Thursday, October 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የአገር ባለውለታዎች በሕይወት እያሉ ይታወሱ!

  አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ አደባባዮች ሰንደቅ ዓላማዋ ከፍ ብሎ በተደጋጋሚ እንዲውለበለብ ካደረጉ ድንቅ ልጆቿ መካከል አንደኛው ሰሞኑን ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡ በተለያዩ ኦሊምፒኮችና የዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያን ወርቅ በወርቅ ያደረጉ ጀግኖች አትሌቶች ዋና አሠልጣኝ የነበሩት ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬን የኢትዮጵያ ሕዝብ በሐዘን ሸኝቷቸዋል፡፡ በአትሌቲክስ ስፖርት በአሠልጣኝነት ከፍተኛ ዝና የነበራቸውና በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ማኅበራት ፌዴሬሽን ጭምር ተሸላሚ የነበሩት እኚህ ታላቅ ሰው የአገር ባለውለታ ነበሩ፡፡ እኚህን ባለ ደማቅ ታሪክ የአገር ባለውለታ ባጣንበት በዚህ ወቅት በመሪር ሐዘን ውስጥ ሆነን፣ የአገር ባለውለታዎችን ጉዳይ እያነሳን እንነጋገራለን፡፡

  ኢትዮጵያ በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው የዜግነት ድርሻቸውን በሚገባ የተወጡ በርካታ ዜጎችን ያፈራች አገር ናት፡፡ አገርን ከጠላት በመጠበቅ፣ በግብርና፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በሕግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በንግድ፣ በስፖርት፣ በኪነ ጥበብ፣ በሥነ ጽሑፍ፣ ወዘተ የሚያኮሩ ተግባራት የፈጸሙ የአገር ባለውለታወች በተለያዩ ዘመናት ታይተዋል፡፡ በመንግሥታዊ አገልግሎትና በዲፕሎማሲ አገር ያኮሩ ባለውለታዎችም ነበሩ፡፡ ዛሬም አሉ፡፡ እነዚህን የአገር ባለውለታዎች ዕድሜያቸው ሲገፋ፣ ሲታመሙ፣ ሲቸገሩ፣ ጧሪ ሲያጡና ጎዳና ላይ ሲወድቁ የሚታደጋቸው ማን ነው? በሕይወት እያሉ የአገር ባለውለታነታቸው እየተዘነጋ ለመከራና ለእንግልት ሲዳረጉ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ በረሃብና በእርዛት ምክንያት ተጎሳቁለው ሕይወታቸው ያለፈውን ቤት ይቁጠረው ከማለት ውጪ ምንም ማለት አይቻልም፡፡

  በሌላ በኩል በተለያዩ መስኮች የዜግነት ግዴታቸውን በአኩሪ ስኬት የተወጡ የአገር ባለውለታዎች የሚታወሱት ወይ ታመው አልጋ ሲይዙ፣ ወይም ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ ነው፡፡ አገር ለባለውለታ ዜጎቿ በሕይወት እያሉ ዕውቅና መስጠት ያለባት፣ ወጣቱ ትውልድ በእነዚህ ወገኖች አርዓያነት ለአገሩ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማነቃቃት ነው፡፡ የአገር አንጋፋ ባለውለታዎች ሲዘነጉ ተከታዩ ትውልድም ተስፋ ይቆርጣል፡፡ ለባለውለታዎች ዕውቅና ለመስጠት በሕግ ማዕቀፍ የሚመራ የሜዳሊያና የኒሻን፣ በአገልግሎት ዘመን መጠን የሚበረከት ሽልማትና የምሥጋና ሥነ ሥርዓት ሊኖር ይገባል፡፡ አገርን በፍቅር ማገልግል የውዴታ ግዴታ ቢሆንም፣ አስመሥጋኝ ተግባር ላከናወኑ አኩሪ ዜጎች ዕውቅና መስጠት የአገር ባህል መሆን አለበት፡፡

  በሕዝቡ ዘንድ በአርዓያነታቸውና በተምሳሌትነታቸው ስማቸው ጎልቶ የሚነሳ ዜጎች በስማቸው መንገድ፣ አደባባይ፣ ትምህርት ቤት፣ ሆስፒታል፣ ስታዲየም፣ ወዘተ ቢሰየም ወጣቶች ለአገራቸው ሽንጣቸውን ገትረው እንዲሠሩ ያበረታታቸዋል፡፡ የአገር ባለውለታዎችን በአኩሪ ተግባሮቻቸው ምክንያት ዕውቅና መስጠት ሲገባ፣ ለችግር ሲዳረጉ እንዳላዩ ማለፍ አሳዛኝ ነው፡፡ መልካም ተግባር ፈጽመዋል ለተባሉ ባዕዳን ሐውልት እየቆመና ዕውቅና እየተሰጠ የአገር ባለውለታዎችን እንደ ተራ ነገር ማየት ሊቆም ይገባል፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ የክልል ከተሞች መንገዶችንና አደባባዮችን፣ የትምህርትና የጤና ተቋማትን የመሳሰሉትን በሕዝብ ዘንድ ከበሬታ ላላቸው የአገር ባለውለታዎች መሰየም ትልቅ እርካታ ይፈጥራል፡፡ እነዚህ የአገር ባለውለታዎች እየተበሳጩና እየተብከነከኑ ከዚህ ዓለም በሞት ከሚለዩ ይልቅ፣ ደስ ብሏቸው በአገራቸውና በወገኖቻቸው እየኮሩ ቢያልፉ እረፍት ይሰጣል፡፡

  በመንግሥታዊም ሆነ በግል ተቋማት ውስጥ የሚፈለግባቸውን አገልግሎት አበርክተው በጡረታ የሚሰናበቱ ዜጎች ጭምር ዕውቅና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በመኖሪያ ቀዬአቸው ውስጥ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎችና መናፈሻዎች ባለመኖራቸው ምክንያት የጡረታ ዘመናቸውን የሚያማርሩ ዜጎች በርካቶች ናቸው፡፡ በአነስተኛ ጡረታ ሁልጊዜ ካፌ ለመስተናገድ አቅም የሌላቸው እነዚህ ዜጎች መጻሕፍት የሚያነቡባቸው፣ ከዕድሜ እኩዮቻቸው ጋር የሚያወጉባቸው፣ የቤት ውስጥ ጨዋታዎችን የሚጫወቱባቸውና አካላቸውን የሚያንቀሳቅሱባቸው ሥፍራዎች ባለመኖራቸው ምክንያት ሲቸገሩ ይታያሉ፡፡ አገሩን አገልግሎ ጡረታ የወጣ ዜጋ የሚንከባበው መንግሥትና ማኅበረሰብ ሲያጣ የሕይወት ዘመኑ ያስጠላዋል፡፡ እነዚህን ዜጎች ጭምር ታሳቢ ያደረገ የልማት መርሐ ግብር መኖር ሲገባው እነሱ ግን ተዘንግተዋል፡፡ እነዚህን ወገኖች ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

  በአጠቃላይ ዜጎች በወጣትነትና በጎልማሳነት ዘመናቸው አገራቸውን የማገልገል የውዴታ ግዴታ አለባቸው፡፡ ‹‹ለአገሬ ምን ማድረግ አለብኝ እንጂ አገሬ ምን አደረገችልኝ አይባልም›› እንደሚባለው ለአገር ያለስስት መስዋዕት መሆን ቢገባም፣ የአገር ባለውለታዎችን ማሰብ ጥቅሙ ለአገር ነው፡፡ የአገር ባለውለታዎች በሕይወት እያሉ ስማቸው ሲወሳ፣ ሲሸለሙ፣ በሜዳሊያና በኒሻን ሲደምቁ፣ በስሞቻቸው መታሰቢያ ሲደረግ፣ በእስተርጅና ዕድሜያቸው እንክብካቤ ሲደረግላቸው፣ ወዘተ ወጣቱ ትውልድ እኔም ለአገሬ ብሎ ይነሳል፡፡ ተምሳሌት እንደሆኑ የአገር ባለውለታዎች ለየት ያለ አኩሪ ተግባር ለማከናወን ይተጋል፡፡ የአገር ባለውለታዎች ሲዘነጉና በየጎዳናው ሲወድቁ፣ ጠያቂ አጥተው በሕመም ሲማቅቁ፣ በረሃብና በእርዛት መከራ ሲያዩ ግን የወጣቱ ትውልድ ሞራል ይላሽቃል፡፡ የአገር ባለውለታዎቻችንን በሕይወት እያሉ ዕውቅና እንስጣቸው! መታሰቢያ እናድርግላቸው! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

  በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ በርካታ ሰዎች ወደ ከተማዋ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ገለጹ

  ‹‹የኦሮሚያ ክልል መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳውቀናል›› የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ‹‹ጉዳዩ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ንግግሩን ለማስጀመር ያቀረበውን ጥሪ መንግስት ተቀበለ

  የአፍሪካ ሕብረት በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል የሰላም ንግግር እንዲጀመር...

  የሰብዓዊ መብት ሪፖርቶች ውዝግብ በኢትዮጵያ

  ሰኔ 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማ...

  የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና አባል የክልል ንግድ ምክር ቤቶች ተቋማዊ ጤንነት ሲፈተሽ

  የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የኢትዮጵያን የንግድ ኅብረተሰብ...