Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አገራዊ የንግድ መርከብ አገልግሎትና ፋይዳዎቹ

በሪፖርተር ጋዜጣ ዕትም ቅጽ 21 ቁጥር 1672 እሑድ ሚያዝያ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. አቶ ናታን ዳዊት በተባሉ ጸሐፊ “የንግድ መርከብና የሞኖፖሊ አሠራሩ ተፅዕኖዎች” በሚል ርዕስ፣ በሸማች አምድ የቀረበውን ሐተታ ድርጅታችን ተመልክቶታል፡፡ ርዕሱን አስመልክቶ የቀረበው ሐተታ ከጽንሰ ሐሳቡ ጀምሮ እስከ ቀረበው መረጃ አቅጣጫውን የሳተ፣ ከእውነታ የራቀና ለአንባቢዎች የተሳሳተ መረጃ የሚሰጥ ሆኖ በመገኘቱ ድርጅታችንን በጣም ያሳዘነ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ስለሆነም አንባቢያን ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኙ ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የአገራችን ብሔራዊ የመርከብ አገልግሎት እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ በርካታ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ግዛት ነፃነታቸውን ሲቀዳጁ የውጭ ንግድ ሥርዓታቸው በወቅቱ ከነበሩት ላይነር ኮንፈረንስ የሚባሉ የመርከብ ባለቤቶች የፈጠሩት ካርቴል ሥር የወደቀ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ የመርከብ ኮንፈረንሶች በሚያወጡት የባህር ማጓጓዣ ዋጋ መክፈል ግድ ስለሆነባቸውና ዋጋውም እጅግ ከፍተኛ ስለነበረ እነዚህ የአፍሪካ አገሮች የየራሳቸው መርከብ አቋቁመዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ጋና፣ ናይጄሪያና አይቮሪኮስት ይጠቀሳሉ፡፡ የአገራችን የመርከብ አገልግሎት የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1966 ዓ.ም ሲሆን የአፍሪካውያን አገሮች እንቅስቃሴ አካል መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

በተጨማሪም የአገራችንን ጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ ተከትሎ በወቅቱ በግብፅና በእስራኤል ጦርነት ያንዣበበት ጊዜ ስለነበረ የኢትዮጵያን የውጭ ንግድ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የመርከብ ድርጅት ማቋቋም አስቀድሞ የታሰበበት ጉዳይ ነበር፡፡ በእርግጥም እ.ኤ.አ በ1967 ዓ.ም በግብፅና እስራኤል ጦርነት በመቀስቀሱና የስዊዝ ካናል በመዘጋቱ በደቡብ አፍሪካ በመዞር የአገራችን የውጭ ንግድ እንቅስቃሴ በማስቀጠል የማይተካና የማይረሳ አሻራ ጥሎ ማለፉ የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የሌሎች የአፍሪካ አገሮች የመርከብ ድርጅቶች በተለያዩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮቻቸው ምክንያት አንድ በአንድ እንቅስቃሴያቸው ቆሟል፣ ጥሩ ቁመናና ጥንካሬ ይዞ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የኢትዮጵያ የመርከብ አገልግሎት ብቻ ነው፡፡

የአገራችን የንግድ መርከብ አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ 52 ዓመታት የተቆጠረ ሲሆን፣ ድርጅታችን በአሁኑ ወቅት በአንድ ጊዜ 335,000 ቶን የማንሳት አቅም ያላቸው መርከቦች ባለቤት ነው፡፡

የአገራችን የንግድ መርከብ አገልግሎት አሁን የደረሰበት ደረጃ ለማድረስ በርካታ ውስብስብ ችግሮችና ፈተናዎች ያለፈ ሲሆን፣ እዚህ ላይ ማለት የሚቻለው ግን የአገራችንን ጥቅም ለማስጠበቅና ለአገራችን ሁለንተናዊ ደኅንነት የማይተካ ሚና እንዳለው መረጋገጡ ነው፡፡ ብሔራዊ የመርከብ ድርጅት አስፈላጊነት በዚህ አጭር ጽሑፍ በዝርዝር ማቅረብ አዳጋች ቢሆንም አንኳር ነጥቦችን ብቻ እንጠቅሳለን፡፡

እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ የነበሩና ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች ዛሬም ቢሆን መልካቸውን ቀይረውና ይበልጥ አስፈሪ ሆነው የተከሰቱበት ሁኔታ አለ፡፡ በአሁኑ ወቅት 10 የሚሆኑ የላየነር የመርከብ ኩባንያዎች ከ50 በመቶ በላይ የዓለማችን ኮንቴይነሮች ያመላልሳሉ፡፡ ስለሆነም በዓለም አቀፍ ደረጃ የላይነር ሺፒንግ ሞኖፖሊ እየተፈጠረ ያለበት ሁኔታ ይገኛል፡፡ የበለፀጉ አገሮች የባህር ማጓጓዣ ዋጋን የመቆጣጠሪያ ሕጐችና አሠራሮች ቀይሰው ይቆጣጠራሉ፡፡ በአገራችን ደረጃ ግን ይህ የሚታሰብ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል በአካባቢያችን ለአሥርት ዓመታት የዘለቀው በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ የነበረው የባህር ላይ ውንብድና የአገራችን የመርከብ አገልግሎት በመኖሩ ያለአንዳች ችግርና ተጨማሪ ወጪ ማለፍ ተችሏል፡፡ በሌላ በኩል የአገራችን የገቢ ንግድ ሙሉ በሙሉ በCIF ይገዛ በነበረበት ወቅት ግልጽነት የጐደላቸው ፕሮፎርማዎችንና ኢንቮይሶችን በማዛባት ሕጋዊ በማስመሰል በባንኮቻችን ያለአግባብ ይወጣ የነበረው የውጭ ምንዛሪ በመንግሥት በግልጽ መረጃ በወቅቱ በመረጋገጡ የገቢ ዕቃዎች በFOB እንዲገዙና ለአገራችን መርከቦች ቅድሚያ በመስጠት እንዲጫኑ በ1992 ዓ.ም ፖሊሲ ተቀይሮ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

የመንግሥትን ፖሊሲ ተከትሎ ገቢ ዕቃዎች በFOB እየተገዙ ሲሆን፣ የወጪ ንግድ ዕቃዎች ግን የውጭ ገዢዎች በመረጡት መንገድ በFOB ወይም በCIF ሲሸጡ ይታያል፡፡ የብሔራዊ የመርከብ አገልግሎት ለአገራችን አስፈላጊነት ለመግቢያ ያህል ከላይ የተጠቀሰው ሲሆን ስለአገልግሎት አሰጣጡ መረጃ ለመስጠት እንወዳለን፡፡

በጽሑፉ እንደተገለጸው ገቢና ወጪ ዕቃዎች በሙሉ በኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የሚጓጓዙበት ሁኔታ የለም፡፡ ወደ አገራችን ከሚገባ አጠቃላይ ዕቃ የድርጅታችን በባህር የማጓጓዝ ድርሻ ከ41 በመቶ የዘለለ አይደለም፤ እንደዚሁ ከደረቅ ገቢ ዕቃዎች ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በድርጅቱ እየተጓጓዘ ያለው ከ65 በመቶ አይበልጥም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የወጪ ዕቃው በባህር የማጓጓዝ ድርሻው ከአንድ በመቶ የዘለለ አይደለም፡፡ ሐቁ ይህ ሆኖ ሳለ ጸሐፊው ገቢውና ወጪው ዕቃ በሙሉ በድርጅታችን በሞኖፖሊ ቁጥጥር እንደዋለ አድርገው የጻፉት ከእውነታው የራቀ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ጸሐፊው ከቻይና ወደቦች የባህር ማጓጓዣ በኮንቴይነር 3,800 ዶላር እንደምናስከፍል ተጠቅሰዋል፡፡ በቻይና ከ40 የሚበልጡ ወደቦች እንዳሉ ጸሐፊው ያውቁ ይሆን? በኮንቴይነር 3,800 ዶላር ይከፈላል የተባለውስ ምን ዓይነት ኮንቴይነር ይሆን? ለመሆኑ የኮንቴይነር ዓይነቶች ብዙና የሚጭኑት ዕቃ በርካታ መሆኑና እንደኮንቴይነሩና የዕቃው ዓይነት እንደሚለያይ ያውቁ ይሆን?

ኮንቴይነሮች መደበኛ ባለ 20 ጫማ፣ ባለ 40 ጫማ፣ ሃይ ኪዩብ ስፔሻልና ሌሎች ዓይነቶችን ያካትታሉ፡፡ የሚጭኑት ዕቃም መደበኛ፣ አደገኛና መርዛማ (IMCO Cargo) ወዘተ ዓይነቶችን ያካትታል፡፡

ከተለያዩ የቻይና ወደቦች የሚጫኑ ኮንቴይነሮች የማጓጓዣ ዋጋቸው ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ከ50 በመቶ በአማካይ ቅናሽ ተደርጐባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከሻንግሃይ እስከ ጂቡቲ ወደብ የባለ 20 ጫማ የመደበኛ ዕቃ ማጓጓዣ ዋጋ ከ1,700 ዶላር በላይ የነበረው በአሁኑ ወቅት ከ800 ዶላር በታች ነው፡፡ IMCO Cargo እና ስፔሻል ኮንቴይነሮች የሚጓጓዙት በወቅታዊ ዋጋ ስለሆነ ከ95 በመቶ በላይ በዚህ አማካይነት የምናጓጉዛቸው ኮንቴይነሮች ከገበያ ዋጋ ዝቅ ባለ ዋጋ ነው፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት ከ1.2 ሚሊዮን ቶን ወይም ከ60‚000 የባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮች የምግብ ዘይት ከኢንዶኔዥያና ከማሌዥያ የተጓጓዘ ሲሆን፣ በወቅቱ ለመንግሥት የቀረበለት የአንድ ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነር ማጓጓዣ ዋጋ ከ1,700 እስከ 2,200 ዶላር የነበረ ሲሆን፣ ከፍተኛ ሆኖ በመገኘቱ በድርጅታችን በኩል እንዲጓጓዝ ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት ላለፉት ዓመታት በአማካይ 1,200 ዶላር ለባለ 20 ጫማ በማስከፈል ስናጓጉዝ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ይኸው ዋጋ ወደ 1,000 ዶላር ዝቅ በማድረግ በማጓጓዝ ላይ እንገኛለን፡፡ ለሕዝባችን ፍጆታ የሚውል የምግብ ዘይት የማጓጓዣ ዋጋ በመቆጣጠር ያልተቋረጠ አቅርቦት እንዲኖር በማድረጋችን ድርጅታችን ኩራት ይሰማዋል፡፡

ከላይ ለአብነት የጠቀስናቸው ተወዳዳሪ የማጓጓዣ ዋጋዎች መቆጣጠር የተቻለውና ገበያን መሠረት በማድረግ ግልጽና ተዓማኒነት ያለው የገበያ ዋጋ እንዲኖር ካስቻሉን አሠራሮች አንዱ ግዙፍ ከሆኑ የዓለም አቀፍ ኔትወርክ ካላቸው የመርከብ ኩባንያዎች መርከቦቻቸውን በመጠቀም ኮንቴይነሮችንና ተሽከርካሪዎችን ለማጓጓዝ በፈጠርነው የትብብር ማዕቀፍ አማካይነት ነው፡፡ የሚሰጡትን የማጓጓዣ ዋጋ ገበያውን መሠረት በማድረግ በየስድስት ወራት በማጫረትና በማወዳደር ሲሆን፣ ይህ አሠራር የባህር ማጓጓዣ ዋጋ እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የኮንቴይነር ማጓጓዣ ዋጋ በአማካይ ከ50 በመቶ በላይ ዝቅ እንዲል ከማስቻሉም በላይ ፕሮፎርማችንና ኢንቮይሶችን በማዛባት ይወጣ የነበረው ሕጋዊ ያልሆነ ወጪ አድነዋል፣ የተጠቃሚ ኅብረተሰቡን የገበያ ዋጋን በማረጋጋት በከፍተኛ ደረጃ ረድቷል፡፡

