Thursday, February 29, 2024

ከፖለቲካ ሚናው ይልቅ ትኩረት የሚስበው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽነር ምርጫ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአኅጉሪቱ የጋራ ክንድና ድምፅ፣ የነፃነት ምልክትና የጥቁር ሕዝቦች መስዋዕትነት ሐውልት በመሆን 63ኛ ዓመቱን ሊደፍን በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡

ለዚህ ፓን አፍሪካዊ ተቋም የአኅጉሪቱ መሪዎች ቀላል የማይባል መስዋዕትነት በመክፈል የመሠረቱት የጋራ ድል ነፀብራቅ መሆኑ ታሪክ ሁሌም የሚዘክረው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ድርሻም ትልቅ ሚና እንደነበረው አይዘነጋም፡፡ ለዚህም ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴና አገዛዛቸው ለድርጅቱ ዕውን መሆን ያበረከቱት አስተዋጽኦ፣ በአገዛዝ ዘመናቸው በበጎ ከሚነሱላቸው ሥራዎች ውስጥ በቀዳሚነት ጎልተው ከሚጠቀሱት አንዱ ነው፡፡

ምንም እንኳ በአንዲት አገር የከተናወነ ተግባር በአመዛኙ በመሪው የሚገለጽ ቢሆንም፣ ከመሪዎች ታሪክ ጀርባ የስኬትም ሆነ የበጎና የመጥፎ ተግባራት ዋነኛ የጉልበት ምንጭ የሚሆኑ ግለሰቦች አሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ታሪክ የሚሰጣቸው ቦታ ያነሰ ቢሆንም፣ ለሁሉም ክስተቶች ቁልፍ ቦታ ይይዛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታና ከኢትዮጵያ ሚና ጋር የሚያያዘው የታሪክ ትስስር ውስጥ ይታያል፡፡ በድርጅቱ ምሥረታ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ስም በታሪክ መያያዙ የማያከራክር ቢሆንም፣ ሊዘነጉ ከማይገባቸው ውስጥ በወቅቱ ለንጉሡ ታሪካዊ ማማነት ከጀርባቸው ዋነኛውን ተግባር ያከናወኑት የወቅቱ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ያገለገሉት አቶ ከተማ ይፍሩ በግንባር ቀደምትነት ሲወሱ፣ ሌሎቹ ሚኒስትሮችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡

እንደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነታቸው በአፄ ኃይል ሥላሴ የሚመራውን መንግሥት በመወከልም ሆነ በግል የማሳመን ክህሎታቸውና ታታሪነታቸው አቶ ከተማ በተግባር የፈጸሙት ኃላፊነትና ቆራጥነት፣ ለፓን አፍሪካኒዝም መመሥረትና ለእዚህ መድረክ ቁልፉ የስኬት መሠረት ነው፡፡ ለዚህም መቼም የማይዘነጋ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ሆኖ ይቆጠራል፡፡ በነ አቶ ከተማ ይፍሩ አሻራ የተመሠረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2002 ስያሜውን ወደ አፍሪካ ኅብረት ከቀየረም 14 ዓመታት ሊያስቆጥር ተቃርቧል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት ታዲያ ከመነሻው ለተቀደሰ ዓላማ እንደ መመሥረቱ ከዚህ ያፈነገጠ ትችትና ወቀሳ እየቀረበበት ቀላል የማይባሉ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ለጥቁር ሕዝቦች ነፃነታቸውን የሚያጣጥሙበትና የጋራ ድምፅ በማስተጋባት ከድህነት የመውጫ የጋራ መድረክ ተደርጎ የሚቆጠር ተቋም ከመሆን ይልቅ፣ በአባል አገሮች መሪዎች ፍላጎት ብቻ የሚንቀሳቀስ ኃይል አልባ ተቋም እንደሆነ ትችት ሲሰነዘርበት መስማት አዲስ አይደለም፡፡ በተለይ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን በሚሹ የአባል አገሮች ጉዳይ፣ ምንም ሊፈይድ የማይችል ጥርስ የሌለው የፖለቲካ ተቋም እንደሆነም መስማት እየተለመደ መጥቷል፡፡

በተለይ በቀጣናዎችም ሆነ በአኅጉራዊ ጉዳዮች ላይ ክትትል የሚያደርጉ ተንታኞች፣ ኅብረቱ በፖለቲካዊ ተቋምነቱ ከሚንቀሳቀስባቸው ጉዳዮች ይልቅ፣ ተቋሙን ለመምራት በሚደረጉ የአባል አገሮች ፉክክር በተሻለ ቀልብ እየሳበ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ለዚህም የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንን በዋና ኮሚሽነርነት ለመምራት የሚደረገው የሊቀመንበርነት ምርጫ፣ የብዙዎችን ቀልብ በአንፃራዊነት መሳብ እየቻለ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል በመጪው ሐምሌ ወር በሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የአኅጉሪቱ መሪዎች 28ኛ ጉባዔ ላይ፣ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በሊቀመንበርነት የሚመሩት የኮሚሽነሩ ምርጫ ከወዲሁ መነጋገሪያ መሆን የቻለው፡፡

በእርግጥ ቀደም ባሉ ዓመታት የኮሚሽኑን የሊቀመንበርነት ሥልጣን ለመያዝ የሚደረገው የመምረጡ ሒደት፣ በአብዛኛው ውስጥ ለውስጥ አገሮች ባላቸው የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረት ነው፡፡ በዚህ መሠረት በሚስጥር ስምምነት ላይ ተደርሶበት ነበር በዋናው ጉባዔ ላይ ይፋ ሲደረግ የነበረው፡፡

የምርጫ ሒደቱን ውስጥ ለውስጥ በሚስጥራዊነት ከማካሄድ ልማዱ ወጥቶ ከመሪዎቹ ጉባዔ ቀደም ብሎ፣ የዕጩነት ፉክክሩ ለመጀመርያ ጊዜ በአደባባይ የሚሰማ አጀንዳ መሆን የጀመረው ከአራት ዓመት በፊት ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ የተስተናገደው ፉክክር የወቅቱ የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ደቡብ አፍሪካዊቷ ዶ/ር ድላሚኒ ንኮሳዛና ዙማና በኋላ ያሸነፏቸው የቀድሞው ኮሚሽነር ጋቦናዊው ዦን ፒንግ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ የኋላ ኋላ ዶ/ር ዙማ የሊቀመንበሩን ቦታ ማሸነፍ ቢችሉም፣ ፉክክሩ እንደ ቀደምት ዓመታት ቀላል አልነበረም፡፡ ይልቁንም ሁለቱ ተፎካካሪዎች እስከ መጨረሻ ድረስ አንገት ለአንገት ተናንቀው በመቀጠላቸው፣ አንዳቸውን ተመራጭ ሊያደርጋቸው የሚችለውን የመሪዎች (የአባል አገሮች) አብላጫ ድምፅ ማግኘት ባመቻላቸው ሦስት ዙሮች መጠበቅ ግድ ብሏቸው ነበር፡፡

በአፍሪካ ኅብረት የውስጥ አሠራር ሥርዓት ለኮሚሽኑ ሊቀመንበርነት የሚቀርብ ማንኛውም ዕጩ፣ የአባል አገሮችን 3/4ኛ አብላጫ ድምፅ ማግኘት ሲችል ብቻ መሆኑ ተቀምጧል፡፡

ይህንን አብላጫ ድምፅ ማግኘት ያለመቻል ነበር ሁለቱን ተፎካካሪዎች ለመምረጥ በአንድ ዙር መጠናቀቅ ያልቻለው፡፡ እንዲሁም ክስተቱ በኅብረቱ ታሪክ የሊቀመንበርነት ምርጫ ትኩረት ሳቢ መሆን የቻለው፡፡ ይህንን የምርጫ ሒደት የመነጋገሪያ አጀንዳ መሆን ያስቻለው ምክንያት፣ ዕጩዎቹ ከእንግሊዝኛ ተናጋሪ (Anglophone) እና ከፈረንሣይ ተናጋሪ (Francophone) ከሚናገሩ አገሮች ጎራዎች መወከላቸው ነበር፡፡

በተለይም አኅጉራዊው ተቋም እ.ኤ.አ. በ2002 ስያሜው ወደ አፍሪካ ኅብረት ሲቀየር፣ ጊዜያዊ የሽግግር ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠው ከነበሩት ኮትዲቯራዊው አማራ ኢሴይ ጀምሮ ከፈረንሣይኛ ተናጋሪ ጎራ የተወከሉ ዕጩዎች በአሸናፊነት ለአሥር ዓመታት ተቆናጠውት ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን የዚህ የአንድ ጎራ የበላይነት ለመጀመሪያ ጊዜ ያበቃው፣ የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ድላሚኒ ዙማ በእልህ አስጨራሹ ፉክክር እ.ኤ.አ. በ2012 ባሸነፉበት ወቅት ነበር፡፡

የኮሚሽኑ የሊቀመንበርነት ዘመን በአራት ዓመት የተገደበ ቢሆንም፣ ለአንድ ዕጩ ሁለት ጊዜ የመወዳደር መብት ይሰጣል፡፡ ይህ የምርጫ ሥርዓት ደግሞ ለሊቀመንበርነት የሚደረገውን የምርጫ አካሄድ ተጠባቂ ያደርገዋል፡፡ ነገር ግን ደቡብ አፍሪካዊቷ ዙማ ዘንድሮ ለሚካሄደው ምርጫ በተመሳሳይ ሁኔታ ቢጠበቁም፣ ራሳቸውን ቀድመው ከዕጩነት ዝርዝር ውስጥ አውጥተዋል፡፡

አባል አገሮች ዕጩዎቻቸውን ማቅረብ እንዲችሉ በኮሚሽኑ የተሰጠው ጊዜም ባለፈው መጋቢት ወር የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ዙማ ስማቸው አልተካተተም፡፡ ምንም እንኳ ሊቀመንበሯ ምክንያታቸውን በይፋ ባይገልጹም፣ ለሌላ ኃላፊነት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት ጠርቷቸዋል የሚሉ የቅርብ ምንጮች አሉ፡፡

ዙማ ወደ ትውልድ አገራቸው ለሌላ ኃላፊነት ለመጠራታቸው ማረጋገጫ ባይገኝም፣ የሊቀመንበሯ ቃል አቀባይ የሆኑ ጃኮብ ኢኖህ ኤበን አዛውንቷ ለሁለተኛ ጊዜ እንደማይወዳደሩ በቅርቡ አረጋግጠዋል፡፡

በአኅጉሪቱ እጅግ ከፍተኛ የተባለውን ይህንኑ የሥራ ኃላፊነት ለማግኘት በርከት ያሉ ዕጩዎች ከአባል አገሮች ፍላጎት እንደሚያሳዩም ቀደም ብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ ነገር ግን እስካሁን በይፋ በዕጩነት ስማቸው ተያይዞ የወጣው ከሦስት አገሮች ብቻ መሆኑን መረጃዎች እያሳዩ ነው፡፡ እነዚህ ስማቸው ይፋ የሆኑትም የ65 ዓመቷ የቦትስዋና የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ሚኒስትር ዶ/ር ፔሎኖሚ ቬንሰን ማይቶይ አንደኛዋ ሲሆኑ፣ ሁለተኛዋ ተፎካካሪያቸው እንደሆኑ እየተነገረ ያለው ኡጋንዳዊቷ የ60 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋዋ ዶ/ር ስፔሲዮዛ ናይጋጋ ካዚብዌ ናቸው፡፡ ሦስተኛው ዕጩ ሆነው የቀረቡት ደግሞ የ51 ዓመቷ አጋፒቶ ምባ ሞኩይ ሲሆኑ፣ የኢኳቶርያል ጊኒ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡

የኡጋንዳዋ ዕጩ ዶ/ር ካዚብዌ እንደ ዙማ በተመሳሳይ የሕክምና ዶክተር ሆነው በሙያቸው ሲታወቁ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤችአይቪ/ኤድስ ልዩ ተወካይ በመሆን እያገለገሉ ናቸው፡፡ ከሁለቱ ዕጩዎች የተሻለ ዝናና የላቀ ዓለም አቀፍ ልምድ እንዳላቸው ይነገርላቸዋል፡፡

በሐምሌ ወር በሚካሄደው ምርጫ ካለፈው ምርጫ የበለጠ ቀልብ ሳቢና የከረረ ፉክክር ሊደረግበት ከሚችልባቸው ምክንያቶች አንዱ፣ የዕጩዎች ቁጥር ከሁለት ወደ ሦስት ከፍ ማለቱ ብቻ አይደለም፡፡ ዕጩዎች በአኅጉሪቱ የተለያዩ ሦስት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀጣናዎች የተወከሉ መሆናቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአንግሎፎንና በፍራንኮፎን በማለት አኅጉሪቷን ቋንቋን መሠረት ያደረጉ በሁለት ጎራዎች ከከፈሉት ያለፉት ውድድሮች መሠረታዊ የአቅጣጫ ለውጥ በማምጣት፣ ወደ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀጣና ጎራዎች የሚያሳዩ ዕጩዎች መቅረባቸው ፉክክሩ የተለየ ቦታ ያሰጠዋል የሚሉ የፖለቲካና የደኅንነት ጉዳዮችን የሚከታተሉ ተንታኞች እየገለጹ ነው፡፡ ነገር ግን ምርጫው ገና ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ የቀሩት ከመሆኑ አንፃር፣ ከሦስቱ ዕጩዎች ምናልባት አንዳቸው ራሳቸውን ከውድድሩ ሊያገሉ እንደሚችሉ የሚገልጹ አሉ፡፡

በአኅጉሪቱ የፖለቲካና የፀጥታ ጉዳዮች፣ እንዲሁም በቀጣናዊ የኢኮኖሚ ትስስሮች ላይ ምርምር ከሚያደርጉ ተቋማት አንዱ የሆነው ኢንስቲትዩት ኦፍ ሴኪዩሪቲ ስተዲስ (ISS) በተባለው ተቋም ውስጥ ተንታኞች የሆኑትና በማማከር ሥራ ላይ የሚገኙት ሊዬሰል ቪው ቫውድራም እና ተመራማሪው ያን ቤድዚጉይ በቅርቡ በጋራ ባሳተሙት ጽሑፍ፣ ከሦስቱ ዕጩዎች በስተመጨረሻ አንደኛው ራሳቸውን ሊያገሉ ይችላሉ ብለው ከሚጠብቁት ውስጥ ናቸው፡፡

‹‹በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ሁሌም እንደሚታወቀው ቦታውን (ሊቀመንበርነቱን) ለማሸነፍ የዕጩዎች የመምራት ብቃት፣ ዝና ወይም በግል ካስመዘገቡት ስኬትና ገጸ ታሪካቸው ይልቅ ወሳኙ ጉዳይ ዕጩዎች ወክለውት የመጡት አገር፣ ከሌላ መንግሥት ያላቸው ድጋፍ፣ እንዲሁም የሚወክሉት አካባቢያዊ ቀጣና፣ ለቦታው የሚሰጠው ትኩረትና ቆራጥነት ነው፤›› ሲሉ ሁለቱ ተንታኞች ‹ዙማን የመተካት ሒደት በድሮ በሬ› በሚል ርዕስ ባሳተሙት ጽሑፍ ይገልጻሉ፡፡

‹‹ከሦስቱ አንዳቸው ወይም ሁለቱ በመጨረሻዋ ደቂቃም ቢሆን ከዕጩነት ራሳቸውን ሊያገሉ ይችላሉ፡፡ በዚሁ የሚገፉበት ከሆነና አሸናፊው የሚፈለገውን ድምፅ ማሟላት ካልቻለ፣ ዙማ ለተጨማሪ ጊዜያት ቢያንስ ከጥቅምት በኋላ እስከ ጥር 2009 ዓ.ም. ድረስ በቢሯቸው እንዲቆዩ ያስገድዷቸዋል፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

የቦትስዋናውን ቬንሰን ሞይቶይ በዕጩነት ያቀረበው የደቡባዊ አፍሪካ የልማት ማኅበረሰብ (ሳድክ) ሲሆን፣ ቀድሞ ወክሏቸው የነበሩት ድላሚኒ ዙማ ለሁለተኛ ጊዜ ቀጣናውን መወከል ባለመቻላቸው፣ አዲሱን ዕጩ በማቅረብ የሊቀመንበርነቱን ቦታ ማጣት እንደማይፈልግ እየተነገረ ነው፡፡

ምንም እንኳ ቦትስዋና በአፍሪካ ኅብረት ከአባልነቷ ባሻገር ራሷን ብዙም ለማስተሳሰር ያላት ፍላጎት እምብዛም ቢሆንም፣ የወቅቱ የቀጣናው ማኅበረሰባዊ ተቋም ሊቀመንበር በመሆኗ ብቻ ቬንሰን ሞይቶይን ዕጩ አድርጎ ቀጣናው የሰየማቸው፡፡ በሌላ በኩልም አብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ዓለም አቀፉን የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ለማውገዝ በጋራ በተሠለፉበት ወቅትም ቢሆን፣ ቦትስዋና ከትብብሩ ውጪ በመሆን ከኅብረቱ ፍላጎት ማፈንገጧን ያሳየች አገር ናት፡፡ ለዚህም ነው ቀድሞ ጋዜጠኛ የነበሩትንና በተለያዩ የመንግሥት ሥራዎች በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ያገለገሉትን ዶ/ር ቬንሰን ሞይቶይን ዕጩዋ አድርጋ የምትቀርበው፡፡ የደቡባዊ አፍሪካ ማኅበረሰቡ በቀጥታ የሊቀመንበርነቱን ቦታ ያገኛል የሚል የጋራ ስምምነት እዚህ አዲስ አበባ እንደሌለ እየተነገረም ይገኛል፡፡ በእርግጥ ለዚህ ደግሞ ማሳያ የሚሆነው ከአራት ዓመት በፊት የዙማን አሸናፊነት ያረጋገጠው ምርጫ እስካሁን ድረስ በአባል አገሮች መካከል ቅሬታን በመፍጠሩ፣ እንዲሁም ደቡባዊ ማኅበረሰቡና ደቡብ አፍሪካ አሸናፊ ስለሆኑበት መንገድ የተነሳው ጥያቄ በመቀጠሉ ነው፡፡

ሌላዋ ዕጩ የሆኑት ኡጋንዳዊቷ ዶ/ር ካዝዌ በሕክምና የካበተ ዓለም አቀፍ ልምድ ይዘው ብቅ ቢሉም፣ ለሊቀመንበርነቱ ምርጫ ማሸነፍ ግን የግል ማንነታቸውም ሆነ ልምድና የትምህርት ደረጃቸው እዚህ ግባ የሚባል ፋይዳ አይኖረውም ሲሉ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ ይልቁንም የአፍሪካ ኅብረት ለሴቶች እሰጠዋለሁ ከሚለው የፆታ ስብጥር አንፃር ኡጋንዳዊቷ ሴት መሆናቸው ምናልባት የተሻለ ትኩረት ሊያሰጣቸው ይችላል፡፡ እኚሁ ዕጩ በምሥራቁ የአፍሪካ ክፍል የሚገኘውን የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ማኅበረሰብ (ኮሜሳ) እንደመወከላቸው የመንግሥታት ድጋፎች፣ የኡጋንዳ መንግሥትና ዲፕሎማቶቻቸው የሚኖራቸው ሚና ወሳኝነት እንደሚኖረው ታምኖበታል፡፡

በሌላኛው ተቃራኒ የአኅጉሪቱ ፅንፍ ፉክክሩን የተቀላቀሉት ምባ ሞኩይ፣ አገራቸው ኢኳቶሪያል ጊኒ በአባልነት የተጠለለችበትን የምዕራባዊ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኤኮዋስን) ወክለው ነው ለሊቀመንበርነቱ በዕጩነት የቀረቡት፡፡ አገራቸው ከቦትስዋና በተሻለ ለአፍሪካ ኅብረት ካላት ቀረቤታ በተጨማሪ፣ በኅብረቱ ውስጥ ዋና ተዋናይ ተደርገው ከሚጠሩት አባል አገሮች ውስጥ ትመደባለች፡፡ ነገር ግን የኢኳቶሪያል ጊኒ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰት ከፍተኛ ትችት ከሚሰነዘርባቸው መካከል አንዱ በመሆኑ፣ አገሪቱን በመጥፎ ጎንዋ የሚያስነሳት ሌላኛው ገጽታ ሆኖ እየታየም ይገኛል፡፡ ይህ ደግሞ አገሪቱን ለ37 ዓመታት ሲገዟት የኖሩት ፕሬዚዳንት ቴዎዶሮ ኦቢያንግ ንጉኤማ ምባሶጎ በቅርቡ ለተጨማሪ ዓመታት በምርጫ አሸናፊ በተባሉበት ወቅት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የሚለው ትችት አስነስቶባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ መሪ ሆነው የዘለቁት ፕሬዚዳንት ኦቢያንግ የቅርብ አማካሪያቸው ሆነው ያገለገሏቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን፣ ለኅብረቱ ሊቀመንበርነት ዕጩ አድርገው የሰየሟቸው፡፡

ፕሬዚዳንቱም ሆኑ አገራቸው ኢኳቶሪያል ጊኒ ለኅብረቱ ያላቸውን ቀረቤታም ሆነ አስተዋጽኦዋቸውን በማየት፣ ዕጩው ሞኮይ ቀላል ተፎካካሪ እንደማይሆኑም ነው የሚገመተው፡፡ ለዚህ ደግሞ ፕሬዚዳንት ኦቢያንግ በቅርብ ጊዜያት እንኳ በርካታ የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባዎችን ለማስተናገድ ላይ ታች ሲሉ ቆይተዋል፡፡ የተለያዩ አኅጉራዊ ጉባዔዎችንና ኮንፈረንሶችን በዋና ከተማዋ ማላቦ በሚገኝ ቅንጡና ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ለዚሁ ሲባል በመገንባት፣ ለአኅጉራዊ ኅብረቱም ሆነ መሰል ጉዳዮች ያላቸውን ድጋፍና ባለድርሻነት ያደረጉዋቸው ጥረቶች ተሳክተውላቸዋል ተብሎም ይነገራል፡፡ ይህ ጥረታቸው ደግሞ የአባል አገሮችን መንግሥታት ድጋፍ ሊያስገኝላቸው እንደሚችል ግምቶች ይሰማሉ፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች ነው መጪው የኪጋሊ ጉባዔ ማንን ለአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ለሊቀመንበርነት መርጦ ሊጠናቀቅ ይችላል ለሚባለው፡፡ ለዚህም ነው ከአሁኑ አጓጊ ያደረገው፡፡ በጉባዔው ዕጩዎቹ ምንም ሆኑ ምን ወይም በግል ካሉዋቸው ልምዶችም ሆነ ካካበቱት ዕውቀትና የመሪነት ክህሎት በላይ የመሪዎቹ ፖለቲካዊ ድርድር፣ ቀጣናዊ ትብብርና የየግል ፍላጎቶቻቸው ወሳኝ ናቸው፡፡ ውሳኔዎቹም ኅብረቱን ወደ ተሻለ ሽግግር ሊመራው የሚችልና ወደ ስኬት ጉዞ የሚመራው ኮሚሽነር ያስገኙ ይሆን የሚለውን ተጠባቂ አድርጎአቸዋል፡፡ የኢንተርናሽናል ሴኩዩሪቲ ስተዲስ ባለሙያዎችም ይህንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡

ድምፅ ለመስጠት ድምጿን ያጠፋችው ኢትዮጵያ

ለዕጩዎች የየአገሮቻቸው መንግሥታት የሚያደርጉት ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ ለአሸናፊዎቹ ከሚኖረው ሚና በተጨማሪ፣ የሌሎች አገሮች ድምፆች ወሳኝነትም ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ከዚህ ጉዳይም ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት ካሁኑ ለማን ድምፅ ሊሰጥ እንደሚችል ለማወቅ ሪፖርተር ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ ኢትዮጵያ ‹‹ጊዜው ሲደርስ›› ድምጿን እንደምትሰጥ ተናግረዋል፡፡

‹‹የምንመርጠው አፍሪካዊ ስለሆነ የግዴታ ከወዲሁ ብዙ ጥናትና ምርምር ወይም መጠበብ የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ይህ ቦታ የብቃት ቦታ ነው፡፡ በብቃት አስተባብሮ የመምራት ጉዳይ ስለሆነ የተሻለ ችሎታ ያለውን፣ ብቁ ነው ብለን የምናምንበትን ጊዜው ሲደርስ እናሳውቃለን፤›› በማለት አምባሳደር ታዬ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

እስከዚያው ድረስ ግን የዕጩ ተወዳዳሪዎቹ አገሮች በግላቸውም ሆነ በየተወከሉበት ቀጣናዊ ማኅበረሰብ አማካይነት የኅብረቱ አባል አገሮችን ድጋፍ እያሰባሰቡ ይቀጥላሉ፡፡ ለአብነትም ለኡጋንዳዊቷ ዕጩ ዘጠኝ ያህል አገሮች እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ድረስ ድጋፋቸውን ከወዲሁ ሰጥተዋቸዋል፡፡

እንዲሁም የቦስትዋናን ዕጩ የደቡብ አፍሪካ መንግሥትን ጨምሮ የተወሰኑ የቀጣናው ማኅበረሰብ አባል አገሮች አለሁልሽ እያሏቸው ነው፡፡ ለጊዜው የኢኳቶሪያል ጊኒው ዕጩ በይፋ እስካሁን ከአገራቸው መንግሥት ውጪ ድጋፋቸውን የገለጹላቸው ባይኖሩም፣ ቀጣናውን እስከወከሉ ድረስ ከኤኮዋስ አገሮችና ከሌሎች ማግኘታቸው እንደማይቀር እየተገለጸ ነው፡፡

የኪጋሊው የመሪዎች ጉባዔ የሚያስተዋውቀው አዲሱ ወይም አዲሲቷ ሊቀመንበር በእርግጠኝነት ማን ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት ቢያስቸግርም፣ መነጋገሪያነቱ ግን ይቀጥላል፡፡ ኅብረቱ በአዲስ ስያሜ መጠራት ከጀመረበት ባለፉት 14 ዓመታት በአራት ሊቃነመናብርት ሲመራ ቆይቷል፡፡ አሁን አምስተኛው/ዋ ሊቀመንበር ማን መሆን እንደሚችል 66 ቀናት መጠበቅ የግድ ነው፡፡ ምናልባትም ዕጩ ሆነው ከቀረቡት አንዱ/ዷ የሚፈለገውን አብላጫ ድምፅ ማግኘት ከተሳናቸው፣ ለተጨማሪ ሰባት ወራት እስከ ጥር 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሚካሄደውን የመሪዎች ጉባዔ ለመጠበቅ ያስገድዳል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -