የጃፓኑ ቶሚዛዋና ኩባንያው የተሰኘ ድርጅት ከ20 ዓመት በፊት የፈበረከው ቴክኖሎጂ፣ የመኪኖችን የሞተር ደኅንነት ከመጠበቅ፣ ብቃታቸው እንዲጨምርና የመኪኖችን ፍጥነት ለማሻሻል ከመርዳት ባሻገር፣ መኪኖች ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን በካይ ጭስ የሚቀንስ መሆኑ የተነገለት አድፓወር የተሰኘ ምርት ለአገር ውስጥ ገበያ መቅረብ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡
ኩባንያው በአገር ውስጥ ወኪል አስመጪው ከሆነው ኤልያስ ተስፋዬ አስመጪ ከተባለው ድርጅት ጋር በመሆን ሊያስገባው የተዘጋጀው ቴክኖሎጂ፣ የቁስል ፕላስተር የሚያክል፣ ስስ ፕላስቲክ መሳይ ነገር ሲሆን፣ የመኪኖች አየር ማጣሪያ ወይም ፊልትሮ የሚባለው የመኪና ክፍል ላይ የሚለጠፍ ነው፡፡ አንድ ጊዜ በሚለጠፈው አድፓወር ለሁለት ዓመታት ያህል መጠቀም እንደሚቻል ለሪፖርተር የገለጹት፣ የቶሚዛዋና ኩባንያው ፕሬዚዳንት ቶሩ ቶሚዛዋ ናቸው፡፡
ቶሚዛዋ እንዳብራሩት ከሆነ፣ በጃፓን ከመኪኖች የሚመነጨው በካይ ጋዝ እ.ኤ.አ. 1998 ኩባንያቸው ቴክኖሎጂውን እንዲፈለሰፍ መንገድ ከፍቶለታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 20 አገሮች በአድፓወር እየተጠቀሙ እንደሚገኙ፣ ከጃፓን ባሻገር በአሜሪካን በአውሮፓ ሰባት አገሮች የባለቤትነት መብት እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡
ምንም እንኳ በኢትዮጵያ የሚታየው የከባቢ አየር ብክለት እንዲሁም ከመኪኖች የሚመነጨው በካይ ጋዝም የሚያደርሰው ተፅዕኖ ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በየጎዳናው በብዛት የሚሽከረከሩ በመሆኑ በከነዳጅ ፍጆታ በተጨማሪ ለከባቢ አየር ጉዳት የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች አድፓወርን በመጠቀም የደከሙ ሞተሮቻቸውን ፍጥነት ማሻሻል እንደሚችሉ ቶሚዛዋ ያምናሉ፡፡
የኤልያስ ተስፋዬ አስመጪ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ መልዓከ ወልደ ሰንበት እንደገለጹት፣ ከጃፓኑ ኩባንያ ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት አንዷን አድፓወር በአንድ ሺሕ ብር ለገበያ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል፡፡ ይሁንና ቴክኖሎጂው በሚመለከተቻው አካላት ፈቃድ ማግኘት ስለሚኖርበት ይህ ሒደት በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡
ከልዩ ቀለማት ውህድ፣ ከልዩ መዳብ ወይም አሎይ እንዲሁም ከፋይበር ግላስ ተዳቅሎ የተሠራው አድፓወር፣ መኪኖች በሞተሮቻቸው በኩል የሚለቁትን በካይ ጋዝ በማጽዳትና በማመቅ በአንፃሩ ወደ ሞተሮቹ የተጣራ አየር ወይም ኦክሲጂን እንዲያስገቡ ኤልክተሮኖችን በጨረራ በመልቀቅ የሚሠራ ቴክኖሎጂ መሆኑ ተብራርቷል፡፡ በአውሮፓ በተደረገለት ፍተሻም ቴክኖሎጂው ከ40 ከመቶ በላይ በካይ ጋዞችን የማጣራት አቅም አለው ተብሏል፡፡
ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት ዓለም እጅግ የተራቀቁና ከከባቢ አየር ጋር ተስማሚ የሆኑ የመኪና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ ላይ ትገኛለች፡፡ የአሜሪካው ቴስላ ኩባንያ፣ በኤሌክትሪክ የሚሠሩ አስገራሚ መኪኖችን በብዛት ለማምረት ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡ የጃፓኑ ቶዮታ ኩባንያም ኃይድሮጂን ሃይብሪድ የተሰኙ የተለዩ መኪኖችን በማምረት ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ሁሉ እየመጣ ባለበት ወቅት አድፓወር የመሳሰሉትን ቴክኖሎጂዎች ማምጣቱ ዘላቂነቱ ምን ያህል ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ቶሚዛዋ፣ በነዳጅ የሚሠሩ መኪኖች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከገበያ ውጭ ይሆናሉ ስለማይታሰብ ቴክኖሎጂው ለበርካታ ዓመታት ገበያ ላይ የመቆየት ዕድል ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ኩባንያው በቬትናም በቅርቡ ከበቁጥር ከ40 ሺሕ አድፓወር ለመሸጥ እንደቻለ አስታውቆ፣ በኢትዮጵያ ግን ለመሻው ከሁለት ሺሕ ያላነሰ ለማቅረብ ማሰቡን አቶ መልዓከ ገልጸዋል፡፡