ጸሐፊው ዕቃዎች በመጫኛ ወደቦች ሳይነሱ ለወራት ይቆያሉ በማለት ያሰፈሩት ሐሳብ ያለውን ነባራዊ ሁኔታን ያላገናዘበ ነው፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ድርጅታችን 130‚000 የሚሆን ባለ 20 ጫማ ኮንቴይነሮች ያጓጓዘ ሲሆን፣ ለመጫን ዝግጁ ሆነው በቀረቡ በአማካይ በ7.5 ቀናት ውስጥ ተነስቷል፡፡ የባህር ትራንዚት ጊዜያቸውም ከተያዘው ስታንዳርድ አኳያ አፈጻጸሙ ከ90 በመቶ በላይ ነበር፡፡ የተሽከርካሪ፣ የጥቅል ዕቃና ብረት ከኮንቴይነር አነሳስ ከተያዘው ዕቅድ አንፃር አፈጻጸሙ ዝቅ ያለ ቢሆንም፣ ከዕቃዎቹ ባህሪ አኳያ ብዙ ቆይቷል የሚያስብል አልነበረም፡፡ ከአንዳንድ ወደቦች ዕቃ በወቅቱ ማንሳት እንደማይቻል አስቀድሞ ሲታወቅ፣ የተለያዩ አማራጮች በመስጠት ሳይዘገይ እንዲነሳ የሚደረግበት አሠራር አለ፡፡

አገራችን ብሔራዊ የንግድ መርከብ አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ባለቤት በመሆኗ የባህር ማጓጓዣ ዋጋን የመቆጣጠር አቅም ፈጥሮላታል፣ ሸማቾች ለዋጋ ግሽበት እንዳይዳረጉ የራሱ አስተዋጽኦ ከማድረጉም በላይ ልዩ ልዩ ግብዓቶች በወቅቱ እንዲያገኙ አድርገዋል፡፡

ድርጅታችን በአሁኑ ወቅት 12 የሚሆኑ በዓለም አቀፍ በኮንቴይነርና ተሽከርካሪ ማጓጓዝ በቁንጮነት ከሚመደቡት የመርከብ ኩባንያዎች የፈጠረው የትብብር ማዕቀፍ አገልግሎት አሰጣጡ ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ የማጓጓዣ ዋጋውን በገበያው እንዲመራ አስችሎታል፣ ግልጽነት የጐደላቸው የፍሬት ዋጋ አጣጣል አስቀርተዋል፣ ለአገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት የማይተካ ሚና እንዲኖረው አስችሎታል፣ ለሸማቾችም አጋርነቱን አረጋግጦለታል፡፡

በቅርቡ ከተደረጉት የደንበኞች መድረክ አንድ ደንበኛ ያሉትን በመጥቀስ እናጠቃልል፣ “በፊት እናንተ እኛን ትፈልጉ ነበር፣ አሁን እኛ ነን እናንተን አጥብቀን የምንፈልገው፡፡”

በትክክለኛ ዕውAnchorቀትና መረጃ ያልተመሠረቱ ሐተታዎችና ጽሑፎች የሚፈጥሩት ውዥንብር ቀላል ስለማይሆን፣ ድርጅታችን ለማንኛውም ወገን ትክክለኛና ተጨባጭ ሁኔታዎችን መሠረት ያደረገ መረጃ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡

(የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት)

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት