Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምሊቢያ አዲሷ አይኤስን መፋለሚያ ምድር

ሊቢያ አዲሷ አይኤስን መፋለሚያ ምድር

ቀን:

ሊቢያውያን ለ40 ዓመታት ሲያስተዳድሯቸው የነበሩትን ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊ እ.ኤ.አ. በ2011 ከሥልጣን በሞት ካስወገዱ በኋላ ሰላምን አግኝተው አያውቁም፡፡ በወቅቱ ጋዳፊን ከሥልጣን ለማውረድ ሲዋጉ የነበሩ ኃይሎችን ሲደግፍ የነበረው ኔቶ፣ ሊቢያ በቀውስ ማጥ ውስጥ ስትዋዥቅ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ማምጣት አልቻለም፡፡ በአገሪቱ የነበረው ሰላም ደፍርሶ የጦርነት አውድማ ስትሆንም፣ የጋዳፊን አስተዳደር ለመደርመስ በነበረው ፍጥነት ያህል ሰላም ለማስፈን አልሮጠም፡፡ በመሆኑም ሊቢያውያን ከእርስ በርስ ጦርነት አልፈው የአይኤስ መፈንጫ ሆነዋል፡፡ ሊቢያም ለአይኤስ አዲስ የተስፋ ምድር ከሆነች ሰነባብታለች፡፡

በነዳጅ ሀብቷ በበለፀገችውና ነፃ የሕክምናና የትምህርት ዕድል በመስጠት በአፍሪካ ለሕዝቦቿ ከፍተኛውን የኑሮ ጣሪያ ያስቃኘችው ሊቢያ፣ ዛሬ ተሽመድምዳለች የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥም ገብታለች፡፡ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህም ማንኛውም የጦር መሣሪያ ያነገበ እንዳሻው እያስተዳደራት ይገኛል፡፡

 ቢቢሲ እንደሚለው፣ እስካሁን 1,700 ያህል መሣሪያ የታጠቁ ቡድኖች በሊቢያ ተፈልፍለዋል፡፡ አገሪቷም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በሚደግፈውና በማይደግፈው ሁለት መንግሥታት እየተወዛገበች ትገኛለች፡፡ ይህም ለሕዝቡ ግዞትን፣ ለአይኤስ ምቹ ምኅዳርን ፈጥሯል፡፡

- Advertisement -

የጋዳፊ የትውልድ ሥፍራ የሆነችው ሰርት፣ ለጀሃዲስቶች ማሠልጠኛ፣ ገቢ ማሰባሰቢያና ጥቃት ለሚፈጽሙባቸው ሥፍራዎች ዕቅድ መንደፊያ ሆናለች፡፡ ሊቢያ በአጠቃላይ ከጋዳፊ የጦር መጋዘኖች በተዘረፉና ከውጭ በሚገቡ መናዊ የጦር መሣሪያዎች የጦርነት መናኸሪያ ሆናለች፡፡

ጋዳፊ ከተወገዱና ለሁለት ዓመታት ያህል የውስጥ ጦርነት ከተካሄደ በኋላ እ.ኤ.አ. በ2014 ጠቅላላ ምርጫ የተደረገ ቢሆንም፣ በትሪፖሊ ሥልጣን ይዘው የነበሩ ወገኖች ከሥልጣን መውረድን አልፈቀዱም፡፡ በመሆኑም ሌላኛው ወገን በቶብሩከ የራሱን ፓርላማ መሥርቶ መንቀሳቀስ ጀምሯል፡፡

በቶብሩክ የራሱን መንግሥት የመሠረተው ወገን በተባበሩት መንግግሥታት ድርጅትና በኃያላን አገሮች ድጋፍ ቢኖረውም፣ ጋዳፊን ለመጣል አንድ የነበሩት ከሥልጣን ጋር በተያያዘ ሊሰማሙ ባለመቻላቸውና ጥምር መንግሥት ባለመመሥረታቸው፣ አይኤስ አድማሱን እንዲያሰፋና በሊቢያ ላይ እንዲሠለጥንም ሌላው ምክንያት ሆኗል፡፡

ከኢራቅ፣ ከሶሪያና ከቱኒዚያ የመጡ የአይኤስ ተዋጊዎች ተስፋፍተዋል፡፡ በተለይ ሰርትን ተቆጣጥረው ይገኛሉ፡፡ አይኤስ በሰርት ወታደራዊ ቤዝ አለው፡፡ 1,500 የሚጠጉ ተዋጊዎችም በከተማው ይገኛሉ፡፡ የአይኤስ ሕገ ደንብም በሰርት በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ ወንዶችና ሴቶች ምን ዓይነት አለባበስ መከተል እንዳለባቸውም መመርያ ተሰጥቷል፡፡ ሃይማኖታዊ ፖሊስ የተቋቋመ ሲሆን፣ ሕገ ደንቡን የተላለፉ ሞት ይጠብቃቸዋል፡፡

