Sunday, June 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፒራሚድ ሽያጭ ስልት በመጠቀም የተጠረጠሩ ዋስትናቸው ወደ 100 ሺሕ ብር ከፍ ተደረገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንደተጣሰ በመግለጽ አቤቱታ አቀረቡ

በኢትዮጵያ ሕግ ዕግድ የተጣለበትን ወይም ክልከላ የተደረገበትን ‹‹ፒራሚድ የሽያጭ ስልት›› በመጠቀም፣ የግዙፉ የቻይናው ኩባንያ ቲያንስ ምርቶችን በማከፋፈልና በመሸጥ ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ፣ በ10 ሺሕ ብር ዋስ ተለቀው የነበሩት ተጠርጣሪዎች፣ የተፈቀደላቸውን የዋስትና መጠን በአሥር እጥፍ ከፍ በማድረግ የ100 ሺሕ ብር ዋስ እንዲያስይዙ ፍርድ ቤት ባስተላለፈው ትዕዛዝ ላይ አቤቱታ አቀረቡ፡፡

ቲያንስ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሚያስመጣቸውን የጤና መጠባበቂያ፣ መዋቢያና አጋዥ ምርቶችንና ዕቃዎችን በመቀበል፣ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ ሕጋዊ ፈቃድ በማውጣት በችርቻሮ የሚሸጡ ነጋዴዎች መሆናቸውን የሚናገሩት እነ ዶ/ር ኤርሚያስ መለስ፣ ከየካቲት 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሥራቸው ጋር በተገናኘ ተጠርጥረው መታሰራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ጉዳዩን የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ስምንተኛ ወንጀል የጊዜ ቀጠሮ ችሎት እያንዳንዳቸው በ10 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲለቀቁ መጋቢት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. መፍቃዱንና ከሳሻቸው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ፣ ዋስትናውን ተቃውሞ ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደርጎ መፅናቱን ገልጸዋል፡፡

በተፈቀደላቸው የ10 ሺሕ ብር ዋስትና ከእስር ተፈትተው እንዳሉ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ዓቃቤ ሕግ፣ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቂርቆስ ምደብ ወንጀል ችሎት የመሠረተው ክስ ደርሷቸው መቅረባቸውን እነ ዶ/ር ኤርሚያስ አስረድተዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ግን ቀደም ብሎ የተጠበቀላቸውን የ10 ሺሕ ብር ዋስትና በአሥር እጥፍ አሳድጎ 100 ሺሕ ብር ማድረጉ ገቢያቸውን ያላገናዘበ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆናቸውንና ቋሚ አድራሻ ያላቸው መሆኑን ከግምት ውስጥ ያላስገባ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸውን የሚጋፉ መሆኑን በመጠቆም ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አመልክተዋል፡፡ በመሆኑም የተሰማሩበትን አነስተኛ የሽያጭ ወኪል የንግድ ዘርፍና ያስመዘገቡትን የካፒታል አቅም በማየት ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት፣ የሥር ፍርድ ቤት የወሰነላቸውን የ10 ሺሕ ብር ዋስትና እንዲያፀናላቸው ጠይቀዋል፡፡

በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 685/2002 አንቀጽ 30(6) መሠረት ክልከላ የተጣለበትን ‹‹የፒራሚድ ሽያጭ ስልት›› ማለትም ‹‹… አንድ ሸማች አንድን የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት መግዛቱ ተጨማሪ ገንዘብ ወይም የዓይነት ጥቅም እንደሚያገኝ በመግለጽ፣ በሸማቹ አሻሻጭነት ከእሱ ቀጥሎ ሌሎች ሸማቾች የንግድ ዕቃውን ወይም አገልግሎቱን የሚገዙ ወይም መዋጮ የሚያደርጉ ከሆነ፣ በሸማቾቹ ቁጥር ልክ ተጨማሪ የገንዘብ ወይም የዓይነት ጥቅም እንደሚያገኙ…›› በመግለጽ በበርካታ ዜጎችና በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን፣ የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን በክሱ ጠቁሟል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የንግድ ሥርዓት ‹‹የፒራሚድ ንግድ›› ሕገወጥ መሆኑ እየታወቀ፣ ንግድ ሚኒስቴር ቲያንስ ኢትዮጵያ ለተባለ ኩባንያ እንዴት የንግድ ፈቃድ ሊሰጥ እንደቻለ ሚኒስትሩ አቶ ያዕቆብ ያላን መጠየቁ ይታወሳል፡፡ ሚኒስትሩ በበኩላቸው ለቲያንስ የተሰጠው ፈቃድ ‹‹የፒራሚድ ንግድ›› እንዲያከናውን አለመሆኑንና በኢትዮጵያ ንግድ ፈቃድ የወሰደው ሦስት የምርት ዓይነቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መሆኑን መግለጻቸውም አይዘነጋም፡፡ ለቲያንስ ኢትዮጵያ ሻይ ቅጠልና ዲተርጀንቶችን ለማስመጣት፣ እንዲሁም አልሚ ምግቦችን ለማስገባት እንደሆነ ጠቅሰው፣ ድርጅቱ በሦስተኛ ፈቃድ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች