Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዙን ሲቀጥል በኢትዮጵያ ድርቅ ያስከተለው ጫና የዕድገት መሰላሉን እንዳዛባ ተመድ አመለከተ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከጥቂት ቀናት በፊት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዳዮች መሥሪያ ቤት ይፋ የተደረገው የዓለም የኢኮኖሚ ሁኔታ አመላካች ሪፖርት፣ የዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ይበልጥ ተዳክሞ መቀጠሉንና እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገሮችም በድርቅ ምክንያት ሲያስመዘግቡት የነበረው ኢኮኖሚያ ዕድገት መቀዛቀዙን አመለከተ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 አጋማሽ ዓመት ድረስ ስለነበረው የዓለም ኢኮኖሚያዊ ተርታ ሪፖርቱን ይፋ ያደረገው የተመድ መሥሪያ ቤት በተለይ በአፍሪካ ባለፈው ዓመት የታየው የሦስት ከመቶ አኅጉራዊ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ በዚህ ዓመት ከዚህም ቀንሶ ወደ 2.8 ከመቶ ዝቅ እንደሚል አስፍሯል፡፡ የዓለም ኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዙ እንደ አፍሪካ ያሉ ቀጣናዎች ጥገኛ በሆኑባቸው የሸቀጥ ምርቶች ላይ የሚታየው ዝቅተኛ ዋጋ ከየአገሮቹ የፊስካልና የከረንት አካውንት መዛባት እንዲሁም ከጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲዎች ጋር ተዳምረው የዓመቱን የዕድገት ትንበያ ወደታች እንዳወረደው ተመድ በሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

በዓለም ላይ ከሀቻምና ጀምሮ እየተቀዛቀዘና እየቀነሰ በመጣው የዓለም የሸቀጦች ዋጋ ምክንያት፣ የበርካታ አፍሪካ አገሮች የወጪ ንግድ በአሳሳቢ ሁኔታ እየወረደ ሲመጣ፣ በዚህ ሳቢያም በአንዳንድ አገሮች ላይ የመሠረተ ልማት አለመሟላት ችግሮች እንዲስፋፉ፣ የኃይል አቀርቦት እጥረት እንዲባባስ፣ የጤና ክብካቤ አገልግሎቶች እንዲስተጓጎሉ ማስገደዱን ተመድ አስታውቋል፡፡ በተለይ እንደ ናይጄሪያና ደቡብ አፍሪካ ባሉት አገሮች ውስጥ የኃይል አቅርቦት እጥረት እንዲባባስ ምክንያት መሆኑ ታይቷል፡፡

ይህ ክስተት ባለበት ወቅት፣ በዚምባቡዌ፣ በደቡብ አፍሪካ እንዲሁም በኢትዮጵያ ላይ በከፍተኛ መጠን በተከሰተው የድርቅ አደጋ ሳቢያም በአገሮቹ ሲመዘገብ የነበረው የኢኮኖሚ የዕድገት ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩ ተመልክቷል፡፡ አስከፊው ድርቅ ከኢትዮጵያ እስከ ሶማሊያ ያለውን የምሥራቅ አፍሪካ ክፍል ማዳረሱ ይህንን ዓመት ብቻም ሳይሆን በመጪው ዓመትም ሊኖር በሚችለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ አሳሳቢ ተፅዕኖ ማሳደሩን የተመድ ሪፖርት ይጠቁማል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ከሳምታት በፊት ይፋ የተደረገው የዓለም የገንዘብ ድርጅት ሪፖርት፣ በኢትዮጵያ የሚጠበቀውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወደ 4.5 ከመቶ ዝቅ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡ ከሰሐራ በታች በሚገኙ አገሮች ባለፉት 16 ዓመታት ውስጥ ከነበረው ይልቅ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ተመዝግቦበታል በተባለው በዚህ ዓመት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ የዓመቱ የዕድገት ምጣኔ ቀድሞ በመንግሥት ከተተነበየውም ዝቅ እንደሚል ይጠበቃል፡፡

የተመድ ሪፖርት በአፍሪካ አገሮች ለታየው ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ማገገሚያ መንግሥታቱ አዳዲስ የገቢ ምንጮችን እንዲያፈላልጉ ያሳስባል፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገሮች እ.ኤ.አ. በ2008 ከተከሰው የዓለም የፋይናንስና የኢኮኖሚ ቀውስ በኋላ በበርካታ የብድር ዕዳዎች ውስጥ ለመዘፈቅ እንደተገደዱ ያመለከተው ተመድ፣ ምንም እንኳ በወቅቱ ከዶላር ብድር ጋር በተያያዘ በነበረው ዝቅተኛ የወለድ መጠን ምክንያት ተጠቃሚ ለመሆን ቢችሉም፣ በአሁኑ ወቅት ያንሰራራው የዶላር ምንዛሪና የተፈጠረው ዝቅተኛ የሸቀጥ ገበያ ዋጋ ጫና ውስጥ እንደከተታቸው ጠቁሟል፡፡

በኢትዮጵያ ቡናን ጨምሮ ዋና ዋና የወጪ ንግድ ሸቀጦች ላይ የታየው የዓለም ዋጋ ቅናሽ በአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩም በዘጠኝ ወራት ውስጥ የተከናወኑ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ሪፖርቶች እያመለከቱ ይገኛሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች