Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የምን መጓተት ነው?

እነሆ መንገድ። ከሜክሲኮ ወደ ሳር ቤት ልንጓዝ ነው። ስትበር ያገኘናት በራሪ ታክሲ ለቃቅማ ሞልታን ቦታ ቦታ ይዘናል። ሳንዘራ በምንለቀምበት በዚህ መንገድ ሁላችንም የነፍስ አድን ኑሮ ተኮር ሩጫችን ላይ እንረባረባለን። የሩጫችንን ጎዳና ላስተዋለው ትዕይንቱ ዓምደ ብዙ ነው። ገሚሱ ግራ ቀኝ ሳይል እንደ ጋሪ ፈረስ፣ ከልጅነት እስከ እውቀት በተገራበት የሕይወት ፍልስፍና ይሮጣል። ገሚሱ ሩጫና ዕርምጃን እያፈራረቀ ሪከርድ መስበር ሳያምረው ባደረሰው ሰዓት ለመጨረስ ተሳታፊ ነው። አንዳንዱ ያለ መስመሩ እየገባ፣ ተደናቅፎ እያደናቀፈ ለራሱም ሳያፍር ለሌላውም ሳይገደው የሯጭነቱን ሚና ትቶ መሰናክልነቱን ተያይዞታል። አንዳንዱ ደግሞ የመጣበትን እየረገመ፣ ያፈሰሰው ላብ ሳያሳዝነው ወደ አባት እናቱ የትዝታ ቀዬ፣ ወደ ጥንት ጠዋቱ ያለፈ ጊዜ ልመለስ ብሎ ወደ ኋላ ሲሮጥ ባለ ራዕዮቹን ያምታታል።

እንባና ሳቅ ከሞሉበት ከዚህ ጎዳና አረፍ ስንል ታክሲያችንን ውስጥ ሽንቆጣው፣ ቁም ነገሩ፣ ሒሱና ሽሙጡ ደርቷል። “ወይ ጉድ ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው?” ይላል የወያላው መከዳ ላይ የተቀመጠ ጎልማሳ። “ምነው?” ይላል ወያላው። “ሳንሠለፍ ታክሲ ተገኘ ብዬ ነዋ። በሰላም ነው? እንጃ አንድ ነገርማ አለ፤” ይላል በለበጣ ፊቱን አውዝቶ። “ምን ነገር ይኖራል? አገሩም ሰላም ምድሩም ልማት ላይ ነው፤” አለችው ነጠላ አዘቅዝቃ ተከናንባ ከጎኑ የተሰየመች ተሳፋሪ። “የለም! ያለመድነው ነገር ሲሆንማ መጠርጠር አለብን፤” ሲላት፣ “ምነው ታዲያ ሚሊዮነር ሲበዛ የማንጠረጥር?” አለችው። “እኔ እሱን አላልኩም። ሠልፍ ከቀረብን፣ መብራት ካልጠፋብን፣ ውኃ ካልሄደብን፣ የቤት ኪራይ እያደር ካልጨመረብን ነገር አለ ነው ያልኩት፤” ሲላት፣ “አንተው ታመጣው አንተው ታሮጠው፤” ብላ ሳቅ አለች። ጨረሱ ብለን ስንደላደል፣ “ምን ዋጋ አለው ብናሯሩጠው? ካላቀዳደምነው?” ብሎ መለሰላት። መቀዳደሙና መጓተቱ ላይ ጥያቄ ስላለ ነዋ?

