Sunday, March 3, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የቀድሞ ኃላፊ የአሥር ዓመት ጽኑ እስራትና የገንዘብ መቀጮ ተወሰነባቸው

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት የቀድሞ ኃላፊ የአሥር ዓመት ጽኑ እስራትና የገንዘብ መቀጮ ተወሰነባቸው

ቀን:

በከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መሥሪያ ቤት የቀድሞ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ የነበሩት አቶ ወልደ ሥላሴ ወልደ ሚካኤል፣ በአሥር ዓመት ጽኑ እስራትና 50 ሺሕ ብር እንዲቀጡ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ግንቦት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ውሳኔ ሰጠ፡፡

ከኃላፊው ጋር ተከሰው የነበሩት ወንድማቸው አቶ ዘርዓይ ወልደ ሚካኤል አራት ዓመት ጽኑ እስራትና 20 ሺሕ ብር እንዲቀጡ የተወሰነ ሲሆን፣ እህታቸው ወ/ሪት ትርሀስ ወልደ ሚካኤል ሦስት ዓመት ከሦስት ወራት ጽኑ እስራትና በ10 ሺሕ ብር እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን 11 ክሶች ሲመረምር የከረመው ፍርድ ቤቱ፣ ሚያዝያ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በዋለው ችሎት አቶ ወልደ ሥላሴን በሰባት ክሶች፣ አቶ ዘርዓይን በሁለት ክሶችና ወ/ሪት ትርሀስን በአንድ ክስ ጥፋተኛ ማለቱ ይታወሳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

አቶ ወልደ ሥላሴ ጥፋተኛ የተባሉት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መሥሪያ ቤት ዋና መምርያ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኃላፊ ሆነው ሲሠሩ፣ ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም ‹‹Terrorism in Ethiopia and the Horn of Africa›› የሚል መጽሐፍ ማሳተማቸውን ፍርድ ቤቱ በቅጣቱ ላይ ጠቁሟል፡፡ በመሆኑም በመሥሪያ ቤታቸው ውስጥ ያላቸው ኃላፊነት ማማከር ሆኖ እያለ ከዚህ ውጪ የማማከር ኃላፊነታቸውን ያላግባብ በመገልገል፣ የመሥሪያ ቤቱን የሰው ኃይል ሠራተኛ መጽሐፋቸውን ለማሳተም የስፖንሰር ትብብር እንዲደረግላቸው የትብብር ደብዳቤ ማጻፋቸውን በቅጣት ውሳኔው ተገልጿል፡፡ በተጻፈው የትብብር ደብዳቤ አማካይነት በወቅቱ የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ዋና ሥራ አስኪያጅ ለነበሩት አቶ በየነ ገብረ መስቀል መጽሐፉ በግላቸው እንዲታተም መሥሪያ ቤታቸው መስማማቱን ገልጸውላቸው መጽሐፉ እንዲታተምላቸው በማድረግ፣ 600 ሺሕ ብር ሕገወጥ ገቢ በማግኘታቸው ጥፋተኛ መባላቸው ተገልጿል፡፡

አቶ ወልደ ሥላሴ ሌላው ጥፋተኛ የተባሉበት ወንጀል ወይዘሮ ግርማነሽ ይኩኖ አምላከ ወይም ሩት የተባሉ ግለሰብ፣ ለግል ጉዳያቸው ሲንቀሳቀሱ የመሥሪያ ቤቱን መኪና ነዳጅ እየሞሉና የመሥሪያ ቤቱን ሾፌር አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረጋቸው ነው፡፡ ግለሰቧ በፍርድ ቤት የነበራቸውን ጉዳይ የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች እንዲያስፈጽሙ ማድረጋቸውንም ጠቁሟል፡፡ አቶ ወልደ ሥላሴ ለሚሠሩት ቤት የጣሊያን ሴራሚክ እንዲገዙላቸው ታዋቂውን ነጋዴ አቶ ሳቢር አርጋውን በማዘዝ፣ የ65 ሺሕ ብር ሴራሚክ አስገዝተዋል ተብለው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ አቶ ወልደ ሥላሴ ከ2001 ዓ.ም. እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ ያሳተሙትን መጽሐፍ የሸጡ ቢሆንም፣ ለግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት አሳውቀው መክፈል የነበረባቸውን 496,159 ብር የትርፍ ገቢ ግብር ባለመክፈላቸውም ጥፋተኛ መባላቸውን የቅጣት ውሳኔው በችሎት ሲነገር ተጠቅሷል፡፡ ከግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ካገኙት የኪራይ ገቢ መክፈል የነበረባቸውን ተርን ኦቨር ታክስ ባለመክፈላቸውም ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡

አቶ ወልደ ሥላሴ ሦስት ክሶች ተጣምረው ጥፋተኛ ያሰኟቸው ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም መጽሐፍ በማሳተም ከሽያጩ 600 ሺሕ ብር በማግኘታቸው፣ የ65 ሺሕ ብር ሴራሚክ በማስገዛት የማይገባ ጥቅም በማግኘታቸው፣ 496,159 ብር ግብር ባለመክፈላቸው፣ ከኪራይ ገቢ ካገኙት ተርን ኦቨር ታክስ ባለመክፈላቸውና ከተጠቀሱት ወንጀሎች ያገኙትን ገንዘብ ከሕጋዊ ገንዘባቸው ጋር በመቀላቀል በባንክ የዝውውር ምኅዋር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ተጨማሪ ጥቅም ላይ በማዋላቸው መሆኑን፣ የቅጣት ውሳኔው በዝርዝር ያስረዳል፡፡

አቶ ዘርዓይ ጥፋተኛ የተባሉት በሁለት ክሶች ሲሆን፣ ከ2005 ዓ.ም. በኋላ ከቤት ኪራይ (የአቶ ወልደ ሥላሴን ቤት በማከራየት) ከተገኘ ገቢ ላይ ተርን ኦቨር ታክስ አሳውቀው ባለመክፈላቸውና ከአቶ ወልደ ሥላሴ ሙሉ ውክልና ከተቀበሉ በኋላ ከእሳቸው ሒሳብ ላይ 700 ሺሕ ብር ወደ ራሳቸው ሒሳብ እንዲተላለፍ በማድረግ፣ ገንዘቡ በተለያዩ ባንኮች እንዲንቀሳቀስ በማድረግ፣ ገንዘቡ የተገኘበትን ሕገወጥ ምንጭ ለመደበቅ ተሳትፈዋል በማለት መሆኑን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ወ/ሪት ትርሀስ ደግሞ ጥፋተኛ የተባሉት ከአቶ ወልደ ሥላሴ ጋር የብድር ውል በማዘጋጀት 350 ሺሕ ብር በማስተላለፍና ከሜጋ አሳታሚና ማከፋፈያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሁለት ቼኮች ለአቶ ወልደ ሥላሴ የተጻፈን 399,920 ብር ለእሳቸው እንዲከፈል በማድረጋቸው ነው፡፡ አቶ ወልደ ሥላሴ በወንጀል ያገኙትን ገንዘብ ከራሳቸው ሕጋዊ ገንዘብ ጋር በመቀላቀል ለመርዳትና ገንዘቡ የተገኘበትን ሕገወጥ ምንጭ ለመደበቅ በመሳተፋቸው መሆኑ ፍርድ ቤቱ አብራርቷል፡፡

እንደ ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔ አገላለጽ፣ ሦስቱም ተከሳሾች የተጠቀሱባቸው የወንጀል ሕጐች በራሳቸው ከባድ በመሆናቸው፣ ዓቃቤ ሕግ ተፈጽሟል የተባለው የወንጀል ደረጃ ከፍተኛ እንዲሆን ያቀረበውን ጥያቄ አልተቀበለውም፡፡ የወንጀል ደረጃውንም ዝቅተኛ በማድረግ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን ጥያቄ መቀበሉን ፍርድ ቤቱ አሳውቋል፡፡

የቅጣት ማቅለያን በሚመለከት አቶ ወልደ ሥላሴ ቀደም ባሉት ጊዜያት ምንም ዓይነት ወንጀል ስለመፈጸማቸው በዓቃቤ ሕግ በኩል የቀረበባቸው ማስረጃ ባለመቅረቡ የነበራቸው ባህሪ መልካም እንደሆነ ተደርጐ ስለሚታሰብ፣ እንደ አንድ የቅጣት ማቅለያ መያዙን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ ከ1972 ዓ.ም. እስከ 1983 ዓ.ም. ሕወሓትን በመቀላቀል የደርግ ሥርዓትን ለመታገል በተደረገው ፍልሚያ ውስጥ በመሳተፍ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን፣ ከ1983 ዓ.ም. በኋላም በተለያዩ ኃላፊነቶች ለአገሪቱ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንና አራት መጻሕፍትን በማሳተም በተለይ የሽብርተኝነትን ጐጂነት ኅብረተሰቡ ማወቅ ስላለበት ነገር ከማሳወቃቸውም በላይ፣ በተለያዩ ጊዜያት ሥልጠና በመስጠት ከፍተኛ ተሳትፎ በማድረጋቸውም በሁለተኛ የቅጣት ማቅለያነት እንደተያዘላቸው ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

በሦስተኛ የቅጣት ማቅለያነት የተያዘላቸው የቤተሰብ አስተዳዳሪና ኃላፊ መሆናቸው በማስረጃ በማረጋገጣቸው መሆኑ ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡ በመሆኑም አቶ ወልደ ሥላሴ ጥፋተኛ በተባሉባቸው ሰባት ክሶች የተጣለባቸው ቅጣት ሲደመር 31 ዓመት እስርና የገንዘብ መቀጮውም 79 ሺሕ ብር የነበረ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የእስራት ቅጣት ጣሪያ 25 ዓመት በመሆኑ፣ 31 ዓመታት የሆነው ቅጣት ወደ 25 ዓመት ዝቅ ተደርጐ በተያዘላቸው ሦስት የቅጣት ማቅለያ በእያንዳንዱ ሦስት እርከን፣ በድምሩ ዘጠኝ እርከን ተቀንሶላቸው አሥር ዓመት ጽኑ እስራት 50 ሺሕ ብር እንዲቀጡ በሙሉ ድምፅ መወሰኑን ፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡

አቶ ዘርዓይ መልካም ባህሪ እንደነበራቸውና የቤተሰብ ኃላፊና አስተዳዳሪ መሆናቸው በመረጋገጡ፣ የሚጥል ሕመም እንዳለባቸው ማስረጃ በማቅረባቸውና ከ1976 ዓ.ም. ጀምሮ በሕወሓትና በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ በመሆን እስከ 1999 ዓ.ም. ድረስ ማገልገላቸው በማስረጃ በመረጋገጡ፣ አራት የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸውና እያንዳንዱ የቅጣት ማቅለያ ሦስት እርከን፣ በድምሩ 12 እርከን ተቀንሶላቸው፣ ለመነሻነት ከተያዘው 12 ዓመት እስርና 32 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት ተቀንሶላቸው፣ አራት ዓመት ጽኑ እስራትና 20,000 ብር እንዲቀጡ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ መሰጠቱን ፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡

ወ/ሪት ትርሀስም ሁለት የቅጣት ማቅለያ ተይዞላቸው ለመነሻ ቅጣት ከተያዘው ዘጠኝ ዓመትና 30 ሺሕ ብር ቅጣት ተቀንሶላቸው፣ በሦስት ዓመት ከሦስት ወራት ጽኑ እስራትና 10 ሺሕ ብር እንዲቀጡ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ መሰጠቱን ፍርድ ቤቱ በማስታወቅ መዝገቡን ዘግቷል፡፡ ከእነ አቶ ወልደ ሥላሴ ጋር ክስ ተመሥርቶባቸው እንዲከላከሉ ከተደረጉ በኋላ፣ በብቃት መከላከላቸው ተገልጾ በነፃ ስለተሰናበቱት የአቶ ወልደ ሥላሴ የቅርብ ጓደኛ መሆናቸው ስለሚነገረው አቶ ዶሪ ከበደ መዘገባችን ይታወሳል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...