Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መንታ ገጽታ

የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መንታ ገጽታ

ቀን:

በአገሪቱ ቀደምት ታሪክ ካላቸው የእግር ኳስ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ አንዱና የመጀመርያ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው የውድድር ዓመት 80ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓሉን በማክበር ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ክለቡ ምንም እንኳ ከአገሪቱ ቀደምትነቱና ታሪካዊነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ‹‹የሚመጥነው ተቋማዊ አደረጃጀት የለውም እና ሊኖረው ይገባል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በተለይም በአሁኑ ወቅት በባለሀብቶች መልካም ፈቃደኝነት ካልሆነ በስሙ የ‹‹እኔ›› ብሎ የሚጠራው አንዳችም ነገር የለውም ሲሉ የሚከራከሩ አሉ፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአገሪቱ ከማናቸውም ክለቦች በተሻለ ውጤታማ ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹ተቋማዊ አደረጃጀት በሚል ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ወገኖች የግል ጥቅማቸው የተነካባቸው ናቸው›› በሚልም የሚከራከሩ አሉ፡፡ በሌላ ወገን አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ምንም እንኳ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፎ ዛሬ ላይ መገኘቱ ጥንካሬው እንደተጠበቀ፣ የክለቡ ደጋፊዎች የበላይ አካል የሆነው ጠቅላላ ጉባዔ ላለፉት አራት ዓመታት ተጠርቶ እንደማያውቅ፣ በዚህ ምክንያትም ከክለቡ የፋይናንስ ሥርዓት ጀምሮ የአሠልጣኞችና ተጫዋቾች የቅጥር ሁኔታ፣ ገቢና ወጪውም በተመሳሳይ እንደማይታወቅ የሚናገሩ አሉ፡፡ ከነዚህ ደጋፊዎች መካከል ላለፉት 30 ዓመታት ከደጋፊነትም አልፈው በክለቡ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ማገልገላቸውን የሚናገሩት አቶ ዳንኤል ካሳ የሚናገሩት አላቸው፡፡ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር ለረዥም ዓመታት ከሚታወቁ ደጋፊዎች አንዱ ነዎት፡፡ ከዚህም አልፎ ከ2002 እስከ 2003 ዓ.ም. ድረስ ለአንድ ዓመት የክለቡ የቡድን መሪ ሆነው ማገልገልዎ ይታወሳል፡፡ ከኃላፊነት እንዲለቁ የተደረገበትን ምክንያት ያውቁታል?

አቶ ዳንኤል፡- ይህን ጉዳይ በሚመለከት ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያቱን ሊነግሩን አይችሉም?

አቶ ዳንኤል፡- በወቅቱ የተለያዩ ያልተዋጡሉኝ ነገሮች ነበሩ፡፡ ቢሆንም ከክለቡ ኃላፊዎች አገልግሎቴን አስመልክቶ ‹‹ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ለሠሩት ሥራ እያስመሰገንን በቦታው ግን ሌላ ሰው የተካን መሆኑን እንዲያውቁ›› ብለው ነግረውኛል፡፡ ዝርዝር ምክንያቱን አስመልክቶ ግን በግሌ ለማወቅ ሞክሬያለሁ፡፡ ሌላ ጊዜ ትክክለኛው መድረክ ላይ የምናገረው ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከ30 ዓመት በላይ ከደጋፊነት እስከ አመራርነት በተለያየ ጊዜ አገልግለዋል፡፡ ክለቡን ካወቁበት ጊዜ ጀምሮ ውጤቱንና ስኬቱን እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ዳንኤል፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከታሪካዊ አመጣጡ ስንመለከተው ትልቅ ክለብ ነው፡፡ ብዙ ታሪካዊ ገድሎችን አሳልፎ እዚህ ደረጃ የደረሰ ክለብ ነው፡፡ ከጣሊያን ወረራ ጀምሮ የአንድነትና የነፃነት ተምሳሌት ሆኖ የቆየ ክለብ ነው፡፡ ክለቡ ከእግር ኳሳዊ ፋይዳዎች በላይ ለአገሪቱ አንድነትና ነፃነት ያደረገው አስተዋጽኦ ታሪክ የሚያውቀው ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በንጉሡ ጊዜም ሆነ ከዚያ በኋላ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፏል፡፡ ይባስ ብሎ በደርግ መንግሥት ህልውናው ሳይቀር አደጋ ላይ የወደቀበት አጋጣሚም ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩ ባለሥልጣናት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማፍረስ ያልሞከሩት ነገር አልነበረም፡፡ ሆኖም በክለቡ የቁርጥ ቀን ደጋፊዎችና ወዳጆች ምንም እንኳ ስሙን ቀይሮም ቢሆን ህልውናው እንዲቆይ አድርገዋል፡፡ በወቅቱ የነበሩ የክለቡ ደጋፊዎች እስከነ ችግሩ ውለታቸው እንዲህ በቀላሉ የሚነገር እንዳልሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡

ሪፖርተር፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከፋብሪካው ስያሜ ወጥቶ አሁን የያዘውን ተክለ ሰውነት ያገኘው ከመቼ ጀምሮ ነው? የደጋፊዎቹስ ሚና?

አቶ ዳንኤል፡- እንደነ አስፋው ከበደና አብነት ገብረመስቀል የመሳሰሉትና ሌሎችም በጊዜያዊ ኮሚቴነት ተሰይመው ክለቡ በቀድሞ መጠሪያው እንዲጠራ በ1988 ዓ.ም. ማለት ነው እልህ አስጨራሽ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ አድርገው እንደገና ሕዝባዊነቱን እንዲያገኝ ሆኗል፡፡ በ1992 ዓ.ም. ደግሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሕዝባዊነት ይፋ ሆነ፡፡

ሪፖርተር፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደቀደምትነቱና ታሪካዊነቱ በአሁኑ ወቅት እግር ኳስ ከደረሰበት ዕድገት አኳያ ደረጃውን እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ዳንኤል፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችች ዘንድ ዋናውና አንገብጋቢ ጥያቄ እየሆነ የመጣው ይኼ ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ቀደምትነቱና ታሪካዊነቱ ከአገር ውስጥም አልፎ በአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች ተሳታፊነቱ አሁን ያለው መዋቅራዊ ይዘቱ ያንን የሚመጥን አይደለም፡፡ ይኼ ማለት ክለቡ በቦርድ የሚመራ ነው፡፡ በቦርዱ ውስጥ ደግሞ ለክለቡ መልካም ነገር በማድረግ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን ሳይቀር የሚሰዉ አሉ፡፡ ነገር ግን በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ተቋማዊ አደረጃጀት የለውምና ነው፡፡ በግለሰቦች በጎ ፈቃድ ላይ የተንጠለጠለ መሆን የለበትም፡፡ ክለቡ የሚመራበት ሲስተም መዘርጋት አለበት፡፡ ተጠያቂነትና ግልጽነት ያለበት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል፡፡ ይኼ የአሠራር ሥርዓት ካለ እገሌ ወጣ እገሌ ገባ ምንም ዓይነት መጨናነቅ ሳይፈጠር፣ ክለቡ ክብሩንና ዝናውን ጠብቆ ይኖራል፡፡ ዕድገቱም አይገታም፡፡ እርግጥ ነው በሲስተሙ የሚካተቱ ሰዎች እነማን ናቸው? የሚለው መዘንጋት ያለበት አይመስለኝም፡፡ አቅማቸውና ችሎታቸው እንዲሁም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ያላቸው ፍቅር ጭምር በክለቡ የደጋፊዎች ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ትክክለኛ ምርጫ ሊደረግ ይገባል፡፡ አሁን ያለው ከምናወራው ጋር ሲነጻጸር የቅዱስ ጊዮርጊስን ዕድሜና ዝና የሚመጥን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ዕድሜው፣ እንደ ታላቅነቱ፣ እንደ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፈር ቀዳጅነቱ ተቋማዊ መዋቅሮችን በመዘርጋት ለሌሎቹ አርአያ ሊሆን በተገባ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀደምት ደጋፊዎች መካከል እርስዎንና ራስዎን የመሳሰሉ ክለቡ በተለይም በአሁኑ ወቅት የሚገኝበትን ጠቅላላ ሁኔታ አስመልክቶ የምታነሷቸው ጥያቄዎች እንዳሉ፣ እንዲያውም ክለቡ የሚገኝበት ሁኔታ ያሳስበናል በሚል ጊዜያዊ የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ መሥርታችሁ እየተንቀሳቀሳችሁ መሆኑም ይነገራል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው?

አቶ ዳንኤል፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀደምትነቱ፣ ከታሪካዊነቱና ዝናው አኳያ አሁን በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሚለውን መነሻ በማድረግ በተለይም ቅዱስ ጊዮርጊስ እየተከተለው ያለው አሠራር በብዙዎቻችን የክለቡ ደጋፊዎች ዘንድ ሥጋት ፈጥሯል፡፡ ለዚህ በማሳያነት መጥቀስ የሚቻለው ለአራት ተከታታይ ዓመታት ጠቅላላ ጉባዔ አልተጠራም፡፡ ይኼ በክለቡ ደጋፊዎች መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 15 ቀጥር 1 የተቀመጠውን፣ ጠቅላላ ጉባዔ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ መደረግ እንዳለበት የሚለውን የሚቃረን ነው፡፡ የጠቅላላ ጉባዔ አስፈላጊነት ክለቡ በውድድር ዓመቱ ያከናወናቸው ዕቅዶችን ጠንካራና ደካማ ጎናቸው ተገምግምው፣ የፋይናንስ ሥርዓቱ በውስጥና በውጭ የሒሳብ ባለሙያተኞች ታይቶ በጉባዔ ከፀደቀ በኋላ ለሚመለከተው አካል መቅረብ እንደሚገባው ነው የሚታመነው፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ሕጋዊነትም የሚረጋገጠው በዚህ ዓይነት አሠራር መንቀሳቀስ ሲቻል ነው፡፡ አሁን ግን ይኼ እየሆነ አይደለም፤ አሠራሩም ኃላፊነት ከሚሰማው ቦርድ በፍፁም የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ምናልባት በአንዳንድ ችግሮች ምክንያት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በቀኑ ላይካሄድ ቢችል ምንም አይደለም፡፡ አራት ዓመት ግን ከባድ ነው፡፡ ይኼ ሕግ ባለበት አገር ዛሬ ባይሆን ነገና ከነገወዲያ ጥያቄ ማስነሳቱ የማይቀር ነው፡፡ ምክንያቱም አራት ዓመት ሙሉ ጠቅላላ ጉባዔ ሳያደርግ፣ ኦዲት ሳይደረግ፣ እንዴት ነው ክለቡስ ውድድር የሚያደርገው? የማኅበር ፈቃዱስ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ሥጋቶች በመፍራት መፍትሔዎችንም ለመሻት ብለን የምንቀሳቀስ ደጋፊዎች አለን፡፡ ራሳችን ላወጣነው መተዳደሪያ ደንብ ተገዥ መሆን ስላለብን፣ እያንዳንዱ የስፖርት ክለብም ሆነ ማኅበራት በዓመት ውስጥ ቢያንስ አንድ ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔ ማካሄድ እንደሚኖርባቸው ይታመናል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሕዝብ ነው ከተባለ ሀብቱም የሕዝብ ስለሚሆን ማለት ነው፡፡ መንግሥት ያወጣው የስፖርት ፖሊሲ ሕዝባዊነትን የሚያበረታታና የሚደግፍ ነው፡፡ ያንን መብታችንን አግባብ በሆነ መንገድ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስና ደጋፊዎቹ ያንን አድርገን ማሳየት ይኖርብናል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ከፋይናንስ ሥርዓታችን ጀምሮ እያንዳንዱ የሕዝቡ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉ ማረጋገጫ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይኼ ብቻ አይደለም፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አንድ ክለብ ሊኖረው ስለሚገባው መዋቅራዊ ቁመና ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ክለብ በአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ለመሳተፍ ምን ምን ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላት እንዳለበት ካየ በኋላ ነው የተሳትፎ ፈቃድ የሚሰጠው፡፡ ከመስፈርቶቹ አንዱ ክለቡ በሜዳ ላይና ከሜዳ ውጪ የሚባሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ሜዳ ላይ ሲባል ክለቡ የሚጠቀምበት ማዘውተሪያ በዋናነት ሲጠቀስ፣ ከሜዳ ውጭ ደግሞ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚመለከት ነው፡፡ በኢትዮጵያ እስከዛሬ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ተሟልተዋልን? በፍፁም አልተሟሉም፡፡ ከነዚህ በተጨማሪ የወጣቶች የሥልጠና ፍልስፍና ተጠቃሽ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች በአገሪቱ እንዴት ናቸው? ዝርዝሩን ብናገር ለቀባሪው አረዱት ስለሚሆን እተወዋለሁ፡፡ በእርግጥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢሾፍቱ (ደብረዘይት) ላይ የወጣቶች አካዴሚ እያስገነባ ነው፡፡ የሚደገፍ ነው፡፡ ሌላው የካፍ መስፈርት የክለቦች የገቢ ምንጭ ነው፡፡ በዚህ በኩልስ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዴት እየሄደ ነው የሚለው አይታወቅም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ዙሪያ ያለው የአሠራር ክፍተት አሳስቦናል ካላችሁ በቀጣይ ለማከናወን ያሰባችሁት ምንድነው?

አቶ ዳንኤል፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ያለው ጠቅላላ የአሠራር ሥርዓት በገሃድ አደባባይ ወጥቶ መነጋገርን የሚፈልግ ነው፡፡ ምክንያቱም የቅዱስ ጊዮርጊስ አብዛኛው ደጋፊ በክለቡ ጉዳይ፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት በየካፌው ሳይቀር እየተነጋገረ ነው፡፡ በውስጡ ከፍተኛ ሥጋት አለ፡፡ እስካሁን ግን ከማጉረምረም ያለፍ ይኼ ነው የሚባል ነገር አልተፈጠረም፡፡ አሁን ግን በቅርብ የምንተዋወቅ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ምንድነው ነገሩ? ችግሩ ወደ ከፋ ነገር ከመሸጋገሩ አስቀድሞ ለመፍትሔ ለምን አንነጋገርም? ብለን መወያየት ጀምረናል፡፡ የዚህ ተቆርቋሪ ስብስብ ዋና ዓላማ አንድና አንድ ነው፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ዙሪያ አሁን የሚታዩት ችግሮች በደጋፊዎች ዘንድ የፈጠረው ሥጋት ግልፅ እንዲሆን ነው፡፡ በቦርዱና በደጋፊው መካከል የተፈጠረው መራራቅና ጠቅላላ ጉባዔ ሳይጠራ አራት ዓመት ቀላል ጊዜ ባለመሆኑ ማለት ነው፡፡ ይኼ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማሳደግ ለሚደረገው ርብርብ አራት ዓመት በከንቱ ባክኗል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ችግሮች ነቅሰን በማውጣት፣ ከመላው ደጋፊ ጋር በመነጋገር ጉዳዩን ለቦርዱ ለማቅረብ ነው፡፡ ከዚያም በመድረኩ በችግሮቹ ዙሪያ በግልፅ በመነጋገር የመፍትሔው አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ የእኛ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ጊዜ ሆኗችኋል?

አቶ ዳንኤል፡- እንቅስቃሴው ከተጀመረ የሁለት ወር ዕድሜ ቢኖረው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስብስቡ በደጋፊው ዘንድ የተለያዩ አመለካከቶች እንዲቀረፅ አድርጓል፡፡ ከፊሉ ጥቅማቸው የተነካባቸው ናቸው ሲል፣ ከፊሉ ደግሞ የእናንተን አካሄድ የሚደግፍ ነው፡፡ በሁለቱ አመለካከቶች ዙሪያ ያለዎት አስተያየት ምንድነው?

አቶ ዳንኤል፡- እውነት ነው፡፡ የእኛ እንቅስቃሴ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ በህቡዕ ተደራጅተን ለሥልጣንና አንዳንድ አካላት እንደሚሉት፣ ለጥቅም የሚመስላቸው እንዳሉ እናምናለን፡፡ እውነቱ እስኪወጣ ያለውን ተቀብሎ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሲባል ምንም የምለው አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- በእርስዎና እርስዎን በሚመስሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተነሳሽነት የተሰባሰባችሁበት መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ በክለቡ ችግሮች ዙሪያ ከቦርዱ ጋር ተቀራርቦ ለመነጋገር ያደረገው ጥረት አለ? ምክንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአንዳንድ አስተዳደራዊ ክፍተቶች በተጓዳኝ በውጤት ደረጃ ከአገሪቱ ክለቦች በተሻለ ተጠቃሽ በመሆኑ ማለት ነው፡፡

አቶ ዳንኤል፡- የሚገርመው ቅዱስ ጊዮርጊስ በውጤት ደረጃ ዛሬ አይደለም ክለቡ ምንም ሳይኖረው ሻምፒዮን የሆነባቸው ጊዜያት ብዙ ናቸው፡፡ ተጨዋቾች ምንም ሳይኖራቸው በደጋፊዎች ጣል በምትደረግላቸው ጥቅማ ጥቅሞች ቅዱስ ጊዮርጊስን አሳፍረውት አያውቁም፡፡ በታክሲ አበል ብቻ ክለቡ አሸናፊ ነበር፡፡ የአሸናፊነት መንፈሱ በደሙ ውስጥ ያለ ነው፡፡ አሁንም ቀደም ሲል ከገለፅኳቸው ክፍተቶች ውጭ ክለቡ ለሚጠይቀው ዓመታዊ በጀት ወደ ኋላ የማይሉ የቦርድ አመራሮች አሉ፡፡ ነገር ግን ክለቡ ቀጣይነት ያለው ተቋማዊ ቅርፅ እንዲኖረው እያደረጉ ግን አይደለም፡፡ አሁን ያለው ድጋፍ በባለሀብቶች በጎ ፈቃድ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች የቆሙ ቀን ግን ሁሉ ነገር ያቆማል፡፡ ስለሆነም የእኛ ጥያቄ ክለቡ እያስመዘገበ ያለው ጊዜያዊ ውጤት በቂ አይደለም፡፡ አስተማማኝ የሆነ የገቢ ምንጭ እንፍጠርለት ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ቅዱስ ጊዮርጊስ በስሙ የተቀመጠ ተቀማጭ ሀብት የለውም፡፡ ይኼ ነው የእኛ ሥጋት፤ እርግጥ ነው አንዳንድ ችግሮች ሲፈጠሩ አቶ አብነት ገብረመስቀል ናቸው የሚደርሱለት፡፡ ይኼ ደግሞ እስከ መቼ ይዘልቃል? ነው ሥጋታችን፡፡ ከቦርዱ ጋር ስለተባለው እስካሁን ተቀራርበን አልተነጋገርንም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ዳንኤል፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ሥጋት የሌለው ደጋፊ የለም፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ በርከት ያልን ደጋፊዎች ተቀራርበን እንነጋገር የሚል እንቅስቃሴ ጀምረናል፡፡ ገፍተንበት ከቦርዱ ጋር ተቀራርበን ችግሩን ለመፍታት እንሞክራለን፡፡ እስካሁን ግን ግልጽ መድረክ ተፈጥሮልን መነጋገር ስላልቻልን እንዲህ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ እርግጥ ነው እንቅስቃሴያችን በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ ሌላ ትርጉም እየተሰጠው ቦርዱን ለማፍረስ ነው የሚሉ እንዳሉ እንሰማለን፡፡ ለምሳሌ የክለቡን ችግሮች ከዚህ በፊት በሰጠኋቸው ቃለ መጠይቆች የተናገርኳቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ በእነዚያ ዙሪያ ሁሉም ቦርድ ጭምር አምኖ የተቀበለበት አጋጣሚም ነበር፡፡ ከተነሱት ጥያቄዎች ክለቡ ሜዳ የለውም፣ እውነት ነው፡፡ የራሱ የገቢ ምንጭ የለውም፣ እውነት ነው፡፡ የማኔጅመንት ክፍተቶች አሉ፣ እውነት ነው ብለው አምነዋል፡፡ ነገር ግን ይኼ በክለቡ ደጋፊዎች ሲነገር ሥልጣን ናፋቂና ከፋፋይ በሚል ይተረጐማል፡፡ ጥያቄያችን የተደበቀ ምንም ዓይነት አጀንዳ የለውም፤ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ አንድ ቀን ግን እውነተኛው የእኛ አጀንዳ ቦርዱ አካባቢ ሲደርስ ተቀባይነት እንደሚኖረው አልጠራጠርም፡፡

ሪፖርተር፡- ጉዳዩ ለቦርዱ እንዳይደርስ የሚያደርግ አካል አለ ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ ዳንኤል፡- ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በቦርዱ ዙሪያ ያሉ ጥቅማቸው የሚነካባቸው የሚመስላቸው አይጠፉም፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተስ በቦርዱ እምነት አላችሁ?

አቶ ዳንኤል፡- አሁን አሁን በቦርዱ ያለን እምነት ተሸርሽሯል፡፡ ምክንያቱም የቅዱስ ጊዮርጊስ ችግሮች በሜዳ ላይ በሚገኝ ውጤት መሸፈን ወይም ተደባብሶ እንዲያልፍ የሚያደርጉ ነገሮችን እንመለከታለን፡፡ ለዚህ እንደ ምሳሌ ማንሳት ቢያስፈልግ የክለቡ ጽሕፈት ቤት አደረጃጀትና የቴክኒክ ዲፓርትመንቱ ጭምር ግልጽነትና ተጠያቂነትን የተላበሰ አይደለም፡፡ የአሠልጣኞቹና የተጨዋቾች ቅጥር፣ ለእያንዳንዱ የክለቡ ክፍሎች የሚጠየቀው የትምህርት ደረጃና መስፈርት አይታወቅም፡፡ ስለሆነም እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊነታችን እነዚህ ክፍተቶች ቦርዱ ባለበት ግልጽ ውይይት ተደርጎባቸው የመፍትሔ አቅጣጫ እንዲቀመጥላቸው እንፈልጋለን፡፡ እውነተኛ የጊዮርጊስ ሰዎች ነን የምንል እነዚህ ችግሮች ለመኖራቸው ለአፍታም አንጠራጠርም፡፡ በችግሮቹ ዙሪያ በጋራ ተነጋግረን መፍትሔ ይመጣል የሚልም እምነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- በዋናነት እነዚህ ኃላፊነቶች የማን ናቸው?

አቶ ዳንኤል፡- የሚያጠራጥር አይደለም፤ የቦርዱ ነው፡፡ ቦርዱ መድረኩን መፍጠር ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ እንደሚናገሩት ይኼ መፍትሔ አፈላላጊ ብላችሁ ያቋቋማችሁት ስብስብ በክለቡ አንዳንድ የቦርድ አመራሮች ይሁንታን ያገኘ ስለመሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡ የሚሉት ይኖርዎታል?

አቶ ዳንኤል፡- ይኼ በፍፁም የተሳሳተ መረጃ ነው፡፡ ለዚህ ነው ቀደም ሲል ቦርዱ መድረክ ይፈጠርና እንነጋገር ያልነው፡፡ እንደነዚህ የመሰሉ መረጃዎች እንዲነገሩ የሚፈልጉት፣ አሁንም በክለቡ እንጠቀማለን ብለው ከሚያምኑ ሰዎች የሚመነጭ ካልሆነ በዚህ ጉዳይ ከቦርድ ሰዎች ጋር የተነጋገርንበት አጋጣሚ የለም፡፡ ተቆርቋሪ በመምሰል እነ እከሌ የሚል አጀንዳ የሚፈጥሩ በክለቡ ዙሪያ በርክተዋል፡፡ የሚገርመው እንኳን በምንወደው ክለባችን ቀርቶ በአገራችን በማናቸውም ጉዳይ ለመናገርና ለመጻፍ ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ነው፡፡ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሚመስሉኝ ጋር መነጋገር ማንም ሊነሳኝም ሆነ ሊሰጠኝ አይችልም፣ መብቴ ነው፡፡ ልጠየቅ የሚገባው መብቴ ያልሆነውን የሰው መብት ስነካ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ጊዮርጊስን አስመልክቶ ስንነጋገር ወይም በምንነጋገርናቸው መድረኮች ለማንኛውም የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ክፍት መሆናቸውን የምንናገረው፡፡ በግሌ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዳይ መናገር እየፈለግኩ በውስጤ አፍኜ የምይዘው አንዳችም ሊኖር አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ከንግግርዎ መረዳት የሚቻለው በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ደጋፊዎች ዘንድ ግርታ እንዳለ ነው?

አቶ ዳንኤል፡- ምንም ጥርጥር የለውም፤ አንዳንዱ እውነታን እያወቀ፣ ነገር ግን ገና ለገና የግል ጥቅሜ ይነካል በሚል የሚያወናብድ አለ፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ክፍተቱ መኖሩን አውቆ ያንን አውጥቶ የሚናገርበት መድረክ በማጣቱ ብቻ ዝምታን የመረጠ አለ፡፡ ሌላው ደግሞ ጊዜያዊ ውጤትን ብቻ በመመልከት ወደ ዝርዝር ውስጥ መግባትን የማይፈልግ አለ፡፡ በአጠቃላይ ግን ደጋፊው በግርታ ውስጥ መኖሩ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ አሁንም ቢዘገይም መፍትሔው ቦርዱ ጋር አለ፡፡ መድረክ ከተፈጠረ በህቡዕ የምንባለው ሁሉ የያዝነው አጀንዳ ወጥቶ እውነታው ይታወቃል፡፡ ጥፋተኛ ሆነን ከተገኘንም እንታረማለን፡፡ ለማንም ሲባል አይደለም፤ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ሲባል ነው፡፡ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በክለቡ ዙሪያ ለሚፈጠሩ ትርምሶችና አለመግባባቶች መንስዔ የሚሏቸው ይኖሩ ይሆን?

አቶ ዳንኤል፡- ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን እንደምንናገረው ተቋማዊ አደረጃጀት ፈጥሮ፣ በሥርዓት መመራት ከጀመረ ጥቅማቸው የሚነካ የሚመስላቸው ሰዎች የሚፈጥሩት ነው፡፡ በቦርዱ ዙሪያ በዚህ በሽታ የተለከፉ ሰዎች አሉ፡፡ በእኔ እምነት ይኼ አካሄድ እስካልጠራ ድረስ ቅዱስ ጊዮርጊስ የትም መድረስ አይችልም፡፡ ጊዜው የሚጠይቀው ተቋማዊ ቅርፅና ይዘት የግድ ያስፈልገዋል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብና በቦርዱ ዙሪያ በእግር ኳሳዊ አነጋገር ‹‹የውሸት ዘጠኝ ቁጥሮች›› ብዙ ናቸው፡፡ ከቦርዱ በላይ አቅምና የመወሰን ኃይልም ያላቸው ናቸው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...