ጉዟችን መጀመሩ ነው። ድንገት አንድ ባለ ገብስማ ፀጉር በምልክት ቅርብ ወራጁነቱን ጠቁሞ አስቆመንና ወያላው አስገብቶት ሞተሩ ላይ አስቀመጠው። እጅ እየነሳ፣ “እንኳን ደስ አላችሁ ብያለሁ፤” አለ። መሀል መቀመጫ የተቀመጡ ደርባባ ወይዘሮ፣ “እንኳን አብሮ ደስ አለን፤” ብለው አፀፋውን መለሱ። ሦስተኛው ረድፍ ከጎኔ የተቀመጠ የፌስቡክ ሱሰኛ፣ “በባዶ ሜዳ ዋንጫ መሳም ተጀመረ?” አለ ጮክ ብሎ። “ባትሰማ ነዋ። አገራችን እኮ በሚሊየነሮች ቁጥር ከአፍሪካ አንደኛ ሆነች፤” ገብስማ ፀጉሩን እያሸ የደስታውን ምክንያት አበሰረ። “አቤት? ቆይ ምንድነው በአፍሪካ አንደኛ ከመሆን ጋር ያለን አባዜ? ከራሳችን ጋር አንፎካከርም መጀመርያ?” ስትል ከወይዘሮዋ ጎን የተቀመጠች መለሎ፣ “ታዲያ አሁንስ ከማን ጋር ተፎካከርን? አፍሪካውያን አይደለንም እንዴ?” አላት ጎልማሳው ዘወር ብሎ።

“ይደገም! ይደገም! በሚሊኒየማችን ነው በሚሊየነሮቻችን ቁጥር ነው አንደኛ ያወጣነው?” አሉት መጨረሻ ወንበር የተቀመጡ ተራቢ ወጣቶች። “በሚሊየነሮች ቁጥር፤” አለ ገብስማው። ከልቡ እንደፈነደቀ ዓይኖቹ ውስጥ ተጽፏል። “እንዴ! ሳናፀድቅላቸው? ማን ወክሉንና ተወዳደሩ ብሏቸው ነው ቆይ?” ሲል አንደኛው፣ “ማንን ወክለህ የምታውቀውን ነው?” ብላ ቆንጂት ሰረበችለት። “ኧረ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዳይሰማ?” ጋቢና የተቀመጠ ተሳፋሪ አስተጋባ። “ኤጭ ምናለበት ሚሊየነሮቻችንን ዘክረን ብንጨርስ? ምን ውክልና ላይ አስኬዳችሁ እስኪ?” አሉ ወይዘሮዋ። “ዘንድሮ ሳይወከሉ ሚሊየነር መሆን አይቻልማ፤” ሲላቸዌ ጎልማሳው “እኮ ማነው ወካይ ማነው ተወካይ?” ትኩር ብለው ሲያዩት፣ “ኪራይ አሰብሳቢና ኪራይ ሰብሳቢ፤” አላቸው። “የትም ፍጩት ዱቄቱን አምጡት ተብለን ነዋ። ምን እናድርግ ታዲያ?” ብለው ሳይጨርሱ፣ “ሁላችንም ስንፈጭ ዱቄት ባንሆን ይቆጨኝ ነበር’ ያለችው ሽንብራ ናት ጤፍ?” ብሎ ፀጉረ ገብስማው አስፈገገን። ጊዜ ያገዘው የትም ፈጭቶ ያደቃል፣ እኛ እዚህ በነገር ወፍጮ አሽሙር እንፈጫለን። ወይ መጅና ታክሲ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወይዘሮዋ ስልካቸውን አውጥተው ለመደወል ፈለጉና ዓይናቸው እንቢ አለ። መነፀራቸውን ከሰገባው መዘው የአፍንጫቸው ዘንግ ላይ አመቻቹ። ጥቂት ቁጥሮች ተጭነው ሃሎ አሉ። “ምን እየሠራሽ ነው? ጎመኑን ጣድሽው? ያን የፋሲካ ፍሪጅ ውስጥ ያስገባነውን ሥጋ አውጨውና በረዶው ይቅለጥ። ደግሞ በረዶው እስኪቀልጥልኝ ነው ብለሽ ዛራና ቻንድራ ላይ ቀልጠሽ ቅሪ አሉሽ . . . ምንድነው የምሰማው? ቴሌቪዥኑ ክፍት ነው እንዴ? ሃሎ ሃሎ…” ሲሉ ኔትወርክ እልም አለ። “የት አገር ልሰደድ እናንተ በደከመ አቅሜ” ብለው ሲያጉረመርሙ፣ “ቆይ እኔ ጥሩ የቴሌቪዥን ቤት የሚሠራ የብረታ ብረት ሠራተኛ አውቃለሁ። አገናኝዎታለሁ…”  ማለት ጎልማሳው።

“ይኼማ መረጃ የማግኘት መብትን መጋፋት ነው። ቴሌቭዥንን ማሰር ነፃ ፕሬስን ከማፈን ምን ለየው?” አለ ቅርብ ወራጅ ነኝ ብሎ ሞተሩ ላይ ተሟሙቆ የቀረው ገብስማ። “አይ የለም በገዛ ቤቴ በገዛ ቴሌቭዥኔ ያረረ ምግብ ልብላ ታዲያ? ድስት ማሳረርስ ሠርቶ የማግኘትና የመብላት መብትን አይጋፋም ያለው ማን ነው?” ወይዘሮዋ ቱግ አሉ። “ቆይ ግን በምን መሥፈርት ነው አንድ ሰው የጣቢያ ባለቤት እየሆነ ያለው?” ስትል ቆንጂት ሁሉም ተደናግጦ ተያየ። “መሬት የግል ሳይሆን ጣቢያ ለግለሰብ ተፈቀደ ነው የምትይን? የመንግሥቱን ሳንችለው?” ብሎ ጎልማሳው ቀላቀለው። “ኧረ ስለቴሌቪዥን ጣቢያ ነው ያወራሁት፤” ከማለቷ፣ “ነው እንዴ? በምንስ መሥፈርት ቢሆን ዋናው ነገር ከአንድ ጣቢያ አገዛዝ ወደ አማራጭ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች መሸጋገራችን አሪፍ ነው። ነገ ደግሞ ከአንድ ፓርቲ ወደ ሁለት ሦስት እንሻገር ይሆናል። አይደለም እንዴ?” ብሎ በዓይኑ ጠቀሰን። ሚሊየነር ያበዛልን ሚሊኒየማችን ዕድሜና ጤና ያደለው መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ላያሳየን ነው? የምን በቴሌቭዥን በገሀድ ነው እንጂ!

            ወያላው ሒሳብ ተቀብሎን ሲያበቃ መልስ ላለው እያረፈ ይመልሳል። መጨረሻ ወንበር ወደ ተቀመጡት ወጣቶች ጠጋ ብሎ ሳንቲም ሲያድል፣ “እግዜር ይስጥልኝ፤” አለው አንዱ። “መልስህ እኮ ነው?” ወያላው ግራ ገባው። “ድሮ ድሮ እናንተ ነበራችሁ የመልስ ፀር። ዛሬ እናንተ ስለተሻላችሁ ነው የማመሰግንህ፤” አለው ሌላኛው። “ማን ባሰ ደግሞ?” ወደ መስኮቱ ጥግ የተቀመጠች ተሳፋሪ ጠየቀች። “ማን ያልባሰ አለ። ይኼው አታይም እንዴ ለአቅመ ጥያቄ፣ ሒስና ክርክር ያልደረሰ ርዕሰ ጉዳይ እየተነሳ የመለፍለፍ ችግር በማያውቃቸው አላዋቂ አጥፊዎች አገር ሲታመስ? ‘እረፉ እኔም ባለሙያ እንደሆንኩ እወቁ’ የሚል ሰው እንደ ጠፋ፤” አላት ቱግ ቱግ እያለ። “አልገባኝም?” ስትለው “ምሳሌ ልስጥሽ” ብሎ ጀመረ።

“የውጭ ፊልሞችን በአማርኛ ተርጉሞ የሚያሳይ የቴሌቭዢን ጣቢያ ተከፈተ። ከዚያስ? ‘መንግሥት እንዴት አገር ሲወረር ዝም ይላል?’ ብሎ አንዱ ለኮሰ። ‘ሌላው ተቀብሎ ታላቅ የባህል ወረራ ብቻ ሳይሆን ልጆቻችንን ተንኮል ለማስተማር ቆርጦ የተነሳ ጣቢያ ነው’ ሲል አራገበው። ፈጣሪ ያሳይሽ። ጭራሽ መከልከል አለበት፣ መዘጋት አለበት፣ መጠርቀም አለበት እያለ ማንም እየተነሳ የገዛ ቤቱን፣ የገዛ ጉዱን መሸፈኛ በር መዝጋት ያቃተው ሁሉ ሕግ አውጪ ሆነ። እህ?  ‘ልጅ ፊት አይወራም፣ ልጄ ፊት አይባልም’ ማለት የማናውቅ ወላጆች፣ ሕፃናት ፊት የታባቱ የታባቷ እያልን የምንዛዛት ሰዎች ሰበብ ተገኘ ለወቀጣ። ልጆቻችንን ዘመናዊ ያደረግን መስሎን ያለገደብ ባሸከምናቸው የቴክኖሎጂ መሥሪያዎች ሌት ተቀን ልቅ የወሲብ ፊልም ሱሰኛ ያደረግን፣ ኃጥያተኛ ተገኘ ተብሎ ወገራ። ከእጅ አይሻል ዶማ እኮ ነው ይገርምሻል፤” ብሏት አረፍ ሲል፣ “እኮ እኛ ተንኮል፣ ምቀኝነት፣ ደባ፣ አላዋቂና ጨዋ ሆነን ተገኝተን የተንኮል ተማሪ ልንሆን?” ብላ ከት ብላ ሳቀች። ምናለበት ግን መንግሥት ‘ሪሞት ኮንትሮሉ ያለው በእጃችሁ እኔን ምን አድርግ ትሉኛላችሁ?’ ብሎ ቢገላግለን?!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ሁለም አጠገቡ አብሮት ከተቀመጠው የወንበር ደባሉ ጋር ይነጋገር ይዟል። ሁሉም የሦስተኛ ወገን ጨዋታ ይዞል። ራሱን የሚሔስ ራሱን የሚያዳምጥ ጠፋ። ይኼኔ በዝምታ ምስጥ ብለው የቆዩት ደርባባ ወይዘሮ፣ “መቼ ይሆን ሰበብ መደርደሩን ትተን እንደ ጥንታውያን ግብፆች ስማችንን የሚዘክር ጡብ መደርደር የምንጀምረው?” አሉ። “አልተከልንም እንዴ እማማ? አክሱም፣ ላሊበላ እ… …ፋሲል የእኛ አይደሉም እንዴ?” አላቸው ከጎኔ የተየመው ወጣት ለመጀመርያ ጊዜ ከፌስቡኩ ላይ ዓይኑን ነቅሎ። ወይዘሮዋም መለስ ብለው፣ “መቼ ይሆን ያለፈን ታሪክ ተደግፈን ማውራት የምናቆመው?” ሲሉ፣ “አቁመንማ መሰለኝ የህዳሴውን ግድብ ግማሽ ያደረስነው፤” አላቸው።

“ቆይ እስኪ አስጨርሳቸው አንተ” ሲለው ጎልማሳው በወንድማዊ ቁጣ ወይዘሮዋ “እኔስ ጨርሻለሁ ይብላኝ ለዘመኑ ሰው፡፡ የአባቴ ቀበቶ የእናቴ መቀነት እያለ መደናቀፉ ሳያንስ ቁስሉን እያመረቀዘ ተቀምጦ ለቀረው፤” ብለው በረጅሙ ተነፈሱ። “ሰው ማለት ማኅበራዊ እንስሳ ነው ይባል አይደል እንዴ? አንዱ ሲሠራ ሌላው እያፈረሰ አንዱ ሲተክል ሌላው እየነቀለ እንዴት እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን መሆን እንቻል ታዲያ?” ስትላቸው ቆንጂት፣ “የእኔ ልጅ የአንቺ ድርሻ የምትችያትን ጠጠር መወርወር ብቻ ነው። ሌላውን የሚዳኝ ይዳኘው። አለበለዚያ በመተማማት፣ በመሰዳደብ፣ በመወቃቀስ የት ይደረሳል? ከሥልጣን ሁሉ ትልቁ ሥልጣን ራስን መግዛት፣ ራስን ማሸነፍ ብቻ ነው። ችግሩ ሥልጣኑን የማያውቅ ባለሥልጣን መብዛቱ ነው፤” ሲሉ ወያላው “መጨረሻ” ብሎ አወረደን። እውነት ግን ከራስ በላይ ምን ሹመት አለ? አጉል ከመጓተት ሀቅን መረዳት ይሻላል፡፡ መልካም ጉዞ!  

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት