Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ከ250 በላይ ፕሮጀክቶችን ተረክበን የመሥራት ዕቅድ አለን››

አቶ ኃይለ መስቀል ተፈራ፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ

መንግሥት የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለማሳደግ ያስችላሉ በማለት ውሳኔ ከሰጠባቸውና እንዲቋቋሙ ካደረጋቸው ኮርፖሬሽኖች ውስጥ፣ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አንዱ ነው፡፡ እንደ አገር በቀል ኮንትራክተሮች የሚቆጠሩትን መንግሥታዊዎቹን የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት በአንድነት አጣምሮ እንዲያስተዳድር ኃላፊነት ተሰጥቶት ግዙፍ ኮርፖሬሽን መፈጠሩ ተገልጿል፡፡ በእነዚህ ተቋማት የሚከናወኑ ሥራዎችን የበለጠ ለማሻሻል፣ እንዲሁም ቀደም ሲል ባልተሳተፉባቸው አዳዲስ የኮንስትራክሽን ሥራ ዘርፎች መሳተፍ እንዲችሉ መንግሥት እነዚህን ሁለቱን ተቋማት በአንድ ተቋምነት እንዲደራጁ ማድረጉ ጠቃሚ ዕርምጃ ነው ተብሏል፡፡ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተገንጥሎ መሥራት ከጀመረ አምስተኛ ዓመቱን የያዘውን የኢትዮጵያ መንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንንና የኢትዮጵያ የውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ውህደት የፀናው፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 366/2008 ታኅሳስ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው፡፡ አዲሱ የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ20.3 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ ሥራውን ለመጀመር ከተፈቀደለት ካፒታል ውስጥ 7.7 ቢሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብና በዓይነት የተከፈለ ነው፡፡ ከዚህም በኋላ አቅሙን ለማጐልበት ካፒታሉ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል፡፡ ኮርፖሬሽኑ አዋህዶ ከያዛቸው ከሁለቱ ትልልቅ የመንግሥት ድርጅቶች በተጨማሪ፣ ሦስት አዳዲስ ኮርፖሬሽኖች እንዲያቋቁምና እንዲያስተዳድርም ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ተቋም በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት ኮርፖሬሽኖች በግዙፍነቱ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው ተብሏል፡፡ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይለ መስቀል ተፈራ እንደገለጹት፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ቀጥሎ ከፍተኛውን ካፒታል የያዘ ነው፡፡ የአገሪቱን የመንግሥት የኮንስትራክሽን ግንባታዎችና ሌሎች ተደራራቢ ሥራዎችን የተሸከመው ይህ ግዙፍ ተቋም በርካታ ኃላፊነቶች ያሉበት ሲሆን በተለያዩ የግንባታ ሥራዎች፣ የተገነቡ ግንባታዎችን የማስተዳደር፣ የሰው ኃይል ሥልጠናና ሌሎችንም እንዲያከናውን ታስቦ የተቋቋመ ነው፡፡ በሥሩ ከመንገድ ኮንስትራክሽንና ከውኃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ሌላ በግድብ ግንባታና አስተዳደር፣ በመስኖ ልማት፣ በሕንፃ ግንባታና በኮንስትራክሽን ዕቃዎች ማምረት ላይ የሚሠሩ ራሳቸውን ችለው እንደ አንድ ቢዝነስ ተቋቁመው በኮርፖሬሽኑ ሥር የሚተዳደሩ ተቋማትንም ይፈጥራል፡፡ የየዘርፉ ሥራ አስኪያጆችም የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ሆነው ይሠራሉ፡፡ ኮርፖሬሽኑ የተሰጠው ኃላፊነት እጅግ የበዛ ነውም ተብሏል፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ የሥራ ተቋራጭ በመሆን መንገዶችን፣ ድልድዮችን፣ የግድብና የመስኖ ሥራዎችን፣ የውኃ ማከፋፈያና የቆሻሻ ማስወገጃ መስመሮችን፣ የወንዝ መቀልበስና የጥልቅ ውኃ ጉድጓድ ሥራዎችን፣ የሕንፃና የአውሮፕላን ማረፊያዎችን፣ የባቡር መንገዶችንና የወደብ ግንባታ ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎችን የመገጣጠም፣ የጥገና አገልግሎት የመስጠትና የማከራየት፣ መለዋወጫዎችን የማምረትና የመሸጥ፣ መጋዘኖችንና ሕንፃዎችን የማከራየት ሥራ ያከናውናል፡፡ በፌደራል መንግሥት በጀት የተገነቡና የሚገነቡ የመስኖ ግድቦችንና ጥልቅ የውኃ ጉድጓዶችን ያስተዳድራል፤ ከተጠቃሚዎችም ገቢ ይሰበስባል፡፡ የሚፈልገውን የሰው ኃይል በራሱ የማሠልጠኛ ማዕከል የማብቃት ወይም ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የማሠልጠኛ ተቋማት ጋር በቅንጅት ይሠራል፡፡ እንዲሁም ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎችንም ያከናውናል የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ውጭም እንዲሠራ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሚያወጣውን መመርያ፣ እንዲሁም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር የሚሰጠውን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ ቦንድ የመሸጥና ዋስትና የማስያዝ፣ እንዲሁም ከአገር ውስጥና ከውጭ የገንዘብ ምንጮች ጋር የብድር ውል በመደራደር ሲፈቀድም እንደሚፈርም ሁሉ የመቋቋሚያ ሰነዱ ያመለክታል፡፡ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሚረዱ ሌሎች ተዛማጅ ሥራዎችንም እንዲያከናውን የተለጠጠና እጅግ ሰፊ ኃላፊነት የተሰጠው አዲሱ ኮርፖሬሽን፣ በሥሩ ያጠቃለላቸውና የሚያቋቁማቸውን ኩባንያዎች ሥራ ሁሉ ተረክቦ ይሠራል፡፡ ከሌሎች ኮርፖሬሽኖች በተለየ ተደራራቢ ኃላፊነት የተሸከመ እንደሚሆን የሚነገርለት ይህ ኮርፖሬሽን በጠቀለላቸው ተቋማት ሥር ከ15 ሺሕ በላይ ሠራተኞች ይዟል፡፡ በመንገድ ዘርፍ ከ5.8 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ጅምር ፕሮጀክቶችን ለማስተዳደር ተረክቧል፡፡ በአሁኑ ወቅት አደረጃጀቱን ጨርሶ ወደ ሥራ የገባ ሲሆን፣ የእዚህ ግዙፍ ኩባንያ አፈጣጠር፣ አስፈላጊነትና አጠቃላይ ዕቅድ ላይ ሐሙስ ግንባት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሰየሙትና የቀድሞ የሥራና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ኃይለ መስቀል ተፈራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫውን ተንተርሶ ዳዊት ታዬ አቶ ኃይለ መስቀልን በማነጋገርና ከጋዜጣዊ መግለጫው ያጣቀሰበትን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ግዙፍ ኩባንያ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማ እንዴት ይገለጻል? አስፈላጊነቱስ?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- በኮንስትራክሽን ግንባታ አፈጻጸም የሚታዩ ክፍተቶች አሉ፡፡ በሰፊው ያቀድናቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች በምንፈልጋቸው የጥራት ደረጃ ያለመሆን ጐልቶ ወጥቷል፡፡ ስለዚህ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን የተያዙ የኮንስትራክሽን ግቦችን ሊያሳካ የሚችል፣ ክፍተቶችን የሚሞላ የሚችል ተቋም እንዲፈጠር ነው የተፈለገው፡፡ ለኮርፖሬሽኑ መቋቋም ካስፈለገባቸው ምክንያቶች አንዱ ሊጠቀስ የሚችለው ይኼ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ኮርፖሬሽኑን ለማቋቋም ያስፈለገበት ምክንያት ዘላቂ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት የውስጥ አቅማችንን ማጠናከር ወሳኝ በመሆኑ ነው፡፡ የአገር ውስጥ አቅም ወሳኝ ነው፡፡ ልማትና ዕድገት ያለ ውስጥ አቅም ሊታይ አይችልም፡፡ ስለዚህ የማያቁርጥ የውስጥ አቅም ወይም የማስፈጸም አቅም ክፍተት ብለን በየጊዜው በመገምገም የምናስቀምጠውን ጉዳይ ሊፈታና የግሉን ዘርፍ ጉድለት ሊሞላ የሚችል ተቋም እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ኮርፖሬሽኑ ልማቱን እያከናወነ በሒደት በግሉ ዘርፍ የሚታዩ የማስፈጸም አቅም ክፍተቶችን በግንባታው በቀጥታ ከሚሰማራው ፈጻሚ ባለሙያ፣ በተቋራጭና በአማካሪዎች የሚታዩ ክፍተቶችን እንዲሞላ ተልዕኮ ተሰጥቶታል፡፡

ተቋሙ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ በንግድ ሥራ ላይ የሚሰማራ ቢሆንም፣ ሁለት ዋና ዋና ግዙፍ ተልዕኮዎችን ተሸክሞ የተቋቋመ ነው፡፡  በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የሚታዩ ጉድለቶችን ለምሳሌ የፕሮጀክቶች መጓተት፣ የጥራት ችግርና በአጠቃላይ ከጥራት ችግር ጋር ተያይዞ የሚታዩ የማስተዋሉ የዋጋ መናር ጉዳዮችን ገበያውን እያረጋጋ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እያስተዋወቀ ልማቱን የማፋጠን ድርሻም ይኖረዋል፡፡ ከዚህ አኳያ እየገባንባቸው ያሉት ሥራዎች የማናውቃቸውና ያለመድናቸው ናቸው፡፡ በውስብስብነታቸውም ሆነ በባህሪያቸው የተለዩ ናቸው፡፡ ከፍተኛ ካፒታልና አቅም የሚጠይቁ ናቸው፡፡ እነዚህ ሥራዎች ውስጥ የግል ዘርፉ አይገባም፡፡ መንግሥት ግንባር ቀደም ሆኖ አቅም እየፈጠረ በሒደት የተፈጠረውን አቅም ደግሞ ለግሉ ዘርፍ እያሸጋገረ፣ በሚያቋርጥ የዕድገት ሒደት ውስጥ ሊሄድ የሚችል የኮርፖሬት ተቋም እንዲሆን ከማሰብ ጭምር ነው የተቋቋመው፡፡ የሌሎች አገሮች ልምድ የሚያሳየውም ይህንን ነው፡፡ መንግሥት የገበያ ጉድለት ባለባቸው መስኮች እየገባ እየመራ የሚሄድበት አግባብ ነው ያለው፡፡ ይህንን በላቀ ደረጃ ትኩረት ሰጥተን መሄድ አለብን በሚል መንግሥትም አቋም ይዞ፣ በእነዚህ ነባር ተቋማት ተበታትነው ሳይሆን አቅማቸውን አሰባስበውና በአዲስ አሠራር ታጥቀው ግንባር ቀደም ሆነው እንዲሠሩ ለማስቻል ነው፡፡ እስከ ዛሬ ያልተገባባቸው የደረቅ ወደብ ግንባታ የፍጥነት መንገድ የግድብ ግንባታና ኃይሎች ያልተገባባቸው ሥራዎችን ይሠራል፡፡ የሕንፃ መገጣጠሚያ አካላት ማምረቻ ይኖረዋል፡፡ ለዚህም የሕንፃ መገጣጠሚያ ኢንተርፕራይዝ ወደ ኮርፖሬሽኑ ተጠቃሏል፡፡ የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች መገጣጠሚያና ሌሎች ሥራዎችንም ይሠራል፡፡ ግድቦችን የማስተዳደርና የመስኖ ውኃዎችን የመሸጥ ሥራ ሁሉ የዚህ ኮርፖሬሽን ኃላፊነት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ስለኮርፖሬሽኑ አወቃቀርና ስለሚሠራቸው ሥራዎች ሲገለጽ እንደሰማነው እጅግ በርካታ ሥራዎች የሚከናወኑ መሆኑን ነው፡፡ በኮንስትራክሽንና ከኮንስትራክሽን ሥራዎች ጋር በተያያዙ ሥራዎች ውስጥ ሁሉ ይገባል፡፡ በሥሩም ትልልቅ ተቋማትን ይፈጥራል ተብሏል፡፡ ነገር ግን በሥሩ ከያዛቸው ተቋማት ውስጥ የመንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን አንዱ ነው፡፡ ይህ ተቋም ብዙ ጥናት ተደርጐ ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ተገንጥሎ ለብቻው እንዲሠራ ከተደረገ ገና አምስት ዓመቱ ነው፡፡ አሁን ደግሞ እንደገና በአዲሱ ኮርፖሬሽን ሥር እንዲደራጅ ተደረገ፡፡ እንዲህ ባለው ሁኔታ በማደራጀት ተቋማት በራሳቸው አቅም ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራ ከመሥራት ይልቅ በማደራጀትና በማዋቀር ብቻ ጊዜ እየፈጁ ነው፡፡ በተለይ አሁን እንደተጀመረው የተለያዩ ተቋማትን በአንድ ኮርፖሬሽን ሥር ማደራጀቱ ውጤታማ አለመሆኑም እየታየ ነው፡፡ ለምሳሌ የስኳር ኮርፖሬሽን መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሁንም ግዙፍ ኮርፖሬሽን መፍጠሩ ምን ውጤት ያስገኛል? ይህንን ሁሉ ለመሥራት አቅሙስ አለ?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- የአቅም ጉዳይ የምንስማማበት ነው፡፡ በአገራችን የልማት እንቅስቃሴ ሒደት ውስጥ አለብን ብለን ያስቀመጥነው የአቅም ችግር ነው፡፡ ይኼንን የአቅም ችግር አለ ብሎ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን፣ እንዴት ነው የሚፈታው የሚለው ጥያቄ የተመለሰበትም ነው፡፡ እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያስፈልጋል፡፡ በእኛ ነባራዊ ሁኔታ አቅም ፈጥረን አይደለም ወደ ልማት የምንገባው፡፡ እየሠራን ነው የምንለማው፣ እየሠራን ነው አቅም የምንፈጥረው፡፡ አሁን መሠረታዊው መርህና ኮርፖሬሽናችን እየተከተለ ያለው አሠራር አለ፡፡ በአጠቃላይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ ያለው ችግር ምንድነው ብሎ ያለውን ክፍተት ለይቷል፡፡ መለየት ብቻ ሳይሆን መግባባት ተፈጥሯል፡፡ በዕቅዳችን ይኼ የአቅም ችግር እንዴት መፈታት እንዳለበትም መልስ ተሰጥቶበታል፡፡ ይህንን ለመፍታት ካስቀመጥናቸው መካከል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምንሠራው ሥራ አንዱ ነው፡፡ አንድ የውጭ ሥራ ተቋራጭ መንገድ ሲገነባ የሚያስተዳድርበት መንገድና እኛ የምናስተዳድርበት መንገድ ታይቷል፡፡ በውጭ ኮንትራክተሮችና በአገር ውስጥ መካከል ያለውን ልዩነት በሚገባ አውቀናል፡፡ እዚህ ላይ ነው የምንሠራው፡፡ አሁን በምንገባበት ሥራ ብዙዎቻችን ወይም ባለሙያዎቻችን ልንሠራ ያሰብናቸውን ሥራዎች ዓይተናቸው የማናውቃቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ዕድገታችን የፈጠራቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ሒደት ውስጥ እንዴት ነው መምራት የምንችለው የሚለው ጥያቄ ነው የሚመጣው፡፡ ሌሎቹ ይህንን እንዴት ነው ያለፉት? ይህንን ለይተናል፡፡ ይህንን ሒደት ለማለፍ መጋፈጥ ብቻ ነው፡፡ ምንም ምርጫ የለንም፡፡ ስለዚህ በዚህ ሒደት እያለፍን፣ አቅም እየፈጠርን፣ እየበቃንና እያበቃን የምንሄድበትን አቅጣጫ ነው የምንከተለው፡፡ ይኼ አቅም የመፍጠር ሒደት ውስብስብ ነው የተዘጋጀም አይደለም፡፡ ብዙ ጉዳዮችን የያዘ ነው፡፡

ጥሩ ነገሩ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በኮንስትራክሽን ዘርፍ እያደገ የመጣ አቅም አለ፡፡ ግን ችግሩ ፍጥነት ላይ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የምንጠቀማቸው የዲዛይንና የቴክኖሎጂ መረጣ ላይ ያሉ ክፍተቶች አሉ፡፡ እነዚህ በጥናታችን የተለዩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ተምረን ምን ዓይነት ቴክኖሎጂ መረጣ ማድረግ እንዳለብን እንድናውቅ አድርጐናል፡፡ እነዚህ የአቅም መፍጠሪያ ዘዴዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ዕውቀቱ ካላቸው የውጭ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኩባንያዎች ጋር በአጋርነትና በሽርክና ስትራቴጂ እንሠራለን፡፡ የሌለንንም ካለበት አምጥተን እንሠራለን፡፡ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው በውኃ ሥራ ሩዋንዳዎች ወደ ኢትዮጵየ መጥተው የኢትዮጵያ የውኃ ሥራዎች ያካበተውን ትንሽን ልምድ ወስደዋል፡፡ ምክንያቱም እዚያ ክፍተት ስላለ ነው፡፡ እኛ ደግሞ ከዚህ በላይ ለመሄድ ነው፡፡ የበለጠ አቅም ለመፍጠር ነው፡፡ ባለው እየሠራን በሌለን ላይ ደግሞ አቅም እየፈጠርን የምንሄድበትን መንገድ ነው የምናየው፡፡   

ከኮርፖሬሽኖች አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ያሉ ክፍተቶች አሉ፡፡ ያጋጥማሉ፡፡ ነገር ግን ሊያስደምመን የሚገባው ክፍተቶች መፈጠራቸው አይደለም፡፡ ወሳኙ ነገር ክፍተቶችን የመፍታት አቅማችንና ቁመናችን ነው፡፡ ለዚህ የሚመጥን አደረጃጀት፣ የባለሙያ አቅምና አመራር ላይ ጫን ማለት አለብን፡፡ ከዚህ አንፃር ተምረናል ብለን እናስባለን፡፡ በአዲሱ ኮርፖሬሽናችን ሥራዎቻችን በሚከናወኑበት ቦታ ላይ ሠራተኞች ብቁ በመሆን ሥራ ከጫፍ ጫፍ መምራት የሚያስችላቸውን ትጥቅ፣ መሣሪያና ዕውቀት እንዲይዙ የማስቻል አቅጣጫ ነው የምንከተለው፡፡ ከዚህ አኳያ በተለያዩ ኮርፖሬሽን አደረጃጀቶች ላይ ሲገጥሙን የነበሩ ችግሮች በቅርፃቸው ከምንደርስበት የዕድገት ደረጃ ጋር የተለያዩ ከመሆናቸው ጋር የተያያዙ ካልሆኑ በስተቀር፣ እየተፈቱ ሊሄዱ የሚችሉበትን አቅጣጫና ስትራቴጂ መከተል አለብን ብለነው የምናስበው፡፡ ጥሩ ነገሩ በኮንስትራክሽን ላይ ስንመጣ ደግሞ ኮንስትራክሽን በባህሪው ፈተና ነው፡፡ ግን በተቀናጀ ሁኔታ መፍታት ነው፡፡ ችግር ባይኖር የማኔጅመንት ሲስተም አይመጣም፡፡ አሁን ባለን ልምድ ካለፈው አፈጻጸማችን በመነሳት በቀላሉ ሊስተካከል የሚችል የሰው ኃይል አለን ብለን እናስባለን፡፡    

ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚመሩት ኮርፖሬሽን የተሰጡት ሥራዎች ብዙ ከመሆን አልፈው በንግዱ ውስጥም ይገባሉ፡፡ ይገነባል፣ ያስተዳድራል፣ ያመርታል፣ ይሸጣል፡፡ አንድ ተቋም ሁሉንም ዓይነት የግንባታ ሥራዎች እየሠራ የራሴ ፋብሪካ ይኖረኛል፣ ሕንፃ ገንብቼ አከራያለሁ፣ እሸጣለሁ፤ ከገነባሁ በኋላ አስተዳድራለሁ፣ ውኃ እሸጣለሁ በማለቱ በኢኮኖሚክሱ ጽንሰ ሐሳብ እንዲህ ያሉ ሥራዎች እንዴት ይገልጻሉ? እንደ አንድ ኮንትራክተር ትወዳደራላችሁ? ወይስ የገበያ ክፍተት ያለበት ቦታ ብቻ ነው የምትሠሩት?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- በኮርፖሬሽን ማደራጃ ላይ አንዱ የተሰጠን ሥራ የመንግሥት የልማት ድርጅት ሆኖ፣ በንግድ ሥርዓትና ሕግ የሚተዳደር ሆኖ፣ በተጨማሪ የተሰጠው ኃላፊነት ለራሱም ሆነ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሰው ኃይል ያለማል የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ያለንን እያበቃን የተሻለ የዕውቀት ደረጃ እንዲከተል እናደርጋለን፡፡ የሌለንን ደግሞ ካለበት በማምጣት፣ እዚህ አገር ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ባለሙያዎች ስላሉ ከእነሱ ጋር በማቀናጀት ክፍተቱን እንሞላለን ብለን እናስባለን፡፡ በሒደት አቅም የምንፈጥረው በዚህ መንገድ ስንሄድ ብቻ ነው፡፡ በአንድ ጊዜ የተሰጠን ተልዕኮ እንወጣለን ብለን አናስብም፡፡ ግን የተሰጠንን ሥራ እየሠራን እንሄዳለን፡፡

ሪፖርተር፡- የማስተዳደርና የመገንባት ሥራው መደበላለቁስ እንዴት ይታያል? ቢዝነሶቹ ብዙ ናቸው፡፡

አቶ ኃይለ መስቀል፡- ይህ የመገንባትና የማስተዳደር ሥራ እኛ ዘንድ አዲስ አስተሳሰብ ነው፡፡ ማስተዳደርና መገንባትን ዓለም የተሸጋገረበት ነው፡፡ ኢኮኖሚያችን እየዳበረ በሚሄድበት ጊዜ ኩባንያዎች ማቅረብ ያለባቸው ሁሉንም አንድ ላይ ነው፡፡ ትልቅ አቅም ያለው የግል ኩባንያ ቢኖር ገንዘቡን ያመጣል፣ ግድቡን ይሠራል፣ ኃይል ያመነጫል፣ ኃይል ያሠራጫል፣ ገንዘቡን ይሰበስባል፡፡ ነገር ግን የግሉ ዘርፍ በዚህ ኢንቨስትመንት ውስጥ መግባት አይፈልግም፡፡ ምክንያቱም ካፒታል የሚበላ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ የኢንቨስትመንት ወጪውን ስለማይመልስለት አይገባም፡፡ እንዲህ ያሉ ሥራዎች ላይ እንደ መንግሥት እየገባን ያለነው ለዚህ ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ እስኪመጣ ድረስ የገበያ ጉድለት እንሞላለን ሲባል አንደኛው የዕድገት ደረጃ ነው፡፡ መንግሥት  የገበያ ጉድለት ካለና የሚያስተዳድርለት የግል ዘርፍ ከሌለ ማስተዳደር አለበት፡፡ ምክንያቱም ክፍተት ስላለ ማለት ነው፡፡ እስቲ ውኃን እንመልከት፡፡ የብዙ አገሮች ልምድ እንደሚያሳየውና ትልልቅ ተቋማት ከተገነቡ በኋላ እነሱን የመንከባከብ፣ የመጠገን የማስተዳደር ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ ይህንን ልምድ በእስራኤል፣ በግብፅ፣ በደቡብ አፍሪካና በመሳሰሉት አገሮች የሚተገብሩት ነው፡፡ በተወሰነ ደረጃ የግል ዘርፉ የሚገነባባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ እነሱም ቁጥጥር አለባቸው፡፡ ለምሳሌ በእስራኤል የግል የውኃ አልሚዎች አሉ፡፡ እነዚህ የሚያለሙትን ውኃ የሚሸጡት ለመንግሥት ነው፡፡ በአሜሪካም የግል ውኃ አልሚዎች አሉ፡፡ አንድ ከተማ የሚያህል ውኃ አልምተው ውኃ ማሠራጫው ላይ ያገናኛሉ፡፡ ስለዚህ ዞሮ ዞሮ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነው የሚያርፉት፡፡ ይህ የሚሆነው ግለሰብ የማስተዳደር አቅም ስለሌለው ነው፡፡ ይኼ ነው ልምዱ፡፡ እኛም ዘንድ ሲመጣ በጊዜ ሒደት ከዚህ ውጪ አይሆንም፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ ግን የግድብ አስተዳደሩ ላይ ስንመጣ ባለቤት ሊሰየምለት ይገባል፡፡ ገንቢውና አስተዳዳሪው የተለያዩ ናቸው፡፡ የሚገነባው አልሚ ነው፡፡ የውኃ መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፍ ሆኖ እንደ አንድ የቢዝነስ ዩኒት ነው የተደራጀው፡፡ ከግድብ አስተዳደር ጋር ኮንትራታዊ ዝምድና ነው ያላቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- እዚህ ላይ ግን የግድብ አስተዳዳሪው የግድቡ ገንቢም እንደ አንድ ኩባንያ የሚታዩ ናቸው፡፡ በኮርፖሬሽኑ ሥር የሚመሩ መሆናቸው እንዴት ይታያል?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- ቆይ … ምናልባት ሊነሳ የሚችለው በአንድ ኮርፖሬሽን ሥር ሆነው እንዴት እንዲህ ዓይነት ሥራ ሊሠሩ ይችላሉ ሊባል ይችላል፡፡ ቻይና ውስጥ በአንድ ኮርፖሬሽን ሥር ወደ 400 ኮርፖሬሽኖች አሉ፡፡ በራሳቸው የሚቆሙ ሆነው በጋራ የሚሠሩ ሥራዎችን ደግሞ በጋራ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ራሳቸውም የሚቆሙበት አለ፡፡ የእኛ የግድብ አስተዳደር ግንባታው የተጠናቀቀው ግድብ ከተሰጠው በኋላ ወደ ኢኮኖሚ ንብረትነት ቀይሮ ሀብት እያመነጨ ለቀጣይ ኢንቨስትመንት መሥራት ነው፡፡ ባለቤት ነው የሚሆነው፡፡ አሠራሩ እንዲህ ነው፡፡ እኛ ትልቅ ዕርምጃ ወስደናል ብለን የምናስበውና መታየት ያለበት ከዚህ በፊት የነበረው፣ በተለይ ለብዙዎቹ እንደ አብነት የምንወስደው ስኳር ኮርፖሬሽንን ነው፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽን የፋብሪካው፣ የእርሻው፣ የመስኖው መሠረተ ልማትና የግድቡ ባለቤት ሆኖ ሲሠራ ነበር፡፡ ይህ አሠራር ግን ሊሆን አይችልም፡፡ የገበያ ችግር ስለነበረብን፣ ከሆነ ቦታ መጀመር ስለነበረብን የገባንበት ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ አይሆንም፡፡

አሁን ካሉት ግድቦች አንዳንዶቹን የሠራቸው ስኳር ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ለምሳሌ የወልቃይትንና የኩራዝ ግድብን ስኳር ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ነገር ግን ጥሩ የሚሆነው ስኳር ቢያመርት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው አሠራር የግድብ ማስተዳደሩ ሥራ የተሰጠው ለኮርፖሬሽናችን ነው፡፡ በሚቀጥለው ዘመን ደግሞ ምንድነው የሚሆነው የሚለውን ሰደርስ ነው የምናየው፡፡ ሒደቱ ግን ይኼ ነው፡፡ አንተ ያነሳኸው የኮርፖሬሽኖቹ ክፍተት ወይም ጫና ይኼ ነው፡፡ የኮርፖሬሽኖቹ ብቃት ማነስ አንዱ ምክንያት የሆነው የአስተዳደር ሥርዓታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን የማስተካከልና በትክክለኛው አቅጣጫ የማራመድ ሥራ ነው እያከናወን ያለነው፡፡ ሥራው ወደሚሠራበት ደረጃ ነው የተሄደው፡፡ ሲሰበሰቡ አቅም ነው እየፈጠሩ ያሉት፡፡ ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ዕድል ነው የሚፈጥርላቸው፡፡ በነገራችን ላይ አሁን በኮርፖሬሽናችን ሥር እንዲጣመሩ ከተደረጉት አንዱ የሆነው የመንገድ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን የአውሮፕላን ማረፊያዎችን ይሠራል፡፡ የውኃው ኢንተርፕራይዝ ደግሞ በተመሳሳይ አውሮፕላን ማረፊያዎችን እንዲገነባ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በአንድ የመንግሥት ተቋም ውስጥ ሁለት ተወዳዳሪ ኩባንያዎች ሊኖሩ አይገባም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ዓይነት አቅሞች ነው እየተሰበሰቡ ያሉት፡፡ ሀብቱ ወደ አንድ ይሰባሰባል፡፡ ሥራው አንድ ይሆናል፡፡ መንግሥት በአንድ ጉዳይ ላይ በተደራጀ መንገድ እንዲገባ ለማድረግ ነው እየተሠራ ያለው፡፡ ስለዚህ አደረጃጀቱ ውስጥ የሚታየውን ክፍተት የሚፈታ የኮርፖሬሽናዊ ሲስተም ነው እየተከተልን ያለነው፡፡ ከዚህ አንፃር ወደ ውጤት ያስገባናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ከውድድር አንፃር የምንሰማራው በውድድር ሕግ ነው፡፡ ለአብነት ያህል የመንገድ ግንባታ ሥራዎችን ያገኘነው ከግሉ ዘርፍ ጋር ተወዳድረን ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ የተለየ ባህሪ ላላቸውና ጨረታም ቢወጣ ገንቢ የማይገኝባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶችን ወይም ተሞክሮ ያልተሳኩት ሊሰጡን ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በሒደት የግሉ ዘርፍ አቅሙን ሲገነባ እኛ እየወጣን ውስብስብና ስትራቴጂክ ወደሆኑ ሥራዎች እንገባለን፡፡ ቅኝቱም ይኼ ነው፡፡ የብዙዎችን የዓለም አገሮች ልምድ ስናይ ይኼ ነው ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህንን ሁሉ ድርጅት ማሰባሰቡና በአንድ ማምጣቱ ችግር አይኖረውም?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- እንደ አገር የኮንስትራክሽን ፍላጐቱ እያደገ ነው፡፡ ይህንን ፍላጐት በተለይ በገበያ ውስጥ ያለውን በፍላጐትና በአቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የግድ እንዲህ ተደራጅቶ መሥራት ያሻል፡፡ አሁን ካለው ፍላጐት አንፃር የታቀዱ አንዳንዶቹ ሥራዎች ሳይፈጸሙ ይቀራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- በተለይ የግሉ ዘርፍ አቅም ስለሌለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የመንግሥት ዋነኛ ዓላማዎች ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው የገበያ ጉድለቱን መሙላት ነው፡፡ ሁለተኛው የኮንስትራክሽን ሥራዎችን በተለይ ግዙፎቹን በማያቋርጥ ሁኔታ መገንባት የገባንበት ደረጃ ላይ ነው የምንገኘው፡፡ ለግዙፎቹ የሚሆን አቅም ደግሞ አልተፈጠረም፡፡ ስለዚህ በግል ዘርፉ አሁን በአገር ደረጃ አምስት ሺሕ የሥራ ተቋራጮች አሉ፡፡ አንድ ግድብ የሚሠራ ተቋራጭ የለም፡፡ እንዲያውም የአምስት ድርጅት አቅም ተደምሮ ይህንን መሥራት የሚችል አቅም አይደለም ያለው፡፡ ስለዚህ ወደ ውጭ መሄድ እንገደዳለን፡፡ ለምሳሌ በአገራችን በኃይድሮ ፓወር አንድም አገር በቀል ተቋራጭ የለም፡፡ ስለዚህ የእኛ ዓላማ ይህንን መቀየር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የውጪዎቹም  ኩባንያዎች ቢሆኑ ከ50 በመቶ በላይ፣ አንዳንዶቹም ከ80 በመቶ በላይ የአገር ውስጥ ዕውቀት ነው የሚጠቀሙት፡፡ ይኼ ኃይል ይበተንብናል፡፡ ሥራው ሲሠራ የሚፈጠረውን የሚሸከም ኩባንያ ያስፈልጋል ከተባለ፣ የእኛ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በጣም አዋጪ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ሁኔታዎችን ስናይ ግልገል ጊቤና ተከዜ ከተገነቡ በኋላ ብዙዎቹን ባለሙያዎች መልሰን ልንጠቀምባቸው ሲገባ ከአገር ይወጣሉ፣ ይበታተናሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ለምን? ምክንያቱስ?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- ተቋማዊ ሥራዎቹ አሉ፡፡ ሥራው የሚሠራው በዓለም አቀፍ ደረጃ ነው፡፡ የኃይድሮ ፓወር ግንባታና የመስኖ ግንባታ ደረጃው በዓለም አቀፍ ዕውቀት ነው፡፡ ይፈለጋል፡፡ የገበያ እጥረቱ አለ፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ የፍጥነት መንገዶች ከዚህ ወደ ምዕራብ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ የሚሄዱ አሉ፡፡ ሥራውና አቅሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታይ ነው፡፡ ስለዚህ የበቃ ባለሙያ እጥረት ወዳለበት መሄዱ አይቀርም፡፡ ስለዚህ በእንደዚህ ዓይነት ክስተቶች ባለሙያዎቻችን መሄዳቸው ለእኛ ስኬት ነው፡፡ በሌላ በኩል ስናየው ደግሞ በአገር ውስጥ ያሉ ባለሙያዎቻችን ከግንባታ ፍላጐታችን አንፃር መሄዳቸው ጉዳት ነው፡፡ ይህንን ጉዳት ሚዛናዊ ለማድረግ ተቋም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የወጡ ባለሙያዎቻችን ወደ ኮርፖሬሽኑ እየተመለሱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ያመጣችኋቸው ባለሙያዎች አሉ ማለት ነው?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- አዎ እየመጡ ያሉ አሉ፡፡ አሁንም መስመር ላይ ያሉ አሉ፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ መስመር ውስጥ እየገባን ነው፡፡ እኛ ተቋማዊ በሆነ መንገድ ይዘን የምንሄድ ከሆነ የእኛ ባለሙያ በተደራጀ መንገድ በዚህ ኮርፖሬሽን በኩል ነው ወደ ውጭ መውጣት ያለበት ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ ኮርፖሬሽን አደረጃጀቱን ጨርሷል፡፡ ከ2009 በጀት ዓመት ጀምሮ ለአራት ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ አውጥቷል፡፡ እተገብራቸዋለሁ ካላቸው መካከል የግድብ ሥራ አንዱ ነው፡፡ በእርግጥ በኮርፖሬሽኑ ደረጃ ቢያንስ አንድ ግድብ ገንብታችሁ ሥራ ላይ ለማዋል እንችላለን ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- በእርግጠኝነት አዎ፡፡ እኛ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በእርግጠኝነት የምንገባበት ሥራ አለ፡፡ በተለየ ደረጃ ያሉ ግድቦች አሉ፡፡ አነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ የሚባሉ ግድቦች አሉ፡፡ የስኳርን መሠረተ ልማት ተከትለው ያሉ ግድቦች አሉ፡፡ ከፍተኛ የውኃ ግድቦች አሉ፡፡ ለምሳሌ የኦሞን የተፈጥሮ ኃይል ፍሰት መሸከም የሚችል ካናል እንሠራለን፡፡ ይህንን በአራት ዓመታት ውስጥ እናሳካለን ብለን አቅደናል፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ፕሮጀክት አዲስ ነው?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- ይህ አዲስ ሥራ ነው፡፡ ከዜሮ ነው የምንጀምረው፡፡ አሁን የተጀመሩ አዳዲስ ግድቦች አሉ፡፡ የእነዚህን የመስኖ መሠረተ ልማቶች ለመጨረስ ታቅዷል፡፡ ይህ ትልቅ ዕቅድ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የመስኖ መሠረተ ልማት ላይ የምትሠሩት ምንድነው?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- ከግድቡ ወደ እርሻው የሚሄዱ ካናሎች አሉ፡፡ ከዋናው ካናል ወደ እያንዳንዱ እርሻ የሚወስዱ ቦዮች አሉ፡፡ ከቦዮቹም ለእያንዳንዱ የእርሻ ተክል ውኃ የሚለቀውን መስመር ሁሉ ያጠቃልላል፡፡ እነዚህን መስመሮች የመዘርጋት ሥራ ይሠራል፡፡ አንዳንዴ ስለመስኖ ማውራት የፈለገ ስለግድብ ያወራል፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የተለያዩ የመስኖ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ እንደነ መገጭና አልዌሮ ያሉ ግድቦችን አይቻለሁ፡፡ ፕሮጀክቶቹ ከተጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ሥራቸው ያለቀም ያላለቀም አሉ፡፡ ግን በእነዚህ ግድቦች የመስኖው ሥራ በተፈለገው ደረጃ አልተሠራበትም፡፡ እስከ ዛሬስ እንዴት ነበር የሚተዳደሩት? እናንተ አሁን እነዚህን ግድቦች እናስተዳድራለን ብላችኋል፡፡ ምን ጥቅም ይገኛል?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- በቀድሞና በአሁኑ አሠራር መሀል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ እነዚህ ትልልቅና ውስብስብ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ተራ ፕሮጀክቶች አይደሉም፡፡ የሕዝብ ጥቅም አለ፡፡ በየግድቦቹ የተያዘው ውኃ ለአርሶ አደሩ የምታሠራጨው ነው፡፡ ግድብ ስትሠራ ሰፊ ቦታ ስለሚሸፍን የሠፈራ ጉዳይ ይመጣል፡፡ በባህሪው ውስብስብ ነው፡፡ ከለማ በኋላ ያንን የሚያህል መሠረተ ልማት ማስተዳደር ቀላል አይደለም፡፡ ሊፈርስና ሊሸነቆር ይችላል፡፡ ውኃ ከሌሎች ሥራዎች ይለያል፡፡ ሕንፃ ጊዜ ይሰጥሃል፡፡ ውኃ እንደዚያ አይደለም፡፡ ውኃ ካፈተለከ አደጋ አለው፡፡ ከጥቅም ውጭ ይሆናል፡፡ ትንሽ ነው የሚበቃው፡፡ ስለዚህ ለዚህ የሚመጥን የፕሮጀክት አመራር ሥርዓት ይዘን አልነበረም ስንሠራ የነበረው፡፡ ለዚህ የሚመጥን የአደረጃጀት ቁመና ይዘን አይደለም ሥንሠራ የነበረው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለቤት ይሰየምለታል፡፡ ለመስኖ ሥራ የራሱ ባለቤት፣ ለግድቡም ባለቤት ይኖረዋል፡፡ የግድቡንም የመስኖውም ሥራ እንደየባህሪያቸው የሚያስተዳድር ባለቤት ይኖራቸዋል፡፡ ግድብ ማስተዳደር ቀላል ሥራ አይደለም፡፡ ውኃን በአግባቡ ካላስተዳደርክ ጉዳት አለው፡፡ ውኃን ያላግባብ ከለቀቅህ በድርቅ ትመታለህ፡፡ ስለዚህ ይህንን በአግባቡ ማስተዳደር ያሻል፡፡ ይኼ ትልቅ ዕውቀት ይጠይቃል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ሥራዎች ግን ብዙ ያልሠራንባቸው ናቸው፡፡ ባለቤት ያልሰየምንባቸው ናቸው፡፡ በጣም ልንሠራባቸው የሚገቡ መስኮች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ውኃም ይዘን ውኃውን የማንጠቀምበት ጊዜ አለ፡፡ ውኃው አጠገብ የማይለማ መሬት አለ፡፡ ስለዚህ አሁን እኛ ባለቤት ስንሆን ብር አለን ማለት ነው፡፡ የሚሸጥ ውኃ አለን ማለት ነው፡፡

እኔ ውኃዬን ካልሸጥኩት ግድቤን ማስተዳደር አልችልም፡፡ ሌላም መሠረተ ልማት ልሠራ አልችልም፡፡ ስለዚህ ማድረግ ያለብኝ ሄጄ የሚለማ መሬት ፍላጐት እንዲፈጠር ልሠራ ነው፡፡ ምክንያቱም ውኃዬ እንዲሸጥልኝ እንዲህ ማድረግ አለብኝ፡፡ ፆም የሚያድር መሬት እየፈለግሁ ውኃ እያመረትኩ ለመሬቱ ልማት የሚሆን ውኃ መሸጥ አለብን፡፡ የእኔ ሥራ እንደ ድሮው አይደለም፡፡ እንደ ድሮው ግድብ ሠርቶ ዞር ማለት አይደለም፡፡ ግድቡን ማስተዳደር ያስፈልጋል፡፡ ግድብ ከተገደበ ደግሞ ማኔጅመንት የሚባል ነገር ይመጣል፡፡ ከዚህ ቀደም ሙሉ ለሙሉ ባለቤት አልነበረውም፡፡ ባለቤት ስላልነበረው ለፕሮጀክቱ መጓተትና ለፕሮጀክቶቹ አቅጣጫ ማጣት አስተዋጽኦ አድርጓል ብለን እናምናለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ኮርፖሬሽኑ ይተገብራቸዋል ብላችሁ ከተነሳችሁባቸው ሥራዎች ውስጥ የግድብ ግንባታውን ካጠናቀቃችሁ በኋላ ራሳችሁ ማስተዳደር፣ ከዚያም የግድቡን ውኃ ለመስኖ ልማት መሸጥን ጭምር ያጠቃልላል፡፡ የመስኖ ውኃው ሽያጭ እንዴት ይከናወናል? የዋጋ ተመኑስ እንዴት ነው? አሠራሩስ?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- ነገሩን በቀላል ቋንቋ ላስቀምጥልህ፡፡ ቤትህ ቧንቧ አለ፡፡ በምትጠቀምበት ውኃ መጠን ተለክቶ ትከፍላለህ፡፡ የመስኖ ውኃውም ተመሳሳይ ነው፡፡ ለዚህ ማስፈጸሚያ የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን አስመጥተን እንሠራባቸዋለን፡፡ ጥናቶቹ እየተሠሩ ነው፡፡ በራዳር ሲስተም አውቶሜትድ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች አሉ፡፡ በእያንዳንዱ ላይ የምትገባውን ውኃ የሚለካ ሜትር አለ፡፡ ምን ያህል ውኃ እንደተጠቀመ ስለሚታወቅ በየወሩ ቢል ይሰጠዋል፡፡ ይህ የሚሆነው በተገባው የኮንትራት ስምምነት መሠረት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ አንድ ነገር ልንገርህ፡፡ በቅርቡ ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር የምንፈጽመው ስምምነት ነው፡፡ እኔ ለስኳር ኮርፖሬሽን ውኃ ሻጭ ነኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ስኳር ኮርፖሬሽን ውኃ በነፃ አይወስድም፡፡ ለዚህ የሚሆን የታሪፍ ረቂቁን ተዘጋጅቶ አልቋል፡፡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል፡፡ ስለዚህ የምንዘረጋቸው ሲስተሞች አሉ፡፡ ውኃው በቱቦ ነው የሚወሰደው፡፡ ውኃዬ ሳይባክን እርሻው ላይ መድረስ አለበት፡፡ የተሠራጨው ውኃ ደግሞ በትክክል ሥራ ላይ ውሎ ወደ ገንዘብ መቀየር አለበት፡፡ ይህንን እሰበስባለሁ፡፡ ይህንን አሠራር በመንግሥት ተቋማት ላይ መተግባር ቀላል ነው፡፡ አሠራሩን ወደ ግል ስንወስደው ደግሞ ሌላ ሥልት ይኖራል፡፡ መስኖ ለማልማት አርሶ አደሩ ይደራጃል፡፡ በራሱ አደረጃጀት ውኃውን ይከፋፈላል፡፡ ከዚያ ቢሉን ሰጥቼ በተከፋፈለው ውኃ ልክ ይከፈላል፡፡ በዓለም ላይ ያለውም አሠራር ይኼ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- አሁንም ተመሳሳይ ጥያቄ ላቀርብ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ነገር ተግባራዊ ለማድረግ አቅሙ አለ ወይ?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- አቅም ብለህ ላነሳከው ጥያቄ መልስ የሚሆነው አቅም የምንፈጥረው እየሠራን ነው፡፡ አጠቃላይ አሠራሩ ከፍተኛ ዋጋ ይጠይቃል፡፡ ይህንን ገንዘብ ከመንግሥትም ከባንኮችም ተበድረን ይህንን ቴክኖሎጂ እንተገብራለን፡፡ በማዕከል ደረጃ አንድ መቆጣጠሪያ ይኖረናል፡፡ እያንዳንዱ ግድብ ምን ያህል ውኃ እንደያዘ የሚያሳይ ሲስተም ይኖራል፡፡ የትኛው ካናል ላይ ምን ያህል ውኃ እየፈሰሰ እንዳለ የምንቆጣጠርበት ነው፡፡ ቴክኖሎጂው ውስብስብ ነው፡፡ እንዲህ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ይህንን ማምጣት ግን ምርጫ የለንም፡፡

ሪፖርተር፡- የኮርፖሬሽኑ አወቃቀርም ቢሆን የተወሳሰበ ይመስላል፡፡ ከመንግሥት ኮርፖሬሽኖች ጋር ሲነፃፀር ደረጃው እንዴት ይቀመጣል? የመጪው አራት ዓመት ዕቅዳችሁስ?

አቶ ኃይለ መስቀል፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ኮርፖሬሽኖች ትልቁ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ነው፡፡ በካፒታል የተደራጀ ከኤሌክትሪክ ኃይል ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ነው፡፡ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን 140 ቢሊዮን ብር ካፒታል አለው፡፡ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ከ42 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ከ250 በላይ ፕሮጀክቶችን ተረክበን የመሥራት ዕቅድ አለን፡፡ 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...