Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርጨረታው በሕግና በመመርያ መሠረት የተካሄደ ነው

ጨረታው በሕግና በመመርያ መሠረት የተካሄደ ነው

ቀን:

የአዲስ አበባ ቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ (40/60 ቤቶች ልማት ፕሮግራም) በተቋቋመ አጭር ጊዜ ውስጥ በ13 የግንባታ ሳይቶች 38,790 ቤቶችን እየገነባ ሲሆን፣ በቅርቡም በሰንጋ ተራና በክራውን አካባቢዎች የግንባታ ሥራቸው የተጠናቀቁ 1,292 ቤቶችን ለተጠቃሚዎች ለማስተላለፍ በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡

የግንባታ ሥራቸው በመፋጠን ላይ ያሉ 38,790 ቤቶችን ለማጠናቀቅ እንዲሁም በቀጣይ የግንባታ ሥራቸው ለሚጀመሩ ቤቶች የሚሆኑ የተለያዩ የግንባታ ግብዓቶችን ከውጭና ከአገር ውስጥ ሲገዛ ቆይቷል፡፡ በቀጣይም የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማጠናከር መንግሥት የሰጠውን ትኩረት በመደገፍ ኢንተርፕራይዙ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራል፡፡

በቅርቡም በግንባታ ላይ ላሉ እንዲሁም በቀጣይ ለሚጀመሩ ቤቶች የሚሆኑ የተለያየ ዓይነትና መጠን ያላቸው ንብረቶችን ለመግዛት የአገር ውስጥ አምራች የሚሳተፉበት ጨረታ አውጥቶ የተጫራቾችን የጨረታ ሰነድ መክፈቱ ይታወቃል፡፡ ይህን አስመልክቶ ሪፖርተር በረቡዕ የሚያዝያ 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ዕትሙ (ገጽ 3 እና 6) ‹‹ለ40/60 ቤቶች 150 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ብረት ጨረታ ተከፈተ፤›› በሚል ርዕስ ዜና መሥራቱ ይታወሳል፡፡ ለሕዝቡ ሚዛናዊ ዘገባ በማቅረብ ለአገር እያደረገ ያለውን ጥረት ኢንተርፕራይዛችን ለሪፖርተር ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ከፍ ያለ አክብሮትና አድናቆት ያለው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ በተገለጸው ቀን በወጣው የዜና ዘገባ ላይ ትክክለኛነት የጎደላቸው መረጃዎች ያሉበት በመሆኑ በሚከተለው መንገድ እንዲታረም እንጠይቃለን፡፡

‹‹በአገር ውስጥ ፋብሪካ ላላቸው ኩባንያዎች ብቻ ባቀረበው የብረት ግዢ ጨረታ፣ የጨረታ ዋስትና ማስከበሪያ አለመጠየቁ አነጋጋሪ ሆኗል፤›› በሚል ሐሳብ ተጫራቾች የጨረታ ዋስትና ማስከበሪያ አለመጠየቁ ከአሠራር ውጪ መሆኑን በሚያሳይ መንገድ የቀረበው መረጃ በእኛ እምነት ትክክል አይደለም፡፡

ዜናው ትንታኔውን ሲቀጥል ‹‹ጨረታ የሚያሸንፈው ኩባንያ የሚጠበቅበትን ተግባር ባያከናውን ለጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና የሚያስይዘው ገንዘብ ገቢ የሚደረግበት አሠራር አለ፡፡ ነገር ግን በዚህ ጨረታ ዋስትና አለመኖሩ ግርምት እንደፈጠረባቸው በጨረታው የተካፈሉ ኩባንያዎች ተናግረዋል፤›› በሚል ኢንተርፕራይዙ ጨረታውን የመራበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ በዘገባው ለማሳየት ሞክሯል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የግዥ አዋጅ አንቀጽ 42(4) እና የአፈጻጸም መመርያ ቁጥር 3/2002/22.2.5 መሠረት የጨረታ ማስከበሪያ መጠየቅ ቁጥራቸው ውስን የሆኑትን ተጫራቾች በጨረታው ውድድር እንዳይሳተፉ ያደርጋል ብሎ መሥሪያ ቤቱ ሲያምን፣ የጨረታ ማስከበሪያ ማስያዝ ሳያስፈልግ ዕጩ ተጫራቾች በዚህ መመርያ አባሪ 5 የተመለከተውን የስምምነት ማረጋገጫ (በተጫራቾች የሚሞላ የጨረታ ማስከበሪያ ቅጽ) ፈርመው ከጨረታ ሰነዳቸው ጋር እንዲያቀርቡ ሊደረግ ይችላል፤›› ይላል፡፡ ኢንተርፕራዙም መንግሥት በሰጠው የትኩረት አቅጣጫ የአገር ውስጥ አምራቾች በጨረታው እንዲሳተፉ ለማበረታታት መመርያውን ተከትሎ ትክክለኛውን ሥራ ነው የሠራው፡፡ ይኼን ሕጋዊ አሠራር ሕዝቡም ሆነ ተጫራች ድርጅቶች ቢገነዘቡት ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ጋዜጣው በዚሁ ዜና ላይ ጨረታው ገና በሒደት ላይ መሆኑ እየታወቀ የጨረታው ሒደት እንደተጠናቀቀ የሚያስቆጥሩ መረጃዎችን ማሰራጨቱም ትክክልና ሕጋዊ መሠረት ያለው ነው ብለን አናምንም፡፡ በሌላ በኩልም አጠቃላይ የጨረታው ሒደት ላይ ውሳኔ የሚያሳርፈው የኢንተርፕራይዙ የበላይ ኃላፊ መሆኑ እየታወቀ፣ የጨረታ ውጤቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ እንደሚፀድቅ ተደርጎ በዜናው የቀረበው መረጃም ትክክል ስላልሆነ እርማት እንዲደረግበት እንጠይቃለን፡፡

የጨረታው ሒደት ምንም ዓይነት የሕግና የአሠራር ጥሰት በሌለበት መንገድ አዋጁንና መመርያውን መሠረት አድርጎ የተከናወነ መሆኑ ታውቆ፣ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ባወጣው ዜና ላይ ከላይ የገለጻቸውን መረጃዎች መሠረት በማድረግ አስፈላጊውን ማስተካከያ (እርምት) እንዲሰጥ ስንል እንጠይቃለን፡፡   

(በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ)

* * *

ሥር የሰደደ ነገር ግን መፍትሔ ያላገኘ ችግር

በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ አንድ ሠራተኛ ለመቅጠር ማስታወቂያ በማውጣቱ ከ60 በላይ ወጣቶች ይመዘገባሉ፡፡ የፈተናው ቀን ደርሶ ለመፈተን በአንድ አዳራሽ ተሰብስበው ሳለ አንዲት ወጣት በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ፈተናውን ጨርሳ ትወጣለች፡፡

ቀድሞውኑ በዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ውስጥ ዘመድ ስላላት ፈተናው አስቀድሞ ደርሷታል የተባለችው ወጣት አንደኛ ወጥታ አለፈች በመባሉ፣ አስቀድሞውኑ ጥርጣሬ የገባቸው ወጣት ተፈታኞች፣ ፈተናው ሙስና አለበት ይጣራ በማለት ለዞኑ አስተዳደር ያመለክታሉ፡፡ ጉዳዩ ሲጣራ የዞኑ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዎች አስቀድመው ፈተናውን በመስጠት ያለችሎታዋ ሳትሠራ እንድታልፍ ማድረጋቸው ስለተደረሰበት በኋላ ፈተናው ሙሉ በሙሉ ሊሰረዝ ችሏል፡፡

መንግሥት በየዞኑና በየወረዳው የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከሕዝብ ጋር በመወያየት መፍትሔ እየሰጠ ባለበት ወቅት፣ የተጣለባቸውን የመንግሥትና የሕዝብ አደራ በአግባቡ ያልተወጡ ባለሥልጣናት የማይወጡት ላይ ምን እየተደረገ ነው የሚለው አጠያያቂ ይመስላል፡፡ ከዚህ በፊትም ሆነ ወደፊትም ለሚፈጠረው የመልካም አስተዳደር ችግር የደቡብ ምዕራብ ሸዋ አስተዳደርና የድርጅት ቢሮ ምን ዕርምጃ ወሰደ? ጥያቄው ምላሽ ይሻል፡፡ ሥር የሰደደ አሁንም መፍትሔ ያላገኘ ችግር ነውና የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሊሰጡበት ይገባል?

(ግንፍሌ፣ ከወሊሶ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...