገድ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት የድርጅታችን አባላት ጥያቄ እስከሆነ ድረስ የድርጅቱን ስያሜ ጨምሮ ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮችም በአግባቡ እየተፈተሹ፣ ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ ማሻሻያ ሊደረግባቸው እንደሚችል ማዕከላዊ ኮሚቴው ያምናል፤›› ሲል የውሳኔውን አስፈላጊነት ያብራራል፡፡

የወሰንና የድንበር አከላለል

የብአዴን መግለጫ ከተመለከታቸው ጉዳዮች መካከል የክልሎች ወሰን አከላለልና የአማራ ክልል ከሱዳን ጋር የሚካለልበት ድንበር ጉዳይ ተጠቃሽ ናቸው፡፡

መግለጫው የክልሎችን አከላለል በሚመለከት፣ ‹‹በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ የሕዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የእኩልነትና የፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በነፃነት የመሥራትና የመኖር መብቶች ሁሉ በትክክለኛው ገጽታና በተሟላ መንገድ እንዲከበሩና ኢትዮጵያ ለሁላችንም የተመቸች አገር እንድትሆን፣ ብአዴን ከሌሎች እህት ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን ይሠራል፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት አባላት ክልሎች አከላለል በሕዝቦች እውነተኛ ፍላጎትና ንቁ ተሳትፎ፣ ብዝኃነትንና አገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር አግባብ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርጎ እንዲከለል እንታገላለን … የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው በሕዝብ ነፃ ተሳትፎ እንዲፈቱ ብአዴን በምክንያት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ትግል ያካሂዳል፤›› ይላል፡፡

እነዚህ የክልል ወሰን አከላለል ጥያቄዎች ክልሉን በክልሉ ወሰኖችና በሌሎችም የአገሪቱ ክልሎች መዋሰኛዎች አካባቢ ግጭቶችን ያስከተሉ እንደነበሩ የሚገልጸው የብአዴን መግለጫ፣ የወሰኖቹ ማካለል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አስቀምጧል፡፡

ካሁን በፊት በሶማሌ ክልልና በኢሮሚያ ክልል፣ በኦሮሚያ ክልልና በደቡብ ክልል፣ በአማራ ክልልና በትግራይ ክልል መካከል ወሰንን የሚመለከቱ ግጭቶች የተስተዋሉ ሲሆን፣ በአንዳንዶቹ አካባቢዎች ማንነትን የሚመለከቱ ጥያቄዎች ቀርበው ሕዝበ ውሳኔ እስከማካሄድ ተደርሶ ነበር፡፡

ብአዴን ሌላው በማዕከላዊ ኮሚቴው የተወያየበትና በመግለጫው ያተተው ተያያዥ ጉዳይ ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ጉዳይ ሲሆን፣ የፌዴራል መንግሥት ትክክለኛ ትኩረት ሰጥቶት በአስቸኳይ እንዲፈታም ጥሪ አቅርቧል፡፡

መግለጫውም ከሱዳን ጋር ያለውን ድንበር በሚመለከት፣ ‹‹በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ማካለል ጉዳይ በዘላቂነት እስኪፈታ ድረስ የሁለቱም ወገን አርሶ አደሮች የያዙትን የእርሻና የደን መሬት እንደያዙ እየተጠቀሙ እንዲቆዩ፣ በሁለቱ አገሮች መንግሥታት መካከል ስምምነት ተፈርሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በተለይ በመተማ ወረዳ ልዩ ስሙ ደለሎ በተባለው አካባቢ ታሪካዊ ዳራውንና ነባር የይዞታ መብታችንን ያላስጠበቀ፣ የሚመለከታቸውን አካላት ያላሳተፈና የጋራ አቋምም ያልተያዘበት ውሳኔ ተሰጥቶ እንደነበር አውቀናል፡፡ ይህ ውሳኔ ብአዴንና አመራሮቹ ለረዥም ጊዜ በሕዝብ ዘንድ ባልተገባ መልኩ ሲታሙና ሲጠረጠሩ እንዲቆዩ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ውሳኔው በፌዴራል መንግሥት በኩል አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲደረግበት እንጠይቃለን፤›› ብሏል፡፡

ለጋራ የፀጥታ ማስከበር ሥራም በአካባቢው የሰፈረው የሱዳን መከላከያ ሠራዊት ካምፑን እያሰፋ መቆየቱ ተገቢ እንዳልሆነ የገለጸ ሲሆን፣ የሱዳን ጦር በፍጥነት ከይዞታው ለቆ እንዲወጣና የፌዴራል መንግሥትም ይኼንኑ እንዲያስፈጽም ማዕከላዊ ኮሚቴው ጥሪ አቅርቧል፡፡

የዜጎች ግለሰባዊ መብት መከበር

ብአዴን በመግለጫው ካነሳቸው ያልተለመዱ ሀተታዎች አንዱ የግለሰብ መብትን የሚመለከት ሲሆን፣ ይህም እስካሁን የቡድን መብት ሲከበር የግለሰብ መብቶች አብረው ይከበራሉ በሚለው የድርጅቱ እሳቤ የግለሰብ መብቶች ሲጨፈለቁ ነበር በሚሉ አካላት ከፍተኛ ትችት ሲቀርብበት የቆየ ጉዳይ ነው፡፡

የግለሰብና የቡድን መብቶች ተጣጥመው መከበር እንዳለባቸው አምናለሁ ያለው ድርጅቱ፣ የግለሰብ መብት ሳይኖር የቡድን መብት ሊኖር እንደማይችልና ያለቡድን መብት ደግሞ የተሟላ ዴሞክራሲ እንደማይመጣ በመግለጫው አስታውቋል፡፡

ይኼንንም በሚመለከት፣ ‹‹የግለሰብና የቡድን መብቶች ተጣጥመው መከበር እንዳለበቸው እናምናለን፡፡ የግለሰብ መብት ባልተከበረበት የቡድን መብት ቦታ እንደማይኖረው፣ የቡድን መብት ባልተከበረበትም የተሟላ ዴሞክራሲ እንደማይኖር የታወቀ ነው፡፡ ሁለቱን መብቶች አጣጥሞ በመሄድ ረገድ ሕገ መንግሥታችን ብዙ ርቀት ተጉዟል፡፡ በመሆኑም በአገራችን ትክክለኛ ዴሞክራሲ እንዲገነባ ትልቅ መሠረት ተጥሏል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት በሁሉም መስኮች በቂ ሥራ ካለመሠራቱም በላይ፣ በተለይ ደግሞ ለቡድን መብት መከበር የተሰጠውን ትኩረት ያህል ለግለሰብ መብትም ስላልተሰጠ የተጀመረው የቡድን መብት የማስከበር ሥራ ወደፊት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ትኩረት ተነፍጎት የቆየው የግለሰብ መብት በሚዛናዊነት የሚከበርበት ሥርዓት ዕውን እንዲሆን ይደረጋል፣›› ሲል አስታውቋል፡፡ ‹‹ዜጎች በገዛ አገራቸው ተዋርደው ሊኖሩ እንደማይገባ፣ በዚህ ረገድ የሚፈጸምን ማንኛውንም ኢሕገ መንግሥታዊ ድርጊትም ውጉዝ እንደሆነ ብአዴን አጥብቆ ያምናል፤›› ብሏል፡፡፡

ነባር አመራሮችን ማገድ

በብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከተላለፉ ውሳኔዎች አንዱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት አልቻሉም በተባሉ የድርጅቱ አመራሮች ላይ ዕርምጃ መውሰድ ነው፡፡ ይኼንንም ተከትሎ የድርጅቱ ነባር ታጋዮች አቶ በረከት ስምፆንና አቶ ታደሰ ካሳን የድርጅቱ ጉባዔ እስከሚካሄድ ድረስ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አግዷል፡፡

‹‹ብአዴን በውስጡ ጤናማ የሆነ የአመራር ቅብብሎሽ ሥርዓት ይኖር ዘንድ ለአመራር ግንባታ ሥራ በቂ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል፡፡ በተለይም አሁን እየታየ ያለውን ከፍተኛ የፖለቲካ ንቃትና ምርጥ ሕዝባዊ ማዕበል በዕድልነት በመጠቀም በድርጅቱ ውስጥ በብቃት የተገነባ ብልህ፣ አርቆ አሳቢና አስተዋይ ተኪ አመራር እንዲኖር የተማረውን ወጣት ማዕከል ያደረገ የአመራር ምልመላና ግንባታ ሥራ ያካሂዳል፡፡ በአንፃሩም አሁን ከተደረሰበት የትግል መድረክና ከለውጡ እንቅስቃሴ ጋር አብረው መጓዝ በተሳናቸውና ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት ባልቻሉ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ለይ ዕርምጃ የተወሰደ ሲሆን፣ ድርጅቱ ራሱን የማጥራት እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ይቀጥላል፤›› ሲል አሁን የተወሰደውን ዕርምጃ አስታውቆ ተመሳሳይ የሆኑ ዕርምጃዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ጠቁሟል፡፡

ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት የታገዱት አቶ በረከትና አቶ ታደሰ በጋራ ባወጡትና በማኅበራዊ ሚዲያና በድረ ገጾች ሲዘዋወር በነበረ አስተያየት፣ ‹‹አንድ የፖለቲካ ድርጅት በውስጣዊ አሠራሩ መሠረት በአባላቶቹ ላይ የሚያስተላልፈው የቅጣት ውሳኔ እንዴት ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰበር ዜና እንደሚሆን ግልጽ አይደለም፤›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ምናልባት ማዕከላዊ ኮሚቴው ዜናውን በማስጮህ ለማግኘት የከጀለው የትርፍ ሥሌት ሊኖር ይችል ይሆናል እንጂ፤›› በማለት ደምድመዋል፡፡

በድርጅቱ አሠራር መሠረት አባሉ ራሱን መከላከል በማይችልበት ሁኔታ ላይ ሆኖ ሳለ እንዲህ ያሉ ዕርምጃዎችን መውሰድ ልክ እንዳልሆነ አስታውቀው፣ ባልተገኙበት ስብሰባ የተላለፈውን ውሳኔ በመወረፍ በስብሰባው ላይ ያልተገኙበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡

ይኼንንም ሲገልጹ፣ ‹‹በስብሰባው መገኘት ነበረባቸው የሚል መከራከሪያ ሊቀርብ እንደሚችል እንገምታለን፡፡ ያልተገኘንበት ምክንያት ግን ለማዕከላዊ ኮሚቴው ሥውር አይደለም፡፡ ታደሰ ጥሪው ቢላክለትም አልደረሰውም። በረከት ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት ነሐሴ 9 ቀን 2010 ዓ.ም. በተላከ ኢሜይል የስብሰባው ጥሪ ደርሶታል። ጥሪው እንደደረሰው ለጊዜው የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለሆኑት ለአቶ ጌታቸው ጀንበርና መልዕክቱን ለላኩት ለአቶ ዘለቀ አንሉ በስብሰባው ላይ ቢሳተፍ ደስ እንደሚለው፣ ነገር ግን በክልሉ በሌለበት ጭምር እየተካሄደ ባለው ተደጋጋሚ የጥቃት ሙከራ ሰለባ መሆን እንደማይፈልግና አመራሩ የፀጥታ ዋስትና ከሰጠው መምጣት እንደሚችል አሳውቋል። የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊዎችም ችግሩ ተጨባጭ እንደሆነ እንደሚቀበሉና መፍትሔ እንደሌላቸው ገልጸውለታል። ‹የመጣው ቢመጣ መገኘት አለባችሁ፣ እኛ/እኔ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ› የሚል ደፋር በሌለበት ሁኔታ፣ እንኳን እኛ ከወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ጋር ትውውቅ ያለን ሰዎች፣ ሌላውም ቢሆን አደጋን ከሩቁ ተመልክቶ ለማስወገድ ይሞክራል እንጂ፣ ራሱን በጀብደኝነት አሳልፎ የሚሰጥ አይመስለንም፤›› ብለዋል፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ከእነዚህ ውሳኔዎች በተጨማሪ ጥረት ኮርፖሬትና የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ተጠሪነታቸው ለፓርቲው መሆኑ ቀርቶ፣ ለክልሉ መንግሥት እንዲሆንም ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

የብአዴንን መግለጫ የተከታተሉ አካላት በተለያዩ መድረኮች በሰጧቸው አስተያየቶች፣ የተላለፉት ውሳኔዎች በፓርቲው ውስጥ ክፍፍሎች አሁንም ድረስ እንደሚታዩና የኢሕአዴግ ወደ አንድ አገራዊ ፓርቲ የመቀየርም ሆነ የጥምረቱ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሆነ ለመናገር አዳጋች ጊዜ ላይ እንደሚገኝ እየገለጹ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -