Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየኢትዮጵያና የኤርትራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ምን ፍሬ አፈራ?

የኢትዮጵያና የኤርትራ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ምን ፍሬ አፈራ?

ቀን:

በቃለአብ ወልደኪዳን

የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት በሁለት ሉዓላዊ አገሮች ውስጥ የሚካሄድን ግንኙነት ለማጠናከር የሚረዳ የዘመናዊ ዲፕሎማሲ አካል ነው፡፡ በተለይ አገሮች በግጭት ውስጥ ካሉ ሊያግባባቸው የሚችል አወዛጋቢ ጉዳይ ካለ ወይም የባለቤትነት ጥያቄም ሆነ የታሪክ ሽሚያ የሚታይበት መንግሥታዊ ፉክክር ከነገሠ፣ መፍትሔ አምጪው አንዱ መድረክ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከርና በሒደት ወደ መንግሥታትና ሥርዓት ደረጃ ማሳደግ ነው፡፡

በዚህ ረገድ በዓለም አቀፉ የሕዝብ ለሕዝብ መድረክ ተጠቃሽ የሆኑ ተሞክሮዎች እንዳሉም ይታወቃል፡፡ በቀዳሚነት የእስራኤልና የፍልስጤም ተሞክሮ ይጠቀሳል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1975 በአንድ ኖርዌጂያዊ ምሁር አነሳሽነት ግንኙነቱ ተጀምሮ የቀድሞው የእስራኤል መሪ ይስሃቅ ራቢንና የፍልስጤም ነፃ አውጪ ድርጅት መሪ የነበሩት ያሲን አራፋት የኦስሎ ስምምነትን ፈርመዋል፡፡ እንደ አገር ዕውቅና የመሰጣጣትና የሰላም ድርድሮችም የተጀመሩት ከዚያ በኋላ ነበር፡፡

- Advertisement -

ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ከወጡ በኋላ ለሁለት የተከፈሉት ህንድና ፓኪስታን ከሦስት ጊዜ ጦርነት በኋላ የጀመሩት የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትም በመስኩ ተጠቃሽ ተግባር ነው፡፡ በአፍሪካ የሩዋንዳና የብሩንዲ፣ ከእስያ የጃፓንና የቻይና ተሞክሮዎችም አብነቶች ናቸው፡፡

ወደ አገራችን ሁኔታ ስንመለስ ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በግብፅና በሱዳን በኩል ለሚነሱ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥያቄዎች የሕዝብ ዲፕሎማሲ (Public Diplomacy) አንዱ መፍትሔ ሆኗል፡፡ በዚህም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደረጃ ራሱን የቻለ ዳይሬክቶሬት ተቋቁሞለት፣ ሙያተኞች ተቀጥረውለት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ እንደ አገርም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የሚመራ የፖለቲከኞች፣ የምሁራን፣ የማኅበራት መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሥነ ጥበብና የመገናኛ ብዙኃን መሪዎች የተካተቱበት የሕዝብ ዲፕሎማሲ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል፡፡

ከዚያም አልፎ ቡድኑ ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ፕሬዚዳንት ጋር ተገናኝቶ በመምከር ግብፅና ሱዳን ተጉዞ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመወከል ምክክር አድርጓል፡፡ ከዓመት በፊት የግብፅን የሕዝብ ለሕዝብ ቡድን በቅርቡም የሱዳን ልዑካን በመቀበልም አዎንታዊ ግንኙነትና መተማመን መፍጠር ተችሏል፡፡

ከአሥራ ስምንት ዓመታት በፊት ጦርነት ውስጥ ገብተው ‹‹በሰላም የለም ጦርነት የለም›› ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያና ኤርትራ ግን በሕዝብ ለሕዝብ መስክ ያሳዩት ጥረት የለም፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የተቋቋመው ግብረ ኃይልም ስለ ኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡ እንዲያውም የዚህ ቡድን አባል የሆነ ምሁር ‹‹የኢትዮጵያና የኤርትራን የሕዝብ ለሕዝብ መጋረጃ በጥሶ ጠንከር ያለ የንቅናቄ ሥራ ለመሥራት መንግሥታት ያጡት ቁርጠኝነት ዋነኛ እንቅፋት ሆኗል፤›› ማለታቸው አይዘነጋኝም፡፡

ከዚህ ይልቅ መንግሥታዊ የሆነውና ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሆኑ የሚታወቀው ‹‹የኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት›› እያደረጋቸው ያሉ ሙከራዎች እንዳሉ ይሰማል፡፡

በተለይ ካለፉት አራትና አምስት ዓመታት ወዲህ ተቋሙ በኢትዮጵያ በኩል የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማቶች አመራረጥና ሽማግሌዎች መለየት ላይ ግልጽነት ያለው አሠራር፣ መድረኮች፣ ልዩ ልዩ ጥናቶችና ኅትመቶችን በመሥራት ላይ ነው፡፡ ስደተኞቹ የትምህርት ዕድል፣ አመቺ የሥራ ሁኔታና ወደፈለጉት አካባቢ የመጓዝ ዕድል እንዲያገኙም የመንግሥት ፖሊሲን እየተከተለ በመሥራት ላይ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ግን አሁን ጥያቄው ‹‹የኢትዮ-ኤርትራ ሕዝብ ለሕዝብ ጥረት ምን ፍሬ አፈራ!?›› የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ እውነት ለመናገርስ ከሁለቱ አገሮችና
ሕዝቦች የታሪክ፣ የባህል፣ የሃይማኖት፣ የቋንቋና የጂኦግራፊ ጠቀሜታ አንፃር ሲታይ የግብፅና የሱዳን በልጦና ቅድሚያ የሚሰጠው ሆኖ ነው የሰሜኑ የሕዝብ ለሕዝብ በር የተዘጋበት!? ነው ወይስ የኤርትራ መንግሥት በጀመረው መንገድ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዙንና ፀብ አጫሪነቱን ከቀጠለ ሳይወድ በግድ ራሱን ጠልፎ ስለሚጥል ችግሩ ይፈታል በሚል?

በእርግጥ የኤርትራ ሕዝብ አሁን በገጠመው የኑሮ ጣርና አፈና በስፋት እየተሰደደ ነው፡፡ ምሁራን፣ የአገርና የሃይማኖት ሽማግሌዎች እንዲሁም የተወሰኑ የአገሪቱ ተቆርቋሪ ፖለቲከኞችን ሻዕቢያ አስሯል፣ አሳድዷል፡፡ ያመቸውንም አሰቃይቶ ገድሏል፡፡ ቀደምት የግንባሩ ታጋዮች ላቀረቡት ሥልጣንን በሒደት ለሕዝብ የእናስረክብ ጥያቄ እንኳን በአጸፋው እስራትና አደገኛ ቅጣት ነው ያከለበት፡፡

በተለይ የኢሳያስ አፈወርቂ መራሹ የኤርትራ አምባገነናዊ አገዛዝ ይበልጡኑ በራሱ ግፊትና ጀብደኝነት ከአገራችን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቱ ይታወቃል፡፡ በተለይ ከ1990 እስከ 1993 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ የሁለት አገሮች ወጣቶች እልቂትና ከደሃ አገሮች ኢኮኖሚ አንፃር ከፍተኛ የሚባል ሀብት ለጦርነቱ ተማግዷል፡፡ በዚህም ምክንያት ሻዕቢያ ለከፍተኛ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተደርጓል፡፡

ከላይ እንደተገለጸው ለብዙዎች እስራትና ስደት መንስዔ ከሆነ የፖለቲካ ውዝግብ ባሻገር የሕዝብ ድምፅ ያሰሙ የነበሩ የግል ጋዜጦችም ተዘጉ፡፡ ጋዜጠኞችም እስካሁን ያሉበት ሁኔታ እንኳን አይታወቅም፡፡ በዜጋው ደጃፍና አደባባይ ሳይቀር የስለላና የጆሮ ጠቢዎች ትስስር በመዘርጋት ፍርኃትና አለመተማመን እንዲንሰራፋ መደረጉን፣ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሳይቀር የዘገቡት እውነት ነው፡፡

የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶችን የሚያነሱ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ በረሃ እስር ቤቶች ተግዘው ተቋሙ መዘጋቱ፣ ወጣቱ በብሔራዊ ግዳጅ ስም በወታደርነት ተጠምዶ መቆየቱ፣ የሥርዓቱ ቁንጮዎች ሙስና፣ ፈላጭና ቆራጭነትም ኤርትራዊያኑን በአገራቸው ባዳና ተሰዳጅ አድርጓቸዋል፡፡ በዚህም ለከፋና ትልቅ ስደት እንዳደረጋቸው ይታወቃል፡፡

መውጫ እንዳጣ ጭስ ባገኘው ክፍት ቦታ ሁሉ እየተሰደደ ያለው የኤርትራ ወጣትና አምራች ኃይል አምባገነናዊ ጭቆናውንና ምዝበራውን ሊቋቋመው ባለመቻሉ ነው፡፡ ያም ሆኖ ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው ሰፊ ፍልሰትና ስደት ‹‹የቸገረው እርጉዝ ያገባል›› የሚያስብል አይደለም፡፡ ምክንያቱም የሁለቱ አገሮች ሕዝቦች ከነበሯቸው የጋራ እሴቶችም በላይ በታሪክ አጋጣሚ በአንድ ሉዓላዊ ግዛት ሥር የነበሩና ክፉውንም ደጉንም በጋራ ያሳለፉ ነበሩ፡፡

እንዲያም ሆኖ በተለይ በአዲሱ የኤርትራ ትውልድ ላይ ላለፉት 25 ዓመታት ሲነዛ የኖረው ጥላቻና የበቀል ፕሮፓጋንዳ ሳይሟሽ፣ በመጠጋገንና በውሸት ሲገመድ የኖረው የአገራቱ የታሪክ ዳራና ፈለግ በሀቅና በጥናት ሳይዳሰስ፣ ከታሪክ ይልቅ ፖለቲካና ጦረኝነት ወሳኝ በነበሩበት ሁኔታ ቅልቅል የመሰለውን ስደትና የስደት ተቀባይነት ማስቀጠል አስቸጋሪ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ ምናልባት ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ከፖለቲካ ጫና ነፃ የሆነ አገርን ሊወክል የሚችል የሕዝብ ለሕዝብ ቡድንን በሁለቱም ወገን አቋቁሞ መሥራት ይሻል ነበር፡፡

በእርግጥ በአንድ እውነት መተማመን ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም፣ የኤርትራ ስደተኞችን ለማስተናገድና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱም እንዲሻሻል ከሻዕቢያ የተሻለ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህን ሁኔታ በተጨባጭ መገለጫዎች ማየት ይቻላል፡፡

በኤርትራው አመፀኛ አገዛዝ ውስጥ እንኳንስ የኢትዮጵያ ስደተኞች ሊኖሩ ይቅርና የራሱንም ዜጎች አላስቆም አላስቀምጥ ያለ ነው፡፡ ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ግን አንዳንዴ ከሕዝቡ ፍላጎትም ያለፈ የሚመስል ዕገዛና ድጋፍ ለኤርትራውያኑ በማድረግ ላይ ነው፡፡

ለአብነት ያህል የኤርትራ ስደተኞች በተለያዩ የሠፈራ ጣቢያዎች ማለትም ሽመልባ፣ ማይህይኒ፣ አዲሃሩሽ፣ አሳሂታ፣ በርሐለ በመቀበል እንደ ማንኛውም ስደተኛ እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡ የውኃ፣ የእንጨት፣ የመሬትና የጥበቃ አቅርቦት ያደርጋል፡፡

ኤርትራውያን ስደተኞች ግን ከሌሎች አገሮች ስደተኞች በተለየ የመንቀሳቀስ፣ የመሥራት፣ ከዘመድ አብሮ የመኖር መብቶችን ያገኛሉ፡፡ ለዚህም የሚጠቀሰው ዋነኛ ምክንያት በኤርትራ ካሉት ዘጠኝ ብሔረሰቦች አምስቱ (ትግረኛ፣ አፋር፣ ሳሆ፣ ብሌንና ኩናማ) ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉ የቅርብም ይሁን የሩቅ ዘመድ ስላላቸው ነው፡፡ ለነገሩ ከሃያ አምስት ዓመታት በፊትና ከዚያም በኋላ እስከ 1990 ዓ.ም. ድረስ እንደ አንድ አገር ሕዝብ በመኖራቸው ብቻና መወለድ አስተሳስሯቸው እንደነበር አይካድም፡፡

ኤርትራውያን ወጣቶች እንኳን ተሰደው በአገራቸው እንኳን ያላገኙት የከፍተኛ ደረጃ የትምህርት ዕድልም እንዲያገኙ በመፈቀዱ በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ወጣቶች ከመጀመርያ ዲግሪ እስከ ድኅረ ምረቃ በመላው አገሪቱ ይማራሉ፡፡ ሌላው ተጠቃሚነታቸው የሚገለጸው ደግሞ እስካሁን ወደ ኢትዮጵያ መሰደድ ከጀመሩ ከሃምሳ ሺሕ የሚበልጡ ኤርትራውያን ወደ ምዕራባውያን መልሶ ስደት አግኝተው መጓጓዛቸው ነው፡፡ ይህ በህንድ ውቅያኖስ በየበረሃው ተሰቃይተው እንኳ ከማያገኙት ዕድል አንፃር ሲታይ ትልቅ አማራጭ ሆኗቸዋል፡፡

በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ ቤት ንብረታቸውን ትተው ወደ ኤርትራ ተመልሰው የነበሩ ሰዎችም አዲስ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ይኸውም የዋስትና መብታቸውን በመጠበቅ በፈለጉት ጊዜና ሁኔታ ተመልሰው ንብረታቸውን እንዲረከቡና በወኪላቸው በኩል እንዲሸጡና እንዲለውጡ መፈቀዱ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ተግባር የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለኤርትራ ሕዝብ ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት በተግባር ያሳዩበት ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡

በሌላ በኩል ማንም በውጭ አገር የሚኖር ኤርትራዊ ኢትዮጵያ ውስጥ የፈለገውን ዓይነት ኢንቨስትመንት (እስከ ግሮሰሪና ሽሮ ቤት ድረስም ቢወርድ የሚከላከል አይመስለኝም) እንዲያደርግ ተፈቅዷል፡፡ ይህም ቢሆን በአገራቸው ሊያገኙት ያልቻሉትን የዜግነት መብት በኢትዮጵያ እንዲቋደሱ ተደርጓል፡፡

ለዚህም ነው በተለይ በአዲስ አበባ አንዳንድ ሠፈሮች የኤርትራ ስደተኞች በብዛት ከትመው የፈለጉትን እየሠሩ መኖር ከመቻላቸውም ባሻገር ‹‹እስመራ››፣ ‹‹አባ ሻውል›› ‹‹ደቀመሐሪ›› … ዓይነት የመንደርና የብሎክ ስሞች ዳግም እየተፈጠሩ ነው ያሉት፡፡

በተቃራኒው ሻዕቢያ አሁንም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በማጥላላት ላይ ተጠምዷል፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንን ማየትና ማንበብ ከመከልከል ባሻገር የአማርኛ ሙዚቃን እንኳን ሕዝብ ውስጥ ለውስጥ እየኮመኮመ ቢሆንም፡፡ አንድ የቅርብ ጊዜ የኤርትራ ስደተኛ፣ ‹‹የኤርትራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ወገኑ በመነጠሉ ብቻ ሳይሆን ሻዕቢያን ለመሰለ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ ተደርጎ ችግር ላይ በመውደቁ ክፉኛ የሚፀፀትበት ጊዜ አሁን ነው፤›› ብሏል፡፡

እንግዲህ በሁለቱ አገሮች በኩል ያሉት መንግሥታት ፖሊሲ ይህን ያህል የጎላ ልዩነት ያለው ቢሆንም፣ ሕዝቦቹ እንደ ሕዝብ ይበልጥ እንዲቀራረቡ እየተሠራ ያለው ሥራ ግን በቂ የሚባል አይደለም፡፡ በአንድ ወቅት በተለይ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ያለምንም የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ውህደት ከመሀል አገር ወደ ኤርትራ ብዙ ዜጎች እየተጋዙ እንደሚሰፍሩ፣ አሁንም ያለበቂ ትስስር ብዙ ኤርትራዊያ ወጣቶችን ወደ ኢትዮጵያ አስገብቶ ማስፈሩ ብቻ ትስስርን አይፈጥርም፡፡

እንዲያውም ሕዝብ ለሕዝብ ጠንከር ያለ መቀራረብ፣ ይቅር መባባል፣ ብሔራዊ ዕርቅና የአብሮነት መንፈስን የሚያመጡ ፖለቲካዊ ዕርምጃዎች አለመወሰዳቸው በኢትዮጵያውያኑ በኩል ‹‹ተመልሰው መጡብን፣ ኑሮ ውድነት አባባሱብን (በተለይ የኮንዶሚኒየም ቤት ኪራይ)፣ አንዳንዶቹ የኤርትራ መንግሥት መረጃ ሰዎች ቢሆኑስ? ሕገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው (ኮንትሮባንድ፣ ኢንተርኔት፣ ስልክ) መንግሥት ዝም አላቸው …›› ዓይነት ጥርጣሬን ይፈጥራል፡፡ ደግሞም እየፈጠረ ነው፡፡

በኤርትራ ስደተኞች በኩልም በመተማመንና ይበልጥ በመቀራረብ ከአገሬው ጋር አብሮ ከመኖር ይልቅ መጠራጠርና ‹‹የራስን ወገን›› ብቻ የመፈለግ ዝንባሌ ይታያል፡፡ አሁን ለሻይ ለቡናም ሆነ ለመኖር እንዳለው መሳሳብ ዓይነት፡፡ በሌላ በኩል ይፋዊ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር አለመደረጉም ኢትዮጵያን ለመሸጋገሪያ የመጠቀም እንጂ፣ በዘላቂነት ለመኖሪያ እንዳይመርጡት (በተለይ እዚህ ዘመድ የሌላቸው) እያደረጋቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም የጎረቤት አገሮች ሕዝቦች ጋር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር መሥራት አለባት፡፡ ታላቅ ሕዝብ ያላት በኢኮኖሚም እየተቀየረች ያለችና ስትራቴጂካዊ ቦታ የያዘችው ኢትዮጵየ ጉርብትናዋን በመንግሥታት ፖሊሲ ብቻ ቀይዳ ረዥም ርቀት መሄድ አይቻላትም፡፡ በተለይ ደግሞ በታሪክ አጋጣሚ በአንድ ባንዲራ፣ ድንበርና ሉዓላዊነት ሥር የኖሩት የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በትኩረት ሊታይ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ የሰላምና የልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት አጀማመርም በአንድ እግር እንደ መራመድ በመሆኑ፣ ሁሉን አቀፍ ጥረት በአዲስ መልክ ሊጀመር ይገባዋል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...