በበሪሁን ተሻለ
ከሚዲያ አገልግሎቶች አንዱና ይበልጥ ዋነኛው ዜናና ኢንፎርሜሽን ለኅብረተሰቡ ማቅረብ ነው፡፡ የኢንፎርሜሽን ጥያቆት ወይም ፍላጎት ደግሞ በየትኛውም መልክ ለተቧደነው ለሰው ልጅ ሁሉ ሲበዛ መሠረታዊ ነው፡፡ በጥንት በጠዋቱ የኅብረተሰብ የዕድገት ደረጃ ላይ በነበረው ኅብረተሰብ ውስጥ የሆነ ሰው የዚያ ‹‹አገር›› ዘብ፣ ጥበቃ ተመልካች ሆኖ ይሠራል፡፡ ይኸው ሰው ወይም ሌላው ከሰዎች መካከል ተመርጦ ሻልና ከፍ ያለ ቦታ ወይም ዛፍ ተፈልጎ የአደጋ ሆነ የምልኪ፣ የዝናብ ሆነ የእሳት፣ የምግብ ይሁን የጠላት ምልክት ከአድማስ ባሻገር ጭምር ዓይቶ መረጃ እንዲሰጥ ይመደባል፡፡ ኅብረተሰቡ ለህልውናው በዚያ ሰውዬ ሪፖርት ላይ ይመካል፡፡
በዘመናዊው ዓለም ከፍ ያለ ቦታ ወይም ረዥም ዛፍ ላይ ወይም የተመረጠ ገዢ መሬት ላይ ያወጣነው፣ የሰቀልነውና ያስቀመጥነው ሰው ጋዜጠኛው ነው፡፡ እዚያ ቦታ ላይ ሆኖ አካባቢውንና አድማሱን ሁሉ የቅርቡንም አሻግሮ ማየትና መቃኘት እንዲችል ሆኖ ተመቻችቶ መቀመጥን መቆምን የሚያውቅበት ሰው እሱ ነው፡፡ ሰውዬውን የሰቀልንበት የተመረጠው ከፍ ያለና ገዢ ቦታ እያገዘው፣ የሰውዬው እዚያ ቦታ ተመቻችቶ የማቃኘት ዕውቀትና ክህሎት ተባብሮና ተረባርቦ እየረዳው ‹‹ዓለማችን›› ውስጥ የሚሆነውን ሁሉ ያያል፣ ይሰማል፡፡ የሰማውንና ያየውን ይነግረናል፡፡ የዜናና የኢንፎርሜሽን ጉዳይ እያደገ መጥቶ እዚህ የደረሰው ከዚህ መሠረታዊ ጥያቆት ነው፡፡ የቅንጦት ጉዳይ አይደለም፡፡ የተረፈው ሰው፣ የደላው ሰው ሲተርፈው የሚሻው ትርፍ ጉዳይ አይደለም፡፡
የሳይንስ ሊቃውንት አሁንም ገና አዲስ በሚባለው ግኝታቸው አረጋገጥነው ብለው ሲናገሩ እንደሰማነው፣ የሰው ልጅ የሠራ አካላቱ እንዲህ የተቀነባበረውና የተቀናጀው በእኛ በመሃይማኑ አባባል ደግሞ አፍንጫ ሲመታ ዓይን የሚያለቅሰው ሰውነታችን የተገነባበት እያንዳንዱ ህዋስ የገዛ ራሳቸውን ኢንፎርሜሽን ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ህዋስ የሌላውን ህዋስ ኢንፎርሜሽን ጭምር አሟልቶና አካትቶ፣ ሳይዘገይና ሳይዛባ ስለሚያውቅ ነው ይሉናል፡፡ ስለዚህም አፍንጫ ሲመታ ዓይን ያለቅሳል፡፡ አልሰማሁም አላየሁም አይልም፡፡
ኅብረተሰብ የሰውነታችንና የሠራ አካላታችን ዓይነት ቅንጅትና ሥርዓት ስለመገንባቱ ለእኔ ገና ባይገለጥልኝም፣ የአገሬ የወሬ ነገር ግን ከምናውቀውና ከነበርንበት የባሰ፣ ግፋ ቢል ሻል አልኩ የማይል ነው፡፡ ዛሬም ከንጉሡ ዘመን በከፋ አኳኋን እንደ ወታደራዊው መንግሥት ዘመን አገር ማወቅ ያለበትን፣ ስለአገር መታወቅ ያለበትን የሚወስነው የዜናና የኢንፎርሜሽን ሥራን፣ ተቋማትን፣ አውታሮችንና ሥርዓትን በምኖፖልነት የያዘው መንግሥት ነው፡፡ አታሚው፣ አሳታሚው፣ አሠራጩ መንግሥት ነው፡፡ ወይም ፈቃድ ሰጪው እሱው ነው፡፡
