በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቋቋመውን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤትን በዋና ዓቃቤ ሕግነት እንዲመሩ፣ የፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው አምባዬ ተሾሙ፡፡
የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ቀድሞ ለፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ ተሰጥተውት የነበሩት ሙሉ ኃላፊነትና ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በፍትሕ ሚኒስትርነት ያገለገሉትን አቶ ጌታቸው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግን እንዲመሩ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ዕጩ ሆነው ከቀረቡ በኋላ ምክር ቤቱ በሙሉ ድምፅ አፅድቆላቸዋል፡፡
በአዲሱ አዋጅ መሠረትም ጽሕፈት ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ነክ ሥራዎችን ሙሉ ለሙሉ ጠቅልሏል፡፡ ለሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ለንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ቀድሞ በአዋጅ የተሰጡዋቸው የዓቃቤ ሕግነት ሥራዎችን በብቸኝነት እንዲያስፈጽም መደረጉ ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መንግሥትን ወክሎ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች ይከሳል፣ ምርመራ ያደርጋል፣ ክስም እንዲቋረጥ ያደርጋል፡፡
ምንም እንኳ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በብዙ አገሮች የተለመደ አሠራርና የመንግሥት መዋቅር ሆኖ የሚያገለግል ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ መቋቋሙ ክርክር ተነስቶበት እንደነበር ይታወሳል፡፡