በግቢው ቅጠል እንኳን ቢወድቅ የሚሰማ የሚመስል ዓይነት ፀጥታ ሰፍኗል፡፡ ግቢው ውስጥ ባለ አንድ ሰፊ ክፍል ጥቂት ሰዎች በተመስጦ ይቀመጣሉ፡፡ እጃቸውን ያነባበሩት እግራቸው ላይ በማድረግ ነው፡፡ የልብ ምታቸውን ሳይቀር እስከማዳመጥ በሚያስችል ተመስጦ ውስጥ እነደሚገቡ ቦታው ላይ የተገኙ ይናገራሉ፡፡ እርስ በርስ አይነጋገሩም፡፡ ሲንቀሳቀሱም በፍፁም እርጋታ ነው፡፡ ስልክ፣ መጽሐፍ፣ ሌሎችም ነገሮችን መጠቀም ስለማይቻል ከራስ ጋር ከመሆን ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ በዚህ ፀጥታ ውስጥ በዚህ መንገድ ለአሥር ቀናት መቆየትም ይጠበቃል፡፡
ይህ የሚስተዋለው ቪፓሳና የተባለ የሜዲቴሽን ቴክኒክ ለመተግበር ሞጆ ውስጥ በከተሙ ሰዎች ነው፡፡ ሰዎቹ በፍፁም ተመስጦ ሆነው ለመቆየት ወደ አካባቢው ያመሩ ሲሆኑ፣ በዚህ መንገድ ብዙዎች ሜዲቴት አድርገዋል፡፡ ሜዲቴሽንን የሕይወታቸው አካል ለማድረግም እንደ አጋጣሚ የወሰዱትም አሉ፡፡
ሜዲቴሽንን በተለያየ መንገድ የሚጀምሩ አሉ፡፡ ተሞክሯቸውን ካካፈሉን አንዱ ከሃያ ዓመታት በፊት ደብረዘይት ከተማ ውስጥ በሚገኝ አንድ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ‹‹ዮጋ›› የሚል መጽሐፍ ያገኝና መግቢያው ስላስደሰተው ከቆመበት ሳይንቀሳቀስ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ምዕራፍ አጠናቀቀ፡፡ በዮጋ ጽንሰ ሐሳብ ስለተደነቀም ለመሞከር ወሰነ፡፡ በመጽሐፉ እየተመራ በየቀኑ ለተወሰነ ሰዓት ከሰው ተገልሎ ዮጋ መሥራቱን ተያያዘው፡፡ ስለሜዲቴሽን ማንበብና ሜዲቴት ማድረግ የጀመረውም በዛው ወቅት ነበር፡፡
መላኩ በላይ (ስሙ ተቀይሯል) ከዛን ጊዜ ጀምሮ ዘወትር ሜዲቴት ያደርጋል፡፡ በአንድ ወቅት ቦሌ አካባቢ ብራማ ኩማሪስ በተሰኘ የሜዲቴሽን ማዕከል ውስጥ ሜዲቴት አድርጓል፡፡ አሁን በብዛት ሜዲቴት የሚያደርገው በግሉ ሲሆን፣ ጊዜና ቦታ አይወስነውም፡፡ ‹‹ሜዲቴሽን አእምሮን አካልንም ያክማል፡፡ በዚህ ሩጫ በበዛበት ዓለም ለመንፈስና ልቦና የሚሰጠው ጊዜ አነስተኛ ስለሆነ ሜዲቴሽን ያሻል፤›› ይላል፡፡
ሜዲቴሽን ለራሱ፣ ለሰዎችና ለአካባቢው ያለው አመለካከት ቀና እንዲሆን እንዳደረገው ይናገራል፡፡ ሜዲቴሽን ሰውን ለሰዎች የሚያስብ፣ ማንም ላይ ጉዳት የማያደርስ፣ ለሰዎች ችግር መፍትሔ የሚያፈላልግና ሁሉን የሚወድ ሰው የማድረግ አቅም እንዳለው ያስረዳል፡፡ ሜዲቴት የሚያደርጉ ሰዎች ስለራሳቸው ማንነት ተገንዝበው አካባቢያቸውንም የሚረዱና በበጎ መንፈስ የተሞሉ እንደሆኑ እምነቱ ነው፡፡
መላኩ የቅርብ ከሚላቸው ሰዎች ውጪ ለማንኛውም ሰው ሜዲቴት እንደሚያደርግ አይናገርም፡፡ ምክንያቱም ሜዲቴሽን ግላዊ የሆነ ተሞክሮ እንደሆነ ያምናል፡፡ ብዙዎች ሜዲቴሽን ከሰው ባህሪ ውጪ ያለ ጽንሰ ሐሳብ ቢመስላቸውም፣ ሜዲቴሽን ሰዋዊ ባህሪ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ሰዎች በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴያቸው ወይም በሃይማኖታቸው ያሉ ሕግጋትን በመከተል ተመስጦ ውስጥ ይገባሉ፡፡ ተመስጦ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የተያያዘ በመሆኑ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ዘወትር ይተገበራል፡፡ የሜዲቴሽንን ጽንሰ ሐሳብ ተገንዝቦ በመደበኛ ሁኔታ ማካሄድ ደግሞ የተመስጦን ጠቀሜታ ያጐላዋል፡፡
ሐሳቡን በሜዲቴሽን ውስጥ ያሉ ሰዎች እንዲሁም ተመራማሪዎችም ይጋራሉ፡፡ ሜዲቴሽን (ተመስጦ) ለሰው ልጅ አእምሯዊና አካላዊ ጤንነት እንደሚሰጥ ይስማሙበታል፡፡ ከጥንት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ሜዲቴሽን፣ አእምሮን ነፃ ከማድረግና ቀልብን ከመሰብሰብ ጋር ይገናኛል፡፡ ለራሳቸው የጥሞና ጊዜ ሰጥተው በግላቸው ወይም ከሌሎች ጋር ሜዲቴት የሚያደርጉም ብዙዎች ናቸው፡፡ ሜዲቴሽን ፍቅር፣ ርኅራኄና መልካምነትን ያበረታታል፡፡ ሜዲቴት የሚያደርግ ሰው በተረጋጋ መንፈስ ነገሮችን የማየትና አቅሙን በተሻለ የመጠቀም ብቃት እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
በተለይም በሩቅ ምሥራቅ አገሮች በስፋት የሚዘወተረው ሜዲቴሽን፣ ዛሬ በዓለም ላይ የብዙዎች የአኗኗር ምርጫ ሆኗል፡፡ በተለያየ ዘርፍ ስኬታማ ከሆኑ ሰዎች መካከል ሜዲቴሽንን የሚተገብሩም ጥቂት አይደሉም፡፡ ቢል ጌትስ፣ ስቲቪ ወንደር፣ አርኖልድ ሸዋዚንገር፣ ዊል ስሚዝና ታይገር ውድስን መጥቀስ ይቻላል፡፡ በሜዲቴሽን የዓለማችን ፈላስፋዎችና ታላላቅ ጸሐፍትም ይነሳሉ፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ሜዲቴሽን የምን ያህል ሰዎች አኗኗር ዘይቤ ነው? ስለሜዲቴሽን ምን ዓይነት ግንዛቤ አለ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ይቻላል፡፡ በእርግጥ ሜዲቴሽንን የሕይወታቸው አካል ያደረጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ የመጣ ይመስላል፡፡ ሥልጠና በመስጠትና የሜዲቴሽን ቦታ በማመቻቸት ረገድ የሚሠሩም አሉ፡፡ እንደ ክሁል ሆሊስቲክ ዴቨሎፕመንት ሴንተርና ደሃማ ያሉትን ተቋሞች መጥቀስ ይቻላል፡፡ መላኩ እንደሚለው፣ እንደ ሊዮናርዶ ዳቪንቺና ማይክል አንጀሎ ያሉ ጠቢባን የጥሞና ጊዜ እንደነበራቸው ሁሉ በኢትዮጵያውያን ባህልና ሃይማኖትም ተመስጦ ይስተዋላል፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው የሱርማ ማኅበረሰብ ዘወትር ከከሰዓት በአካባቢያቸው ባለ ጥላ ቦታ ላይ ለሰዓታት በጥሞና መቀመጣቸውን ነው፡፡ ሜዲቴት የሚያደርግ ሰው ለሰዎችም እፎይታ ይሰጣል፤›› ሲል ይገልጻል፡፡
በአገራችን በሜዲቴሽን ያለው እንቅስቃሴ አበረታች ቢሆንም ጽንሰ ሐሳቡን ከሃይማኖት ጋር በማያያዝ የማይቀበሉትም እንዳሉ በዘርፉ ያሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ ‹‹ብዙዎች ሜዲቴሽንን ከሃይማኖት ጋር ስለሚያያይዙት ለመቀበል ይቸገራሉ፡፡ ሜዲቴሽን ግን የየትኛውም ሃይማኖት አይደለም፡፡ ሰዎች ይህንን በመገንዘብና ከሜዲቴሽን የሚገኘውን ጥቅም በማወቅ ቢተገብሩት መልካም ነው፤›› የምትለው ደግሞ ማርታ ንጉሤ ናት፡፡
በእሷ እይታ ሜዲቴሽን መልካምነትን ከማዳበሩ በተጨማሪ ማኅበራዊ ግንኙነትን ቀላል ያደርጋል፡፡ የየትኛውም ሃይማኖት ተከታዮች ሜዲቴት ማድረግ እንደሚችሉም ታስረዳለች፡፡ ሜዲቴሽን ውስጥ ያሉ ቴክኒኮችን በተለያዩ ሃይማኖቶች ማግኘት ቢቻልም፣ ሜዲቴሽንን በአንድ ሃይማኖት ለመገደብ እንደሚያስቸግር ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ክርስትናና እስልምናን ጨምሮ ሌሎችም ሃይማኖቶች ጽሞና፣ ተመስጦና አርምሞን ይተገብራሉ፡፡
ማርታ ሜዲቴሽን ከጀመረች ሰባት ዓመት ሆኗታል፡፡ ሜዲቴሽን የአኗኗር ዘይቤን እንደሚለውጥ አንዲት ጓደኛዋ ስትነግራት እንደ ቁም ነገር አልወሰደችውም ነበር፡፡ ቢሆንም ጓደኛዋ ደሃማ የተሰኘው ተቋም የሚሰጠውን የቪፓሳና ሜዲቴሽን (ቪፓሳና ሜዲቴሽን ጐታማ ቡድሀ የተሰኙ ህንዳዊን አስተምሮ የተመረኮዘ ሲሆን፣ ነገሮችን በጥሞና መገንዘብ ላይ ያተኩራል፡፡) ሥልጠና እንድትወስድ አደረገቻት፡፡ ሥልጠናውን ከወሰደች በኋላ በአመለካከቷና አኗኗሯ ለውጥ ስላስተዋለች ሜዲቴሽን ቀጠለች፡፡
ሜዲቴት ማድረግ ከጀመረች በኋላ ከአመጋገቧ ጀምሮ በርካታ ነገሮች በሕይወቷ እንደተለወጡ ትናገራለች፡፡ ዘወትር ማለዳ አንድ ሰዓት ቤቷ ውስጥ ሜዲቴት ታደርጋለች፡፡ በሳምንት አንድ ቀን ሜዲቴት የሚያደርጉ ጓደኞቿን ጋብዛ በኅብረት ሜዲቴት ያደርጋሉ፡፡ ማርታ ቬጂቴሪያን ስትሆን መጠጥ አትጠጣም፡፡ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ትረዳለች፡፡ በየሆስፒታሉ በመዞር ህሙማንን ትጠይቃለች፡፡ ‹‹በሕይወቴ ባለኝ ነገር ሁሉ ደስተኛ ነኝ፡፡ ነገሮችን ቀለል አድርጌ አያለሁ፡፡ ከሰዎች ጋር አልጋጭም፡፡ ሆኖም አኗኗሬ ትክክል እንዳልሆነ የሚነግሩኝ ሰዎች አሉ፤›› ትላለች፡፡ ነገሮችን ቀለል አድርጋ መመልከቷና ለሁሉም ነገር ቀና ምላሽ መስጠቷ ጤናማ እንዳልሆነ የሚያስቡ ሰዎች ይተቿታል፡፡ ሜዲቴሽን እንድታቆም የመከሯትም እንደነበሩ ትናገራለች፡፡
ሜዲቴሽን የአኗኗር ዘይቤ እንደመሆኑ ማንኛውም ሰው በምርጫው የሚያደርገው ነው፡፡ የተለያየ ዓይነት የሜዲቴሽን ቴክኒክ በመጠቀም ሕይወታቸውን የሚመሩ ቢኖሩም፣ አብዛኛው ማኅበረሰብ እየተገለገለበት እንዳልሆነ የምትናገረው ማርታ፣ ሰዎች ጥቅሙን ተረድተውና መርጠውት ሜዲቴት እንዲያደርጉ የሜዲቴሽን ማዕከሎች ቢበራከቱ መልካም ነው ትላለች፡፡ በአገር ደረጃ ከጭንቀትና የተለያዩ ሱሶች ብዙዎችን ለማውጣት የሚጠቀሙበት አገሮችን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ፣ በአገራችንም የብዙዎች አኗኗር ምርጫ ቢሆን ማኅበረሰባዊ ለውጥ ሊመጣ ይችላል ስትል እምነቷን ትገልጻለች፡፡
ማርታ የቪፓሳና ሜዲቴሽን ሥልጠና ከወሰደች በኋላ ሌሎችም የሚሠለጥኑበትን መንገድ ታመቻቻለች፤ ያሠለጠናትን ተቋምም ትደግፋለች፡፡ ተቋሙ የበጐ ፈቃደኞች ሲሆን፣ ደሀማ በሚለው ዌብ ሳይት ሜዲቴት ማድረግ የሚፈልጉ ሰዎችን በመመዝገብ የአሥር ቀን ሥልጠና ይሰጣሉ፡፡ ሥልጠናው የሚካሄደው ሞጆ ሲሆን፣ ሠልጣኞች ለአሥር ቀናት ስልካቸውን ያጠፋሉ፤ እርስ በእርስም አይነጋገሩም፡፡ አገልግሎቱ የሚሰጠው በነፃ ነው፡፡
ማትያስ ክፍሌ (ስሙ ተቀይሯል) ሥልጠናውን ከወሰዱ አንዱ ነው፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ነበር ኦን ላየን ተመዝግቦ ለሥልጠና ወደ ሞጆ ያመራው፡፡ በመጀመሪያ ወደ 20 ለሚደርሱ ሠልጣኞች ስለሜዲቴሽን ቴክኒክ ገለጻ ተደረገላቸው፡፡ ከዛም ዘወትር ጠዋት እየተነሱ ወደ ሜዲቴሽን አዳራሽ ይገባሉ፡፡ ረዘም ላለ ጊዜ ሜዲቴት ካደረጉ በኋላ እረፍት ወስደው ይመገባሉ፡፡ የሚመገቡት አትክልት ነክ ምግቦች ብቻ ሲሆን፣ ሜዲቴት ከማድረግ ውጪ ሌላ እንቅስቃሴ አያደርጉም፡፡ ‹‹መረጃ በፍጥነት መለዋወጥ ተለምዶ ከስልክና ንግግር መቆጠብ ቢከብድም ከጥቂት ቀናት በኋላ ይለመዳል፤›› ይላል ማትያስ፡፡
በሥልጠናው ወቅት ትንፋሽ ሲገባና ሲወጣ ከማስተዋል አንስቶ አእምሮና ሰውነትን የመሰብሰብ ትምህርት ወስዷል፡፡ ብሪዚንግ ሜዲቴሽን ወይም የትንፋሽ ሜዲቴሽን በቀላሉ የሚሠራ ሆኖ ጥቅሙ የጐላ ነው፡፡ ለማትያስ የመጀመሪያዎቹ ቀናት ቀላል ባይሆኑለትም ቀስ በቀስ እየለመደው ሄዷል፡፡ ከአሥር ቀን ቆይታ በኋላ ነገሮችን በትዕግስት ማለፍና በሕይወት ቦታ ሊሰጣቸው ስለሚገቡ ነገሮች ተምሯል፡፡ ሜዲቴሽን ሰዎች ነገሮችን የሚያዩበትን መንገድ ቀና እንደሚያደርግና መረጋጋት እንደሚሰጥም ይናገራል፡፡ ዘወትር መሯሯጥ ሳይሆን ሰከን ብሎ አካባቢን ማስተዋል ከሜዲቴሽን ውጤቶች አንዱ ነው፡፡
ከሥልጠናው በኋላ ለተወሰኑ ወራት በመደበኛነት ሜዲቴት ቢያደርግም አልቀጠለም፡፡ አሁን አልፎ አልፎ ካልሆነ ሜዲቴት አያደርግም፡፡ ያስፈልገኛል ብሎ በሚያምንበት ወቅት ግን በእግሩ እየሄደም ቢሆን (ኪንሂን ሜዲቴሽን) ያደርጋል፡፡ ሜዲቴሽንን በአንድ ቦታ ወይም በተወሰነ የሰውነት አኳኋን ማድረግ ግዴታ አይደለም፡፡ ጊዜ ወስደው፣ ፀጥ ያለ ቦታ መርጠው፣ እግራቸውን አጣምረውና ለሜዲቴሽን የሚያስፈልጉ ነገሮችን በሙሉ አሟልተው ሜዲቴት የሚያደርጉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል በግርግር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም ቀልባቸውን ሰብስበው ሜዲቴት የሚያደርጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በተለያዩ አገሮች ሙሉ ሕይወታቸውን በሜዲቴሽንና ተያያዥ ሁነቶች ብቻ ለማሳለፍ ተገልለው የሚኖሩ ሰዎችም አሉ፡፡
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ ሜዲቴሽን የተለያዩ በሽታዎችን ለመከላከል ያገለግላል፡፡ እንደ ማይግሬን፣ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ልብ፣ ስትሮክ፣ አስምና አልዛይመር ላሉ በሽታዎች ተጋላጭነትን ይቀንሳል፡፡ ጭንቀትና ድብርት እንደሚያስወግድም የሥነ ልቦና ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡ ሜዲቴሽን በሳይኮቴራፒ ይተገበራል፡፡ የአእምሮን ጡንቻ በማፍታታትና ሰውነትን ዘና በማድረግ ለሕክምና ይውላል፡፡ ሰው መውደድና ደግነት፣ በጐ አድራጊነትና ችግሮችን በቀላሉ የመፍታት ልምድን ያዳብራል፡፡ የሜዲቴሽን ጽንሰ ሐሳብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደተለያዩ አገሮች ሲስፋፋ ልዩ ልዩ ቴክኖችም አብረው ዳብረዋል፡፡
በአገራችን የተለያዩ የሜዲቴሽን ቴክኒኮች ሥልጠና ከሚሰጡበት ተቋም አንዱ ወሎ ሰፈር የሚገኘው ክሁል ሆሊስቲክ ዴቨሎፕመንት ሴንትር ነው፡፡ የማዕከሉ መሥራች፣ ሥራ አስኪያጅና አሠልጣኝ ዮፍታሔ ማንያዘዋል (ሃፒ)፣ ማዕከሉ ማኅበረሰባዊ ግንባታ ላይ እንደሚሠራ ይናገራል፡፡ እሱ ከልጅነቱ ጀምሮ ዮጋ በመሥራትና ሜዲቴት በማድረግ ውስጥ አድጓል፡፡ ስለእነዚህ የአኗኗር ዘዬዎች ሥልጠናም ይሰጣል፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያን ወክሎ በዩናይትድ ኔሽንስ የኦልተርኔቲቭ ሜዲስን ስብሰባ ተከፍሏል፡፡ እንደ ሜዲቴሽንና ዮጋ ያሉ መንገዶችን ለተለያዩ በሽታዎች እንደ አማራጭ መድኃኒት በመውሰድ ላይ ውይይት ተደርጐ ነበር፡፡
በዘርፉ ያሉ አሠልጣኞችና ሜዲቴሽንን የሚተገብሩ ሰዎች ውስን ቢሆኑም፣ ስለለሜዲቴሽን ያለው አመለካከት እየተለወጠ መምጣቱ ተስፋ ሰጪ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ‹‹ሜዲቴሽን የሚያስደስተኝ የሕይወት ዘዬ ነው፡፡ በኢትዮጵያ መጤ እንደሆነ ቢታሰብም በኢትዮጵያ ታሪክ ያለ ነው፡፡ እንደ ዘርአያዕቆብ ያሉ ታላላቅ ፈላስፋዎች የፍልስፍና ክህሎትን ያገኙት ከተመስጦ ነው፤›› ይላል፡፡ ሜዲቴሽን በኢትዮጵያውያን በተለያየ መንገድም ቢሆን ይተገበር እንደነበረም ያክላል፡፡
‹‹የሰው ልጆች ለአካላችን የምናደርጋቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም ለአእምሯችን የሚሆን ነገር አንሰጠውም፡፡ ሜዲቴሽን ዘወትር አእምሮን በማደስ የአኗኗር ለውጥ ያመጣል፤›› በማለት ይገልጻል ዮፍታሔ፡፡ ሰዎች በግል ሕይወታቸው ከሚያገኙት ጥቅም ባሻገር እንደ ማኅበረሰብም ያለውን ጠቀሜታ ያስረዳል፡፡
ሜዲቴሽን ጠቅለል ባለ መልኩ ማይንድፉልነስና ኮንሰንትሬሽን በሚል ይከፈላል፡፡ ማይንድፉልነስ አእምሮና ቀልብን ሳይበታትኑ በአንድ ተግባር ላይ ማኖር ነው፡፡ በተወሰነ ጊዜና ሰዓት ላይ የሚከናወን እንቅስቃሴን በሙሉ ልብ ማካሄድ ማይንድፉልነስን ይገልጻል፡፡ ኮንሰንትሬሽን ሜዲቴሽን ለምንፈልገው ነገር ትኩረት መስጠትና ማስተዋልን ያመለክታል፡፡ ሜዲቴት የሚያደርጉ ሰዎች በጊዜ ብዛት ወደተለያየ የሜዲቴሽን ደረጃ ከፍ ይላሉ፡፡ ሰዎች ሜዲቴሽንን እያዳበሩ ሲሄዱ በግርግር በተሞላ ቦታ ቢሆንም እንኳን ሜዲቴት የማድረግ ክህሎትን ያዳብራሉ፡፡ ዮፍታሔ እንደሚለው፣ ከዘመኑ የጥድፊያ አኗኗርና በአእምሯዊና አካላዊ ጤና ላይ ከተጋረጡ በሽታዎች አንፃር ሜዲቴሽን እንደ አማራጭ ሕክምና በብዙዎች ቢለመድ መልካም ነው፡፡