የሚያሳዝነው ፈቃድ ሰጪው መንግሥት ነው፡፡ ፈቃድ ሰጪው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ነፃና በራሱ የሚያዝ አይደለም ብሎ መናገር የማይገባበት፣ ‹‹ታዲያ ምን ችግር አለው አለው?›› የሚባልበት፣ ፍርድ ቤትም እኮ የትም አገር የመንግሥት ነው የሚል አፀፋዊ መልስ የሚያሰጥበት ጉዳይ ሆኗል፡፡ ዛሬም ቢሆን የመገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ የምርጫ አካላት፣ የመከላከያና የፖሊስ ተቋማት በፓርቲ ተቀጽላነት ውስጥ መውደቅ የለባቸውም ማለት፣ የአገር ወግና ሕይወት ቀርቶ ሕግ እንኳን በቅጡ አልሆነም፡፡ በዚህ የ25 ዓመት ጊዜ ውስጥ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት መንደርደሪያ ዓመታት ውስጥ የታየው የሐሳብ ነፃነት ማሳያ ወይም የሐሳብ ነፃነት ያለማስመሰያ የነበረው፣ የግል ጋዜጦች ጫጫታና የጥቂት የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ጩኸት፣ እንዲሁም የሠልፍና የአደባባይ ስብሰባ ቀርቶ ዛሬ ግርግር የሌለበት አጠቃላይ ዝምታ ሰፍኗል፡፡ ተናግቶ የነበረው የአደባባይ አንገት መድፋት ተመልሶ በሕዝብ ላይ ወድቋል፡፡
መጀመርያ ላይ እነ ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ ኋላም እነ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ሾልከውም ድንገት ሰተት ብለውም ገብተው ምክር ቤቱን በድን ከመሆን አትርፈውት በነበሩት በተቃዋሚዎች ትችት መለብለብ፣ የሐሳብ ነፃነት ያለ ከማስመሰል ጥቅሙ ይልቅ ውድቀትን መጋበዝ የመሆኑ ፍርኃት በልጦ እርም ተብሏል፡፡ ገና በ1984 ዓ.ም. ግንቦት ወር በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሥርጭት አገልግሎት (በጋዜጣና በመጽሔቶች ኅትመት ጨምሮ) ላይ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ወደ ፊት መንግሥት በሚያወጣው ፖሊሲና ሕግ መሠረት ይወሰናል የተባለው፣ በኢንቨስትመንት ማበረታቻ ማስፋፊያና ማስተባበሪያ አዋጁ የተገባው ቃል ያለፈቃድና የፕሬሱ ሕግ ሳይወጣ በፊት መታተም የጀመሩትን መጽሔቶችና ጋዜጦች ዓይቶ እባብ አየሁ ብሎ በረየ፡፡
የብሮድካስት ሕግ ለማውጣት አንኳን (ግንቦት 17 ቀን 1984 ዓ.ም. በወጣው የኢንቨስትመንት ሕግ ቃልና ተስፋ መሠረት) ድፍን ሰባት ዓመት ወሰደ፡፡ በሰኔ 1991 ዓ.ም. የወጣውና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በሥራ ላይ ዋልኩ ያለው የብሮድካስት ሕጉ አንድም የህልውና ምልክት ሳያሳይ ሌላ ስምንት ዓመታት ነጎዱ፡፡ በስምንተኛው ዓመት መጨረሻ ላይ ሐምሌ 16 ቀን 1999 ዓ.ም. ነባሩ የብሮድካስት ሕግ ተሽሮ በሌላ አዲስ ሕግ ተተካ፡፡ የመጀመርያው የግል የብሮድካስት (ለዚያውም የሬዲዮና የኤፍኤም ሬዲዮ ብቻ) ሁለት ፈቃዶች የተሰጡት በዚህ ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ የኅትመት ውጤቶች ብዛት፣ የኅትመት ውጤቶች ሥርጭት ብዛት ለወሬ የማይመች ነው፡፡
በአጠቃላይ መንግሥት ዛሬም በሚዲያ ባለቤትነት፣ ይዘትና አጠቃቀም ላይ ባለሙሉ ሥልጣን ነው፡፡ ፍፁም ቁጥጥሩና ሥልጣኑ የእሱው ነው፡፡ ስለዚህም የሕዝብ ፍላጎት፣ ስሜትና አስተያየት የሚገለጽበትና የሚንፀባረቅበት ነፃ መድረክ አልተፈጠረም፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም (የመገናኛ አውታሮች) ነፃ ሆነው አልተዋቀሩም፡፡ ‹‹የተለያዩ አስተያየቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ አንዲመራ ይደረጋል፤›› የሚለው የሕገ መንግሥቱ የአንቀጽ 29/5 ቃል ዛሬም ያልተፈጸመ ትንቢት ነው፡፡ የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን የሕዝብ ሮሮ፣ ስሜትና ህልም ማስተናገድ ቀርቶ ዓይን ያወጡ የአገርና የሕዝብ አጀንዳዎችን እንኳን ዜና የማያደርጉት ፀጋዬ ገብረ መድኃን ለሌላ ጉደይ በተጠቀሙበት ቋንቋ፣ ትናጋቸውን የቡድን ፖለቲካ ያረሳቸው፣ የማሳቸውና ያበሰበሳቸው ቀና ብለው እውነት እንዳያዩ የፓርቲ ተቀፅላነት እባጭ ጫንቃቸውን እንደ ኮረብታ የተጫናቸው ምስኪን፣ ብኩን መጻጉ ናቸው፡፡ የዜና ምርጫና ቅደም ተከተልን ጨምሮ ወቅታዊ ሪፖርት፣ የሚዲያ ዳሰሳ፣ የአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች አስተያየት፣ የምሁራን ማብራሪያ፣ የዲፕሎማቶች ‹‹ምስክርነት›› የበዓላት መሪ ቃል የሚቃኙባቸው አቅጣጫዎች ሁሉ ከዚህ በፊት በደርግ ዘመን ለ17፣ አሁን ደግሞ ለ25 ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ የኖረባቸውና እንዴት እንደሚወጠወጡ አሳምሮ የሚያውቃቸው፣ ገና ከርቀት በጠረን ብቻ የሚለያቸው ‹‹ቴአትር›› ዓይነት ምርቶች ናቸው፡፡
አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፡፡ ከአገራችን ዋነኛ አጀንዳዎች አንዱና ቀዳሚው ዛሬም ድርቅ ነው፡፡ የአሁኑ ዙር ድርቅ ደግሞ የዓለም ታላላቅ የመገናኛ ብዙኃን የሚቲዎሮሎጂ ዜና ዋና ርዕሰ ጉዳይ የሆነ የጎርፍ አደጋ ይዞ መጥቷል፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት ልማት ሊሳካላት ቀርቶ ከረሃብ የማምለጥ ጥያቄ ዋና እስከ መሆን የገዘፈባት አገር ናት፡፡ የዚህ ምክንያት የዕድገት ችግራችን የት ቦታ ላይ ነው ያለው የሚለውን ጉዳይ በአግባቡና በግልጽ ሳንፈራ፣ ሳናፍርና ሳንሸፋፍን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ባለመመለሳችን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለምለምና ድንግል ናት እየተባለ ቢዘፈንም አጥንቷና ጉልጥምቷ ወጥቶ ድርቅና ረሃብ የሚያዘወትራት አገር ሆና ኖራለች፡፡ ገዢዎቻችን የዕድገት እንቅፋታችንና የመራባችንን ምክንያት ተፈጥሮ የምታደርስብን በደል፣ የአየር ንብረት መዛባት ነው ሲሉን ለዘመናት ኖረዋል፡፡ በየተራ የተቆጣጠሩት የመገናኛ ብዙኃንም ይህንን ምክንያት እያሽሞነሞኑ ሲያፀድቁና ሲመርቁ፣ እውነቱንም ሲደብቁና ሲያድበሰብሱ ኖረዋል፡፡ ሆኖም ይህ ከተጠያቂነት ማምለጫ እንጂ ሁሉንም እውነት የሚናገር አይደለም፡፡ የተፈጥሮ ፀጋ በራሱ ብቻውን ለዕድገት ምክንያት እንደማይሆን ሁሉ፣ ድርቅም ላለመልማት ምክንያት አይሆንም፡፡ ድንግል የተፈጥሮ ሀብት በአያሌው ታቅፈው እየተላለቁና እየተራቡ ያሉ አገሮች እንዳሉ ሁሉ፣ የተፈጥሮ ጥፋቶችንና ኮትቻነትን አሸንፈው ለመበልፀግ የቻሉ አገሮችም አሉ፡፡ በአገራችን የሚታየው ድርቅ የሚያደርሰው ጉዳት አንድ ነገር ነው፡፡ የድርቁ ምልልስና የበረሃማነት መስፋፋት ራሱ ደግሞ ከራሳችን ከሰው ልጅ አጥፊ ሚናና ከልማታችን ችግር ጋር በእጅጉ የተያያዘ ነው፡፡ የአፈርና የደን መራቆት ለምሳሌ ያለማደጋችን ምክንያት ሳይሆን የዕድገት ዕጦት ውጤቶች ናቸው፡፡
ዛሬም ከሰበብ አስባቦች ተላቀን የችግራችንን ጓዳ ጎድጓዳ በእውነት ጎዳናና በተጠያቂነት መንፈስ መመርመር አልቻልንም፡፡ ሚዲያው ይህንን አደባባይ ማውጣት ቀርቶ የመደበቅ ሥራው ቀንደኛ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል፡፡ በዚህም ምክንያት ይህንን የሚመለከተው የሚዲያው አጀንዳ በኤልኒኖ ታሪካዊ አመጣጥ መግቢያና መግለጫ የተወጣ በኤልኒኖ ቅጽል የተሞሸረ ነው፡፡ ለፓርላማ የቀረበው የስኳር ኢንዱስትሪው ንዑስ ዘርፍ የ2008 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት (ሚያዝያ 2008) ራሱ ድርቁ በዘርፉ ለዕቅድ ከለላ እንዳደረገ ይናገራል፡፡ ‹‹የአየር ንብረት መዛባት በመከሰቱ ለፋብሪካና ለመስኖ የሚሆን የውኃ አቅርቦት እጥረት በማጋጠሙ›› የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የምርት ሥራውን አቋርጦ የጥገናና የማስተካከያ ሥራዎች በመሥራት ላይ ነው ይላል፡፡ ሪፖርቱ ለኦፕሬሽን አፈጻጸም ማነስ ዋነኛ ምክንያቶች በሚላቸው ዝርዝር ውስጥ የድርቅ መከሰትና የውኃ እጥረት ከሌሎች መካከል አንዱ ነው፡፡ ለተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ (Phase 1) ፕሮጀክት ዕቅድ አፈጻጸም የሚናገረው የሪፖርቱ ክፍል ‹‹ከውኃ ጥራት ማነስና ድርቁ ባስከተለው የውኃ እጥረት ምክንያት ወደ ምርት መግባት›› አልተቻለም ይላል፡፡ በፕሮጀክት ሥራዎች ስላጋጠሙ ችግሮች ሲነገርም፣ የአዋሽ ወንዝ በመድረቁ በተንዳሆ የመስኖ ውኃ እጥረት መከሰቱ ፋብሪካውን ለማስነሳት አለመቻሉ፣ በማሳ ላይ የሚኘው አገዳ አብዛኛው ውኃ እያገኘ ባለመሆኑ እየደረቀና በቀጣይም ከፍተኛ የምርት መቀነስ የሚያጋጥም መሆኑ፣ እንዲሁም ‹‹ከድርቁ ጋር ተያይዞ የሸንኮራ አገዳ በማኅበረሰቡ ከብቶች መበላቱ›› ናቸው ይላል፡፡
ይህ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የስኳር ኢንዱስትሪው ንዑስ ዘርፍ ብቻ ሪፖርት ያደረገው ችግር ነው፡፡ በሕዝብ አጠቃላይ ሕይወት ውስጥ ያለው ድርቁ ያስከተለው ችግር ግን በየሰው፣ በየቤቱ፣ በየቤተሰቡ ቅሬታ፣ ብሶት፣ ማመልከቻ፣ አቤቱታ፣ ስሞታ፣ ዋይታ ውስጥ ብቻ የቀረው ነው፡፡ ይህንን በየአካባቢው አስተውሎና ታዝቦ መረጃውን በፈርጅ በፈርጅ ለይቶና አዛምዶ፣ በልክና በመልኩ አዘጋጅቶ፣ ለሕዝብና ለመንግሥት ያስተጋባው የለም፡፡ ነጋ ጠባ ጠዋትና ማታ እንዴት አደራችሁ? እንዴት ዋላችሁ? ኢትዮጵያስ እንዴት ሰነበተች? እያሉ የሚነዘንዙን የመንግሥት ሚዲያ ሲሆን የውሏችንን እውነተኛ ገጽታ ፈልፍሎ ለአገር ማቅረብ፣ የማዕከላዊም ሆነ የክልል እንዲሁም የአጥቢያ መንግሥትን አሠራር ማሳወቅ ይገባው ነበር፡፡ ሙያውና ሥራው አደራውና አጀንዳው ግን ይህ አልሆነም፡፡ ከናካቴውም የሚታወቁና የተመዘገቡ ሀቆችን ማውገርገሪያና ማደናበሪያ ሥራ ዋናው ፊታውራሪ ነው፡፡
በዚህ መካከል በ1994 እና በ1995 ዓ.ም. ድርቅ ከ14 እስከ 15 ሚሊዮን ሕዝብ በረሃብ አደጋ ውስጥ እንደገባው፣ አሁንም ከአሥር ሚሊዮን በላይ ሕዝብ የድርቅ አደጋ ሰለባ ሆነ፡፡ ይህ ራሱ እንደ ድርቁ መላልሶ የግብርና ልማቱን ድክመት ደጋግሞ እያሳጣ ነው፡፡ ዝናብን ብቻ በማመን የትም እንደማይደረስ አምርሮ አሳየ፡፡ ኢትዮጵያ እንደገና ተራበች፣ ኢትዮጵያውያን ደግሞ እንደገና ይኸው ተራቡ የሚል ጩኸት አለመከተሉ የሚያስደስተውና መንግሥትን የሚያስመሰግነው ስለደበቀው ሳይሆን ስለተከላከለው ነው፡፡ በአጠቃላይ ልማታችን ድንገተኛ አደጋን መከላከል የሚችል ሥርዓት አደራጅቶ የዝናብ መቅረትና መጥፋት፣ የድርቅ መመላለስ፣ መራብ አለመሆኑን ማረጋገጥ አልቻልንም፡፡ ሚዲያው የሚደብቀው ይህንኑ ጭምር ነው፡፡
የጎርፍ አደጋ የመንግሥት ሚዲያ ሽሽትና ሽፍንፍንነትም ተመሳሳይ ክፋትና አደጋ ያለው አሠራር ነው፡፡ ድሬዳዋ ላይ አሠራሁት የሚለውን ቋሚ ስቱዲዮ ለመመረቅ ለማሳየትና ደጋግሞም ለመጠቀም መከራ የሚያየው የመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የድሬዳዋን የጎርፍ አደጋ ዜና የነገረን አንድም በአገር ውስጥ ዜና መጨረሻ ላይ፣ የመጨረሻው ዜና አድርጐ ነው፡፡ አድበስብሶም ነው፡፡ ይህ በምን መለኪያ ልማታዊውን መንግሥት እንደሚጠቅም እንደምንስ አድርጐ ልማታዊ ጋዜጠኝነት እንደሚሆን የሚያውቀው የመንግሥቱን ሚዲያና አመራሩን የተጠናወተው አባዜ ራሱ ብቻ ነው፡፡
በአገራችን በዕለት ተዕለት የሕዝብ ሕይወት ውስጥ ራሳቸው ፈቃድ የሌላቸው፣ ወይም ያልተፈቀደ መሣሪያ የያዙ ትክክለኛ የአቋም መፈተሻ ማለፍ ያልቻሉ በሕክምና፣ በመድኃኒት ሽያጭ፣ በሕዝብ ትራንስፖርት፣ በኮንስትራክሽን፣ በ‹‹ሰበነክ›› እና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ ሰዎች ሕዝብ ላይ የአደጋ መዓት እያወረዱ ነው፡፡ መኪና፣ ሾፌር፣ መንገድ፣ ጋራዥ እየተባበሩ የሕዝብ የዕልቂት ግንባር ሆነዋል፡፡ መላ የፈለገለት፣ መላ እዚህ ይገኛል ያለ የለም፡፡
በአልኒኖም ሆነ በሌላ የሚያሳብቡትና የሚያድበሰብሱት፣ የኮንስትራክሽን ውስጥ አደጋም የመንገድ ትራንስፖርት አደጋውን ካላስከነዳሁ ሞቼ እገኛለሁ እያለ ነው፡፡ አልረሳንም ያለንን አደጋ እኛ እየረሳን እንጂ የአይደርን ትምህርት ቤት ጭፍጨፋ ለመዘከር የተሰበሰቡትን ሕፃናት ዕልቂት ያስከተለው ይኸው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ አደጋ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍና የዘርፉን ሥራ በሚቆጣጠረው የመንግሥት የሥልጣን አካል ሹማምንት ላይ በይፋ ማሽሟጠጥ የጀመረው አደጋ፣ ሚዲያው እንደ ፍጥርጥሩና ‹‹ጊዜ ሲያገኝ›› የሚዘግበው ብቻ አይደለም፡፡ ሕይወት እየቀጠፉ የአካል ጉዳት እያደረሱ ሳይጠየቁ መቅረት የተሾመበትና የደራበት ሌላው የዕልቂት ግንባር እሱው ነው፡፡
የሚዲያው የዚህ ዘርፍ ዘገባ ደግሞ አዲስ ሪከርድ ሲያስመዘግብ በዓይናችን፣ በጆሮአችን መሰከርን፡፡ አያት አካባቢ የንግድ ባንኮች የሠፈሩበት ሕንፃ መከራ መክሮት፣ የፈረሰውን ሕንፃ አጋጣሚ ያስተዋለ ባለሙያ ደጋግሞ ለምድር ለሰማይ ጉዳዩን ገልጾ ካስጠነቀቀና ‹‹ከእኛ የበለጠ ታውቃለህ!?›› ቢጤ ከተባለ በኋላ ነው፡፡ ኢቲቪ ይህን ዜና የዘገበው የትንሳዔ በዓል ካለፈ በኋላ ውሎ አድሮ ነው፡፡ ይህን ወሬ በሰማንበት የዕለቱ የኢቲቪ የሁለት ሰዓት የዜና ፕሮግራም ውስጥ የተለመደው የቢዝነስ፣ የሚቲዎሮሎጂ የስፖርት ዜና ተከተለ፡፡ እንደተለመደው ‹‹በመጨረሻም ስፖርት›› ሲባል ባንሰማም በብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ ወቅት ስለሞቱት ሰዎች የተነገረን በስፖርቱ ዜና ውስጥ ነው፡፡ ዜናውን የስፖርት ካደረገው የሙያ ሥራ ጥበብ ይልቅ እንዲያ ያለውን የሕይወት መብት ጉዳይ ውራ ያደረገው የኤዲቶርያል ሥልጣኔ ይበልጥ ያማል፡፡
ሕገ መንግሥቱ ዝም ብሎ ‹‹ሞኝ›› ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የማይደፈርና የማይገሰስ፣ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብት አለው ይላል፡፡ በተከታዮቹ የአንቀጽ 15፣ 16 እና 17 ድንጋጌዎች እነዚህን የሕይወት፣ የአካል ደኅንነትና የነፃነት መብቶችን ይደነግጋል፡፡ በሚያዝያ ወር ውስጥ ነው አሉ ወላጆች ልጃቸውን ሄደሽ ሹርባ ተሰርተሽ ነይ ብለው ያዛሉ፡፡ በዚያ ዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኘው መለስተኛ ወጣት ሹርባ ሠሪዋ ዕረፍት ላይ ናት፣ ሥራ አትገባም ብላ ለወላጅ አሳውቃ ፀጉሯን ካስክ ውስጥ ገብታ ፈታ ፈታ እንዲያደርጉላት የተቀበለችውን የወላጅ ትዕዛዝ ለማስፈጸምና ለመፈጸም ወደ ፀጉር ሠሪ ትሄዳለች፡፡ ‹‹ካስክ›› ገብታ ትሞታለች፡፡ የእንቅርት ሕመምተኛዋ ሆዷን ተቀዳ ራሷን ስታውቅ በዓይኗ አልቅሳ በእጇ አብሳ ቁጭ ብላለች፡፡ በአንድ የአገራችን የሕክምና መስጫ ተቋም ሆድሽ ውስጥ ከፍተኛ እጢ አለ፤ አስቸኳይ በኦፕራሲዮን ካልወጣ የማይቀለበስ አደጋ አንዣቦብሻል ተብላ የደነገጠች ሴት አቅሙ ያላት ኖሮ ጀርመን አገር ሄዳ ስትመረመር በአገር ዶክተር ፊርማና ጽሑፍ ዕጢ የተባለው የሦስት ወራት ጽንስ ሆኖ ያርፈዋል፡፡ ዝርዝሩ ብዙና አስደንጋጭ ነው፡፡ ይህ ሁሉ የሚሰማው ከአፍ ወደ አፍ በሚሠራጭ ጋዜጣ ነው፡፡
የአገራችን የንግድና የሙያ ሥራ ፈቃድ ሥርዓት እልህ አስጨራሽና የተወሳሰበ ነው፡፡ የብቃት ማረጋገጫ የሚባል ሌላ ሕመም ያለበት መላ የለሽ ከልካይ አሠራር ነው፡፡ እንዲያም ሆኖም እንደ ቁንጅና ሳሎን የፀጉር ሥራ ያሉ የወንድም የሴትም ሥራዎች ማንም ሰተት ብሎ ቢገባባቸው፣ ምንም ዓይነት መሣርያና የመሣርያ አገጣጠም ቢኖረው ከልካይ ተቆጣጣሪ የሌለባቸው ናቸው፡፡ እያጠፉ መማር እየተሳሳቱ መለማመድ ይቻላል፡፡ በተግባር እንደሚታወቀው የክፍለ ከተማና የወረዳ የፈቃድ ሰጪ ሹማምንት ጭንቅና ጥብ በገዛ ራሱ ምክንያት ግብ የሆነውን መሰናክል ማብዛት፣ የባለ ጉዳዩን የወጪ ምክንያት ማንዛዛት፣ የመንግሥትን ገቢ ከፍ ማድረግ እንጂ የሰው ጤናና ደኅንነት ጉዳያቸው አይደለም፡፡ ለዚህ የሕይወት፣ የአካል ደኅንነት መብት ከልብ የሚደነግጥ ማንም የለም፡፡ ኢትዮ ቴለኮምን የመሰለ ግዙፍ ተቋምና ከፍ ያለ ኮርፖሬት ኃላፊነት ሊሰማው የሚገባው ድርጅት፣ ራሱ የሆነ የ‹‹ገበታ›› አገልግሎቱን በሚያስተዋውቅበት የቴሌቪዥን ማስታወቂያ ሥራው የአንድ የፀጉር ማስተካከያ ሱቅ/ቤት የቴሌን የኢንተርኔት የአገልግሎት ዓይነቶችና አማራጮች ሲያስኮመኩም በዝርዝር ያሳያል፡፡ በዚህ ትዕይንትና ሒደት ውስጥ ማስታወቂያውን ‹‹ከሚያሳምሩት›› ጉዳዮች መካከል ፀጉር አስተካካዩ በሚያስተካክለው ሰው አንገት/ጭንቅላት ላይ የስለት መሣሪያውን ደግኖ፣ ሥራውን ሳያቋርጥ ከቤት ውጪና ከመንገድ ባሻገር ሰው ሰላም ሲል የሚያሳየው የተለመደውና የታወቀው የፀጉር አስተካካዮች ምግባር ነው፡፡ እንዲህ ያለ ነገር ሥነ ምግባር ያለው ፀጉር አስተካካይ አሠራር አይደለም ማለት፣ በማስታወቂያ ሥራ ለተሰማራም ለማስታወቂያ አስነጋሪውም ለማስታወቂያ አሠራጩም ገና ያልተገለጸ ነውር ያልሆነ ነገር ነው፡፡
በቀን ተቀን የሕዝብ ሕይወት ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ሕዝብ ላይ አደጋዎች የሚያዘንቡ ሰዎች ጉዳይ በተለመደና በተሽሞነሞነ ስሙ የመልካም አስተዳደር ችግር ይባላል፡፡ ይህን የመንገድ ላይ የኮንስትራክሽን፣ የሕክምና ውስጥ፣ ወዘተ. አደጋና ሞት ሚዲያው የአገር አጀንዳ ማድረግ አለበት፡፡ ይህን ያደርግ ዘንድ መጠነ ሰፊው ችግር የተደበቀበትን ስያሜ ትቶ የችግሩን ምንጭ በስሙ መጥራት አለበት፡፡ እኩይ አስተዳደር ይበለው መንጃ ፈቃድ ዝም ብሎ የሚያድለው አስተዳደር እኩይ ነው፡፡ መንገድ ላይ የሚነዱ መኪኖች የሚለቀቁበት አሠራር ከእኩይ አስተዳደር የመነጨ ነው፡፡ የትኛዋም እናት ከጤና ተቋም ውጪ አትወልድም እያልን ጤና ተቋሙን የሚጐበኙ ሴቶች በግል ጉዳያቸውና ወሬ በተጠመዱ፣ ሲያናግሩም መርዝ በሚተፉ (ማን እግርሽን አንሽ አለሽ? በሚሉ) ሰዎች ይስተናገዱ ማለት መልካም አስተዳደር አይደለም፡፡
ብሔራዊ የሐዘን ቀን አውጀን ባንዲራ ዝቅ አድርገን ያውለበለብንለት የጋምቤላው አደጋ ዛሬም ገና የአገር ውስጥ ከፍተኛ አጀንዳ ነው፡፡ በርካታ ሕይወት ጠፍቶበታል፡፡ ታግተው የተወሰዱት ሕፃናት ገና ሁሉም አለተመለሱም፡፡ ከአደጋው በፊትና ከዚያም በኋላ የሆነውና የአኳኋናችንና የአያያዛችን ጉዳይ ከውይይትና ከንግግር በላይ መሆን የለበትም፡፡ ጋምቤላ የሆነውን ሁሉ በስሙ መጥራት አለብን፡፡ በሕይወት፣ በነፃነት፣ በአካል ደኅንነትና በንብረት ላይ የተሠራ ወንጀል ነው፡፡ ቅድመ ወንጀል የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ፣ ድኅረ ወንጀል ፈጥኖ የመድረስና የምላሽ ሥርዓታችንስ ምን ዓይነት ነበር ብለን መገማገምም አለብን፡፡ ሁሌም በማዕከላዊ፣ በክልልና በአጥቢያ ደረጃ የሚገኙ የመከላከያ ተዋንያን የፀጥታ ጥበቃ ሰዎች ምን አደረጉ? ምንስ አላደረጉም? ማለት የሚያስፈራና የሚያሳፍር ጥያቄ መሆን የለበትም፡፡
በዚህ ረገድ ግድያን፣ ጠለፋንና ማገትን እንዲሁም ከከብት ዘርፍ ጋር የተያያዙ ደመ ነውጠኛ ተግባሮችን እንደ ወንጀል ያለመቁጠርና እነዚህን ወንጀሎች የፈጸሙትን ሰዎች ሳይጠይቁ መቅረት የሚያፀድቅና የሚመርቅ፣ ለረዥም ጊዜ ሥር ሰዶ የቆየ እምነትን መታገልና መቀልበስ ይኖርብናል፡፡ በይነ ማኅበራዊ ነውጠኝነቱንም ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ወግና ልማድ ተከታይና ቀጣይ አሠራር፣ ስለዚህም ሊረዱት የሚገባ አሠራር ነው ማለትን የሚያቋቁም ሚዲያው በፊታውራሪነት የሚያራምደው እምነት በሰው ላይ ሲጫን እንሰማለንም፡፡
ይህ የወንጀል ድርጊትን በስሙ ከመጥራት ይጋርዳል፡፡ የመንግሥትን ግዴታም ያውገረግራል፡፡ በተለይም ኢሕአዴግ ሲበዛ አከብረዋለሁና እሞትለታለሁ በሚለው የቡድን/የሕዝብ መብት ላይ ልክ የለሽ ንቀት የተቃጣ ያስመስላል፡፡
አዲስ አበባ ላይ አንድ የወንጀል ድርጊት ሲፈጸም የወንጀሉን ድርጊት የፈጸመው ሰው/ሰዎች በዚያው ተጠርጣሪነታቸው (ተከሳሽነታቸው የሚገባቸው መብት የሌላቸው ይመስል) ሕዝብ (የሕዝብ ክፍል) በትግታና በግርታ ሆ ብሎ ተነስቶ ያዙልኝ ልቀቁኝ በሚባልበት አገር፣ በመቶ ቤት የሚቆጠሩ ሕፃናትን ጠለፋ እየሰሙ ዝም ማለት ወይም እነሱ ልማዳቸው ባህላቸው ነው ማለት የደኅንነት፣ የነፃነት መብትን ሁሉ አቀፋዊነት አልገባንም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለ በሕይወት፣ በደኅንነትና በነፃነት ላይ የሚሠራ ወንጀል አዲስ አበባ ላይ ሲፈጸም አሸባሪነት የሚባልበት ወይም በአሸባሪነት የሚጠረጠርበት፣ ሌላ ቦታ ልማድ የሚሆንበት ብዙ ቆይተን ከእንቅልፋችን ስንነቃ ደግሞ ‹‹ፀረ ሰላም›› የምንልበት አካሄድና ሥርዓት መላና ብልኃት ሊበጅለት ይገባል፡፡
የመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን የሰብዓዊ መብትን (የቡድንን ጨምሮ)፣ የሕግ የበላይነትን ጉዳይ ከአፍና ከተውኔት ይልቅ በተግባር ሲያከብሩ ለምናይበት ጊዜ በትጋት እንሥራ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