Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ከ50 ከመቶ በላይ የመርከብ አገልግሎት ቅናሽ ማድረጉን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከተቋቋመ 52 ዓመታት ያስቆጠረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅትና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በአገሪቱ እያደገ የመጣውን የጭነት መጠን የማጓጓዝ አቅሙ እያደገ ቢመጣም፣ አሁንም ግን ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታይ አነስተኛውን የጭነት መጠን በማጓጓዝ ላይ ይገኛል፡፡

ይሁንና አስመጪዎች በዓለም የንግድ መድረክ በሚያከናውኑት የገቢ ንግድ ድርድር ወቅት መደራደር አቅማቸው ደካማ ከመሆኑም ባሻገር፣ ስለሚያስመጧቸው ሸቀጦች ያላቸው ቅድመ ጥናት እንዲሁም የዕቃዎቹን የጥራትና የደረጃ ልክነት ወዘተ. የሚያውቁበት አማራጭ ሥርዓት መፈተሽ ላይ ችግር እንደሚታይ ድርጅቱ ይገልጻል፡፡

ይህም ሆኖ ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ ለሚያጓጉዛቸው ጭነቶች አቅም በመገንባቱ በአሁኑ ወቅት የዕቃዎች አማካይ ቆይታ 7.5 ቀን ሊደርስ መቻሉንና ይህም ከዓለም አቀፉ የሰባት ቀናት አሠራር አኳያ ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ የመርከብ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ እንዳብራሩት፣ የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ መጠን እያደገ ቢመጣም አሁንም ከሌሎች አገሮች አኳያ ሲታይ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በጠቅላላው በአሁኑ ወቅት ባሉት መርኮች አማካይነት በአንድ ጊዜ ከ335 ሺሕ ቶን በላይ ጭነቶችን የማንሳት አቅም ላይ የሚገኘው ድርጅቱ፣ በዓለም አቀፍ ንግድ ላይ የአገሪቱ አስመጪዎች ያላቸው የድርድር አቅም አነስተኛ መሆን አገሪቱን ትልቅ ጫና ውስጥ እየከተተ እንደሚገኝ ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ ገልጸዋል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአብዛኛው አስመጪዎች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ለሚገዟቸው ዕቃዎች፣ ሻጮች ለተገዛው ዕቃ እስከሚጓጓበት ወደብ ድረስ ሊኖር የሚችለውን የመድን ዋስትና፣ የጭነትና የማጓጓዣ ወጪን (ኮስት ኢንሹራንስ ኤንድ ፍሬይት – CIF) እንዲሸፍኑ የሚያስችል ቢሆንም፣ ይህ አሠራር አገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ለማጣት እንድትገደድ ሲያደርጋት መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ አንደኛው የአስመጪዎች የመደራደር አቅም ብቃት ማነስ ሲሆን፣ ሌላኛውና ትልቁ ግን ለባንኮች የሚቀርቡ ፕሮፎርማዎችና ደረሰኞች የተዛቡና ግልጽነት የጎደላቸው ሆነው መታየታቸው ነው፡፡

በመሆኑም በፍሬይት ኦን ቦርድ (FOB) የሚደረግ ስምምነት ገዥውን ብቻም ሳይሆን አገርን የሚጠቅምበትን አሠራር አብራርተዋል፡፡ የFOB ተቃራኒ በሆነው በCIF አማካይነት በሚደረግ ስምምነት መሠረት የሚደርሰውን ጉዳት ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ ያብራሩት፣ ለባንኮች የሚቀርቡት የግዥ ሰነዶችና ደረሰኞች የሚጣሩበት ዕድል የሌለ በመሆኑ ጭምር ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንዲህ ያለው አሠራር እንዲስፋፋ በር በመክፈት የሚታሙት በአብዛኛው የግል የንግድ መርከቦች እንደሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡

የግል መርከቦች የሚያዘጋጁት የፕሮፎርማ ሰነድ በCIF መሠረት ሲሆን፣ ግልጽነት ስለሚጎድለው፣ ዕቃዎች በተጭበረበረ መንገድ እንዲገዙ ዕድሉን ስለሚሰጥበት መንገድ ሲያብራሩም፣ ባንኮች በ70 ወይም በመቶ ዶላር የሚገዛ ዕቃ በ120 ዶላር እንደሚገዛ በማስመሰል የሌተር ኦፍ ክሬዲት እንዲከፍቱላቸው በአስመጪው አካል ጥያቄ ይቀርብላቸዋል፡፡ ባንኮቹ ይህ ገንዘብ ተገዝቶ ለሚመጣው ዕቃ ትክክለኛው መጠን ስለመሆኑ የሚያጣሩበት ዕድል ስለሌላቸው የተጠየቁትን የውጭ ምንዛሪ ይሰጣሉ፡፡ ሻጩ አካል ወይም የግል ንግድ መርከቦች ሁለት ዓይነት ሰነድ በማዘጋጀት የተዛባውን ለገዥው፣ ትክክለኛውን ለራሳቸው በማስቀረት የሚሠሩበት አግባብ በሰፊው እንደሚታይ አብራርተዋል፡፡

ይህ ሁሉ ከዚህ ቀደም የአገሪቱ የገቢ ንግድ በሙሉ CIF በነበረበት ወቅት ያጋጥም የነበረ ችግር በመሆኑ፣ መንግሥት ዕቃዎች በFOB እንዲገዙ በማድረግ ከ1992 ዓ.ም. ወዲህ በዚህ የግዥ ሒደት እየተመራ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በአገልግሎት አሰጣጡም በአሁኑ ወቅት ዕቃዎች ለመጫን ዝግጁ ሆነው በቀረቡ ጊዜ በሰባት ቀን ተኩል በማንሳት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ በዋጋ ደረጃም ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በዋና ዋና ወደቦች አማካይነት ባለ20 ጫማ ኮንቴይነሮችን በባህር ትራንስፖርት ያጓጓዘበትን ታሪፍ ድርጅቱ ይፋ አድርጓል፡፡

የቀድሞው ንግድ መርከብ ድርጅት ብሔራዊ የመርከብ አገልግሎት ሰጪ አካል ሆኖ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ ሲቋቋም በወቅቱ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃነታቸውን የተቀዳጁበት ወቅት ነበር ያሉት ቺፍ ኢንጂነር፣ እነዚህ አገሮች የውጭ ንግድ ሥርዓታቸው በወቅቱ የነበሩትና Liner Conference የሚባሉት የመርከብ ባለቤቶች የፈጠሩት ካርቴል ሥር የወደቀ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ እንዳልወሰደባቸው ያብራራሉ፡፡

እነዚህ የመርከብ ኮንፈረንሶች በሚያወጡት የባህር ማጓጓዣ ዋጋ መሠረት መስተናገድና ክፍያ መፈጸም ግዴታ ስለነበር፣ ዋጋውም እጅግ ከፍተኛ ስለነበረ የአፍሪካ አገሮች የየራሳቸው መርከብ ለማቋቋም ተገደዋል፡፡ ጋና፣ ናይጄሪያና አይቮሪኮስት ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ተከትሎ በወቅቱ በግብፅና በእስራኤል መካከል የተካሄደውና የስድስቱ ቀን ጦርነት እየተባለ የሚጠራው ግጭት ያንዣበበት ጊዜ ስለነበር፣ ‹‹የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የመርከብ ድርጅት ማቋቋም አስቀድሞ የታሰበበት ነበር፡፡ በእርግጥም እ.ኤ.አ በ1967 በግብፅና እስራኤል ጦርነት በመቀስቀሱና የስዌዝ ካናል በመዘጋቱ በደቡብ አፍሪካ በመዞር የአገራችን የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ በማስቀጠል የማይተካና የማይረሳ አሻራ ጥሎ ማለፉ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፤›› በማለት ንግድ መርከብ ድርጅት በብሔራዊ ደረጃ እንዲመሠረት ያስገደደበትን ኢኮኖሚያዊና ታሪካዊ አስገዳጅ ምክንያቶችን ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ወቅት የበርካታ የአፍሪካ አገሮች የመርከብ ድርጅቶች በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮቻቸው ምክንያት ቀስ በቀስ እንቅስቃሴያቸውን ለማቆም እተገደዱ መምጣታቸውን፣ በአንፃሩ የኢትዮጵያ መርከብ አገልግሎት ግን ‹‹ጥሩ ቁመናና ጥንካሬ ይዞ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ብቸኛው ተቋም ነው፤›› ሲሉ ቺፍ ኢንጂነሩ አስታውቀዋል፡፡

ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ባለፉት ስድስት ዓመታት በስምንት የተመረጡ ዋና ዋና ወደቦች አማካይነት፣ ለባለ 20 ጫማ ኮንቴይነር ጭነት የባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየበትን ታሪፍና በስድስት ዓመታት ውስጥ በአማካይ በ54 ከመቶ ቅናሽ አደርጌያለሁ ያለበትን ዝርዝር መረጃ ለሪፖርተር በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2011 እስከ 2016 ባሉት ዓመታት ለባለ 20 ጫማ ኮንቴይነር ሲያስከፍልበት የነበረውን የታሪፍ መጠንና ለውጥ (በዶላር) ከዚህ በታች በተመለከተው ሰንጠረዥ አሳይቷል፡፡

ተ.ቁ.

ወደብ

2011

2012

2013

2014

2015

2016

የስድስት ዓመት አማካይ ቅናሽ (በመቶኛ)

1

ሻንጋይ

1700

1720

1440

1315

1055

791

47

2

ቲያንጂን

1700

1810

1630

1420

1140

950

56

3

ሲንጋፖር

1225

1500

1325

1335

1065

843

69

4

ፖርት ክላንግ

1475

1480

1430

1335

1095

899

61

5

ሐምቡርግ

1400

1250

1190

1225

1080

899

64

6

ጄኖዋ

1450

1660

1450

1265

1035

675

47

7

ሙምባይ

1275

1320

1175

1190

850

617

48

8

ጀበል አሊ

1050

990

960

900

600

470

45

አማካይ ለውጥ

54

 

 ምንጭ፡ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች