Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹የሐዘን ቀን››

‹‹የሐዘን ቀን››

ቀን:

አገር በአንድ የሚያዘንባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በእነዚህ አጋጣሚዎች ብሔራዊ ሐዘን ቀን ይታወጃል፤ ሰንደቅ ዓላማም ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ይደረጋል፡፡ ይህንንና ሌሎችም ተያያዥ ነገሮች የአገር የሕዝብ የጋራ ሐዘንን መግለጫዎች ተደርገው ይታያሉ፡፡ ብሔራዊ የሐዘን ቀን የሚታወጀው መሪዎች ሲሞቱ፣ ዜጎች በተለያየ ምክንያት ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ዕልቂት ሲደርስና በሌሎችም ተመሳሳይ አጋጣሚዎች ሊሆን ይችላል፡፡ አገሮች ብሔራዊ የሐዘን ቀን እወጃንና ተከታይ ሥርዓቶችን በሚመለከት የተለያዩ ሕጋዊ መሠረትንና ደንብን ይከተላሉ፡፡ ይህ በአንድ አገር ከሥርዓት ሥርዓት ሊለያይም የሚችል ነው፡፡ ለምሳሌ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን (1923-1967) ብሔራዊ የሐዘን ቀንን የሚመለከት አዋጅ ነበር፡፡

በ1950ዎቹ በንጉሣውያን ቤተሰቦችና ከፍተኛ ሹማምንት ላይ ሐዘን ሲደርስ የሐዘኑ ዜና የሚነገረው ሰባት ጊዜ መድፍ ተተኩሶ ነበር፡፡ በ1949 ዓ.ም. የልዑል መኰንን ኃይለ ሥላሴ ዜና ዕረፍትን ተከትሎ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ታውጆ ነበር፡፡ በዚህም ሴቶች ጥቁር የሐዘን ልብስ ለብሰው፣ የሐዘን ሽርጥም አሸርጠው ነበር፡፡ ወንዶች ደግሞ በግራ ክንዳቸው የሐዘን ምልክት ጥቁር ቱቢት አድርገው፣ ጥቁር ከረባትም አሥረው ነበር፡፡ የጦር ሠራዊትና የክብር ዘበኛ የፖሊስ መኮንኖች ደግሞ የሐዘን ምልክት ከክንዳቸው ላይ አኑረው ነበር፡፡

የቀብር ሥነ ሥርዓት ሲፈጸምም የማርሽ ባንድ አባላት የሐዘን ምልክት ሲያደርጉ ተመሳሳይ ምልክት የሙዚቃ መሣሪያቸውም ላይ አድርገው ነበር፡፡ ሐዘን በአደባባይ ሲገለጽም ሐዘን ገላጮች ሠልፍ ይዘው በተራ ነበር፡፡ በተለያዩ መጻሕፍት ላይ እንደተቀመጠው፣ የሐዘን ቀን ተብለው በታወጁት ቀናት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚለዋወጧቸው ደብዳቤዎች፣ ኤንቨሎፖችና ወረቀቶች ሁሉ በጥቁር የተከፈፉ ነበሩ፡፡ ቴአትርና ሲኒማ ቤቶች ቴአትርና ፊልም አያሳዩም፣ በሬዲዮም ዘፈን አይለቀቅም ነበር፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የ28 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የቡርኪና ፋሶው የሆቴል ጥቃት፣ 86 የሚሆኑ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡበት የቱርኩ ባቡር ጣቢያ ጥቃት፣ የፈረንሳዩ ቻርሊ ሔክዶና ሌሎችም በቅርቡ አገሮች ብሔራዊ የሐዘን ቀን ያወጁባቸው አስከፊ አጋጣሚዎች ናቸው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው አገሮች የሐዘን ቀንን እወጃ በመገናኛ ብዙኃን ከመንገር ጀምሮ ዜናው በማን ይነገር? እንዴት ይነገር፣ የሕዝብ አገልግሎቶች በሚሰጥባቸው አካባቢዎች እንቅስቃሴዎች ምን ይምሰሉ? አለባበስ የሚሉና ሌሎች ጉዳዮችን እንደ የሕግና ደንባቸው በግልጽ ያስቀምጣሉ፡፡

በዚህም ብሔራዊ የሐዘን ቀኖች ሲታወጁ በአደባባዮች፣ በመዝናኛዎች በመንግሥት ተቋማት የሚኖሩ እንቅስቃሴዎች ወጥ እና የተቀመጠውን ነገር የተከተሉ ይሆናሉ፡፡ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ሥራም እንዳይኖርና ምንም ዓይነት የመዝናኛ ፕሮግራሞች እንዳይካሄዱ በሬድዮም ምንም ዓይነት ሙዚቃ እንዳይለቀቅ ዜጎችም በሐዘን ቀናት ደማቅ ቀለም ያላቸውን ልብሶች እንዳይለብሱ የሚያደርጉ አገሮች አሉ፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት በጋምቤላ የደረሰውን ቀውስ ተከትሎ መንግሥት የሁለት ቀን ብሔራዊ የሐዘን ቀን አውጆ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ብሎም በሊቢያ የኢትዮጵያውያንን በአይኤስ መገደልን፣ እንዲሁም በደቡብ አፍሪካ የሦስት ኢትዮጵያውያን የዘረኝነት ጭፍጨፋ ሰለባ መሆንን ተከትሎ መንግሥት የሦስት ቀን ብሔራዊ ሐዘን ቀን አውጆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ከዚያም በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኅልፈትን ተከትሎ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ታውጆ ነበር፡፡

እንደ እነዚህ ባሉ አጋጣሚዎች ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሲታወጅ በተቋማት መደረግ ያለበት ምንድነው? የመገናኛ ብዙኃንስ ፕሮግራሞች ምን መምሰል አለባቸውና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮችን በሚመለከት በግልጽ የተቀመጠ ነገር አለ ወይ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡

የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ የሐዘን ቀን እወጃን በሚመለከት ይህ ነው የሚባል አዋጅ የለም፡፡ ስለዚህም ነገሮች ወጥነት የጎደላቸውና የሚጋጩ ሁሉ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሲታወጅ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሁለት አንቀጾች የሰንደቅ ዓላማ አዋጅ (በብሔራዊ ሐዘን ቀን ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንደሚውለበለብ የሚገልጸው አንቀጽ) እና ከኃላፊነት የተነሱ የአገርና የመንግሥት መሪዎች፣ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የምክር ቤት አባላትና ዳኞች መብቶችና ጥቅሞችን በሚመለከተው አዋጅ የሚገኙ ናቸው፡፡

ሁለተኛው አዋጅ እንደሚያስቀምጠው፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዜና ዕረፍት መነገር ያለበት በዜና አንባቢ ወይም ጋዜጠኛ ሳይሆን በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ነው፡፡ ቢሆንም ግን የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዜና ዕረፍት የተነገረው በጋዜጠኛ መሆኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡

ራሱን በቻለ ብሔራዊ የሐዘን ቀንን በሚመለከት አዋጅ እንኳ ባይሆንም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዜና ኅልፈት በማን ይነገር የሚለው በግልፅ የተቀመጠ ሆኖ ሳለም እንደዚህ ስህተት ሊፈጠር መቻሉ አንድ ነገር ሲሆን፤ የብሔራዊ ሐዘን ቀን እወጃን በሚመለከት ወጥና ዝርዝር ጉዳዮች የተመለከቱበት ሰነድ አለመኖር የተለያዩ ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ይችላል፡፡

የብሔራዊ ሐዘን ቀን እወጃን ተከትሎ መደረግ ያለባቸው፣ የሌለባቸው ነገሮች ምንድናቸው? የሚለው ቀዳሚው ጥያቄ ይሆናል፡፡ እንደዚህ ያሉ ነገሮች በግልፅ ተቀምጠው ብሔራዊ የሐዘን ቀን አገር በአንድ ላይ የሚያዝንበት፣ ሐዘኑን የሚያሳይበት ካልሆነ የሐዘን ቀን ብሎ ማወጁ ፋይዳ ምንድነው? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ለምንድነው የሚታወጀው? ማን ነው የሚያዝነውና ሌሎችም ጥያቄዎች ይከተላሉ፡፡

በተለያዩ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ቦታዎች የብሔራዊ የሐዘን ቀን መታወጅ ተከትሎን ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን ለማየት የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ተዘዋውረን ጠይቀናል፡፡ ምንም እንኳ እኩል ብሔራዊ የሐዘን ቀን የታወጀባቸው ቢሆንም፣ አንዳንዶች ከአንዱ ለአንዱ የተሻለ ትኩረት ሰጥተው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ብዙም ስሜት ሳይሰጣቸው ያለፈ ብሔራዊ የሐዘን ቀን እንደነበር የገለጹልን አሉ፡፡ የግድ ሁሉ ሰው ይሰማው ይዘን ማለት ባይቻልም፣ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ተብሎ እስከታወጀ ድረስ ሰዎች በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች፣ የመንገድ ላይ አገልግሎት የሐዘን ቀን መሆኑን የሚያስታውሱ ነገሮች እንዲኖሩ ሊሆን ይችላል፡፡ የሐዘን ቀን መሆኑን የሚያስታውሱ ነገሮች እንዲኖሩ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ አያከራክርም፡፡ በሌላ በኩል ኮሙዩኒኬሽኑ ከየትኛው የመንግሥት አካል ነው የሚመጣው የሚለው ላይ ግልፅ የሆነ ነገር ባይኖርም፣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በሙስሊሙ ማኅበረሰብም ብሔራዊ የሐዘን ቀኖች በጸሎት ታስበው ይውላሉ፡፡

በሬስቶራንቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ ታክሲ ላይና በመሳሰሉት ብሔራዊ የሐዘን ቀን በታወጀባቸው ቀናት የሚኖረው ነገር በባለቤቶች መልካም ፈቃድ፣ በደንበኞች፣ በአስተናጋጆች ኃላፊ ወይም በዲጄዎች ስሜትና መግባባት የሚወሰን ነው፡፡ ታክሲ ላይም እንደ አሽከርካሪው ለመረጃ ቅርብ መሆንና ለጉዳዩ ክብደት መስጠት ይወሰናል፡፡ ስለዚህ ይህ ማለት የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ከማወጅ ጋር የሚሄዱ ነገሮች ሲንፀባረቁ በሌላ ወገን እንደ ጭፈራና ዳንኪራ ያሉ ነገሮችም ይስተዋላሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ የብሔራዊ የሐዘን ቀን እወጃ ምን ያህል ትርጉም ይኖረዋል የሚል ጥያቄ የሚያነሱ አሉ፡፡

ያነጋገርናቸው የሬስቶራንቶችና ካፍቴሪያ ኃላፊዎች እንደገለጹልን፣ ብሔራዊ የሐዘን ቀን መታወጁን እንደሰሙ የሚለቀቁ ሙዚቃዎች በመሣሪያ ብቻ የተቀነባበሩ እንዲሆኑ እንደሚያደርጉ፤ ነገር ግን ነገሩን ከገበያ ጋር በማያያዝ ቤታቸው እንዳይቀዘቅዝ የሚፈልጉ ባለቤቶች ውሳኔያቸውን የሚቃወሙበት አጋጣሚ እንዳለም ይገልጻሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሙዚቃ እንደማንኛውም ቀን ሲለቀቅ ቅሬታ የሚያሰሙ እስከ ፀብ የሚደርሱ ተስተናጋጆችም አሉ፡፡ የሙዚቃ ድምፅ ከመቀነስ ውጭ የሚለቀቁ ሙዚቃዎች ከሐዘን ጋር የሚሔዱ (በመሣሪያ የተቀነባበሩ) ሆኑ አልሆኑ ብለው እንደማይጨነቁና እንደማያደርጉ የገለጹልንም አሉ፡፡ ሰዎች ባር ላይ መቀመጥን እስከመረጡ ድረስ ከሌላው ቀን በተለየ መልኩ ሙዚቃ ለመምረጥም ለመቀነስም እንደማይሞከር የገለጹልንም ሬስቶራንቶች አሉ፡፡

በቅርቡ በጋምቤላ የደረሰውን የዜጎች ግድያና እገታ ተከትሎ በታወጀው ብሔራዊ የሐዘን ቀን የነበረውን ነገር ስትገልጽ፣ ብዙም ከሌላው ጊዜ የተለየ ነገር እንዳላስተዋለች ቦሌ በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ ዲጄ የሆነችው ትርሲት አሸናፊ ትናገራለች፡፡ እሷም የባለቤቶች ፍላጎት ነገሮችን ይወስናል በሚለው ሐሳብ በመስማማት እንደ ቀኑ (ብሔራዊ የሐዘን ቀን) እንሁን የሚለው ነገር ከባለቤቱ ካልመጣ አስቸጋሪ እንደሆነ ትገልጻለች፡፡

ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ከመደረጉ በስተቀር በትምህርት ቤቶች ያለው ነገርም የተለያየ ነው፡፡ በአንድ የግል ትምህርት ቤት ውስጥ መምህር የሆነችው ሽግግር ዳንኤል እንደምትለው፣ እሷ በምታስተምርበት ትምህርት ቤት ጠዋት ሠልፍ ላይ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ሲደረግ፣ እዚያው ሠልፍ ላይ ኋላም በሚኒሚዲያ የሐዘን ቀን የታወጀበት ምክንያት ይነገራል፡፡ ታች ክፍል ላሉ እንኳ ሊረዱት በሚችሉት መልክ ስለ ዕለቱ የተወሰነ ነገር ይነገራል፡፡

በሌላ በኩል የሐዘን ምልክትና መግለጫ ይሆን ዘንድ ተማሪዎች ክንዳቸው ላይ ሪባን ወይም ባጅ እንዲያደርጉ የሚያደርጉ ትምህርት ቤቶችም አሉ፡፡ በተቃራኒው ስለ ዕለቱ ጨርሶ ምንም ሳይባል የሚታለፍባቸው ትምህርት ቤቶች ቁጥርም ጥቂት አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ወጥነት መጉደልና ብሔራዊ የሐዘን ቀን ተብሎ በታወጀበት ዕለት እዚህና እዚያ የሆኑ ነገሮች መታየት ብሔራዊ የሐዘን ቀን ምን መምሰል አለበት? ምን መደረግ፣ አለመደረግስ አለበት? የሚለው ባለመታወቁና በግልፅ ባለመቀመጡ ነው፡፡

የብሔራዊ የሐዘን ቀን ማኅበራዊ አንድምታ ላይ ጥናት የሠሩ ምሁራን እንደሚሉት፣ የብሔራዊ ሐዘን ቀን እወጃ መሠረቱ ፖለቲካ ሲሆን ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ረገድም አስተዋጽኦው ቀላል አይደለም፡፡ ይህ ግን ብሔራዊ የሐዘን ቀን ስለታወጀ ብቻ ሳይሆን ምንድነው? ምን ይደረጋልና አይደረግም የሚሉ ነገሮች በግልፅ ተቀምጠው ነገሮች በዚህ መሠረት ሲመሩ ነው፡፡

ቴአትር ቤቶች ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሲታወጅ ፕሮግራሞቻቸውን የሚሰርዙ ቢሆንም፣ በብሔራዊ የሐዘን ቀን ቴአትር ለመመልከት ከቴአትር ቤት ጎራ የሚሉ ግን ጥቂቶች እንዳልሆኑ ተረድተናል፡፡ በሲኒማ ቤቶች በኩል ያለው ነገርም ከዚህ የተለየ አይሆንም፡፡

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሰነዶች ማረጋገጫ ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ እስማኤል መሐመድ እንደሚሉት፣ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሲታወጅ የተለየ ሥነ ሥርዓት ባይደረግም ጸሎት ይኖራል፡፡ ሐዘን ወይም ሌላ ችግር ካለ ክፉው ወደ መልካም እንዲቀየር ጸሎት ይደረጋል፡፡ በተመሳሳይ ለሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ተነግሮ የሐዘን ቀን እንደታወጀበት ምክንያት የፍትሐት ጸሎት አልያም የምህላ ጸሎት እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የብዙሃን መገናኛ ድርጅት ኃላፊ መምህር ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል ይናገራሉ፡፡ በሊቢያው ሰማዕት እንደሆኑት ኢትዮጵያውያን ወይም የመሪዎች ሞትን ተከትሎ ብሔራዊ የሐዘን ቀን ሲታወጅ ደግሞ ልዩ ሥነ ሥርዓት ይደረጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...