አይኤስ በሶሪያና በኢራቅ ያጣውን ምኅዳር በሊቢያ እያገኘ መሆኑን በመጥቀስ፣ አሜሪካና ፈረንሣይ በተባበሩት መንግሥታት ድርድት የሚደገፈውን የሊቢያ መንግሥት መሣሪያ በማስታጠቅና ወታደራዊ ድጋፍ በመስጠት አይኤስን እንደሚዋጉ አስታውቀዋል፡፡

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ኃያላን አገሮች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሊቢያ ላይ የጣለውን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንዲያነሳ እንዲጠይቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

‹‹አይኤስ ለሊቢያ ተጨማሪና አዲስ ሥጋት ስለሆነ አይኤስን ማስቆም ወሳኝ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ባለፈው ወር በተባበሩት መንግሥታት ድጋፍ ድጋፍ ያለው የሊቢያ መንግሥት፣ ‹‹አይኤስን ማስቆም ካልተቻለ ሊቢያ ሙሉ ለሙሉ በቡድኑ እጅ ትወድቃለች፤›› ሲል አስጠንቅቆ ነበር፡፡

ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ውይይት ያደረጉት ጆን ኬሪ፣ በሊቢያ በየቦታው ተበታትነው የሚዋጉ ኃይሎችን ማሰባሰብና አንድ አካል መፍጠር ለሊቢያ ህልውና ዋናው መሠረት ነው ብለዋል፡፡ ይኼን ማድረግ ካልተቻለ አይኤስን ከሊቢያ ማጥፋት እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

በሁለት መንግሥት በምትመራው ሊቢያ ግልጽ የሆነ ሥርዓት የለም፡፡ በመሆኑም ለሊቢያ የጦር መሣሪያ ገደቡን ማንሳት መሣሪያው በማናቸውም እጅ እንዲገባ በር መክፈት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ቀድሞውንም በቡድን ለተሰበጣጠሩትና በሁለት መንግሥታት ትዕዛዝ ለሚተዳደሩት ሊቢያውያን ተጨማሪ ፈተናና ለአይኤስ የመንሠራፋት ዕድልን ማስፋፋት ነው የሚል ድምፅም ይሰማል፡፡

ጆን ኬሪ በሊቢያ ጂኤንኤ (ገቨርንመንት ኦፍ ናሽናል አኮርድ) አገሪቷን አንድ ሊያደርግ የሚችል አካል እንደሆነ ያምናሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ድጋፍ የሰጠው ለዚሁ አካል ነው፡፡ የጦር መሣሪያ ገደቡን ቢያነሳም ይህ አካል ኃላፊነት ሊወስድ እንደሚችል፣ አይኤስንም ለማጥቃት ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

የሊቢያ መንግሥት የመሣሪያ ገደቡ እንዲነሳለት ያቀረበው ጥያቄ በቅርቡ ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አሜሪካም የጦር መሣሪያ ገደቡ መነሳትን ትደግፋለች፡፡

ሰሞኑን በቪዬና ተካሄዶ በነበረው ስብሰባም ጆን ኬሪ ሊቢያን መሣሪያ በማስታጠቅና ወታደራዊ ባልሆኑ ቁሳቁሶች መደገፍ ከኃያላን አገሮች ጋር የተስማሙባቸው አጀንዳዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከአፍሪካ ወደ አውሮፓ ለሚጓዙ ስደተኞች መናኸሪያ የሆነችውን ሊቢያ መታደግ፣ በስደተኞች ጎርፍ እየተጥለቀለቁ የሚገኙትን የአውሮፓ አገሮች ለመታደግም ነው፡፡ በመሆኑም ሊቢያን ከአይኤስ ማላቀቅም ሆነ በአገሪቱ አንድ መንግሥት መመሥረት ወሳኝ ነው ተብሏል፡፡

ጆን ኬሪ እንደሚሉት ጂኤንኤን መደገፍና በቀጣናው ካሉ አገሮች ጋር በመተባበር በሰዎች ሕገወጥ ዝውውርና በሽብር የተሰማሩ ቡድኖችን ማጥፋት ግድ ይላል፡፡ ለእዚህም አሜሪካ የሊቢያ መንግሥት የጠየቀውን ወታደራዊ ሥልጠናና ለባለሥልጣናት ጥበቃ የሚያገለግሉ የጦር መሣሪያዎች ለመስጠት፣ እንዲሁም በሊቢያ የሚገኙ ቡድኖችን ጠራርጎ ለማስወጣት እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ በዚህም ምክንያት ሊቢያ አዲሷ አይኤስን መፋለሚያ ምድር ለመሆን እየተዘጋጀች ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...